በውኑ ኢየሱስ በፕሮቴስታንት
ቤተ እምነት አይታወቅምን?
(ለቀሲስ ዶር ዘበነ ለማ ሐሳዊ ክስ የተሰጠ ምላሽ)
የማኅበራዊ
የመገናኛ ዘዴዎች እድገት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ መንፈሳዊ በረከትን
የተሞሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ትምህርትና የዝማሬ መልእክቶችን በቀላሉ ልናገኛቸው ችለናል፡፡ በአንጻሩም ደግሞ ከማኅበራዊ ገጾች ሰምተን የምንባረክባቸው መልእክቶች እንዳሉ
ሁሉ አንዳንድ ሰንፋጭ ትምህርቶችንም ደግሞ ለመስማት እንገደዳለን፡፡
አድማጮችም ካልተጠነቀቁ የስሕተት ትምህርቶች ሰለባ የመሆን
አጋጣሚዎች ሰፊ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ቅዱሳን ወገኖቻችን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያልተደላደለና የተምታታ ትምህርት ሰምተው እንዳይደናገሩ ለመርዳትና የእግዚአብሔርን ቃል
በማንበብና መጽሐፍ ቅዱስን በግልም ሆነ በጋራ እያጠኑ የስሕተት ትምህርቶችንም
በመመከት እንዲተጉ ለማበረታታት ነው፡፡ በዩቲዩብ ከተለቀቁት ስብከቶች አንዱ በቀሲስ ዘበነ ለማ የተሰበከ “ኢየሱስ ማን ነው?” የሚለው ስብከት ነው፡፡ አብዛኛዎቻችን ይህን ስብከት የተመለከትነው ይመስለኛል፡፡ ቅዱሳን
ሁላችሁ ይህን ጽሑፍ በምታነብቡበት ጊዜ አስቀድማችሁ የመምህሩን ስብከት ከዚህ ቀጥሎ ባለው የፌስቡክ ሊንክ https://www.facebook.com/birhan.maray/videos/1679458008990526/ላይ መመልከት ይጠቅማል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የትኛውንም
ቤተ እምነት ለመኮነን ሳይሆን ወይም ግለሰቦችንም ለመንቀፍ ሳይሆን ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ሲበረዝና ካልተጣራ ትምህርት ጋር ሲደባለቅ፣
ያውም ደግሞ በማኅበራዊ ገጾች ሲለጠፍና ያየው ሁሉ ሲደናገርበት እያየንና እየሰማን ዝም ማለት አግባብ ስላይደለ ብቻ ነው፡፡ ማንም ተናገረ ስሕተት ምን ጊዜም
ቢሆን ሰሕተት በመሆኑ የሚሰሙት ምዕመናን እንዳይጠቁና እንዳይደነጋገሩ ለመርዳትም ጭምር ነው፡፡ ይኸው ታውቆ ምዕመናን ማንኛውንም
ትምህርት ሲሰሙ ህያው በሆነውና ሥልጣን ባለው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈትሹና እንዳይደናገሩ፣ ቃሉን በግልም ሆነ በጋራ በማጥናት
እንዲተጉ ለማበረታታት ነው፡፡
ቀሲስ
ዘበነ ለማ መድረክ ባገኙ ቁጥር የፕሮቴስታንትን ቤተእምነት ሲቃወሙ ሲያሰኛቸውም ሲሳደቡ ብዙ ጊዜ ሰምተናቸዋል፡፡ በቅርቡ በዩቲዩብ
በተለቀቀው ስብከታቸውም ቢሆን ኢየሱስ ማን ነው በሚል ርዕስ ቃሉን እያነበቡ በውስጣቸው የሞላባቸው መንፈስ እንዳሳያቸውና እንደመራቸው እየተረጎሙ ያስተምሩ እንጂ ከጊዜአቸው አብላጫውን
ያጠፉት ስለ ተለያዩ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች
ያነበቡትንም፣ በጨረፍታ የሰሙትንም ሲናገሩ ነው፡፡ ስለ ክርስቶስ
አምላክነት ከዮሐ. 1፡1፣ ቲቶ 2፡12፣ ሐዋ. 20፡28፣ ሮሜ
9፡5፣ 1ኛ ዮሐ. 5፡20 በማንበብ ለአድማጮቻቸው እንዳሳዩት ለመቀጠልም አቅም አልነበራቸውም፡፡ በሐቅ ላይ የተመሠረተ፣ መሬት የረገጠና፣ የቃሉ ወተት ያለበት ስብከት ቢሆን
ኖሮ ሁላችንም ጠጥተነው በታነጽንበት ነበር፣ ግን ይህኛው ስብከት ሳይሆን እጣቢ ነው፡፡ በትምህርታቸው ከአንዲት ሃይማኖት በቀር ሌሎች በአገራችን ያሉት ቤተ እምነቶች በሙሉ እውነተኞች እንዳይሉ አድርገው ሁሉንም በአንድ ሙቀጫ በጅምላ ከመውቀጥም አልፈው ጭራሹኑ በፕሮቴስታንት እምነት ኢየሱስ አይታወቅም ሲሉ ለአፋቸው እንኳ
ያዝ አላደረጋቸውም፡፡ ደጋግመው እውነተኛ ሃይማኖት አንዲት ናት የሚሏት የቷ
እንደሆነች ግን ሳይናገሩ አለፉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናትን “የእምነት ድርጅት” እያሉ መጥራታቸውም ራሱ የሚሉትን የማያውቁ
የሚያሰኛቸው ነው፡፡ እውነት ለመናገር ይህ ስብከት የሚደበቅ እንጂ ሰው ሁሉ በሚያየው ቦታ ላይ
መለጠፍ የሚገባው አይደለም ምክንያቱም የአለሁ አለሁ ባይ የስልጡን አፍ ሥራ እንጂ የሚለውን ከሚያውቅ አስተማሪ በተለይም ከሃይማኖት
መምህር የሚተላለፍ ዓይነት አይደለምና፡፡
ቀሲሱ
እንዲሁ ቆላና ደጋውን ሲረግጡ ውለው ስብከቻቸውን ያጠናቀቁት በአደናጋሪ ድምዳሜ ነው፡፡ ምናልባት ፕሮቴስታንቶች ዘንድ የኢየሱስ አምላክነት የማይታወቅ ስለሆነ እርሳቸው
አዲስ መገለጥ ያመጡ መስሎአቸው ከሆነ ያ ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ እርሳቸውም ቢሆኑ ልብም አቅምም አግኝተው ስለ ክርስቶስ አምላክነት ለመናገር
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማንበብና ማስነበብ ጀምረው ሳለ ብዙም ሳይራመዱ እንደለመዱት
ቤተ እምነቶችን ወደመሳደቡ ዘለው ገቡ እንጂ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ አምላክነት ቃሉ እንደሚለው አስረግጠው ማስተማር አልቻሉም፡፡
ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ማን እንደሚሰብክ ሲናገር እንዲህ አለ፡ ‘መቼም
አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፣ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካን” ( 1ኛ ቆሮ.. 1፡22-23)፡፡ ቀሲስ ዘበነ
መምህሩ ሌላውን ሁሉ ትተው ክርስቶስን ቢሰብኩ ምንኛ መልካም ነበር፡፡
ቀሲሱ እንደሚሉት ኢየሱስ በፕሮቴስታንት እምነት አይታወቅምን? በስብከቶቻቸው የሚያንኳስሷቸው የወንጌላውያን
ቤተ እምነቶች ግን ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተመሥርተው ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ያምናሉ፣ ያስተምራሉም፡፡ ራሱን ብቻ የሚያይ
ሰው የራሱ ልክ እንጂ የሌላው ስለማይታወቀው ከሁሉም በላይ ሊቁ እርሱ ብቻ ስለሚመስለው ካልሆነ መምህር ዘበነ ፕሮቴስታንት የክርስቶስን
አምላክነት አያውቁም ለማለት ገና የበቁ አይመስለኝም፡፡ በፕሮቴስታንት እምነት ዘንድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የሃይማኖተኝነት ስሜት
ሳይሆን የክርስቶስን አምላክነት ፣ ደኅንነትም በእርሱ ብቻ እንደሆነ ማመንና እርሱን ከሁሉም በላይ የማድረግ ሕይወት ነው፡፡ ስለ ክርስቶስ አምላክነት፣ ስለ ቃሉ እውነተኛነት ፣ በእምነትና በጸጋ ብቻ ስለሚገኝ ደህንነት፣ ማስተማርና መስበክ
ከቀድሞ አባቶቻቸው ጀምሮ የነበራቸው ተግባራቸው ነው፡፡
በዚህ ስብከት ውስጥ ቆብ እንደቀደዱ
ከሃዲ ተደርገው መምህር ዘበነን በመሰለ ሰው ሲጠላሹ የነበረው የተሃዲሶ አስተማሪ ማርቲን ሉተርና ፈረንሳዊው ዮሐንስ ካልቪን የትምህርታቸው
ማእከልና በጊዜው የነበሩ አማኞች እንደ መፈክር የሚያስተጋቡአቸው አምስት ሶላዎች (ብቻዎች) (the five solas) አሉ፡፡ ሶላ ከላቲን ቋንቋ የተወሰደ ቃል ሲሆን
ትርጓሜውም ( “Alone” “Only” “ብቻ” ) ማለት ነው፡፡ ለቀሲስ
ዘበነ ባይዋጥላቸውና በአንዱ ስብከታቸው እነዚህን አምስቱን ሶላዎች ትክክል አይደሉም ለማለት የማይገናኙት ነገሮች እያገናኙ ፕሮቴስታንትን
እምነት ቢያጥልሉትም በተለይም በተሐድሶ አማኞች ዘንድ የሚታወቁት ሶላዎች 1. (Sola Christus) ማለትም ደህነንት
በክርስቶስ ብቻ፣ 2. Sola Sctuptura ለደህንነታችን የሚሆነውን አስፈላጊ ትምህርት የሚያስተምረን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፣
3. Sola Gratia ደህንነት በጸጋ ብቻ ነው፣ 4. Sola
De gloria ደህንነታችን በእግዚአብሔር የተገኘ በመሆኑ ክብር የሚገባው እግዚአብሔር ብቻ ነው፣ እንዲሁም 5. Sola
Fide ሲሆን ይህ ደግሞ ደህንነት በእምነት ብቻ ማለት ነው የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሶላዎች የፕሮቴስታንት እምነት ዶግማዎች ሳይሆኑ
ደህንነት የሚገኝበትን መንገድ ለማሳየት የቀድሞዎቹ አስተማሪዎች ለምዕምናኑ ያስረዱአቸው ትምህርትች ናቸው፡፡ ዶግማና የአንድ ትምህርት
ርዕስ ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ቀሲሱ መሸሸግ አልነበረባቸውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚገኙ ወንጌላውያን ቤተ እምነቶችም ሆነ የተሐዲሶ እንቅስቃሴዎች እነዚህን አምስቱን ሶላዎች እንደመመሪያ በድርገው
ባይዙትም መሠረታዊ አሳቡን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይቀበሉታል፡፡
ዛሬም የፕሮቴስታንት ፣ ወንጌላውያን አማኞችና የተሃድሶ ቤተ እምነቶች እንደ ቀድሞዎቹ
የተሃድሶ አራማጆች ለደኅንነታችን ክርስቶስ ብቻ በቂ ነው የሚለውን
እምነት አጥብቀው ይዘዋል፡፡ ለሰው ልጆች ደህንነት መንገድ እውነት ሕይወት የሆነው፣ ነፍሱን ለእኛ አሳልፎ የሰጠው ፣ ለኃጢአታችን
የሞተው አሁንም ሊያድነን የተቻለው ክርስቶስ ብቻ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እርሱ እንደሚያስተምረን ሕግና ነቢያት ስለ እርሱ
የመሰከሩለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን እናምነዋለን፣ እናመልከዋለንም፡፡ እርሱ ለእኛ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፣ የእምነታችን ጀማሪና ፈጻሚ፣ የተመሠረትንበትና
የተደላደልንበት የከበረው የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ እርሱ አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛ ፣ ትናንት የነበረ ዛሬም ያለና ነገም
ለዘላለም የሚኖር፣ የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ፣ በሰማይ በምድር ሥልጣን ያለው ፣ የሞትና የሲዖልን መክፈቻ በእጁ ያያዘ፣ ሞትንና
ሲዖልን የረታ፣ በአጋንንት፣ በደዌና በክፉ ኃይላት ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው ፣ ምላስ ሁሉ ማዳኑን የሚያወሩለት፣ ጉልበትም ሁሉ የሚንበረከክለት
ጌታ ነው፡፡ የብሉይና የሐዲስ ኪዳናት ማዕከላዊ መልእክት እርሱ ብቻ ነው፡፡ ቀሲሱ ግን በፕሮቴስታንት እምነት ኢየሱስ አይታወቅም
ሲሉ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ከሚነግረን የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነው ኢየሱስ ሌላ ኢየሱስ አላቸው ማለታቸው
ይሆን?
ወንጌላውያን
አማኞች የክርስቶስን አምላክነት እርሳቸው የጠቀሱአቸውን ክፍሎች ጨምሮ በጣም በጠለቀ አኳኋን በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በመመሠረት ያስተምራሉ፡፡ ቀሲስ ዘበነም እስከ አሁን
ሳያዩአቸው ቀርተው ከሆነ ከጥቂሶቹ የተወሰኑት እነሆ፣ ዮሐ. 20፡28፣ ቆላ. 1፡15-17፣ 2ኛ ጴጥ. 1፡1፡፡ በወንጌላውያን
አማኞች እምነት መሠረት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት በቀጥታ በቃል ጥቅስ ከምናነበው በተጨማሪ ክርስቶስን መለኮት ነው እንድንል ስለሚያደርጉ የእርሱ መለኮታዊ
ባሕሪያት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ አምላክ ብቻ ያለው መለኮታዊ ባሕሪያት በክርስቶስ ላይ በመገለጣቸው በእርሱ አምላክነት እናምናለን፡፡ ለምሳሌ ፈጣሪነቱ (ዘፍ. 1፡1-3፣ ቆላ.
15-17 )፣ ኃጢአትን ይቅር ማለቱ፣ ሁሉን አዋቂነቱ፣ ኃጢአት ያልተገኘበት መሆኑ፣ መላእክትን መዘዝ መቻሉ፣ የአምላክን ባሕሪይ
መካፈሉ ሁሉንም ለመጥቀስ የዚህ ገጽ ውስንነት ስለማይፈቅድ ለማስረጃነት
ይህ ይበቃል ብዬ የምተዋቸው ሌሎችም ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት የማያውቁቱትን
ነገር እንዲያ በውስጡ እንዳለፈበት ወይም ከጉዳዩ ጋር አብሮ የተፈጠረ ያህል አስመስሎ መናገር በሐሰት ከመመስከር የከፋ አደገኛ
ወንጀልም ስለሆነ ሌላው ቢቀር የኅሊና ዳኝነት እንኳ የማይኖራቸው ምን ቢሆኑ ነው ያስብላል፡፡
በጥቅሉ
ቀሲስ ዘበነ ከሌሎች ጊዜያቶች ሁሉ ይልቅ በዚህ ስብከታቸው የባሰ ስሕተት ታይቶባቸዋል፡፡ ትምህርታቸው በጣም
አሳዛኝና ዘግናኝ የሆነ አስተምህሮአዊ ስሕተት የታጨቀበት ነው፡፡ ታሪክን የማፋለስ፣ የቅዱሳት መጽሐፍትን ሥነ አፈታት
(Heremeneutics) የማንጋደድ፣ እና በቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ያልተጻፈውን እንደተጻፈ አድርገው በማንበብ ቅዱሳንን የማሳት
ችግር ታይቶባቸዋል፡፡ ከስሕተት ሁሉ የከፋው ስሕተት የእግዚአብሔርን ቃል ማጣመም ስለሆነ ይህ አንድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ማስጠየቁ
አይቀርም፡፡
በአእምሮው
ያለ ሰው ሊገነዘበው የሚችለውን አንድ አሳብ እናንሳ፡፡ የክርስትና ሃይማኖት የራሱ የእምነት መጽሐፍ አለው እንጂ በአንዲት በራሪ
ወረቀት ፓምፍሌት የተመሠረተ አይደለም፡፡ መላው የወንጌላውያን አማኞች የምናምንበትና የቆምንበት
የእግዚአብሔር ሥልጣናዊ ቃል በሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ቀሲስ ዘበነ ፕሮቴስታንቶች አንድን ትራክት እንደ ትልቅ መመሪያ
አድርገው በዓለም ዙሪያ ሁሉ እንደሚጠቀሙባት መናገራቸው መሠረተ ቢስ ዝርጠጣ ነው፡፡ “አማላጃችን ማነው?” የሚለውን ትራክት ያሳተመው በአሜሪካን አገር የሚገኘው “ጎሰፕል ትራክት
ሚኒስትሪ” የተሰኘ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም እንደሆነ ቀሲሱ ራሳቸው ይመሰክራሉ፡፡ ያ ድርጀት ክርስቲያናዊ የጽሑፍ አገልግሎት እንጂ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ያሉት መንፈሳዊ ተቋማት ( የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ ኢንተርናሽናል ባይብል ሶሳይቲ፣ ካምፓስ
ኪሩሴድ ፎር ክራይስት፣ ግሎብ ሥነ ጽሑፍ ድርጅት፣ አፍሪካን ኢቫንጄሊሰቲክ ኢንተርፕራይዝ ወዘተ) ቤተ እምነቶች አይደሉም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በመተርጎም ፣ በማሳተም፣ በማሰራጨትና በማስተማር በክርስትና
እምነት ያሉትን ሁሉ በእኩል መንፈስ የሚያገለግሉ የአገልግሎት ክፍሎች ናቸው፡፡ ጎስፕል ትራክት
ሚኒስትሪ የሚባል የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን የለም፡፡ ይህ
አገልግሎት በአንድ
ቤተ ክርስቲያን ሥር ያለ፣ ወይም ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ መንፈሳዊ ተቋም ሊሆን ይችላል፡፡ ሠራተኞቹም ከየትኛውም ቤተ እምነቶች
የተውጣጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ትራክቱም ቢሆን የፕሮቴስታንት ወይም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የእምነት አቋም ሰነድ
አይደለም፡፡ ቀሲሱ ግን ይህን ሁሉ ሳያጣሩ ትራክቷን እንዳገኙ ብቻ የእምነታችንንና የትምህርታችንንም ዋጋ የሚያሳብሩበት መንገድ ያገኙ መስሎአቸው
ለስድብና ለትችት ተጣደፉ፡፡ ስብከታቸውም ቢሆን ያልተዘጋጁበት መሆኑን መላው ከጠፋበት ተፋልሶውና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ጨምሮ
ሁሉም የክርስትና ቤተ እምነቶች በሚያምኑበት አስተምህሮተ-ሥላሴ ላይ ከፈጠሩት ብዥታ መረዳት ይቻላል፡፡
የእግዚአብሔር
ቃል የሳቱትን እንዲመልሱ የእውነተኛ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን እንደሚጠይቃቸው አውቀው (ይሁ. 22-23፣ ገላ. 6፡1-2) ቀሲስ
ዘበነ ለማ በጎስፕል ትራክት ሚኒስትሪ የሚያገለግሉት ሰዎች የተሳሳቱ ከመሰላቸው እንደ በሳል ሰው የእግዚአብሔርን
ቃል ይዘው ሰዎቹን ከስሕተታቸው
ለመመለስና ለማቃናት ምን እንዳደረጉ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ይህንን ያላደረጉ ከሆነ ከአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መምህር የሚጠበቅባቸውን
ኃላፊነት አልተወጡም፡፡ ስሕተት የተገኘባቸው ቤተ እምነቶች ያሉም ከመሰላቸው ምንጩ ተቀድቶ በማያልቀው በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በማስደገፍ እንጂ
ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ የፈጠራ ተረት ሌሎችን ለማድከም መሞከር
ላይገድሉ ካራ መዘዙ ያሰኛቸው እንደሆነ እንጂ ቤተ እምነቶችን አያስበረግጋቸውም፡፡
ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ቃል
ማጣመም ወይም የሌለውን ነገር በላዩ ላይ መጨመር ወይም ከተጻፈው ከመቀነስ የከፋ በደል መሆኑን ራእ. 22፡17-19 ያሳያል፡፡
ለዚህም ቀሲስ ዘበነ በዘፍ. 11 ላይ የሚገኘውን ታሪክ እንዴት አድርገው
እንደገለጹትና እንደተረጎሙት መመልከት ብቻውን በቂ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ መንኩራኩር ወደ ጠፈር የተላከው በዘፍጥረት 11 ላይ
ነው ይላሉ ቀሲሱ፡፡ እንዲህ አሉ
ባቢሎናውያን በሰነናዖር ሜዳ ላይ ትልቅ ግንብ ሠሩና መንኩራኩራቸውን
ወደ ሰማይ አመጠቁ፡፡ ግንቡን የሠሩበት ምክንያት ፍልውኃ [1]
እንደገና ከመጣ እንዳንጠፋ ብለው ነው፡፡ የኖህ መርከብ ሄዳ ያረፈችው በአራራት ተራራ ላይ ስለሆነ ከተራራው የሚበልጥ ግንብ ሠርተን
እንተርፋለን ብለው፣ ሁለተኛ ዘራችን ከምድር ላይ ሳይበተን ስማችንን እናስጠራ ፣ ሦስተኛ ይህን አባቶቻችንን ያጠፋውን እግዚአብሔርን
እንውጋውና የእርሱን ከተማ እንውረሰው ብለው ነው፡፡ ዛሬ ይህ ነው
በጠፈር ላይ መዝናኛ የሚሠራው፡፡ ከመንኩራኩራቸው ደጋግመው ወደ ሰማይ ጦር ወረወሩ፣ ጦሩ ደም እየነካው ተመልሶ መጣ፡፡ ከላይ ደም የሚቀባላቸው ርኩስ
መንፈስ ነው፡፡ ይህን ሲያዩ እነርሱም ይህን እግዚአብሔርን ገደልነው አሉ፡፡
እነርሱም ደግሞ ሦስት ጊዜ ደጋግመው ጦር እንደወረወሩና በሦስቱም ደም የነካው ጦር ተመልሶ ወደ እነርሱ እንደመጣ ይናገሩና
ለአራተኛ ጊዜ የተወረወረውን ጦር ደም አልነካውም አሉ፡፡ ሦስት ጊዜ ደም ነክቶ መምጣቱ የሦስትነታቸው ምስጢር ነበር ፡፡
ትምህርታቸው ተረት ብቻ ሳይሆን አስደንጋጭና ዘግናኝ ስሕተት አለበት ያልኩት ለዚህ
ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ የመንደር ፈጠራ
ወሬ ይባል እንደሆነ እንጂ የሥነ መለኮት ትምህርት ይዘት የለበትም፡፡ ሳይንስ እንዳንለው ሳይንስም ቢሆን ቢያንስ እውነታን ለማሳየት ይሞክራል፡፡ እንዲያው ከምንም የሌለበት ብለን
እንዳንልፈው የእርኩስ መንፈስን ተሳትፎ እናይበታለን፡፡ መቼም ቀሲስ
ዘበነ ራሳቸውም ቢሆኑ ይህንን በአብርሆተ- መለኮት የተገኘ
ትምህርት ነው እንደማይሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አብርሆተ- መለኮት (Illumination) ማለት ቅዱሳን መጻሕፍትን በምናጠናበት
ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የምንባብ ክፍሉን እንድንረዳ ቃሉን ለአእምሮአችን የሚያበራበት ሂደት ነው፡፡ የተሸቃቀጠ ትምህርት መስጠት ከመንፈስ
ቅዱስ ባሕሪይ ጋር የማይሄድ ስለሆነ ማንም መጽሐፍ ቅዱሱን ከልቡ የሚያነብ ሰው በዚህ ይታለላል ብለን አናምንም፡፡ ቀሲሱ ግን እውነት
አስመስለው ይህንን ጉድፍ አስተማሩት፡፡
ቀሲሱ ይህንን ትምህርት ከየት
እንዳመጡት አይታወቅም (ከማብራሪያ መጽሐፍ Commentary እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡) ይህ አሳብ በዘፍ. 11 ላይ የለም፡፡ አገላለጡ
ራሱ የፈጠራ ተረት እንጂ እግዚአብሔር ቃል አይደለም፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደዚህ ዓይነቱን ትምህርት ፡ “ለዚህ ዓለም የሚመችና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ የሚመስል ተረት ”
ይለዋል ( 1 ጢሞ. 4፡7፣)፡፡ በ2ኛ ጢሞ. 2፡ 16 ላይ ደግሞ
“ለዚህ ዓለም የሚመች ከንቱ መለፍለፍ” ፣ ሲል እውነተኛውን
ወንጌል ከመስማት ይልቅ እንደዚህ ያለውን መከተል የሚወዱትን ደግሞ እውነትን
ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ (2ኛ ጢሞ. 4፡3-4) ይላቸዋል፡፡ ይህ ትምህርት የፈጠራ ተረትነቱ ብቻ ሳይሆን በአስተምህሮተ ሥላሴ ላይ ያደረገው
ክህደት ሌላው ጥፋት ነው፡፡ ርኩስ መንፈስ በጦር ጫፍ ላይ ደም እየነከረ በመስጠት የሥላሴን ሦስትነት እንዳረጋገጠልን ማስተማራቸው
ትምህርታቸውን አጋንንታዊ ሊያሰኘው ይችላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር መለኮታዊ አንድነትና አካላዊ ሦስትነት የሚነገረን የእግዚአብሔር
ቃል እንጂ ሰይጣን አይደለም፡፡ ደግሞ ሰይጣን የቅዱሳት አስተምህሮ ፈታሽና አረጋጋጭ የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው? ማንስ ነው የሾመው?
በቃሉ የተጻፈው አልታመን ብሎን እንደ እውነተኝ ምንጭ ሰይጣን ተጠየቀ ማለት ነው? ለነገሩ ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ መስሎ
በመምጣት እንዲህ ዓይነት ትምህርት በሕዝበ ክርስቲያን መካከል ሊበትነው ይችላልና ምዕመናን መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ይህ አባባላቸው
የሚያሳየው ሰይጣን ስለ ሥላሴ የሚናገረውን መቀበላቸውን ነው፡፡ ይህ የትምህርታቸውን ምንጭም ያመለክታል፡፡
ቀሲሱ በእግዚአብሔር ቃል ላይ
የሌለውን ሌላ ልበ-ወለድ የጨመሩት በማቴ. 21 ላይ “የቢታንያ ድንጋዮች እንደ ሰው ተነሥተው ሆሳዕና እያሉ ለኢየሱስ ምስጋና በማቅረብ ዝማሬ መዘመር ጀመሩ” በማለት
ነው፡፡ ይህም ሌላ ተረት ነው፡፡ ቀሲስ ዘበነ ማቴ. 21ን በደንብ ያነበቡ አይመስሉም፡፡ ምናልባት በሉቃ. 19፡28-40
ላይ የተጻፈውን ታሪክ ለመናገር ፈልገው ይሆን? በዚያ ክፍልም ቢሆን
ድንጋዮች ተነሥተው ዘመሩ የሚል የለበትም፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስን
ጨምሮ አራቱም ወንጌላት ጌታ ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ እንዴት እንደተቀበሉት በመልእከታቸው ጽፈዋል
(ማቴ. 21 ፡1-11፣ ማር. 11፡1-10፣ ሉቃ. 19፡28-40፣ ዮሐ. 12፡12- 19)፡፡ ከአራቱ ወንጌላውያን ሉቃስ ብቻ ፈሪሳውያን
የሚዘምሩ ሰዎችን ወይም ደቀመዛሙርቱን ዝም እንዲያሰኛቸው ኢየሱስን ሲጠይቁት እርሱ መልሶ “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ”
እንዳለ ዘግቧል ፡፡ ከዚያ ውጭ አራቱም ወንጌላውያን በጻፉአቸው መልእክቶች
ውስጥ የቢታንያ ድንጋዮች እንደ ሰው ቆመው ኢየሱስን አመሰገኑ የሚል የለበትም፣ አልተጻፈምም፡፡ ያልተጻፈውን እንደተጻፈ አድርገው
ማቅረባቸው ስህተት ብቻ ሳይሆን ኃጢአትም ነው (ራእ. 22፡17-19)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በእጁ የያዘ አንድ መምህር ይቅርና በኅብረተሰባችን
ተራ ሰው እንኳ ሐሰት መናገር ብርቱ ወንጀል ከመፈጸም ይቆጠር የለም ወይ?
“ሐሰተኛ ያወራውን ፈረሰኛ አይመልሰውም ” እንደሚባለው
እንዳይሆን ምዕመናን እንደዚህ ዓይነት ቅይጥ ስብከት ሲሰሙ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡
በፕሮቴስታንቱ
ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አይታወቅም ይላሉ መምህሩ፡፡ ይበሉ እንጂ እርሳቸው ራሳቸው “ኢየሱስ ማን ነው?” ብለው በተነሱበት ርዕሰ ጉዳይ በበቂ
ሁኔታ ስለ ማንነቱ ማስተማር ትተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አመጸኛ ትውልድ ምልክትን ይሻል እንደለው እርሱ ባደረገው ተአምራት
ላይ ነው ያተኮሩት፡፡ ይህ የሐሰተኞችና የዓመጸኞች መለያ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናቸውም በደንብ ያስቀመጠችውና አባቶቻችንም ኖሮውበት ያለፉ ትምህርት እንዳለ ተናገሩ፡፡ ታዲያ ያ ትምህርት ስለ ኢየሱስ ምን ይላል? ኢየሱስንስ ማን ይለዋል? ያ እርሳቸው
የሚቆጥሩትን ተአምራት ያደረገው ኢየሱስ ማነው? በቃ ኢየሱስ ማነው
የሚለው ጥያቄ ሌሎችን እምነት በመሳደብ መልስ ያገኛል ማለት ነው?
ነቢያት በትንቢታቸው፣ ሐዋሪያትም በትምህርታቸው፣ ስለ ኢየሱስ የተናገሩትን ብቻ በመናገር የምዕመናንን ሕይወት ማነጽ
ቅድሚያ ሰሰጠት ነበረበት፡፡ እርሳቸው ግን ያንን ከማድረግ ይልቅ
ተራ
የቃላት ርክፍካፎ በተበራከተበት ትምህርት እምነትን ለመከላከል መሞከራቸው አሳዛኝም አሳፋሪም ነው፡፡
ኢየሱስ አምላክ ስለሆነ ፈራጅ
እንጂ አማላጅ አይደለም ይላሉ ቀሲሱ፡፡ ከየትኛው መዝገበ ቃላት እንዳገኙ
ባይታወቅም አምላክ ማለት ፈረጅ ዳኛ ማለት ነው ብለውም ተርጉመዋል፡፡ በእርግጥ ኢየሱስ እርሳቸው እንደሚሉት አማላጅ
አይደለምን? እርሳቸው ኢየሱስን አማላጅ አይደለም ለማለት ከሚያቀርቧቸው
ምክንያቶች አንደኛው እርሱ አምላክ ሆኖ ሳለ እንዴት አማላጅ ይሆናል በማለት ነው፡፡ ሁለተኛ አማላጅ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ የተጨመረው ከ1940 ዓ.ም. ወዲህ በታተሙት እትሞች ሲሆን ቃሉን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጨመረው ማርቲን ሉተር ነው፡፡ ሦስተኛ
በግሪኩ ትርጉም አማላጅ ሳይሆን ፈራጅ ነው የሚል አለበት ይላሉ፡፡
እንግዲህ እነዚህን አባባሎች አንድ በአንድ መገምገሙ በጣም ጥሩ ይመስለኛል፡፡
ኢየሱስ ፈራጅ ሆኖ እንዴት አማላጅ
ይሆናል የሚለውን እንፍታ፡፡ ቀሲሱ ራሳቸው በእጃቸው የያዙትን መጽሐፍ
ቅዱስ ከፍተው የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ፡ “የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን
የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡” እንደሚል እያነበቡ የሚማልደው ሳይሆን
የሚፈርደው ማለት ነበረበት አሉ ፡፡ ይህ እርሳቸው እንደሚመኙት ሁሉ
ነገር እንዲሆንላቸው ካላቸው ፍላጎት የመነጨ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰው
ወፈፍ ባረገው ቁጥር እየተነሳ ቅዱስ ቃሉን እንዲህ ማለት ነበረበትና እንዲህ እናድርገው እያለ ቢለውጠው ኖሮ እስከ አሁን ድረስ
መጽሐፍ ቅዱስ እየተሰረዘና እየተደለዘ ከእግዚአብሔር ቃልነት ወደ ግለሰብ የልበ-ወለድ መለመማጃ ንድፍነት በተቀየረ ነበር፡፡ ቀሲሱ
የምንባቡን አውድ ለመጠበቅ ብለው ይሆናል፣ በክፍሉ ትንሽ ከፍ ብለን እናንብብ አሉና አንድ ቁጥር ብቻ ከፍ ብለው የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኮንንስ
ማነው የምትለዋን ብቻ መዝዘው በማውጣት በዚያ ምክንያት ክፍሉ ስለ ኢየሱስ ፈራጅነት እንጂ ስለ አማላጅነቱ አይናገርም ብለ አረፉ፡፡
አንድን የምንባብ ክፍል ሙሉ አሳብ ለማግኘት አንድ ቁጥር ያህል ብቻ
ከፍ ወይም ዝቅ በማለት ሳይሆን፣ ወይም አንባቢው በሚፈቅደው ሳይሆን
አውደ- ምንባቡ እስከሚፈቅደው ድረስ ወደ ላይም ከፍ ወደታችም ዝቅ ብሎ በማንበብ ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ ቁጥር 34 ስለ አማላጅነት
ወይስ ስለ ፈራጅነት ይናገራል ለማለት አውዱን ከቁጥር 34 ወደ 33 ብቻ ፈቀቅ ብሎ ማንበብ ሳይሆን ከላይ በኩል እስከ ቁጥር 20 ከታች በኩል እስከ ቁጥር 39 ድረስ
በማንበብ ሙሉ አሳቡን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ እንዲያስ ቢሆን የሚኮንን የሚለው ቃልና የሚያማልድ የሚሉት ቃላት ሁለት የተለያዩ ቃላት ናቸው እንጂ ከቶውኑስ መቼ አንድ
ሆኑ? በዚያ ክፍል ጳውሎስ የሚያስተላልፍልን መልእክት ለሰዎች ልጆች ደኅንነት የነበረው
የእግዚአብሔር ሉዓላዊ እቅድ (ቁጥር 20-30) እና እግዚአብሔር
በስሙ ለምናምን ሁሉ በፍቅሩ ያዘጋጀልን የደህንነት ዋስትና (ቁጥር 31-39) መሆኑን ከአውዱ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በሮሜ
8፡34 ላይ ኢየሱስ ፈራጅ ነው ሳይሆን አማላጅ ነው መባሉ ትክክል ነው።
ምክንያቱም ያ ክፍል በጥቅሉ ስለ ፍርድ ሳይሆን እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ያሳየውን የእርሱ ታላቅ ፍቅርና የደህንነትን
ዘላለማዊ ዕቅድ ይነግረናልና፡፡ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ አውደ ንባብ ለመረዳት ቁንጽል አሳብን መዝዞ በማውጣት ለራስ እንደሚመች
አድርጎ መተርጎም ወደ ከፍተኛ ስሕተት ስለሚመራ ከዚያ ራስንም ለመጠበቅ የምንባብ ክፍሉን አውዳዊ አሳቡን መከተል ያስፈልጋል፡፡
ምናልባት ቀሲስ ዘበነ አውደ ወጥ የሆኑበት ምክንያት ለቅዱሳት
መጻሕፍት ሥነ-አፈታት መርህ እንግዳ ስለሆኑ ፣ አሊያም እግዚአብሔርን ቃል በትክክል የመተርጎም ጉዳይ ብዙም ስለማያሳስባቸው ይሆናል፡፡
ኢየሱስ ፈራጅ መሆኑን የእግዚአብሔር
ቃል ይነግረናል፡፡ ሆኖም ግን የፍርድ ጊዜ ገና ስላልደረሰ እርሱ አሁን በፍርድ ተግባር ላይ አይደለም፡፡ በጎችን ከፍየሎች የሚለይበት (ማቴ. 25፡32-44)፣ ስንዴውን ከእንክርዳዱ፣
ገለባውን ከፍሬ ለይቶ ስንዴውን ወደ ጎተራው የሚከትበትና ገለባውን በማይጠፋ እሳት የሚያቃጥልበት የፍርድ ቀን ገና አልደረሰም
(ማቴ. 3፡8-12-፣ ማቴ. 13፡1-50)፡፡ ሮሜ 8፡34 ስለ አለፈውና
ስለ አሁኑ ጊዜ የኢየሱስ ተግባራት የሚናገር ክፍል እንጂ በመጨረሻው ቀን ፍጻሜ እርሱ ስለሚሠራቸው ሥራዎች አይደለም፡፡ ስለ አላፊ
ጊዜያት ተግባራቱ ማለትም ስለ ሞቱና ከሙታን ስለ መነሣቱ ሲሆን ስለ
አሁኑ ተግባሩ ደግሞ በአብ ቀኝ ስለ መቀመጡና ስለ እኛ ስለ መማለዱ ይነግረናል፡፡ ከዚህ በኋላ ክርስቶስ አይሞትም ከሙታንም ይነሳል
ተብሎ አይጠበቅም ግን ዳግመኛ ሲመጣ በህያዋንና በሙታን ላይ ይፈርዳል፣ ያ ቀንም ሲደርስ እርሱ ለሁሉም ፍርድን ይሰጣል፡፡ ጊዜው እስኪደርስ ድረስ አሁን ያለንበት ዘመን ወንጌል የሚሰበክበት፣ የጠፉት
የሚፈለጉበት፣ የምህረት፣ የንስሐ ጥሪ ጊዜ እንጂ ፍርድ የሚሰጥበት
ጊዜ አይደለም፡፡ ኢየሱስም በአብ ቀኝ ተቀምጦ ስለ እኛ እየፈረደ
ሳይሆን እያማለደ ነው፡፡ እርሱ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስ በእግዚአብሔርና
በእኛ መካካል መካከለኛ አስታራቂ ፣ በድካማችን የሚራራና የሚማልድልን አማላጅ እንጂ ፈራጅ አላስፈለገንም፡፡ የእርሱ ዙፋን የፍርድ
ሳይሆን በእምነት ወደ እርሱ የቀረቡት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የሚረዳቸውን ጸጋ የሚያገኙበት የጸጋ ዙፋን ነው (ዕብ. 4፡14-17)፡፡
ስለዚህ ፍርድ የሚሰጥበት ቀን እስኪደርስ ድረስ ሁሉም እንዳለ እንደሚቀጥልና በመጨረሻው ቀን ለእያንዳንዱ ዋጋውን እንደሚሰጥ
ጌታ ራሱ ተናግሮአል። ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዓመፀኛው ወደ ፊት
ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል
ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ (ራእ. 22፡
10-13)። መምህሩ ያላወቁት ነገር ቢኖር ይህንን ነው፡፡
ኢየሱስ ፈራጅ ሆኖ አማላጅ አይሆንም
ማለታቸውም የሚገርም ሰውኛ መረዳት ነው፡፡ የእግዚአብሔር አስተሳሰብ ግን እንደ ሰው አለመሆኑ እንዴት እንደጠፋቸውም ይገርማል፡፡ ሰዎች በኃጢአታቸው ተናዝዘው ንሰሐ በመግባት ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ
የተሰጣቸው ይህ ንስሐ፣ የምልጃ፣ የምሕረትና የተሐድሶ ጊዜ ሲያበቃ
የፍርዱ ጊዜ ስለሚሆን ያኔ ኢየሱስ ለሁሉም ፍርድን ይሰጣል ብሉ ባማረባቸው
ነበር፡፡ በሰው አተረጓጎም አንድ ፈራጅ ( ዳኛ ) የፍርድ ውሳኔ
ብቻ ይሰጣል እንጂ ሌላ ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ወይም የአሜሪካን Supreme
court ዳኛ የአቃቤ ሕጉን ክስ፣ የተከሳሹን ምላሽና መከላለከያ
ምስክር፣ የከሳሽን ምስክሮች ቃል ሰምቶና ግራና ቀኙን አዳምጦ ብያኔ ይሰጣል እንጂ ራሱ ዳኛ ራሱ ከሳሽ ወይም ምስክር አይሆንም፡፡
ነገር ግን የክርስቶስን ዳኝነትና ፈራጅነት ከሰው ፈራጅነት ጋር በአንድ
ዓይን መመልከት ስሕተት ነው፡፡ በእግዚአብሔር አስተሳሰብና አደራረግ ግን ሊፈርድ ያለው ኢየሱስ የፈራጅነት
ማዕረግ ያለው ቢሆንም የፍርዱ ጊዜ ገና ስላልደረሰ አሁን አማላጅ ነው፡፡
አማላጅ የሚለው ቃል በሮሜ 8፡34 ላይ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ ለሊቀ ካህናትም ሁሉ
እንደሚያማልድ በዕብ. 7፡ 25 ላይ የተጸፈውን መመልከት ይቻላል፡፡
ኢየሱስ አማላጅ ብቻ ሳይሆን ጠበቃም ነው( 1ኛ ዮሐ. 2፡1)፡፡ ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ለተከሳሹ ከማንም በላይ ወሳኝ ሰው በፍርድ ዳኛ ፊት እርሱን ወክሎ የሚናገር
ጠበቃ የተባለ ሰው ነው፡፡ ስለ የአገሪቱ ሕግ በቂ እውቀት እንዳለው
ተረጋግጦ ፈቃድ የተሰጠውና የመናገር መብትም ብቃትም ያለው ጠበቃ ተከሳሹን ለሞት ከሚያበቃው ወንጀል እንኳ ነጻ ሊያስለቅቅ ይችላል፡፡
የሰውን ልጆች በኃጢአት ምክንያት ከሚደርስበት አስከፊ የሞት ፍርድ
ያስመልጠን ዘንድ ኢየሱስ ጠበቃችን እንደሆነልን ቃሉ በግልጽ ይነግረናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ዕብ. 7፡22 እንደሚናገር ጌታ
ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኗልና ፈራጁ ኢየሱስ ዋስም ነው፡፡ ኢየሱስ ፈራጅ፣ ጠበቃ፣ ዋስ፣ ብቻ ሳይሆን ምስክርም ነው (ዮሐ. 7፡7-8፣
ማቴ. 10፡32)፡፡ ደህንነትና ጽድቅ ለሰው ልጆች የሚገኘው እንዲሁ
በቀላሉ ሳይሆን ኢየሱስ ባሳየው ታላቅ መለኮታዊ ብቃት ነው፡፡ ኢየሱስ
ፈራጅ ስለ መሆኑ ለማስተማር ከተፈለገ ደግሞ ሮሜ 8፡34ን የግድ ከመጠምዘዝ ይልቅ ዮሐ. 5 ፡22-23፣ ያዕ. 5፡9ንና ሌሎች ክፍሎች በቀጥታ መናገር በተቻለ ነበር፡፡ እንግዲህ ቀሲስ ዘበነ ከኢየሱስ
ሌላ አማላጅ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል የሚሉ ከሆነ እንሰማቸዋለን። ግን እንደለመዱት ቃሉን ካላወላገዱ በቀር ከመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ ከየትም ሊያመጡ እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡
ቀሲስ ዘበነ ሲያስረዱ በሮሜ
8: 34 ላይ አማላጅ የሚለውን ቃል የጨመረው ማርቲን ሉተር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚያ የተነሣ ከ1940 ወዲህ የታተሙ እትሞች
በሙሉ አማላጅ የሚለውን ቃል ተጠቀሙ እንጂ የድሮው የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ፈራጅ ይላል፣ መሆን ያለበት ፈራጅ ነው አሉ፡፡ ማርቲን
ሉተር አዲስ ኪዳንን ወደ ጀርመንኛ ተረጎሙት እንጂ ሌላ ትርጉምና ማሻሸያ እንዳላደረጉ ታሪክን መመልከት የተሻለ ነው፡፡ ከላይ የተመለከትናቸውን
እንደ ጠበቃ፣ ዋስ፣ ምስክር ፣ የሚሉትንም የጨመራቸው ማርቲን ሉተር ነው ሊሉን ይሆን? ይህ አባባላቸው
በታሪክም ላይ ከፍተኛ ተፋልሶ እንደሚታይባቸው ያመለክታል፡፡
የግሪኩ መጽሐፍ ሮሜ 8፡34ን
ስለ እኛ የሚፈርደው ኢየሱስ ነው እንደሚል ወይም እንደማይል ወይም
እርሳቸው በግምት ተናግረውም ከሆነ እንደገና ቢመለከቱት የተሻለ ነው፡፡
አሁን የምንጠቀምበት በእጃችን ያለው፣ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተተረጎመው እትም እንደዚህ ይላል፡፡ “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር
ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው?የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ
ኢየሱስ ነው።” የግሪኩ ትርጉም ደግሞ እንደዚህ ይላል፡፡ የሚፈርድ ማነው? ማንም! ለምን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ? ይህ ብቻ አይደለም፣ ተነስቶም በእግዚአብሔር
ቀኝ አለ፡፡ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ስለ እኛ ይማልዳል፡፡” ሁለቱም
ትርጉሞች በሚያስተላልፉት መልእክት ምንም መሠረታዊ ትርጉም ልዩነት የለም፡፡ የሚማልደው የሚለው የግሪኩ ቃል ἐντυγχάνει ነው። ἐντυγχάνω ከሚል ግስ የወጣ ነው። ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን 5 ጊዜ የተጻፈ ሲሆን ከሮሜ 8፥34 የቀሩት ሌሎቹ፣ ሐዋ. 25፥24፤
ሮሜ 8፥27፤ 11፥2፤ እና ዕብ. 7፥25 ናቸው። እነዚህ ቃሎች መፍረድ ይሉና አይሉ እንደሆነ በስፍራቸው ማየቱ የቃሉን ትርጉም
ግልጽ ያደርገዋል።
ወደራሳችን
ቋንቋ ብንመጣ ደግሞ፣ የ1879ኙ የአማርኛ ትርጉም “ያስምረናል”
ወይም “ምሕረት ያስገኝልናል” ይላል፡፡ ሌላው ቢቀር የ1954ቱ
ትርጉም የኦርቶዶክስ እትም ስለ እኛ “የሚማልደው” እንደሚል መምህሩ አላዩትም ይሆናል፡፡ በግዕዝ አዲስ
ኪዳን ወይትዋቀስ
በእንቲአነ ትርጓሜውም “ስለ እኛ የሚዋቀሰው ወይም የሚከራከረው” ይላል፡፡ ቀሲስ ዘበነ እነዚህን እትሞች በደንብ ያዩአቸውና አዲስ
ኪዳን ወደተጸፈበት የመጀመሪያ ግሪክ ትርጉም ሄደው በጥንቃቄ የተመለከቱት አይመስለኝም፣ ያን አድርገው ቢሆን ኖሮ የግሪኩ ቃል ፈራጅ
እንደሚል ባልተናገሩ ነበር፡፡ ግልጽ ያልሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሥረ- መሠረታዊ ትርጉም ለማግኘት ቃሉ ወደተጻፈበት የመጀመሪያ
ቋንቋ መሄድ ግድ ይላል፡፡ ነገር ግን ሊቅ ለመባል የግድ ስለ ግሪኩ
መናገር አያስፈልግም፡፡ ምዕመናኑ እኮ ግሪኩ ምን እንደሚል አንብበውም የሚረዱበት መስመር ገና ስላልተዘረጋላቸው አንብበው በሚረዱት
ቋንቋ የተጻፈውን እትም በተገቢ ሁኔታ በመተርጎም ማስተማር አገልጋዮችን
አላዋቂ የሚያስብላቸው አይመስለኝም፡፡ የግሪኩን ትርጉም ለመመልከት
የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና ግሪኩን ካላወቅነው ደግሞ የሚያውቁትን መጠየቅ አላስፈላጊ ስሕተት ከመፍጠር ያድናል፣ ጠይቆ ከመረዳትም
