Monday, July 21, 2014

ልባችሁ አይውደቅ


የልብ መውደቅ ምንድነው? ልብስ እንዴት ይወድቃል? የልብ መውደቅ ማለት፣ የልብ መታወክ፣ መናወጥ ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ የልብ መቅለጥ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የልብ መዛል ሲባልም ይደመጣል፡፡ የልብ መውደቅ የሙሉና ጽኑ ልብ ተቃራኒ ነው፡፡ በመከራና በችግር ውስጥ ሲያልፉ የሚቆምና የሚጸና ልብ ተቃራኒ የወደቀ ልብ ነው፡፡ አንድን ሰው ልቡ ወደቀ ካልን ተስፋ ቆረጠ ሁሉንም ትቶ ተሸነፈ፣ ለመከራና ለችግር ለቆ ተገዛ ማለታችን እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ የሰው ልጅ ተሸነፈ የሚባለው ልብ ሲሸነፍ ነው፡፡ ውስጡ ጥንካሬውን ሲያጣና ሲልፈሰፈስ ነው፡፡ ውስጡ የተሸነፈበት ሰው በሌላ ቦታ ማሸነፍ አይችልም፡፡ ስለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃል በተደጋጋሚ ልባችንን በጌታ እንድናበረታ የሚመክረን፡፡
የዕድሜዬን ከግማሽ በላይ ያሳለፍኩት በእግዚአብሔር ቤት አገልገግሎት ውስጥ ነው፡፡ አገልግሎት ምንም ሰልፍ የማያውቀው፣ በጣምም የተደላደለ ሕይወት የምንኖርበት የሚመስለን ጊዜ ሁሉ አለ፡፡ እንዲያውም እኔ ገና የወንጌላዊነት አገልግሎት በጀመርኩ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በጣም እድለኛ እንደሆንኩ እድርገው እንኳን ደስ ያለህ ብለውኛል፡፡ በእርግጥም ለእኔ ጌታን ማገልግል ትልቅ እድልም ታላቅ በረከትም ነው፡፡ ሰዎቹ ያሰቡት ግን በዚህ መልክ ሳይሆን ከውጭ ድርጅት ጋር የተገናኘሁና በየወሩ ዳጎስ ያለ ብር የሚሰፈርልኝ ስለመሰላቸው ነው፡፡ ያ አሳብ በልባቸው ስላለ እኔ የሌለኝን ያህል ገንዘብ እንድሰጣቸው ጠይቀውኝ ያንን ላደርግ ስላልቻኩ በልብቸው ቅር የተሰኙም እንዳሉ ሁሉ ትዝ ይለኛል፡፡ አገልጋዮች ስንሆን ብዙውን ጊዜ ሙሉ ልብስ ለብሰን ፣ ካራባትም አስረን ስለሚያዩን ኪሳችንም የዚያውኑ ያህል አበጥ ያለ አድርገው የሚያስቡ አሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሌባ የተከታተለንን ጊዜ ሁሉ አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ ግን እኔ ሙሉ ልብስ ለብሼ ብሄድም የአጭር ርቀት የታክሲ ሂሳብ ለመክፈል ስላልቻልኩ በእግር የተጓዝኩባቸው ጊዜያቶች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ሰዎች ግን ችግራችንን ስለሚያውቁ ለመዝናናት የምናደርግ ይመስላቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን መልእክት በመድረክ ላይ ሆነን ስናካፍል የብዙዎች ሕይወት ሲጠገን፣ ልባቸውም ከወደቀበት ሲነሳ፣ የተጨነቁና ግራ የተጋቡ ወደ ታላቅ መጽናናት ውስጥ ሲገቡና ጌታን ሲያመሰግኑ ጌታ አሳይቶናል፡፡ ስለ ሰጠን ፀጋ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን፡፡ የእኛ ሕይወት ደግሞ መፈተኑና የእንቆቅልሽ መብዛት እጅግ በጣም የሚያስገርምና የሚያስደንቅ ነው፡፡ እንግዲህ ምን ማለቴ ነው? በግልም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ባለን አገልግሎት በአንድም ሆነ በሌላ ልባችንን የሚያፈርሱ ሁኔታዎች ይገጥሙናል፡፡ በመጋቢነት ባገለገልኩባት ቤተ ክርስቲያን የእኔንም ሆነ አብረውኝ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ልብ የሚያነቃንቅ ፈተና የገጠምንን ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2003 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያናችን ለነበርነው መሪዎች እጅግ ከባድ መራራ ሁኔታ ገጥሞን ስለነበር ተጨንቀን በፀሎት ወደ እግዚአብሔር ፊት በቀረብንበት ጊዜ እግዚአብሔር አንድ አስደናቂ መልእክት ሰጠን፡፡ መልእክቱ ከእርሱ የተነሳ የማንም ልብ አይውደቅ የሚል ነው፡፡ ይህ መልዕክት እንዴት እንዳጽናናንና እንዴትስ ባለ ደስታ ውስጥ እንዳስገባን አስታውሳለሁ፡፡ ጌታም እንደተናረው ሁሉ አድርጎልን፣ ልባችንን ሲያናውጥ የነበረውንም ሁሉ አሽንፎልን፣ ሁሉም እንደቃሉ መልካም ሆኖ አይተነዋል፡፡ ከእርሱ የተነሳ የማንም ልብ አይውደቅ ያለው ዳዊት ነው፡፡ አሳቡን የምናገኘው በ1 ሳሙኤል 17፡32 ላይ ነው፡፡ እርሱ ተብሎ በተውላጤ ስም የተጠቀሰው ጎልያድ ነው፡፡ በሌላ አባባል ከጎልያድ የተነሳ የማንም ልብ አይውደቅ እንደማለቱ ነው፡፡
1ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 17 በጣም አስደናቂ የእግዚአብሔር ሥራ የታየበትን ታሪክ ይነግረናል፡፡ ታሪኩ በእሥራኤላውያንና በፍልስጥኤውያን መካካል ስለተካሄደው ጦርነት የሚያወሳ ነው፡፡ ይህ ጦርነት ከፍልስጥኤማውያን በተለይም ለእሥራኤል ሕዝብ እጅግ ፈታኝ የሆነ ጦርነት ነበር፡፡ ምክንያቱም ጎልያድ የተባለ ብርቱ ጀግና የእሥራኤልን ሕዝብ እያስደነገጠ ስለነበረ ነው፡፡ ዳዊት ወደ ሰልፉ አካባቢ የመጣው ለጦርነት ብሎ አልነበረም፡፡ የወንድሞቹን ደህንነት እንዲጠይቅ አባቱ ስላዘዘው እንጂ፡፡ ዳዊት ለእሥራኤል ህዝብ ችግር መፍትሔ ያመጣል ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም፡፡ አባቱ እንኳ የቤት ልጅ፣ ለወንድሞቹ ስንቅ የሚያመላልስ ተላላኪ ፣ ደህንነታቸውንም ለአባታቸው የሚያመጣ፣ ሌላ ወሬም ካለ ወስዶ የሚያቃምስ ወሬ አመላላሽ እንጂ ለጦር ሜዳ ስልት የገባው አድርጎ በጭራሽ አላሰበውም፡፡ ወንደሞቹም ቢሆኑ የተላከበትን መልእክት አድርሶ ቶሎ ወደ ቤት እንዲመለስ እንጂ ወደ አዋቂ ተግባር ውስጥ እንዲገባ ያውም የጦርን ወሬ ማዳመጥ የልጅ ወግ ስላይደለ ተቆጡት፡፡ ኩታራ የሚያምርበት እቤት አካባቢ አልያም ኮሮጆውን አንግቦ የበጎችን ጭራ ሲከተል ነው ብለው ያምኑ ስለነበር የዳዊት ወደ ጦር ሜዳ መምጣት ያስደሰተው ማንም አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ከማናቸውም የጦር ጀግኖች ይልቅ በአፉ የተስፋ ቃል፣ በልቡም እምነትና ድፍረት የነበረው ዳዊት ብቻ ነበር፡፡
ዳዊት ወደዚያ የጦር ሰፈር ሲመጣ ሁለት ነገሮችን አስተዋለ፡፡ አንደኛው የእሥራኤል ሕዝብ በሠረገላ መበቡን አየ( 1ኛ ሳሙ 17፡20)፡፡ የነበሩበት ሠፈር በተራ ሠረገላ ሳይሆን በጦር ሠረገላ የተከበበ ሠፈር ነበር፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ሕዝብ በጣም አሰጨናቂ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ሁለተኛ የእሥራኤልን ፍርሃት አየ፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል እንደምንረዳው ይህ ወቅት በእሥራኤል ሕዝበ ላይ ከፍተኛ ፍርሀት የወደቀበት ወቅት ነው( 1ሳሙ 17፡24)፡፡ ከፊቱ እስክሸሹ ድረስ የእሥራኤል ሕዝብ ጎልያድን ፈርተው ነበር፡፡ ያልፈራ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ያለ ምንም ልዩነት ሁሉም የፈሩበት በጣም መራራ ጊዜ ቢኖር ይህ ጊዜ ነው፡፡ ሠራዊቱ፣ ሕዝቡ፣ የጦርነት ልምድ ያለውና ፈጣን ተዋጊ የነበረው ንጉሡ ሳዖልም ጭምር እንስክራወጥ ድረስ የሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ንጉሡ ጎልያድን ለሚያሽንፍ ልጄን እድርለታለሁ ያለው እኮ አማች ስላስፈለገው ሳይሆን ከፍርሃቱ ብዛት የተነሳ የተናገረው ነው፡፡ የሰዎች ልብ መውደቁና መሸነፋቸው ከሚታወቅበት መንገድ አንዱ ንግግራቸው ነው፡፡ “ ጎልያድን ለሚገድል ንጉሥ ልጁን ይድርለታል” የሚለው ንግግር እኮ የሽንፈት ድምጽ ነው፡፡ በአገሪቱ አሉ የተባሉ ሁሉ አንዱን ጎልያድ ሲያዩ ሁሉም ግብአ መሬታቸው ያን ቀን የሚፈፀም መሰላቸው፡፡ ይህን ጊዜ ዳዊት ከሁሉም በሚልቅ ማንነቱ ተገለጠ፡፡ ሁሉም ሽንፈትን ሲያወሩ እርሱ ግን ከእሥራኤል ተግዳሮትን እንደሚያርቅ በፍፁም መተማመን ተናገረ፡፡ ልጅ ቢሆንም እርሱ የተናገረው ቃል ተስፋ ለቆረጠውና ለፈራው ሕዝብ እንደ መድኃኒት ስለታያቸው ወደ ንጉሡ ይዘውት መጡ፡፡ ያኔ ዳዊት በንጉሡ ፊት “ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ “አለ፡፡ የዚህ አጭር ጸሑፍ ዓላማ እግዚአብሔርን እያመለኩና እያገለገሉ ልባቸው በተለያዩ ምክንያቶች የዛለባቸውን ቅዱሳን ለማበረታታትና ለማጽናናት ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ በአገልግሎታቸው ሰልፍ የበዛባቸው ካሉ ፣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የወደቁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን እውነተኛ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል ልባቸውን ለማጽናት ነው፡፡ ያለንበት ምድር ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ ቢሆንም ልባችሁ አይውደቅ ፣ ወይም ልባችን አይውደቅ!
እንዴት ልባችን አይወድቅም? ሁኔታዎች እየተፈራረቁብን ናቸው፡፡ የምናስባቸውና የምንጠብቃቸው ነገሮች እንደፈለግናቸው እየሆኑልን አይደለም፡፡ ለጌታ የተጠራንበት መጠራት ራሱ ብቻ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ ለጌታ መለየት ራሱ ብቻውን ዋጋ ሲያስከፍለን እያየን ነው፣ታዲያ እንዴት ልባችን አይወድቅም? የምትሉ ወንድሞችና እህቶች ዛሬ ለእናንተ ያለኝ ጥብቅ መልእክት አሁንም ልባችሁ አይወደቅ የሚል ነው፡፡ ባላችሁ መከራ፣ችግር ጭንቀት፣ እጦት ብቸኝነትና ወዘተ ምክንያት የማናችሁም ልብ አይውደቅ፡፡ ከ1ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 17 በመነሳት ልባችን መውደቅ እንደሌለለት የሚያጽናኑን የሚከተሉትን መሠረታዊ አሳቦችን እንመለከታለን፡፡ ለምንድነው ልባችን መውደቅ የሌለበት?
