Thursday, June 11, 2015
የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ወይስ የሙሉ ልብ አገልጋዮች?
በቤተክርስቲያን ለምናገልግል አገልጋዮች "የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች" የሚል ስያሜ ወይም ማዕረግ ይሰጠናል፡፡ ወንጌላውያን መጋቢያንና አስተማሪዎች ብሎ ባለን ጸጋና በተሰማራንበት የአገልግሎት ሥፍራ መሠረት መጥራት በቂ አይደለምን እየልኩ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ እኔም በቤተክርስቲያን ሳገለግል ከሌሎች ጋር በአንድ ላይ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እየተባልን ስንጠራ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይህ አበባል አገልጋዮቹ የትኞቻችንም ቢንሆን ሙሉ ጊዜአችንን ለጌታ አገልግሎት የሰጠን መሆናችንን የሚያመለክት አባባል ነው፡፡ ወንጌላዊም ሆነ መጋቢ ሌላውን ትተው ለጌታ ስራ ሙሉ በሙሉ ጊዜኣቸውን ስለሰው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ብለን ብንላቸው ምንም ስህተት የለበትም፡፡ ይሁን እንጂ የአገልጋዮችን አገልግሎት ከጊዜ ጋር ካያያዝነው በአገልጋዮችና በሰራተኞች መካከል ልዩነት መኖር አለመኖሩን መመልከት ይኖርብናል፡፡ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች የምንላቸው አሉ፡፡ እነዚህ በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች በቀን 8 ሰዓት በሥራ የሚያጠፉ ሲሆኑ ከዚያ በታች የሚሠሩ ከሆነ ደግሞ የግማሽ ጊዜ ሠራተኞች ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሙሉ ጊዜ ወይም የግማሽ ጊዜ ሠራተኝነታቸው የሚወሰነው ሠራተኞቹ በሥራ ላይ የሚያሳልፉት የሰዓት መጠን ነው፡፡የሚያገኙት የገንዘብ መጠንም በዚያው መጠን የተለያየ ይሆናል፡፡ በቀን 5 ሰዓት የሠራ ሠራተኛ የሚያገኘው ደመወዝ በቀን 8 ሰዓት የሚሠራው ሠራተኛ ከሚያገኘው እጅግ ያነሰ ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሠራተኞቹ በሥራ ቦታቸው የሚያስመዘገቡትም ውጤት የዚያውኑ ያህል ልዩነት አለው፡፡
ወደ አገልጋዮች ሁኔታ በምንመለስበት ወቅት የእኛን ሁኔታ ከሠራተኞች ሁኔታ ለይቶ መመልከት ይቻላል፡፡ የአገልጋዮች የአገልግሎት ሁኔታ በሰዓት የሚወሰን ሳይሆን ከጌታ ዘንድ በተቀበልነው ጥሪና በውስጣችን ባለው፣ በእኛም በሚገለጠው ጸጋ መሠረት የሚወሰን ይሆናል፡፡ ወንጌላዊን ወንጌላዊ የሚያሰኘው እርሱ በቤተ ክርሰቲያን ያሳለፈው ሰዓት መብዛት ወይም ማነስ ሳይሆን ጥሪውንና ጸጋውን የገለጠበት መንገድና ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ ነው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከምንባል ወንጌላውያን ፣ መጋቢያን፣ ወይም መምህራን ብንባል ይሻላል ያልኩት፡፡
አገልጋዮች ራሳቸን ስለ ራሳችን ስንናገር የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነን ስንል እንደመጣለን፡፡ እኛ ካልነው ደግሞ በግልጽ መታየት ያለበት ነገር አለ፡፡ አገልግሎትም ቢሆን ከጊዜ ጋር የሚሄድ እንጂ ከተሰጠን ጊዜ ውጭ የሚሰራ ነገር አይደለም፡፡ ጊዜዬን ሙሉ በሙሉ ለጌታ ሰጠሁ የሚል ከሆነ ከእኛ አንድ አገልጋይ በቀን ስንት ሰዓት በጌታ ሥራ ላይ ያሳልፋል? ወይስ እኛ ቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊ ብላ ስለተቀበለችን ሌላ ሥራ ሳንሠራ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ስለምናሳልፍ ብቻ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ተባልን? በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ካለን አገልጋዮች መካከል በቀን 8 ሰዓት ይቅርና በታማኝነት 4 ሰዓት የምንሠራ ስንቶቸችን ይሁን?ይህንን ለመመዘን የሚያስችል ሥርዓት በቤተ ክርሰቲያን ውስጥ ስለሌለ እንዲሁ በደፈናው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እየተባልን አገልግሎቱ ይጓተታል፡፡ በሌላም በኩል አገልጋዮቹ ትክክለኛ የጌታ ጥሪ የደረሳቸው ሲሆኑ ቀስቃሽና ጎትጓች ሳይፈልጉ የኃላፊነት ስሜት እየተሰማቸው አገልግሎታቸውን በትጋት ይወጡታል፡፡ በውስጣቸው ያለው የአገልግሎት ሸክም በአጥንታቸው ውስጥ እንደሚሄድና እንደሚነድድ እሳት ሲሆንባቸው ጊዜ እንቅልፍ እንኳ ሳይተኙ ለጌታ ሥራ ሌት ቀን ይሮጣሉ፡፡ ምንደኝነትና የአገልጋይነት ስም የቀላቀለባቸው አገልጋዮች ግን ከሥራ ይልቅ ስለሚሰጣቸው ስም ሲሟገቱ የአገልግሎት ጊዜአቸው ከፊታቸው ሮጦ ያልቅባቸዋል፡፡ እኔና አንባቢ ከየትኞቹ ነን?
በትጋት የሚያገልገሉ አገልጋዮች ከሚገባው ሰዓት በላይ ሰርተው ነገ ለሚጠብቃቸው አገልገሎት ጉልበት እንዳያጡ፣የዛሬው ዉጤታቸውም እንዳያንስ ቤተ ክርስቲያን ተገቢ እንክብካቤና ጥበቃ ታደርጋለች ወይ የሚለው ደግሞ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ እንዲያውም አንዱ ሲሰራ ቆመን ጸሐይ ከምንሞቅ አገልጋዮች ይልቅ በሥራ በሚጠመዱ ላይ ተጨማሪ ሥራ በላይ በላዩ እየተሰጣቸው ከጫና ብዛት የተነሳ እንዲገዳገዱ ይደረጋል፡፡ ቆመን የሚናወራውና የሚንተቸው ግን የሥራ ኃላፊነት መሸከም የማንፈልግ ደግሞ ተደማጭነት ያለን እኛው መሆናችን የበለጠ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሠራተኞች እያሉ ተናጋሪዎችን ፊት ለፊት እያቆሙን ሰዎች ምሥጋናውን ሁሉ ለእኛ ይሰጡናል፡፡ ምክንያቱም እኛ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እያልን ስለሚያወራና ስለሚናስወራ ለሰዎች የተሸለ መንፈሳዊ እንመስላቸዋለን፡፡ አሁን አሁን በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ትኩረት የሚሰጠው ለሚሰሩ ሳይሆን ብዙ ለሚያወሩ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን በአፋቸው ለሚኖሩ የተሸለ መሸሸጊያ ሆናለችና፡፡ ሥራ ካጣሁ ካጣሁ ወንጌላዊነት እንኳ ቢሆን አገኛለሁ እንጂ አልወድቅም ያለም ወንጌላዊ እገሌ ፣ፓሰተር እገሌ እየተባለ ነው፡፡ አንባቢ አጋነንክ አይበለኝ እንጂ አሁን አሁንማ ያሉን ምዕመናን የግማሽ ያህሉ ፓስተር ሊሆን ነው፡፡ ፓስተርነት ግብር የማይከፈልበት የገቢ ማሰገኛ መንገድ ስለሆነ ሰዎች የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ሃይ በል የሚሉት ከፓስተርነት ነው፡፡ ስለዚህ የምዕመናንም ሕይወት ጥራት የዚያኑ ያህል ነው፡፡
እዉነተኞች አገልጋዮች ለእግዚአብሔር ቤት እድገትና ለወንጌል መሥፋፋት በጣም የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ እነርሱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የምንላቸው ሳይሆን የሙሉ ልብ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጉት የሙሉ ጊዜ ሳይሆን የሙሉ ልብ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ጌታ ከማንም ቢሆን ጊዜውን ሳይሆን ልቡን ይፈልጋልና፡፡ ሙሉ ጊዜውን ሰጠ የምንለው ሙሉ ልቡን የሰጠው ሰው ነው፡፡ የሙሉ ልብ አገልጋዮች እንሁን ፣ የሙሉ ልብ አገልጋዮችንም እናፍራ ፣ ላሉትም እንጠንቀቅላቸው፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment