Wednesday, February 12, 2014

የሴቶች ኤጵስ ቆጶሳዊ አገልግሎት በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ


የሴቶች ኤጵስቆጶሳዊ አገልግሎት በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ
ከፓስተር ሳሙኤል ሾንጋ
satemefe@yahoo.com

በአሁኑ ወቅት በቤተክርስቲያን የሚነሱ ውዝግቦችና ንትርኮች በአብዛኛው ከአመራር ጋር የተያያዙ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች የሚታዩ መለያየቶችና ጥላቻዎች የአመራር ቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች የፈጠሩአቸው ናቸው፡፡ ልብ ብለን የተመለከተትን እንደሆነ "እኔ ለምን አልመሰክርም?”; "እኔ ለምን ለድሆች አልሰጥም?""ለምንስ የክርስቶስን ወንጌል ለሚጠፉት የማድረሱን አገልግሎት ለማፋጠን የበኩሌን ድርሻ አልወጣም?” በሚል የሚነሱ ውዝግቦች ብዙ አይታዩም፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶች ደግሞ በባሕሪያቸው የሚያወዛግቡ አይደሉምና፡፡ ነገር ግን "እኔ ለምን መሪ አልሆንም ? "ወይም እገሌና እገሊት ለምን መሪ አይሆኑም? " የሚለው ጥያቄ እያየለ መጥቶ መላ አካሉን እስከ ማናጋት የደረሰበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ከምትጋፈጣቸው ፈተናዎች አንዱ የሴቶችን አገልግሎትና አመራር አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎችን የመመለስ ሂደት ነው፡፡ በአንዳንድ ቤተ እምነቶች ሴቶች የወንድ ረዳቶች ስለሆኑ በቤተ ክርስቲያን የመሪዎችን አገልግሎት የሚደግፉ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ሴቶቹ የመመረጥ ያለ መመረጥ ጥያቄ ማንሳት ይቅርና በሽማግሌዎችና በመጋቢያን ምርጫ ወቅት ተገኝተው ድምጽ እንዲሰጡ እንኳ የማይፈቅዱ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ በአሜሪካን አገር የሚገኙ የሰባተኛ ቀን አድቬንትስትና የዴች ሪፎርምድ ቤተ ክርስቲያናት በምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለይም አንዳንድ የሪፎርምድ ቤተ እምነቶች ሴቶች በመሪዎች ምርጫ እንዲሳተፉ አይፈቅዱም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጠንካራ አቋም ብዙ ኩርፊያን አትርፏል፡፡ በቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ በበለጠ የሚሳተፉ ሴቶች አገልግሎታቸው ከወንዶች አገልግሎት ጋር እኩል ዋጋ የተሰጠውና የሚደነቅ አልመስል ስላላቸው በግራ የመጋባት ስሜት ተጠቅተዋል፡፡ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው የሴቶች አገልግሎት ውስጥ ከፍ ያለውን ሚና የሚጫወቱ ሴቶች አገልግሎታቸው ዝቅ ተደርጎ የታየባቸው ስለ መሰላቸው ጠንካራ ቅሬታ ይሰነዝራሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ሚና አለመሳተፋቸው የቅሬታውን መጠን የበለጠ አሳድጎታል፡፡ በአብዛኛዎቹ ወንጌላውያን (ኢቫንጄሊካል) ቤተ ክርስቲያናት ውሳኔ የሚሰጠው በተሾሙ ወንድ አመራር ሰጪዎች ሥልጣን አማካይነት ብቻ ስለሆነ የሴቶች ሚና ቦታ አልተሰጠውም በሚል ብዙዎች ቅር ተሰኝተዋል፡፡
ሴቶች ብቃታቸውን፣ የአመራር ችሎታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ከቤተ ክርስቲያናቸው ውጭ ባለው የሥራ መስክ እያዋሉት ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ግን ይህንን እምቅ አቅማቸውን አልተጠቀመችበትም የሚለው አሳብ ከግራና ከቀኝ በመወራጨፉ ቤተ ክርስቲያን ወደ ባሰ ውጥረት ውስጥ ልትገባ ችላለች፡፡ ከተሰጠን ስጦታ፣ ችሎታችንና ዜአችን ከፍለን ከቤተ ክርስቲያን ዉጭ ላለው ሥራ ማዋል ምንም ስህተት የለበትም ፣ግን የእግዚአብሔር ሰዎች ከመንፈስ ቅዱስ ተሰጣቸውን መንፈሳዊ ስጦታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሕዝቡ የጋራ ጥቅም እንዲያውሉት ታዘዋል( 1 ቆሮ. 127)፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ለእግዚአብሔር ቤት ፍቅር ያላቸው ሴቶች በችሎታቸው የውጭ ድርጅቶችን ቢያገለግሉም በቤተ ክርስቲያናቸው እንደ ልባቸውና እንደ ተሰጣቸው ስጦታና የአገልግሎት ጥማት ያህል ካላገለገሉ ደስተኞች አይሆኑም፡፡ በርካታ ቤተ እምነቶች እነዚህንና መሰል ኩርፊያዎችን ለማብረድ ሲሉ ባያምኑበትም ሴቶችን ወደ አመራር ተሳትፎ እያመጡ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶች በእምነት አቋማቸው የተጻፈውን እንኳን ሳያሻሽሉ ነው ሴቶችን አመራር ሰጭ እያደረጉት ያለው፡፡ ለምሳሌ በእምነት አቋማቸው የሴቶችን መሪነት እንደማይቀበሉ የሚያሳይ ሐሬግ ተቀምጦ ሳለ አስተዳደራዊና የአመራረር መዋቅራቸውን እየቀየሩ ያሉ ቤተ እምነተች አሉ፡፡ ሴቶችን ወደ አመራር ከማምጣታቸው በፊት የእምነት አቋማቸውን እንዳይከልሱና እንዳያሻሽሉ የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ ነገር ግን የሴቶችን አመራር በሚከለክለው የእምነት አቋማቸው ምንም ለውጥ ሳይደረግበት ሴቶችን ወደ አመራር ሰጭነት ቦታ እያመጡ ይገኛሉ፡፡ ይህ የሚሆነው በእርግጥ ታምኖበት ሳይሆን ኩርፊያው እያየለ ቢሄድ በቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል በሚል የተደረገ ይመስላል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ከመጀመሪያውም ቢሆን ሴቶች አመራር ሰጪዎች መሆን እንዳለባቸው የሚያምኑና በዘርፉ እያሳተፉ ያሉ ቤተ እምነቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ቤተ እምነቶች ሴቶች በሽምግልና፣ በወንጌላዊነት፣ በመጋቢነት፣ በሌሎች የአስተዳደር ሥፍራዎች ወዘተ ተሹመው ጉባኤያቸውን እየመሩ ናቸው፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡአቸው በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ክፍሎችም አሉአቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙ ሴቶች በትላልቅ ቤተ ክርስቲያናት አመራር በመስጠትና በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ባለበት ጉባኤ ፊት እየሰበኩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል እነ ዶር ሪታ ትዊጅስ፣ዶር ካሮልይን ሾዌል፣ዶር ጃስሚን ስኩላርክ እና ሌሎች ብዙዎች በስብከት አገልግሎታቸው በተለይም በአዲስ እምነት እንቅስቃሴዎች ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት ወንድ ፓስተሮች የአሰባበክ ስልታቸውን እንደ ሴቶች ለማድረግ ሲጥሩ ይስተዋላሉ፡፡ የቃላት አጠቃቀማቸው፣የድምፃቸው ቅላጼ አወጣጡ፣ የመድረክ አቋቋም፣ ከስብከት በፊት ለጉባዔ የሚሰጠው የሰላምታ አቀራረብ ሁሉ የተለየ ሲሆን በኢትዮጵያና በሌሎች የውጭ አገሮች መድረክ ላይ የሚወጡ አንዳንድ ወንዶች የእነ ዶር ጃስሚን ስኩላርክን አይነቱን እንቅስቃሴ እየገለበጡ እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ለምሳሌ ፓስተር ቶሚ ባቴስ ወንድ ነው፡፡ የእርሱን የስብከት አቀራረብ ከዶር ስኩላርክ ጋር ማነጻጸር ብቻ በቂ ነው፡፡ በስም መጥቀስ ባያስፈልግም የኢትዮጵያዎቹም ወንድሞቻችን አንዳንድ ስታይላቸውን የቀዱት ከዚያው ነው፡፡ ለጋ ወጣቶቹ ከአገር ቤቶቹ ታላላቆቻቸው ሲገለብጡ ፣ ቀዳሚዎቹ ግን ከምእራቡ ተሌብዥን መሆኑን ከስብከት አቀራረባቸው እስከ ሰውነት እንቅስቃሴአቸው ያለው ሁኔታ ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ሴቶች እህቶቻችን በአንድም ሆነ በሌላ ተጽእኖ እያሳደሩ ለመሆናቸው ምልክት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሴቶች አገልግሎትና አመራር ምን ይላል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ይሆናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የማይለወጥና የማይሻር የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ክርስቲያኖች ሁላችንም እናምንበታለን፡፡ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ለሚተገበሩ ሥራዎች፣ ለትምህርቶችና ለስብከቶች፣ እንዲሁም ደግሞ ለሚወሰዱ የሥነ ሥርዓት ርምጃዎች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መሆን አለበት፡፡ በተለይም ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አመራር በእግዚአብሔር ቃል መፈተሽ እንዳለበት የታመነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መልስ የማይሰጥባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን አመራርን በተመለከተ ግን ግልጽ መመሪያ ያስቀምጥልናል፡፡ አንድ የቤተክርስቲያን ሽማግለሌ፣መጋቢ፣ወይም ቄስ ምን ዓይነት ሰው መሆን እንዳለበትና፣ ማንስ አመራር ሰጪ መሆን እንደሚገባ የማያሻማ መመሪያ ተሰጥቶናል፡፡ ይህንን ግልጽ የሆነ መለኮታዊ መመሪያ በመከተል ቤተ ክርስቲያንን መምራት ለጤናማ አገልግሎትና አመራር ይጠቅማል፡፡ የአምላካችን ቃል በማያሻማ ሁኔታ የሚያስቀምጠው ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡
1. ከተፈጥሮ አንፃር.
ከተፈጥሮ አንጻር ስንል ከሰብአዊ ማንነት አንጻር ማለታችን እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ወንዶችና ሴቶች ሁለቱም በእግዚአብሔር የተፈጠሩ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሰው የሚለው ወንድንም ሴትንም ጭምር ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንደ መልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር ሲል፣ በራሱ መልክና አምሳል የፈጠረው ወንድንም ሴትንም ነው ( ዘፍጥረት 126-27)፡፡ ሁለቱም በእግዚአብሔር አምሳል ስለ ተፈጠሩ በስብእናቸው ምንም መበላለጥና መተናነስ ሳይኖር እኩል ናቸው፡፡ ወንድም ሴትም የእግዚአብሔርን ባህሪይ ያንፀባርቃሉ፡፡ ይህ ማለት በእያንዳንዳቸው የሕይወት አኗኗር የእግዚአብሔርን መልክና አምሳል የተባለውን መንፈሳዊ ባህሪያትን እናያለን ማለት ነው፡፡ ሁለቱም በእግዚአብሔር አምሳል ስለ ተፈጠሩ ለእግዚአብሔር ያላቸው ተፈላጊነት፣ለሰውም ያላቸው ጠቃሚነት እኩል ነው፡፡ በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠው አዳም ብቻ ሳይሆን ሔዋንም ጭምር ናት(ዘፍ 51)፡፡ በዚህም ወንድና ሴት የሚባለው የጾታ ልዩነት እንጂ የስብዕና ልዩነት አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ ሰው የተለያየ ጾታ ይዞ ወንድና ሴት ሆኖ መፈጠሩ አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ የሚያደርግ ሳይሆን ለሁለቱም የጋራ ጥቅምና ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሆን ነው፡፡ ሴት ያለ ወንድ ፣ ወንድም ያለ ሴት ሊሆኑ አይችሉምና፡፡ የአንዱን ጉድለት ሌላው ይሞላዋል፣ በድካሙም ያግዘዋል፡፡ እግዚአብሔር አንዱን ጌታ ሌላው ተገዥ አድርጎ ሳይሆን አንዱን የሌላው ረዳት፣ ሌላውን ደግሞ የበለጠ ኃላፊነት ተሸካሚ አድርጎ ነው የፈጠረው፡፡ ወንድና ሴት በፆታ ይለያዩ እንጂ የእግዚአብሔር መልክና አምሳል በሁለቱም በመገለጡ በተፈጥሮ አንዱ ከአንዱ ምንም ልዩነትና የክብር መበላለጥ ሳይኖር እኩል ናቸው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም እኩል ስለሆነ ምንም ዓይነት የበላይነትና የበታችነት የለም፡፡ ስለዚህ ወንድም ሴትም አንዳቸው ለአንዳቸው ክብር ሊሰጡ ይገባል( ምሳሌ 31102830)፡፡ ወንድ ስለ ሴት ሴትም ስለ ወንድ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባቸዋል፡፡

2. ከድነት አንፃር
ድነት እግዚአብሔር የሰዎች ልጆች በኃጢአት ምክንያት ከመጣባቸው የዘላለም ሞትና ፍርድ እንዲድኑ በልጁ በኢየሱስ በኩል ያዘጋጀላቸው የማምለጫ መንገድ ነው፡፡ ወንድም ሴትም ኃጢአተኞች በመሆናቸው ድነት ያስፈለገው ለሁለቱም ነው (ሮሜ 323)፣ በወንጌል ስብከት አምነውና ድነው የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑት ወንዶችም ሴቶችም ናቸው (ዮሐ 112፣ገላ 327-28)፡፡ እግዚአብሔር ያዘጋጀው የደህንነት መንገድና የቃል ኪዳን ተስፋ ያለ ምንም ልዩነት ለወንድም ለሴትም የተሰጠ ነው ( ገላትያ 43) ፡፡ ሐዋሪያው ዮሐንስ ስለ አመኑት ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል፡፡ ለተቀበሉት በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው ዮሐ 112)፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን በጌታ በኢየሱስ በማመን የሚገኝ ሥልጣን ነው፡፡ ያመኑት ሁሉ ለእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጌታ በማመናቸው ብቻ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ ስለዚህ ነው ጳውሎስ "አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና" ያለው( ገላትያ 327-28)። የዳኑት ልጆች ደግሞ የመንግሥቱ ወራሾች ናቸው፡፡
3. ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አንፃር
በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን አገልግሎት በተመለከተ መንፈስ ቅዱስ በወንድም በሴትም ያለ ልዩነት ስጦታ አፍስሷል፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደሚፈስና ሰዎችም እንደ ተሰጣቸው ስጦታ መሠረት እንደሚያገለግለሉ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ ትንቢቱ እንደሚከተለው ተቀምጧል፡፡ ህ በኋላ እንዲህ ይናል፤መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንደችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ሽማግሌዎችም ሕልምን ያልማሉ፤ጎበዞቻችሁም ራእይ ያሉ፤ደግሞም በዚያን ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈስሳለሁ( ኢዩኤል 228-29)፡፡ ይህ ትንቢት ፍጻሜን ያገኘው የእግዚአብሔር መንፈስ በዓለ አምሳ በተባለው ቀን በኢየሩሳሌም ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ ጊዜ ጀምሮ የፀጋ ስጦታ የተሰጠው ያለ ምንም ልዩነት ለወንድም ለሴትም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ወንድም ሴትም በተሰጣቸው የጸጋ ስጦታ  ቤተ ክርስቲያንን እኩል ያገለግላሉ፡፡ ሴቶች በጸጋዎቻቸው በማገልገል ብዙዎችን ጠቅመዋል፡፡ ለምሳሌ፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአገልግሎቱ ወቅት ያገዙት ሴቶች ናቸው(ሉቃስ 81-3)፡፡ እንደነ ፌቤን ዓይነቶች ደግሞ የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ነበሩ (ሮሜ 161-3)፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለወንድ ብቻ ሳይሆን ለሴቶችም ጭምር የተሰጠ ነው፡፡ እንዲያውም ያለ ሴቶች ተሳትፎ መንፈሳዊ አገልግሎት ጉድለት የበዛበት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡ ወንድ ብቻ ያለበት ኳየር አለ፡፡ ሌላ ደግሞ በርከት ያሉ እህቶች ያሉበት ኳየር ደግሞ አለ፡፡ የትኛው የበለጠ ሰሚውን የሚያነቃቃው ቢባል ሁለተኛው ነው፡፡ የጸሎት አገልግሎት፣ የወንጌል ምስክርነት አገልግሎት፣ የዲቁና አገልግሎት ወዘተ በእህቶቻችን ተሳትፎ ምክንያት አገልግሎት ምክንያት ሕይወት ያገኛል፡፡ ስለዚህ እህቶቻችን በጸጋ ስጦታቸው የሚሰጡትን አገልግሎት ቤተ ክርስቲያን መጠቀም አለባት፡፡
4. ከቤተ ክርስቲያን አመራር አንፃር
የቤተ ክርስቲያን አመራርን በተመለከተ እግዚአብሔር ለሴቶችና ለወንዶች የሰጠው ኃላፊነት የተለያየ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ባለች በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ውስብስብና አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም የሴቶች አገልግሎትና ክህሎት እየጎላ በመምጣቱ ነው፡፡ ከፍ ብሎ እንደተገለጸው ሴቶች በመድረክ አገልግሎታቸው ተጽእኖ ማሳደር እየቻሉ ናቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባለው አመራር ቦታዎችም ላይ ክርስቲያን የሆኑ ሴቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ የአመራር ብቃታቸው እያደገና ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ሰዎች ይህንን በሚያዩበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያንም አመራር ቢሰጡ ውጤታማ ይሆናሉ ወደሚለው ድሚዳሜ ለመድረስ ተገድደዋል፡፡ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት የቱ እንደሆነ እንመልከት፡፡
አንዱና ትልቁ አነጋጋሪ ጉዳይ የሆነው የሹመት ጥያቄ ነው፡፡ ሴቶች አመራር ሰጪ ሆነው መሾም ይገባቸዋል ወይ የሚለውን የተመለከትን እንደሆነ ትክክለኛ መልሱ ለመስጠት የሚቻለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ አፈታት መርህ ስንከተል ብቻ ነው፡፡ ሹመት ምን እንደ ሆነና ምን እንደሚያካትት በውል መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን በከፍተኛ የአመራር ቦታ ስትሾም ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከእግዚአብሔር የተሰጠውን በሰዎች ያለውን ስጦታ ለማስተዋወቅ፣ ለማበረታታትና እውቅና ለመስጠት ነው፡፡ ሹመት ቅድስናን ወይም የተለየ መለኮታዊ ኃይል እንደማያስገኝ የታወቀ ነው፡፡ ቢሆንም እግዚአብሔር በአመራር ስጦታ የባረካቸው ሰዎች ስጦታቸውና አመራራቸው ሕዝባዊ እውቅና የሚያገኘው በሹመት ነው፡፡ አንዲት ቤተ ክርስቲያን አመራር ሰጪዎችን በምትሾምበት ጊዜ እውነትን ከማስተማርና ከመስበክ በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄዱ፣እንደ ጥምቀት፣ ቅዱስ ቁርባን፣ጋብቻ፣ የልጆች ቡራኬ፣ አባላትን የመቀበልና የማሰናበት፣ እንዲሁም የአማኞችን የቀብር ሥርዓት የመሳሰሉ ቅዱስ ሥርዓቶችንም እንዲያስፈጽሙ ሙሉ ቤተ ክርስቲያናዊ መብትና ሥልጣን ( Ecclesiastical Authority ) በመስጠትም ጭምር ነው፡፡
የቤተ ክርሰቲያን ሹመት ( Ecclesiastical Ordination) የዓለም አቀፋዊና የአጥቢያዊ ነው፡፡ በአለም አቀፋዊ ሹመትና በአጥቢያዊ ሹመት መካከል ትርጉም ያለው ልዩነት አለ፡፡ ድንበር ዘለል የሆነ አገልግሎት ( Cross cultural or Global ministry) የሚሰጡት መጋቢያን፣ ወንጌላውያን፣ ሚሲዮናውያን ሲሆኑ የእነዚህ አገልግሎት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የአጥቢያዊ አገልግሎት( Local church ministry) ማለት ደግሞ ለአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቻ ኃላፊነት ይዞ እንዲያገለግሉ የሚደረግ ሹመት ሲሆን በዚህ የሚካተቱት ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ናቸው፡፡ ሽማግሌዎች ከራሳቸው አጥቢያ ውጭ የአመራር ሥልጣናቸውን መተግበር የማይችሉት ለዚህ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ሴቶች ለቤተ ክርስቲያን አመራርና ለመንፈሳዊ ሥልጣን ቦታ መሾም አይኖርባቸውም፡፡ ምክንያቱም የሴቶች አመራር በአዲስ ኪዳን እውቅና ያገኘ አይደለም፡፡ ይህን ስል ሴቶችንና አገልግሎታቸውን ላለመቀበል ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል መከበሩ ለሴቶች ለራሳቸውም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በረከት ስለሆነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሴቶችን አገልግሎት ያበረታታል፣ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ታደርጋለች፡፡ ነገር ግን አመራር መስጠትና በጸጋ ስጦታ ማገልገል ለየብቻ መተንተን ያለባቸው ቁም ነገሮች ናቸው፡፡ ለምንድነው ሴቶችን ኤጰጵስ ቆጶስ ወይም የበላይ አመራር ሰጪ ማድረግ የለለብን?
