Wednesday, March 25, 2015

የፓስተሩ በወሲብ መፈተንና የአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ እወጃ

የአደጋውን መንስኤ ካወቅን ጉዳተኞችን እናድናቸው
የምንኖርባት ምድር በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎችን እንደምታስተናግድ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በየብስ የሚሽከረከሩ፣በባሕር ላይ የሚጓዙና በአየር የሚበሩ መጓጓዣዎች አንዴ በሚከሰትባቸው አደጋ ከፍተኛ የሕይወትና የንብረት ውድመት ይደርስባቸዋል፡፡ አንድ አደጋ ሲከሰት ኃላፊነት የሚመለከታቸው አካላት አደጋው የተከሰበትን ጊዜ፣ ቦታ፣ የደረሰውን አካላዊና ቁሳዊ ጉዳት፣ የአደጋውን መንስኤዎችና ወዘተ ይመረምራሉ፡፡ በሥራ ላይም ሆነ በሰው ሆን ተብሎ በሚደረጉ ወንጀሎች ምክንያት በተከሰተው አደጋ የጠፋውን ንብረት ፣ የአደጋውን ሁኔታ፣ ወዘተ ከመተንተን ይልቅ ቢቻል አደጋው እንዳይከሰት ማድረግ ለሁሉም ዋስትና ሊሰጥ እንደሚችል የሚታመን ነው፡፡ ግን እንዲህ አይነቱ በራሱ የሚቻል አይደለም፡፡ ለምሳሌ የመኪና አደጋ መከላከያ የለውም፡፡ አውሮፕላን እንዳይከሰከስ የሚያደርግ መከላከያ የለም፡፡ ከአዳገው የተረፉትንና የተጎዱትን መርዳት ግን ከምንም ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡
ይህንን አሳብ ያነሳሁት ስለ ሰው ሠራሽና ተፍሮአዊ አደጋ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ሳይሆን ቤተክርስቲያናችን እየደረሰባት ስላለው መንፈሳዊ አደጋ ትንሽ ለማውጋት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተከርስቲያን በትልቅ አደጋ እየተመታች መሆኑዋን አላወቅሁም የሚል ካለ ከባድ እንቅልፍ አሽልቦታል፣ ወይም ከነአካተው በሞት ጣር ውስጥ ነው ያለው፡፡ እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ቤተ ክርስቲያናችንን አደጋ እያጠቃት እንደሆነ ካላወቅን በአደጋው ምክንያት ሁሉም ነገር ወደ ፈርስራሽ እስክለውጥ ሊገባን አይችልም፡፡ ዋና ትኩረቴ ይህ ሁሉም ሳይሆን በቅርቡ በራሳቸውና በሰው ትዳር ላይ መማገጣቸው በአሜሪካን ድምፅ ራዲዮ ከተነገረ በኋላ የኢትዮጵያውያን ልብ የሰበረ ወገኖቻችን ጉዳይ መነሻ በማድረግ የተደቀነብንን የውድቀት አደጋ ለመጠቆም ነው፡፡ የማናውቀውን አዲስ ነገረ- ጉዳይ ማውሳቴ አይደለም ግን እንደገና እንድናስብበት ብዬ ነው፡፡ ይህንን አደጋ ያልኩበት ምክንያት ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ እንግዳ ነገር በድንገት ስለ ወደቀብን ሳይሆን በየጓዳው እግዚአብሔር የመጠቀምባቸው አገልጋዮችን እየጠለፈ የሚጥል የኃጢአት ገመድ መጠኑን እየጨመረና ባሕሪዩን እየለዋወጠ ስለሚሄድ ነው፡፡ ሰዎች በኃጢአት ሲወድቁ ያለ ልክ የሚኮንኑና ያለገደብም የሚያበረታቱ የጽንፈኞች ተግባር የባሰ ሌላ አደጋ የሚጨምርብን ሆኖ ስለታየኝም ነው፡፡
ፓስተር ዘማሪ ተከስተ ጌትነት ቢያንስ ሁለት ሀይማኖታዊ ማዕረጎችን የደረበ፣ ከኢትዮጵያ ተነስቶ በዓለም ዙሪያ ባሉ አህጉራት ባልሳሳት ደቡብ አፍሪካ ፣በአውሮጳና አሜሪካ አገሮች ተዘዋውሮ በዝማሬ ኢትዮጵውያንን ያገለገለ ታዋቂ አገልጋይ ነው፡፡ ይህ አገልጋይ አንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያንን በተሰጠው የዝማሬ አገልግሎት እየጠቀመ ይገኛል፡፡ ይህ እንዲህ ሆኖ ሳለ አንዳንዶቻችን የእዚህን አገልጋይ በዝሙት ኃጢአት መውደቅ ከአሜሪካን ራዲዮ የሰማነው እየጎመዘዘንና እየተናነቀን ነው፡፡ እውነት ለመናገር የራዲዮ እወጃውን ከሰማን በኋላ የምንለውም የምናደርገውም ጠፍቶን ምድር የዞረችብንም ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ጆሮአችንን ማመን አቅቶን ጭራሽ ሰውነታችን ተሟገተብን፡፡ “ይህ የጌታ ባሪያ ይህን አያደርግም ፣ እሬ ምን ቆረጠውና እንዲህ ያለ ነገር….. በኢየሱስ ስም የጠላት ወሬ ነው”፣ብለን ራሳችንን ለማሳመን ብንሞክርም ነገሩ እኛ ወደ ምንጎትተው አቅጣጫ ሊጎተትልን ሳይችል ቀረ፡፡
አንዳንድ “ምን አለበት ታዲያ የማይወድቅ ሰው አለ እንድዬ? ዳዊት ወድቆ የለም ወይ? የገለሞታ መንፈስ የደሊላ መንፈስ ተዋጋው እግዚአብሔር ይገስጸው” የሚሉ በርካታዎች መኖራቸውም ታይቷል፡፡ እነዚህን አደጋ ሲከሰት አስፈላጊው ርዳታ መደረግ የለበትም፣ የተጎዱትም ባወጣቸው ይውጡ፣ሌላም አስፈለጊ ጥንቃቄ ማድረግ አይገባም የሚሉ ዓይነት አድርጌ አወስዳቸዋለሁ፡፡ አገልጋይ በኃጢአት ሊወድቅ እንደሚችል የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ነው ሐዋሪያው ጳውሎስ ፓስተር ጢሞቴዎስን ከኃጢአት እንዲሸሽ የመከረው(1ጢሞ.6፡11)፡፡ ካልሸሸ ተጠልፎ እንደማይወድቅ ምንም ዋስትና የለውምና፡፡ አገልጋዮች ተሠርተን ያለቅን አይደለንም( ፓስተር ኃይሉ ቸርነት)፡፡ ዳዊትም የወደቀውና የእግዚአብሔርን ቅጣት የተቀበለው ስላልሸሸ ነው፡፡ ቃሉም የሚነግረን ከዳዊት ውድቀትና መቀጣት ተምረን እንድንጠነቀቅ እንጂ ኃጢአትን እንድንለማመደው አይደለም፡፡ የገለሞታና የደሊላ መንፈስ የሚባለውም ቢሆን ተመዝኖ የቀለለ አጉል ቃላተ- ቋጥኝ(jargon) ነው፡፡ ተከስተን ስለወደድነው የደሊላ መንፈስ ወይም የጋለሞታ መንፈስ ተዋጋው ካልን ከእርሱ ጋር ያመነዘረቺውን ሴትና ትዳሩዋን የሚወዱ ደግሞ ምን ሊሉ ነው? ”እህታችንን የአመንዝራ መንፈስ ተዋጋት እግዚአብሔር የምታው” ብሉ ተሳሳቱ እንል ይሆን? ሁለቱም የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው ሳለ በትዳራቸው ላይ ያማገጡ ደፋሮች አይደሉምን? ስለዚህ ታዋቂ ዘማሪና ፓሰተር የሆነውን ወንድማችንን አይዞህ ካልን በቃል ኪዳን ያገባት ሚስቱ ምን ትሁን? ስለ እርሷስ ምን ተሰምቶናል ወይስ የትዳር ጉዳይ ከመድረክ አገልግሎት የበለጠ ዋጋ እንደሚሰጠው ጠፍቶብን ነው?
