Thursday, April 6, 2017

እንጀራው


በዚህ ሳምንት እኔና ውድ ባለቤቴ የወር አስቤዛችንን ( ቀለባችንን ማለቴ ነው) ለመሸማመት ከመኖሪያ ቦታችን ትንሽ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ገበያ አዳራሽ ሄድን፡፡ የገበያ ቦታው ሜድቴራኒያን ፉድ ማርኬት Mediterranean food market ተብሎ የሚጠራ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከሌሎች ገበያ አዳራሾች ሁሉ ይልቅ ይኸኛውን አዘውትረው የሚጎብኙበት ትልቁ ምክንያት የአበሻ ምግብ ለመሥራት የሚያስችሉ ቅመማቅመሞች በየዓይነቱ ስለሚገኙበት ነው፡፡ ለምሳሌ ፡ በርበሬ፣ ኮረርማ፣ እርድ፣ ቀረፋ ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ምጥምጣ፣ ቡና፣ ወዘተ ሁሉም በየዓይነቱ ይሸጥበታል፡፡ ቅመሞቹ በትናንሽ ብልቃጦች እየታሸጉ በላያቸው ላይ ምንነታቸውን የሚያሳይ ጽሑፍና መለያ ቁጥር ከታተመባቸው በኋላ በተመደበላቸው መደርደሪያ ላይ በተርታ ተደርድረው ይገኛሉ፡፡ እንዲያው ባንገዛቸውም እንኳን እነዚያን ማየት ለዓይን ምግብ ነው፡፡ ታዲያ በአገር ቤት ሳለን እንደነበረው በትንሽ ብር ፌስታል ሞልቶ መመለስ ያለ እንዳይመስለን አደራ፡፡ በአንዲት ትንሽ ብልቃጥ የታሸገችው በርበሬ ዋጋ አይቶ በአገራችን ገንዘብ ካሰሉት ዋጋው ያስደነግጣል፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር ለመግዛት ሲታሰብ በአገር ቤቱ ገንዘብ ማስላት አይታሰብም፣ ማስላቱም ተገቢ አይደለም፡፡ 
የአሜሪካኖች ምግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልታሰበ ቦርጭ እያሸከመ ስለሚያስቸግር ከዚህ ሁሉ እዳ ውድም ቢሆን የአገራችንን ምግብ ለምን አልበላውም በሚል እዚህ አገር ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ሽሮና እንጀራ ተለይቶን አያውቅም፡፡ ለታናሽ ልጃችን ፌቬን ደግሞ የአሜሪካኖች ምግብ ተመራጭ ብቻ ሳይሆን ከተመራጭ በላይ ነው፡፡ አልፈ አልፎ እንገዛላታለን እኛም የምንቀማምሰው በእርሷ ምክንያት ነው፡፡ ከፈቀድንላትማ ያለ እርሱ ባትበላ ደስታውን አትችለውም፡፡ እውነት መናገር ይሻላል የአሜሪካኖች ምግብ ሲጣፍጥ አይጣል ነው፡፡ ቢሆንም የሽሮን ውለታ መርሳት ጥሩ አይደለም ብለን ስለመከርናት እግዘር ይስጣትና እሺ ብላ ከእኛ ጋር የአበሻውን ምግብ በሥነሥርዓት እየበላችው ነው፡፡ ከምግብ ሁሉ ታማኝና ባለውለታችን ሽሮ ነው፡፡ መሸለም ቢያስፈልግ በመጀመሪያው የክብር መዳሊያ መጥለቅ ያለበት በሽሮ አንገት ነው፡፡ አንድም ቀን ሰልችቶን አያውቅን ፣ እኛም አንሰለቸውም፡፡ ይኸውና ሽሮአችን ባሕር ተሸግሮ በመምጣት የተለመደ አገልግሎቱን እየሰጠን ነው፡፡ ባለቤቴ ተዋበች ሌላ ማንኛውንም ምግብ ብትበላ እንጀራ ካልቀመሰች የሆነ ነገር