መጽሐፍ
ቅዱሳዊ ይቅርታ
(ክፍል አንድ)
(ክፍል አንድ)
ከፓስተር
ሳሙኤል ሾንጋ
ዘመናችን
ከምን ጊዜም በላይ የቴክኒዮሎጂ ምጥቀት
የሚታበት እየሆነ መጥቷል፡፡ አንዱን የቴክኒዮሎጂ
የፈጠራ ውጤት አይተን ሳንጠግበው ሌላው ሲመጣ
ጉድ ያሰኛል፡፡ አሁን አሁንማ የሚታዩ የሰው
ልጆች የፈጠራ ሥራዎች ሕይወት የላቸውም እንጂ
የማያስገርሙት ሰው አለ ማለት አይቻልም፡፡
ኮምቲዩተር የተባለ መሣሪያ በሁሉም ቦታ
ከመገኘቱም በላይ ወደ የሰው ቤት ሁሉ ሊገባ
የሚችል ነገር እየሆነ ስለ መጣ ዶክዩሜንትና
ዎርድ ስለሚባሉ ነገሮች ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡
አንድ የጸፍነው ወይም የምንፈልገው ሰነድ
የሚቀመጠው በአብዛኛው ዶክዩሜንት በተባለው
ቦታ ላይ ነው፡፡ ይህ ቦታ ሰነዶቻችንን ፊት
ለፊት ልናገኛቸው የምንችልበትና ግልጽ የሆነ
ቦታ ነው፡፡ በዚህ ሥፍራ የተቀመጠውን ፋይል
ማጥፋት ይቻላል፡፡ የማንፈልጋቸውው ሰነዶች
ካሉ እንዲያጠፋ ለኮምፒዩተሩ ስንነግረው ራሱ
ያጠፋውና ቦታውን አጽድቶ ንጹህ ያደርገዋል፡፡
ይሁን እንጂ ያንን አያስፈልግም የተባለውን
ሰነድ ሪሳይክል ቢን በተሰኘው ድብቅ ቦታ ላይ
ወስዶ ያስቀምጠዋል እንጂ ሙሉ በሙሉ አጥቦታል
ማለት አይደለም፡፡ የኮምፒዩተሩ ባለቤት
ቢፈልግ ያንን አጥፋው ያለውን ሰነድ እስቲ
ልየው ቢሎ ቢያስብ ወደ ኮምፒዩተሩ ሪሳይክል
ቢን ውስጥ ገብቶ እንደገና ወደ ዶክዩሜንት
እንዲመለስ አድርጎ እንደ አዲስ እንደቀድሞው
በአግባቡ መጠቀም ይችላል ማለት ነው፡፡ ሲፈልግ
ደግሞ ወደማይታየው ሪሳይክል ቢን ወደተሰኘው
ድብቅ ቦታ መልሶ ማስቀመጥ ይችላል ማለት
ነው፡፡ ታዲያ ምን ጊዜም አልፈልገውም ብሎ
ከቆረጠ ደግሞ ከሪሳይክል ቢንም ውስጥ አስወግድልኝ
ብሎ ኮምፒዩተሩን ማዘዝ ይችላል፡፡ ያን ጊዜ
በምንም ሁኔታ ሰነዱ አይገኝም ጨርሶ ከኮምቲዩተሩ
ማስተዋል ተወግድዋል ማለት ነው፡፡ መልሶ
ያንን ሰነድ የሚያገኝበት መንገድ አይኖርም፡፡
ከዚህ
የምንማረው አንድ እውነት አለ፡፡ ከሰዎች
ጋር ስንኖር አዎንታዊም አሉታዊም ጉዳዮች
ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ ምንም ይሁን ምን
በሚገጥሙን ጉዳዮች ተቻችለን ለመኖርና ለማለፍ
መንፈሳዊ አቅም ያስፈልገናል፡፡ ራሱ ክርስትና
እኮ እንደ ምንዘምረው ያህል ቀላል አይደለም፡፡
ወደ ተግባር ለመለወጥ ስናስብ የዳገት ያህል
አዳጋች የእሬትም ያህል መራራ ይሆንብናል፡፡
ክርስትናን
ፈታኝ የሚያደርገው አንዱ ጉዳይ የበደሉንን
ይቅር እንድንል የሚጠይቀን ትዕዛዝ ነው፡፡
ይቅር ብያለሁ ማለት በጣም ቀላል ነው፡፡ ይቅር
ያሉትን ጉዳይ በልብ ውስጥ ደብቀው ሳያስቀምጡ
