Wednesday, March 25, 2015

የከበረ ሀብታችሁን አትጣሉ( ክፍል ሁለት)

2. ጸጋችሁን አትጣሉ፡፡
ባለፈው እግዚአብሔር የሰጠንን የከበረ ሀብት እንዳንጥል የሚያሳስበንን ትምህርት መማራችን ይታወቃል፡፡ በትምህርታችን ወቅት እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠንን ስጦታ ዋናና አስፈላጊ ብለን ለሁለት መክፈላችንም አይረሳም፡፡ በተለይም ደግሞ መንፈሳዊ ሀብታችን ከሁሉም የላቀ ስለሆነ ስለ ምድራዊውና ስለ አስፈላጊው ስንል ሰማያዊውንና ዋና የሆነውን ባለጠግነት እንዳንጥል ፣ ቸልም እንዳንል የሚስተምረንን ትምህርት አብረን ተቋድሰናል፡፡ መንፈሳዊና ዋና ሀብት ከምንላቸው አንዱ መንፈሳዊ ብኩርናችን መሆኑን አይተን ነበር ያበቃነው፡፡ በዛሬው ትምህርታችን እንደምንመለከተው ደግሞ ትልቁ ሀብታችን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ስጦታ "ጸጋ" የተባለው ነው፡፡ ይህንን ጸጋ እንዳንጥል የሚያሳስበንን ትምህርት እነሆ!
የሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ አማኞች በጻፈው መልእክት የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም ይላል(ገላትያ 2፡21)፡፡ ሐዋሪያው በዚህ ክፍል ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት አስቀድመን መመልከቱ የተሻለ ነው፡፡ እርሱ የመጀመሪያውን ሓዋሪያዊ ሚስዮናዊ ጉዞውን በእስያ ባደረገበት ወቅት የወንጌሉ መልእክት ያተኮረው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ነበር፡፡ ደህንነት የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በጸጋ ብቻ ነው ብሎ በመስበክ በገላትያ አውራጃዎች ብዙዎችን ወደ ክርስቶስ በማመልከት ቤተክርስቲያን ተከለ፡፡ ከዚያ በኋላ ጳውሎስ ካስተማረው ወንጌል የተለየውን የሚሰብኩ ሌሎች ሰዎች ተነስተው ለደህንነት መልካም ሥራን መሥራት፣ ሕግን መጠበቅና መገረዝ ወዘተ ያስፈልጋል ብለው በማስተማር ምዕመናንን አሳቱአቸው፡፡ ጳውሎስ ከሰበከው የጸጋ ወንጌል ሌላ የተለየ መልእክት ያለው ወንጌል ሁሉ "ሌላ ወንጌል" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑትን እንዲያው ያድናቸዋል የሚል መልእክት ያለበት ወንጌል ደግሞ የጸጋ ወንጌል ነው፡፡ ይህ የጸጋ ወንጌል ደግሞ እኛ የዳንንበት ወንጌል ነው፡፡
ጸጋ ማለት ምሕረት ለማይገባው ኃጢአተኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚሰጥ የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ነው፡፡ ዋጋው በሰው አእምሮ የማይታሰብና የማይገመት ግን ከእግዚአብሔር ቸር ለጋስነት የተነሳ እንዲሁ በነጻ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ጸጋ በእኛ ሕይወት የሚያደርጋቸው ሁለት ታላላቅ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ደህነነትን ማስገኘቱ ሲሆን ሁለተኛው በምንኖረው ኑሮ የምናልፍባቸውን መንገዶችና ውጣ ውረዶችን ሁሉ ተቋቁመን እንድናልፍ ኃይልን ወይም ብቃትን ይሰጠናል፡፡ ወንጌላችንም የሚያመለክተው ደህንነት በሰው ሥራ ወይም በማንም መልካምነት ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እንግዲህ ሐሰተኞች የሚሰብኩት ሌላ ወንጌል ይህንን ጸጋ ዝቅ የሚያደርግ ፣ አማኞችም ቸል እንዲሉት የሚያደፋፍርና እውነትነት የሌለበት ነው፡፡
