አንድ በጣም አድርጌ የምወደው በጌታ የተወደደ ወንድሜ ስለ እርሳስ አንድ የሚያስገርም ምሳሌ አጫወተኝ፡፡ ስሙ ዶር ይርጋለም ይባላል፡፡ እንዲህ ነው ምሳሌው፡፡ እርሳስ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ወደ ሥራ ከመሰማራቱ በፊት ወደ ሠሪው ይሄድና ምክር ሰጠኝ አለው፡፡ የእርሳስ ሠሪውም ምክር በመጠየቁ እጅግ በጣም ተደሰተና አምስት ወሳኝ የሆኑ ምክሮችን ሰጠው፡፡ አንደኛ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ከውጭ ማንነትህ ይልቅ ለውስጥ ማነትህ ዋጋ ስጥ፡፡ እንግዲህ እርሳስን እርሳስ የሚያደርገው የውጭ ያለው እየተቀረጸ የሚጣለው አካል ሳይሆን የውስጠኛው ሊድ የምትባለዋ ነች፡፡ ስለዚህ እርሳስ ምን ጊዜም ለዚህ በጣም ተፈላጊ ለሆነው ለውስጥ ነገሩ ዋጋ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛ፡ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ሊጠቀምብህ በሚችል ሰው እጅ ላይ ውደቅ አለው፡፡ ይህ ለእርሳስ ትልቅ ምክር ነው፡፡ እርሳሱ የከበረውን ሥራ ሠራ ማለት የሚቻለው በማን እጅ ላይ እንደወደቀ ሲታወቅ ነው፡፡ እንደነ ኢንጂነር እና የህክምና ባለሙያ ወይም የሕንጻ ዲዛይነር ወይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ፣ ወይም የዓለም ሎሬት በሆነ ሰዓሊ በመሳሰሉት ሰዎች እጅ የገባ እርሳስ የሚሠራው የላቀና ከፍ ያለ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እርሳስ በከሰል ችርቻሪ እጅ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በለማኝም እጅ ሊወድቅ ይችላል፡፡ አንዳንዴም ደግሞ የተጭበረበሩ የብር ኖቶችን በሚሠሩ ሰዎች እጅም ልወድቅ ይችላል፡፡ የሥራውም ሁኔታና ክብር የዚያውኑ ያህል ልዩነት አለው ማለት ነው፡፡ ሦስተኛ፡ በሕይወትህ ዘመን ሥራህን ስትሠራ ድካም ሊገጥምህ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን በፍፁም ተስፋ አትቁረጥ ነገር ግን በድካምህ ሊያግዝህና ኃይልህ እንዲታደስ የሚያደርግ ከፊት ለፊትህ አንድ ኃይል አለና እርሱ እንዲያድስህ ፈቃደኛ ሁን፡፡ እንግዲህ እርሳስ በባሕሪይው ከመሥራት የሚደለዱምበት ሁኔታ አለ፡፡ ተጠቃሚው በመቅረጫ ይቀርጸውና እንደ አዲስ መሥራት ይጀምራል ማለት ነው፡፡ አራተኛ፡ ተግባርህን በሚታከናውንበት ጊዜ ስህተት ልትፈጥር ትችላለህ፡፡ ስህትት ስለፈጠርክ አትጠቅምም ማለት አይደለም፡፡ ስህተትህን የሚያርምልህና የሚያስተካከልልህ ሌላ ኃይል ከኋላህ በኩል ተገጥሞልሃልና ሲያርምህ ለመታረም ፈቃደኛ ሁን፡፡ ይህ ደግሞ ላጲሱ መሆኑ ነው፡፡ በእርሳስ የሚሠራው ሥራ እንዲታረም ሲፈለግ ያ ያልተፈለገው በኩል በላጲሱ ይነሳና የተፈለገው እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ አምስተኛ፡ የትም ቦታ ብትሆን በሄድክበት ሁሉ የማንነትህን አሻራ አሳርፍ፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው; እርሳስ የማይጽፍበት ቦታ የለም፡፡ በድንጋይ ላይ፣ በወረቀት ላይ፣ በጣውላ ላይ፣ በጨርቅ ላይ ፣ በግድግዳ ላይ፣ በቆርቆሮ ላይ፣ ከውሃ በቀር በማንኛው ነገር ላይ ጽፎ ያልፋልና ይህንን ነው እንግዲህ የሕይወት ዘመን በየትኛውም ቦታ የማንነትህ አሻራ አሳርፍ የተባለው፡፡
ስለ እርሳሱ የሚነገረው ምሳሌያዊ አባባል ይሁን እንጂ ትልቅ መንፈሳዊ ቁም ነገር ያለበት ትምህርት ነው፡፡ እስቲ ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ አምስተኛውን ብቻ መዝዘን እናውጣና የዛሬውን ውይይታችን በዚያ ዙሪያ እናውጠንጥን፡፡ በየትኛውም ሥፍራ ብትሆን የማንነትህን አሻራ አሳርፍ የሚለውን! ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በየሄድንበት ቦታ ሁሉና ባገኘናቸው ሁሉ ላይ የማንነታችንን አሻራ ማሳረፍ እንደሚገባን የሚያሳስበን አሳብ ነው፡፡ የማንነትን አሻራ ማሳረፍ ስንል የጽድቅን ተጽዕኖ ማምጣት ማለታችን እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ክርስትናችን ራሱ የጽድቅን ተጽዕኖ የማምጣት እምነት እንጂ እንዲሁ ባህል ወይም ልማድ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፣ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ ሲለን በጨለመው ዓለም ላይ ብርሃን የመሆን ተጽዕኖ በመራሪቱ ምድርም ላይ ተገኝታች የምታጣፍጡ ናችሁ እያለን እንደሆነ ለማንም ግለጽ ነው፡፡ ብርሃን ሲመጣ ጨለማው ሳይወድ የግዱን ሥፍራ ይለቃል፣ የት እንደሚገባም አይታወቅም፡፡ ብርሃን ሁለት ታላቅ ባሕሪያት አሉት፡፡ አንደኛው ማሳየቱ ሲሆን ሁለተኛው መታየቱ ነው፡፡ ብርሃን ካልታየ ማሳየት አይችልም፡፡ ሲታይ ግን እንደ ብርሃነቱ እንጂ እንደሌላ ሆኖ ከታየ ማሳየት ያቅተዋል፡፡ በኣማኞች ሕይወት የሚጎድለን ብርሃን መሆን ነው፡፡ ለማሳየት እንጣደፋለን እንጂ በብርሃንነታችን የመታየት አቅም ግን የለንም፡፡ ጨውም ቢሆን ወደ መረረው ቦታ ሁሉ እየገባ ያጣፍጣል፡፡ ከጎመን ጋር ጎመን አይሆንም፡፡ የጎመንን ሕይወት ግን ይለውጠዋል፡፡ ከሥጋ ጋር ሥጋ አይሆንም ነገር ግን በሥጋ ውስጥ ገብቶ የሥጋን ጣዕም ይቀይረዋል፣በውስጡ ያለውንም ጀርም ይገድልለታል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ክርስቲያኖች ምድርን ለማጣፈጥ እጥራለን ግን ማጣፈጥ የሚያቅተን ከምድሩ ሥርዓት ጋር የተመሳሰልንና የተቀያየጥን እንደሆነ ነው፡፡
እንግዲህ በለንበት ሥፍራና በምንኖርበት ጊዜ ሁሉ የማንነታችንን ኣሻራ ማሳረፍና የጽድቅን ተጽዕኖ ለማምጣተት ይገባናል ፡፡ የቀደሙት አባቶቻችንን ታሪክ በምንመለከትበት ወቅት በዙሪያቸው ባሉት ሁሉ ላይ ተጸእኖ በማምጣት የማንነታቸውን አሻራ አሳርፈዋል፡፡ እኛም እንደዚሁ ሆነን እንድናልፍ እግዚአብሔር ይፈልጋል፡፡ አማኞች በታላላቆችና በታናናሾቻችን ላይ እንዴት አድርገን የማንንታችንን አሻራ ማሳረፍ እንደሚገባን ከእግዚአብሔር ቃል እንመለከታለንለ፡፡ ለዚህም አሳባችን መሠረት የሚሆነን ሓዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በወንጌል ለወለደው ልጁ ለጢሞቴዎስ የጻፈው መልእክት ነው፡፡ እስቲ 2ኛ ጢሞቴዎስን ምዕራፍ አንድ ቁጥር አንድ እሰከ ሰባት ያለውን ክፍል እንመልከት፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚሆን የሕይወት ተስፋ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ። ስለዚህ ምክንያት፥ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፥ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ(2ኛ ጢሞ.1፡1-6)።
1. በንጹህ ህልና እግዚአብሔርን ማምለክ
እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹህ ህልና የማመልከውን እግዚአብሔር አመሰግናለሁ፡፡ ከንባብ ክፍላችን እንደምንማረው በሌሎች ላይ የጽድቅን ተጽዕኖ ለመምጣት ከሚያስችለን ባሕሪያት አንዱ በንጹህ ህልና እግዚአብሔርን ማምለክ ነው( ቁ 3)፡፡ ንጹህ ሕልና ማለት ያልቆሸሸ፣ እድፈት የሌለበት ፣ በኃጢአትና በበደል ምክንያት ከሚመጣበት ክስ ነጻ የሆነ ህልና ማለት ነው፡፡ ጳውሎስ በንጹህ ህሊና አምላኩን እንዲያመልክ በጎ ተጽዕኖ ተደርጎበታል፡፡ ሐዋሪያው ይህንን ማለፊያ የአምልኮ ሕይወት የተማረውና የለመደው ከእርሱ በፊት ከነበሩ አባቶቹመሆ የነጠረ እውነት ነው፡፡ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹህ ህልና የማመልከውን እግዚአብሔር አመሰግናለሁ ይላል፡፡ የቀደሙት አባቶች አምላካቸውን እግዚአብሔርን በንጹሕ ህልና በማምለካቸው በሚከተሉአቸው እንደነጳውሎስ ባሉ ላይ የጽድቅን ተጸዕኖ አሳድረዋል፡፡ እነዚህ በጳውሎስ ላይ የማንታቸውን አሻራ ያሳረፉት የቀደሙት አባቶቻችን እነማን እንደሆኑ የንባብ ክፍላችን በግልጽ ባይነግረንም ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እንደሚሉት እነአብርሃም፣ እንደነይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ ፣ ሄኖክ፣ ኖሕ፣ ዳዊት፣ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እንደሚያምኑት የቀደሙት ነቢያቶች በተለይም መጻሕፍትን ያልጸፉ ግን ታላቅ የእግዚአብሔርን ሥራ የሠሩ(Non classical prophets) የሚባሉት እንደ ኤልያስና ኤልሳ ወይም እንደነኖሕና እንደነሄኖክ ያሉ ነቢያት ወይም ደግሞ መጻሕፍትን የጻፉ(classical prophets) የሚባሉ እንደነኢሳያስ፣ ኤርምያስ፣ ዳንኤል፣ሕዝቅኤል፣ዮናስ፣እንባቆም ወዘተ የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነርሱ ብቻ ሳይሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋሪያት እነ ዮሐንስ፣ ጴጥሮስ፣ያዕቆብ፣ስምዖን፣ፊልጶስ፣ ቤርተሜሎስ፣ ቶማስ ፣ እልፍዮስ ወዘተ እና ከእነርሱ አልፎ ደግሞ እንደነ እስጥፋኖስ፣ ባርናባስ የመሳሰሉ በእምነታቸው ጳውሎስን የቀደሙት ሁሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ የሆነ ሆኖ ጳውሎስ አባቶቼ የሚላቸው ማናቸውም ይሁኑ ማን ባለውለታው ናቸው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔርን በንጹህ ህልና እንዲያመልክ በእርሱ ላይ የማንታቸውን አሻራ አሳርፈው አልፈዋልና፡፡ አምላኬን በንጹህ ሕልና አመልከዋለሁ እንዲል አድርገውታል፡፡ በብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን የነበሩ እንዳደረጉት ሁሉ በታማኝነት በንፁህ ህልና አምላኩን አገልግሏል፡፡ ጳውሎስ አገልግሎቱን ጨርሶ ወደሚወደው ጌታ በሚሄድበት ጊዜ ሕልናውን የሚከሰው ነገር የለውም ማለት ነው፡፡ አምላኩን ሲያመልከውም ሆነ ሲያገለግለው እንደ አባቶቹ አድርጎ በንጹህ ህልና በታማኝነት ስለሆነ ማንም ሊከሰውና ሊነቅፍበት አይችልም ማለት ነው፡፡
እኛም በዘመናችን ከእኛ በኋላ የሚመጡ ሰዎች አምላካቸውን በንጹሕ ህልና እንዲያመልኩ የሚያደርግ ማንነት ይኖረን ይሆን? ሰዎች ከፊታቸው ያለውን እየተመለከቱ ርምጃቸውን የወሰን ባሕሪይ አላቸው፡፡ የቀደመውንም እያዩ እንደዚያው ለመሆን ራሳቸውን ያዘጋጃሉ ይሆኑታልም፡፡ በቤተ ክርስቲያንም እንደዚሁ ነው፡፡ መሪዎቹ ወይም አገልጋዩቹ ወይም በእምነት ነገር የቀደሙት ሰዎች የሚሉትን ማለትና የሚሆኑትን መሆን ግዴታቸው ይሆናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን በንጹህ ህልና እናምልክና ትውልዳችን ለእግዚአብሔር መንግሥት እናዘጋጅ፡፡
2. የእምባ ሕይወት
እምባህን አይቼ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ፡፡ በሌሎች ላይ የጽድቅን ተጸዕኖ የምናመጣበት ሁለተኛው መንገድ የእምባ ሕይወት ነው፡፡ የእምባ ሕይወት በመኖር በጳውሎስ ላይ የጽድቅን ተጽዕኖ ያመጣው ሌላው ሰው ጳውሎስ ራሱ በወንጌል የወለደው ልጁ ጢሞቴዎስ ነው፡፡ ይህ በጣም አስደናቂ የሆነ የሕይወት ምሳሌነት ነው፡፡ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ፣ የክርስትና ሕይወትና አኗኗር ያስተማረው ፣ ያሰለጠነው፣ መንፈሳዊ አባቱና በመጋቢነት አገልግሎትም የሾመው መሪው ነው፡፡ እንዲህም ቢሆን ታናሹ ጢሞቴዎስ በታላቁና በእምነት አባቱ በጳውሎስ ላይ የማነቱን አሻራ አሳረፈ፡፡ ሐዋሪያው ይህንን መልእክት በሚጽፍበት ወቅት በሮም እሥር ቤት እንዳለ ይታወቃል፡፡ የሮም መንግሥት እሥረኛ መሆን ብቻ ሳይሆን በቅርብ ጊዜ እንደሚሰዋ በመንፈስ ተረድቷል(2 ጢሞ.4፡)፡፡ በዚህን ጊዜ በእንደዚያ ባለ እሥር ቤት ላለ ሰው አጽናኝና ልቡን የሚደግፍ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ሥራ አብረው በሠሩባቸው በቀደሙት ወራት የጢሞቴዎስን እምባ ሕይወት እያየ ሲደሰት ስለኖረ በእሥር ቤትም ሆኖ ያንኑን የየጢሞቴዎስን እምባ ደግሞ ለማየት ይናፍቅ ነበር፡፡ ጢሞቴዎስ ደግሞ ከሌሎች የጳውሎስ የወንጌል አጋሮች የሚለይባቸው መንገዶች ነበሩ፡፡ ከሁላቸውም ይልቅ ልጅ እርሱ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ጳውሎስ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው እያለ ያጽናነዋል(1ጢሞ 4፡12)፡፡
አይናፋርና ፈሪ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሐዋሪያው በእኔ በእሥረኛው አትፈር ይለዋል( 2ጢሞ.1፡8)፡፡ ጳውሎስ በሌላ ቦታም ለቆሮንቶሰ አማኞች ሲናገር ጢሞቴዎስ ወደ የመጣ እንደሆነ በእናንተ ዘንድ ያለፍርሃተ እንዲኖር ተጠንቀቁ፣ እንደ እኔም ደግሞ የጌታን ሥራ ይሠራልና ማንም አይናቀው(1ቆሮ.1፡10) ያለውም ጢሞቴዎስ በእምነቱና በአገልግሎቱ ምክንያት የሚደረስበትን ተቃውሞ ስለሚፈራ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በሕመምም የሚጠቃው ከሌሎች ይልቅ እርሱ በመሆኑ ስለ በሽታህና ስለ ሆድህ ሕመም ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ ወደ ፊት ውሃ ብቻ አትጠጣ እያለ ይመክረው ነበር(1 ጢሞ 5፡23)፡፡ ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስ ከድከሙ በላይ ጳውሎስን የሚያጓጓ ፣ መንፈሳዊ ሕይወት ጥራት ያለው ሰው ሆኖ ተገኘ፡፡ ያው የእምባ ሕይወት ነው፡፡ ለምን እንደሚያነባ ባናውቅም ለአገልግሎቱ፣ በጨለማ ስላሉ ሰዎች ሕይወት፣ የእግዚአብሔርን ሥራ አብረው ስለሚሠሩ እንደነጳውሎሰ ላሉ ሰዎች ሊሆን እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም፡፡ ያንን ደግሞ ጳውሎስ ያውቅ ስለነበር እምባህን አይቼ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ አለ፡፡
ሐዋሪያው ራሱ በእምባ የማገልገልን ሕይወት የተለመደ ሰው ስለነበር ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን አማኞች የሚናገረው ይህንን ነው፡፡ ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ በትህትና ሁሉና በእምባ ከአይሁድ በደረሰ ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ እንዴት እንደኖርሁ እናንተ ታውቃላችሁ( ሐዋ.20፡19) ይል ነበር፡፡ እርሱ ከኤፌሶን አማኞች ጋር ሲኖር ከሳያቸው የሐዋሪያዊ ባሕሪያት አንዱ የትህትናና የእምባ ሕይወቱ ነው፡፡ ታላቅ ሥራ ከሠሩ ሰዎች ጋር አብሮ የእምባ ሕይወት እንዳለ መዘንጋት የለብንም፡፡ ጳውሎስ አማኞችን የሚመክረውና የሚገስጸውም በእምባ ነው( ሐዋ.20፡31) ይህንን አገልግሎቱን የለመዱ አማኞች እርሱ ትቶአቸው