ጨርሶ ማጥፋት ግንመንፈሳዊ
ጥንካሬን የሚጠይቅና የሚፈታተነን ነው፡፡
የኮምፒዩተሩ ባለቤት ሪሳይክል ቢን በተሰኘው
ድብቅ ቦታ የተቀመጠውን ሰነድ ሲፈልግ እያወጣ
እንደሚጠቀምበት በልባቸው ¹ዳ
ደብቀው ያሰቀመጡትን ቂም ከዚያ ውስጥ እየመዘዙ
እያወጡ እንደ አዲስ የሚያደርጉ ብዙ ክርስትያኖች
አሉ፡፡ የረሱትንና ይቅር ያሉትን ከሪሳይክል
ቢንም ውስጥ እንደሚያስወግድ ሰው ከራሳቸውም
የልብ ¹ዳ ፈፅመው
ማጥፋት ስላልቻሉ ራሳቸውንም ሌላውንም የሚጎዱ
ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በአንድ ጉዳይ
መግባባት አቅቶአቸው በወንድሞች አማካይነት
ይቅርታ ከተጠያየቁ ከዓመታት
በኋላ እንኳን በሌላ
ጉዳይ ቢገናኙ ያንኑ የተረሳውን እንደ አዲስ
አንስተው የሚወቃቀጡ አገልጋዮችም ብዙ ናቸው፡፡
አንዳንድ
ሰዎች ባልንጀራቸውን ይቅር ማለት እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ እንዴት ይቅር ማለት እንዳለባቸው
ግን ይቸገራሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች
ለአገልጋዮችና ለቤተክርስቲያን ትልቅ ፈተና
የሚሆኑት ይቅርታ ለማድረግ ያልተዘጋጀ ልባቸው
ከሚያመነጨው ባህሪያቸው የተነሳ ነው፡፡ ስለ
ይቅርታ ተገቢ እውቀትና ግንዛቤ የጎደለው
ክርስቲያን በበቀልና በመራርነት የተሞላ
ይሆናል፡፡ ክርስቲያኖችን ደቀመዝሙር
እንዲያደርጉ የሚጠበቅባቸው ጊዜያቸውን የሰጡ
አገልጋዮች እርስ በእርሳቸው በክፋት ሲፈላለጉና
አንዱ በአንዱ ላይ መራራ ነገር ሲያደርግበት
ሲታይ ያሳዝናል፡፡ ይቅርታ አገልጋይ በመባል
ብቻ የሚመጣ አይደለም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ
ተማሪ በመሆንም የሚገኝ ነገር አይደለም፡፡
ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም በሆነው
ለውጥ እንጂ፡፡ ይሁና ይቅርታን ከነትርጉሙ
ማወቅና መተርጎም እንዲቻል ለዛሬው ይቅርታ
ምን እንዳይደለ ከሚለው እንጀምርን፡፡
- ይቅርታ ዝም ብሎ የሚሰማን ስሜት አይደለም፡፡ብዙ ጊዜ በስብከት ተጎትጉተው ወይም የበደለው ሰው ምንም ሳይሰማሙ አስታራቂው አስቀድሞ ስላለቀሰ በይሉኝታ ስሜት እሺ ታርቀናል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እኛ በባህሪያችን ከእውነት ይልቅ የስሜቶቻችን ተገዥዎች ነን፡፡ በይሉኝታ ስሜት ተነድተው ይቅርታ ማድረግ አደገኛነቱ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይቅርታ ከፍፁም መታዘዝ የሚመጣ የውስጥ ውሳኔ ነው፡፡ የሆነ ኃይለኛ ስሜት ወደ እኛ እየጎረፈ መጥቶ ይቅር ወደ ምንልበት መድረክ ጠርጎ እንዲያወጣን መጠበቅ አይኖርብንም፡፡ ግን ጌታ ይቅር ተባባሉ እንዳለው ቃል ሳንጨምርበት ሳንቀንስበት ሌላም መከራከሪያ ሳንሰጥ በልባችን ሪሳይክል ቢን ውስጥ ደብቀን ያስቀመጥነውን የበቀል ስንቅ ከዚያም ውስጥ ቢሆን አውጥተን መጣል ካልተቻለ ዝም ብሎ በማለቀስ ብቻ የምንገልፀው ውጫዊ ገጽታ ይቅርታን አይወክልም፡፡ እግዚአብሔር እኛን እንደተመረጡ ሰዎች ነፃ እንድንሆንለት ይፈልጋል፡፡ በውስጡ ይቅርታን ፍፁም ያላደረገ ሰው ነገር ግን በአንደበቱ ይቅር ብያለሁ ብሎ በልቡ ቂመን ሸፍኖ የሚኖር ሰው መንፈሳዊ ነፃነት ይሰማዋል ማለት አይቻልም፡፡ " እኔ ይቅር እንዳልኳችሁ እናንተ እርስ በእርሳችሁ ይቅር ተባባሉ" ጌታ የእኛን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ይቅር ብሏል እንጂ ወደ ኋላ ያስቀረው የለም፡፡ ስለዚህ ይቅርታን የምንማረው ከጌታ ከራሱ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ይቅርታን የጊዜው ስሜት ብቻ አድርገን መውሰድ የለብንም፡፡
- ይቅርታ ተበዳዩ የሚጠይቀው አይደለም፡፡አንዳንድ ሰዎች ሰዎችን ሲያስታርቁ የተበደለውን ወገን ይቅርታ እንዲጠይቅ ይመክራሉ፡፡ እንዲያውም በበዳዩ እግር ላይ ወድቆ ይቅርታ እንዲጠይቅ ይገፋፋሉ፡፡ ለምን ቢባል አንዴም ምን አለበት? ሰላም ይውረድ እንጂ የሚል መልስ ይሰጣሉ፡፡ አሊያም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ አባቴ ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሏል፡፡ እስጢፋኖስም እንዲህ አድርጓልና የሚል ቅጥስ ለመጥቀስ ይቃጣቸዋል፡፡
እንግዲህ
ይህ በጣም ሰውኛ የሆነ ትምህርት ነው፡፡
የተበደለው ይቅርታ ጠያቂ አይደለም፡፡ ቅዱሳት
መጽሐፍትም ይህንን አያስተምሩም፡፡ ይልቁንስ
የተበደለ ሰው ሁለት አስፈላጊ ነገሮችን
ሊያደርግ ይችላል፡፡ አንደኛው ክርስቶስ
ይቅር እንዳለ እንዲሁ በራሱ ይቅር ብሎ ማለፍ፣
ሁለተኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረው
የበደለውን ወንድሙን ሄዶ መውቀስና ከሰማው
ወንድሙን ገንዘብ ማድረግ ማቴ 18፡15-2ዐ፡፡
ጌታችን
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ ልብሱን ሲከፋፈሉት
የነበሩትን ሰዎች ይቅርታ አልጠየቃቸውም፡፡
የሚሰሩትን ኃጢአት እግዚአብሔር እንዳይቆጥርባቸው
አምላኩን ተማፀነ እንጂ ፡፡ "
አባት
ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው"
ሉቃስ
23፡34፡፡
እስጢፋኖስም ቢሆን በድንጋይ የሚወግሩትን
ሰዎች እባካችሁ ይቅርታ አድርጉልኝ አላለም፡፡
ነገር ግን ስለ እነርሱ ማለደ፡፡ እንዲህም
ሲል "
ጌታ
ሆይ ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው"
ብሎ
በታላቅ ድምፅ ጮኸ ሐዋ 7፡
8
፡፡
ኢየሱስ ይቅርታ ጠየቀ ብንል አንድ የበደለው
ወይም የሠራው ስህተት አለ ወደሚለው ድምዳሜ
እንዳያመራን እንፍራ፡፡ እስጢፋኖስም ቢሆን
ስለ ክርስቶስ ትንሳኤ ከመስበክና እውነትን
ከማስተማር ውጭ የሠራው በደል ስላልነበረ
ይቅርታ የሚጠይቅበት ምንም ምክንያት ስላልታየው
ይቅርታን ከሚጠይቅ ይልቅ ስለ በደለኞች
መማለድን መረጠ፡፡ ስለ በደሉት ሰዎች
ከእግዚአብሔር ይቅርታን መለመንና የበደሉትን
ሄዶ ይቅርታ መጠየቅ ሁለቱ የተለያዩ ጉዳዮች
ናቸው፡፡ በእርግጥ የተበደለ ሰው ወደ በደለው
ወንድም መሄድ ይኖርበታል፡፡ የሚሄደው ግን
ይቅርታ እንዲጠይቅ ሳይሆን ሊወቅሰው ነው፡፡
ይህንን ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን፡፡
የበደለው እያለ የተበደለው ይቅርታ የሚጠይቅ
ከሆነ በደለኛው በበደሉ ይቀጥላል፣ ከስህተቱም
የሚማርበት ዕድል የለውም ማለት ነው፡፡
የተበደለ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚያሳይ
እንዲያውም ኢየሱስ ተበድሎ ይቅርታ እንደጠየቀ
ተደርጎ የሚሰጥ ትምህርትና ስብከት አለ፡፡
አንዳንድ ዘማሪዎችም እንዲህ አድርገው
ዘምረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ቃሉ መሠረት
መመለስ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ይቅርታ ማድረግም
ይሁን ይቅርታ መጠየቅ እንደ እግዚአብሔር
ቃል አስተምህሮት መሆን አለበት እንጂ ይቅርታ
መጠየቅ የተበዳይ ኃላፊነት አይደለም፡፡
- ይቅርታ ሰው የሠራውን ጥፋት ችላ ማለት አይደለም፡፡
አንዳንድ
ሰዎች አጥፊው ከነጥፋቱ ችላ ከተደረገ ሌላ
ምን ያስፈልጋል ብለው ስለሚያስቡ ይቅርታ
ማድረግን ቸል ይላሉ ወይም ይቅርታ ለማድረግ
ያቅማማሉ፡፡ የፈለገውን ይሁን እኔ እርሱ ጋ
ካልደረስኩ እርሱም እኔጋ ካልደረሰ ምንም
ሳንቸገርና ሳንቀያየም መኖር ስለምንችል
እርሱ ያደረገብኝን ለማሰብ አልፈልግም ይላሉ፡፡
ሌሎች ደግሞ ያደረገብኝን ነገር ንቀው ስለ
ተውኩት አሁን ምንም አያስፈልገኝም ይላሉ፡፡
እነዚህ
ሁሉ መልካም ሐሳቦች ይመስላሉ፡፡ ግን መልካም
ሐሳቦች ሳይሆኑ በውስጣቸው ችግር የቋጠሩ
ናቸው፡፡ እንዲያውም እውነተኛ ከሆነው የይቅርታ
ሕይወት ተስፈንጥረን እንድንወድቅ የሚያደርጉ
ናቸው፡፡ ይቅርታ ማድረግ ለተበዳዩም ለበዳዩም
ለሁለቱም ጥቅም ነው፡፡ የተበደለውን ሰው
ለማጽናናትና የበደለውን ለመኮነን የሚደረግ
ይቅርታ የለም፡፡ ለሁለቱም ከሚሰጠው ጥቅም
አንፃር ብናየው ጥሩ ነው፡፡
ከይቅርታ
አድራጊው አንፃር፡-
ይቅርታ
አድራጊ የምንለው የተበደለው ሰው ነው፡፡
- እርሱ በደል ያደረሰበትን ሰው ይቅርታ በሚያደርግበት ጊዜ ራሱን ከመራርነት እስራት ነፃ ያደርጋል፡፡ ምንም እንኳን ንቄ ትቼዋለሁ ቢልም ስለ ሰውዬው ባሰበ ቁጥር መመረሩ አይቀርም፡፡ ይቅርታ ሲያደርግ ግን የውስጡ ምሬት ተወግዶለት እረፍት ያገኛል፡፡
- ይህ ብቻ ሳይሆን ይቅርታ ካላረገ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ አያገኝም፡፡ አንዳንድ ሰው እኔ አላዘንኩም ይል ይሆናል፡፡ ቢሆንም ክርስቶስ ይቅር እንዳለ ለሰዎች ይቅር ማለት ካልተቻለ ከእግዚአብሔር ምህረትን አገኛለሁ ማለት እንዳይችል ቃሉ በግልጽ ይነግረናል፡፡ #ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ይቅር ይላችኋልና ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁምና፡፡; ማቴ 6፡14-16
- የሰዎች ፀሎትና ፆም በእግዚአብሔር ፊት ሊከበር የሚችለው የበደልን እስራት ሲፈቱ/ ይቅር ሲሉ ነው/ ኢሳ 58፡6/. በጣም ብዙ ፀሎት ይደረጋል፡፡ ለአያሌ ቀናት የፆምም ይጨመርበታል፡፡ የፀለይነውንና የፆምነውን ያህል ግን መንፈሳዊ ተሐድሶ የመንፈስ ቅድስም አሰራር አይገለጥም፡፡ ምክንያቱም ፆምና ፀሎት ከበደል እስራት ጋር ነው፡፡ ከቂም ጋር ነው፡፡ ይህ በመሆኑ የብዙዎች ፈውስ ዘግይቷል፡፡ ብዙዎች ተበድለው ሳለ ይቅርታን ማድረግ ባለመቻላቸው በታላቅ ቁዘማ ውስጥ አሉ፡፡
ከይቅርታ
ተቀባዩ አንፃር፡-
ይቅርታ
ተቀባዩ ወንድሙን የበደለ ሰው ነው፡፡ እርሱ
ደግሞ በደሉን አውቆ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
ይህንን ሲያደርግ ከዕዳ ነፃ ይሆናል፡፡
ወንድሙን የበደለ ሰው ነገ የሚከፍለው ዕዳ
አለ፡፡ ዛሬም ቢሆን የህሊና ክስ ውስጥ ይኖራል፡፡
"አትሳቱ
እግዚአብሔር አይዘበትበትም፡፡ ሰው የሚዘራውን
ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፡፡"
ገላ
6፡7
ወዳጆች
ሆይ፡ ራሳችሁን አትበቀሉ ለቁጣ ፈንታ ስጡ
እንጂ በቀል የእኔ ነው እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ
ይላል ጌታ፡፡ ሮሜ.12፡19
ይህ
ማለት ታዲያ እግዚአብሔር በበደለኛው ሰው
ላይ ይፈርድበታል ለተበደለውም በፅድቅ ይበይናል
ማለት አይደለምን?
የእግዚአብሔርን
ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ስንመለከት በሰዎች ላይ
በደል ያደረሱ ነገር ግን ከሰውም በእግዚአብሔርም
ምህረትንና ይቅርታን ያልለመኑ ሁሉም ብድራታቸውን
ተቀብለዋል እንጂ ሳይቀጡ አልቀሩም፡፡ በዳዩ
በደሉን አውቆ ከወንድሙ ይቅርታ ቢጠይቅ
እግዚአብሔርንም ምህረት ቢለምን ሙሉ ነፃነት
ያገኛል፡፡ ለእርሱም ጥቅም አለው የምንለው
ለዚህ ነው፡፡
- ይቅርታ ውስጣችን እየታመመ ለማስመሰለ የምናደርገው ጉዳይ አይደለም፡፡ይቅርታ አድርጌአለው እየተባለ ህመሙ ካልዳነ ይቅርታው እውነት አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ አሁንም ደጋግመን በዓመቱ የተደረገብኝ ነገር እየተባለ የሚመረር ከሆነ እውነተኛ ይቅርታ አልተደረገም ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ልብ እያዘነ ምንም አልተቀየምኩም እያሉ አብሮ መብላትና መጠጣት እርስ በእርስ መሳሳም አደገኛ ባህሪይ ነው፡፡ እንደዚያ የሚያደርጉ ሰዎች የበደላቸውን ሰው የሚጥሉትን ገመድ ወይም ወጥመድ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በውስጥ የጋለ ጥላቻ ስሜት ይዘው በውጭ ሰውነታቸው ግን የፍቅር ፊት የሚያሳዩ አደገኛ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ መማር አለባቸው ፡፡ ኢየሱስ በተቆጣ ጊዜ በቤተመቅደስ ውስጥ ያለውን ገበታ ገለበጠ እንጂ ስቆ ወይም አሽማጥጦ አላለፈም፡፡ ዮሐ 2፡15-16፡፡ ልቡ ስለሰዎች አለማመን ባዘነ ጊዜ አለቀሰ እንጂ አልሳቀም ዮሐ. 11፡፡ አሁን አማኞች የምናሳየው ባህሪይ ኢየሱስ ካሳየን ምሳሌያዊ ሕይወት ጋር የሚቃረን በመሆኑ መለወጥ አለበት፡፡ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ተገቢ ካልሆኑ ነገሮች አንዳንዶችን ለመጥቀስ በወንድማቸው ላይ ሲያዝኑ " ጌታ ይባርክህ" " ኢየሱስ ጌታ ነው" " እኔ እወድሃለው/እወድሻለው/" ይላሉ፡፡ ያውም ያንኑን እየደጋገሙ ያሰሙታል፡፡ ልብ ብለን ስናየው ግን እንደዚህ የሚሉት በእውነት ከልባቸው አይደለም፡፡ ቅሬታን ለመግለፅ ጌታ ይባርክህ የሚል ዐ.ነገር መጠቀም የሚያስፈልግ አይደለም፡፡ በድለኸኛልና አዝኜብሃለሁ ማለት ይሻላል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ጌታ ነው ማለትም ትክክለኛውን ሐሳብ ለተጣመመ ስሜት መጠቀም ይሆናል፡፡ እወድሃለሁ እያሉ መሸንገልም ግብዝነትን ከማጉላት በቀር ሌላ ጥቅምና ትርፍ ስለማይኖረው ያለምንም ማስመሰል አዝኜብሃለው/አዝኜብሻለው/ ብሎ መውቀስ ትክክለኛ የክርስትያን ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
- ይቅርታ ማድረግ ሰዎችን ከኃላፊነታቸው ነፃ የሚያደርግ አይደለም፡፡አንድ በደል በይቅርታ ብቻ ሊረሳ ይችላል፡፡ የተሠራውን በደል ተከትሎ ከሚመጣው ኃላፊነት ለመሸሽ ግን አያስችልም፡፡ ለምሳሌ፡ ሚስቱ ሳታውቅ ከሌላ ጋር ያመነዘረ አንድ ሰው ሚስቱን ግልጽ ይቅርታ ቢጠይቅ እርስዋም ብታደርግለት ነገሩ እዚያ ጋ ሊያበቃ ይችላል፡፡ በእግዚአብሔርም ፊት በሠራው በደል ምህረት ቢለምን ጌታም ይቅር ይለዋል፡፡ በዚህ ወቅት ልጅ ወልዶ ቢሆን ግን ያንን ልጅ የማሳደጉ ኃላፊነት ይጣልበታል እንጂ ባሌቤቱንና እግዚአብሔርን ይቅርታ ስለጠየቀ ከኃላፊነት ነፃ ይሆናል ማለት የሚቻልበት መንገድ የለም፡፡ ባለቤቱም ይቅርታ ስላደረገችለት ተብሎ እንደ ልÍ እንድትቀበለው ማስገደድ አይቻልም፡፡ ከዚህም ባለፈ የምንዝርና ኃጢአት በፈጸመበት ወቅት ምናልባት በሆነ ምክንያት የአካል ጉዳት እንደነዓይን መጥፋት፣የአጥንት መሰበር ወዘተ ደርሶበት ቢሆን ያንኑ የመሸከም ኃላፊነት የባለቤቱ ይሆናል እንጂ ይቅርታ ስለተደረገ ዓይኑ አይተካለትም፡፡ እጁን ተቆርጦ ቢሆን አይቀጠልለትም፡፡ ይህንን የሚመስሉ ሌሎችም የኃላፊነት ዓይነቶች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡
- ይቅርታ ማድረግ ጀግንነት ወይም ትምክህት አይደለም፡፡ማንኛውንም ነገር ብናደርግ ማድረግ የሚገባነንን ግዴታ ተወጥተናል እንጂ ያንን ስለ ሠራን በፊታችን የምናስነፋው ምንም ዓይነት መለከት ሊኖር አይገባም፡፡ እኛ ባለንበት ዘመን አገልጋዮች እንè ሳይቀሩ ይቅርታ ስላደረጉ ትምክህት ይሰማቸዋል፡፡ እግሬ ላይ ስለ ወደቀና ስለተማጠነኝ እንጂ እስከ መቼውም ዓይኑን አላየውም ነበር የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይቅርታ ማድረግ የሚኖርብን በዳዩ ስለተማጠነና እግር ላይ ስለወደቀ ሳይሆን ጌታ ስለታዘዝን ብቻ የሚደረግ መሆን አለበት፡፡ በዳዩ ባይጠይቅና መጥቶ እግር ላይ ባይወድቅ ይቅርታ አናደርግም ማለት ነው? ከፍ ብሎ የተመለከትነው ይህንን ነው፡፡ ወንድምህ ቢበድልህ ውቀሰው ይላል ቃሉ፡፡ በወቀስነው ጊዜ በዳዩ አላውቅልህም ምንም አልበደልኩህም ቢል ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮችን ይዘን ሄደን እናነጋግረዋለን፡፡ እነርሱን ባይሰማ ወደ ቤ/ክ ሽማግሌዎች እናቀርበዋለን፡፡ ቤ/ክንን ባይሰማ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁን ይላል ማቴ.18፡15 -20፡፡ ይህ ማለት ግን የበደለንን ሰው ይቅር አንለውም ቂምን ይዘን እንቀጥላለን ማለት ነው? በእርግጥ እንደዚህ አይደለም፡፡ በዳዩ ይቅርታ ቢጠይቅም ባይጠይቅም፣እግራችን ላይ መጥቶ ቢወድቅም ባይወደወቅም እኛ ስለ ታዘዝን ብቻ የበደለንን ይቅር የማለት ግዴታ አለብን፡፡ ስለዚህ ይቅርታ ያደረገ ሰው እነ እገሌ ስለለመኑኝና እርሱም ስለ ወተወተ ይቅር አልኩት እንጂ ወደብዙ ቦታ አደርሰው ነበር እያለ መፎከር ያለንን የመንፈሳዊ ሕይወት ለፈስፈሳነትን የሚያመላክት ነው፡፡