እግዚአብሔር ምሕረትና ጥንቃቄውን ያድርግ እንጂ ዘማሪ ፓሰተር ተከስተ በፈጸመው ድርጊት የአቶ መላኩ የሺዳኛ ቤት እንዳይፈርስ ምን መተማመኛ አለን? ያንን ቤትና ትዳር ከተከስተ አገልገሎት እኩል ማየት ከተሳነን የአንድ ወገን ቲፎዞዎች ብቻ ያስመስለናል፡፡ እኛስ እንዲያው ስለዚያ ቤተሰብ አስበን ካልጸለይንና ተከስተ በመዝሙር ስላስደሰተን ብቻ አይዞህ የምንል ከሆነ ፍቅራችን እውነተኛው የክርስቶስ የመስቀሉ ፍቅር ለመሆኑ እንዴት እርግጠኛ እንሆናለን? ወንድማችንን አሰናከለቺው ማለትስ ተገቢ ነው? እርሱስ አላሰናከላትምን? ቢያንስ እኮ እንደ ፓስተርነቱ ለሕይወቷ መጠንቀቅና ሊያስተምራት በተገባው ነበር፡፡ ከዋሽንግተ ዲሲ ወደ ሜኒሶታ የሄደው፣ እርሱ በራሱም ምኞት ተስቦ ወይስ ሴትዮዋ አሰናክላው ነው? በሜኒሶታ ሆና በዲሲ አገልግሎት ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ሰው ልታሰናክል እንደምትችል የሚታሰበው በምን መለኪያ ነው? ከዚህ ሁሉ ይልቅ የወደቀውን የሚያነሳ የምሕረት አምላክ የሆነውን እግዚአብሔርን ስለ ሁሉም ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አገልጋያችን የበደውን ትዳርና የትዳር አጋሮችን፣ የሚያገለግውን ሕዝብ ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግልጽ ይቅርታ እንዲጠይቅና እንዲታደስ ማድረግ የእውነተኞች ወዳጆች ተግባር እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ዘማሪ ፓስተር ተከስተ ያደረገው ይህንን በመሆኑ ከአድናቂዎቹ ይልቅ እግዚአብሔር ይባርክህ መባል ያለበት እርሱ ነው፡፡ ምክንያቱም “ከአገልግሎት ሪቄ ራሴን እያሰታመምኩ ነኝ፣ለሆነው ነገር ሁሉ አቶ መላኩን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ፣ በሁኔታዎች ራሴን መግታት ነበረብኛና ያ ባለመሆኑ በመጀመሪያ እግዚአብሔርን በድለናል ቀጥሎም አቶ መላኩን፣ጥፋት ጥፋት ነውና እኔ ጥፋቱን እቀበለላሁ ይቅርታ ልጠይቀው እፈልጋለሁ” ማለቱን የቮኦኤ ጋዜጤኛ ራሱ መስከሮአል፡፡ አቶ መላኩ ራሳቸውም ቢሆኑ ተከስተ ድርጊቱን እንደፈጸመው ማመኑንና ይቅርታም መጠየቁን በይፋ መስክረውለታል፡፡ ይህ ከአንድ እውነተኛ የንስሐ ልብ ካለው አገልጋይ የሚጠበቅ ተግባር ነውና ምንም እንኳ የንስሐውን ፍሬ ፈጥነን ባናየውም ቢያንስ ጎሽ እደግ እንድንለው ይህ በቂ ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔርም እንደገና በገናውን አንስቶ ቅኔውን የሚቀኝበትና በአዲስ ጉልበት የሚቆሚበትን አቅም ይሰጠዋል ብለን እናምናለን፡፡ የጸጋ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ሽማገሌ ለቪኦኤ የሰጠው ምስክርነት ወንድማችን ተከስተ አውነተኛ የንስሀ ልብ እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ በራሱ ተነሳሽነት የትዳር ጓደኛውን፣ የሚያገልግልበትን ማህበረ ምዕመናንንና እንዲሁም ሌሎች በዚህ የተጎዱትን ሁሉ ይቅርታ መጠየቁንና ራሱን በራሱ ከአገልግሎት አግልሎ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን የሚያይበትን ጊዜ እየወሰደ መሆኑን ስንሰማ በእውነት ልባችን አርፏል፡፡
ሌሎች ደግሞ አይዞህ ተኬ እንወድለን ወዘተ የሚል በፌስ ቡክና በሌሎች ማበራዊ ገጾች ፎቶ በመለጠፍ ስሜታቸውን የገለጡም አልታጡም፡፡ እነዚህ ደግሞ ምንም ብታደርግ ከጎንህ ነንና አታስብ የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ይህ ፍቅር ይሉት ጥፋት፣እልህ ይሁን ሌላ አይታወቅም፡፡ ታዲያ ይህን ወንድም አይዞህ ብለን ብቻ ማለፍ ፍቅር ነው? ካልንም ስለ ወንድማዊ ፍቅር ገና እንግዶች ያስብለናል፡፡ እነዚህ ወገኖች ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና ዶር ቶሎሳ ጉዲና በአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ አሳብ እንዲሰጡ የተደረገው ዓይነት እድል ቢያገኙ ምላሻቸው ምን ይሆን ነበር? ተከስተን እንወደዋለን ምንም ችግር የለበትም ብለው ሁሉንም ነገር ሊያበላሹብንና ገደል ሊከቱብን እንደሚችሉ አያያዛቸው ይመሰክራል፡፡ ፍቅራቸው መሬት ያልረገጠና ቅዱስ ቃሉና መንፈሱ የማያውቁት መሆኑን ድርጊተ- ሥራቸው ያሳያል፡፡ አንደኛ ነገር ፣ ይህ ሰው ንስሐ እንዲገባና ከመንገዱ እንዲመለስ አንድም የወንድማዊ ምክር ቃል አልሰጡትም፡፡ ሁለተኛ ፣የሰውን ሚስት ያማገጠ ፓስተር ፎቶ ከራሳቸው ፎቶ ጋር አድርገው እየለጠፉ የጅላጅል ጨዋታቸውን ሲንቦጫረቁበት አልከለከላቸውምና ፌስ ቡክ የሥራውን ይስጠው፡፡
የእግዚአብሔር የትዕግሥቱ ጽዋ ሞልቶ ወይዘሮ ሆሳዕና አዳዳ ለአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ አሳወቀችና ጉዳዩ የማይሸሸግና የማይታፈን ሆነ እንጂ ሌሎችም የተደበቁ ነገሮች አይኖሩም ማለት እንችላለን? ድርጊቱ እኮ የለመደ ሰው ሥራ ይመስላል፡፡ ሥር የሰደደ ልምምድስ ያለው ባይሆን ከሴትዮዋ ጋር በተኛባቸው ቀናት የጠጣው መጠጥ በአገሩ እያለ የሚያውቀው ነበር እንዴ? በእንዲህ ዓይነቱ አነቃቂና አስካሪ አልኮል መራጨት ከጀመረ ምን ያህል ጊዜው ይሆን? የቆሎ ተማሪ፣ ደበሎ ለባሽ ሲባል የነበረ በጌታ ምክንያት ክብር ቢያገኝና በቅዱሳን መባና አሥራት የሚሰፈርለትን ቀለብ ለዝሙት ተግባሩ አልቤርጎ ይከራይበታል፣ የወሲብ ማነሳሻ መጠጥ ይሸምትበታል፡፡ ተሳሳተ፣ ሰይጣንም ተዋጋው ከምንለው ያለፈ መሆኑን ሳንዘነጋ ከጎንህ ነን ማለቱን ትንሽ ቀዝቀዝ እናድርገው፡፡ ይልቁንም የተጀመረው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሽምግልና ወንድማችን እንዲታደስ ይረዳዋልና ብዙም አንፍረድበት እንጸልይለት እንጂ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰይጣን ሲያሰናክልንም ሆነ እኛው በምኞታችን ተስበን ስንወድቅ ሳይቀጣን አያልፍም፣ እንደ ተከስተ በእውነት ስንመለስ ግን ወሰን በሌለው ምሕረቱ ይምረናልና በእርሱ ብቻ እንታመን፡፡
ተከስተ በዚህ ኃጢአት ስለወደቀ ብቻ አብቅቶለታል፣የክርስትናውና የአገልግሎቱ ነገር በአራት ነጥብ ተደምድሟል ብንል ትልቅ ስህተት ይሆንብናል፡፡ እግዚአብሔር የምህረት አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርሰቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ሊያነጻ የታመነ፣ የወደቁትንም የሚያነሳ ሩህሩህ አምላክ ነውና፡፡ በዝሙት ኃጢአት አገልጋዮች ማለትም ፓስተር፣ ዘማሪ ፣ ወንጌላዊ ፣ቄስ ሲወድቅ ተከስተ ጌትነት በዚህ ምድር የመጀመሪያው ሰው አይደለም፡፡ ብዙዎች ወድቀው ከወደቁበትም በእግዚአብሔር ምሕረት ምክንያት ተነስተው ፣ እንደገና የእግዚአብሔርን ጸጋ ተቀብለው የሕይወትና የአገልግሎት ሩጫቸውን እየሮጡ እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ግን ታዲያ ይህን የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲቀበሉ በእውነተና ንስሐ ወደፊቱ እንዲቀርቡ ከማበረታታት ይልቅ በየፌስ ቡኩ አይዞህ እንወድሃለን መባባል ምን የሚሉት ነው?
የወንድማችንን የተከስተ ጌትነትን ስህተት የመላው ፕሮቴስታንት አማኞች ውድቀት አድርገው ሁሉን በገፍና በጅምላ የሚያብጠለጥሉም አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ የአንድ ወይም የሁለት ሰው ውድቀት የመላው ቤተ እምነት እንዳይደለ ወይም ተከስተ ጌትነት ከዲሲ በአይሮፕላን ተሳፍሮ ሜኒሶታ የሄደው የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማስፈፃም ሳይሆን ከወይዘሮ ሆሳዕና ጋር የዝሙት ፍላጎቱን እውን ለማድረግ እንደሆነ አላሰቡበትም፡፡ የኃጢአት ፈተና ማንንም የማይለይ እንዲያውም ሰይጣን በአገልግሎት የሚታወቁትን እየጠለፈ በመጣል ምዕመናንን የሚያሳቅቅበት መሣሪያው ዝሙት እንደሆነ ማወቅ ለምን እንደተሳናቸው ግልጽ አይደለም፡፡ የሰውን ትዳር አበላሸ፣ ይኼው አስነወራአት በማለት በወደቀ ዛፍ የምሳር ብዛት እንደሚሉት በወንድማችን ላይ የስድብ ሩምታ የሚያዘንቡ የአሸዋ ያህል ናቸው፡፡ በቤታቸው እንግዳ ሲጋብዙ በተለይም በእንግዶች መካከል የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ከተገኘበትማ ሆን ብለው የአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ ያደረገውን ቃለ ምልልስ የሚከፍቱ ይኼውና ጴንጤዎች እንደዚህ ናቸው በሚል ጥቂት አይደሉም፡፡
በዚህ ውድቀት ምክንያት አንጀቱ የራሰው ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር አዝኗል፣ ቅዱሳን ደንግጠዋል፣ በቃል ኪዳን የቆመው ትዳር ተጎድቷል፣ በኃጢአት የወደቁ ወገኖቻችንም ልብ በመንፈስ ቅዱስ ወቀሳና በህሊና ክስ መሰቃየቱና አንገታቸው መሰበሩ አልቀረም፡፡ ተከስተ ጌትነት ጌታ ኢየሱስን ለመከተል ሲወስን ዘማሪ እሆናለሁ ብሎ ሳይሆን የዘላለምን ሕይወት አገኛለሁ በሚል ነው፡፡ የመረጠው ጌታ ጨምሮ የወንጌሉ አገልጋይ አድርጎ በመቀባት በሕዝቡ ፊት ገለጠው እንጂ፡፡ አገልጋዮቻችን በሕይወትና በኑሮአቸው ከምዕመናን በልጠውና ተሽለው መገኘት ስላለባቸው የወቀሳውና የሀይማታዊ ቅጣቱ ደረጃ ጠንከር ይል ይሆናል እንጂ በተከሰተው ነገር የጥፋተኛነቱን ክብደት የምናሸክመው ሁሉንም ነው፡፡ ዘማሪውን ብቻ መግቢያ መድረሻውን አሳጥተን የምናበቃው አይደለም፡፡
እውነት ለመናገር እህታችን ሆሳዕና አደዳም ብትሆን እንዲያው እሾክ አይውጋሽ የምንላት አይደለችም፡፡ እርሷም ለዚህ ውድቀት የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ እርሰዋ ብቻ እንደተደፈረች አድርገው የሚናገሩ ወገኖች ምነው ቆም ብሉና ቢያስቡስ ? የስልክ ጥሪውን ከተቀበለች በኋላ ባለቤቷ በሌለበት ምሽት ወንድ ወደተከራየው አልቤርጎ መሄዷ ምን ቢያምራት ነው ብለው ለምን አይጠየቁም? እሺ የመጀመሪያውን ቀን ምናልባት ስላልተጠራጠረች ሄደች እንበል፡፡ ሁለተኛ ቀን ወንድን ለወስብ በሚያነሳሳ መልኩ ልብሷን ቀይራ ያውም የትላንትናውን ያላማረ አቀራራቡን ካስተዋለች በኋላ ተመልሳ መሄዷ ከወቀሳ ነጻ የሚያስለቅቃት በየትኛው ፍርድ ይሆን? ለሰው ሁሉ የማይታይና ማንም እንደፈለገው የማይነካካው የሰውነታችን ክፍሎች አሉ፡፡ ጡት፣ ዳሌ፣ ደረት፣ ከንፈር ወዘተ በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው የሰውነት ክፍሎች ሲሆኑ በተለይም ላገቡት ከትዳር ጓደኛቸው በስተቀር ሌላ እንደዚህ ያሉ የአካል ክፍሎችን እንዲያየቸውም እንዲነካቸውም አይፈቀድም፡፡ ለላጤዎች የተፈቀደ ነው ማለቴ እንዳይደለም ያዙልኝ፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ጡቷን ፎቶ ላንሳ ሲል ደረቷን ገልጣ ማሳየቷና መፍቀደዋ ምትሆነውን ብያሳጣት ነው አያስብልምን? በዚያው ላይ ደግሞ የጓደኛዬ ባል ስለሆነ ልጠይቀው ብዬ ነው አለች፡፡ በዚህ ምክንያት ጠያቂ አያሳጣሽ ብትባልም የጓደኛዋን ባል ነድፋ በመጣልዋ ግን አላበጀሽም ለማለት ምነው የማይደረስ የወንጭፍ ያልህ ሩቅ የሆነባቸው? ደግሞ በጉዳዩ ጨርሶ የሌለበትን ዘማሪ ሳሙኤል ተክለማርያምን በመላው ክርስቲያን አፍ እንዲገባ መድረጓስ በእግዚአብሔርም በሰውም የተጠላ ተግባር አይደለም ወይ? ለአሜሪካ ድምዕ ራዲዮ ያለቺውን እነሆ፡
“ሳሚ የሚባል ጓደኛ አለውና ለእርሱ ከእኔ ጋር ስላለው ግንኙነት ሲነግረው እርሱም መልሱ እንኳን እኔ እግዚአብሔርም ደስ ይለዋል… አለው እና እርሱም የሚያሳየው መጠጥ አለ አለኝ፣ ገዝቶ ይዞ ገባ፡፡ መጠጡ ጠንካራ መጠጥ ነው … ለእኔ ግን ሻፓኝ ገዛልኝ፡፡ ሆቴል ውስጥ እንደገባን መጠጦቹን ደረደረና ፎቶ አነሳ፡፡ መጀመሪያ ለእኔ ሻፓኙን ሰጠና ለራሱ ያኛውን መጠጥ አንስቶ መጠጣት ጀመረ ማለት ነው፡፡፡ ያንን ፎቶ ለጓደኛው ለሳሚ ላከለት፡፡ ደግሞ ጡቴን ፕክቼር ነገር ብድግ አደረገና ላከለት ቴክስት አደረገለት፡፡ ከዚያ ይህንንማ ለብቻህ አትችለውም አጋዥ ያስፈልግሃል አለኝ አለ፡፡ እስቲ አናግሪው ብሎ ወዲያው ሰጠኝ፡፡ ከዚያ እመጣለሁና አብሬን መገናኘት እንችላን ብሎ ወሬ ማውራት ጀመረ፡፡ …. ከእኔ ጋር ለሁለት ሊወጡ አሳብ እንዳላቸው ማውራት ጀመሩ ማለት ነው፡፡”
የጸጋ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ሸማግሌ ከሌሎች ጋር ሆነው ባደረጉት ማጣራት ዘማሪ ሳሙኤል ተክለማርያም ስለዚህ ጉዳይ ምንም እንደማያውቅ መናገሩን ተከስተም ሳሙኤል በነገሩ ውስጥ ጨርሶ እንደለሌበት መመስከሩን ይፋ አድርጓል፡፡ መቼም በጌታ ስም ካላቸውም የአገልግሎት ኃላፊነት የተነሳ በጉዳዩ የገቡ የተከበሩ መሪዎቻችን የሚዋሹበት ምንም ምክንያት አይኖራቸውም፡፡ ግን ለመሆኑ እህታችን ሆሳዕና ከላይ የተመለከተውን አሳብ ተናግራ የእግዚአብሔርን አገልጋይ ስብዕና ያጠላሸቺው ለምን ይሆን? ሁሉንም ገደል ልክተታቸው ካልሆነ እንዲያው ምን ሊባል ይችላል? በሰጠችው ቃል ያሳሳተቺው ሰው ጥቂት አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ዘማሪ ሳሙኤል ተክለማሪያምን እንደ አገር አጥፊ ቦዜኔም ሳይይቆጥሩት የቀሩ አይመስለኝም፡፡ መደበቅ ምን ያረጋል እኔ ራሴ ልቤ በሳሙኤል ላይ ክብዶብኝ ነበር፡፡ ባለቤቷ መላኩም ተከስተ ይቅርታ እንደጠየቀና ንስሐ መግባቱን እየመሰከረ ለቪኦኤ የደውለው ሳሙኤል ንስሐ እንዲገባ ብሎ መሆኑን ተናገረ፡፡ እህት ሆሳዕና ከቤቷ ከጀምራ እስከ አገር ድረስ ያለነውን ሁሉ ፈራጆች አደረገቺን፡፡ ለምን ይህንን እንዳደረገቺው ለእርሷ መተው ይሻላል፡፡ ተከስተን የምንወቅሰው አቅዶና አልሞ ለዚህ ተግባር ራሱን በመስጠቱ ነው እንጂ ከፍ ብሎ እንዳየነው ሰው ነውና ወደቀ ከሚሉ ወገኖች ጋር እኔም እስማማለሁ፡፡ ሰው ምንጊዜም ደካማ ነውና ሊሰናከል እንደሚችል አለማሰባችን ለምንድነው? ዘማሪና ፓስተር ቢሆንም ልታሰናክለው እንደምትችል እርጠኛነቱ ስለነበራት እንጂ ልብስ ቀይራ በምሽት ወደ በርጎ የሄደችው ለየትኛው ድግስ ስለተጋበዘች ነው? ያውም ባሏ ወደ ሥራ የሚሄድበትን ሰዓት ጠብቃ! ደጋግሞ ስልክ ቢደውልም እቤቷ ቁጭ ብትል ጎትቶ የሚያወጣት በምን ይሆናል ብላ ነው? ስለዚህ በሁለቱም ትዳሮችና በቅዱሳን ላይ ለደረሰው አደጋ መንስኤ ሁሉም ናቸው፡፡ ምንም ይሁን ምን እርሷም ሰው ናትና መሳሳቷን ባንክድም እንዲያው እጅና እግሯ ታሥሮና ተገድዳ አልተደፈረችም ብንል ጨካኞች ያደርገናል ብዬ አላስብም፡፡ የምናምነው አንድ እውነት ግን አለ፡፡ ያውም በእውነተኛ ንስሐ ወደ እግዚአብሔር ፊት ከቀረበች እግዚአብሔር ለእርሷም ምሕረት እንደሚያደርግላት የሚያጠራጥረን ነጥብ የለንም፡፡
