Friday, February 5, 2016

ቤተ ክርስቲያን ጉበኛ ትሁን፣ ዘብም ትቁም

                                   
    
                                                   Pastor Samuel Shonga 
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጊዜያት የግብረሰዶማዊነትና የውርጃን አደገኛ አካሄድና የዓለም ሕዝቦች የሚያሳዩትን አቀባበል አስመልክቶ መጠነኛ ውይይቶች እንዳደረግን ይታወሳል፡፡ የዛሬውን አያርገውና ከብዙ ዓመታት በፊት በአገራችን ፈርሃ- እግዚአብሔር ሰፍኖ ስለነበር አንድ ሰው በዝሙት ኃጢአት ወድቆ እንደሆነ በመራራ ልቅሶ በህዝበ ክርስቲያን ፊት ቆሞ ንስሐ እንደሚገባና እንደዚያ አይነት ኃጢአት በጣም አንገት የሚያስደፋ እንደሆነ ትዝ ይለናል፡፡ የግብረሰዶማዊነት ጉዳይ በሃይማኖቱ ጎራ ያሉትን ብቻ ሳይሆን የሰማውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይዘገንንውና ይቀፈው እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር እንቀደላል እየተወሰደ መጣ፡፡ ምዕራባውያን ይህንን ልምምድ ሥራዬ ብለው ከተያያዙት በጣም ሰንብቷል፡፡ የጀመሩት ከፊቺና ከውርጃ ነው፡፡ ከዚያ ወደ ግብረሰዶማዊነት እያሉ አሁን ደግሞ ከእንስሳ ጋር ወደ መተኛትና የመጋባት ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎአቸው ከዛፍ ጋር መጋባት ጀምረዋል፡፡ እኛ እንደምናየው የዓለም ሥልጣኔ ቁንጮዎቹ እነዚህ አገራት ሲሆኑ ከጋብቻ ጋር በተገኛኘ የሚያደርጉት ሥልጣኔ ነው ማለት ይቻል ይሁን? እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ አገሮች የምዕራባውያንን ልምምድ ሁሉ እንደ ሥልጣኔ ከወሰድን ከእንስሳና ከዛፍ ጋር ጋብቻ ወደ መመሥረቱ መሸጋገራችን ይቀራል ብላችሁ ታስባላችሁ? 
ለምሳሌ ያህል አርጄንቲናዊው ሪቻርድ ቶሬ .. . ዲሰምቤር 11 ቀን 2013 ላይ ድል ባለ ድግስና በቃል ኪዳን ሥነ ሥርዓት በወንዝ ዳር ከቆመ ትልቅ ዛፍ ጋር የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን መፈጸሙን የሰማና ያየ ሁሉ ተገርሟል፡፡ ቶሬ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን ሲፈጽም ብዙ ታዳሚዎች፣ ሚኒስክርት የለበሱ ሴቶች ሚዜዎች፣ ወንድ ሚዜዎች፣ አበባ በታኝ ልጆች፣ የካሜራ ባለሙያዎችና ሌሎችም ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ የሚያምር ነጭ ሙሉ ልብስና አሬንጓዴ ባርኔጣ አድርጎ ከወደደው እንጨት ጋር ጋብቻውን የፈጸመው ቶሬ
በአስፈጻሚዎቹ አማካይነት ከፍቅረኛው ዛፍ ጋር የጋብቻ ቃል ኪዳን ከፈጸመ በኃላ ቀለበትም አድርጓል፡፡ በእድምተኞቹ ፊት ዛፉን እወድሻሁ በማለት አቅፎ ከሳመና ከላሰ በኃላ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችንም ጋብዟል፡፡ የቶረ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ በፈረንጅ አገር ሰው ለሰው ከሚደረገው ሠርጎች የሚበልጥ እንጂ የላነሰ ሕዝብ የተገኘበት ነው፡፡ ይህንን ላየና ለሰማ እውነተኛ ክርስትያን ሁሉ ሰይጣን በረቀቀ መንገድ እየሠራ መሆኑ በደንብ ይገባዋል፡፡
ከጋብቻ ጋር በተያያዘ የሻሮን ታንድሌር ጋብቻ ሌላው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ፎክስ የተሰኘ በአሜሪካ ዜና አዋጅ ነጋሪ ... ጃንዋሪ 3 2006 የአሶሺየትድ ፕሬስን ጠቅሶ እንደዘገበው 41ዓመቷ እንግሊዛዊቷ ቱጃር ሻሮን ታንድሌር በታህሳስ ወር 2005 ከዶልፊን ጋር ጋብቻዋን የፈጸመችው የሚያምር ቬሎ አድርጋ የሙሽራውን ጉንጭ ደጋግማ በመሳም ነው፡፡ ከጋብቻዋ በፊት 15 ዓመታት ያህል ከዶልፊኑ ጋር ፍቅረኛው ሆና የኖረችው ታንድሌር ከማንም ፍቅረኛ ይልቅ ካንዲን እወደዋለሁ ብላለች፡፡ ካንዲ የዶልፊኑ ወይም የባሏ ስም ነው፡፡ ታዲያ ታንደሌር አንድ ቀን ያልጠበቀችው ነገር ገጠማት፡፡ ከፍቅረኛዋ( ከባልዋ) ካንዲ ከተባለው ዶልፊን ጋር ለመዋኘት ከገባችበት ባህር ውስጥ ሳትመለስ በዚያው ፍጸሜዋ ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው ክቡር ጋብቻ ምን ያህል እየረከሰ እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ እኛ ባለንበት ዘመን የሰው ልጅ በከፍተኛ ውድቀት ውስጥ እንዳለ ለማሳየት ይህ ብቻ በቂ ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶች አሳፋሪና አሳዛኝ የሆኑ፣ የሰው ልጆች ውድቀቶችን መስማት ተራ ነገር እየሆነ መጥቷል፡፡
እንግዲህ ይህንን የሚመስሉ ብዙ አስነዋሪና አሳሪ ልምምዶች አደጉ በሚባሉ አገሮች እየሆነ ነው፡፡ ዛሬ ወንድ ከወንድ ጋር ለመጋባት የተነሳው የመብት ጥያቄ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቷል፡፡ ግብረሰዶማውያኑም በይፋ ጋብቻቸው ከማካሄዳቸውም በላይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰተት ብለው ገብተው ግራ እያጋቡን ነው፡፡ በአገራችንም በሆን ሕጋዊ ፈቃድ አያግኝ እንጂ የግብረሰዶማውያን ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ሕጋዊ ፈቃድም ይሰጠን ለማለት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ከእንስሳት ፍቅር የያዛቸው አንዳንድ ምዕራባውያን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሕጋዊ ፈቃድ ቢጠይቁ የመብት ጥያቄአቸው የሚነፈግ ይመስለን ይሆን? ከተፈቀደስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላይመጡ ነው? በኢትዮጵያስ ይህ እንዳይታይ ለመዋጋትና ለመከላከል ጉበኛ የሚሆን ይኖር ይሆን? የፓለቲካው ዓለም የቱንም ቢበይን ምንም ማድረግ አንችልም፣ ግን አብያተ ክርስያናት ምን ቢያደርጉ ይበጃል? አቤት ድማው ዳገት እንዴት ይታለፍ ይሁን? ቤተክርስቲያንም እየመጣባት ያለው ወራሪ ኃይል ለመመከት ከአሁኑኑ ትጥቋን መዘጋጀት፣ ጉበኞቿንም ማሰለፍ ካልቻለች ወደ ጥልቅ ማጥ ውስጥ ልትዘፈቅ ትችላለች፡፡
የሆነ ሆኖ አሁን በአገራችን አግጥጦ ከመጣብን ከውርጃ አንጸር እግዚአብሔር አምላክ በቃሉ ምን መመሪያ ሰጠ ከሚለው እንጀምርና ወደ ሌሎች ጉዳዮች እንሸጋገራለን፡፡ ነገር ግን ቤተ ከርስቲያን በቂ መሰናዶ እንዳታደርግ በርካታ መሰነናከሎች አሉባት፡፡ እነዚያ መሰናክሎች ምንድናቸው? የሚለውን ብናስቅድም ማለፊያ ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡ ስለዚህ እነሆ፡
1. የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ማነስ፡፡
እምነት ከእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ሁሉ ጥፋትም ቃሉን ካለማወቅ የሚመጣ አደጋ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ትምህርት ጠንክራ ማስተማር ይኖርባታል፡፡ ሰውን ነጻ የሚያወጣው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ብቻ ነው፡፡ እውነት አርነት ያወጣል፡፡ ይህ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡ አሁን ያለብን ትልቅ ችግር የእግዚአብሔር ቃል በየቦታው እየተጣሰ ነው፡፡ ቅዱስ ቃሉን ችላ ማለት የውድቀት ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ ቤተ ክርሰቲያን በሰንብት ትምህርት ቤት በሥልጠና ፕሮግራሞች፣ በእሁድ አምልኮዎች ቃሉን በጥልቀት ማስተማር ይገባታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አዳዲስ አማኞች የክትትል ትምህርት ከተማሩ በኋላ በቀጣዩ ደግሞ ጠንከር ወዳለው ትምህርት ገብተው መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚመግቡበት የሰንብት ትምህርት ቤት ፕሮግራም የሌላቸው ቤተ ክርስቲያናት ብዙ ናቸው፡፡ መንጋው ትምህርት አለ ወደተባለው ሁሉ ይሄድና ይቀላውጣል፡፡ ከደፈረሰውም ኩሬ ጠጥቶ ጠግቦ ይመጣል፡፡ ስለዚህ የኃጢአትና የጽድቅ ልዩነት የማይገባቸው ብዙ ናቸው፡፡ ኃጢአት ማለት ዝሙት መፈጸም እንጂ ያለ ዝሙት ሌላው ኃጢአት ያለም የማይመስላቸው ጥቂት አይደሉም ፡፡ ይህ ሁሉ ያለማስተማር ውጤት በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ካልሰጠች ትልቅ ችግር ይገጥማታል ብሎ ለመናገር ፍርሃት አያስፈልግም፡፡ 
2. በራዦችን አለማጥራት፡፡
የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምሩ ጥቂት ሰዎችና በትምህርት ላይ የሚያተኩሩ አብያተ ክርስያናት አሉ፡፡ ነገር ግን የሚበርዙና የሚሸቅጡ ደግሞ ተበራክተዋል፡፡ ብረዛና ሽቀጣ በእውነተኛው ትምህርት ላይ የቆሸሸውን በመቀላቀል የትምህርቱን ንጽሕና ማደፍረስ ሲሆን ይህንን ለይቶ ማጥራት ጊዜንም የሚወስድ ዋጋንም የሚያስወጣ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን በምን አደከመኝ ሰበብ ዝም ትለዋለች፡፡ አንዳንድ መሪዎች ደግሞ ቃሉን መማር እንደ ስህተት ይቆጥራሉ፡፡ የወንጌል ቃል የተሸቀጠው ትላልቅ ስም በምንሰጣው ሰዎች በትላልቅ ቤተ ክርስቲያናት መድረክና በሚዲያውችም ጭምር ነው፡፡ አንድ ጊዜ በነበርኩበት ቤተ ክርስቲያን አንድ ጌታ ይጠቀምበታል ሲባል የነበረ ሰው በሳምንታዊ ፕሮግራማችን ላይ እንዲሰብክ እድል ተሰጠው፡፡ ታዲያ መድረክ ላይ ወጥቶ ቃሉን መግለጥ ትቶ የባጥ የቋጡን ሲዘላብድ ከሚሰሙ አድማጮች አንዱ በትንሽ ብጣሽ ወረቀት "ወንድሜ ሆይ ለምን ቃሉን አታነብልንም" ብሎ በልጆች በኩል ላከለት፡፡ ሰባኪውም ወረቀቷን ከተጠቀለለችበት ዘርግቶ አነበበና እንዲህ አለ፡፡ "በጣም ትገርማለችሁ አሁን እኔን ቃሉን አይሰብክም ለማለት ፈልጋችሁ ነው አይደለም፡፡ እንዲያውም ከእግዲህ ወዲህ በእግዚአብሔር መንፈስ ሆነን ጌታ የሚነግረን ከአእምሮአችን ስለምንሰብክ መጽሐፍ ቅዱስ አያስፈልገንም፡፡ እስቲ የገባው አንድ ሰው ጮሆ አሜን ይበል" አለ፡፡ ጉባኤውም በከፍተኛ ድምጽ "አሜን" አለለት፡፡ ከዚያም ሌሎች መሰል ነገሮችን እየተናገረ "እስቲ የገባው አንድ ሰው ጮሆ አሜን ይበል" እያለ አሜንም እያስባለ ቃሉን እንደማይጠቅም አድርጎ ወረደ፡፡ ግን እኮ እንዲሰብክ የተጠራው ቃሉን ነነበር፡፡ ይህን ሰው ማናገር ነበረብኝና ሳናግረው የሰጠኝ መልስ እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡ እንዲህ አለኝ "ይህን በመናገሬ ነገ መድረክ ብትከለክለኝ ሄጄ የምሰብክበት ብዙ በር ተከፍቶልኛል፡፡ ይህንን አድርግ ያንን አትበል ልትለኝ አትችልም፣ እኔ የጌታ መንፈስ እንደሚመረኝ አደርጋለሁ"ብሎ ከብሮዬ ወጥቶ መሄዱን አስታውሳለሁ፡፡ እንዳለውም እርሱ በሌሎች መድረኮች ተመሳሳይ ነገሮችን እያደረገ ቀጠለ፡፡ ይህ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ልምምድ ብቻ አይደለም፡፡ በብዙ ቦታዎች የሚታየው ነገር ተመሳሳይ ነው፡፡ ቃሉ የተበረዘው በስብከት ብቻ ሳይሆን በመዝሙር በኩል፣ በጸሎት ሁሉ ስህተቶች እየተላለፉ ናቸው፡፡ ብዙ የተሳሳተ መልእክት ያላቸው መዝሙሮች በአብየተ ክርስቲያናት እየተመሩ ናቸው፡፡ ሰዎች የሚጸልዩትን አንዳንድ የጸሎት ቋንቋዎችን ልብ ብለን ስንሰማ የተሳሳተ አንዳንዱ ጭራሽ የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋፋ ነው፡፡ ብዙ የስህተት ትንቢቶች ተላልፈዋል፡፡ ሁሉንም በጅምላ አሜን ብለን እቀበላለን እንጂ እንደ እግዚአብሔር ቃል መመርመርና መለየት ያኔ ድሮ ቀርቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንዚህን በራዥና ሸቃጭ መልእከቶችን የመለየት ልምዷን ከአሁኑኑ ማዳበር ይኖርባታል፡፡
3. የእምነት አቋምን አለማክበር፡፡ 
ይህ ያልታወቀ የቤተክርሰቲያን እንቅፋት ነው፡፡ አንዲት ቤተ ክርሰቲያን ግልጽ የሆነ የእምነት አቋም ሊኖራት ይገባል፡፡ መምአእመነናነን አገለልገጋየዮቸችነና መሪዎች ያንን የእምነት አቋም ጠንቅቀው ማወቅ ማክበርና ማስከበር አለባቸው፡፡ የአንዲት በቤተ ክርስቲያን መታወቂያዋ እምነቷ ነው፡፡ እምነቷን የጣለች ቤተ ክርስቲያን የማንነት ቀውስ identity crisis ውስጥ የተዘፈቀችና ለሌላው የምታስወርሰው ቅርስ heritage የሌላት ናት፡፡ ብዙ አማኞች የቤተ ክርስቲያናቸውን የእምነት አቋም አያውቁም፡፡ አማኞች አለማወቃቸው አስጨናቂ ላይሆን ይችላል ምክንየያቱም ካስተማሩአቸው ይረዱታል፡፡ ነገር ግን ከወንጌውያንና ከሙሉ ጊዜ አገልጋዮች መካካል የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን እምነት ጠንቅቀው የማያውቁ መኖራቸው ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ወንጌላውያን በራሳቸው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ቆመው የእምነት አቋማቸውን የሚያፈርስ መልእክት ሲያስተላልፉ ተሳስተሃል ብሎ የሚያርም የለም፡፡ ይህ አንዱ ችግር ነው፡፡ በጴንጤቆስጣዊ እምነት እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነው የጌታ ራት ማለት የኢየሱስ ሥጋ ደም ነው የሚሉ ወይም ሥጋውን እንበላለን ደሙንም እንጠጣለን የሚሉ አገልጋዮች ብታገኙቸው ታዝናላችሁ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ማለት በልሳን መጸለይ ማለት ነው የሚል የመጥመቃውን ወንጌላዊ ቢገጥመን እናዝናለን፡፡ የተጋዲሶ እምነት ተከታይ ወይም ካልቪናዊ ሆኖ የአንድ ሰው ደህንነት በአንድ ቀን ሀጢአት ምክንያት ይጠፋል ሲል ብትሰሙት በጣም አድርጋችሁ ትተክዛላችሁ፡፡ ግን እየሆነ ያለው ሐቅ ይህ ነው፡፡ እነዚህ እንግዲህ በመቀላቀላችን ምክንያት ከአንዱ ወደ ሌላው እየተወራረሱ የመጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ የእድሜ ልክ ትሥሥር ነው የሚለው የእምነት አቋም የሁሉም ቤተ እምነት መሆን አለበት፡፡ ከዚህም ጋር አያይዞ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ሰው ለሰው ብቻ የሚደረግ መሆኑን በቤተ ክርስቲያን እምነት አንቀጽ ውስጥ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ያለዚያ ነገ ቤተ ክርስቲያን የዜጎችን መብት ተጋፋች ተብላ ልትክሰስ ትችላለች፡፡ አማኞችም አስቀድመው የእምነት አቋማቸው መቀበላቸው መረጋገጥ አለበት፡፡
4. ወንጌልን ለተሳሳተ ዓላማ መጠቀሚያ ማድረግ፡፡ 
አበዛኛዎቹ ቤተ ክርስቲያናት የሚከፈቱት የእግዚአብሔርን መንግሥት ከማስፋፋት ዓላማ አንጻር ሳይሆን ከራስ ክብርና ጥቅም አንጻር ነው፡፡ ካለምንም አንቱ የሚባሉበትና ግብር የማይከፈልበት ዳጎስ ያለ ገቢ ማግኛ መንገድ ቤተ ክርስስቲያን መክፈት ነው፡፡ ነገር ግን እውነተናዋ ቤተ ክርስተቲያን የምታደርገው ሁሉም ለአባላት መታነጽና ለወንጌል መስፋፋት ይሁን፡፡ የብዙ እምነት እንቅስቃሴዎች የብልጽግና ውላጅ በመሆናቸው ስለ ጽድቅ ኑሮ አይገዳቸውም፡፡ የኃጢአትንም አደገኛ ፍጻሜ ለምእመናን አያሳዩም ፡፡ የምንጠለጠሉት ኪሱ በሞላውና እጁን በሚከፍት ሰው ላይ ብቻ ነው፡፡ ማንም ሰው የሐሰትን ትምህርት ቢያስተምርና እውነትን ባይናገር ሰው ከሳቀና ሞቅ ብሎት አሥራቱን ከሰጠ መጋቢዎቹ ስለሌላው ነገር አይገዳቸውም፣ አይሞቃቸውም፣ አይበርዳቸውምም፡፡ በአሜሪካን አገር አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን የምንሰበሰብበት በአንድ የኢትዮጵያውን ቤተ ክርስቲያን ደጋግመው የሚሰብኩ ሰው ነበሩ፡፡ ትምህርታቸውና ስብከታቸው በፍጹም መጽኸፍ ቅዱስ የሚያውቀው አይደለም ግን ፓሰተሩ እኒህ ከወንጌላውያን ቤተ ክርስቲናት እምነት ጋር የማይጣጣም አቋም ያላቸውን እንዲያውም የሐሰት እምነት ውስጥ ያሉ ሰው እየመጡ እንዲሰብኩ የሚያደርጋቸው ለምንድነው ፣ስህተታቸውንስ ለምን አያርምም የሚል ጥያቄ ነበረን፡፡ ግን እኒህ ሰው የሚያመጡት ትምህርት ሕዝቡን እንዲጠቅም ሳይሆን ሰውዬው ለፓስተሩ እጅ የሚከፍቱለት ሰው ስለሆኑና ፓስተሩም ይህም በመሆኑ ማንም ምንም ቢሰማ ለእምዕመኑ ግድ የሌለው እንደሆነ ታወቀና ዝም ተባለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ልምምድ በብዙ ቦታዎች ያለ ሲሆን ቤተ ክርስቲያናችን የእምነቷ ዳርና ድንበሩ እስከ የት እንደሆነ የማይታወቅ አድርጎአታል፡፡ ስለዚህ በብዙ ቦታዎች ለስብከት የተጋበዘው ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ከመስበኩ በፊት የጋበዘውን ፓስተር አስቀድሞ መካብና ስለ እርሱ በምዕመናኑ ፊት ብዙ መናገር ይጠበቅበታል፡፡ የስብከቱን ሩብ ሰዓት ያህል ተጠቅሞ ፓሰተሩን ማወደስ ከፍ ከፍ ማድረግ ያልሠራውንም ሁሉ እንደሠራ አድርጎ ወደ ሰማይ መስቀል የይኖርበታል፡፡ አብረውትያሉ ምእመናን ስለፓስተራቸው ከሀ እስከ ያውቃሉ ግን ለቀባሪው አረዱት ዓይነቱ እንግዳ ሰባኪ ደግሞ ሰሱ በቤት ምዕመኑ የማያውቁትን ምስጥር ስለ ፓስተሩ ይተነትናል፡፡ ካልሆነ ደግሞ በሚቀጥለው እርሱ በተራው በሮችን በመዝጋት ይበቀላል፡፡ ስለዚህ እርስ በርሳቸው በሕዝብ ፊት ይካካባሉ፡፡ ሁሉም ነገር በአንድ ፓስተር አእምሮ የሚወሰንባት ቤተ ክርስቲያንና በውስጧ ያሉ ምእመናን እጅግ በጣም የሚያሳኑ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ለፓስተሩ ይመቸው እንጂ ሌላ ጉዳይ አይመለከተውምና፡፡ ስለዚህ ሽማግሌዎች ኖረው የሚተላለፈው መልእክት ለወንጌል አገልግሎትና ለመንጋው መታነጽ ምን ያህል ጠቀመ የሚለውን መመዘንና አስቸኳይ የእርምት እርምጃ መውሰድ አለባቸው፡፡ 
5. የአብያተ ክርስቲያናት መለያየት ፡፡
ቤተ እምነቶች አንድ መሆን ይገባቸዋል፡፡ መቼም ቢሆን በኢትዮጵያ ያሉ ወንጌላውያን አማኞች አንድ ቤተ ክርሰቲያን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ግን የጋራ እምነት አላቸው፡፡ ስለዚህ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ አንድ ድምጽ ማሰማት ይኖርባቸዋል፡፡ ግብረሰዶማውያን የመብት ጥያቄ ቢያነሱና ቢፈቀድላቸው ውድቀቱ የአንድ ቤተ እምነት ብቻ ሳይሆን የሁሉ ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በሚፈጠረው ችግር ሊጎዳ ይችላል፡፡ ግብረሰዶምነት ኃጢአት የሚሆነው ለመጥመቃውያን፣ ለሜቶዲሰቶች፣ ወይም ለእርቶዶክሶች፣ ወይም ለካቶሎኮች ወይም ለወንጌል አማኞች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም የጋራ ፎረም ሊመሠርቱና የጋራ ችግራቸውን በጋራ መመከት ያስፈልጋል፡፡ ወራሪ በፍጥነት እየገሰገሰ እያዩና እየሰሙ ዝም ማለት ባለአደራነትን ችላ እንደደመባል ተቆጥሮ በምእመናንና የእረኞች አለቃ በሆነው ጌታ እንዳያስጠይቀን ያስፈራል፡፡ እባካችሁ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለእውነትነና ለፍትህ ለሰዎች ልጆች ሞራል እና ሰብአዊ መብት መጮኽ የሚገባት የመጀመሪያዋ ኤጄንት በምድር ላይ ያለችዋ እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲን ነች፡፡ ቤተ ክርስያን ዝም ካለች፣ አውሬው መንጋውን የቀራመተዋል፡፡ ለጥቁሮች መብት የታገሉ ማርቲን ሉተር ክንግ የአንዲት አሜሪካ ወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ዋና መጋቢ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ድምጸቸውን እያሰሙ ያሉት እነ ፈራንክሊን ግርሃምና እነ ጆን ማክርተር ወንጌል ሰባኪዎችና የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች ናቸው፡፡ እነ ዴዝ ሞን ቱቱ በአፍረካ የፖለቲካውን ትኩረት ቢስቡም የቤተ ክርስቲያን ሰባኪዎች ናቸው፡፡ የክርስያቲን አገር ናት በተባለችው ኢትዮጵያም እምነት መሪዎች ለእምነታቸው ጠባቂ፣ ለሕዝባቸው አለኝታና ለድምጽ አላባዎች ድምጽ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ የወንጌል አንዱ አካል ነውና፡፡ እንመለስበታል


No comments:

Post a Comment