Thursday, June 11, 2015

ሥልጠና በኢትዮጵያ ላሉ ለወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናት

      ሥልጠና በኢትዮጵያ ላሉ ለወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናት

በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የኤች አይ ቪን ሥርጭት ለመከላከል የተለያዩ ሥልጠናዎች ይሰጡ ነበር፡፡ በየቤተ ክርስቲያናት ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች በበጎ ፈቃደኝነት መንፈስ ተነሳስተው በሙያቸው በእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አገልጋዮችንና አባላትን በማሰልጠን አመረቂ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ በአንጻሩም ደግሞ በየአጥቢያው ብዙ የተማሩና በሙያው የተካኑ ሰዎች እያሉ አንዳንድ ከሙያው ጋር ብዙም ቅርበት የሌላቸው ሰዎች ስለ ኤች አይ ቪ ሥልጠና አዘጋጅቻለሁና ሰልጥነው ሊያሰለጥኑ የሚችሉ 5 ሰው፣ 6 ሰው፣ 4 ሰው ወዘተ ከነመመዝገቢያ ብር ጋር ላኩልን እየተባለ በየጊዜ ጥሪ ይደረግ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የተባለው ሥልጠና የሕክምና ባለሙያዎች በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ከሚሰጡት ጋር ሲነጻጸር ግን እንዲያው የማላከፍ ያህል እንጂ ቀረብኝ የሚያሰኝ አልነበረም፡፡ አልጠቀመንም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ሌላም ጊዜ ለተመሳሳይ ሥልጠና እነዚያውኑ ሰዎች ይጠሩና አሁንም ሰዎች ተዋጥተው ይሄዱና የተባለውን ሥልሥተና ይካፈሉና ይመጣሉ፡፡ መጥተው እንዳያሰለጥኑ በሕክምና ሙያ እውቀታቸው አጥናፍ ያለፈ ፣ በማስተማር ሙያቸውም እኔ ነኝ ያሉ ሐኪሞች እዚያው እያሉ ደፍረው ላድርግ ማለት ይሳናቸዋል፡፡ ሌላም ጊዜ ሌላው ወገን ደግሞ በኤች አይ ቪ ኤዲስ በዓይነቱ ልዩ ሥልጠና ልሰጥ ተነስቻለሁ ይልና አሁንም ለየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ጥሪ ይበትንና ይህን ያህል ሰው ከመመዝገቢያ ጋር ላኩልን፣ እንዳያመልጣችሁ! ሲል አሁንም ሰዎች ይላኩና ሰልጥነው ይመጣሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደተባለው ሁሉ የሚሄድ አንድ ወንጌላዊ ነበርና አሁንም በሌላ ጊዜ ለተመሳሳይ ሥልጠና ሰው ይመረጥ ሲባል ያ ወንጌላዊ ተጠቆመ፡፡ ይህን ጊዜ አንድ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ አሉ፡፡ ይህ ወንጌላዊ እገሌ ኤች አይ ቪ በአገራችን ከተሰማበት ጊዜ አንሥቶ የሚሰጠውን ሥልጠና አንድም ሳይቀር ሁሉን ተካፍሏል ፣ ታዲያ የዶክተር ዲግሪ ቢሰጠውስ ምን አለበት እንዳሉ አስታውሳለሁ፡፡ እውነት ለመናገር ያ ወንጌላዊ ሥልጠና ወዳለበት ሁሉ ይሄዳል፣ ይካፈላል እንጂ የሰለጠነውን ግን ለሌላው አያስተላልፍም ነበር፡፡ ለሕዝብ ሥልጠና ይሰጥ ሲባል እርሱም ሆነ ሌሎች ከሌላ ቦታ ሌላ ሰው ይጋብዛሉ እንጂ አይ ብዙ ሰልጥኛለሁና አሁን እኔ ላሰልጥን ሲል አይታይም ፣ አይደመጥምም ነበር፡፡
ስለ ኤች አይ ቪ እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ ብዙ ተደጋጋሚ ሥልጠናዎች ይሰጡ ነበር፡፡ ለሕዝብ የሚዘጋጁ የሥልጠና ፕሮግራሞችን በሚመለከት በጣም የሚታወቁት፣ የጸረ ኤች አይ ቪ ሥልጠና ፣ የወንጌል ሥርጭት ሥልጠና፣ የመሪዎች ሥልጠና፣ ሲሆኑ አልፎ አልፎ የጸሎት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በተደጋጋሚ የሚሰጠው ሥልጠናዎች በይዘታቸው አንድ ዓይነት እንጂ ምን ልዩነት አይታይባቸውም፡፡ ይህ መሆኑ እየታወቀ ሰዎች በተደጋጋሚ እየሄዱ ይካፈላሉ፡፡ ከዚህ ጋር አንድ ላይ ማየት የሚገባው ሌላው ነገር ሥልጠና አዘጋጆቹ ዓላማ ነው፡፡ በየትኛውም ዘርፍ ቢሆን ሥልጠና የሚያዘጋጁ ሰዎች ከዚያ ሥልጠና ምን ጠብቀው ነው ቢባል ብዙዉን ጊዜ ያላቸው ዓላማ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ሳይሆን የአዘጋጆቹ የራሳቸው ዓላማ ነው፡፡ ይህን ለማወቅ ሥልጠናው ያዘጋጁ ሚኒስቲሪዎች የሥልጠናቸውን ሪፖርት የሚያቀርቡት ሰልጣኞችን ለላኩት ቤተ ክርስቲያናት ሳይሆን በገንዘብ ለሚደግፉአቸው ድርጅቶች መሆኑን መረዳት በቂ ነው፡፡ የተቀረጸው ምስል፣ የተደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ የሚነገረው ለውጭ ድርጅቶች ብቻ ነው፡፡ በአገልገሎት መስኩ አብረው ስለተሰለፉ ለእነርሱ ሪፖርት መቅረቡ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ለአነርሱ ብቻ ምንጭር ቆራጭ ከመሆን ባለፈ ለአብያተ ክርስቲያናት ምንም አለማለት ደግሞ ሌላው ድክመት ነው፡፡ ሥልጠናው በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ያመጣው በጎ ተጽእኖስ ምንድነው የሚለውን ለማወቅ መጣር እኮ አንድ ነገር ነው ግን በሚኒሰቲሪዎችችን በኩል ይህ ብዙም አይታይም፡፡
በአብዛኛው የተለቀቀው በጀት ዝም ብሎ እንዳይመለስ ቶሎ ቶሎ ብለን ሥልጠና እናዘጋጅ በሚል የሚሰጥ ሥልጠና በጣም በርክቷል፡፡ የሚሰጠው ሥልጠና የቤተ ክርስቲያናትን ዓላማ ለማስፈጸም ምን ያህል ይረዳል የሚለውን በአጥቢያ ቤተ ከርስቲያን ማየት ብዙም አይታሰብም፡፡ ሥልጠና ሰጪዎቹስ ለምን ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ጋር አብረው ተመካክረው የሥልጠና መርሀ ግብር አይዘረጉም? ቢባል መጀመሪያውም ገንድሰው የወጡት እነርሱ ስለሆኑ፣ አሁን አብረው ለመሥራት አይችሉም፡፡ እንዲያውም የአንዳንዶች ልብ በራስ የግል ዓላማ በእልክ ተጨብጦ ስላስቸገራቸው ፣ አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የሌላትን እኔ አምጥቻለሁ ስለሚሉ ሩቅ ሆነው ወደራሳቸው ይጠራሉ እንጂ አብረው መሥራት ይፈሩታል፡፡ ወይ ሥልጠና………
በአንድ ወቅት አንድ ሚኒሰትሪ እኔ ልዩ ነገር ታይቶኛልና የልጆች ሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪዎች ሥልጠና ልሰጥ ነው ብሎ ጠራና በጣም ጠቃሚና ቁም ነገር ያለበትን ነገር ለአገልጋች ያስጨበጠበት ጊዜ ደግሞ ነበር፡፡ ያንን አይተው ይመስለኛል ሌሎች ደግሞ ለሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪዎች ሥልጠና አዘጋጅቻለሁና ሁላችሁም ኑ ብሎ የሰጠውን ስልጠና ስናየው ከመጠነኛ ለውጦች በቀር የዛኛውን አሠራር እንደነበር ገልብጠው የመጣበት ነበር፡፡ የሚገርመው ግን ያዘጋጀሁትም ሥርዓተ ትምህርት አለና እንኩ፣ ከዛሬ ጀምሮ እርሱን ለልጆቻችሁ አስተምሩ ሲል ቤተ ክርሰትያንም ተቀብላ ማስተማር ጀመረች፡፡ ይሁን እንጂ ራዕይው ከመጀመሪያውም የቤተ ክርሰቲያንና የአገልጋዮቿ ስላነበር ብዙ የተደነጋገሩ ነገሮችና ብዥታዎች አንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡ ወይ ሥልጠና››››››››
በአገር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሞላ ጎደል እዚያው ስለሆኑ ቤተ ክርስቲያናት ስላሉበት ተጨባጭ ሁኔታ መቃኘት ብዙም አያቸግራቸውም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ቤተ ክርስቲያን ካለችበት ሁኔታ ጋር የተቀራረበ የሥልጠና ፕሮግራም ማቀድ ይችላሉ፡፡ የሚያስገርመው ከባህር ማዶ የሚመጡ አሰልጣኖች ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በአሜሪካን አገር ሰንብትበት ያሉ አገልጋዮች ወደ አገር ቤት ሲሄዱ ስልጠና ልሰጣችሁ ጌታ በልቤ አስቀምጧልና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁኝ ካሉ ሁሉ ነገር አለቀ፡፡ ምን ዓይነት ሥልጠና ነው የምትሰጠን? በምን ርዕስ ነው የምታሰለጥነን? የሥልጠናህስ ዓላማ ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ምንም አይጠየቅም፡፡ ለነገሩ ከዚያ በዘለለ መልኩ አንተ ባለህበት የምትኖረው አንዴት ነው? ለመሆኑ ያለህበትን ቤተ ክርስቲያን አማኞች ምን ያህል አሰልጥነህ አዘጋጅተሃል? በምትሰጠውስ ሥልጠና ምን ያህል ቀደ መዛሙርትን አፍርተሃል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የአገር ቤት ቤተክርስቲያንም ደግሞ ይህ ሥልጠና ካለንበት ሁኔታ፣ ካነገብው ዓላማ፣ እና ከራዕያችን ጋር ምን ያህል ይሄዳል የሚለውን በሰከነ አኳኃን አይገመግሙትም፡፡ ብቻ ከአሜሪካ ነው የሚመጣው ሲባል ከሰሙ ሣር ቅጠሉን ሁሉ ያሯሩጡታል፡፡ በተለይም አንድ ፈረንጅ አስከትሎ የሚሄድ ከሆነ አገልጋዩም ምድር ደህና ሁኚ ይላል፣ የአገር ቤት ሰዎችም እንዲያው ታይቶ የማይታወቅ ነገር እንደሆነ አድርገው ይራቆቱበታል፡፡ እነዚያ አገልጋዮች በአሜሪካን አገር እንዴት እንደሚኖሩ ቀርበው ቢያዩ ማ ኖሮ ሥልጠናው ቀርቶ አንተ በሰላም ወደ መጣህበት በተመለስክልን ባሉ ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ ከአሜሪካን ወደ ኢትዮጰያ የሚሄዱ ሰዎች ብልጥ መሆን እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ከረጅም ዘመን የውጭ ቆይታ በኋላ ቤተ ሰባቸውን ለመጠየቅ ሲሄዱ የትኬት ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ አንድ ፈረንጅ ቢያባብሉት እንደበረከት ይቆጥርና አብሮ ለመሄድ ከተስማማ የአየር ትኬቱን ዋጋ የሚሸፍነው ያ ፈረንጅ ነው፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ፈረንጅ ከተገኘ ማ በቃ የአየር ትኬት ብቻ አይደለም ሌላው ወጪ ሁሉ ይሸፈናል፡፡ ይህንን የኢትዮጵያ አገልጋዮች በጭራሽ አያውቁትም፡፡ ስለዚህ አንድ ያንን ፕሮግራም ማስተባበር የሚችል አዳማቂ ሰው በአገር ቤት ማዘጋጀት አንዱ ስልት ነው፡፡ እርሱ ሁሉንም ነገር ያሰናዳል፡፡ የአሜሪካው ሰዎች አስክመጡ ድረስ ሁሉንም ቀምሞ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከዚያ የተፈለገው ነገር ተሳካ ማለት ነው፡፡ እኔም ይህ ነገር የገባኝ አሜሪካን አገር ከመጣሁና ስለ አንዳንድ የሰው ልጆች ብልሃቶችና በእግዚአብሔር አገልግሎት ስም የሚደረጉ ቅጥፈቶችን ካየሁ በኋላ ነው፡፡ በእውነት ሕዝባችንን በደረቁ እየላጥነው ነው ያልኩት አሁን ነው፡፡ ሰዎቹ እንደማናችንም ትምህርት ቃርመው ሊሆን ይችላል፡፡ ያ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ እውነተኛና ትሁት ልብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ መዝናናት ኃጢአት እንዳይመስላቸው ህልናቸው ስለታመመባቸው ግድ የላቸውም፣ ቀጥሎ ስለሚሆነው ነገር ደንታ ቢሶች ናቸው፡፡ ይህን ነው እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መንቃት ያልቻሉት! ለምን ቢባል ከአገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ስለ ሰጡት ሥልጠና እዚሁ እንደ ጉድ ያስወራሉ እንጂ ያ ሥልጠና በምን ሥራ ላይ ዋለ ብለው አይጠይቁም፡፡ ሥራ ላይ የሚውል አለመሆኑን ገና ከዚህ ሲነሱ በደንብ ያውቁታል፡፡ ሥራውም ሲታይ ከቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታና አገልግሎት ጋር የማይዋሄድ ብትን ሥራ እንደሆነ የሁሉም ሆድ ያውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚያስፈልጋት የሚያውቅ በአሜሪካን ያለ አንድ አገልጋይ ወይም