የጓዳችን ነገር ግድቡን አፍርሶ ወደ አደባባይ ወጣና ዓለም ሁሉ እንዲሰማው በመደረጉ የሐይማኖት መሪዎችም አስተያየት እንዲሰጡበት ከጋዜጠኞቹ ግብዣ ቀረበላቸው፡፡ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በኩል በራዲዮ ጣቢያው ምርጫ የተጋበዙ ስመ ጥሩ ሰው የተናሩት አሳብ ያልተያያዘ ብትን ሥራ መስሎ ታየኝ፡፡ እንዲህ ነው ያሉት፡
"በአገልጋዮቻችን መካከል እየሆነ ያለው አስነዋሪና አሳፋሪ ነገር አንድ ወሳኝ የሆነ ክፍተት እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡ በባህላችን መንፈሳዊ ሰዎች ይታመናሉ ይወደዳሉ፡፡ ስለሆነም መናገር ከቻሉ ይሰብካሉ፡፡ ድምፅ ካላቸው ይዘምራሉ፣ ይቀድሳሉ፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ስምና መድረክ ይሰጣቸዋል፡፡ እነርሱም የሚችሉትን መስጠት እንጂ ከአገልግሎት ጋር የሚመጣውን በረከት ተወዳጅነት ዝና ታዋቂነት እንዲሁም ተጠያቂነት ለማስተናገድ በቂ ትምህርት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ እንግዲህ ለወደፊት ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሞራል ጉዳይ ሆነ የአገልግሎት ብቃት የሚያስመሰክር ስልጠናና ብስለት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንደዚሁም ሲያጠፉ የሚመልሳቸው ሲወድቁ የሚያነሳቸው መንፈሳዊ መሪ ሥር መሆን የግድ ነው፡፡"
ይህ የምንወዳቸው አባታችን የዶር ቶሎሳ ጉዲና አስተያየት ነው፡፡ ዶክተር ብዙም ሳያስቡ የተናሩት ወይም የተከስተን ቤተ ክርስትያን መሪዎችን ሳያማክሩ ያስተላፉት አሳብ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እረኛ ስላለውማ በቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዓት ርምጃ ሥር መሆኑ እየተነገረ እረኛ ሥር መሆን እንዳለባቸው ግድ ነው ማለት ዶክተሩ ካለው የቤተ ክርስቲያናትና የአገልጋዮች ተጨባጭ ሁኔታ ርቀው ያሉ እንዳያስመስላቸው ፈራሁ፡፡ ደግሞ ሥልጠና ከፈተናና ከመሰናከል እንደሚያድን የሚናገረው የትኛው የወንጌል ክፍል ነው ብዬ ባስብ መልስ አጣሁ፣ ይህም በጣም ከማከብራቸው ከዶር ቶሎሳ ስለተነገረ ልክ አይደለም ለማለትም አቅም ከዳኝ፡፡ ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል ሕግን በመጠበቅ የሚለውን የዳዊትን ቅኔ ሊያሳዩን ይሆናል ብዬ ራሴን በራሴ ሰበክሁ፡፡ አገልጋዮችስ መናገር ስለቻሉ የሚሰብኩበት፣ ድምጽም ስላላቸው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ስምና መድረክ ተሰጥቶአቸው የሚዘምሩበትና የሚቀድሱበት ባህል ያላት የትኛዋ ቤተክርስቲያን ነች? አንድ ሰባኪ ከመስበኩ በፊት የስብከት የጸጋ ስጦታ እንዳለውና ለዘማሪም መድረክ የሚሰጠው ስጦታው ታይቶ መሆኑ እንዴት ሊረሳ ቻለ? ዶር የሰጡት አስተያያት ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወይስ ስለ ሌላ ነው ለማለት ተገደድኩኝ፡፡ ያለ ስጦታቸው የሚሰብኩ መኖራቸውን ባንክድም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የመናገር ችሎታ እና ድምፅ ላለው ብቻ መድረክ የሚሰጥ ቤተ ክርሰቲያን እንዳለ አድርገው በዓለም መድረክ መናገራቸው ያስመስግናቸዋል ለማለት አልችልም፡፡ መቼም የዶክተርን ያህል በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የቆየን ባንሆንም ትክክለኛ የአመራር መዋቅር ያላት እውነተኛዋ ቤተ ክርሰቲያን አገልጋዮችን በአገልግሎት ከማሰማራቷ በፊት እንዴት እንደምትፈትናቸው እያየን ነው፡፡ የዶክተሩ አባባል ግን ከእውነታው ጋር ተጋጨብኝ፡፡ ሲወድቅ የሚያነሳ እረኛ ሲሳሳቱ የሚመልስ እረኛ ያስፈልጋል ማለታቸው እውነት ነው፡፡ ግን እረኛው ሲሳሳትስ የሚመልሰው ማነው? ሲወድቅስ የሚያነሳው ማን ነው? ዶር ቶሎሳ የሚናገሩት ስለ የትኛው እረኛ ነው? ከማንም በላይ እኔ ነኝ ስለሚለው ፈላጭና ቆራጭ እረኛ ነው ወይስ በቤተ ክርስቲያን የጋራ አመራር በሚያምንና ሲሳሳት የሚመልሱት ሲወድቅ የሚያነሱት አካላት ስላለው ሎሌያዊ አገልጋይ ነው የሚናሩት? ፓሰተር ተከስተስ እረኛ ቢሆንም ከእረኞች ሥር ስለሆነ ምክር የሚቀበልበት እድል አግኝቷል፡፡ ይህን የማይፈልጉ እረኞችስ ካሉ ችግሮች የሚፈቱት እንዴት ነው? ለምሳሌ በአትላንታ ኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን እረኛና መጋቢ ዶክተር ራሳቸው ናቸው፡፡፡ እርሳቸው ቢያጠፉና ቢሳሳቱ የሚገስጻቸው ከእርሳቸው በላይ ሆኖ መመሪያ የሚሰጣቸው አካል ካለ ጥሩ ምሳሌያችን ናቸው፡፡ ካልሆነስ እርሳቸው የማይነኩ እንደሆኑ የሚያስቡ ወጣት አገልጋዮችም በጋራ አመራር አያምኑምና ፈልጠውና ቆርጠው መኖር የሚያዋጣ ቢመስላቸውና ቢሳሳቱ ችግርም ቢገጥማቸው ዶክተር ቶሎሳ በምን ሥልጣን ሊወቅሱአቸው ነው፡፡ ወጣት መጋቢያን የሚማሩት እንደነዶር ካሉት ነዋ? ስለዚህ የሚሉትን ክፍተት የፈጠረው ማን ነው? የሚለውን ዶር ቢመልሱልን እድለኞች ነን፡፡
ከላይ ያየናቸው አሳቦች እንዳሉ ሆነው ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ከቃኘን በኋላ ሊመሰገኑ የተገባቸውን ሳናመሰግን ማለፍ ተወቃሽ ያደርገናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ ካወቅን የአደጋው ተጠቂዎችን ከፍርስራሹ ውስጥ ለማውጣት በምንችለው ሁሉ መትጋት ይገባናል ባይ ነኝ፡፡ ወይዘሮ ሆሳዕና በመንፈሳዊ ህይወቷ ምን ያህል የበሰለች እንደሆነች አላውቅም ግን ልትመሰገንበት የሚገባት ጉዳይ አለ፡፡ ውድቀቷን ከትዳር አጋሯ ደብቃ፣ ለስሟ ተጠንቅቃ የቻለቺውን ያህል ዓመት መኖር አላስፈለጋትም፡፡ አስፈሪ ቢሆንም ደፍራ ራሷን ገለጠች፡፡ ይህን ለማድረግ ኃይል እንዴት እንዳገኘች ቢያስደንቀንም ከዚህ በላይ መንፈሳዊነት አለ ብዬ ማመን ይቸግረኛል፡፡ እግዚአብሔር እኮ በኃጢአት በሚወድቁት እንደሚያዝባቸው ሁሉ በሚናዘዙ ደግሞ የበለጠ ደስ ይለዋል፣ እነርሱንም ያለመልማቸዋል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ታዋቂነት ያለው ዘማሪያችን ሳሙኤል ተክለማሪያም እንዳለው እኔ ይህንን አላደረግኩም ብላ በመሸምጠጥ እግዚአብሔር ነገሮችን ወደ ፀሐይ እስክያመጣው ድረስ መቀጠል አልፈለገችም፡፡ ታዲያ አይዞሽ እግዚአብሔር ይቅር ይልሻልና ብልንስ?