የሚጎድልባት ይመስላታል፡፡ በፌቬንና በእርሷ መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ እኔ ባለቤቴን አልፌ አልፎ እመክራታለሁ፡፡ ታበዥዋለሽ እላታለሁ፡፡ እምቢ ስትለኝ “ቃሉ ሁሉንም በልክ አድርጉ ይላል” ብዬ ልሰብካት ብሞክር የቱጋ ነው የጻፈው ትለኛለች፡፡ የተጻፈ ነገር ካለ ንገረኝ እንጂ ያልተጻፈውን አታንብብ ትለኛለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ ውስጥ “አውድ” የሚባል ነገር መኖሩን በሰበብ በአስባቡ የነገርኩአትን ይዛ “አውድ ጠብቅ” እያለች ወደ እኔ ታነጣጥርብኛለች፡፡ በገዛ እጄ ስለ አውድ ነግሬአት ራሴው አፍ አጣሁ፡፡ እንዲያውም የእንጀራና የቡና ፍቅር እየባሰባት መሄዱን ሳይ “ይህ የእንጀራ ፍቅር በዝቷል፣ ወደ ሰማይም ሄደሽ እንጀራ እበላለሁ እንዳትይ እዚያ እንጀራ የሚባል ምግብ አይኖርም ይልቁንስ የተሻለና ከሁሉም የላቀ ሕይወት ነው የሚጠብቀን እንጂ” እያልኩ ሊሰብካት ቢሞክር አሁንም “ይህ ትምህርት ከእውነተኛው አስተምህሮ ጋር ስለጣጣሙ እርግጠኛ ሁን እንጂ እኔ መንግሥተ ሰማይ ሄጄ እንጀራ አልጋግርም የሚጋግርልኝም ይኖራል ብዬ አላስብም” ትለኛለች፡፡፡ ባለቤቴንና ልጀቼን ይህንን አታድርጉ ብዬ በቃል ጥቅስ ከመገሰጼ በፊት አውዱን በጥንቃቄ የመመልከት ግዴታ ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ ያውም እኔው ራሴ አውድ context ስለሚባል ነገር ነግሬአቸው ያመጣሁት መዘዝ ነው፡፡ እኔ የሚቀለኝና ነጻነት የሚሰማኝ በመነቃቂያ ኮንፍራንስ ስሰብክ ነው፡፡ እዚያ ከየት አመጣኸው የሚል የለም፡፡ የተሳሳተም ቢሆን ተናግረው አሜን በሉ ሲባል አሜን የሚባልበት ቦታ ነው፡፡ እኔ እዚያም ቢሆን አውድ እጠብቃለሁ እንጂ ምክንያቱም ወደ ቤት ስመለስ ባለቤቴ “እሺ የዛሬው አገልግሎት እንዴት ነበር ታዲያ?" ብላ ሳትጠይቀኝ አልፋ አታውቅም፡፡ እኔም ‘ጌታ ይመስገን በጣም ጥሩ ነበር” እላታለሁ፡፡ እዚያጋ ቢያበቃ መልካም ነበር ግን አያበቃም፡፡ “ስለ ምን ሰበክ?” የሚለው ጥያቄ ይከተለኛል፡፡ ይህን ጊዜ ከስብከቴ መካከል ደግ ደጉን መርጬ በጥንቃቄ እነግራታለሁ፡፡ ባለቤቴ አገልግዬ ስመለስ በጥያቄ ማጣደፍ ብቻ ሳይሆን በጌታ የተሳካ የስብከት አገልግሎት እንዳቀርብ አጥብቃ ትጸልይልኛለችና ስለ እርሷ ጌታን አመሰግናለሁ፡፡ ታዲያ በእኔ ቤት መንፈሳዊ ነጻነት ፣ በነጻነት መስበክ፣ ጥቅስ እየጠቀስኩ አንዱን ከአንዱ ጋር አገናኝቼ ማሳመን በቀላሉ እልሆን እያለ መጥቷል፡፡ በመሆኑም ደስተኛ ነኝ፡፡ ባለቤቴንና ልጆቼን እግዚአብሔር ስለሰጠኝ ምስጋናዬም የላቀ ነው፡፡
