Thursday, February 9, 2017

ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ ባትሳተፍስ?

ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ ባትሳተፍስ?
ከመጋቢ ሳሙኤል ሾንጋ

 የፖለቲካ ጉዳይ ከነባሕሪዩ አስቸጋሪ፣ ለመተንተን አደጋች፣  በተለይም እንደ እኔ ላለ ፖለቲካ ላልቀመሰ ሰው ደግሞ የባሰ አደናጋሪ ነው፡፡ ለነገሩ ምሁራኑም ቢሆን ፖለቲካን እንደ ቀላል አያዩትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ መሳተፍ የለባትም እያልን ከጎኑ ደግሞ ባለመሳተፏ የሚመጣባት  የጎንዮሽ ጉዳት ሳያስጨንቀን አልቀረም፡፡ በፖለቲካ ካለመሳተፍና ከመሳተፍ መቼም ቢሆን ከሁለት አንዱ የተሻለ መሆኑ ግድ ነው፡፡ ለማንኛውም ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው ባትሳተፍ የምትቸገርባቸው አቅጣጫዎች እነሆ
1.          አገዛዙ ዓለማዊ መሆን፡
ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው ባትሳተፍ የፖለቲካውና የመንግሥት አመራር ሙሉ በሙሉ በዓለማውያን እጅ ይገባል፡፡ የመንግሥትን አመራር እግዚአብሔርን የማያውቁ፣ ፈርሃ እግዚአብሔር የሌላቸው ሰዎች ከተቆጣጠሩት  በምድር ላይ የከፋ አመጽ ይከተላል፡፡ ቤተ ክርስቲያንና አማኞች ከለሉበት የአገር ፓርላማ ያለአንዳች ተከላካይ ቢያንስ የልዩነት አሳብ የሚያቀርብ እንኳ ሳይኖር  በሙሉ ኃይሉና አቅሙ ለቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ እንቅፋት የሚሆን ውሳኔ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ አማኞችም እንደ አናሳ ቡድን (Minority group) ስለሚታሰቡ አስፍተው መራመድ ፣ በአደባባይ መናገር፣ ሁሉ እየቀረ ይመጣል ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፓርላማ በርከት ያሉ ጠንካራ አማኞች ስላልነበሩና ቤተክርስቲያን በዚያ ቦታ በብቃት መሳተፍ ባለመቻሏ የወታደራዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ስለተቆጣጠረው ፓርላማው የሚያወጣው አዋጅና መመሪያ ጸረ እግዚአብሔር፣ ፀረ -ክርስትና ሆኖ ለ17 ዓመት ዘለቀ፡፡  በዚያን ወቅት ጥቂት ክርስቲያኖች መንቀሳቀሳ ሲጀምሩ ብዙም ሳይራመዱ ወጥመድ ይበዛባቸው ጀመረ፡፡ በቤተ ክርስቲያንም አጠቃላይ እንቅቃሴና እምነት ላይ አደጋዎች እየተበራከቱ መጡ፡፡ ያነ ግን አማኞች( ፍርሃ እግዚአብሔርና የክርስትና ልብ ያላቸውን ማለቴ ነው) በርከት ብለው በፓርላማውና በመንግስት ምክር ቤት ተገኝተው ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ ጥፋት አቅም ባላገኘና በእዚያ የነበሩ ጥቂት ወገኖችም አፍ ባላጡ ነበር፡፡ የአሥራ ሰባት ዓመቱ የኮሚዩኑዝም ሥርዓት በአገራችን አደባባዮች እግዚአብሔርንም አምላኪዎቹንም ባለ በሌለ ኃይሉ ይዳሰብ የነበረው  ፖለቲካው ሙሉ በሙሉ  በከሃዲዎች እጅ ስለገባ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የአሁኑዋም ቤተ ክርስቲያን ከዚያ ልምድ በመውሰድ በተለይም ከአሁን በኋላ በሚመጡ መንግሥታትና በዘመናቸው የባለፈው ዓይነት ቀውስ እንዳይከሰት ራሷን ማዘጋጀት ይኖርባታል፡፡