- ይቅርታ አለ ማድረግ የበደለንን ሰው የምንጎዳበት መንገድ አይደለም፡፡እውነት እንነጋገር ካልን ይቅር አልልም የሚል ሰው የሚጎዳው ራሱ ነው እንጂ የበደለ ሰው አይደለም፡፡ የበደለን ሰው ይቅርታ የመጠየቅ ግዴታ ያለበት እንደሆነ ሁላችንም እንስማማበታለን፡፡ የሚገርመው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የበደልናቸውን ሰዎች ይቅርታ እንድንጠይቅ ከሚያዘን ክፍል ይልቅ የበደሉንን ይቅር እንድንል የሚያዘን ትምህርት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ይቅር ባለማለታችን በጣም አድርገን የምንጎዳቸው ይመስለናል፡፡ እነርሱ ግን አይጎዱም፡፡ ከእግዚአብሔርም ጋር ያጋጨናቸው ወይም ከባድ ወደሆነው የእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ያስገባናቸው ይመስለንም ይሆናል፡፡ ሚስጥሩ ግን እንደምናስበው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት በተበዳዩና በበዳዩ መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ አንዱ እግዚአብሔር የሁሉ አባት ነው፡፡ ተበዳዩ በዳዩን ይቅር ባይለው የበደለው ግን ይቅርታ ቢጠይቅና በእግዚአብሔርም ፊት ንስሐ ቢገባ የተበደለው ይቅር አልልም ስላለ ብቻ በደለኛው ታስሮ ይቀራል ማለት አይቻልም፡፡ የአንድ ቀን ስህተት ሕይወትን እንደሚያጠፋ ሁሉ የጥቂት ደቂቃ ንስሐ በእግዚአብሔር ፊት ባለ ብዙ ሞገስ ልታደርግ ትችላለች፡፡ በእርግጥ ነው የሚለው አማኞች ከዚህ አንፀር ራሳችንን ስንፈትሽ ብዙ ጉድለቶች አሉብን፡፡
ማጠቃለያ፤
እንግዲህ ከላይ ያየናቸው ይቅርታን ስለማድረግ
አስመልክቶ ያሉን ግን በመጠኑም ቢሆን የሚታዩብን
ስህተቶቻችን ናቸው፡፡ ይቅርታን እንደስሜት
የሚያዩ ሰዎች ከስሜትነት ወደ እውነተኛ ተግባር
መለወጥ ይኖርናቸዋል፡፡ ተበዳዩ ይቅርታን
እንዲጠይቅ የሚያበረታቱ፣ የሚያስተምሩ፣
የሚሰብኩና የሚዘምሩ ወገኖችም እንዲህ ዓይነት
የመጽ/ቅዱስ
ትምህርት ስለማይኖር ሁሉንም እንደቃሉ እውነት
ማድረግ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ተበድለንም
ቢሆን በደልን ቸል ብሎ ማለፍ እውነተኛ የይቅርታ
መንፈስን ስለማይገነባ የእግዚአብሔር ቃል
እንደሚያስተምረው ውይ መውቀስ ወይ ከልብ
በሆነ ይቅርታ ይቅር ብሎ ቂምንም ከውስጥ
በማውጣት እረፍት ሊያገኙ ይገባቸዋል፡፡
እንደግብዞችም የማስመሰል ይቅርታ በፍጹም
ማበታታት የለብንም፡፡ በደል በይቅርታ የሚታጠብ
ቢሆንም አንዳንዴ ተከትሎት የሚመጡ የተለያዩ
የኃላፊነት ዓይነቶች መኖራቸውን መዘንጋት
ተላላነት ይሆናል፡፤ ስለዚህ እንደ ክርስትያኖች የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስተምረን ራሳችንን በመፈተሸ ወደ እውነተኛ ይቅርታ መመለስ ይኖርብናል፡፡ ታዲያ እውዊነተኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይቅርታ የቱ ነው የሚለውን ለመዳሰስ የሚቀጥለውን ክፍል ሁለት ይመልከቱ፡፡
No comments:
Post a Comment