መከራ ለመቀበል በመንፈስ ታሥሮ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱን አልተው ባላቸው ጊዜ አንገቱን አቅፈው እያሳሙ ያለቅሱ እንደ ነበርም በቁ 37-38 እንመለከታን፡፡ እምባ በልባችን ካለን ፍቅርና ሸክም የተነሳ የሚመነጭ ነው፡፡ የማስመሰል እምባ በየጊዜው ሊፈስስ አይችልምና በጢሞቴዎስና በሌሎች አገልጋዮች የሚታየው እምባ በልብ ውስጥ ስለ ነፍሳት የምንቦገቦገውን የፍቅር ትኩሳት ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ ጢሞቴዎስ ጳውሎስ ወደነበረበት እሥር ቤት ቢመጣ ሁለቱ በእምባ ሊገናኙ እንደሚችሉ ጳውሎስ እርግጠኛ ስለሆነ እምባህን ሳይ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ አለ፡፡ ጳውሎስ ራሱ ደግሞ ስለ ጢሞቴዎስ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ሸክም ነበረው፡፡ በክፍሉ እንደምንመለከተው ቀንና ሌሊት ሳያቋርጥ ስለ እርሱ ይጸልይ ነበር፡፡ ይህ ማሳሰብ የሚለው ቃል አቤቱታ ስለ ማቅረብ ከእምባና ከመወትወት ጋር ስለሌላ ሰው በአንድ ወሳኝ አካል ፊት መቆምን የሚያመለክት ነው፡፡ ስለ አንተ ወደ እግዚአብሔር አቤት እላለሁ ብሎ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ያነሳሳዋል፡፡
ዛሬም ቢሆን የእምባ ሕይወት ያስፈልገናል፡፡ እኛ የቀደሙንን አባቶቻችንን ፣ መሪዎቻችንን፣ አገልጋዮቻችንን ልባቸውን ልናሳርፍ የምንችለው በእምባ ሕይወት ነው፡፡ በታላላቅ አባቶቻችን ሕይወት የጽድቅን ጫና ለመፍጠር የምንችለው በሚረባውና በማይረባው እነርሱን በመከራከር ሳይሆን ፍቅርን በተሞላ ሕይወት በእግዚአብሔር ፊት በእምባ ስንማልድላቸውና እነርሱም ያንን ሲያዩ ነው፡፡ ጢሞቴዎስ የእምባ ሰው መሆኑን ራሱ ጳውሎስ እንደመሰከረው ሁሉ በወንጌል የወለዱንን አባቶቻችንና መሪዎቻችን እምባችንንና የአምባችንን ፍሬ አይተው ደስ እየተሰኙ ከሆነ የጽድቅን ተፅእኖ አሳድረንባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ታላቁን የእግዚአብሔር ሥራ መሥራት የምንችለው በእምባ ነው፡፡ የእምባ ሕይወት ባለበት ደስታ አለ፡፡ የእምባ ሰዎች በበዙበት ሥፍራ ራዕይ አለ፡፡ የመከራውን ብዛት አሽንፈው ለመውጣት አባቶቻችንና እናቶቻችን ሌትና ቀን አልቅሰዋል፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ በቤተ ክርስቲያናት ላይ የተዘረጋውን 17 ዓመት የመከራ ዘመን ገፍፎ ለመጣል ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት መራር ልቅሶ በማልቀስ እምባቸውን አፍስሰዋል፤ እግዚአብሔርም የእምባቸውን አልከለከላቸውምና ታላቅ ድልን ሰጣቸው፣ የመከራውን ጥቁር ማጋረጃ ቀድዶ ወደ ሰፊ ሜዳ አወጣቸው፡፡ ስለዚህ ከፊት ከኋላ ባሉት ሁሉ ላይ የጸድቅን ጫና ለማሳደር የእምባ ሰዎች እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
3. ግብዝነት የሌለበት እምነት
አሁንም በሕይወቱ ጳውሎስን ያስደነቀው ጢሞቴዎስ ነው፡፡ እርሱ የኖረበት ሕይወት ለዛሬ አማኞችና አገልጋዮች ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ በጳውሎስና በጢሞቴዎስ መካከል ምን ዓይነት ፍቅር እንዳለ የሚያመለክት ነው፡፡ ሓዋሪያው በእሥር ቤት ሆኖ አሁንም ጢሞቴዎስን እንደሚያስበው ይናገራል፡፡ ባነበብነው ክፍል ደጋግሞ አስብሃለሁ እያለ ይደጋግማል፡፡ በቁ.3፣4፣ ላይ አስብሃለሁ እያለ ይናገር አንደ ነበር አሁንም እንደገና በቁ. 5 ላይ አስብሃለሁ ይለዋል፡፡ ጢሞቴዎስ የኖረበት ሕይወት ከጳውሎስ ልብና አእምሮ በማይጠፋ መልኩ ታትሟ ማለት ነው፡፡ በጢሞቴዎስ ሕይወት ጳውሎስ ያየውና በእሥር ቤት እንኳ ሆኖ እስክያስበው ድረስ ተጽእኖ ያሰደረበት የሕይወት ጥራቱ ከሆኑት አንዱ እውነተኛ እምነቱ ነው፡፡ ይህንን ጳውሎስ ግብዝነት የሌለበት እምነት ይለዋል፡፡ ግብዝነት ማለት ያልሆኑትን መሆን ማለት ነው፡፡ የሚናገሩት ቃልና የሚኖሩት ሕይወት ሳይገናኝ ሲቀር፣የውስጥ ማንነትና የውጭ ገጽታ የተቃረነ፣ የማስመሰል ሕይወት ግብዝነት እንለዋለን፡፡ ግብዝነት ጌታ ኢየሱስ እጅግ አጠንክሮ ከተቃወማቸው የፈርሳውያን ኃጢአቶች አንዱ ፣ በዘመናችንም ብዙ አገልጋዮችን ጠልፎ እየጣለ ያለ በጉልህ ያላየነው በጣም መጥፎ ኃጢአት ነው፡፡ ታዲያ ጢሞቴዎስ ያልሆነውን እንደሆነ ፣ የሆነውንም እንዳልሆነ አድርጎ ሳያስመስል እውነተኛና ግብዝነት ያልነካካውን ሕይወት በመኖር በጳውሎስ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደረ የእምነት ጀግና ነበር፡፡
እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጣር
በ1988 ዓ.ም. ገዳማ በናዝሬትና በደብረ ዘይት የሚገኙ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲናት ከአፍሪካን ኢቫንጄሊስትክ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባባር በሁለቱም ከተሞች ባሉ ስታዲየሞች አንድ ሰፋ ያለ የወንጌል ሥርጭት
ኮንፈራንስ አካሂደው ነበር፡፡ በዚያ ኮንፈራስ ወደ 710 ሰዎች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ሲቀበሉ ከህመማቸው የተፈወሱና
ከአጋንንት አሥራት የተፈቱ ሁሉ ስለነበሩ ጊዜው ጌታን አመስግነናል፡፡ ይህ ፕሮግራም ካለፈ ከቀናት በኃላ ስለ ፕሮግራሙ በሰፊው የዘገበው
አንድ ክርስቲያን ጋዜጣ በፊት ለፍት ገጹ ላይ በትልቁ በናዝሬት ስታዲየም ታላቅ የወንጌል
ሥርጭት ኮንፍራንስ ተካሄደ ፣ አጋንንትም ከናዝሬት ጓዙን ጠቅልሎ ወጣ፡፡ የሚል ርዕስ ይዞ ታተመ፡፡ ያ ጋዜጣ ስለ ተካሄደው ኮንፍረንስ
የዘገባቸው ብዙ አሳቦች ያሉት ቢሆንም ውስጡ ስነበብ ግን አጋንንት እንዴት አድርጎ ጓዙን ጠቅልሎ ከናዝሬት እንደወጣ የሚናገር አንድም
አረፍተ ነገር አልነበረበትም፡፡ የተሰጠው ርዕስና በውስጡ ያለው አሳብ የማይገናኙ ነበሩ፡፡ ይህ እንግዲህ ለማንም የማይጠቅም ነው፡፡ ዛሬ ብዙ የቤተርስቲያን አገልጋዮች በአገራችንም ሆነ እዚህ እንደምናየው የሰውን ትኩረት ለመሳብ ሲባል በጌታ ስም ያልሆኑትን ነገሮች እያደረግን እገኛለን፡፡ ይህ የግብዝነት ሕይወት ለማንም አይጠቅምም፣ በተለይም እግዚአብሔርን አያስከብርም፡፡
ጢሞቴዎስ ይህንን ግብዝነት የሌለበትን እምነት እንዴት ነው ያገኘው የሚለው ደግሞ አንዱ የትምህርታችን አካል ነው፡፡ እርሱ ጳውሎስ ላይ ያንን መንፈሳዊ ተጽእኖ ያመጣው በሌሎች ተጽእኖ ስለተደረገበት ነው፡፡ በእርሱ ላይ ተጽዕኖ ያደረጉበት እናቱና አያቱ ናቸው፡፡ ይህ እነደሆነም ጳውሎስ ያወቀው እርሱ በገላትያ አውራጃዎች ወንጌልን በሰበከበት ጊዜ ይህንን ቤተሰብ አገልግሏል፡፡ እንዲያውም ሎይድን ኤውንቄን ወደ ክርስቶስ የመራቸው ከነባርናባስ ጋር ወደ ገላትያ ባደረገው የመጀመሪያው የሐዋሪያዊው የወንጌል ጉዞ ራሱ ጳውሎስ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ሴቶች በእርግጥ የብሉይ ኪዳን እውነተኛ ሴቶች ከሆኑት መካካል ሳይቆጠሩም አይቀሩም፡፡ ጢሞቴዎስ አሕዛብ የሆነ አባቱ ከሞተ በኃላ ያደገውና የኖረው ከእነዚህ እግዚአብሔርን ከሚወዱና እምነታቸው እውነተኛና ቀጥተኛ ከሆነው፣ ግብዝነትም ከማይታይባቸው አይሁዳዊ ሴቶች ጋር ነው፡፡ ስለዚህ አያቱና እናቱ በእርሱ ላይ በጎ ተጽእኖ አሳድረውበታል፡፡ ይህንን ነው ጳውሎስ በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነት አስባለሁ የሚለው፡፡ ጢሞቴዎስ በልጅነቱ እውነተኛ እምነትን ተቀብሏል፣ ተለማምዶታልም፡፡ ከእናቱና ከአያቱ ማስመሰል የሌለበትን ንጹህ የእምነት ኑሮ ለመኖር በሚችልበት ተቀርጾ አደገ፡፡ እንዲያውም ከልጅነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጸሕፍትን በማወቅ አድጓል(2ጢሞ.3፡15)
ሎይድና ኤውንቄ ጥልቅና የተትረፈረፈ የእምነትን ውርስ ለጢሞቴዎስ ስላስረከቡት፣ ግብዝነት የማይታይበትና እንደነጳውሎስ ያሉትንም የሚያስገርም ክርስትያናዊ አኗኗር እንዲለማመድ ስላደረጉት ስማቸው በቅዱሳት መጸሕፍት ይኸው እየተዘከረ ይኖራል፡፡ ዛሬ አገልጋዮች፣ መጋቢያን ሽማግሌዎች የምንኖረው ሕይወትና የሚናገለገለው አገልግሎት ምን ይመስላለል;; በግብዝነት የተበከለ፣ ለእግዚአብሔር ክብር የማያመጣ የሚናገለግለቸውንም ሰዎች የማያንጽ እንዲያውም የሚያስተስተዛዝብ ይሆን; በምንም ሁኔታ ብንሆን እግዚአብሔር የሚደሰትበትና በሌሎች ላይ በጎ ጫና ለመፍጠር የሚያስችለን ሕይወት ግብዝነት የሌለበት ነው፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ ፍቅራችሁ ያለግብዝነት ይሁን የሚለው፡፡
ጢሞቴዎስ ይህንን ግብዝነት የሌለበትን እምነት እንዴት ነው ያገኘው የሚለው ደግሞ አንዱ የትምህርታችን አካል ነው፡፡ እርሱ ጳውሎስ ላይ ያንን መንፈሳዊ ተጽእኖ ያመጣው በሌሎች ተጽእኖ ስለተደረገበት ነው፡፡ በእርሱ ላይ ተጽዕኖ ያደረጉበት እናቱና አያቱ ናቸው፡፡ ይህ እነደሆነም ጳውሎስ ያወቀው እርሱ በገላትያ አውራጃዎች ወንጌልን በሰበከበት ጊዜ ይህንን ቤተሰብ አገልግሏል፡፡ እንዲያውም ሎይድን ኤውንቄን ወደ ክርስቶስ የመራቸው ከነባርናባስ ጋር ወደ ገላትያ ባደረገው የመጀመሪያው የሐዋሪያዊው የወንጌል ጉዞ ራሱ ጳውሎስ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ሴቶች በእርግጥ የብሉይ ኪዳን እውነተኛ ሴቶች ከሆኑት መካካል ሳይቆጠሩም አይቀሩም፡፡ ጢሞቴዎስ አሕዛብ የሆነ አባቱ ከሞተ በኃላ ያደገውና የኖረው ከእነዚህ እግዚአብሔርን ከሚወዱና እምነታቸው እውነተኛና ቀጥተኛ ከሆነው፣ ግብዝነትም ከማይታይባቸው አይሁዳዊ ሴቶች ጋር ነው፡፡ ስለዚህ አያቱና እናቱ በእርሱ ላይ በጎ ተጽእኖ አሳድረውበታል፡፡ ይህንን ነው ጳውሎስ በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነት አስባለሁ የሚለው፡፡ ጢሞቴዎስ በልጅነቱ እውነተኛ እምነትን ተቀብሏል፣ ተለማምዶታልም፡፡ ከእናቱና ከአያቱ ማስመሰል የሌለበትን ንጹህ የእምነት ኑሮ ለመኖር በሚችልበት ተቀርጾ አደገ፡፡ እንዲያውም ከልጅነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጸሕፍትን በማወቅ አድጓል(2ጢሞ.3፡15)
ሎይድና ኤውንቄ ጥልቅና የተትረፈረፈ የእምነትን ውርስ ለጢሞቴዎስ ስላስረከቡት፣ ግብዝነት የማይታይበትና እንደነጳውሎስ ያሉትንም የሚያስገርም ክርስትያናዊ አኗኗር እንዲለማመድ ስላደረጉት ስማቸው በቅዱሳት መጸሕፍት ይኸው እየተዘከረ ይኖራል፡፡ ዛሬ አገልጋዮች፣ መጋቢያን ሽማግሌዎች የምንኖረው ሕይወትና የሚናገለገለው አገልግሎት ምን ይመስላለል;; በግብዝነት የተበከለ፣ ለእግዚአብሔር ክብር የማያመጣ የሚናገለግለቸውንም ሰዎች የማያንጽ እንዲያውም የሚያስተስተዛዝብ ይሆን; በምንም ሁኔታ ብንሆን እግዚአብሔር የሚደሰትበትና በሌሎች ላይ በጎ ጫና ለመፍጠር የሚያስችለን ሕይወት ግብዝነት የሌለበት ነው፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ ፍቅራችሁ ያለግብዝነት ይሁን የሚለው፡፡
4. ሰዎችን ለአገልግሎት ማነሳሳትና ማበረታታት
በዚህ ምክንያት እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለው የእግዚአብሔርን ሥጦታ እንድታነሳሳ አሳስብሃለሁ(ቁ.6)፡፡ ጳውሎስ ጠሞቴዎስን ለወንጌል አገልግሎት ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር የሰጠውን የጸጋ ስጦታን እንዲያነሳሳ ይመክረዋል ያደፋፍረዋልም፡፡ በሰዎች ያለውን ስጦታ የምናነሳሳው በእነርሱ አገልግሎት ሌሎች እንዲጠቀሙበት ነው፡፡ የአንድ ሰው ስጦታ የሚገለጠው ያ ሰው በአገልግሎት በተሰማራበት ሁኔታና አውድ መሠረት ነው፡፡ አገልግሎት ከሌለ የጸጋ ስጦታን ማየት አይቻልም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በውስጡ እግዚአብሔር የሰጠው ስጦታ አለ፡፡ ያንን ስጦታ አውጥቶ እንዲጠቀምበት የወገኖች ማበረታታት እጅግ በጣም አስፈጊ ነው፡፡ መቼም ጢሞቴዎስ በሕይወቱ የሆነለትን የጳውሎስን ድጋፍ የሚረሳው አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ጳውሎስ እርሱ ብቻ ማበረታታት ሳይሆን ሌሎችም ጢሞቴዎስን እንዲቀበሉ አድርጓል፡፡ እጁንም በመጫን እግዚአብሔር የሰጠውን ስጦታ እንዲነሳሳ አበረታታቷል፡፡ ጢሞቴዎስ ከእግዚአብሔር የአገልግሎትን የጸጋ ስጦታ ከተቀበለ በኋላ ምናልባት ጳውሎስ እጁን እስከሚጭንበት ጊዜ ድረስ በአይናፋርነቱና በፍርሃቱ ምክንያት ከአገልግሎት ቦዝኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ በአንተ ያውን የእግዚአብሔርን ስጦታ አነሳሳ እያለ እጁን እንደጫነበት ይናገራል፡፡ ምክንያቱም በአንድ ሰው ላይ እጅን መጫን የሌለውን የጸጋ ስጦታ የሚያስገኝ ሳይሆን ከእግዚአብሔር መንፈሳዊ ሥልጣን የተሰጣት ቤተ ክርስቲያን ስጦታው የተሰጠውን ሰው ለአገልግሎት ማሰማራቷንና መረጋገጫና እውቅና መስጠቷ የሚያሳይ ነው፡፡ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጸጋ ስጦታ ባይሰጠውም ያለውን ስጦታ እንዲጠቀምበት ያነቃቃው እጁን በመጫን ነው፡፡ እጅን በሰው ላይ መጫን በዛሬው ጊዜ ተራና ማንም ሳይገባውም ሳይገባውም የሚያደርገው ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ቃል ትምህርት መሠረት ግን እጅግ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉም ያለበት ነው፡፡
ዛሬ ቤተክርስቲያንን እግዚአብሔር በጸጋው የተቀቡ ልጆችን በመስጠት ባርኮአታል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ልነቃቁ ይገባቸዋል፡፡ አንዳንዶች የሚያነሳሳቸውንም ይፈልጉ ይሆናል፡፡ እንደነጢሞቴዎስ ያሉ ብዙ ድካም ያለባቸው ግን ደግሞ በእግዚአብሔር ጸጋ የተሞሉ ድፍረትንም ያላገኙ ይኖሩ ይሆናል፡፡ ፀጋቸውን ሰዎች ያላዩላቸው ፣ ድካማቸው ብቻ እየታየላቸው እንደነጳውሎስ ኣይነት ተመልካች ያጡ ይኖሩ ይሆናል፡፡ እነዚህን እይዞአችሁ፣ በርቱ እትፍሩ ፣ እያልን ካስፈለገ እጃችንንም ቢሆን እየጫንንባቸው ለመንግሥቱ ሥራ ድፍረት እንዲያገኙ ማድረግ ይገባናል፡፡ ምናልባት በቤታችን ያላነሳሳናቸው ሆነው ሳናውቃቸው አፈትለከው በሄዱበት ሌሎት ፈጥነው እጃቸውን በመጫን እዚያው የቀሩአቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነርሱስ እያገለገሉ ናቸው ግን በአጠገባችን ያሉትን ብናበረታታቸው በእነርሱ ላይ የሚናመጣው መንፈሳዊ ጫና እጅግ ታላቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እውነተኛ እምነትና የአገልግሎት ጥሪ ያላቸውን ሌሎች ልዩ ልዩ ታለንት ያላቻውን ለእግዚአብሔር መንግሥት እንዲጠቅሙ በማድረግ ሲናነሳሳቸው የጽድቅን ተጽዕኖ እናመጣለን ፣የማነታችንም አሻራ አሳርፈንባቸው እናልፋለን ማለት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment