ንቅስ ያለ የልብ ሰው ይሁንላችሁ፡፡
I. መግቢያ
ቆንጅናና ውበት በምን ይለካል? በጥቁረት ወይ በቅላት? በውፍረት ወይስ በቅጥነት? በርዝመት ወይስ በእጥረት? ውበት በእርግጥ ውበት የሚሆነው እንዴት ነው? እኔ እንደምረዳው ለቁንጅና የሚሰጠው ብያኔ እንደየሰው አተያይ ይለያያል፡፡ ለአንዱ ምድር ፊት የሆነ ፉንጋ የተባለ ለሌላው ታይቶ የማይጠገብ የዓይን ምሳ ነው፡፡ ለአንዱ እራሪ -ድንኪዬ የተባለ ለሌላው ጌጥ ፣ ለአንዱ ሸበላ ሲባል የኖረ ወደ ሌሎች ጋ ሲደርስ ፊታቸውን ሊያዙበት ሁላ ይችላሉ፡፡ ክብ ፊት የላቸውን ሰዎች የሚወድዱ እንዳሉ ሁሉ ረዘም ያለና ሾጣጣ ፊት የሚማርካቸው ብዙ ናቸው፡፡ የረዘመ አፍንጫ ያለውን ሰው ሰልካካ ብንለውም አፍንጫ ቢርዝም ማር አይቆርጥ የሚሉ ያዚያኑ ያህል ናቸው፣ እንዲያውም የተጠረበ እንጨት የሚመስላቸውም አይታጡም፡፡ ታዲያ ውበትና ቁንጂና የቱጋ ናቸው? በአገራችን አንድ ሰው ወፈር ካለና ሆዱ አካባቢ ቦርጭ ጣል ካደረገበት ተመችቶታል ከማለት አልፎ ሀብት እንዳለውም ሲታሰብ በተቃራኒው በምዕራባውያን ዘንድ ሰውን ወፍራም ነህ ማለት ሊያቀያይም ስለሚችል የማይፈለግ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ውበት አንጻራዊ ነው ብል ብዙዎቻችሁ የምትስማሙ ይመስለኛል፡፡ የውጭ ሰውነታችን የሚያምር ብቻ ሳይሆን የሚያየን ሁሉ የሚወድደው እንዲሆን እንቀባባዋለን ፣ በተቻለን መጠን እናስውበዋለን፡፡ በሰለጠነው ዘመን ብዙዎች እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ውበታቸው የቀነሰባቸው ስለሚመስላቸው የፍታቸውን መልክ በቀዶ ጥገና ዜዴ እንደ ወጣት ደምግባት ያላቸው ለመምሰል ሲሉ ከፍተኛ መጠን ያለውን ንዋይ ያፈስሱበታል፡፡ ይህን ያህል ከተለፋም በኃላ ሰው ለቁንጅና የሚሰጠው ቢያኔ ለየራስ ስለሆነ በሁሉ መደነቅና ሁሉን መማረክ አለማቻላቸው ከንቱ ኪሳራ ያስብላቸዋል፡፡ ሰው የቱንም ያህል ፊቱን ቢያሳምርና ቢቀያይር የውጭ ገጽታው እውነተኛ ማንነቱን ሊወክል አለመቻሉ በጣም አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ ለዚህ የሚደረገው ጥረት ከፈጣሪ ጋርም የሚያጣላ ሆኗል፡፡ በሰው ፊት መልካቸው የሚያምር ግን ስንት ሰም- ለበስ የሆኑ ክፉዎች እንዳሉ ቤት የቁጠረው ማለት ብቻ ይበጃል፡፡ አንነድች ውበት ማለት የውስጥ ጉዳይ ነው የሚሉት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እኔም ላሰምርበት የምፈልገው ይህንን የሚመስል ብርቱ ጉዳይ ነው፡፡እናም እንዲያው ባጭሩ ስለ የውስጥ ሰውነት ማማር ለቅምሻ ያህል የወግ ወጉን ብቻ መርጠን በእጥኑ እንመልከት፡፡
የእግዚአብሔርም ቃል ሲናገር ሰው ፊትን ያያል ይለናል፡፡ ሰው ፊትን ያያል ሲል መልክን ፣ ቁመናን፣ አለባበስን፣ አነጋገርን፣ ከሌሎች ጋር ያለ “አቀራረብ ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን እኛ እንደምናይ ፊትን አይቶ አይበይንም፡፡ እርሱ የሚያየው ልብን ነው፡፡ የሰው ልብ ከባልንጀራው የተሰወረ ነው፣ ለእግዚአብሔር ግን በግልጽ ይነበብለታል፡፡ ሰውን ሁሉ ግሩምና ድንቅ አድርጎ የሠራው እግዚአብሔር ያ ቆንጆ ነው ይህ ግን አይደለም የሚል ድራማም ከእኛ ጋር ለመጫወት ጊዜውን አይሰጥም፡፡ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነው ሐዋሪያው ጴጥሮስ ጌታ የውስጥ ሰውነታችንና ማንነታችን እንደሚያይ ብቻ ሳይሆን እንደሚያከብረውም ጭምር ሲያመለክት በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ ፣ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ ይለናል (1 ጴጥ 3፡4)፡፡ ሐዋሪያው በወንድና በሴት ማለትም በባልና በሚስት መካካል ስላለው የፍቅር ትሥሥር ሲያስተምር ነው ይህንን አሳብ ያመጣልን፡፡ ባልና ሚስት ሁለቱም በየራሳቸው ለትዳራቸው መስመር ሊጫወቱ ስለሚገባቸው ሚና በመተንተን እየተናገረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ የሚለውን ወሳኝ መልእክት ያስተላልፍልናል፡፡ እረ ለመሆኑ እንደ ፊት መልክ የልብ ሰውነትን ተመልክቶ ነጭ ወይ ጥቁር ወይም ጠይም፣ አይነ ልም ወይም መልከ መልካም ማለት ይቻል ይሆን; ካልተቻለስ ;
II. የልብ ሰው መገለጫዎች
1. በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው የከበረ ነው፡፡
ምእራባውያን ጊዜ ወርቅ ነው ፣ ክቡር ነው ይላሉ፡፡ ቤንጃሚን ዲርሳይሊ የተባሉ ሰው ግን- "ጊዜ ወርቅ ነው እውነት ግን ከጊዜ ይልቅ ውድ ነው " ሲሉ ፣ኤልሳቤጥ ጆርጅ የተባሉ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ሴት ደግሞ "እያንዳንዱ ቀን የሚናደርገውን ሁሉ እግዚአብሔርንና መንግሥቱን ለማገልገል የሚናውለው ከሆነ የከበረ ነው " አሉ፡፡ ጆን ፓይፔር የተባሉ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰውም እንዲህ ብለው ሰበኩ- "የሚያድን እምነት ያላችሁን ሁሉ ብትሸጡና በኃጢአት የሚገኘውን የዓለም መዝገብ ሁሉ ብትተውት የሚያስተማምናችሁ ነው፡፡ የተሰወረው የቅዱስ ደስታ መዝገብ ጥልቅ ለሆነው የውስጣችሁ ጥማት ርካታን ይሰጠዋል፡፡ ከልብ የሆነው የሚያድነው እምነት ኢየሱስን በውስጣችሁ እውነት ማድረግ ብቻ ሳይሆን እርሱን ሁል ጊዜ እንድትናፍቁት ያደርጋችኋል ፣ ኢየሱስ በተስፋው በኩል ወደ እናንተ መምጣቱ በዓለም ካለው ሁሉ ይልቅ አብልጠን የምንፈልገው ትምክህታችን ነው፡፡"