እስቲ ሁላችንም ራሳችንን በአቶ መላኩ የሺዳኛ ጫማ እናቁምና ህመሙን እናዳምጠው፡፡ በፍቅር የተሳሰሩ የልጆቹ እናት የሆነቺው አካሉ ከሌላ ወንድ ጋራ ለመተኛት ራሷን ገላልጣ መስጠቷን ሰምቶ በሰላም ለመኖር መወሰኑ እውነተኛ የእግዚአብሔር ሰው አያሰኘውምን? በዝሙት ምክንያት ካልሆነ ሚስቱን የሚፈታ አመንዝራ ያደርጋታል የሚለውን ጥቅስ ተመርኩዘው ሰው አንዴ በዝሙት ከወደቀ ትዳሩን መፍታት አለበት በሚል ትዳሩን ለመፍረስ የሚጣደፍ ሰው በበዛበት በዚህ ክፉ ዘመን ሁሉንም ዋጥ አድርጎ አብሮአት ለመቀጠል መወሰኑ በሳልና ለባሎች ሁሉ ምሳሌ ሊሆን የሚችል አያደርገውምን? የቃል ኪዳን አሳቢነት ለልጆቹ ተቆርቋሪነት፣የእግዚአብሔር ፍርሃት፣የባለቤቱም ኃላፊነት ሁሉ የተሰማው ሰው ነውና ቢቻል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ካልሆነም ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ ተባረክ ተመንደግ በማለት ትዳሩም ዳግም ልዩ ጣዕም እንዲኖረው እግዚአብሔርን መለመን ይገባል ባይ ነኝ፡፡
አደጋው መከሰቱን በመስማት የተጎዱትን አካላት ሁሉ ለመታደግ የእረኝነትና የካህንነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የተንቀሳቀሱ የወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያናት መሪዎች በእውነት ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ ያሉ የቤተክርስቲያን መሪዎች ወንድማችንን ተከስተ ጌትነትን ከአገልግሎት በማገድ ራሱን እንዲያይ በማድረጋቸው እርሱ ለቤተክርስቲያን ሥልጣን ራሱን በማስገዛቱ እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን ይህ ውድ ነገር ነው፡፡ ይህን በመስማቴ እየተጽናናሁ ዶር ቶሎሳ ለአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ ከተናገሩት አሳብ ጋር መስማማት ያቃተኝ ለዚህ ነው፡፡ የሐይማኖት መሪዎች አስተያየት ጉዳይ ከተነሳማ የፕሮፌሴር ጌታቸው ኃይሌ አስተያየት ሚዛኑን የጠበቀ ነው፡፡ እንዲህ ነው ያሉት፡
"ይህ ችግር የዛሬ አይደለም፡ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ በሰው ልጅ መካከል ያለ ነው፡ እንዲውም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትልቁ ኃጢአት የወሲብ ጉዳይ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ በሰው ላይ ያለ ነው፡……፡፡ ይኼ በተለይም መንፈሳውያን የሆኑትን በበለጠ ያስቸግራል፡፡ በየመጻሕፍቱ ሁሉ ላይ ስናየው፣ በየገድሉ ሁሉ ላይ ሲናየው፣ በተለይ በካህናቱ ላይ ይጠነክራል ይኼ ደግሞ፡፡ ለእኛ አዲስ የሚሆንብን…… በካህናት ላይ ሲመጣ ነው፡፡ ያን ጊዜ ነው የሚያስደነግጠን፡፡ ነገር ግን ታስታውሱ እንደሆነ ዳዊት ሰለሞንን የወለደው በኃጢአት ነው የዳዊት ልጅ እህቱን የደፈረው በኃጢአት ነው፣ እና ይህ ትላልቆቹን መንፈሳውያንን በበለጠ ይጎዳቸዋል፡፡…….ይኼ በተለይም መንፈሳውያን የሆኑትን በበለጠ ያስቸግራል፡፡ በየመጻሕፍቱ ሁሉ ላይ ስናየው፣ በየገድሉ ሁሉ ላይ ሲናየው፣ በተለይ በካህናቱ ላይ ይጠነክራል ይኼ ደግሞ፡፡ ለእኛ አዲስ የሚሆንብን…… በካህናት ላይ ሲመጣ ነው፡፡ ያን ጊዜ ነው የሚያስደነግጠን፡፡ ነገር ግን ታስታውሱ እንደሆነ ዳዊት ሰለሞንን የወለደው በኃጢአት ነው የዳዊት ልጅ እቱን የደፈረው በኃቲአት ነው፣ እና ይህ ትላልቆቹን መንፈሳውያንን በበለጠ ይጎዳቸዋል፡፡……አባቶች ከእግዚብሔር ቀጥሎ እሰከ መመለክ የሚደርሱ ናቸው፡፡ እና ያ ነው እንግዲህ የሚያስደነግጠን፡፡ በዚያ ደግሞ በአንድ በኩል ሕዝበ ክርስትያኑ መነገር አለበት ማወቅ አለበት፡፡ እንደዚህ ያለ ነገር ከሕብ ክርስቲኑም መጠበቅ አለበት፡ … ካህናቱም ወጥተው ሲያስተምሩ እኛ ሁላችንም ደካሞች ነን፡፡ እርዱን ማለት አለባቸው፡፡ ይህናው ሕዝበ ክርስቲያኑም መርዳት አለበት ለማለት ነው፡፡"
ስለዚህ እኒህን ሰው እግዚአብሔር ይባራካቸው ማለት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የእምነት አባቶቻችን በማሕበራዊ ገጾች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በሚጋበዙበት ጊዜ ከብዙ አንጸር በጥንቃቄ መናገር እንዳለባቸው መምከር ያለብን አይመስለኝም፣ለዚያ የሚሆን አቅም ገና የለኝምና፡፡
ልትረሳ የማይገባት ሰው የዘማሪ ፓስተር ጌትነት ባለቤት ነች፡፡ ምንም እንኳን ባሌ ለትዳሩ ታማኝ አይደለም እና ልለየው እፈልጋለሁ ብትል ማንም ቢሆን ለትዳሩ መፍፈረስ ምክንያት የሚያደርገው ተከስተን እንጂ እርስዋን አይደለም፡፡ እርሷ ግን ከመብቷ ይልቅ በቃል ኪዳን በታሠረችበት ባሏና በፍቅሩ ተረታች፡፡ ማህበረ ምዕናኑን ይቅርታ ሲጠይቅ አብራው ሆና ከጎኑ እንደቆመችና ይቅርታ እንደለመነች ተመስክሮላታልና እግዚአብሔር ይባርካት፡፡ ሰይጣንን ማሳፈር ከተባለ እንዲህ ዓይነቱ ቀዳሚ ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻም፡ በተፈጠረው አደጋ የተጎዱትን ሁሉ ለማዳን የፍቅርና የርሕራሄ ልብ ያስፈልገናል፡፡ በምሕረት ዓይኖች እንድናያቸውም ያሻናል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በጸጋ ዘመን ብንሆንና እኛው በጸጋው የዳንን ጸጋው የበዛልን ብንሆንም በኃጢአት ጸንተን እንድንኖር ቃሉ አይፈቅድምና ለኃጢአት ከሚያጋልጡ ሁኔታዎችና ቦታዎች ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡ ሰዎች በተለይም አገልጋዮች ተፈትነው ሲወድቁ ከውድቀታቸው የሚነሱበትን መንገድ እንፈልግላቸው የጌታንም ታላቅ ምሕረት እናሳየቸው እንጂ ያለርህራሔ አንውገራቸው፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ቢሆንም የሚባላ እሳትም መሆኑን ሳንረሳ በኃጢአት የወደቀውን ሰው በጭፍኑ ምንም አትሁን የሚል ተስፋ በመስጠት የንስሐ ዕድል እንዳንከለክለውና በጣም ወደ ጥግ ከተለጠጠው ቲፎዞነት መቖጠብ ይኖርብናል፡፡ ማናችንም ፈጥነን ከምንፈርድ ይልቅ የቅጣቱንም ሆነ በነጻ የመልቀቁን ኃላፊነት እግዚአብሄር መንፈሳዊ ሥልጣን ለሰጣት ቤተ ክርሰቲያን እንተውላትና ከእርሷ ድምጽ በመስማት የምናድረጋቸውን ሁሉ እናድርግ፡፡ ራሳችንንም በፍርድ ወንበር ላይ ፈጥነን እንዳናወጣ ጌታ ይጠብቀን፡፡ በሆነው ነገር ያዘኑትን፣ የተጎዱትን ሁሉ እግዚአብሔር በምሕረቱ ያስባቸው!! አሜን

የከበረ ሀብታችሁን አትጣሉ( ክፍል ሁለት)

2. ጸጋችሁን አትጣሉ፡፡
ባለፈው እግዚአብሔር የሰጠንን የከበረ ሀብት እንዳንጥል የሚያሳስበንን ትምህርት መማራችን ይታወቃል፡፡ በትምህርታችን ወቅት እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠንን ስጦታ ዋናና አስፈላጊ ብለን ለሁለት መክፈላችንም አይረሳም፡፡ በተለይም ደግሞ መንፈሳዊ ሀብታችን ከሁሉም የላቀ ስለሆነ ስለ ምድራዊውና ስለ አስፈላጊው ስንል ሰማያዊውንና ዋና የሆነውን ባለጠግነት እንዳንጥል ፣ ቸልም እንዳንል የሚስተምረንን ትምህርት አብረን ተቋድሰናል፡፡ መንፈሳዊና ዋና ሀብት ከምንላቸው አንዱ መንፈሳዊ ብኩርናችን መሆኑን አይተን ነበር ያበቃነው፡፡ በዛሬው ትምህርታችን እንደምንመለከተው ደግሞ ትልቁ ሀብታችን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ስጦታ "ጸጋ" የተባለው ነው፡፡ ይህንን ጸጋ እንዳንጥል የሚያሳስበንን ትምህርት እነሆ!
የሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ አማኞች በጻፈው መልእክት የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም ይላል(ገላትያ 2፡21)፡፡ ሐዋሪያው በዚህ ክፍል ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት አስቀድመን መመልከቱ የተሻለ ነው፡፡ እርሱ የመጀመሪያውን ሓዋሪያዊ ሚስዮናዊ ጉዞውን በእስያ ባደረገበት ወቅት የወንጌሉ መልእክት ያተኮረው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ነበር፡፡ ደህንነት የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በጸጋ ብቻ ነው ብሎ በመስበክ በገላትያ አውራጃዎች ብዙዎችን ወደ ክርስቶስ በማመልከት ቤተክርስቲያን ተከለ፡፡ ከዚያ በኋላ ጳውሎስ ካስተማረው ወንጌል የተለየውን የሚሰብኩ ሌሎች ሰዎች ተነስተው ለደህንነት መልካም ሥራን መሥራት፣ ሕግን መጠበቅና መገረዝ ወዘተ ያስፈልጋል ብለው በማስተማር ምዕመናንን አሳቱአቸው፡፡ ጳውሎስ ከሰበከው የጸጋ ወንጌል ሌላ የተለየ መልእክት ያለው ወንጌል ሁሉ "ሌላ ወንጌል" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑትን እንዲያው ያድናቸዋል የሚል መልእክት ያለበት ወንጌል ደግሞ የጸጋ ወንጌል ነው፡፡ ይህ የጸጋ ወንጌል ደግሞ እኛ የዳንንበት ወንጌል ነው፡፡
ጸጋ ማለት ምሕረት ለማይገባው ኃጢአተኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚሰጥ የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ነው፡፡ ዋጋው በሰው አእምሮ የማይታሰብና የማይገመት ግን ከእግዚአብሔር ቸር ለጋስነት የተነሳ እንዲሁ በነጻ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ጸጋ በእኛ ሕይወት የሚያደርጋቸው ሁለት ታላላቅ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ደህነነትን ማስገኘቱ ሲሆን ሁለተኛው በምንኖረው ኑሮ የምናልፍባቸውን መንገዶችና ውጣ ውረዶችን ሁሉ ተቋቁመን እንድናልፍ ኃይልን ወይም ብቃትን ይሰጠናል፡፡ ወንጌላችንም የሚያመለክተው ደህንነት በሰው ሥራ ወይም በማንም መልካምነት ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እንግዲህ ሐሰተኞች የሚሰብኩት ሌላ ወንጌል ይህንን ጸጋ ዝቅ የሚያደርግ ፣ አማኞችም ቸል እንዲሉት የሚያደፋፍርና እውነትነት የሌለበት ነው፡፡
በገላትያ የኖሩ ሰዎች ጳውሎስ የሰበከውን የጸጋ ወንጌል ሰምተው በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ከተቀበሉ በኋላ የሐሰት አስተማሪዎችን ትምህርት በመስማታቸው ወደ ሌላው ወንጌል ትምህርት ዘወር ብለው ነበር፡፡ ይህም ማለት የእግዚአብሔርን ጸጋ ጣሉት ማለት ነው፡፡ በመልካም ሥራቸው ወይም በመገረዛቸው ወይም ሕግን በመጠበቃቸው ምክንያት ድነትን እናገኛለን በሚል በጸጋ ላይ የራሳቸውን ሥራ ሊያክሉበት ፈለጉ፡፡ እግዚአብሔር ለደህንነታችን መንገዱ እርሱ በልጁ በኢየሱስ በኩል የሰጠን ጸጋ እንዲሆን ያደረገው ደህንነት የሰው ርዳታ የማያስፈልው በጸጋ ብቻ የሚከናወን በመሆኑ ነው፡፡ የሰው ሥራ ለደህንነት የሚያስገኘው ትርፍ የለም፡፡ ይህም በመሆኑ ሐዋሪያው የገላትያ አማኞችን እንደገና የሚያሳስባቸው ይህን ነው፡፡ ማንም በራስ መልካምነትና ጥረት እድናለሁ ቢል እኔ ግን የዳንኩበትን የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም በማለት እውነቱን ይነግራቸዋል፡፡
የሐሰት አስተማሪዎች በገላትያ አውራጃዎች የሚገኙ አማኞችን ሌላ ወንጌል በመስበክ የእግዚአብሔርን ጸጋ አስጥሎአቸዋል፡፡ ከእውነተኛውም የደህንነት ትምህርት ዘወር እንዲሉ አድርጎአቸዋል፡፡ በዛሬውም ዘመን ይህ ዓይነት እንቅስቃሴ በቤተክርስቲያን በስፋት ይታያል፡፡ ሐሰተኞች አስተማሪዎች አማኞችን የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚያስጥሉአቸው በተለያዩ መንገዶች ነው ፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወንጌልን በሰበከበት ዘመን የነበሩ ሐሰተኞች እውነተኛውን ትምህርት በማጣመም ሲሆን በእኛ ዘመን ያሉት ደግሞ የተለያዩ የማሳሳቻ መንዶችን በመጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በአገራችን ሲሆን ያየነው ለዚህ በቂ ምሳሌ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነገረንና እኛም እንደተማርነው የሰውን ኃጢአት የሚያስወግድ በመስቀል ላይ የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ለመንፈሳዊ ሕይወት ለውጥ፣ ለኃጢአት መንጻት እና ለኑሮ ስኬት የተለያዩ ሳሙናዎች፣ የታሸጉ ውሃዎችና ዘይቶች እየተሸጡ መሆናቸውን ያየነውንና የሰማነውን ሁሉ አሳዝኖአል፡፡ የሣሙናና የዘይት ቸርቻሪዎች ይህንን መንገድ የመረጡት ብቸኛ የገቢ ማስገኛ እንደሆነ ስለገባቸው ነው፡፡ ችግሩ በእግዚአብሔር ስም ማድረጋቸው ነው እንጂ፡፡ ታላላቅ ሱፐር ማርኬት ያላቸው ሀብታም ነጋዴዎች ዓመት ሙሉ ቢሰሩ የማይሸጡትን ያህል ነጋዴ-ነቢያቶችችን በግማሽ ቀን ውስጥ ያጣሩታል፡፡ የአዲስ አባባውን ሚሊኒየም አዳራሽ የሞላ ሕዝብ አንዳንድ ዘይትና ሳሙና እንዲሁም የታሸገ ዉሃ ከገዛ ምን ያህል ሊሸጥ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ነጋዴ- ነቢያቱ የግል ሄሊኮፍተሮች ያሉአቸውኮ በጽድቅ ከሚያገለግሉ ከሌሎች አገልጋዮች ይልቅ የተለየ ቅባት ስላላቸው ሳይሆን የንግድ ብልሃታቸው የረቀቀ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከመንግሥት የንግድ ፈቃድ ያለው አንድ ነጋዴ በሚሊኒየም አዳራሽ ውሃና ዘይት እሸጣለሁ ቢል እንደ ነጋዴ- ነቢያቶቹ ሊሳካለት አይችልም፡፡ አንደኛ ውሃውን የሚገዛው የለም ፣የተለመደ ነውና፡፡ እንደሱ ዓይነት ዉሃ በሸሚሱ ሱቅ በቅርቡ ስላለ ማንም ያንን ለመግዛት ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ አይሄድም፡፡ ሁለተኛ ሰውዬው በነጋዴነቱ ስለሚታወቅ ለመንግሥት የሚከፍለው ግብር ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ነጋዴ- ነቢያቶቻችን ግን ውሃውን መንፈሳዊ ስያሜ በመስጠት መንፈሳዊ አድርገውታል፣ የማቅረቢያ ዕቃውም ከዚያኛው ይበልጥ ማራኪ ነው፡፡ እንደገናም በመንፈሳዊ ኮንፍራንስ ስም ስለሚደረግ የሚከፈል ምንም ግብርና ቀረጥ የለበትም፡፡ ይህ እንግዲህ እጅግ የሚያስገርም ነገር ነው፡፡ ለነገሩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሐይማኖትን ካባ ደርበው ሳይታወቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን መድረኮች ከወጡ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ አዎንታዊ ትንቢቶች የሚነገሩት ዳጎስ ያለ ገንዘብ በሚያስገኙ አካባቢዎች ከሆኑ ስንብተዋል፡፡ ይህ ገንዘብን ለማግኘት ሲሉ የሐሰት አስተማሪዎች የቀመሙት የውንብድና መንገድ ነው፡፡
አማኞች ግን የተማሩትንና የሰሙትን እውነት ወደ ጎን ትተው ከኃጢአታችሁ ምትታነጹበት ውሃና ሳሙና እንዲሁም ዘይት ይዤላችሁ መጥቻለሁ የሚለው አጭበርባሪ ያቀረባቸውን ጥሪ መቀበላቸው በጣም ያስገርማል ያሳዝናልም፡፡ ምዕመናን ብቻ ሳይሆኑ መሪዎችና አገልጋዮች ተብዬችም የዚህ ነገር ተባባሪዎች ሆነው መገኘታቸው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የሐሰት አስተማሪዎች በተጋበዙባቸው ቦታዎች ሁሉ ትኩረት እየተደረገ ያለው በሚያደርጉት ድንቃድንቅ እንጂ በሚያስተምሩት ትምህርት አለመሆኑ ብዙዎችን አሳስቷል፡፡ ምልክትና ድንቅ ሰይጣንም እንደሚያደርግና እንዲያውም በመጨረሻው ዘመን የተመረጠትንም እስክያስት ድረስ በታላቅ ታምራቶችን እንደሚታጀብ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ያስተምራል፡፡ የሐሰተኞች መለያ በሚያደርጉት ተአምራት ሳይሆን በዋናነት በሚያስተምሩት ትምህርት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ቤትም ሆነ ከአገር ውጭ ባሉ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የተሰበኩ ስብከቶች በዩ ቲዩብ በመለቀቃቸው ብዙ መልካም ትምህርቶች በአጭር ጊዜ በምድሪቱ ላይ በቀላሉ ሊሠራጩ ችለዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ነቢያት ተነስተዋል ፣ ድንቅም ናቸው፣ የሚያስገርሙ ናቸው ተብለው ከመድረክ የተቀረጸበት ፊልም ሲታይ የተናገሩት ሚስጥራዊ ነገሮችና ድንቃንቆች ናቸው እንጂ ስለደህንነት፣ ስለ አስተምህሮ ክርስቶስ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ ፣ ስለቅድስና፣ ስለ ትክክለኛ ክርስትና አኗኗር ወዘተ ምን እንዳስተማሩ አይታይም፡፡ ነቢያቶቹ ትምህርት የላቸውም ማለት ነው? ወይስ ከወንጌል አስተምሮተ- ስብከት ይልቅ በጣም አስፈላጊው ምልክትና ተአምራት ሆኖ ተገኝቶ ነው? ተአምራት የሚደረገው እኮ ሰዎች ለጸጋ ወንጌል መልእክት ልባቸውን እንዲከፍቱ ማድረግ እንጂ ያለ ወንጌል ትምህርት የሚደረግ ተአምር በራሱ የአገልግሎታችን ዓላማ አይደለም(የሐዋ 20፡30-31)፡፡ ሰዎችን ወደ ደህንነት የሚያመጠው እውነተኛ የወንጌል መልእክት እንጂ ተአምርና ምልክት አይደለም፡፡ ምዕመናንና የቤተክርስቲያን መሪዎች በእነዚህ እውነታዎች መካከል መለየት አለመቻላቸው እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ለምሳሌ ከኃጢአታችሁ ለመነንፃት ውሃና ሳሙና ግዙ የሚለውን ሰው አንተ የእግዚአብሔር ሰው ነህ ማለት ሳይሆን ሐሰተኛ ነህ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ቃሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻል ስለሚል(1ዮሐ 1፡9)፡፡ ሰው ከኃጢአቱ ለመንፃት ምንም ዋጋ መክፈል አያፈልገውም ምክንያቱም ደህንነትና መንጻት በነጻ ያለዋጋ ነውና( ኢሳ 55፡1-3)፡፡ በሕይወቱ ድካም ያለበትና የእግዚአብሔርን ርዳታ የሚፈልግ ማንም ቢኖር የነጋዴዎችን ዘይትና ውሃ መግዛት ሳይሆን በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳውን ጸጋ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ዙፋን ፊት በእምነት መቅረብ ይኖርበታል( ዕብ. 4፡14-16)፡፡ ይህ ጸጋ ብቻውን በቂ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ያልቻለውን የሚችል ምንም ዓይነት ሰው ሠራሽ ዘይትና ሳሙና የለም፡፡ የጸጋው ስፋት መሸፈን ያቃተውና በዘይት ፣ በሳሙናና በታሸጉ ውሃዎች የምንሸፍናቸው ቦታዎች የሉም፡፡ የአምላካችን ጸጋ ከየትኛውም አጥናፍና የምድር ስፋት ሁሉ ያለፈ ነው፡፡ የሰው ሥራም ሊስተካከለው አይችልም፡፡ ስለዚህ የሐሰት አስተማሪዎች በጳውሎስ ዘመን ብቻ ሳይሆን አሁን እኛ ባለንበት ዘመንም ቢሆን አማኞችን የእግዚአብሔርን ጸጋ እያስጣሉ መሆናቸውን በውል ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን ደህንነትን ያስገኝልናል፣ የሕይወት ውጣ ውረዶቻችንንም ሁሉ እንድናሽንፋቸው ያስችለናል፡፡ ደህንነትና ጽድቅ በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን ኤፌ 2፡8፣ ቲቶ 2፡11፣ ሮሜ 3፡23-24፣ሮሜ 5፡12-19፣ ገላትያ 216 ወዘተ መመልከት በቂ ነው፡፡ በሕይወታችን የሚገጥመውንም ፈተና በእግዚአብሔር ጸጋ እንደምናልፍ ቃሉ ያስተምረናል( 2 ቆሮንቶስ፡12፡7-10፣ዕብ 4፡14-16)፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ መከራ ሕመም ሲበዛን ያንን እንችለውና እንድናሸንፈው ፣ ጉልበታችን ሲዝል እንድንበረታ ያደርገናል፡፡ ሕይወታችን ሲቀዘቅዝ የሚያሞቀን ከመሆኑም በላይ፣ በወጀብና በአውሎ ነፋስ ውስጥ መርከብ ይሆነናል፡፡