ባለቤቴ ቡናንም ስትወድ አይጣል ነው፡፡ እኔ ደግሞ ቡና አልጠጣም፡፡ ጧትና ማታ ቡና ካላፈላሽ እያልኩ የማስቸግር ባል ባለመሆኔ ራሱ ልታመሰግነኝ ሲገባት “ባትጠጣ ሙሉ መብት አለህ፣ ማንም በግድ ጠጣ አይልህም፣ ደግሞ ብትጠጣም ችግር የለውም ለራሴ ሳፈላ እግሬ መንገዱን ትጠጣለህ” ትለናለች፡፡ይህ እኮ በእኛ ቤት የሴቶች እኩልነት ብቻ ሳይሆን የሴቶች የበላይነትም መኖሩንም ያሳያል፡፡ አሁን አሁን በተለይም ወተት በቡና የሚባለውን በትንሽ በትንሹ ስትሰጠኝ ቀየችና ለእኔ በማይገባኝ ሁኔታ የቡናውን መጠኝ ከቀን ወደ ቀን በዛ እያደረገች ምን አለፋችው በቡና ሱስ አስያዘቺኝ፡፡ አሁን በቁጥጥሯ ሥር ገብቻለሁ፡፡ በአገሬ ሳለሁ ለቡና ሱስ ያልተንበረኩ ሰው አሁን ከምሳ በኋላ ያቺን ወተት በቡና የምትለዋን ካልጠጣሁ ይደክመኝ ጀመረ፡፡ 
ለማንኛም እኔና ባለቤቴ ወደ ሜዲትራኒያን ገበያ አዳራሽ የሄድነው ጤፍ፣ ገብስና ቡና ለመግዛት ነው፡፡ እዚያ የኢትዮጵያ ቡናም አለ፡፡ባለቤቴ የምትፈልገውን ዕቃ እየመረጠች በጋሪው ላይ ስታስቀምጥ የእኔ ሥራ ጋሪውን እየገፋሁ ከኋላዋ መከተል ነው፡፡ እርሷ የመረጠችውን ብቻ ነው እንጂ የእኔ ምርጫ ውሃ አያነሳም፡፡ ከኋላዋ ሆኜ ያንን ጋሪ እየገፋው እያለ ዓይኔ በአንድ ነገር ላይ አረፈ፡፡ ከፊት ለፊታችን ባለው ጠሬጴዛ ላይ በሚያምር ንጹሕ ላስትክ ታሽጎ የተደረደረ ደስ የሚል ነገር፡፡ ምግብ ነው ታዲያ! ገበያተኞች አንዱ ከሌላው እየተከተሉ የሚያነሱት፡፡ ገበያ አዳራሹ የዐረቦች በመሆኑ ምክንያት ብዙ ዐረቦች ይገበዩበታልና እነርሱም ያንን ሲያነሱ አየሁ፣ ሶማሊያውያንም ፣ ሱዳናውያንም በየተራ እየመጡ ሲወስዱ አየሁ፡፡ እኔም ተጠጋሁና አይቼ ልቤን ደስ አለው፡፡ ለባለቤቴ አሳየሁአት፣ አየሽው ይህንን ነገር አልኩአት፡፡ ለካ እርሷ ከእኔ በፊት አይታዋለች ግን እንደ እኔው አልገረማትም፡፡ ነገሩ እንጀራ ነው፡፡ እንጀራ በዚህ ገበያ ሲሸጥ ከዚያም አልፎ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑትም ጭምር ተሻምተው ሲወስዱ አታይም እንዴዬ አልኳት፡፡ ያውም እኮ ነጭ ወረቀት የመሰለ እንጀራ እኮ ነው፡፡ የእንጀራ ፍቅር የባለቤቴን ያህል ባይሆንም እንጀራን እወደዋለሁ ፡፡ የአገሬ ምግብ እንደዚያ ሲሸጥ በማየቴ ኩራት ኩራት አለኝ፡፡ በአገራችን የነጭ ጤፍ እንጀራ የሚበላው ሀብታም ሰው ቤት ነው ፡፡ ይህ ደግሞ ከንጣቱ ጋር ልስላሴው ራሱ ብላው ብላው የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን እንጀራ ወዳድ ባለቤቴ ያሳየችው ቸልተኝነት አንድ ጥየቄ እንድጠይቃት አደረገኝ፡፡ ይህንን እንጀራ አልወደድሺውም አልኳት፡፡ እርሷም መልሳ እንዲህ አለችኝ “እንጀራ ይመስልሃል? ይህ እኮ እውነተኛ እጀራ ሳይሆን ዱቄቱን ሳልፍራይዜር ከሚባል ኬምካል ካር ቀላለቅለው ስለሚጋግሩ የነጣው በዚያ ምክንያት ነው የለሰለሰውም ለዚያ ነው፡፡ እውነተኛ እንጀራ ግን እንደዚህ አይለሰልስም አይነጣምም፡፡ ይህኛው ሁለትና ሦስት ቀን እዚህ ቢውል አይደርቅም አይሰባበርም፡፡ እውነተኛው እንጀራ ግን ጠሬጴዛ ላይ እንደዚህ አይቀመጥም ፣ በልዩ ጥንቃቄ በኮባና በሌሎች ቅጠሎች ተሸፋፍኖ በእቃ ውስጥ ነፋስ በማይነካው መልኩ ይቀመጣል፣ ይህኛው እንጀራ ከኬሚካሉ የተነሳ ለጤና ጎጂ ሲሆን እውነተኛው ግን በጣም ጤናማ ነው፣ ጤፋችን ብረት በተባለ ንጥረ ነገር የበለጸገ ስለሆነ ለጤና ጠቃሚ ነው፣ አሁን እኔ የጤፉን ዱቀት ወስጄ ስጋግረው የሚወጣው እንጀራና ይህኛው እንጀራ በምንም ሊገናኙ አይችሉም” አለችና አስዳችኝ፡፡ 