በገላትያ የኖሩ ሰዎች ጳውሎስ የሰበከውን የጸጋ ወንጌል ሰምተው በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ከተቀበሉ በኋላ የሐሰት አስተማሪዎችን ትምህርት በመስማታቸው ወደ ሌላው ወንጌል ትምህርት ዘወር ብለው ነበር፡፡ ይህም ማለት የእግዚአብሔርን ጸጋ ጣሉት ማለት ነው፡፡ በመልካም ሥራቸው ወይም በመገረዛቸው ወይም ሕግን በመጠበቃቸው ምክንያት ድነትን እናገኛለን በሚል በጸጋ ላይ የራሳቸውን ሥራ ሊያክሉበት ፈለጉ፡፡ እግዚአብሔር ለደህንነታችን መንገዱ እርሱ በልጁ በኢየሱስ በኩል የሰጠን ጸጋ እንዲሆን ያደረገው ደህንነት የሰው ርዳታ የማያስፈልው በጸጋ ብቻ የሚከናወን በመሆኑ ነው፡፡ የሰው ሥራ ለደህንነት የሚያስገኘው ትርፍ የለም፡፡ ይህም በመሆኑ ሐዋሪያው የገላትያ አማኞችን እንደገና የሚያሳስባቸው ይህን ነው፡፡ ማንም በራስ መልካምነትና ጥረት እድናለሁ ቢል እኔ ግን የዳንኩበትን የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም በማለት እውነቱን ይነግራቸዋል፡፡
የሐሰት አስተማሪዎች በገላትያ አውራጃዎች የሚገኙ አማኞችን ሌላ ወንጌል በመስበክ የእግዚአብሔርን ጸጋ አስጥሎአቸዋል፡፡ ከእውነተኛውም የደህንነት ትምህርት ዘወር እንዲሉ አድርጎአቸዋል፡፡ በዛሬውም ዘመን ይህ ዓይነት እንቅስቃሴ በቤተክርስቲያን በስፋት ይታያል፡፡ ሐሰተኞች አስተማሪዎች አማኞችን የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚያስጥሉአቸው በተለያዩ መንገዶች ነው ፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወንጌልን በሰበከበት ዘመን የነበሩ ሐሰተኞች እውነተኛውን ትምህርት በማጣመም ሲሆን በእኛ ዘመን ያሉት ደግሞ የተለያዩ የማሳሳቻ መንዶችን በመጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በአገራችን ሲሆን ያየነው ለዚህ በቂ ምሳሌ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነገረንና እኛም እንደተማርነው የሰውን ኃጢአት የሚያስወግድ በመስቀል ላይ የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ለመንፈሳዊ ሕይወት ለውጥ፣ ለኃጢአት መንጻት እና ለኑሮ ስኬት የተለያዩ ሳሙናዎች፣ የታሸጉ ውሃዎችና ዘይቶች እየተሸጡ መሆናቸውን ያየነውንና የሰማነውን ሁሉ አሳዝኖአል፡፡ የሣሙናና የዘይት ቸርቻሪዎች ይህንን መንገድ የመረጡት ብቸኛ የገቢ ማስገኛ እንደሆነ ስለገባቸው ነው፡፡ ችግሩ በእግዚአብሔር ስም ማድረጋቸው ነው እንጂ፡፡ ታላላቅ ሱፐር ማርኬት ያላቸው ሀብታም ነጋዴዎች ዓመት ሙሉ ቢሰሩ የማይሸጡትን ያህል ነጋዴ-ነቢያቶችችን በግማሽ ቀን ውስጥ ያጣሩታል፡፡ የአዲስ አባባውን ሚሊኒየም አዳራሽ የሞላ ሕዝብ አንዳንድ ዘይትና ሳሙና እንዲሁም የታሸገ ዉሃ ከገዛ ምን ያህል ሊሸጥ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ነጋዴ- ነቢያቱ የግል ሄሊኮፍተሮች ያሉአቸውኮ በጽድቅ ከሚያገለግሉ ከሌሎች አገልጋዮች ይልቅ የተለየ ቅባት ስላላቸው ሳይሆን የንግድ ብልሃታቸው የረቀቀ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከመንግሥት የንግድ ፈቃድ ያለው አንድ ነጋዴ በሚሊኒየም አዳራሽ ውሃና ዘይት እሸጣለሁ ቢል እንደ ነጋዴ- ነቢያቶቹ ሊሳካለት አይችልም፡፡ አንደኛ ውሃውን የሚገዛው የለም ፣የተለመደ ነውና፡፡ እንደሱ ዓይነት ዉሃ በሸሚሱ ሱቅ በቅርቡ ስላለ ማንም ያንን ለመግዛት ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ አይሄድም፡፡ ሁለተኛ ሰውዬው በነጋዴነቱ ስለሚታወቅ ለመንግሥት የሚከፍለው ግብር ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ነጋዴ- ነቢያቶቻችን ግን ውሃውን መንፈሳዊ ስያሜ በመስጠት መንፈሳዊ አድርገውታል፣ የማቅረቢያ ዕቃውም ከዚያኛው ይበልጥ ማራኪ ነው፡፡ እንደገናም በመንፈሳዊ ኮንፍራንስ ስም ስለሚደረግ የሚከፈል ምንም ግብርና ቀረጥ የለበትም፡፡ ይህ እንግዲህ እጅግ የሚያስገርም ነገር ነው፡፡ ለነገሩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሐይማኖትን ካባ ደርበው ሳይታወቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን መድረኮች ከወጡ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ አዎንታዊ ትንቢቶች የሚነገሩት ዳጎስ ያለ ገንዘብ በሚያስገኙ አካባቢዎች ከሆኑ ስንብተዋል፡፡ ይህ ገንዘብን ለማግኘት ሲሉ የሐሰት አስተማሪዎች የቀመሙት የውንብድና መንገድ ነው፡፡
አማኞች ግን የተማሩትንና የሰሙትን እውነት ወደ ጎን ትተው ከኃጢአታችሁ ምትታነጹበት ውሃና ሳሙና እንዲሁም ዘይት ይዤላችሁ መጥቻለሁ የሚለው አጭበርባሪ ያቀረባቸውን ጥሪ መቀበላቸው በጣም ያስገርማል ያሳዝናልም፡፡ ምዕመናን ብቻ ሳይሆኑ መሪዎችና አገልጋዮች ተብዬችም የዚህ ነገር ተባባሪዎች ሆነው መገኘታቸው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የሐሰት አስተማሪዎች በተጋበዙባቸው ቦታዎች ሁሉ ትኩረት እየተደረገ ያለው በሚያደርጉት ድንቃድንቅ እንጂ በሚያስተምሩት ትምህርት አለመሆኑ ብዙዎችን አሳስቷል፡፡ ምልክትና ድንቅ ሰይጣንም እንደሚያደርግና እንዲያውም በመጨረሻው ዘመን የተመረጠትንም እስክያስት ድረስ በታላቅ ታምራቶችን እንደሚታጀብ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ያስተምራል፡፡ የሐሰተኞች መለያ በሚያደርጉት ተአምራት ሳይሆን በዋናነት በሚያስተምሩት ትምህርት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ቤትም ሆነ ከአገር ውጭ ባሉ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የተሰበኩ ስብከቶች በዩ ቲዩብ በመለቀቃቸው ብዙ መልካም ትምህርቶች በአጭር ጊዜ በምድሪቱ ላይ በቀላሉ ሊሠራጩ ችለዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ነቢያት ተነስተዋል ፣ ድንቅም ናቸው፣ የሚያስገርሙ ናቸው ተብለው ከመድረክ የተቀረጸበት ፊልም ሲታይ የተናገሩት ሚስጥራዊ ነገሮችና ድንቃንቆች ናቸው እንጂ ስለደህንነት፣ ስለ አስተምህሮ ክርስቶስ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ ፣ ስለቅድስና፣ ስለ ትክክለኛ ክርስትና አኗኗር ወዘተ ምን እንዳስተማሩ አይታይም፡፡ ነቢያቶቹ ትምህርት የላቸውም ማለት ነው? ወይስ ከወንጌል አስተምሮተ- ስብከት ይልቅ በጣም አስፈላጊው ምልክትና ተአምራት ሆኖ ተገኝቶ ነው? ተአምራት የሚደረገው እኮ ሰዎች ለጸጋ ወንጌል መልእክት ልባቸውን እንዲከፍቱ ማድረግ እንጂ ያለ ወንጌል ትምህርት የሚደረግ ተአምር በራሱ የአገልግሎታችን ዓላማ አይደለም(የሐዋ 20፡30-31)፡፡ ሰዎችን ወደ ደህንነት የሚያመጠው እውነተኛ የወንጌል መልእክት እንጂ ተአምርና ምልክት አይደለም፡፡ ምዕመናንና የቤተክርስቲያን መሪዎች በእነዚህ እውነታዎች መካከል መለየት አለመቻላቸው እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ለምሳሌ ከኃጢአታችሁ ለመነንፃት ውሃና ሳሙና ግዙ የሚለውን ሰው አንተ የእግዚአብሔር ሰው ነህ ማለት ሳይሆን ሐሰተኛ ነህ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ቃሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻል ስለሚል(1ዮሐ 1፡9)፡፡ ሰው ከኃጢአቱ ለመንፃት ምንም ዋጋ መክፈል አያፈልገውም ምክንያቱም ደህንነትና መንጻት በነጻ ያለዋጋ ነውና( ኢሳ 55፡1-3)፡፡ በሕይወቱ ድካም ያለበትና የእግዚአብሔርን ርዳታ የሚፈልግ ማንም ቢኖር የነጋዴዎችን ዘይትና ውሃ መግዛት ሳይሆን በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳውን ጸጋ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ዙፋን ፊት በእምነት መቅረብ ይኖርበታል( ዕብ. 4፡14-16)፡፡ ይህ ጸጋ ብቻውን በቂ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ያልቻለውን የሚችል ምንም ዓይነት ሰው ሠራሽ ዘይትና ሳሙና የለም፡፡ የጸጋው ስፋት መሸፈን ያቃተውና በዘይት ፣ በሳሙናና በታሸጉ ውሃዎች የምንሸፍናቸው ቦታዎች የሉም፡፡ የአምላካችን ጸጋ ከየትኛውም አጥናፍና የምድር ስፋት ሁሉ ያለፈ ነው፡፡ የሰው ሥራም ሊስተካከለው አይችልም፡፡ ስለዚህ የሐሰት አስተማሪዎች በጳውሎስ ዘመን ብቻ ሳይሆን አሁን እኛ ባለንበት ዘመንም ቢሆን አማኞችን የእግዚአብሔርን ጸጋ እያስጣሉ መሆናቸውን በውል ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን ደህንነትን ያስገኝልናል፣ የሕይወት ውጣ ውረዶቻችንንም ሁሉ እንድናሽንፋቸው ያስችለናል፡፡ ደህንነትና ጽድቅ በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን ኤፌ 2፡8፣ ቲቶ 2፡11፣ ሮሜ 3፡23-24፣ሮሜ 5፡12-19፣ ገላትያ 216 ወዘተ መመልከት በቂ ነው፡፡ በሕይወታችን የሚገጥመውንም ፈተና በእግዚአብሔር ጸጋ እንደምናልፍ ቃሉ ያስተምረናል( 2 ቆሮንቶስ፡12፡7-10፣ዕብ 4፡14-16)፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ መከራ ሕመም ሲበዛን ያንን እንችለውና እንድናሸንፈው ፣ ጉልበታችን ሲዝል እንድንበረታ ያደርገናል፡፡ ሕይወታችን ሲቀዘቅዝ የሚያሞቀን ከመሆኑም በላይ፣ በወጀብና በአውሎ ነፋስ ውስጥ መርከብ ይሆነናል፡፡
ጳውሎስ የሥጋዬ መውጊያ የሚለው በሽታውን እንደሚሆን ብዙዎቻችን እንስማማበታለን፡፡ በሽታው ይህ ነው ብሎ በግልጽ ማስቀመጥ ባይቻልም ምናልባት በልስጥራና በደርቤ ወንጌልን በሚሰብክበት ወቅት የወንጌል ተቃዋሚዎች እስክዝለፈለፍ ድረስ በዱላ ሲደበድቡት ሰውነቱ ለመጥፎ የአካል ጉዳት ተጋልጦ ይሆናል( ሐዋ.13-14)፡፡ ወይም ደግም አይሁድ አንድ ሲጎዲል 40 ግርፈት አምስት ጊዜ በመግረፋቸው ምናልባት የነርቭ ችግር ገጥሞት ሊሆን ይችላል፡፡ወይም ደግሞ ወደ ደማስቆ ባቀናበት ወቅት ከሰማይ በታየው ታላቅ ብርሃን ምክንያት አይኑ እንደታወረበትና ቅርፍትም ከዓይኑ ላይ እንደወደቀ በሐዋ. 9 ላይ የምንመለከተው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የዓይን ሕመም ገጥሞት ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱ እንዲያውም ለገላትያ አማኞች በጸፈው መልእክት ቢቻልስ ዓይናችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ ( ገላትያ 415)፣እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደጻፍሁላች እዩ(ገላትያ 6፡14) ያለው ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛውም ይሁን ብቻ የእግዚአብሔር ፈውስ እንዲሆንለት ሦስት ጊዜ አምላኩን ሲለምን የአምላክ መልስ ግን "ጸጋዬ ይበቃሃል" የሚለው ሆነ፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ጳውሎስ ከሚፈልገው ፈውስ ይልቅ እጅግ የላቀ መሆኑን በዚህ መረዳት እንችላለን፡፡
እኛ በዚህ ምድር ላይ በመኖራችን ምክንያት የሚያታግሉን ብዙ ነገሮች እንዳሉብን በጣም ግልጽ ነው፡፡ በሚገጥሙን ሁሉ ግን ርዳታ እንፈልጋለን፡፡ እውነተኛ እርዳታ የሚገኘው ግን ከጌታ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ደግሞ በማናቸውም ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን የሚረዳንን ጸጋ እንደሚሰጠን የዕብራውያን ጸሐፊ ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ርዳታ በሚያስፈልገን በማናቸውም ጊዜያት የሚረዳንን ጸጋ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ፊት በእምነት መቅረብ እንዳለብን ቃሉ ያሳስበናል( ዕብ 4፡14-16)፡፡ የእግዚአብሔር ዙፋንም ደግሞ የጸጋ ዙፋን ነው፡፡
በዘመናችን ያሉ የሐሰት አሠራሮች በሥጋችንም በምንኖረው ሕይወት ሁሉ በእግዚአብሔር ጸጋ ከመደገፍ ይልቅ በሰዎች ድንቅና ምልክት ላይ አይናችንን እንድናኖር እያደረጉን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የፈውስን ስጦታ የሰጣቸው አገልጋዮች አሉ፡፡በእነርሱ በኩል በእውነት አስገራሚ አገልግሎት አየተሰጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር ታምራት የሚገልጠው በሰዎች በኩል ስለሆነ የሚጠቀምባቸው ብዙ ባሪያዎች ስላሉት ስሙን እንባርካለን፡፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ያለ እኛ መሥራት ይችላል፡፡ እኛ ግን ያለ እግዚአብሔር መሥራት አንችልም እንጂ፡፡ ይህም በመሆኑ ታምራትንና ድንቅን የሚያደርገውን ጌታና የእርሱን ጸጋ ከማሳየት ይልቅ አገልጋዮች በጣም አስደናቂ ሰዎች መሆናቸውን የሚያውጁና የሚያዳምቅላቸውን ደቀ መዛሙርት በየቦታው የሚያቆሙ ሐሰተኛ ነቢያቶችና ተከታዮቻቸው አማኞችን ጸጋን እያስጣሉ ናቸው፡፡
ከዚህም በላይ ነጋዴ-ነቢያቶቹ የልባቸውን ካደረሱና የሚበቃቸውን ያህል ከቀረቀቡ በኋላ ማንም ቢቃወመኝ እግዚአብሔር በሞት ይቀጣዋል ብለው ማስፈራራታቸው ሌላው አስቂኝ ነገር ነው፡፡ እሰቲ ተመለከቱ እግዚአብሔርን የራሳቸው ወታደር ወይም ልዩ የግል ጠባቂ/ body guard / ሲያደርጉት አያስገረምም? በጌታ አምኖ የዳነውን ታላቅ ሕዝብ በሞት ማስፈራራት እንዴት ያለ ስህተትና ድፍረት እንደሆነ ተመለክቶ እንዴት እንደዚህ ልትል ቻልክ የሚል የእግዚአብሔር ቤት ቅንዓት የሚበላው ሰው ምነው ጠፋሳ! የአፍሪካ አገሮችን አቋርጠው መጥተው ወደ ኢትዮጵያ ታላቁ ቤተ መንግሥትም ዘልቀው ገብተው ከአንጋፋ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝዋልና፣ ፎቶም አብረው ተነስተዋልና የተቀቡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው በማለት የሚያወሩላቸውን መለከት ነፍዎችን በየቦታው መሰየማቸውን ማየት ሌላው አስገራሚ ነገር ነው፡፡ ይህ ለመቀባታቸው መረጋገጫ ከሆነ ወደ ቤተ መንግሥት ያልገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ አገልጋዮቻችን ቅባቱጋ አልደረሱም ማለት ነው? እስከ አሁን ደረስ በቤተ መንግሥት የተስተናገዱት ኢቬሰተሮችና ዲያሰፖራዎች የተቀቡ እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው ማለት ነው? ወደ ቤተ መንግሥት የገቡ ኢትዮጵያውያን አገልጋዮችንስ ምነው አይናችን ያላያቸው? ወይስ የተቀቡ ለመባል እንደ እነ ቡሽሪ ሄሊኮፒተር ገዝተው ማሳየት ይኖርባቸዋል ማለት ነው ?
የእግዚአብሔር መንፈስ ታዛዥና ታማኝ የሆኑ አገልጋዮችን በመጠቀም የሚያስገርሙ የሥጋ ፈውሶችን ያደርጋል፡፡ በእርግጥ ማናቸውንም ሰዎች ለዚህ የተባረከ ሥራው መጠቀም ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን የሥራው ባለቤት ራሱ መንፈስ ቅዱስ እንጂ አገልጋዮቹ ስላይደሉ ክብርና ሙገሣንም ቢሆን ፈዋሽ ለሆነው ጌታ መስጠት እንጂ ሰዎችን ከጌታ በላይ ልናደርጋቸው አይገባም፡፡ በእውቀት ማነስ ምክንያት መጠነኛ ስህተት የሚፈጽሙ ቅን አገልጋዮችን መታገስ አስፈላጊ ነው፣ ምክንያቱም እንደነዚህ ዓይነቶች በምክርና በጤናማ ትምህርት እየተቃኑ ለትውልድ የሚጠቅሙ የጌታ አገልጋዮች ይሆናሉና፡፡ ስለ አገልጋዮቹ ግን እግዚአብሔርን እያመሰገንን በበለጠ ጌታን እያስከበሩና እንዲያገለግሉ ልንጸልይላቸው ይገባል፡፡ አንዳንድ በገንዘብ ጥቅምና በክብር የሚፈተኑ አገልጋዮች አልፎ አልፎ መታየታቸው ግልጽ ቢሆንም ክብሩን ግን ጌታ ብቻ መውሰድ እንዳለበት ራሳቸው ያውቃሉ፡፡ እነዚህ ከሐሰት አስተማሪዎች የተለዩ ናቸው፡፡
ሐሰተኞች ግን እንደዚህ አይደሉም፡፡ የሐሰተኞች ችግር የእውቀት ማነስ ሳይሆን ከራሳቸው ፍላጎትና አሳብ በስተ ኋላ በመሮጥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ወደማያስፈልግ መንፈሳዊ ልምምድ ውስጥ መክተት ነው፡፡ እነርሱ የፈለጉት ንዋይ፣ ክብርና ዝና ይገኝላቸው እንጂ ምዕመናን በእግዚአብሔር ነገር ይደጉ አይደጉ፣የሚሰበከው ወንጌል እውነት ይሁን ሐሰት ምንም ግድ የላቸውም፡፡ ይህንን አበጥረው ማወቅና መለየት ያለባቸው የቤተክርሰቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ሲሆኑ ምዕመናንም ቢሆኑ ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት ራሳቸውን በማስረከብ ከተሳሳት አሠራር መራቅ አለባቸው፡፡ ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ጸጋ የከበረ ሀብታችን ስለሆነ በእነዚህ በተሳሳቱ አሠራሮች ምክንያት እንዳንጥለው እንጠንቀቅ፡፡ የከበረውን ጸጋችሁን አት
ጣሉ!

No comments:

Post a Comment