ኢትዮጵያን በእግሩ ረግጦ የማያውቅ ፈረንጅ ሳይሆን የኢትዮጵያ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እረኛ ነው፡፡ ካስፈለገም አቅም አንሳቸው ይሆናል እንጂ በኢትዮጵያ ያሉ እረኞች ለአሜሪካን አገልጋዮችም የሚሆን ስልጠና መስጠት ይችሉ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በጸጋ ስጦታው ባርኮአቸዋል እያልኩ ነኝ፡፡ በፈረንጅና በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው የቆዳና የቋንቋ ልዩነት እንጂ የእግዚአብሔር ጸጋ አይበልጥም አያነስምም፡፡ ማንም ይሁን ማን በአንድ ቀን ሥልጠና የሚያመጣው ታአምር የለም፡፡
አውነተኞች የተከበሩ ኢትዮጵያውያን አገልጋዮች በአሜሪካን አገር አሉ፡፡ ይህም የሚያስገርም ነገር ነው፡፡ወደ ኢትዮጵያም በመመላለስ ከሥልጠናም ባለፈ ትላልቅ ሥራዎችን የሠሩና ለቤተ ክርስቲያን በብዙ እየተረፉ እንዳሉ የታመነ ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ከመጀመሪያውም ከኢትዮጵያ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር አብረው ስለ ነበሩ የሚያደርጉትን ያውቁበታል ፣ እኔ ይሁንልኝ፣ ደህናም አድርጌ ልቀርቅብ እንጂ ሌላው የራሱ ጉዳይ የሚሉ አይደሉም፡፡ እንደነዚህ ያሉት ምንም እንኳን ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ቢሆን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አገልሎት የሚጠቅም ሞልቶ የተረፈ ነገር አላቸው፡፡ ሥልጠናና ትምህርት ለምን እንደሚሰጡ ያውቃሉ ፣ ከቤተ ክርስቲያንም ጋር እጅና ጓንት ስለሆኑ እነርሱ ባሉበት ሻሞ ሆይ አይባልም፡፡ የሥልጠናቸው ይዘት እንደነዚኛዎቹ ሥር የሌለው ቁርበተ- ነክ አይደለም፡፡ ስለ እነርሱ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል፡፡
ስለዚህ፣ እኔ ያለኝ መልእክት ቢኖር ሥልጠና፣ ሥልጠና፣ ሥልጠና እየተባለ እንደ አዝማች ከመደጋገም በሥልጠናው አስፈላጊነት ላይ አስቀድሞ መወሰን ጥሩ ነው፡፡ ደግሞ በአሜሪካን ያሉ ኢትዮጵያውያን አገልጋዮች ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲያስቡ ያለ ሥልጠና የማይታያቸው ምን ነክቶአቸው ነው? ሥልጠና መስጠት ከፍ ብለን አንደተመለከትነው የአጭር ጊዜ ስለሆነችና የአገር ቤቱን ወጭ ለመሸፈን ስለሚትረዳ ወይስ ሌሎች አባቶችና ወንድሞች ሲያደርጉ ሲሳካላቸውም እንዲሁም ከመልካም ሥራቸው የተነሳ ዝናቸው ሲወጣ ሰላየን እኛም ለምን በዚህ ስማችንን አናስጠራም በሚል ይሆን? ዝና እኮ መልካሙን ሥራ ስንተገብር ያዩ ሰዎች ሰብሰብ ብለው የሚያስተጋቡት የሠፈር ወሬ ነው፡፡ እኛ መልካሙን ከሠራን ሰዎች አንዱ ለሌላው እያሰማ ሳናውቀው ዝናችን ሊወጣ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እግዚአብሔርን ይወዳል፣ ይፈራልም፡፡ ግን እንዲያው ምንም የማይገባው ድፍን ቅል አኮ አይደለም፡፡ እንግዳ ይወዳል ያቀበላል ግን በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ሌባ ሁሉ ሲመዠርጠው አይሰማውም ማለት እንዳይደለ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም ለወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ሥልጠና አዘጋጅቻለሁ የሚሉ ወንድሞች ምን አስበው እንደሚያደርጉት አስቀድሞ ይታወቅ፡፡ በሥልጠና ብቻ ቤተ ክርስቲያንን ማሳደግ፣ መደገፍ፣ የወደፊት ራዕይዋንም መሳካት አይቻለልም፡፡ ሥልጠና የሚያስፈልግባቸው ሁኔታዎች የትኞቹ አንደሆኑ የአጥቢያ እረኞች ያስቡበት እንጂ ሩቅ ሆነን እኛ እናውቅላችኋለን ማለት ከልክ ያለፈ ቀልድም በደልም ነውና ሁላችንም እናስብበት፡፡

No comments:

Post a Comment