ጳውሎስ የሥጋዬ መውጊያ የሚለው በሽታውን እንደሚሆን ብዙዎቻችን እንስማማበታለን፡፡ በሽታው ይህ ነው ብሎ በግልጽ ማስቀመጥ ባይቻልም ምናልባት በልስጥራና በደርቤ ወንጌልን በሚሰብክበት ወቅት የወንጌል ተቃዋሚዎች እስክዝለፈለፍ ድረስ በዱላ ሲደበድቡት ሰውነቱ ለመጥፎ የአካል ጉዳት ተጋልጦ ይሆናል( ሐዋ.13-14)፡፡ ወይም ደግም አይሁድ አንድ ሲጎዲል 40 ግርፈት አምስት ጊዜ በመግረፋቸው ምናልባት የነርቭ ችግር ገጥሞት ሊሆን ይችላል፡፡ወይም ደግሞ ወደ ደማስቆ ባቀናበት ወቅት ከሰማይ በታየው ታላቅ ብርሃን ምክንያት አይኑ እንደታወረበትና ቅርፍትም ከዓይኑ ላይ እንደወደቀ በሐዋ. 9 ላይ የምንመለከተው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የዓይን ሕመም ገጥሞት ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱ እንዲያውም ለገላትያ አማኞች በጸፈው መልእክት ቢቻልስ ዓይናችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ ( ገላትያ 415)፣እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደጻፍሁላች እዩ(ገላትያ 6፡14) ያለው ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛውም ይሁን ብቻ የእግዚአብሔር ፈውስ እንዲሆንለት ሦስት ጊዜ አምላኩን ሲለምን የአምላክ መልስ ግን "ጸጋዬ ይበቃሃል" የሚለው ሆነ፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ጳውሎስ ከሚፈልገው ፈውስ ይልቅ እጅግ የላቀ መሆኑን በዚህ መረዳት እንችላለን፡፡
እኛ በዚህ ምድር ላይ በመኖራችን ምክንያት የሚያታግሉን ብዙ ነገሮች እንዳሉብን በጣም ግልጽ ነው፡፡ በሚገጥሙን ሁሉ ግን ርዳታ እንፈልጋለን፡፡ እውነተኛ እርዳታ የሚገኘው ግን ከጌታ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ደግሞ በማናቸውም ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን የሚረዳንን ጸጋ እንደሚሰጠን የዕብራውያን ጸሐፊ ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ርዳታ በሚያስፈልገን በማናቸውም ጊዜያት የሚረዳንን ጸጋ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ፊት በእምነት መቅረብ እንዳለብን ቃሉ ያሳስበናል( ዕብ 4፡14-16)፡፡ የእግዚአብሔር ዙፋንም ደግሞ የጸጋ ዙፋን ነው፡፡
በዘመናችን ያሉ የሐሰት አሠራሮች በሥጋችንም በምንኖረው ሕይወት ሁሉ በእግዚአብሔር ጸጋ ከመደገፍ ይልቅ በሰዎች ድንቅና ምልክት ላይ አይናችንን እንድናኖር እያደረጉን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የፈውስን ስጦታ የሰጣቸው አገልጋዮች አሉ፡፡በእነርሱ በኩል በእውነት አስገራሚ አገልግሎት አየተሰጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር ታምራት የሚገልጠው በሰዎች በኩል ስለሆነ የሚጠቀምባቸው ብዙ ባሪያዎች ስላሉት ስሙን እንባርካለን፡፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ያለ እኛ መሥራት ይችላል፡፡ እኛ ግን ያለ እግዚአብሔር መሥራት አንችልም እንጂ፡፡ ይህም በመሆኑ ታምራትንና ድንቅን የሚያደርገውን ጌታና የእርሱን ጸጋ ከማሳየት ይልቅ አገልጋዮች በጣም አስደናቂ ሰዎች መሆናቸውን የሚያውጁና የሚያዳምቅላቸውን ደቀ መዛሙርት በየቦታው የሚያቆሙ ሐሰተኛ ነቢያቶችና ተከታዮቻቸው አማኞችን ጸጋን እያስጣሉ ናቸው፡፡
ከዚህም በላይ ነጋዴ-ነቢያቶቹ የልባቸውን ካደረሱና የሚበቃቸውን ያህል ከቀረቀቡ በኋላ ማንም ቢቃወመኝ እግዚአብሔር በሞት ይቀጣዋል ብለው ማስፈራራታቸው ሌላው አስቂኝ ነገር ነው፡፡ እሰቲ ተመለከቱ እግዚአብሔርን የራሳቸው ወታደር ወይም ልዩ የግል ጠባቂ/ body guard / ሲያደርጉት አያስገረምም? በጌታ አምኖ የዳነውን ታላቅ ሕዝብ በሞት ማስፈራራት እንዴት ያለ ስህተትና ድፍረት እንደሆነ ተመለክቶ እንዴት እንደዚህ ልትል ቻልክ የሚል የእግዚአብሔር ቤት ቅንዓት የሚበላው ሰው ምነው ጠፋሳ! የአፍሪካ አገሮችን አቋርጠው መጥተው ወደ ኢትዮጵያ ታላቁ ቤተ መንግሥትም ዘልቀው ገብተው ከአንጋፋ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝዋልና፣ ፎቶም አብረው ተነስተዋልና የተቀቡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው በማለት የሚያወሩላቸውን መለከት ነፍዎችን በየቦታው መሰየማቸውን ማየት ሌላው አስገራሚ ነገር ነው፡፡ ይህ ለመቀባታቸው መረጋገጫ ከሆነ ወደ ቤተ መንግሥት ያልገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ አገልጋዮቻችን ቅባቱጋ አልደረሱም ማለት ነው? እስከ አሁን ደረስ በቤተ መንግሥት የተስተናገዱት ኢቬሰተሮችና ዲያሰፖራዎች የተቀቡ እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው ማለት ነው? ወደ ቤተ መንግሥት የገቡ ኢትዮጵያውያን አገልጋዮችንስ ምነው አይናችን ያላያቸው? ወይስ የተቀቡ ለመባል እንደ እነ ቡሽሪ ሄሊኮፒተር ገዝተው ማሳየት ይኖርባቸዋል ማለት ነው ?
የእግዚአብሔር መንፈስ ታዛዥና ታማኝ የሆኑ አገልጋዮችን በመጠቀም የሚያስገርሙ የሥጋ ፈውሶችን ያደርጋል፡፡ በእርግጥ ማናቸውንም ሰዎች ለዚህ የተባረከ ሥራው መጠቀም ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን የሥራው ባለቤት ራሱ መንፈስ ቅዱስ እንጂ አገልጋዮቹ ስላይደሉ ክብርና ሙገሣንም ቢሆን ፈዋሽ ለሆነው ጌታ መስጠት እንጂ ሰዎችን ከጌታ በላይ ልናደርጋቸው አይገባም፡፡ በእውቀት ማነስ ምክንያት መጠነኛ ስህተት የሚፈጽሙ ቅን አገልጋዮችን መታገስ አስፈላጊ ነው፣ ምክንያቱም እንደነዚህ ዓይነቶች በምክርና በጤናማ ትምህርት እየተቃኑ ለትውልድ የሚጠቅሙ የጌታ አገልጋዮች ይሆናሉና፡፡ ስለ አገልጋዮቹ ግን እግዚአብሔርን እያመሰገንን በበለጠ ጌታን እያስከበሩና እንዲያገለግሉ ልንጸልይላቸው ይገባል፡፡ አንዳንድ በገንዘብ ጥቅምና በክብር የሚፈተኑ አገልጋዮች አልፎ አልፎ መታየታቸው ግልጽ ቢሆንም ክብሩን ግን ጌታ ብቻ መውሰድ እንዳለበት ራሳቸው ያውቃሉ፡፡ እነዚህ ከሐሰት አስተማሪዎች የተለዩ ናቸው፡፡
ሐሰተኞች ግን እንደዚህ አይደሉም፡፡ የሐሰተኞች ችግር የእውቀት ማነስ ሳይሆን ከራሳቸው ፍላጎትና አሳብ በስተ ኋላ በመሮጥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ወደማያስፈልግ መንፈሳዊ ልምምድ ውስጥ መክተት ነው፡፡ እነርሱ የፈለጉት ንዋይ፣ ክብርና ዝና ይገኝላቸው እንጂ ምዕመናን በእግዚአብሔር ነገር ይደጉ አይደጉ፣የሚሰበከው ወንጌል እውነት ይሁን ሐሰት ምንም ግድ የላቸውም፡፡ ይህንን አበጥረው ማወቅና መለየት ያለባቸው የቤተክርሰቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ሲሆኑ ምዕመናንም ቢሆኑ ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት ራሳቸውን በማስረከብ ከተሳሳት አሠራር መራቅ አለባቸው፡፡ ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ጸጋ የከበረ ሀብታችን ስለሆነ በእነዚህ በተሳሳቱ አሠራሮች ምክንያት እንዳንጥለው እንጠንቀቅ፡፡ የከበረውን ጸጋችሁን አት
ጣሉ!