2.   የመብት መገደብ፡
አማኞች ወይም ቤተ ክርስቲያን ከፖለቲካው ከራቁ  የቤተ ክርስቲያን እና የክርስትና መብት ይገደባል፡፡ የማምለክ መብት፣ ወንጌልን በአደባባይ የመስበክ መብት፣ ነጻነታችን ሁሉ ይገደባል፡፡ በግል ክርስቶስን መከተል ባይከለከልም እንደ ቤተክርስቲያን በጋራ አዳራሽ ሞልተን አደባባይ አጣብበን ማምለክ፣ መዘመርና ማእለል ሁሉ ይገደባል፡፡ ቤተ ክርስቲያንና ሚኒስትሪ መክፈት፣ በየቀበለው ከፍተኛ የድምፅ ማጉያ  ተክለን ስብከታችንንም ሆነ ምስጥራዊ ሊሆኑ የሚገባቸውን ጸሎቶቻችንን ሁሉ ጭምር ለአቅራቢያው እስክናሰማ ድረስ የምናደርገው አካሄድ እያጠረ ፣ ቀስ በቀስ አንዳንዴ በፍጥነትም ሁሉም እየተሰፈረ መሰጠት ይጀምራል፡፡ የአምልኮ ቦታ በሕጋዊ መንገድ የመጠየቅ መብት እንደበፊቱ በነጻነት አይሆንም፣ ገመዱ እያጠረ ይሄዳል፡፡ አሁን አስፍተን የምያናቸውን ሁሉ በቀዳዳ በኩል  በአንድ ዓይን እንድናያቸው የሚያደርግ ጫና ሊደረብን ይችላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት በሓይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለውን መርህ  አየት ማድረጉ አይከፋም፡፡ ይህ ለብዙዎቻችን በጣም ተራማጅና መልካም አሳብ ይመስለናል፡፡ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን እንደዚህ አድርገሽ ስበኪ ወይም አስተምሪ ፣ የጸሎትሽም ይዘት እንደዚህ ይሁን እንጂ ሌላ አልፈልግም እያለ ማድረግ ያለባትን እየመዘነ አይሰጥም ማለት ብቻ ይመስለናል፡፡ ግን ከዚያም ያለፈ ጣጣም አለው፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት ተለያዩ ማለት ማንም ሰው የፈለገውን እምነት የመከተል መብት እንዲኖረውና ቤተ እምነቶችም በሚከተሉአቸው የእምነት አቋማቸው ላይ መንግሥት እጁን አያስገባም ማለት ቢሆንም በአንጻሩ ደግሞ  ማንም ሌላውን ሰው ይህንን እምነት ተከተል ይህንን ደግሞ አትከተል ማለት  እንደማይችልም የሚደነግግም ነው፡፡ በሌላ አባባል ወንጌል በመስበክ የሰዎችን ሃይማኖት ማስቀየር ሊያስከስስ ይችላል እንደማለትም ነው፡፡ ኢየሱስ ያድናለና ጌታን ተቀበል ማለት ሊያስወነጅል የሚችል ይሆና እደማለት ነው፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነትን ፍልስፍና ከመጀመሪያውም የጠነሰሱት  የአሜሪካን የመብት አንቀጽ አርቃቂ የነበሩ እንደ ጃምስ ማዲሴን ያሉ ሲሆኑ አሳባቸው ቤተ ክርስቲያን ወይም ሃይማኖት ከማህበረሰቡ ሥልጣን ውጭ ብትሆንም የአንድ አገር ሕጋዊ ሥልጣን እንደሚመለከታት አልሸሸጉም፡፡ እንደ ማዲሴን አባባል መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት ሁለቱም በሚያደርጉት ውሳኔ የሌላ እጅ ጣልቃ የማይገባበትና የመንግሥትም ሆነ የሃይማኖት ንጽሕና እንዲጠበቅ ያስችላል፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያቶች ተተችቶበት ለ25 ጊዜ ያህል ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነው ውሳኔን ያገኘው፡፡  መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገባም የሚለውን መርሀ ቃል በራሳቸው መንገድ የተረጎሙ እንደ ሞርሞን፣የይሖዋ ምስክሮች፣አሚሾችና ሌሎች የመሳሰሉትም ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 18፡36 ላይ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፣ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ቢሆን ኖሮ ሠራዊቶቼ ይዋጉልኝ ነበረ” ያለውን አሳብ አክለውበት የእኛ መንግሥት ከዚህ ዓለም ስላይደለ የዚህ ምድር መንግሥት በሚያደርገው ሁሉ አንሳተፍም የሚል አቋም ያዙ፡፡ ይህ ማለት መንግሥትን አንደግፍም፣ አገርን አንከላከልም፣ ግብር አንከፍልም ወዘተ የሚል ጥግ ይዘው ተገኙ ማለት ነው፡፡  ነገር ግን የካቶሊክ ቤተ ክርሰቲያን ማንም ሰው እንደፈለገው የሃይማኖት ነጻነት ሊኖረው ይገባል ግን ያ የሃይማኖት ነጻነት በአገሪቱ ሕገ መንግሥት እውቅናን ማግኘት ይኖርበታል የሚል አቋም ያዙ፡፡ ከዚህም ጋራ በመጨመር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ስለማይዋጥላት  መንግስት የሚወስዳቸው ውሳኔዎች ሚዛን እንዲጠብቁ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው በቂ ሚና መጫወት ይኖርባታል የሚለውን መርህ አጠንክራ ያዘች፡፡ የሆነ ሆኖ መንግሥትና ሃይማኖት የመለያየታቸው ጉዳይ የፍርድ ቤት ውሳኔ ካገኘ በኋላ ክርስቲያኖች ከአምልኮ ሥፍራ ውጪ የሚያደርጉአቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ገደብ ይበጅላቸው ጀመር፡፡ በመንግሥት ትምህርት ቤቶችና በሠራተኞች መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ የተሰቀሉ አሥርቱ ትዕዛዛትን የያዙ ጽሑፎች እንዲወርዱ ተጠየቀ፣ወረዱም፡፡ በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የሚደረገው ጸሎት እንዲቀር ተጠየቀ፣ ቀረም፡፡ በየትኛው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክፍል ውስጥ የቡድን መጽኸፍ ቅዱስ ጥናት እንዳይደረግ፣ በግል ትምህርት ቤቶችም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ነክ ትምህርት እንዳይሰጥ ክልከላ እየተደረገ መጣ ፡፡ በአገራችንም መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም እና በቤተክርስቲያን ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለተማሪዎች መንፈሳዊ ትምህርት ማድረግ ፣ ወንጌልን መስበክ፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አንድ ትምህርት መስጠት የማይቻል እየሆነ መጣ፡፡ ይህም በመሆኑ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም የሚለው መርህ ቤተ ክርሰቲያን መንግሥት በሚያደርገው ጥፋት ድምጽ እንዳታሰማ ሊከለክል የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባምና፡፡    
3.   ፍትህ መጉደል፡
አማኞች እና ቤተ ክርስቲያን አማኝ ባልሆኑና በሌሎች ድርጅቶ የታቀደ ጥቃት ሊደርስባቸው ሰሚ ዳኛ ሊያጡ ይችላሉ፡፡ በተለይም የመንግሥት ባለሥልጣናት ክርስትናን የሚቃወሙና የሚጠሉ ከሆነ በየሰበቡ ክርስቲያኖች ይጠቃሉ፡፡ ከቀበሌ እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሉ የሥልጣን እርከኖችና መምሪያዎች አማኞች የሉም ማለት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሁኔታዎች ከበድ ያለ መሆኑን ያሳያል፡፡ የቀበሌ ሊቀመንበር፣ የወረዳው ባለሥልጣናት፣ የፖሊስ አዘዦች፣ የማዘጋጃ ቤት ሹሞችና የመምሪያ ኃላፊች( DEPERETMENTS HEADS ) የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ፣ ሚኒስትሮች ፣ ዴኤታዎች ፣ ከስራቸውም ያሉ የመምሪያ ኃላፊዎች እግዚአብሔርን የማይፈሩና የቤተ ክርስቲያንን መኖር የማይፈልጉ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስባትን ጥቃት ለመቃወምና መብቷን ለማስከበር አቤት የምትልበት ሥፍራ ታጣለች፡፡  የተቀበረውን ሬሳ ከጉድጓድ አውጥተው ሜዳ ላይ ሲጥሉ ወይም እንጨት ላይ ሲያንጠለጥሉ የሟች ቤተሰብ  የሚደርስበትን በደል ለማን እንደሚናገር መላ የሚጠፋው አስተዳደሩ ፀረ ክርስትና  ሲሆን ነው፡፡ የድርጊቱ ተዋኒያንን የሚሸፍን መሪ ባለስልጣን ባለበት አካባቢ ይህ ሲሆን አይተናል፣ ይኸውም ዴሞክራሲ አለ በሚባል አገር!  ባለፈው ሳምንት በናይጄሪያ አምላካቸውን እያመለኩ ባሉ ክርስቲያኖች ላይ ሌላ እምነት  ተከታዮች ከፍተኛ ጥቃት አደረሱ፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ የነበሩ የቅዱሳንን  መኪናዎች አንድ በአንድ በእሳት ካያያዙት በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ዘልቀው በመግባት አማኞች መደብደብና መግደል ጀመሩ፡፡ ያ የሆነበት ምክንያት ሴሌጃ በሚባል በዚያ ግዛት ውስጥ ከሙስሊሞች በስተቀር ሌላ እምነት፣ ከዓርብ በቀር ሌላ የአምልኮ ቀን መኖር የለበትም በሚል ነው፡፡ ይህ ሲሆን ክርስቲያኖች የጸጥታ አካል ወደሆነው ክፍል ቢደውል ፖሊስ የተላከው ሁሉም ነገር ከወደመ በኋላ ነበር፡፡ የናይጄሪያው ክርስቲያን ህብረት ዋና ዳይሬክተር ቄስ ሙሳ አስኬ የመንግሥትን ቸልተኝነት አስመልክተው ሲናገሩ : “መንግሥት ራሱ ክርስቲያኖችን ከዚህ አገር ለማጥፋት ይፈልጋል፡፡ ለሌሎች ሃይማኖቶች ያደላል፡፡ እኛ በዚህ አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንታያለን፡፡ በዚህ አገር ያሉ የጸጥታና የዋስትና ኤጄንቶች ሁሉ በሰሜኑ ሰዎች እጅ ሥር ናቸው፣ በሰሜን የአገሪቱ ክፍሎችስ ክርስቲያኖች የሉንምን ? አሁን ክርስቲያኖች ተገልለናል ግፍም እየደረሰብን ነው፡፡ እኛ ጥቃት እየሰድረብን እያለ መንግስት ለሌሎች ሃይማኖቶች ስለሚያደላ እኛ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረናል፣ ግድ የለም አምላካችን ግን አልተኛም” በማለት ሆድ የሚያብስ ነገር ተናገረ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በክረምት ወር 1984 ዓ.ም በአዲሰ አባባ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ኮንፍራንስ ላይ ዶር አዲዬሞ ቱኩንቦ የተናገረውም ይህንን የሚመስል ነገር ነው፡፡ ዶር ቱኩምቦ ቤተ ክርስቲያን በናይጄሪያ በየጊዜው የሚደርስባትን ጥቃት አስመልክቶ ሰፊ ምስክርነት ከሰጡ በኋላ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች ያሉ ክርስቲያኖች ከሌሎች ጥቃት ሲደርስባቸው መንግሥት ዋስትና ካልሰጠ ራሳቸውን ለማዳን ድምጻቸውን ማሰማት መቻል አለባቸው ይል ነበር፡፡ ካቀረባቸው መብትሔ አሳቦች አንዱ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የሚል ይገኝበታል፡፡ ይህ እንግዲህ ከ25 ዓመት በፊት ነው፡፡ ዶር ቱኩምቦ እንደተናገሩት አስቀድመው ክርስቲያኖች በእጃቸውን ያለውን ሥልጣንና መብት ቸል በማለታቸው  ሌሎች ስለተጠቀሙበት ያ ሁሉ ችግር ደረሰባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያኖችም ፖለቲካን በሩቁ ካሉና ምንም እንቅስቃሴ ካላደረጉ በቆይታ ወይ ከመንግሥት ወይ ከሀይማኖት አካላት ተመሳሳይ ችግር ሊደርስባት ይችላል፡፡ ክርስቲያኖች በፖለቲካው ጉዳይ ቸል ካሉ በእነርሱ ላይ ጥቃት ሲደርስባቸው ቸል የሚል መንግስት በአገር ላይ እንዲሾም እየፈቀዱ ናቸው፡፡
እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ መሳተፍ የለባትም በፖለቲካ ባትሳተፍም ችግር ይገጥማታል ካልን የቱጋ እንሆናለን የትኛው ነው የሚያስፈልጋት የሚለውን መፍታት ይኖርብናል፡፡ 
ከአገርና ከፖለቲካ ውጥረቱ አንጸር ቤተ ክርሰቲያን ምን ታድርግ;
 እስከ አሁን ቤተ ክርሰቲያን በፖለቲካ መሳተፍ አለባት የለባትም በሚለው አሳብ ላይ ብዙ ስናወጋ እዚህ ደርሰናል፡፡ እኔ በበኩሌ ቤተ ክርስቲያናችን በፖለቲካ ከመሳተፍዋ በፊት ተሰጣትን ሥራ ትጨርስ እንጂ ፖለቲካ ውስጥ ካልገባች ብለን ያልተሰጣትን እንድትሠራ አናስገድዳት እያልኩ ቆየሁ፡፡ አሁንም እንደዚያው ነኝ፡፡ በፖለቲካው ባትሳተፍ ግን የሚገጥማት ተግዳሮት መኖሩንም ደግሞ እንደ አቅሜ አስቀምጫለሁ፡፡ ይህንን ስል  ቤተ ክርስቲያን በአገር ጉዳይ ምንም አያገባትም እያልኩ እንዳልሆነ አስምሬበት አልፌአለሁ፡፡ በዛሬው ጽሑፌ የማሳየው ቤተ ክርሰቲያን እንደ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው ተሳታፊ ሆና፣ ወንበርም ተዘጋጅቶላት በፓርላማ ስተቀመጥ ብናይ ሞቅ ሊለን ይችል ይሆናል ፣ ግን ያ ብቻውን የሚሰጠን ረብ ሊኖረው አይችልም፡፡   ሁላችንም እንደምናምነው ቤተ ክርስቲያን የአገር ፍቅር ፣ የአገር ኃላፊነት፣ የሕዝቦች ሸክም ሊሰማት ይገባታል፡፡ በተለይም ደግሞ የወንጌላውያን አማኞች ያለ ምንም ልዩነት የዓለምን ሕዝቦች መውደድ ይኖርባቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስተምረው  በማድረግ የሕዝቦችን ችግር ማቅለል የምትችለው ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ እኛ በርዕሰ ጉዳያችን የምንናገረው ስለ ፖለቲካው ስለሆነ ነው እንጂ የቤተክርስቲያን ኃላፊነት በሁሉም አንጸር ነው፡፡  መንግሥት ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን ቢልም ዝናብ ሲጠፋ ፣ ሰዎችና እንስሳት ከውሃ እጥረት የተነሳ ሲያልቁ ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር እናደርጋለን የሚለው ሁሉ ፉከራ ሳይሥራ ቀርቶ  አይተናል፡፡ ታዲያ ቤተ ክርስቲያን ምን ታድርግ ለሚለው የሚታየኝ ከዚህ በታች ባሉ አምስት አቅጣጫዎች Aspects  ማትኮር ይገባታል ባይ ነኝ፡፡ ከዚየ ቦኃላ ራሷ በቀጥታም ሆነ በተዘዋሪ መንገድ አባላት እንዲሳተፉ በማዘጋት ኃላፊነቷን መወጣት ትችላለች፡፡ ቤተ ክርሰቲያን በፖለቲካ ከምትሳተፍ አማኞች እንደ ግለሰብ ቢሳተፉና ጠንክረው ቢታገሉ የተሻለ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያ እንደ ድርጅት ሰትካፈልና አማኞች ሲሳተፉት አንድ አይደለም፡፡ ልዩነቱን መተንተን የሚያስፈልው አይመስለኝም ግን ከአምስቱ አቅጣጫዎች ለዛሬ ሦስቱ እነሆ፡

1.      መንፈሳዊ አቅጣጫዎች Spiritual Aspects :

ቤተ ክርስቲያን መንግሥትን  ወይም ደግሞ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እንድትቋቋመው የሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ አስቀድመው የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ማሰብ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ፡፡  ጌታ እግዚአብሔር ፣ ኃያሉ አምላክ በልጁ ደም የዋጃት ቤተክርቲያኑ ክብርትና ንጽሕት እንዲትሆን ይፈልጋል፡፡ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ክርስቶስን የምትገልጽ የእርሱ አምባሳደር እንድትሆን ይጠበቅባታል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያን የማንነቷ ጉዳይ ፣ ከምንም ጋር የማታወዳድረው ሀብቷ የምንጊዜም መታወቂያዋ ነው፡፡ ሞገስዋና ጉልበቷ (መንፈሳዊ አቅሟ ማለቴ እንደሆነ ይሰመርልኝ) ያለው እዚህ ውስጥ ነው፡፡ በምድር ላይ ያለቺው ቤተ ክርስቲያ የቱንም ያህል መንግሥትን ብትቃውም ወይም ብትደግፍ ክብሯንና ንጽሕናዋን ፣ የተፈጠረችብትንም ማንነት የጣለችና ያጣች እንደሆነ በምታደርገው ሁሉ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከሚያደርገው በላይ የከበደ ነገር ሊኖራት አይችልም፡፡ ሐዋሪያት የኢየሩሳሌምን ከተማ እና በአካባቢው ያለውን ግዛት ያነቃነቁት መንፈሳዊ ማንነታቸውን ጠብቀው ስለቆሙ ነው፡፡ ከአሁኑዋም ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት አምላካዊ ተልእኮ አለ፡፡ ያውም ወንጌልን ለሰው ልጆች ሁሉ መስበክ፣ ያመኑትን ደቀ መዛሙርት ማድረግ፣ እግዚአብሔር በእውነትና በመንፈስ እንዲመለክ ቅዱሳን ማነሳሳትና ማገዝ ነው፡፡ የምድሩም ጉዳይ ስለሚያገባት አጥብቃ መጸለይ የተሰጣት ተልዕኮ መሆኑን ብሉይም ሆነ አዲስ ኪዳናት የሚያስስቧት ነው( 2ዜና 7፡14፣ 1 ጢሞቴዎስ 2፡1-5)፡፡ መንግሥት ጨካኝና አሬሜአዊ እንኳ ቢሆን የተሰጣት ሃላፊነት መጸለይ ነው፡፡  ሐዋሪያው ጳውሎስ ልመናና ጸሎት ምልጃና  ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትም ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረግ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ ሲል ነገሥታትና መኳንንት እኮ እንደነ ኔሮ ያሉ ጨካኞችና አብረው ያሉት አይደሉምን? ናቸው