ደግሞ ብዙ ትምህርት ይገኛል፡፡
ቀሲሱ
ይህን ሁሉ ያስተማሩት ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም ለማለት ነው። በስብከታቸው መጀመሪያ ላይ ካቶሊኮችና
ፕሮቴስታንቶች ኢየሱስን ሁለት ባሕርይ እንደሚሉትና እነርሱ ግን አንድ ባሕርይ እንደሚሉት በጨረፍታ ብቻ ተናግረው ነበር። ይህንን
ዋና ትምህርት ቢያስተምሩት ኖሮ የአስተምህሮአቸው ምንነት ጎልቶ ይገለጥ ነበር፤ ግን ጨርሶውኑ አላነሡትም። ይህ ተነሥቶ ቢሆን ኖሮ
በተዋሕዶ አስተምህሮ እንዴት የኢየሱስ ሰብዓዊ ባሕርይ በመለኮታዊው ባሕርይ ተውጦ ተዋሕዶ መሆኑን ሊያስረዱ መሞከር ይሆንላቸው ነበር።
በነገራችን ላይ ይህ የተዋሕዶ (monophysite ወይም miaphysite) ትምህርት
በ451 ዓ. ም. በኬልቄዶን ጉባኤ የተረጋገጠውን የእምነት መግለጫ የተቃወመ ቡድን ነው።
መምህሩ ሮሜ 8፡26ን፣ ሮሜ
8፡34ን እና ኤር. 7፡25ን ካነበቡና ካስነበቡ በኋላ አንድ ጥያቄ ጠየቁ፡፡ “አማላጅ ማን ነው? ወልድ ወይስ አብ ወይስ መንፈስ
ቅዱስ?” አሉ፡፡ ለዚያ መልስ ሳይሰጡ አድበስብሰው አለፉ፡፡ ክፍሎቹን ማንበባቸው መልካም ነው፡፡ ሸፋፍነው ማለፋቸው ግን የጥሩ አስተማሪ ሥራ አይደለም፡፡ እንግዲያው እኛ እንመልስ፡፡ ሮሜ 8፡34 መሠረት አማላጃችን ክርስቶስ ሲሆን በሮሜ
8፡26 መሠረት በድካማችን ሁሉ እያገዘን በጸሎታችን ጊዜ እየቃተተ ስለ እኛ የሚማልደው ጌታ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በኤር. 7፡25
መሠረት ደግሞ በዘመኑ ለነበሩ የእሥራኤል ልጆች ነቢያት ለመላክ የማለደው እግዚአብሔር አብ ነው፡፡ ቀሲሱ ኤር. 7፡ 25ን አሳብ ከክርስቶስ የምልጃ አገልግሎት ጋር ለምን እንዳያያዙት ባይታወቅም ክፍሉ የእግዚአብሔርን
አማላጅነት ሳይሆን እርሱ በጠዋት ማልዶ ስለመነሳቱ የሚነግረን አሳብ
ነውና ቀሲስ ዘበነ እንደገና ሊመለከቱት ይገባቸዋል፡፡ በቃሉ የተቀመጠው መሠረታዊ ትምህርት ይህ ነው፡፡ ይህም ቢሆን አማላጅ ማነው
ብለው ራሳቸው ጠይቀው ሳይመልሱ ያለፉትን ጥያቄ እንዲመልሱልን እንደገና
እንጠይቃቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ እንደሚያስተምረን ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ አይደለም ከተባለ ታዲያ አማላጁ ማን
ነው? ቀሲሱ እነዚህ ሦስት ክፍሎች ማስነበባበቸው ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ፥ እግዚአብሔር አማላጅ ናቸው፤ ሁሉም አማላጅ ናቸው
ብሎ ለማፋለስ ቢመስልም የባሰ የራሳቸውን ትምህርት አወሳሰቡት እንጂ ሰሚዎቹን አልረዱም። በኤር. 7፥25 የተጻፈው መማለድ እንጂ
ማማለድ አለመሆኑ እንዴት እንደጠፋቸው የሚያሳዝን ቢሆንም መንፈስ ቅዱስና ኢየሱስ ይልቅስ በተጨማሪ የመንፈስ ቅዱስን የማማለድ ሥራ ያሳያል እንጂ ማማለዳቸው
የኢየሱስን አለማማለድ ወይም ፈራጅ ብቻ መሆን አያሳይም።
ቀሲስ ዘበነ ፕሮቴስታንትን እንዲቋቋሙ ለምዕመናን የሰጡት የቤት ሥራ የሥላሴን ትምህርት
ከሥሩ መንግሎ የሚጥል ነው፡፡ በሥላሴያውያን (ቲሪኒቴሪያን) ወይም በሥላሴ አንድነትነና ሦስትነት በሚያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ አንድ አምላክ ሲሆን ይህ አንዱ አምላክ በሦስት አካላት ተገልጧል፡፡ አንዱ አምላክ ሦስቱ
ሥላሴ እንለዋለን፡፡ የሥላሴ አካላት ሦስት ሲሆኑ እነርሱም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ አንድነታቸው በመለኮትነታቸው ሲሆን
ሦስትነታቸው ደግሞ በስምና በአካል ነው፡፡ አብ ወልድ አይደለም፣ መንፈስ ቅዱስም አይደለም፡፡ ወልድም አብ አይደለም መንፈስ ቅዱስም
አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወልድ አይደለም አብም አይደለም፡፡ ነገር ግን አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ነው፡፡ የሥላሴን ሦስትነት የሚያስተምረን ዘመን የማይሽረው ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔር
ቃል ነው፡፡ የአርዮሳውያንና ፣ የሰባልዮሳውያን ትምህርቶች (ከሌሎቹ ይልቅ እነዚህ ሁለቱ በአገራችን በስፋት ስላሉ እነርሱን ብቻ አነሳሁ እንጂ
ሌሎችም የስሕተት ትምህርች አሉ) ከትሪኒቴሪያን የተለየ
አቋም ያላቸው በጣም አደገኛው ኑፋቄዎች ናቸው ፡፡ አርዮሳውያን አምላክ አብ ብቻ ነው ሲሉ ፣ ሰባልዮሳውያን ደግሞ በሦስት ገጽታ ያስቀምጡታል፡፡ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን አብ ነበር ፣ ከዚያ ሥጋ
ለብሶ ወልድ ሆኖ ወደ ምድር መጣ፣ ከዚያ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋሱን በሰው ውስጥ ያደረው አንዱ ኢየሱስ ነው እርሱ
አብም ወልድም ነውና አምላክ ማለት ኢየሱስ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ የቀሲስ
ዘበነ ትምህርት ከሰባልዮሳውያን ትምህርት ጋር የሚዛመድ ነው፡፡ ቀሲሱ እኔና አብ አንድ ነን ብሎ ኢየሱስ የተናገረውን ቃል ይዘው ኢየሱስ አምላክ ነው አብም አምላክ
ስለሆነ በሁለቱ ምንም ልዩነት የለም አብና ወልድ ሁለት አይደሉም ይላሉ፡፡ ይህ ከእውነተኛው የትሪኒቴሪያን ትምህርት ውጭ ነው፡፡
ስብከታቸው ከእግዚአብሔር ቃል አስተምህሮ የራቀ ፍጹም የተሳሳተ በመሆኑ ወይ እርሳቸው እንዲያርሙት ካልሆነ ምዕመናን እንዲጠነቀቁ
ይገባቸዋል፡፡
በዚህ ሳያበቁ ቀሲሱሩ የሽርከታ
ትርጉማቸውን ቀጠሉበት፡፡ በዮሐ. 14፡6 ላይ ኢየሱስ እኔ መንገድ እውነት ሕይወትም ነኝ ፣ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ሲተነትኑ ቀሲሱ እንዲህ አሉ፡ “በዚህ ምድር ሳለሁ የሠራሁትን ሥራ የሚሠራ ሰው፣ ትህትናን ያሳየ ፣ ቸርነትን ያሳየ ፣ ሲተፉበት ዝም ያለ፣ ሲሰድቡት ዝም ያለ፣ ሲሰቅሉት እነርሱን ማራቸውያለ፣ ይህንን የሚያደርግ ሰው
ወደ አባቴ ዙፋን ይነጠቃል ወይም ይወሰዳል፡፡ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ማለት ይሄ ነው አሉ፡፡” ይህ የእርሳቸው የግላቸው ትርጉም እንጂ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን ትምህርት
አያውቁትም፡፡ ያ እጅግ በጣም ጥሩ ሥነ ምግባር ቢሆንም ብቻውን ግን ወደ ደህንነት የሚያደርስ ባለመሆኑ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና ማንም እንዳይመካ
በሥራ አይደለም ብሏል (ኤፌ. 2፡8-10፣ ሰው ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን
፣ እኛም ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ
ኢየሱስ አምነናል ገላ. 2፡16 ) ይላል፡፡ ታዲያ ይህንን የት ሊያደርጉት
ነው?