1. የሴቶች አመራር መጽፍ ቅዱስ ውስጥ እውቅና አላገኘ፡፡
ይህንን ከፍ ብሎ ተመልክተነዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሁለት ምሳሌዎችን መመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በብሉይ ኪዳን የእሥራኤልን ሕዝብ መንፈሳዊ አገልግሎት የመሩት ካህናትና ነቢያት ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከየነገዱ የተመረጡ የሕዝብ አለቆች ከነገሥታት ጋር በመሆን ሕዝቡን መርተዋል፡፡ በዚያን ጊዜ በጣም ብዙ የእሥራኤል ሴቶች ልጆች እንደ ነበሩ የታወቀ ነው፡፡ እንደነ ሐና ያሉ በጸሎት የተጉ፣ እንደነ ሩት ያሉ እግዚአብሔርን በብዙ መስዋዕትነትና በቁርጠኝነት ለመከተል የወሰኑ፣ እንደነ ረዓብ አይነቶች ምድርቱን የሰለሉትን የእግዚአብሔርርን መልእክተኞችን በእምነት የተቀበሉና ያስተናገዱ ወዘተ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የሕዝቡን መንፈሳዊ አመራር በተለይም በሊቀ ካህንነትና በካህንነት እንዲያገለግሉ ሴቶች አልተሾሙም፡፡ በ2ኛ ዜና 2212 ጎቶልያ የተባች ሴት መንገሥዋን ብናነብም ምን ያህል ጊዜ እንደ ነገሠችና ለንግሥትነትስ ማን እንደቀባት የሚነግረን ምንም ነገር የለም፡፡ ያቺ ሴተት ወደዚያ ቦታ የመጣችው በእግዚአብሔር ፈቃድ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም  ያለ እግዚአብሔር ዕቅድና ፈቃድ ራሳቸውን ንጉስ ብለው የሾሙና ያልተሳካላቸው እንደነ አቤሴሎም አይነቶች ወንዶችም አሉና፡፡ ጎቶሊያም የአንድ ወቅት መጋጋል ያመጣባት ድንገተኛ ነገር ያደረገች ይመስላል፡፡ እርሰዋ እኮ የንጉሡ የአካዝያስ እናት ነበረች እንጂ ለንግሥትነት የሚያበቃት ምንም መሠረት ኖሮአት አልነበረም፡፡ አካዝያስ ለሞተ በኋላ ከቤቱ መንግሥት የሚይዝ ስላልተገኘ እንዲሁ በልሁንታና በድፍረት አደረገችው እንጂ ያ ቦታዋ ሆኖም አልነበረም፡፡
ነገስታት፣ ነቢያትና ካህናት የምንለው በእግዚአብሔር ፈቃድ በካህናት እጅ በመቀባት፣ የትንቢትንም መልእክት ከእግዚአብሔር ተቀብለው የሚቀቡ ነገሥታትና እግዚአብሔር ለዚያ አገልግሎት በቀጥታ ጠርቶአቸው የሚያገለግሉትን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ተቀብተውና ተሹመው ያገለገሉ ሴቶች አልነበሩም፡፡ብዙ መንፈሳዊ ቃላትን የተናገሩ ቢኖሩም በእግዚአብሔር ተልከው ስለ እርሱ ለሕዝቡ የተናገሩ ነቢያት የምንላቸው ሴቶች በብሉይ ኪዳን አልነበሩም፡፡ መቼም ቢሆን ትንቢት የተናገረ ሁሉ ነቢይ ነው የሚል መጽሐፍ ቅዱሱን በደንብ የሚያነብ ሰው አይኖርም፡፡ ትንቢት መናገር ብቻውን ነቢይ አያደርግምና፡፡ ለምሳሌ ጳውሎስ እጅ ጭኖ ሲጸለልይ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በልሳን የተናገሩ፣ ትንቢትም የተናገሩ 12 ሰዎች ትንቢት ስለ ተናገሩ ብቻ ነቢያት ናቸው ካልን እንሳሳታለን( ሐዋ. 191-6)፡፡ በእሥራኤል ሕዝብ ታሪክ የሴቶችን ነቢይነት፣ ካህንነትና ሊቀ ካህንነት እንዲሁም የንጉሥነት ሚና አናይም፡፡ በወቅቱ ሴቶች ስላልነበሩ ወይም ብቃት ስለሚያንሳቸው ሳይሆን እግዚአብሔር የአመራር ኃላፊነቱን የሰጠው ለወንዶች ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህ አንዱ አሳብ ሲሆን ሌላ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስም በምድር ላይ ባገለገለበት ወቅት በጣም ትጉና የተመሰከረላቸው ሴቶች ነበሩ፡፡ ቢሆንም ከሐዋሪያት መካከል አንድም ሴት አልተገኘችም፡፡ እንደ እኛ አመለካከት ቢሆን ሌባው አስቆሮቱ ይሁዳ ቀርቶ በእንባዋ የጌታችንን እግር ያራሰችው መግደላዊት ማሪያም ለሐዋሪያነት በተመረጠች ነበር፡፡ ተጠራጣሪውን ቶማስን አቆይተን እስከ መስቀል ድረስ ኢየሱስን የተከተሉትንና በትንሳኤውም እለት ከሁሉም በፊት የድንጋዩን መንከባለልና የመቃብሩን ደጅ መከፈት ቀድመው አይተው የመጀመሪያዎቹ የምሥራች አዋጅ ያሰሙትን እነ ማሪያንና ሴሎሜን ሐዋሪያ ባደረግናቸው ነበር፡፡ በገንዘባቸው ጌታን ያገለገሉትን ለጋስና ታማኝ ሴቶችን ትቶ ከእግዚአብሔር ቤት ገንዘብ የሚሰርቀውን እንደ ይሁዳ ያሉትን እንድንመርጥ የእኛ ልብ አይፈቅድም፡፡ ጌታ ግን እነዚህን ሁሉ ከእኛ በላይ ቢያውቃቸውም አንዳቸውንም ለሐዋሪያዊ አገልግሎት አልመረጣቸውም፣ አልሾማቸውምም፡፡
የሐዋሪያዊነት መስፈርት ከሆኑት አንዱ ጌታ ኢየሱስን ከጥምቀቱ እስከ ርገቱ ድረስ፣ እርሱ በወጣበትና በገባበት ሁሉ ከኢየሱስ ጋር የነበረ ለትንሳኤውም የዓይን ምስክር መሆን የሚችል እንደ ነበር በሐዋሪ 1፡ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ታዲያ እኮ እነ ማሪያም ከኢየሱስ ጋር ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መስቀል ድረስ አብረው ነበሩ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከሙታን መነሳቱንም ቀድመው ያዩ እነርሱ ነበሩ፡፡ እነ ጴጥሮስ ኢየሱስ መነሳቱን የሰሙት ከሴቶች እኮ ነው፡፡ እንዲያውም ከወንዶች አንዱ (ቶማስ ይባላል) ኢየሱስ በአካል በመካከላቸው ቢገለጥም እንኳ ሊያምን አልቻለም፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ለአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን አመራር ሴቶች አልተሾሙም፡፡ እነ ጵርስቂላ ፣ እነ ልዲያ ፣ዮሐና ፣ሶሲና መሪ መሆን አይገባቸውምን? በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ መሲሁን ካገኘቺው በኋላ የከተማውን ሰው ሁላ ጋብዛ ወደ ኢየሱስ ያመጣችውና ለብዙዎች መዳን ምክንያት የሆነቺው የሳምራዊቲቱ ሴት ሐዋሪያ ሆና ልትሾም አይገባትምን? የጌታ ደቀ መዛሙርት ምግብ ገዝተው እስክመለሱ ድረስ ብዙዎችን ወንጌል ሰምተው ከእየሱስ ጋር እንዲተዋወቁ አድርጋለች(ዮሐ. 439-42)፡፡ በእርግጥ በሰው ዓይን ሲታይ እነዚህ ሁሉ መሪነት ብቻ አይደለም ከዚያም የሚበልጥ ቢኖር የሚገባቸው ናቸው፡፡ የአሁኗም ቤተ ክርስቲያን የእህቶችችንን ትጋትና መልካም ቅንዓት እያየች ለምን አልጠቀምባቸውም በሚል ሹመት እየሰጠች ትገኛለች፡፡ እኔ ራሴ የአንዳንዶችን ሕይወት ሳይ እኔ ምንድነኝ ለምንስ ይህቺ እህት አታገለግልም እስከምል ድረስ የሚያስደንቅ አገልግሎት የሚሰጡ አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ግን የእኛ ምኞት እንጂ የእግዚአብሔር ቃል የሚያውቀው አይደለም፡፡ ስለዚህ እህቶቻችን ለመሪነት መሾም አይኖርባቸውም፡፡

2. እግዚአብሔር ወንዶችን የሴቶች ራስ አድጓል፡፡
ወንድ የሴት ራስ ነው፡፡ ይህ ራስነት በቤትም በቤተ ክርስቲያንም ነው፡፡ እግዚአብሔር ወንድን ራስ አደረገው ስንል በሴቷ ላይ የበላይ ገዥ አደረገው ማለታችን እንዳይደለ ልብ እንበል፡፡ ራስነት የኃላፊነትና የስልጣን ድርሻ የተለየ መሆኑን የሚያመለክት እንጂ የእኩልነትን ቦታ መቀማትም አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሐር ወልድ መካከል ያለው ግንኙነት በባልና በሚስት እንዲሁም በወንዶችና በሴቶች መካከል ላለው ግንኙነት እንደ ሞዴል መወሰድ ይኖርበታል፡፡ የሴቶችን ሹመት አለመቀበል ሴቶችንና አገልግሎታቸውን ዝቅ እንደ ማድረግ የሚተታሰብበት ጊዜ ሁሉ አለ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች፣ሴቶችና ወንዶች በእግዚአብሔር ፊት እኩል ዋጋ እንዳላቸው በግልጽ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር አብና ወልድ እኩል መለኮታዊ ማንነት ያላቸው ቢሆኑም አብ የወልድ ራስ ነው ተብሏል፡፡ ይህ ማለት ወልድ ከአብ ያንሳል ማለት ግን አይደለም፡፡ ወልድ በራሱ ፈቃድ በመታዘዝ ራሱን ለአብ እንዳስገዛ፣ አብም ወልድን እንደ ወደደው እንመለከታለን፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ባል ሚስቱን እንዲወድና ሚስትም ለባሏ ራስዋን እንድታስገዛ ጳውሎስ በቃሉ ይገግረናል፡፡ የአብና የወልድ እኩልነት በቤተሰብና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለወንዶችና ለሴቶች እኩልነት ምሳሌ ሆኖ መታየት አለበት የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ ራስን ለሌላው ማስገዛት የበላይነትና የበተታችነት ጉዳይ ሳይሆን የተለያየ የአገልግሎትና የአመራር ሚና የመቀበል ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራስን የማስረከብ አሳብ የበታችነት አሳብ ተደርጎ የሚወሰድበት አጋጣሚ ቢታይም ራስን ለሌላው በፈቃደኝነት ማስገዛት መለኮታዊ መርህ እንጂ ሰው ሲፈልገው የሚያደርገው፣ ሳይፈልገው ሲቀር ደግሞ የሚጥለው ተራ ተግባር አይደለም፡፡
ኢየሱስ ከእርሱ ጋር በሐዋሪያዊነት አገልግሎት እንዲያገለግሉ ወንዶችን ብቻ የመረጠው እግዚአብሔር ለወንዶችና ለሴቶች የተለያየ ተግባር ስለ ሰጠ ነው፡፡ ለመሆኑ ኢየሱስ ተሳስቷልን? በጭራሽ! ወንድን የሴት ራስ የማድረግ መብት ሰውን ሁሉ የፈጠረው የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ውሳኔ ነው እንጂ ሰው የሚያደርገው አይደለም፡፡ በመሠረቱ ወንድ ወይም ሴት ሆኖ መፈጠር በሰው ምርጫ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ማንም እኔ ወንድ መሆን አልፈልግም ሴት ቢሆን ይሻለኛል ብሎ ከእግዚአብሔር ጋር ሊከራከር አይችልም ፣ሴትም እንደዚሁ፡፡ የመፈጠራችን ምስጢር በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ውሳኔ የተከናወነ ነው፡፡ ራስና አካል መሆንም የተወሰነው በእግዚአብሔርር እንጂ ሰው ስላልወደደ የሚለወጥ ወይም ስለ ተስማማ የሚፀድቅ አይደለም፡፡ ስለዚህ በቤተሰብም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ራስነት(headship) የተሰጠው ለወንድ ስለ ሆነ ሴቶች ይህንን ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ሥልጣንን ለወንድ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ሴቶች ለወንዶች ሥልጣን መገዛት ይኖርባቸዋል እንጂ በወንድ ላይ ሊሰለጥኑ አይገባቸውም፡፡ በቤተ ክርስቲያንን የሥልጣን ይይዙ ዘንድ ቦታቸው አይደለምና፣ አልተፈቀደላቸውምና ለወንዶች ሥልጣን በፈቃዳቸው መገዛት ይኖርባቸዋል፡፡፡፡
3. የሔዋን የፈጠሯ ምክንያት( ዘፍጥረት 218)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ሴት ስለ ወንድ ተፈጥራለች ብሎ በግልጽ ይናገራል፡፡ ሰው ለብቻው ይሆን ዘንድ መልካም አይደለምና የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት(ዘፍ.218)፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክትም ይህንኑን ያስተምረናል፤ ያዘናልም፡፡ ሴት ግን በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር፣ ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ እንድትሰለጥን አልፈቅድም፡፡ አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና በኋላም ሔዋን ተፈጥራለች(1ጢሞ. 211)፡፡ በዚህ መሠረት ሴት ከወንድ በኋላ ስለ ተፈጠረች በወንድ ላይ ልትሰለጥን አይገባትም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በሌላ ሥፍራ ጳውሎስ ሴት ስለ ወንድ ተፈጥራለች የሚለውን ቃል በግልጽ ያስቀምጠዋል፡፡ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት፣ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና፡፡ ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረምና(1ቆሮ.119)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን በግልጽ እያስተማረ እያለ አንዳንድ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አመረራረር ካልሰጠሁ፣ሥልጣንንም ካልተለማመድኩ በሚል ቤቱን ያወዛግባሉ፡፡ አንዳንዶች የሚከራከሩት ስለ ሴቶች እኩልነት ነው፡፡ ሴትና ወንድ እኩል ስለ መሆናቸው ምንም ጥያቄ ሊኖርብንና ሊያድርብን አይገባም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ሴቶች የላቀ ነገር ይታይባቸዋል፡፡ ውይይታችን የሥልጣን ሥፍራንና የአገልግሎት ኃላፊነትን(ministerial function) ከመከፋፈል አንጻር እንጂ ከሰብአዊ እኩልነት አንጻር አይደለም፡፡ ሁላችንም የምንረዳው አንድ እውነት አለ፣ያውም መገዛት ከሌለ ሥልጣን የለም፣ ሥልጣንም ከሌለ መገዛት የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ ሥልጣን ባለበት አመጽና ጦርነት ወይም ትርጉም አልባ ተቃውሞ ጥፋትን ያስከትላል እንጂ ለሰው ጥቅምም ሆነ ለእግዚአብሔር ክብር አይሆንም፡፡
በእርግጥ በጥንት ዘመን ሴቶችን ከእንስሳ ወይም ከእቃ ለይቶ የማያይ እግዚአብሔር ያልወደደው የሮማውያንና የግሪኮች ባህል እንደ ነበረ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ አይሁዶች በፀሎታቸው ወቅት ሴት ፣አህዛብና ባሪያ አድርገህ ስላልፈጠርከኝ አመሰግናለሁ ይሉ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ በኩል ወንጌል ለሰዎች ሁሉ ከተነገረ በኋላ ሴቶች በስብዕናቸው፣በአካላቸው፣ በመንፈሳዊነታቸው፣ በችሎታቸውና በብቃታቸው በሁሉም ከወንዶች ጋር እኩል መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ የሴቶችን የአገልግሎትና የአመራር ሚና ከወንዶች መለየት እነርሱን እንደ ማሳነስ ተደርጎ መወሳት የለበትም፡፡ የአመራር ሚና ለይቶ የሰጠው እግዚአብሔር እንጂ የሰው ጉዳይ ስላይደለ ሁሉም በየቦታው ቢሆን ለጋራ ጥቅም ይረዳል፡፡ እግዚአብሔር በማያሻማ ሁኔታ በቤትና በቤተ ክርስቲያን የበላይ አመራር የወንድ እንደ ሆነ አሳይቶናል፡፡ የስልጣንና የመገዛት ምሳሌው በጌታችን በኢየሱስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደ ተገዛች ሚስት ለባልዋ ትገዛ ይለናል፡፡ ሚስት ለባልዋ ራስዋን ማስገዛት እንደዳለባት የምንክድ ከሆነ ቤተ ክርስቲያንም ለክርስቶስ መገዛት እንዳለባት ልንክድ ነው ማለት ነው፡፡
ሴት ለወንድ መገዛት ያለባት ለምንድነው ቢባል ከፍ ብለን እንደተመለከትነው ወንድ ቀዳሚ ስለ ሆነ ነው፡፡ ወንድ ከመጀመሪያው ከሴት አልተገኘም፣ ከሴት አልተፈጠረም ወይም አልተወለደም፡፡ እግዚአብሔር ወንድን አስቀድሞ ከፈጠረ በኋላ ሁሉን የመቆጣጠሩን ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ሴት የወንድ ረዳት እንድትሆን ከወንድ ከራሱ ነው የፈጠራት፡፡ ወንድን ከአፈር ጭቃ ሲያበጀው ሴትን ግን ከራሱ ከወንድ አካል ክፍል ወስዶ ሠራና ረዳቱ እንድትሆን አደረጋት፡፡ ወንድ ከሴት ሳይሆን የተገኘው ሴት ግን ከወንድ ተገኝታለች፡፡ እግዚአብሔር ሁለቱን አንድ ላይ መፍጠር ይችል ነበር ግን የእርሱ አሠራር እንደዛው አልነበረም( ዘፍጥረት 218)፡፡
እንግዲህ የሴቶችን የአፈጣጠር ሁኔታ ስንመለከት አንድ መሠረታዊ ነጥብ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ሴቷ የተፈጠረችው የወንዱ ተስማሚ ረዳት እንድትሆን ነው፡፡ ይህ እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ነው፡፡ እግዚአብሐር ሴትን የፈጠረበት መንገድ ራሱ በቤት ለባሏ በውጭ ማለትም በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ለወንዶች ረዳት ልትሆን በምትችልበት መልክ ነው፡፡ ካልተሰጠው በቀር ማንም የማን ረዳት ሊሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሴት ረዳት እንድትሆን ሲያደርጋት የወንድ የበታች ማድረጉ ሳይሆን የርሱን ተግባር እንድትወክል በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ከፈተጠራባቸው የማዕረግ ስሞች አንዱ ረዳት የሚል ነው፡፡ እኔ ረዳት ነኝ ብሏል(መዝ 1014211)፡፡ እግዚአብሔር ራሱ ረዳት ተብሎ ሊጠራ ካላፈረብን እህቶቻችን የወንዶችና የባሎቻቸው ረዳት መሆን የሚከብዳቸው ለምንድነው? ረዳ የሚለውን ቃል የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ወደ ግሪክ የተረጎመው ሰፕቱአጂንት የተሰኘው የሊቃውንት ጉባኤ ሀኪም ከሚለው ቃል ጋር እንዳመሳሰለው የሥነ መለኮት ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ሐኪም ለበሽተኛ ልዩ ርዳታ እንደሚያደርግለት ሴትም በሚያስፈልገው ሁኔታና ቦታ እንዲሁም ምቹና ምቹ ባልሆኑ ጊዜያት ሁሉ ለወንድ ርዳታ ታደርግለታለች፡፡ ስለዚህ ርዳታ የሚያደርግ የበታች ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ እግዚአብሐሔርን ለሚፈሩ ሴቶች ከባድ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ለባሏና የቤተ ክርስቲያን የወንዶች ኤጵስ ቆጶሳዊ አገልግሎት ተገዥና ረዳት ናት፡፡ ሥልጣኑ ግን የባል ወይም የወንድ እንዲሆን እግዚአብሔር ወሰኗል፡፡
4 . ለሴት ስም የማጣት ኃላፊነት የተሰጠው ለወንድ ነው፡፡
አዳም ለሔዋን ስም ማውጣቱ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ኃላፊነት የሚያሳይ ነው፡፡ በእግዚአብሔርን ቃል ስንመለከት ለቤተሰቡ ስም የማውጣት ሥልጣን ያለው ወንድ ወይም የቤቱ አባወራ ነው፡፡ ብዙ ሴቶች ልጅ ሲወልዱ ስም አውጥተዋል፡፡ ሐና፣ራሄል፣ርብቃ፣ ሌሎችም ከነበሩበት ሕይወትና በዙሪያቸው ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናኘት ለልጆቻቸው ስም አውጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አባት ያንን ስም ቀይሮ ሌላ ስም ቢሰጥ ያ አባት ያወጣው ስም ይጸናል ፡፡ ይህንን ለመረዳት የሉቃስ ወንጌል 155-66ን መመልከት ይቻላል፡፡ መጥመቁ ዮሐንስ በተወለደ ጊዜ ሴቶችና ሌሎች ስም ሊያወጡ ሞክረው ነበር፡፡ ገምሶቹ ዘካሪያስ ይሁን ሲሉ ገምሶቹ ደግሞ ዮሐንስ ይሁን ሲባባሉ ቆዩና አባት የሆነው ዘካሪያስን ሲጠይቁት አፉ ዱዳ ስለሆነ ብራና እንዲያመጡለት ጠየቀና ስሙ ዮሐንስ እንዲባል ሲነግራቸው ሁሉም መስማማታቸውን እንመለከታለን፡፡ ዘካሪያስ ይሁን ያሉም ሆነ ዮሐንስ ይሁን ያሉ ከዘካሪያስ ጋር የተስማሙት እርሱ የቤቱ ራስ ስለሆነ ነው፣ ሥልጣንም የተሰጠው ለእርሱ ስለሆነ ነው፡፡ ወደ ሰው አጠቃላይ ሁኔታ ስንመለስ እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ሥልጣን መገለጫ ከሆነው አንዱ ከሔዋን ጀምሮ ለሌሎች ሁሉ ስም ማውጣቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረ በኋላ "ሰው" የሚል ጅምላ ስም ሰጠ እንጂ እያንዳንዱ የሚጠራበትን ስም አላወጣላቸውም፡፡ ውስን ስም እግዚአብሔር ያወጣላቸው ጌታ ኢየሱስና መጥመቁ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ያውም ከመወለዳቸው በፊት፡፡ የአዳምና የሔዋን ግን ይለያል፡፡ እግዚአብሔር ሴትና ወንድ አድርጎ ፈጠራቸው እንጂ  ስም የሰጠው አዳም ነው፡፡ አዳም ራሱን ወንድ ሲል ከእግዚአብሔር የተሰጠቺውን ሴት ብሎ ሰየመ፡፡ አዳም ወይም ሔዋን የሚለውን ስም ማን እንዳወጣ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለምና መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ባለው ቦታ እኛም ዝም ብንል ቢያንስ ጥፋት አይሆንብንም፡፡ እግዚአብሔር በዘፍ.3፡10 ላይ አዳም ሆይ ወዴት ነህ እያለ ቢጠራውም ያ ስም ግን በምዕራፍ ሁለት ላይ ተደጋግሞ ተጠርቷል፡፡ ማን እንዳወጣው ግን አልተገለጸም፡፡ በተለይም አምላክ ፈጥሮ ያመጣትን ረዳት ሴት ትባል ያለው እኮ አዳም ነው፡፡ እዚህ ጋ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ አንደኛው እግዚአብሔር የፈጠራትን ሴት ወደ አዳም አመጣት እንጂ አዳም ወደ እርስዋ እንዲሄድ አላዘዘውም፡፡ ሁለተኛው አዳም ሔዋንን ከእግዚአብሔር ከተረከባት በኋላ ከወንድ ተፈጥራለችና ስምዋ ሴት ትባል አለ፡፡ ይህ ወንድ የሥልጣንን ቦታ እንደተሰጠው አያመለክትምን? አዳም ስም ያወጣው ለሔዋን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ለፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ጭምር ሲሆን ይህም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ከሰጠው ሥልጣን አንዱ አካል ነው፡፡ እስቲ ቃሉን እንደገና እንመልከተው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ( ዘፍ 218-19)



ይህ አዳም ለሌሎች እንስሳት ስም ማውጣቱን የሚያሳየን የንባብ ክፍል ነው፡፡ አዳም ስማቸውን ባያወጣላቸው ሊያስተዳድራቸው ባልቻለ ነበር፡፡ ይህ እንዲሁ በድንገት የተደረገ ሳይሆን በእግዚአብሔር ዕቅድና እውቀት የተከናወነ መለኮታዊ አሠራር ነው፡፡ ፍጥረታትን የፈጠረው እግዚአብሔር ለምን ስም አልሰጣቸውም፣ ለምን አዳም እንዲሰይማቸው አደረገ የሚል ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በዘፍጥረት 223 ላይ ይህ አጥንት ከአጥንቴ ናት፣ ሥጋም ሥጋ ናት፤እስዋ ከወንድ ተገኘታለችና ሴት ትባል አለ የሚለውን ቃል ስናነብ እግዚአብሔር ሔዋንን ከሠራ በኋላ ራሱ ለምን ስም አልሰጣትም ለምን ወደ አዳም አምጥቶ ስም እንዲያወጣላት ፈቀደ;የሚለውንም ጥያቄ አብረን መመለስ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ምንም ስሕተት የማይገኝበት ፣ሁሉንም በጥንቃቄ የሚያደርግ በመሆኑ የሥልጣንን ውክልና ለሰው ያውም ለአዳም መስጠቱ ነው፡፡ አዳም ለፍጥረትና ለሔዋን ሞግዚት ሳይሆን የእግዚአብሔር ተወካይ ነው፡፡ እግዚአብብሔር ለአዳም የሰጠው ሥልጣን Vice – gerent በመባል የሚታወቀውን ነው፡፡ ሌላ ደግሞ vice-regent የሚባል የሥልጣን ውክልና ደግሞ አለ፡፡ የመጀመሪያው ሥልጣንን እንዲለማመድና በሌሎች ላይ እንዲገዛ በበላይ አካል ሹዋምነት ውክልና መቀበል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሌላው የስልጣን ባለቤተት እስክመጣ ድረስ ሥልጣን መለማመድ የሚያመለክት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ሥልጣን vice - gerent የሚባለውን ነው፡፡ እግዚአብሔር የትም ቦታ ሳይሄድ በምድርም በሰማይም ሞልቶ እያለ ፍጥረታትን የመግዛት ሙሉ ሥልጣን ለአዳም ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ሴት ለባልዋ ፈቃድ እንድትገዛ ታዛለች፡፡ እግዚአብሔር ሴት ለባልዋ እንድትገዛ ያዘዘው በኃጢአት ከወደቁ በኋላ አልነበረም፡፡ ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል ያለው በእርግጥ ሁለቱም ከተላለፉ በኋላ ቢሆንም ( ዘፍ.315-17) አስቀድሞ ሴትዋን ከፈጠራት በኋላ ወደ ወንድ አምጥቶአታል፡፡ ይህ ሴትዋ በሐጢአት ባትወድቅም ለወንድ ረዳቱ እንዲትሆንለት የሚያደርጋት የጌታ አሠራር ነው፡፡
5. ሴቷ ቀድማ ተላለፈች፡፡
የእግዚአብሔር ቃል የአዳም ኃጢአት ለሰው ልጅ ሁሉ እንደተዳረሰ ይነግረናል፡፡ በአንዱ በደል ሞት በአንዱ በኩል ነገሠ...እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኮኔነ ወደ ሰው ሁሉ መጣ....በአንዱ አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች ሆኑ( ሮሜ 517-19)፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ዓለም ሁሉ እንዲኮነንበትና እንዲፈረድበት የሚያደርገውን ሐጢአት የሠራው አዳም እንደሆነ ቢናገርም ሔዋን ለዚያ ሐጢአት  ምክንያት እንደሆነችም አልሸሸገም፡፡ የሰውን ልጅ ሁሉ የበከለው በደል ምክያንት የሔዋን ቀድማ መተላለፍ ነው፡፡ ሴት በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም፡፡ አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና፣ በኃላም ሔዋን ተፈጠረች፡፡ የተላለፈም አዳም አይደለም፣ ሴቲቱ ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች (1 ጢሞ.111-14)፡፡ እግዚአብሔር መመሪያ ሲሰጣቸው አዳምና ሔዋን አብረው ነበሩ፡፡ እባቡ ሲያታልላት ግን አዳምን ትታ የዛፉን ፍሬ ለመብላት ለብቻዋ ወሰነች፡፡ ይህ ለአዳምም ሆነ ከአዳም በኋላ ለሚመጣው የሰው ዘር ሁሉ ውድቀትን አስከተለ፡፡ ቢሆንም ጌታ ለሴቶችም የራሳቸውን የኃላፊነት ሚና እንዲጫወቱ ድርሻ ሲሰጣቸው እንመለከታለን፡፡ ሔዋን እግዚአሔር የሰጣትን ምቹ ረዳት የመሆንን ኃላፊነት ለመወጣት አልፈለገችም፡፡ እግዚአብሔር ሲሠራት ከወንድ አመራር ሥር በመሆን ረዳቱ እንዲትሆንለት ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚያ እግዚአብሔር ከሰጣት የአመራር ቦታ በራሷ ጥረት ለመውጣት ስለ ፈለገች ያለ አዳም አመራርና ምክር ፣ የእርሱም ከለላ በሌለበት ሁኔታ ለብቻዋ የራሷን እንቅስቃሴ አደረገች፡፡ እግዚአብሔር ባስቀመጣት የኃላፊነት ቦታ ለመገኘት ባለመቻልዋ ለሰው ዘር ሁሉ የሚተላለፍ ብክለትን አስከተለች፡፡ ሔዋን ከአዳም አመራር በታች መሆንን ቸል ማለት ብቻ ሳይሆን ሰይጣን በእባብ አማካይነት የሰጣትን ምክር ሰምታ ከእግዚአብሔርም ጋር እኩል ለመሆን ፈለገች፡፡ ስለዚህ ይህንን መሠረት በማድረግ ጳውሎስ ቀድማ የተላለፈቺው ሴት ስለሆነች በወንድ ላይ እንድትሰለጥን አልፈቀደም፡፡ ጳውሎስ አልፈቅድም ይበል እንጂ የመልእክቱ ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሴቷ የተታለለችው እግዚአብሔር ከሰጣት ራስ ሥር መሆንን ችላ ብላ (refusing to be under the headship ) ለብቻዋ በመሆንዋ ምክንያት ነው፡፡ 1 ጢሞ 214 የሚሳየን ያለ ወንድ የበላይ አመራር ሴት ብቻዋን ሆና ውጤታማ የሆነ መንፈሳዊ አመራር መስጠት እንደማትችል ነው፡፡ የሔዋን መሳሳት ዝም ብሎ መታለል ብቻ ሳይሆን ሊሻሻል የማይችል አሳዛኝ ተላላነት ነው፡፡ የራስዋ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ ሁሉ ሞት ምክንያት የሆነ መተላለፍ ነው፡፡ ቃሉ ተላላፈች ብሎ ይነግረናል፡፡ ተታልላም በመተላለፍ ወደቀች፣ የውድቀት ሁሉ የመጀመሪያ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ በመጣስ ወደቀች፤ ልጆቿንም ሁሉ ይዛ ተንኮታኮተች፡፡


በዛሬውም ዘመን እግዚአብሔር ከባሎቻቸውና ከመሪዎቻቸው ሥልጣን ሥር እንዲሆኑ የሰጣቸውን አመራር በመተላለፍ የራሳቸውን መንገድ የሚሄዱ ብዙ እህቶቻችን አሉ፡፡ ባሎቻቸውን እቤት ቁጭ አድርገው በሰባክነት ስም ከአገር አገር የሚዞሩ ብዙ ናቸው፡፡ መልካም ሴት ቤቷን እንድትመራ እንጂ በሕዝብ ፊት እንድትናገር አልታዘዘችም፡፡ የባልዋንና የልጆችዋን ኃላፊነት ወደ ጎን ትታ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሪ ካልሆንኩ የምትል እህት የእግዚአብሔርን ሕግ የተላለፈችና የሥልጣንና የመገዛትን ሕግ የጣሰቸች ነች፡፡ ብዙዎች የሚያዩት አንደበተ ሪቱእነታቸውን ነው፡፡ ነገር ግን ጥሰው ወደ መድረክ እየወጡ በእግዚአብሔር ማንነት ላይ ሁሉ ለመዳፈር ምንም ጊዜ የማይፈጅባቸው ብዙ ናቸው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ምሕረት የለኝም ፣ንስሐ እንኳን በብትገቡ አልምራችሁም ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ብላ ትንቢት በመናገር የሰውን ሁሉ ትኩረት የሳበች አንዲት እህት ትዝ ትለኛለች፡፡ ይህቺ እህት ግን ስትደመጥ ማራኪ ቃላትን የምትናገር በመሆንዋ የቤተ ክርሰቲያን ቱባ መሪዎችም ጭምር ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱና አንድ እንኳ ምን ማለትሽ ነው፣ ተሳስተሻል እኮ የሚል እንዳልነበረም አስታውሳለሁ፡፡ ይህቺ እህት መድረክ ላይ ወጥታ ያንን የመሰለ ርካሽ ስህተት ከምትሠራ እቤት ከባሏ ብትማርስ ኖሮ ባማረባት ነበር፡፡ ወንጌል እሰብካለሁ በሚል ከአገርን ሲያካልሉ ቤታቸው የተፈታ ስንት እንደሆነ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ አሉን የምንላቸውም መሪዎች ከሞቀው ጋር አብረው መሞቅ ፣ ከጨፈረውም ጋር አብረው ከመጨፈርና ለሁሉም መለከት ከመንፋት ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ስሕተት በማረም አቅጣጫ ለመጠቆም በተገባቸው ነበር፡፡ በየዋህነትም ሆነ በስሜት ተገፋፍተው ያንን የሚመስል ስህተት የሚሠሩ ንስሐ መግባት በቻሉ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ግን ሁሉም የተለቀቀ ይመስላል፡፡ በቤትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ሰዎች የሚገባቸውን ሥፍራ ትተው ያለ ቦታቸው እየሰለጠኑ ነውና ይታሰብበት ባይ ነኝ፡፡ ይቀጥላል፡፡

1 comment:

  1. አንተ የጻፍከውን ነው መ/ቅዱስ የሚያስተምረው
    ተባረክ

    ReplyDelete