ከዛ በኋላ ራሴን ጠየቅኩኝ እነዚያ ሰዎች ታዲያ እንጀራ እንጀራ እያሉ የሚሻሙት ለምንድነው አልኩ፡፡ መልሱ እውነተኛውን እንጀራ ስለማያውቁ ነው፡፡መለስለሱንና መንጣቱን እንጂ በማስመሰል የተሠራ የሀሰት እንጀራ መሆኑን አላውቁትም ማለት ነው፡፡ ሐሰት መሆኑን የምታውቀው ኢትዮጵያዊቷ ባለቤቴ የእውነተኛው እንጀራ ጋጋሪ ኢትዮጵያዊት ስለሆነች ነው፡፡ በመሠረቱ እንጀራ ከመነሻው የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግብ እንጂ የዓረቦችም የሶማሊያውያንም አይደለም፡፡ የሱዳኖችም ምግብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያውያን ምግብ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትየጵያውያን ሐሰተኛውን እንጀራ ከእውነተኛው የመለየት ብቃት አላቸው፡፡ ሌሎች ግን ይህ ብቃት ስሌለላቸው በብረት የበለጸገውን የጤፍ እንጀራ ሳይሆን ኬምካል የተሞጀረበትን ነጭ እንጀራ ይበሉታል፡፡ 
ከዚህ የተማርኩት አንድ መንፈሳዊ ቁም ነገር አለ፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሐሰት አስተማሪዎችንና የሐሰት ትንቢቶችን፣ ተአምራቶችን እንዲሁ በቀላሉ ልንለያቸው አንችልም፡፡ እውነተኛውን ትምህርት ካላወቅን በቀላሉ እንወሰድባቸዋለን፡፡ የሐሰት ትምህርቶች ይመርካሉ፣ ብዙዎች ይከተሉአቸዋል፣ ያደንቁአቸዋልም፡፡ ነገር ግን ከእውነተኛው ትምህርት ጋር ሲያስተያዩት ውስጣቸው በገዳይ መርዝ የተመላ ነው፡፡ እውነተኛው እንጀራ ዋጋው ውድ ሲሆን ሐሰተኛው ደግሞ ቀለል ባለ ዋጋ እንደሚገኝ ሁሉ የስህተት ትምህርትቶችና ትንቢቶች እንደ ልብ ይገኛሉ፡፡ ሐሰተኛውን ከእውነተኛው ለመለየት ቀላሉ መንገድ እውነተኛውን ትምህርት በሚገባ ማወቅ ነው፡፡ባለቤቴ ኢትዮጵያዊ በመሆኗ እውነተኛውን እንጀራ ስለምትጋግር ሱዳናውያንና ሶማሊውያን የሚገዙት ሳልፍራይዜር ያለበት እንጀራ እንደምግብም አልታይ አላት፡፡ እኔም ምስጥሩም ስለማላውቅ ልቤ በዚያ እንጀራ ተማርኮ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ቤተ ክርስቲያን በሐሰት ትምህርትና በጤናማ ትምህርት፣ በሐሰት ትንቢትና በእውነተኛ ትንቢት ፣በሀሰት ተአምራትና በእውነተኛው ተአምራት መካከል ያለውን ልዩነት ምዕመናን ተረድተው በሐሰተኛው መርዝ እንዳይጠቁ እውነተኛውን ትምህርት በማስጨበጥ ልትተጋ ይገባታል፡፡ ፈጣሪ በቸርነቱ ይጠብቀን ይርዳንም ፡፡ አሜን

No comments:

Post a Comment