ውድ ዋጋ አውጥተን ልብስና የወርቅ ጉትቻ የምንገበየው ለብሰን በሰዎች ፊት ለማማርና ለማጌጥ ነው፡፡ የሚያዩንም ደግሞ በለበስነው ልብስና የወርቃችን ጥራት መጠን ያከብሩናል፡፡ የምንሠራውን ሽሩባና የምናንጠለጥለውን ጉትቻ እኛ አናየውም የሚያዩልን ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን የሚያከብረው የልባችንን ጌጥ ነው፡፡ እርሱ ሰው ስለሚያየው የውጭ ማማር ስንጨነቅና ስንወጠር እግዚአብሔር የሚያየው የውስጥ ውበታችን አመድ እንዲለብስብን አይፈልግም፡፡ በእርሱ ፊት እጅግ የከበረ ዋጋ ያላቸው እንደነ ጋብቻ፣ የቅዱሳን አገልግሎትና ሕይወት ወዘተ፣ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱና አውራ የሆነው ሰው ለእግዚአብሔር የሚሰጠው በውስጥ የተሸለመ የልብ ሰውነት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የሚለው ቃል ክብደት ሊሰጠው እንደሚገባ ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡
2. የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለው ነው፡፡
በዚህ ሁለት ቁልፍ አሳቦች ተጠቃለው ቀርበዋል፡፡ አንደኛው የዋህነት ሲሆን ሁለተኛው ዝግተኛ መንፈስ ነው፡፡ የዋህነትና ዝግተኛ መንፈስ ማለት ምን ማለት ነው? ሁለቱም አሳቦች ትህትናን፣ ሰላማዊነትንና ጸጥታን ለማመልከት የተጠቀሱ አይደሉምን? የውጭ ሰውነታቸውን በመሸለምና በማስጌጥ ቁንጅናቸውን ለዓለም ለማሳየት የሚዳክሩ ዓለማውያን ሴቶች በበዙበት ዓለም ለእግዚአብሔር ሰዎች ደግሞ በሚያዩአቸው ሁሉና በአምላካቸው ፊት እውነተኛው ዉበታቸው የዋህና ዝግ ያለ መንፈስ ነው፡፡ በተለይም በጴጥሮስ ዘመን ያላመኑ ባሎች ያሉአቸው ክርስቲያን ሴቶች ባሎቻቸውን ለክርስቶስ ለመማረክ ውጫዊ ሰውነታቸውን ከመሸለምና በማስዋብ ይልቅ በየዋህነትና ዝግ ባለው መንፈስ በመመላለስ እንዳለባቸው ሐዋሪያዊ ትምህርት ተሰጥቶአቸዋል፡፡ የዋህነት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በብዙ መንገድ ተጠቅሷል ፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚገልጸው የዋህነት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው( ገላትያ 5፡22)፡፡ ጌታችን ኢየሱስም የዋህነትን ከእርሱ እንድንማር አሳስቦናል( ማቴ 11፡29-31)፡፡ አማኞች በየዋህነት መንፈስ በመመላለስ ክርሰቶስን መምሰል ይችላሉ፡፡ በቤትና በውጭ የክርስቶስ እውነተኛ ደቀመዝሙርነታችን ከእርሱ በምንማረው የዋህነት ልንገልጸው እንችላለን፡፡ የዋህነት በባልና በሚስት መካከል ላለው ግንኙነት እጅግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ የተለየ ግምት እንስጠው፡፡
3. የማይጠፋውን ልብስ የለበሰ ነው፡፡
የክርስትና ሕይወት ለማይጠፉ መንፈሳዊ ቅርሶች አድሎናል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመናችን የምናገኘቸው ሰማያዊ በረከቶቻችን የማይጠፉ በመሆናቸው ደስታችን የላቀ ነው፡፡ ለምሳሌ፡ የማይጠፋ ሕይወት(1ጴጥሮ.1፡3-4) የማይጠፋ ርስት፣ የማይጠፋ ተስፋ(1ኛ ጴጥ1፡3-4) ፣ የማይጠፋ አክሊል( 1ቆሮ.9፡) ፣ የማይጠፋ ዘር( 1ጴጥ 1፡23)፣ የማይጠፋ ቤት ወይም መኖሪያ(2 ቆሮ 5፡1-4)፣ ወዘተ በክርስቶስ በማመናችን ምክንያት ያገኘናቸው መንፈሳዊ በረከቶቻችን ሲሆኑ እነዚህ ከማናቸውም ምድራዊ እሴቶች ሁሉ ይለያሉ፣ ይበልጣሉም፣ እኛም ልንወርሳቸው ተጠርተናል፡፡ በምንም ሁኔታ ቢሆኑ ከማይጠፉ መንፈሳዊ በረከቶቻችን አንዱ የውስጥ ሰውነታችን የምንሸልመው የማይጠፋው ልብስ ነው፡፡ የልብ ሰው የሚለብሰው ልብስ የማይጠፋ በመሆኑ የተለየ ግምትና ክብር ይሰጠዋል፡፡ ይህን የውስጥ ሽልማታችንን የሚወስድብንም ሆነ የሚያስረጅብን የለም፡፡ የውስጥ ሽልማታችን በወረት ወይም በፋሽን ሽሚያ ምክንያት በሚከወን ድንገተኛ ማባከን አይጠቃም፡፡ ስለዚህ ሐዋሪያው ክርስቲያን ባለትዳር ሴቶችን ከውጭ ይልቅ ውስጣቸውን እንዲያስጌጡና እንዲሸልሙ አጠንክሮ ይመክራቸዋል፡፡ እውነተኛ ውበት የፊት ወዝ ሳይሆን በነፍስ ላይ የሚታይ ብርሃን ድምቀት ስለሆነ የዓለም ያርግልህ/ሽ ማለትስ በውስጥ ሰውነታቸው በማይጠፋ ልብስ የተሸለሙትን ነው! ውስጣችን ምንም ወዝ የጠፋበት ነጫ ጭባ ከሆነ ውጫዊ ሽልማት ብቻ ውብ አያስብለንምና፡፡
4. የተሰወረ የውስጥ ሰው ነው
የውስጥ ሰው የምንለው የማይታየው ማንነታችንን ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ነፍሳችንን፣ መንፈሳችንን፣ እና ህሊናችንን ማለታችን ሲሆን የልብ ጉዳይ ግን አውራ ነው፡፡ የሕይወት መውጫ ልብ ናት፡፡ የሰው ውድቀቱም ሆነ ጥንካሬው እንደልቡ ነው፡፡ የሕይወት አሸናፊነታችንና ጀግንነታችንም የሚገለጸው እንደ ልባችንና እንደ ሐሞታችን ነው፡፡ በእውነት እንነጋገር ካልን ብዙ የመናገራችን ብዛት የልባችንን ምስል አያሳየንም ፣እንዲያውም የጠቢብ ሰው አፍ በልቡ አይደል! ልብና ታማኝነትስ ፍጹም የማይለያዩ ሰምና ፈትል አይደሉ! ስሜታችን ግለቱ ከፍ ሲል ሰዎችን አቅፈን ልንስማቸው እንችል ይሆናል፣እውነተኛ ማፍቀር ግን ከዚያ ይለያል፡፡ አክብሮትንም ለሰዎች ልንቸራቸው እንችላለን ግን ግን ስሜትን ፣አእምሮን፣ስጋንና፣ አስተሳሰብን ሁሉ የሚማርክ ፍቅር የሚመነጨው ከውስጥ ሰውነት ከሆነው ከልብ ነው፡፡ ከልብ የሚመነጨው ፍቅር እንደገለባ እሳት በቅጽበት አይከስምም፡፡ ስለዚህ ነው ፍቅር በትዳር ውስጥ ምሶሶ ነው የምንለው፡፡ ከልብ የመነጨ ፍቅር ካለ የሕይወት ተግዳሮት በሚበዛበት ጊዜ ሁሉ እንኳን ጎጆው ሳይዘምም ይኖራል ምክንያቱም ያ ፍቅር ተሸክሞታልና፡፡
ስለዚህ አማኞች እህቶች ወይም ባለ ትዳሮች የውስጥ ሰውነታቸውን ማጌጥ መርሳት የለባቸውም፡፡ ከሥጋችን ይልቅ ለነፍሳችንና ለመንፈሳችን ግድ ሊለን ይገባናል፡፡ ጌታ ኢየሱስም ሲያስተምር ነፍስ ከመብል ከሰውነትም ከልብስ ይበላጣል ብሎአል(ማቴ 6፡25)፡፡ በእግዚአብሔር ጸጋና በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት እለት እለት ነፍሳችንን ልናረካት እንችላለን፡፡ ታዲያ ውስጣችን እንዴት ነው? ለሰው የተሰወረው ለእግዚአብሔር ግን የሚነበብለት ውስጣዊ ማንነታችን ሕያው ነው ወይ ሞቶብናል? ያ የተሰወረው የውስጥ ሰው!
ለ. የልብ ሰው ባሕሪያት
ይህ ክፍል በጌታ የሆንነውን ሁላችንንም የሚመለከት ሲሆን በተለይም የማያምኑ ባሎች ያሉአቸው ክርስቲያን እህቶች እንዲያተኩሩበት ይሻል፡፡ ክርስቲያን ሴቶች ወይም ሚስቶች የተሰወረ የልብ ሰው መሆናቸውና ውስጣዊ ውበታቸው የሚታወቅባቸው መንገዶች ምን እንደሆኑ የጌታ ቃል የሚናገረንን ግልጽ አሳብ ከዚህ ቀጥሎ እንመልከት፡፡
1. ለባሎታቸው ይገዛሉ፡( 1ጴጥሮ 3፡1፣ ኤፌ 5፡21-22)፡፡
ሚስቶች ለባሎቸቸው እንዲገዙ የሚነግረን የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ነው፡፡ ክርሰቲያን ተጋቢዎች ወደ ክርስትና በመለወጣቸው ምክንያት በሚኖሩበት አካባቢና ዘመን ያለው የትዳር ደንብና ሥርዓት የእነርሱን የማይመለከታቸው አድርገው ለራሳቸው እንዳያስቡና ሌሎች ሰዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ራሳቸውን ለባሎቻቸው እንዲያስገዙ ይመክራቸዋል፡፡ ሐዋሪያው ጴጥሮስ በነበረበት ዘመን ሴት ልጅ ሙሉ በሙሉ በአባቷ ቁጥጥር ሥር ትሆናለች፡፡ ሴቶችን እንደ ሰው በማይቆጥረው የሮማውያን መጥፎ ልማድና ባህል መሠረት አንድ ሰው በሴት ልጁ ላይ የፈለገውን ከማድረግ አልፎ ቢፈልግ ሊገድላት ሁሉ የሚችልበት መብት ሲኖረው ይህንን የሚከለክል ሥርዓት አልነበረም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሴት ባል ስታገባም ፈቃዷ ሙሉ በሙሉ ለባሏ ይሆናል፣ እርሱም በሚስቱ ላይ የፈለገውን የማድረግ ሥልጣን ነበረው፡፡ ባል ሚስቱን ቢገድል እንኳ የሚከለከልው እስከማይኖር ድረስ ሴት ለባሏ እንደ ዕቃ ወይም እንደ ባሪያ ትገዛለት ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን የሆኑ ሚስቶች ለባሎቻቸ እንዲገዙ ጴጥሮስ የሚያሳስበው ከአሬማውያን አገዛዝና ሥርዓት በፍጹም የተለየ ነው፡፡ ክርስቲያን እህቶቻችን ለሚወዱአቸው ባሎቻቸው ሥልጣን ከልባቸው በመነጨ ፍቅር ተነስተው መገዛት እንዲኖርባቸው ጴጥሮስ ያሳስባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ፈቃድ የማይኖሩና አስቸጋሪ የሆኑ ባሎችን ለማሸነፍ የሚረዳ ዋንኛ መንገድ ነው፡፡ ፍቅር የትኛውንም ኃይል የማንበርከክ አቅም አለው፡፡ ለእግዚአብሔር ቃል የማይገዙ ለቤተሰባቸውም የማያስቡ አስቸጋሪ ባሎች በፍቅር ሊንበረከኩ ይችላሉ፡፡ ልዩነቱ አረማውያን ሴቶች ለባሎቻችው የሚገዙት እንደ ባሪያ በግድና በጉልበት ሲሆን የክርሰቲያን ሴቶች መገዛት ግን በፍቅር አስገዳጅነት በገዛ ፈቃዳቸውና በራሳቸው ተነሳሽነት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ተገዙ የሚለው ቃል ሴቶች ለወንዶች ባሪያ ሆነው እንዲረገጡላቸው የሚያዝ ሳይሆን ወድደውና ፈቅደው የሚደርጉት ልዩ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው ነው፡፡ የመገዛቱ አስገዳጅነት ለሚስቶች ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ባሎችም እኮ ለሚስቶቻቸው እንዲገዙ ቅዱስ ቃሉ ያስተምራል(ኤፌ 5፡21፣ 1ጴጥ 3፡7)፡፡ የክርስቲያናዊ ሥልጣንና መገዛት በእግዚአብሔር ፍጹም ፍርሃት በእርስ በርስ የሚደረግ እንጂ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች እግር አጣቢ የሚሆንበት አይደለም፡፡ ይልቁንስ የክርስቶስ ፍርሃትና ባልን የመውደድ ምስጢር ለገባት ሴት ሚስትነት እኮ የተከበረ ፣ ከፍ ያለና ወሳኝ ሰማያዊ ጥሪ ነው፡፡ ስለዚህ ራሷን ለበሏ ስትሰጥ የባሏ ፍቅር ደስታዋን ሙሉ ያደርግላታል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ተገዙ የሚለው አንድ መንገደኛ ለሆነ ወንድ ሳይሆን፣ ወይም የሆነ የጎረበት ሰው ሳይሆን አካሏ ለሆነው ባል ነው፡፡ ባሏ ለእርሷ አካሏ፣ ምርጫዋ ከማንኛውም ወንድ ጋር የማታወዳድረው ልዩ ጌጧ ነው፣ ከወንድሟም ይልቅ የሚቀርባትና የሚጠጋጋት ወዳጇ ነው፡፡ እናት አባትዋን ትታ የተጣበቅችበትና የተጣበቃት አጋሯ ነው ፣ እርሷም አጋሩ ናት፡፡ ታዲያ ራሷን በመስጠት ብትገዛለት ይበዛባታልን? እርሱስ ቢገዛላት ክብር አይሆንለትምን? ክርስቲያን ሚስቶች በፈቃዳቸውና በፍቅር ብቻ ሳይሆን በደስታ ሊያደርጉት ይገባቸዋል፡፡ ለትዳር ጓደኛቸው መልካምን የሚያደርጉ ሰዎች ምንም እንኳ የባሎቻቸው ወይም የሚስቶቻቸው ልብ የብረት ያህል የጠነከረ ቢመስልም በፍቅርና በደስታ በሚያደርጉት መሰጠትና መገዛት ያንን ሁሉ ሊያለሰልሱ ይችላሉ፡፡ አስቸጋሪና አመጸኛ የሆነውን ሰው ልብ ለመለወጥ በምድር ሕግ ከመግዛት ይልቅ በቤተሰብ ውስጥ የሚደረገው ፍቅርና ደግነት የተሻለ ተመራጭነት አለው፣ አላወቅንበትም እንጂ፡፡
2. ሰውነታቸውን በተገቢ ልብስ ይሸልማሉ፡፡
ሐዋሪያው ጴጥሮስም ከውጭ ማገጥ ይልቅ የተሰወረና የከበረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ ብሎ ባለትዳሮችን መከረ፡፡ የልብ ሰው መሆን ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው የሚመች እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ የውስጥ ሰውነታችንን ስለማማር ለእናንተ ጸጉርን ማሸረብ፣ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ፡ ይለናል፡
እግዚአብሔር ስለ አለባበሳችን ይገደዋል ወይ፣ እኛ የፈለግነውን ብንለብስ ምን ኃጢአት አለበት የሚሉ በርካታ ወገኖች እንዳሉ አልጠራጠርም፡፡ በእርግጥ ይህን አትልበስ ይህንን ደግሞ ልበስ የሚል የአዲስ ኪዳን ትምህርትም ሆነ ትዕዛዝ የለም፡፡ ሆኖም በተገቢ አለባበስ ራሳችንን እንድንሸልም ተመክረናል ፡፡