1. እኛ የቃል ኪዳን ሕዝቦች ስለሆንን ነው፡፡
ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች ፡- ይህንን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል ፣ ከእሥራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ምን ይደረግለታል; የሕያውን አምላክ ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው;ብሎ ተናገራቸው( 1ሳሙኤል 17፡27)፣ እኔ ባሪያህ አንበሳንና ድብን መታሁ፣ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል( ቁ.37)፡፡
በጎልያድና በዳዊት እንዲሁም በፍልስጥኤማውያንና በእሥራኤል ሕዝብ መካከል ያለው ልዩነት ከፍተኛ ነው፡፡ በክፍሉ እንደምንመለከተው እሥራኤል የሕያው አምላክ ጭፍራ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን መንፈሳዊ ጦርነት ሊዋጋ የወጣ በመለኮታዊ ዓላማ የተሰለፈ አስደናቂ ሕዝብም ነው፡፡ ሕዝቡን ለሥራው ያሰማራው አምላክ እግዚአብሔር ራሱ ሕያው አምላክ ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የእሥራኤል ሕዝብ የተገረዘ ሲሆን ፍለስጥኤማውያን የጦር አዝማቻቸው ከሆነው ከዋናው ከጎልያድ ጭምር ያልተገረዙ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ዳዊት ወደ ሰልፉ በመጣና ጎልያድን ባየ ጊዜ የተረዳው በጎልያድና በእሥራኤል ልጆች መካከል ያለውን ይህንን ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ ጎልያድ ግዙፍ፣ ጀግና ፣ በጀግንነቱ የተመሰከረለት ሰው ነበር፡፡ እርሱ የሕያውን እግዚአብሔር ጭፍራ የሆነውን የተመረጠውን የቃል ኪዳን ሕዝብ መገዳደረሩ ለእግዚአብሔር የሚቀኑ እንደነዳዊት ያሉትን የሚያስቆጣ ነው፡፡ ከእሥራኤል ይልቅ ፍልስጥኤምና ጎልያድ በጦር ልምድ የተካኑ መሆናቸውእሙን ነው፡፡ የንጉሥ ሳኦል ራሱ የጎልያድን የጦር ልምዱን ሲመሰክር እርሱ ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነው ብሏል፡፡ ይህም በመታወቁ ፍልስጥኤማውያን ሲመኩበትና በእርሱ ምክንያት ሲኩራሩ የእሥራኤል ሕዝብና ንጉሳችው ግን ፈሩ፡፡ ከሁለቱም ወገን የሆኑ ሁሉ ያልተረዱት፣ ዳዊት ግን የተገነዘበው ጎልያድ ያልተገረዘ ሰው መሆኑ ነው፡፡ ዳዊትም ያ ያልተገረዘ አንድ ሰው የተገረዘውንና የሕያውን አምላክ ጭፍራ የሆነውን ሕዝብ ሲያስፈራራና ፣ ሲያንቋሽሽ ተመለከተ፡፡ የመገረዝና ያለመገረዝ ጉዳይ ሲነሳ ግዝረት እሥራኤል ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ይልቅ ለእግዚአብሔር የተለየ የቃል ኪዳን ሕዝብ መሆናቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቃል የመገረዝ አሳቦች ሲነሱ በዋናነት የሚታወሰው እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ነው( ዘፍ. 17)፡፡ እግዚአብሔር ከአብርሃምና ከዘሩ ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ምልክቱ ደግሞ ከአብርሃም አብራክ የወጣው ወንድ ሁሉ(ዘፍ.17፡12 እንዲሁም በቤቱ የሚኖር ባሪያም ሁሉ መገረዙ ነው(ዘፍ.17፡13)፡፡ ይህ ሥርዓት ሕዝበ- እሥራኤል ለእግዚአብሔር የተለየና የተሰጠ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ በዚህ ሁኔታ በእግዚአብሔርና በእሥራኤል ሕዝብ መካከል የተለየ ትሥሥር የተመሰረተ በመሆኑ ሌላ ያልተገረዘ ወገን ከእነርሱ ጋር ሊቀላቀል አይችልም ነበር( ዘዳ 10፡16፣30፡6፣ኤር4፡4፣ኤር 9፡25-56፣ሕዝ 44፡7)፡፡ እንዲያውም እሥራኤላዊ ያልሆነ እንግዳ ሰው ከእነርሱ ጋር ፋሲካን ለመብላት ቢመኝ አስቀድሞ መገረዝ እንዳለበት የእግዚአብሔር ሕግ ያዝ ነበር (ዘጸ. 12፡48)፡፡ ምክንያቱም እንደነ ፍልስጥኤማውያን ያሉ ሌሎች ሕዝቦች ስለ መገረዝና አለመገረዝ የሚገባቸው አይደሉም፣ የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ስለሌላቸው ከቃል ኪዳን ሕዝብ ጋር እኩል ሊካፈሉ አልተገባቸውም ፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ አይመለከታቸውም፡፡ ከእሥራኤል ጋር ለጦር ግጥሚያ በመጡበት ወቅት ከበቂ በላይ የሆነ ወታደራዊ ዝግጅት አድርገዋል፣ አስፈሪና ብቃት ያለው በጦር ልምድ የተካነ አዝማች አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከነጦር መሪያቸውም ጭምር ያልተገረዙ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እሥራኤል የፍልጥኤማውያንን ያህል የጦር ዝግጅት የላቸውም፣ ንጉሣቸውም በፍርሃት ውስጥ ወድቋል፡፡ ሆኖም እነርሱ እጅግ በጣም በተለየ መልክ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያላቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የእሥራኤል አምላክ ደግሞ ከሕዝቡ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚጠብቅ አምላክ ነው፡፡ የመረጠውንና የጠራውን እንዲሁም በቃል ኪዳኑ የያዘውን ሕዝብ ባልተገረዘ እንግዳ እጅ አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ፍልስጥኤማውያንም ሆኑ ጎሊያድ ያላወቁት፣ እሥራኤላውያንም ሆኑ ንጉሥ ሳኦል ያላስተዋሉት እሥራኤል ለእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን በማወቅ ደረጃ ቢያውቁም አሁን ግን ያንን በልባቸው እንዳያስቡት የሚያደርግ አደገኛ ተግዳሮት ተደቀኖባቸዋል፡፡ ስለዚህ ጎልያድ ሲደነፋ እሥራኤል ከነንጉሳቸው ፈሩ፡፡ ቃሉ እጅግ ፈርተው ከእርሱ ሸሹ ይላል(ቁ 24)፡፡ ዳዊት ግን ከምንም በላይ ይህንን ተገንዝቧል፡፡ ድሉ የፍልጥኤማውያን ሳይሆን የእሥራኤል መሆኑን ተረድቷል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ያንን ቃል ኪዳን እንደማይሽርም ገብቶታል፡፡ ስለዚህ ከእርሱ (ከጎልያድ) የተነሳ የማንም ልብ አይውደቅ አለ፡፡
በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አዲስ ቃል ኪዳን ተመሥርቶልናል፡፡ ያለ ምንም ልዩነት በእርሱ የምናምን ሁላችንም ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ልጆች እንድንሆን ተደርገናል፡፡ ይህ ቃል ኪዳን በፍጹም አይሻርም፡፡ እንደዚህ ይህ ሆኖ ሳለ ልባችንን የሚያናውጡ ፈተናዎች በየጊዜ ይገዳደሩናል፡፡ አንዳንዴ በፍርሃት ለመዋጥ እንገደዳለን፣ እንጨነቃለንም፡፡ የተግዳሮቶቻችንን ግዝፈት በአይናችን እያየን፣ የጦርና የሰልፉን ብዛት እንዲሁም ባላንጣችን በእኛ ላይ ሊዘምት የሚደግሰውን የጦር ዝግጅት እየተመለከትን እንረበሻለን፡፡ ይሁን እንጂ ልባችን ልወድቅ አይገባውም፡፡ ምክንያቱም እኛ ለእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝቦች ስለሆንን ለምንም ክፉ አሳፎ አይሰጠንም፡፡
2. ከትላንትናው ይልቅ የዛሬው መከራ ቀላል ስለሚሆን ነው፡፡
ዳዊት ሳኦልን አለው፡ እኔ ባሪያህ የአባቶቼን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፣ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር፡፡ በኋላውም እመለከተውና እመታው ነበር፡፡ከአፉም አስጥለው ነበር፣በተነሳብኝም ጊዜ ጎሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበረ፡፡ እኔ በሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል(ቀ.34-36)፡፡
ዳዊት ይህንን አሳብ እንዲናገር ያደረጉ ሁለት አውራ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ምክንያት እርሱ ወደዚህ ጦርነት ከመምጣቱ በፊት ያለፈበት የጦርነት ልምምድ ነው፡፡ ዳዊት ልጅ ቢሆንም ወደ እሥራኤል-ፍልስጥኤም ጦርነት ከመምጣቱ በፊት ሌላ ጦርነት ውስጥ አልፎ ነበር፡፡ ያ ጦርነት ደግሞ ደግሞ ከሰው ጋር ያደረገው ሳይሆን አንበሳና ድብ ከመሚመስል አውሬ ጋር የገጠመው ጦርነት ነበር፡፡ እርሱ ለብቻው ከአንሳና ከድብ ጋር ባደረገው ጦርነት እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ድል እንደሰጠው ያውቃል፡፡ ከጎልያድ ይልቅ የሚበልጥ ልምድ አካብቷል፡፡ እግዚአብሔር አንበሳንና ድብን ለምን እንዳመጣበት ሳይገባው ቀርቶ አዝኖ ሊሆን ይችላል፡፡ በእግዚአብሔርም ላይ ልቡ ከብዶበት ይሆናል፡፡ ግን እግዚአብሔር ከጎልያድ ጋር ጦርነት እንደሚገጥም ስለሚያውቅ ማንም ሳያውቅ ጦርነት ያለማምደው ነበር፣ ያውም ከአንበሳና ከድብ ጋር፡፡ አምላኩ በጓዳ ያለማመደው የጦርነት ድል በአደባባይ የሚታይበት ዘመን መጣለት፡፡ ከግዙፍ ጎልያድ ጋር የገጠው ጦርነት ስለሰመረለት ዳዊት እልፍ ገደለ እንዲባል ሆነ፡፡ ሁለቱን ብናነጸጽራቸው በምንም መለኪያ ጎልያድና አንበሳ እኩል ሊታዩ አይችሉም፡፡ አንበሳው ጎልያድን ራሱን ለመገነጣጣል ምንም ጊዜ ሊወስድበት አይችልም፡፡ ጎልያድና አንበሳ ቢታገሉ በከባድ ፍጥነት ዝንጥልጥል አድርጎ የሚያሸንፈው አንበሳው እንጂ ጎሊያድ አይሆንም ምክንያቱም ጎልያድ የቱንም ያህል ቢገዝፍ የአንበሳ ያህል ብርታት የለውም፡፡ ዳዊት ግን በእግዚአብሔር ርዳታ ከአንበሳ ጋር ታግሎ አሸንፏል፡፡ እንዲያውም ጎሮሮውን እያነቀው ይገድለው እንደነበር መሰከረ፡፡ ከአባቱ መንጋ መካከል የበግ ጠቦት የነጠቀውን አንበሳና ድብ ማንቁርቱን እያነቀ ያስተፋው ስለነበር ዛሬ የጎልያድን ሁኔታ ሲያየው የመጨረሻ ናቀው፡፡ እኔ አንበሳና ድብ ከመታሁ ይህንን ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማ እንዴታ!፣ ማለትም ትላንትና አንቄ ከገደልኩአቸው አንበሳዎችና ድቦች እንደ አንዳቸው አደርገዋለሁ ወደሚልበት መረዳት መጣ፡፡ የትላንትናዎቹ አንበሳዎችና ድቦች ብዙ ሲሆኑ ጎልያድ ደግሞ አንድ ሰው ነው፡፡ በእግዚአብሔር ርዳታና ድጋፍ ያለፍንበት የትንትናው ፈተናችንና ጦርነታችን ከዛሬው መከራችን እጅግ ያነሰ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው ቅርበት ነው፡፡ በጎልያድና በዳዊት መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው፡፡ በእርግጥ ጎልያድ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በጦርነት ልምድ ያለው፣ በራሱ የሚተማመንና ሕዝበ ፍልስጥኤምም ልባቸውን የሚጥሉበት የሚተማመኑበትም ሰው ነው፡፡ ዳዊት ደግሞ በማንም ዘንድ የሚታወቅ አይደለም፡፡ ማንም ስለ ዳዊት የሚያወቀው በበግ እረኝነት እንጂ አንበሳንና ድብን የሚመታ በእግዚአብሔር ድፍረት የሚሰማራ መሆኑን ሌላው ቀርቶ አባቱም ሆነ ወንድሞቹም እንኳን አያውቁም ነበር፡፡ ስለዚህ ነው ሳኦል አንተ ገና ብላተና ነህ( ልጅ ነህ) ያለው፡፡ ልጅ እቤት ይቀመጣል እንጂ ለጦርነት አይወጣም፡፡ ልጅ ማለት ልምድ የለለው ፣ ብቃትና ችሎታ የሚያንሰው፣ በቀላል ነገር ሊፈራና ሊደነግጥ የሚችል፣ ሰውነቱም ሲታይ ድክም ያለ ወላቃ፣ አቅም የከዳው ኮሳሳ፣ገና የሌላ ሰው ሞግዝትንት የሚሻ ዓይነት ነው፡፡ ዳዊት ደግሞ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው ነው፡፡ ሰዎች የዳዊትን ውጭውን እንጂ ውስጡን ሊያዩ አልቻሉም፡፡ ይህ ደግሞ በሰው አይን እንጂ እግዚአብሔር የሚያየው በተለየ መልክ ነው፡፡ ዳዊት ወደ እግዚአብሔር የተጠጋና በእርሱ የሚታመን ሰው ነው፡፡ እርሱ የእግዚአብሔርን ኃይል ታላቅነት ስለተረዳ ሰዎች ሁሉ የተንቀጠቀጡለት ጎልያድ በጣም ትንሽ ሆኖ ታየው፡፡ እንዲያውም የሆነ ኮሳሳ በዚያም ላይ ድባኖ ሊመስለው ሁላ ይችላል፡፡ ኃያሉ እግዚአብሔር በሕይወቱ የሠራውን ሥራ ሲገነዘብ ጎልያድ አንሶ አንሶ በጣም ትንሽ ሆኖ አገኘው፡፡ ወደ እግዚአብሔር በተጠጋን ቁጥር የሚገዳደረን ሁሉ እምንት ሆኖ ይታየናል፡፡ ጎሊያድ ልምዱንና በእጁ የያዘውን ጦር እንጂ በዳዊት ውስጥ የተቀመጠውን መለኮታዊ ኃይል የሚያይበት ዓይን አልነበረውም፡፡ ዳዊት ግን አምላኩና የአርሱ አስደናቂ ሥራ ይታየው ነበር፡፡ ይህንን ሁኔታ ስንመለከት በዳዊትና በጎልያድ መካከል ያለው ልዩነት ወንጭፍ የማይደርስበት ነው፡፡ ዛሬ በእኛም ሕይወት እንደዚህ ነው፡፡ እኛ ወደ እግዚአብሔር በተጠጋንና በእርሱ ያለን መታመን እያደገ በሄደ ቁጥር የሕይወታችን ጎልያድ፣ በቤታችን የሚናየው የግል ተግዳሮት፣ በቤተ ክርስቲያን የታየው ውስብስብ ጉዳይ ሁሉ ጉልበቱ ደቅቆ እናየዋለን፡፡ ከትናንትና ዛሬ እምነታችን ሲያድግ ፣ መንፈሳዊ ሕይወታችንና ቅድስናችን ከፍ እያለ ሲሄድ በሰዎች ሁሉ ዘንድ አስደንጋጭ የሆነው ጠላትም ሆነ መከራችን ለእኛ እዚህ ግባ የማይባል ይሆንብናል፡፡ ትላንት በእምነት ነገር ሕጻናት በነበርንበት ወቅት መከራና ጭንቀት ፣ በየዕለቱ የሚገጥምን መንፈሳዊ ውጊያ ሁሉ አስፈሪና ልባችንን የሚያናውጥ ሲሆን በመንፈስ እየጎለመስን ስንሄድ ድግሞ ከፍ ያለው ሁሉ ዝቅ ብሎ እናየዋለን፡፡ ጎልያድ ዳዊትን ይናቀው እንጂ ዳዊት ግን ጎልያድን አስቀድሞ ንቆታል፡፡ ጎልያድ ዳዊትን የናቀው ባዶ እጁን ስለመጣ፣ ገና ልጅ ስለሆነ፣ በእጁም ከወንጭፍ በስተቀር ሌላ ምንም ስላልነበረው ነው፡፡ ዳዊት ግን እንደዚያ የደፈረው ከጎልያድ በላይ አምላኩ ስለታየው፣ ትናንትና ጎሮሮአቸውን ያነቃቸውን አንበሶችና ድቦች ስለሚያስታውሳቸው ነው፡፡ አንባቢያ ሆይ ! ዛሬ የሕይወታችሁ ተግዳሮት፣መከራና ጭንቀት ምን ይሆን? ስቃያችሁ ወይም እንቆቅልሻችሁ ምን ይሆን? በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎች ትፈተኑና ትቸገሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር እንድንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡ ያውም ትላንት ታላቅ ሥራ በእናንተ ሕይወት ከሠራው እግዚአብሔርና ከኃይሉ ብርታት የተነሳ የዛሬው መከራ እጅግ ያነሰና የቀለለ ነው፡፡ ይህንን ማወቅ የምንችለው ወደ እግዚአብሔር በቀረብንበት መጠን ነው፡፡ ስለዚህ መከራችሁና ችግራችሁ ምንም ያህል የገዘፈ ቢሆንም ይሸነፋልና ልባችሁ አይውደቅ፡፡ የመከራውን ግዝፈት ስላያችሁ ብቻ የተሸነፋችሁ በሚመስላችሁ ሰዓት እንኳን ልባችሁ አይውደቅ ምክንያቱም ተግዳሮቶቻችሁ በእግዚአብሔር ፊት የተናቀ ነውና፡፡
3. ልባችሁ አይውደቅ ፣እግዚአብሔር ዛሬም በሥራ ላይ ነው፡፡
ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል አለ(ቁ. 37)፡፡
ታሪካቸውን የምንሰማ ብዙ ነገሥታትና ኃያላን በዚህ ዓለም ላይ ነበሩ፡ ባለታሪኮች በዘመናቸው የሠሩት ታሪክ እስከ አሁን ቢወራም እግዚአብሔር የለገሰላቸውን እድሜ ኖረው የመንገዳቸው ጫፍ ሲያልቅ ከዚህ ዓለም ጋር ተፋቱ፡፡ አሁን ምንም ሊሠሩ የሚችሉበት መንገድ የላቸውም፡፡ እግዚአብሔር ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ እርሱ ያለ፣ የነበረና የሚኖር አምላክ ነው፡፡ ዘመናቶቹ አይቆጠሩም ዓመታቶቹም አያልቁም፡፡ በሰው እድሜ ክልል ውስጥ እንደሚያበቃ እንደሰው ዓይነት እድሜ ያለው ሳይሆን ሁሉን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው እግዚአብሔር አልፋና ኦሜጋ ፣ፊተኛውም ኋለኛም እርሱ ነው፡፡ ትላንት አንበሳን እንዲታሽንፍ አድርጌአለሁ፣ ድቡንም በእጅህ ጥዬዋለሁና አሁን ደግሞ አልችልም አይልም፡፡ እንዲያው ትላንትና እግዚአብሔር በእኛም ሆነ በሌሎች ሕይወት የሠራው ሥራ ዛሬ በመከራችን ጊዜ በእርሱ እንድንታመን ያደርገናል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሊሆን ፣ እኛንም ለመታደግ የጊዜ ውል የለውም፡፡ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ እንጂ ያለው( ማቴ.28፡20)፡፡ እግዚአብሔር የትላንትና አምላክ ብቻ አይደለም፣ ዛሬም ሕያው የሆነ አምላክ ነው፡፡ ፡ ትላንትና ከአንበሳው ጋር ስንታገል ረድቶን ድል የሰጠን እግዚአብሔር ዛሬ ጎልያድ ሲደነፋብን ዞር አላላም፡፡ ያው የያኔው እግዚአብሔር እርሱ በሥራ ላይ ነው፡፡ ዳዊትም የሚመሰክረው ይህንን ነው፡፡ ትላንት ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ዛሬ ደግሞ ከጎልያድ እጅ ያስጥለኛል ብሎ በአምላኩ ሕያውነት ፎከረ፡፡ ምክንያቱም የእሥራኤል አምላክ እግዚአብሔር ብቅ ብሎ ጥፍት የሚል ወለብላባ በሕሪይ አይነካካውም፡፡ እርሱ ለዘላለም ፀንቶ የሚኖር ነው፡፡ አንዱን የመከራና የጦርነት ዘመን ስናልፍ ሌላው እንደሚመጣ የታወቀ ነው፡፡ ትላንትናን ያሻገረን እግዚአብሔር ግን ዛሬም ባለን ጦርነት ከእኛ ጋር አብሮ ይሰለፋል፡፡ እስቲ እግዚአብሔር ትላንትና እንዴት እንደረዳን እናስብ! ዛሬም እርሱ በዙፋ ላይ ነው፡፡ እርሱ እኛን የሚሸከመን ከማኅፀን ጀምሮ ፣ ከእናታችን ሆድ ከወጣንበት ጊዜም አንስቶ እስከ ሽበት እስከ ሽምግልና ድረስ እንጂ የተወሰነውን ጊዜ እረዳችኋለሁ ከዚያ በኋላ ያለውን እናንተው ተወጡበት አይልም፡፡ ትናንት በታመምን ጊዜ የፈወሰን፣ በተራብን ጊዜ ያበላን፣ ስንታረዝ አልብሶን ፣ ስንወድቅ ያነሳን እግዚአብሔር ዛሬ ስንሰበር ይጠግነናል፡፡ ትላንት ስናለቅስ እምባችንን አብሶልን ያየነው ጌታ ዛሬ ስናዝን ያጽናናናል፡፡ ያኔ ታሥረን አይቶ የፈታን እግዚአብሔር ዛሬ ባለንጣችን ሲሞግተን ጠበቃችን ይሆንልናል፡፡ ትላንትና የናሱን ደጅ የሰበረልን አምላክ ዛሬ ደግሞ የብረቱን መዝጊያ ይነቅልልናል፣ መወርወረያውንም ይቆርጥልናል፡፡ እርሱ እኛን የሚተውበት ፣ ስለሕይወታችንም ጉዳይ እያወቀና እየተረዳ ዝም የሚልበት ልብ የለውም፡፡ ስለዚህ አንቢያን ሆይ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ ልባችሁን አትጣሉ፡፡ በዛሬው መከራችን ምክንያት የማናችንም ልብ አይውደቅ፡፡ እግዚአብሔር ዛሬም ስለእኛ ያስባል፡፡ እዚህ ላይ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ላክልበት ዘንድ እሻለሁ፡፡ አንደኛው ትንቢተ ኢሳይያስ 40፡27 ጀምሮ ሲሆን ሁለተኛው እብራውያን 13፡8 ነው፡፡ አንባቢያን ትኩር ብለው ቢመለከቱ እግዚአብሔር የእሥራኤልን ሕዝብ እንዲህ ይላቸዋል፡፡ አላወቅህምንን አልሰማህምን? ይላል፡፡ ይህ ሕዝብ በመከራና በስደት ውስጥ ከመግባቱ በፊት እግዚአብሔር እንዴት ያለ ድል እንደ ሰጠው ያውቅ ነበር ግን አሁን እግዚአብሔር ረስቶኛል አለ፡፡ እነርሱ እንደሚያስቡት ሳይሆን እግዚአብሔር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ስለሆነ እርሱን በመተማን የሚጠባበቅ ሁሉ ኃይሉን እንደሚያድስ ተናገረ፡፡ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊም ጌታ ኢየሱስ ትላንትና ዛሬም እስከ ለዘላላምም ያው የሆነ አምላክ መሆኑን አረጋገጠልን፡፡ ስለዚህ ልባችሁ አይውደቅ!
