ዋናውን ሀብት አትጣሉ፡፡
እግዚአብሔር ለሰዎች ልጆች የሰጠው ስጦታ እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡ ስጦታዎችን ዋናዎች(majors) እና አስፈላጊዎች (Importants) ብለን ልንመድባቸው እንችላለን፡፡ አስፈላጊዎች የምንላቸው እንደምግብ ፣ መጠለያ፣ ልብስና ገንዘብ ያሉ መገልገያዎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ቢጎድሉብ የምድር ኑሮአችን ምንቅርቅሩ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ እንደ አማኞች መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው ብለን እናምናለን፣ይህንንም የሚያረጋግጥልን ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ (መክብ 2፡14፣2 ቆሮ 9፡10፣ማቴ 6፡11) እነዚህ ሁሉ ታዲያ አስፈላጊዎች እንጂ ዋናዎች አይደሉም፡፡ ዋናዎች የምንላቸው ደግሞ በሕይወታችን ከምንም ጋር የማናወዳድራቸው እጅግም የላቁ መንፈሳዊ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸር ለጋስነቱ አስፈላጊውንም ሆነ ዋናውንም ይሰጠናል፡፡ ሆኖም በአስፈላጊዎችና በዋናዎች መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ አለ ፣ ስለዚህ ለነፍሳችሁ በምትበሉትና ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን አለ ( ማቴ 6፡25)፡፡ እንግዲህ እዚህ ጋ ሁለት ነገሮች ለንጽጽር ቀርበዋል፡፡ እነርሱም ነፍስና መብል፣ ልብስና ሰውነት ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ነፍስንም መብልንም ሰጠ፡፡ ሆኖም አንዱ ስጦታ ከሌላው የሚበልጥ ሆኖ ተገኘ፡፡ የሚበልጠው ዋና ሲሆን የተቀረው ደግሞ አስፈላጊ ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም በአስፈላጊው ምክንያት ዋና የሆነውን ሀብታችንን መጣል አይገባም፡፡
መጣል ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ጥቂት ማብራራት ተገቢ ነው፡፡ መጣል ስንል አንድን ነገር ማቃለል፣ አሳንሶ ማየት፣መናቅ ወይም ቸል ማለት እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ሀብትን ቸል ካልነው ወይም ከናቅነው የቱንም ያህል የከበረ ቢሆን እኛ በእግራችን ብንረግጠውና ከጭቃ ብናላውሰው ቅር ሊለን አይችልም፡፡ የናቅነውን ወርቅ ከቆሻሻ ጋር አብሮ ልንጠርገው ሁላ እንችላለን፡፡ የከበረውን ሀብት መጣል የሚለውን አሳብ በዚህ መልኩ ከተረዳን ቀጣዩ ንባባችን ግልጽ ይሆንልናል፡፡
ነፍስና መብል ሲነጻጸሩ በምንም መለኪያ መብል ከነፍስ ጋር እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ ነፍስ ከመብል ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ነፍስ ዋና ሲሆን መብል አስፈላጊያችን መሆኑ ነው፡፡ ሰውነትንና ልብስንም እናወዳድር ብንል ሁሉቱም ከእግዚአብሔር የተሰጡን ቢሆኑም በእኩል ዓይን እንድናያቸው አያስፈልግም፡፡ በስጦታነታቸው እግዚአብሔርን እያመሰገንን ለምንለብሰው ልብስ ከምንሰጠው ቦታ ይልቅ ለሰውነታችን የላቀውን አክብሮትና ጥንቃቄ ልናድርግ እንደሚገባን ኢየሱስ ያስተምረናል፡፡ ልብስ አስፈላጊ ሲሆን ነፍስ ግን ዋና ሀብታችን ነው፡፡ ስለዚህ ዋናና ወሳኝ የሆነው ሀብታችንን በአስፈላጊው ምክንያት እንዳንጥል መጠንቀቅ ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ዋናን ማጣት የኪሣራዎች ሁሉ ኪሣራ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበለናቸው በርካታ ስጦታዎች ያሉን ሲሆን ልንጠነቀቅላቸው የሚገባ የከበሩ መንፈሳዊ ሀብቶቻችን የትኞቹ እንደሆኑ በጥቂቱ እንመልከት፡፡