ሐዋሪያው ባገለገልበት ዘመን በዓለም ላይ ምግባረ ብልሹ፣ ሕይወታቸው በርኩሰትና በብልግና የተሞላ ሴሰኛ የሆኑ ሴቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሴቶች በአካላቸው ላይ የተለያዩ ምልክቶችን ከማድረጋቸውም በላይ የአለባበስ ሥርዓታቸውም ሁሉ ከክርስቲያን ሴቶች ሁኔታ በጣም የራቀና ለአእምሮ የማይመች ነበር፡፡ ከእነዚያ ሁኔታዎቻቸው አንዱ የጸጉር አሠራራቸው ነው፡፡ አሬማውያን ሴቶች ያንን ያደርጉት የነበረው በውጭ ሰውነታቸው ብቻ በማማር የውስጣቸውን ባዶነት የሚሞሉ ስለመሰላቸው ነው፡፡ አሬማውያን ሴሰኛ ሴቶች የውጭ ሰውነታቸውን ለመሸለም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያፈስሱት ለትዳር ጓደኛቸው፣ ለልጆቻቸው ወይም ለአጠቃላይ ትዳራቸው የሚሉት፣ የሚቆረቆሩለት የወይም የሚገዳቸው ነገር አልነበራቸውም፡፡ የቤተሰብ ሃላፊነት ስሜትም ስለማይሰማቸው የሚያገኙትን ገንዘብ በሽሩባና በወርቅ ያጠፉት ነበር ክርስቲያኖች ሴቶችም ከእነርሱ በመኮረጅ ልክ ዓለማያን ሴቶች እንደሚያደርጉት ዓይነት ሽሩባ መሠራትና የእነርሱን ዓይነት ልብስ መጎናጸፍ ቢሞክሩ ደግሞ በኑሮአቸው ማባከንንና በትዳራቸውም አለመስማማትን ሊፈጠር ይችላል፡፡፡፡ እነርሱ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው የቤተሰብ ኃላፊነት ስለነበራቸው ከአሬማውያን ሴቶች ይለያሉ፡፡ ከባሎቻቸው ጋር በፍቅር ገመድ የታሠሩ በመሆናቸው ውበታቸው ለባሎቻቸው ነው፡፡ ብዙን ጊዜ የትዳር ጓደኛችንን በምን እናስደስተው ወይም በምን እናስደስታት ለሚለው የብዙዎች መልስ የሚሆነው ልብስ በመግዛት ልዩ ልዩ ስጦታዎችን በማበርከት ወዘተ ነው፡፡ ይህ አባባል እውነት ነው ግን የትኛውም ስጦታና ምግብ ፍቅርን አይተካም፡፡ ሰው የሚፈልገው ምግብና ጨርቅ ሳይሆን ፍቅር ነው፡፡ ሐዋሪያው ሦስት ዓይነት የውጭ ማጋገጫ መንገዶችን ይከለክላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ጸጉርን መሸረብ ሲሆን ሁለተኛው ወርቅን ማንጠልጠል ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ልብስን መጎናጸፍ ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን ስንመለከት መልበስን፣ የወርቅ ጌጥን ፣ ጸጉርን መታጠብና ማማርን እግዚአብሔር አይቀበልም እያለ ነውን; ወይም ደግሞ ወርቅ ማድረግና በልብስ መሸለም ነውር ነው እያለ፣ ጸጉርን መሽረብን እየከለከለ፣ ኃጢአት ነውና ወርቅን አታድርጉ የወርቅንም ጉትቻ ከእናንተ አርቁ እያለ ነውን; በፍጹም አይደለም፡፡ ነገር ግን ወርቅን ማንጠጥልጠል አይሁንባችሁ የሚለው የሐዋሪያ ምክር ክርስቲያን ባለትዳሮች ውጭአቸውን ከልክ በላይ ሊያደምቅ በሚችል ልብስ ራሳቸውን ለመሸለም ሲሉ የሚያደርጉት ጥድፊያ ለመንፈሳዊ ነገር ደንታ ቢሶች እንዳያደርጋቸው የሚያሳስብ ምክር እንጂ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የነበሩ የጥንት ሰዎችን ስንመለከት እነ ርብቃና አስቴርን የመሰሉ የእምነት ሰዎች ከወርቅ በተዘጋጀው ጌጣጌጥ ተውበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ አመንዝራዎች ሴቶችና ጋለሞታዎች ውድ በሆነ ዋጋ ወርቅን በመግዛት ራሳቸውን መሸለምን ምልክታቸውና መታወቂያቸው አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ እግዚአብሔርንም እንዳያመልኩ እንቅፋት ሆኖባቸው ነበር፡፡ የምንምበላው የምንጠጣውና የምንለብሰውና እንዲሁም የምናጠለጥለው ጌጥ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም፡፡ የእምነትን ኑሮ ስንኖር ፣ ብንበላም ብንጠጣም፣ ብንብስብም ሆን ወርቅን ብናጠለጥል ለመንፈሳዊ ህይወታችን ትልቅ ትኩረትና ጥንቀቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ከጌታ ከኢየሱስ ጋር ያለንን መንፈሰዊ ትሥሥራችንን የሚያበላሽብንን ማንኛንም የውጭ ማማር ልንንቀው ያስፈልጋል፡፡ በተጨማርም የምንለብሰው ልብስ፣ የምንሠራው ሽሩባና የምናንጠለጥለው ወርቅ ለትዳር ጓደኛችንና ለልጆቻችን ወይም ለቤተሰባችን ያለንን ፍቅርና ኃላፊነት ካበላሸብን አደጋ መጣብን እንበል፡፡ ክርስቲያን እሕቶቻችን በሁሉም በኩል የቅድስና ኑሮን እንዲታይባቸው እግዚአብሔር ይፈልጋል፡፡ እንደ ክርስቲያን ሴት እኔ ምን ዓይነት ወርቅ ማድረግ ይገባኛል፣ ምን ዓይነትስ ሽሩባ ልሠራ ይገባኛል፣ ለቤተሰቤም ፣ ለእኔም ፣ እንዲሁም ለትዳር አጋሬ ደስ የሚያሰኘን ምን ዓይነት ልብስ ብለብስ ነው ማለት አስተዋይነትም ክርስቲያናዊ ጨዋነትም ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆን ልብስ እንዳለ ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር የማይሆኑ ብዙ ልብሶች እንዳሉ አይኖች ይመልከቱ፡፡ የሚያዩትን ሌሎች ሰዎችን የሚማርኩ ልብሶች እንዳሉ ሁሉ ሰዎችን ለአላስፈላጊ ፈተና የሚያጋልጡ አለባበሶች እንዳሉ ያልተገነዘበ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ደስ ያለንን ብቻ ሳይሆን ልክ የሆነውን ልንለብስና ልናደርግ እንደሚገባን ሁላችንም የምንስማማ ይመስለኛል፡፡ እንመለስበታለን !
No comments:
Post a Comment