4. ልባችሁ አይውደቅ ምክንያቱም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፡፡
ይህ ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን አምላክ እንዳይደለ ያውቅ ዘንድ ነው፣ ሰልፉ የእግዚአብሔር ነውና እናንተን በእጃችን አሳልፌ ይሰጣል አለ( 1ሳሙኤል 17፡47)፡፡
ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ ዳዊት በእሥራኤልና በፍልጥኤም መካካል ሆኖ በጎልያድ ፊት ያወጀው የድል አዋጅ ነው፡፡ ከፍ ብለን የተመከትን እንደሆነ ዳዊት ከማንም የእሥራኤል ጀግና ይልቅ በዚህ ጦር ሜዳ ላይ የድልን ቃል ሲናገር ነበር፡፡ ከድል በኋላ ዳዊት እልፍ ገደለ ብለው ከዘፈኑ ሴቶች በቀር በጦርነቱ ግጥሚያ ጊዜ አንድም እሥራኤላዊም ሆነ ንጉሥ ሳዖል የአሸናፊነት አዋጅ አላወጁም፣ የድልንም ዝማሬ አልዘመሩም፡፡ በጦርነቱ ወቅት በድል ሲፎክሩ የታዩት ጎልያድና ዳዊት ብቻ ነበሩ፡፡ ጎልያድ በጦሩና በጭረው ስለተማመነ፣ በጅግንነቱም ስለተኩራራ .የዳዊትንም ጠቦት ፊት የሆነው መልኩን አይቶ ስለናቀና የእሥራኤልንም ሕዝብ በፍርሃት መቅለጥ ስለተመለከተ ነው፡፡ በእርግጥም የሚያስፈራ ትክለ ቁመናና የጦር ዝግጀት፣ ማለፊያ አለባባስም እንዳለው እሥራኤልም ሆኑ ፍልጥኤምም እያዩት ነው፡፡ የዳዊት አሳብ ግን በሰው ዘንድ የእብድ ንግግር ሊመስል የሚችል ነው፡፡ እመጣብሃለሁ፣ ራስህንም ከአንተ ላይ ከላይ አነሳለሁ( 17፡46) ሲል የሰማ ፍጥረታዊ ሰው ተንከትክቶ ሊስቅ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በእጁ ከወንጭፍ በስተቀር ሌላ ነገር አይታይም፣ የጎልያድ ራስ በምንድነው የሚያነሳው? የጀግናን ራስ ማንሳት እንደዚህ ቀልድ ሆነ እንዴ? ልጁ ነካ ያደርገዋል እንዴ? ጦር የያዘው ጎልያድ ፣ እርሱ በምኑ ነው የሚመታው? የሚያስብል ነገር ነው፡፡ ሰይፍም ያለው በጎልያድ እጅ ነው ፣ እርሱ በምኑ ነው አንገቱን የሚያነሳው? የልቡን ምኞት ነው የሚናገረው? የሚያስብል ንግግር ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ስናየው አሽናፊው ጎልያድ እንጂ ዳዊት ይሆናል የሚል የጦር ተንታኝና ጠበብት ይኖራል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡
ዳዊት በዚህ ሁሉ ውስጥ የተናገረው አንድ አስደናቂ እውነት አለ ፡፡ ያውም ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ ሰልፍ የጎልያድና የዳዊት ወይም የፍልስጥኤማውያንና የእሥራኤላውያን ሳይሆን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ማለትም በሰልፉ ወይም በጦርነቱ የሚዋጋው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ የሚዋጋ ከሆነ ጦርና ሰይፍ አያስፈልግም፡፡ እርሱ በሰይፍና በጦር የሚያድን አምላክ አይደለምና፡፡ እኛን ለማዳን ከተነሳ ጦር አይፈልግም ፣ ሰይፍም አያሻውም፡፡ እርሱ የእኛን ጦርነት የሚዋጋ ከሆነ የእኛ የጦረኝነት ልምድ ምን ውስጥ ሊገባ ይችላል? እግዚአብሔር የሰልፉ ባለቤት ከሆነ የትኛው ጋሻ ይመልሰዋል? እርሱ ስለ እኛ የሚዋጋ ከሆነ ወታደራዊ ልምምዳችን ምን ሊፈይደን ነው? እንግዲህ እነጎሊያድ በከንቱ ለፉ ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ስንመረምር በእግዚአብሔር ዓላማ ያወጣው ሕዝብ ብዙ ሰልፍ አለበት፡፡ ያለ ሰልፍ የኖረበት ዘመንም አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በሁሉም አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ በዙሪያቸው ካሉ የአሕዛብ ሕዝቦች ጋር ሲነጻጸሩ እሥራኤል በጣም ጥቂት ሕዝብ ሆኖ ጠላት የሚያጠቃው ነው፡፡ይሁን እንጂ ከጠላቶቻቸው ጋር በተዋጉበት ጊዜ ሁሉ ግጥሚያው የሚጠናቀቀው በእሥራኤል አሸናፊነት ሲሆን የዚህ ሁሉ ሚስጢር እግዚአብሔር ለቃል ኪዳን ሕዝቡ ስለሚዋጋ ነው፡፡
ቅዱሳን ወገኖቼ ሆይ! እግዚአብሔር አንድ ልማድ አለው፡፡ እርሱም ስለ ሕዝቡ መዋጋት ነው፡፡ የእሥራኤል ሕዝብ ከባርነት ቀንበር ወጥተው ወደ ተስፋው ምድር ሲሄዱ የፈርዖን አስፈሪ ጦር ከኋላው ሲከተለው፣ ከፊቱም የኤሪትራ ባሕር መንገዳቸውን ሲዘጋ አይተው ልባቸው ወደቀ፡፡ ያን ጊዜ መሪያቸው የሆነው ሙሴ እንዲህ አለ፡ አትፍሩ፣ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያንን ለዘላለም አታየአቸውምና ቁሙ፣ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ፣ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋልና እናንተም ዝም ትላላችሁ( ዘጸ.1413-14)፡፡ እግዚብሔር በዚህ ቃል መሠረት ባሕሩን ከፍሎ ሕዝቡን አሻገረና ያሳድዳቸው የነበረውን የፈርኦንን ጦር በባሕር ጣለላቸው፡፡ በእርግጥም ከዚያ በኋላ ግብፃውያን የእሥራኤልን ሕዝብ ሊወጉ አልቻሉም፡፡ እሥራኤልም በግብጽ ያየው የነበረው መከራ ለመጨረሻ ጊዜ ምዕራፉ ተዘጋ፡፡ ይህ የሆነው እግዚአብሔር ሊገመት ከሚችለው በላይ በሆነ መንገድ ለእሥራኤል ሕዝብ ስለተዋጋ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በወጣንበት ሰልፍ ሁሉ ጦርነቱን የሚዋጋልን እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ምትሰለፉበት ሰልፍ ልባችሁ አይውደቅ፣ ሰልፉ የእግዚአብሔር ነውና፡፡ ጠላት ሲሞግታችሁ ልባችሁ አይውደቅ ምክንያቱም እግዚአብሔር የላከልን ጠበቃችን ጌታ ኢየሱስ ከእኛ ጋር ነውና፡፡ መንፈስ ቅዱስም ወደረኞቻችን የማይችሉትን አንደበት ይሰጠናልና፡፡ በቤተ ክርሰቲያን ባለ አድካሚ ከሆነው የጊዜ ሁኔታ የተነሳ ልባችን አይውደቅ፣ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያኑ ከእኛ ጋር አብሮ ይሠራልና፡፡ የኑሮ ሁኔታን ሲታዩ ልባችሁ አይውደቅ ፣ የማይዘሩትንና የማያጫዱትን ጎተራም የሌላቸውን ወፎች የሚመግባቸው እግዚአብሔር ለእኛም እጁን ይከፍትልናል፣ ከመልካምነቱም ያጠግበናልና፡፤ ልባችሁ አይውደቅ እግዚአብሔር የሥጋ ለባሽ ሁሉ እረኛ ነውና፡ ስልፉ የእናንተ አይደለም፡፡ ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው አሜን፡፡
5. ልባችሁ አይወደቅ የእግዚአብሔር ስም አሸናፊ ነው፡፡
ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፡- አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፡፡ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእሥራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም፣ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፡፡ እግዚአብሔር አንተን ዛሬ በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ እመታህማለሁ፣ራስህንም ከአንተ አነሳለሁ፡፡ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፡፡ ይኸውም በምድር ሁሉ በእሥራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዘአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን አምላክ እንዳይደለ ያውቅ ዘንድ ነው ( 1ሳሙኤል 17፡ 46-47)
ዳዊት በዚህ ሥፍራ ደጋግሞ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም ጠራ፡፡ ይህም በእግዚአብሔር የሚደገፍ የእምነት ሰው መሆኑን ያመለክታል፡፡ በሚሆነው ነገር ሁሉ ውስጥ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ መሆኑን ከማሳየት በቀር በንግግሩ ውስጥ በልታይ ባይነት የሚደረግ የቃላት ቅመማ የለበትም፡፡ ይህን ጦርነት ለመዋጋት ሥልጣንና ተልእኮውን ከእግዚአብሔር ተቀብሏል፡፡ ታሪካዊ የሆነው ውጥኑን ለማሳካት ግራና ቀኙን ሳይመለከት፣ ጎልያድ ባነገበውም ጦርና ሰይፍም ምክንያት ሳይሸበር ጦርነቱን ሊገጥም ቆርጦ መጣ፡፡ ጎልያድን ብቻ ሳይሆን የመላው ፍልስጥኤማውያን ሥጋ ለአሞራ የሚሰጥበት ቀን ዛሬ መሆኑን በልበ ሙሉነት ተናገረ፡፡ ምክንያቱም ጎልያድና ፍልስጥኤማውያን ሥጋዊና ምድራዊ ጦር ይዘው ሲመጡ ዳዊት በማይታየው ግን ታላቅ ድል በሚሰጠው በእግዚአብሔር ስም ታምኖ ስለተሰማራ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስም ኃይል አለው፡፡ ጎልያድን የጣለው ዳዊት ሳይሆን በእርሱ ላይ የተጠራው የእግዚአብሔር ስም ነው፡፡ አንተ ሰይፍና ጦር ይዘህ ትመጣብኛለህ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ አለው፡፡ በጎልያድ እጅ ሰይፍና ጦር አለ፡፡ አስፈሪ ቁመናና የጦር ልምድ፣ የጀግንንት ታሪክና ማዕረግ አለው፡፡ የሕዝብ አጀብና ሞራልም አለው፡፡ ጎልያድ ከዚህ ሁሉ የተነሳ ባያዋጣውም አሸንፋለሁ የሚል ኩራትና መተማማን ነበረው፡፡ ዳዊት ግን ይህ ሁሉ የለውም፡፡ ያለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ በልቡ ውስጥ የተሸከመው የእግዚአብሔር ስም አለው፡፡ ይህንን ስም ከፍ አድርጎ ተሸክሞአል፡፡ ስለዚህ በልበ ሙሉነት ለጎልያድ እንዲህ አለው፡፡ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ ራስህንም ከአንተ ላይ አነሳለሁ፡፡ ባዶ እጁን የምንጦለጦል ብላተና በአምላኩ ስም ጀግና ጦረኛ የሆነውን መምታት ይችላል፡፡
ዳዊት እንደፎከረም ጎልያድ ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ድንጋይን ወንጭፎ ግንባሩን መታው፡፡ ጎልያድም ከነግርማ ሞገሱ በሚያደንቁት ፍልስጥኤማውያንና በፈሩት እሥራኤላውያን ፊት በናቀውም ዳዊት ፊት በምድር ላይ በግንባሩ ተደፋ፡፡ ይህ መቼም አስገራሚ ትርዒት ነው፡፡ በተለይም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ ያልተጠበቀ ደንጋጤና የተስፋ መቁረጥ ሊፈጥር የሚችል ነገር ነው፡፡ ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው--- በዳዊት እጅ ሰይፍ አልነበረም፡፡ ዳዊትም ሮጦም በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፣ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፡፡ ራሱንም ቆረጠው( ቁ. 50-51)፡፡ ስለዚህ ነው አስቀድሞ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን አምላክ አይደለም ያለው፡፡ እግዚአብሔር በእርግጥም በሰይፍና በጦር ሳይሆን ሕዝቡን በስሙ የሚያድን አምላክ ነው፡፡ እኛ የምንጠራው የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ከጦርና ከሰይፍ ይበልጣል፡፡ እኛ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የለንም፣ መድፍ መትርየስ የለንም፣ የታጠቅነው የምንበለበል ሚሳየል የለንም፡፡ ይሁን እንጂ ጦረኛውንና የጦርን ኃይል ሁሉ የሚያቀልጥ የእግዚአብሔር ስም አለን፡፡ ይህ ስም የጦርነቱን ታሪክ ይቀጥራል፣ የሕይወትንም ተግዳሮት ሁሉ ይገለብጣል፡፡ በዳዊትና በጎልያድ ጦርነት ፍጻሜ የሚናየው ይህንን እውነት ነው፡፡ ጦርነቱ ሲጀምር በፍርሃት ሲንቦቀቦቁ የነበሩት መላው እሥራኤላውያን ነበሩ፡፡ ዳዊት ጎልያድን ሳይታሰብ ባልተጠበቀም ሁኔታ መትቶ ሲጥለው ነገሩ ተገለበጠና በፍልስጠኤማውያን ላይ የፍርሃት ድባብ ተሳፈረባቸው፡፡ ዋናቸው እንደሞተ ሲያዩ ልባቸው ክፉኛ ስለተደባለቀባቸው በፍርሃት ቀለጡ፣ጊዜም ሳይሰጡ ከቆሙበት ሥራ የት እንደሚሄዱ ሳያውቁ ሸሹ፡፡ ሲፈሩና ሲደነግጡ የነበሩ እሥራኤላውያን ከታየው ተአምር የተነሳ ፍራቻው ከላያቸው እንደጉም ስለሄደባቸው ማለቀስን አቁመው፣ መርበትበታቸውን ትተው ተራው የእነርሱ ሆነና እልልታ አቀለጡ፡፡ የእግዚአብሔር ስም ስለተዋጋ ዳዊትን በትንሽነቱ ቁልቁል እያየ ሲያናነንቀው የነበረው ሰማይ ጠቀሱ ጀግና የትዕቢቱ ክምር ሁሉ በቅጽበት ስለተናደበት ከዳዊት ጫማ ሥር ሆነ፡፡ የተመሰከረለት ጀግና እንደ ፎከረው መዋጋቱ ቀረና መንዛረጥ ሆነበት፡፡ ዳዊትም በላዩ ላይ ቆሞ በመምታትና ትጥቁንም በአሽከሮቹ ፊት ዓይናቸውም እያየ እየፈታ እንዳይላወስ አደረገው፡፡ የእግዚአብሔር ስም ተዋግቶ ታሪክን ይገለብጣል ይሏል ይህ ነው! ያልተጠበቀና ያልተገመተ እግዚአብሔርም ለሕዝቡ የሠራው ተአምር! ዳዊት የጎልያድን አንገት ቆረጠ፡፡ ከየትም ባመጣው ወይም እሥራኤል ባዘጋጁት፣ አባቱ በሰጠውም ሳይሆን ጎልያድ ራሱ በሳለው ሰይፍ መልሶ አንገቱን ቀላ፡፡ ጎልያድ አላወቀም እንጂ ለመሞቻው ሰይፍ ሲስል ነበር ማለት ነው፡፡ ወገኖች ሆይ! ጠላታችሁ ሰይፍ ሲስል በማየታችሁ ብቻ፣ የሰይፉን መብረቅረቅ ብቻ አይታችሁ ልባችሁ አይውደቅ፡፡ እግዚአብሔር ጎልያድን ሰይፍ ያሳለው ለዳዊት እንደሆነ ዳዊትም ጎልያድ በሳለው ጎራዴ ራሱን ጎልያድን እንዳረደው ለእናንተም ይህንን ታሪክ ሊሠራ የሚችል አስገራሚ አምላክ እንደሆነ እዩ፡፡ ስሙንም ጥሩ እንጂ ልባችሁ አይውደቅ፡፡ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር ተሸንፎ አያውቅም፡፡ በራሱ ተማምኖ የሚፎክር የእግዚአብሔርን ሕዝብ አሸንፎ አያውቅም፡፡ የጠላታችሁን ጦርና ሰይፍ የእናንተ ሊያደርገው ለእነርሱ ግን የመጥፊያቸው ሊያውለው የሚችል ተአምረኛ አምላክ ነው፡፡ እኛ የምንጠራው ይህ የእግዚአብሔር ስም ሁል ጊዜ ያሸንፋል፣ ለሕዝቡም ድልን ይሰጣል፡፡ ኦ!! ታላቁ የእግዚአብሔር ስም! ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነ ያ ታላቁ የእግዚአብሔር የአምላካችን ስም!
ወንድሞቼና እህቶቼ! እናንተ የምትጠሩት ይህንን የእግዚአብሄርን ስም ነው፡፡ ዳዊት የጠራውን የእግዚአብሔርን ስም እየጠራችሁ እንደሆነ ምንም አያጠረጠርም፡፡ ምንም እንኳን ግራና ቀኛችሁ ገደል ቢመስል ይህንን የእግዚአብሔርን ስም ጥሩ ፣እርሱ ድልድይ ሆኖ ወደ ማዶ ያሻግራችኋል፡፡ በህመም ውስጥ ሆናችሁ ተስፋ ብትቆርጡ አይዞአችሁ፣ ልባችሁም አይውደቅ ለሕመምተኞች ጤና የሚሰጠው የናዝሬቱ የኢሱሱስ ስም ነው፡፡ እርሱ ሽባዎችን እንደ ሰባ እንቦሳ ያዘልላል፡፡ ልባችሁ አይውደቅ የእግዚአብሔር የአምላካችን ስም የፀና ግምብ ነው፡፡ ወደ እርሱ ስንሮጥ ከውድቀት አንስቶ ከፍ ያደርገናል፡፡ ስሙ የተፈራነው፡፡ ስሙን የሚጠራ ሁሉ ይድናል፣ እርሱም ለሚጠሩት ሁሉ ባለጠጋ የሆነ አምላክ ነው( ሮሜ 10፡12)፡፡ የጌታ ስም ሁሉም ቢጠሩት የሚበቃ ነው፣ የሚጎድለው ነገር የለውም፡፡ ኦ ስሙ የተባረከ ይሁን፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ማለትም ከመከራው፣ ከችግሩ፣ ከጦርነቱ ፣ በሕይወታችን ካለው ከማንኛውም እንቆቅልሽና ተግዳሮች የተነሳ ልባችባችን አይውደቅ፡፡ እግዚአብሔር የዳዊት አምላክ ዛሬም በልጁ በኢየሱስ በኩል የገባልንን ቃል ኪዳን ይጠብቅልናል፡፡ እኛ ለእርሱ የቃል ኪዳን ሕዝቦች ነን፡፡ ዛሬ መከራችሁን አትዩ ትላንት ከአንበሳው ያዳናችሁን ጌታ እያሰባችሁ በዛሬው መከራ ወቅትም እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ መሆኑን አውቃችሁ በርቱ፡፡ እናንተ በጦርነቱ ልታሽነፉ አትችሉም እግዚአብሔር ግን ስለ እናንተ ይዋጋልና ሰልፉም የእርሱ ነውና ልባችሁን በእርሱ አበርቱ፡፡ የምትጠሩት የጌታ ስም ከሁሉም ያድናችኋል፡፡ ስለዚህ ልባችሁ ከ-----የተነሳ አይውደቅ! ልባችሁ አይውደቅ!

No comments:

Post a Comment