ሌላ ቀሲሱ በታሪክ ላይም ያሳዩት
ተፋልሶ እንመልከት፡፡ የማርቲን ሉተርና የባለቤቱን ግንኙነት አስመልከቶ
የተናገሩት በእግዚአብሔርን ቃል ሲተረጉሙት እንዳሳሳቱት ያህል የክርስትና ትምህርታችንን ይጎድፈዋል ብለን ባናምንም ታሪኩን አስተካክለው አልተናገሩትምና ማሻሸያ ያስፈልገዋል፡፡ በመሠረቱ ማርቲን
ሉተርና ካትሪና በገዳም ውስጥ ተገናኙ የተባለውም ቢሆን ከታሪኩ እውነታ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ ማርቲን ሉተር ካቲሪናን ያገባት
መነኩሴ ሆኖ ወደ ገዳም በመጣበት ሳይሆን እርሷ ራሷ ከገዳም አምልጣ በመውጣት ነበር፡፡ ካትሪና ሕጻን ሳለች እናቷ ስትሞት አባቷ ሌላ ሚስት በማግባቱ ምክንያት
ገና በአራት ዓመቷ ወደ ሴቶች ገዳም ተወስዳ እዚያው ማንበብና መጸፍ እየተለማመደች እያለ እድሜዋ 16 ዓመት ሲሆናት የመነኩሴነት
መሃላ እንድትፈጽም በመገደድዋ ሳትወደው አደረገችው እንጂ መምህሩ እንደሚሉት የመነኮሰችው ቀብጣ አልነበረም፡፡ አባቷ ወደ ቤት እንድትመጣ ስለማይፈልግ ሌላ ምርጫ ስላልነበራት በገዳም ቆየች፡፡ ይሁን እንጂ በዊተንቤርግ የካቶሊክ መነኩሴ በነበረው ማርቲን ሉተር አማካይነት እየተከናወነ ስለነበረው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ስለሰማች አንድ ቀን ከገዳሙ ወጥታ ያንን
እንቅስቃሴ የምትቀላቀልበትን አጋጣሚ ስትናፍቅ ነበር፡፡ ምንኩስና ሰላም ያጣችበትና ያለ ምርጫዋ የገባችበት ሕይወት ስለነበረ እንደ እርስዋ ያለምርጫቸው
ከገቡ 11 ወጣት ሴቶች ጋር በዓሣ ነጋዴዎች ጋሪ ውስጥ ተደብቃ ከገዳሙ አመለጠች፡፡ ይህን ድርጊቷን መምህር ዘበነ ቆብ የቀደደች ከሃዲ ቢሉም የወሰደችው ትክክለኛ እርምጃ ነበር፡፡ ምክንያቱም
የገዳም ሕይወት ለ5 ዓመት ልጅ ምን ያህል የስቃይ ሥፍራ ሊሆን እንደሚችል
ማንም ኅሊና ያለው ሰው ይገባዋል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ የራሳቸውን ሕይወት በራሳቸው መወሰን ባልቻሉ እንደ ካትሪና ባሉ ሕጻናት ላይ ብቻ ሳይሆን በማንም አእምሮ
እንደዚያ ዓይነት ድርጊት መጫን ከአጋንንታዊ ትምህርት የመነጨ መሆኑን ሐዋሪያው ጳውሎስ በ1ኛ ጢሞ. 4፡1-4 ድረስ እንዲህ ሲል
ይገልጸዋል “መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት
የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥እነዚህ ውሸተኞች
መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ።” በተለይም ደግሞ ሕጻናትን ከእንዲህ ዓይነት ሕይወት
ነጥቆ ማውጣትና እንደ ሰው ተገቢውን ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ እንደ መምህር ዘበነ ያሉ የሃይማኖት መምህራንና የቅዱሳት መጻሕፍት
አዋቂዎች ኃላፊነት ሆኖ ሳለ ጭራሽ ከዚያ ሕይወት የሚወጡትን የሚኮንኑ ሆነው መገኘታቸው ለጽድቅ ብለው ይሁን ለመረቅ አይታወቅም፡፡
ካትሪና ሉተርን ማግባቷ እውነት
ነው፡፡ ግን ወዲያው ሳይሆን ከገዳም ከወጡ በኋላ ማርቲን ሉተርና ሌሎች የተሐድሶ አጋሮቹ ካትሪናና ሌሎች ከገዳሙ ያመለጡ ልጃገረዶችን ክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ እንክብካቤ እያገኙ እንዲቆዩ ሲያደርጉ ካትሪና ለሁለት ዓመት ፊሊፕ ራይሸንባኽ በተባለው ሰው ቤተ ሰብ ውስጥ የቤት አያያዝ ትምህርት ተማረች፡፡ መምህር ዘበነ እንደሚሉት ሳይሆን ካትሪናና ማርቲን ሉተር የተጋቡት እርሷ ከገዳም ከወጣች ከብዙ ዓመታት በኋላ እድሜዋ 26 ዓመት ሲሆናት ማርቲን ሉተርም የ42 ዓመት
ከሆነው በኋላ ነበር፡፡ መምህር ዘበነ ግን በገዳም ውስጥ ተገናኝተው ሁለቱም ቆብ የቀደዱ ከሀዲዎች ናቸው የሚለው አሳብ ለማጥላላትና ለማንቋሸሽ ብቻ ካልሆነ በቀር ከየት እንደቀዱት በእውነቱ ግልጽ አይደለም፡፡ በቀሲሱ ትምህርት ምዕመናን ግራ ሳይጋቡ እንደማይቀሩ ግልጽ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ምሕረት ያብዛላቸው፡፡ በድፍረታቸውም የሰማይ አምላክ ይቅር ይበላቸው ፣ ልቦናንም ይስጣቸው፡፡
ስንጠቀልለው ቀሲስ ዘበነ አስተምህሮተ- ክርስቶስንም ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ሥነ ፈታትንም ሆነ ታሪክን
ያፋለሱት እስከ አሁን ባየናቸው ጉዳዮች ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች አሉ፡፡ ነገር ግን ለዛሬው እዚህ ላይ እናብቃና
በቀጣዩ እንመለስበታለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከላይ በተነሱት
ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስንሰብክ ራሳችንን ወይም ያለንበትን ቤተ እምነት ሳይሆን የክርስቶስን ማንነትና የቃሉን
እውነተኛነት እየሰበክን የሚመጣውን ጌታ እንጠብቅ፡፡ እርሱ ያኔ የአገልግሎታችንና የድካማችን ዋጋ ይሰጠናልና፡፡ የአምላካችን ሰላም
ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን
[1] ፍልውኃ ያሉት መምህሩ ራሳቸው ሲሆኑ የጥፋት ውኃ ለማለት
ፈልገው ይሆናል፡፡ በፍልውኃና በጥፋት ውኃ መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ የሰው ጥፋት በምድር ከመብዛቱ
የተነሳ እግዚአብሔር ሥጋ የለበውን ሁሉ ከምድር ለማጥፋት ሲል የላከው የጥፋት ውኃ በመባል ይታወቃል፡፡ ዘፍ. 7፡6-7 ላይ በማያሻማ
ሁኔታ የጥፋት ውኃ በሚል ተቀምጧል፡፡