1. ብኩርናችሁን አትጣሉ፡፡
እኛ አማኞች ከልባችን አጥብቀን መያዝ ከሚገባን መንፈሳዊ በረከቶቻችን አንዱና ወሳኙ መንፈሳዊ ብኩርናችን ነው፡፡ ይህንን መንፈሳዊ ብኩርናችንን እንዳንጥል መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ብኩርና ቀድሞ መወለድን የሚመለክት ቢሆንም የአማኞች ብኩርና ቀድመን በመወለድ የምናገኘው ሳይሆን ከመንፈስ ከእግዚአብሔር በመወለድ የሚገኝ መብት(Birthright) ነው፡፡ብኩርና በአይሁድ ሕዝቦች ዘንድ የተለየ ብልጫ ጥቅም ወይም መብት ወይም መታደልን የሚያመለክት ነው፡፡ በእነርሱ ዘመን አካላዊ ብኩርና ጋር የተያያዙ መብቶችን የሚያገኘው በቤት ውስጥ ታላቅ ሆኖ የተወለደ ወንድ ነው፡፡ ብኩርና በእነርሱ አባባል ፕሮቶቶኪያ(prototokia) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በቤት ውስጥ ታላቅ ሆኖ ለተወለደ ወንድ የሚኖረውን ሥልጣንና መብት የሚመለክት ነው፡፡ ይህ መብት ደግሞ ከእርስት ሁለት እጥፍ የመውረስ ብልጫን የሚያስገኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር በራሱ ሥልጣን ካልለወጠውና ካልሻረው በቀር ይህ ብልጫና መብት በምንም ዓይነት መጣል የለበትም፡፡
ብኩርና ርስትን እጥፍ አድርጎ መውረስ መብት ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር አገልግሎት መለየትንም ይጨምራል፡፡ ይህም የሚሆነው እግዚአብሔር የእርሱን አገልግሎት የሚሸከሙትን ሰዎች ስለሚፈልግ ነው፡፡ ሮቤል በእሥራኤል ቤት ታላቅ ቢሆንም በእግዚአብሔር ምርጫ የክህነት አገልግሎት ለሌዊ ተሰጠ(ዘኁልቁ 8፡16 -18)፡፡ እንዲሁም ደግሞ ያዕቆብ ኤፍሬምን ከምናሴ ሲያስቀድመው ለየሴፍ ደግሞ ለበኩር የሚሰጠውን እጥፍ ድርሻ ሲሰጠው እንመለከታለን(ዘፍ 48፡22)፡፡ ሌዊ፣ ኤፍሬምና ዮሴፍ በውልደት ታላላቆች ሆነው ሳይሆን በእግዚአብሔር ልዩ ምርጫ ለዚህ ትልቅ ሥፍራ ስለታደሉ ነው፡፡
ይህ እንዲህ ሆኖ የተሰጣቸውን የብኩርና መብት የጣሉ ሰዎች ደግሞ አሉ፡፡ ከእነርሱ ኤሳውና ሮቤል በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ኤሳው የራሱን የብኩርና መብት ራሱ ሌላ አስፈላጊ(important ) የሚለውን በመምረጡ ምክንያት የጣለ ሲሆን የሮቤልን ብኩርና መብት የሻረው ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡ እስቲ የሁለቱንም በአጭሩ እንመልከት፡፡
ኤሳው በአባቱ ቤት የብኩርና መብት የተገባው ሆኖ የሚኖር ሰው ስለነበረ አባቱ ይህንን የብኩርና መብቱን ጥብቆለት ነበር፡፡ ነገር ግን የተሰጠውን ክብርና የብኩርና መብት ማንም ሳያስገድደው በራሱ መታለልና መሳብ ምክንያት አቃለላት፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች፣ ኤሳውና ያዕቆብ የየራሳቸው ባሕሪያት ያላቸው ሲሆኑ ኤሳው አደን የሚያድን ሲሆን ያዕቆብ ግን ክሽን ያለ የወጥ ሠሪ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሥራው ወጥ ማዘጋጀት ብቻ ነው ማለት ባይሆንም በዘፍጥረት ምዕራፍ 25፡27 ጀምሮ ባለው የንባብ ክፍል ግን ወጥ ስለመሥራቱ በግልጽ ተጠቅሷል፡፡ ያዕቆብ የብኩርና መብት እጅግ መታደል እንደሆነ የገባው ሰው ስለነበር አጥብቆ ይመኛታል፡፡ ኤሳው ግን ለተሰጠው ብኩርና ምንም ግድ የሌለው ሰው ሆነና አቃለላት፡፡
ኤሳው ብኩርናውን ያቃለለበት ሁለት ምክንያች አሉ፡፡ አንደኛው ምክንያት ለብኩርናው ዋጋ አለመስጠቱ ነው፡፡ ለአንድ ነገር ክብር የምንሰጠው ዋጋውን ባወቅነው መጠን ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ስለተሰጣቸው ነገር ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም እንኳ ግድ የሌላቸው የተከፈለላቸው ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ስለማያውቁት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለኤሳው የሰጠው ብኩርና በራሱ አናሳ ሆኖ ሳይሆን ኤሳው ልኩን ስላላወቀ ያዕቆብ ከሠራት ወጥ ይልቅ አሳነሰው፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማረው ምግብ በአፍ ገብቶ በእዳሪ የሚወጣ እንጂ ከብኩሪና ጋር ምናወዳድረው አይደለም፡፡ ኤሳው ግን ለሆዱ የሚበላትን ወጥ የውርስ መብቱንና መታደልን ከሚያሳየው ብኩሪና የበላይ አደረጋት፡፡ "ይህች ብኩርናዬ ለምኔ ናት?” አለ፡፡ ለኤሳው ውድቀት ምክንያት የሆነቺው ይህ ቃል ናት፡፡ ብኩርናው መሸጡ ይህን ቃል ተከትሎ የመጣ ተግባር ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን ያለንም አማኞች በኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊና ምድራዊ በረከት ለመውረስ የተጠራንበት የደህንነታችን ማሕተም ያለን ሰዎች ሆነን ሳለ "ይህች ክርስትናዬ ለምኔ ናት?”,"ጌታን የመከተል ሕይወት ምን ትርፍ አለው?” "አገልግሎቴ ለምኔ ናት?” እያልን በሕይወታችን ዘመን ሁሉ የቀመስነውን መንፈሳዊ ባለጠግነት እናቃልል ይሆናል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት የገጠመው ተግዳሮት ነው፡፡ ኤሳው አዴን ሊያድን ሄዶ አንዳች ሳያገኝ ወደ ቤቱ ሲመለስ ረሀብም ድካምም ተገዳድሮታል፡፡ የሚያድነውን እንስሳ ሲፈልግና ሲያሳድድ ቆይቶ ሰውነቱ ከዛለ በኋላ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ከድካሙና ከረሀቡ የተነሳ የሚሞት እስክመስወው ድረስ ተስፋ ቆረጠ፡፡ እኔ ልሞት ነኝ አለ፡፡ በእርግጥ ረሀብና ድካም ሰውን ስፍራ ያስለቅቃል፣ የማይገባውንም ምግብ እንዲበላ ያደርጋል፡፡ ከአባቱ የኮበለለው አባካኙ ልጅ የእሪያን አሰር ሊበላ የተመኘው ስለራበው እንጂ በመሠረቱ ያ የሚበላ ነገር ሆኖ አይደለም፡፡ ኤሳው ያዕቆብ የሠራትን ወጥ ባይበላ በእርግጥ የሞት ነበርን? ብለን እንጠይቅ፡፡ ለድካሙና ረሀቡ ብቸኛ መፍትሔ አድርጎ ያያት ያችን ወጥ ሰለሆነ እንጂ በእርግጥ አይሞትም ነበር፡፡ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ለምንወስናቸው ውሳኔዎች መጠንቀቅ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡
ኤሳው ከአዴን ሲመለስ ቢርበውም በይስሐቅ ቤት ውስጥ ከዚች ወጥ በቀር ሌላ ምንም ምግብ የለም ማለት አይደለም፡፡ የአባቱ ቤት በሀብት የተትረፈረፈ እንጂ የሚላስ የሚቀመስ ነገር የሌለው ጠኔ የሚያጠቃው ቤት አልነበረም፡፡ በዘፍረት 25፡5 እንደምንመለከተው አብርሃም ያለውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጥቶታል ፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ይስሐቅን በሁሉም በኩል ባርኮታል፡፡ ኤሳው በዚህ ወቅት ወጥ በልቶ ብኩርናውን ከሚያቃልላት ይልቅ እንደ ራበውና እንደ ደከመው ለአባቱ በመንገር የብኩርነቱን መብት ተጠቅሞ ትክክለኛ መፍትሔ ሊያገኝ ይችል ነበር ግን ይህን አላደረግም፡፡ ሁሉም ነገር ባለበት እንዲህ ባለ ቤተ ሰብ ውስጥ ላለ አንድ ሰው ወጥ የነፍሱ መዳኛ ልትሆንለት አትችልም፡፡ ጉልበቱ የተረታበትና የተዝለፈለፈ ሰው በፊቱ የምትቀርብለት ትንሽ ነገር እንጂ የተትረፈረፈው የአባቱ ቤት አይታየውም፡፡ ኤሳውም የሚገባውን የብኩርና መብቱን ሳይጠቀም ቀርቶ በወንድሙ በመታለል ክቡር ብኩርናውን የሸጠወው ለዚህ ነው፡፡
የዛለ ክርስትናም እንዲሁ ነው፡፡ የክርስትና ሕይወት ከደከመ እግዚአብሔር የሰጠው ክቡር ጸጋና ሰማያዊ ባለጠግነት አይታየውም፡፡ አሁን ካለሁበት ሁኔታ ልውጣ እንጂ ይህ ክርስትና ለምኔ ይሆነኛል፡፡ እኔ ልሞት ነው ፣ ጌታም ዝም ብሎኛል ፣ ታዲያ ክርስትናዬ ወይም መንፈሳዊ ብኩርናዬ ምን ይጠቅመኛል ለማለት ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ስለዚህ ነው የእብራውያን ፀሐፊ በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ ፣ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ ያለው(ዕብ. 12፡ 3)፡፡ ብኩርናን ማቃለል እኮ ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው መሆን ማለት ነው፡፡ ይህች ዓለም ሰውን ከምታሳስትበት መንገድ አንዱ በሆዱ በኩል በመምጣት ነው፡፡ እባቡ ሔዋንን ያሳታት የሚበላ ምግብ በማሳየት ነው( ዘፍጥረት 3)፡፡ ሰይጣን በእባብ በኩል ሔዋንን ማሳቱ እንደተሳካለት አየና ሁሉንም የሚያንበረክክበት መንገድ ይህ ስለመሰለው ጌታ ኢየሱስንም ሲፈትን ድንጋይን እንጀራ አድርጎ እንዲበላ ጠየቀው ምክንያቱም ተርቦና ደክሞት ስላየ ነው( ማቴ 4፡1-6)፡፡ ጌታችን ለሰይጣን ፈተና የሚሸነፍበት ማንነት ስሌለለው ረታው እንጂ አስከዚያ ድረስ ሰይጣን ብዙዎችን በምግብ ምክንያት ከትክክለኛ ጎዳናቸው ሲያስወጣ ኖሮአል፡፡ በዓለምና በምግብ ጉዳይ ክቡር ነገራቸውን ከጣሉት አንዱ ኤሳው ነው፡፡ የዕብራውያን ፀሐፊ ሲያስጠነቅቀን “ስለ አንድ መብል ብኩርነቱን እንደሸጠ እንደ ኤሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ “( ዕብ.12፡15) ይለናል፡፡ ዔሳው ብኩርነቱ እጅግ ታላቅ ዋጋ ያላት መሆኗን የተረዳው ከተወሰደችበት በኋላ ነው፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደተጣለ ታውቃላችሁና ፣በእምባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ሥፍራ አላገኘምና( ዕብ. 12፡17)፡፡ ትላንት ስላቃለላት ብኩርና ማንባት ለምን አስፈለገው ቢባል ረሀብና ድካም የብኩርናውን ልቀት የሚያይበትን ዓይኖች ስለጋረዱበት ቢያቃልልም የበላው ወጥ መልሶ ሲያስርበው ለብኩናው ማልቀስ ግድ ሆነበት፡፡ ክርስቲያኖችም ሆነን ጌታ የሰጠንን ክቡር ሀብታችንን እንደሚገባ ሳንይዝ ቀርተን አንዴ ካለንበት ደረጃ ከወረድን በኋላ ወደ ቀደመው ሥፍራ ለመመለስ ብዙ ዋጋ ሳያስከፍል አይቀርም፡፡ ይህንን አውቀን እግዚአብሔር ለሰጠን ክቡር ስጦታ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡
የኤሳው ሌላው ችግር የበኩር ልጅ ቦታ ይዞ አለመገኘት ነው፡፡ የብኩርና መብት ያው ሰው ከቀዬው አካባቢ መራቅ አይገባውም፡፡ በከብቶች በወርቅ ፣ በብር፣ በወንድና በሴት ባሪየያዎች እንዲሁም ደግሞ የአባቱ በሆኑ ሁሉ ላይ የበላይ ኃላፊነት ይዞ በንብረቱ አካባቢ መገኘት አለበት፡፡ ኤሳው ግን ይህንን ሥፍራ ለቆ ወደ በረሀ ሄደ፡፡ ኑሮው በበረሀ ከሆነ እንዴት የሀብት ጠባቂ ሊሆን ይችላል? ይህ እንግዲህ እኛ የማናስተውለው አንዱ ችግራችን ነው፡፡
ሮቤል ብኩርናውን ያጣ ሌላው ሰው ነው፡፡ በእሥራኤል ልጆች መካከል ታላቁና የአለቅነት ሐይል ሁሉ የሚገባው እርሱ ቢሆንም ይህን ሁሉ ማጣት ግድ ሆኖበት ነበር፡፡ ያዕቆብም፡ አንተ በኩር ልጄና ኃይሌ የጉብዝናዬ መጀመሪያ ነህ፣ የክብር አለቃና የኃይል አለቃ አለው(ዘፍጥረት 49፡3)፡፡ ይህ ማለት ሮበል በቤተሰቡ ላይ ሥልጣንም ክብርም የሚገባው ነው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አለቅነት ለአንተ አይሁን ተባለ፡፡ 2ኛ ዜና 5፡ 1 ሮቤል የአባቱን ምንጣፍ ስላረከሰ ብኩርናው ታናሽ ለሆነው ለዮሴፍ ሲሰጠው የሮቤል ትውልድ ከብኩርና ጋር እንዳልተቆጠረ ያስረዳናል፡፡ ሮቤል በቤቱ ውስጥ በኩር ሆኖ የተወለደ ሰው ሆኖ ሳለ ባላ የተባለች ፣የንፍታሌምና የዳን እናት የሆነች፣ የአባቱን ሚስት ስላስነወራት የብኩርና መብትና ክብር ያጣ ሰው ነው፡፡ በእሥራኤል ለጆች ታሪክ ውስጥ የሮቤል ሕይወት ፣ ሥራ፣ ታሪክና ወዘተ ምን እንደሆነ ብዙም አናይም ምክንያቱም በቦታውና በሥፍራው ያልተገኘና እንደውሃ የዋለለ እንዲሁም ያባቱን ምንጣፍ ያረከሰ የመጀመሪያው ሰው ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡
ዛሬም በዚህ ዘመን ያለን አማኞች ከሥጋዊ ብኩርና ይልቅ ከእግዚአብሔር የተሰጠንን መንፈሳዊ ሀብታችንን አጥብቀን ልንይዝ ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን መጠን ለእርሱ ብኩሮች ነን(ያዕ 1 ፡18)፡፡ ለእርሱ በኩሮች ስለሆንን ደግሞ እጥፍ ድርብ እንደምንወርስ ኢየሱስ ነግሮናል፡፡ የብሉይ ኪዳን ብኩርና በሥጋ ውልደት የሚገኝ ( Biological Birthright) ሲሆን እርሱም ሁለት እጥፍ ውርስ የሚያስገኝ መብት ነው፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች የሆንንበት ፣ ሁሉን ትተን ኢየሱስ የነፍሳችን አዳኝ እንዲሆን ልባችንንና ሕይወታችንን ስንሰጥ ያገኘነው የልጅነት መብት ግን በአምበሳውና በእባቡ ላይ የሚያስረግጠን ነው፡፡ የምድሩን ብቻ ሳይሆን የሰማዩን የምንወርስበት በጌታም ዘንድ መቶ እጥፍ ሽልማት የምንቀበልበት ፣ የዘላለምንም ሕይወት የምንወርስበት መብት ነው(ማቴ 19፡29)፡፡ በማትረባ በዚህች ዓለም ጥቅም ምክንያት ወይም በረሀብ፣ በድካምና በእጦት ምክንያት ከጌታ የተቀበልነውን መንፈሳዊ ብኩርና መጣል ከሞኝነትም ቃል የማይገልጸው ተላላነት ነው፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር የሚጠብቅብንን የተቀደሰ ሕይወት ትተን የማይጠብቅብንን የረከሰ ኑሮ በመኖር የተሰጠንን በረከት፣መብትና ብልጫ እንዳናጣ እንጠንቀቅ፡፡ ጌታ ይረዳን አሜን፡፡
ይቀጥላል....