እንጂ! በጸሎትና በጸሎት ኃይል እናምናለን እያልን የመንግሥት አቋም አልዋጥ ብሎን በሚጎመዝዘን ሰዓት የተቃውሞ ሰልፍ ማስተባበርና የአቋም መግለጫ ማውጣት ቤተ ክርስቲያን ከተሰጣት ተልዕኮ ጋር አይገጥምም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ከመስበክና ጸሎት ከማድረጉ ጎን ለራሷ ቅድስትና ንጽሐት መሆኗን ማረጋገጥ ይኖርባታል፡፡ ስለ ቅድስና መስበክ የሚያስፈራን ለምንድነው? እግዚአብሔርን ስለመፍራት ማስተማር እንደጦር የሚያስጋን ምን ብንሆን ነው? ነገራችን እየባሰበት መጥቶ  ፊቺ፣ ዘረኝነት፣ ስርቆት ፣ ዝሙት፣ አመንዝራነት እና የእርስ በርስ መካሰስ ዙፋናቸውን ዘርግተውብን የሚነካቸውም ሆነ የሚደረፍራቸው የታጠው ለምንድነው ማለት አያስፈልግምን? ከዚህ አንጸር ቤተ ክርሰቲያን ሥር ነቀል ተሀዲሶ የሚያስፈልጋት ናት እንጂ መንግሥትን ለመቃወም የሚያስችል ማንነትና መንፈሳዊ ሥልጣን አላት ማለት የሚቻል አይደለም፡፡ እኔ መንግሥትን የሚሾመው እግዚአብሔር እንደሆነና ሰው ሁሉ ለተሸመው ሥልጣን ማስገዛት እንዳበት( ሮሜ 13፡1-) አምናለሁ፡፡ ስልጣን ስንል የመንግሥት ሥልጣን ብቻ ሳይሆን የቤተሰብንም የቤተ ክርስቲያንንም፣ የድርጅትንም ሥልጣን ሁሉ የሚያካትት እንደሆነ መካድ አልፈልግም፡፡ መንግሥት ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ሥልጣን ያለቦታው ሲጠቀምና በሕዝብ ላይ በደል ሲያደርስ ቤተ ክርስቲያን የእኔ ሥራ መጸለይና መስበክ ነውና በሚል በሯን ዘግታ፣ ጭንቅላቷንም አሸዋ ውስጥ ቀብራ አላየሁም፣ አልሰማሁም  ትበል የሚል አቋም የለኝም፡፡ የጨለማውን ሥራ ሁሉ መግለጥ፣ አፍ ላጡ አፍ፣ ድምጽ ላጡ ድምጽ መሆን ይጠበቅባታል፡፡ ያንን ከማድረግ በፊት አስቀድማ ግን የጣለቸውን ማንሳት፣ የለበሰቺውን ድሪቶ ማውለቅ፣ ቤቷንና ጓዳዋን ከቆሻሻ ማጽዳት ይኖርባታል፡፡  እንደገና ጌታንና ከእግዚአብሔር የሚሰጣትን መንፈሳዊና መለኮታዊ ሥልጣን መልበስ ይኖርባታል፡፡ ያኔ መንግሥትም በውስጧ ለተቀመጠው ሥልጣን ቀኝ እጁን ይሰጣል ባይሰጥ ከቤተ ክርሰቲያን ጋር ያለውን የእግዚአብሔርን መኖር ይለማመደዋል ማለት ነው፡፡ 
     
2.     ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫ Economical Aspect

 ገንዘብ የማይገባበት ሥፍራ የለም፡፡ ስልጣንና ገንዘብ አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ስለ ገንዘብ ያላት አመለካከት ራሱ በብዙ አንጻር  ተሃዲሶ የሚያስፈልገው ነው፡፡ አንዳንዶች በባሕታዊነት የሚያምኑ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የብልጽግና ወንጌልን መስበክ ያስደስታቸዋል፡፡ ባህታዊነትና የገዳምን ሕይወት የሚያምኑ አገልጋዮቻቸው ገና ወደ ገዳም ሳይገቡ የባህታዊነትን ሕይወት እንዲኖሩ የሚፈልጉ፣ ያንኑንም የጽድቅ መንገድ አድርገው የሚወስዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሳገለግል ከጓደኛዬ ጋር ምሳ ከበላን በኋላ በአንድ ካፍቴሪያ ሻይ እየጠጣን ሳለ ኬክም አዝዘን ስንበላ እግር ጥሎአቸው ወደነበርንበት ካፍቴሪያ የመጡ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ተቆጡን ፣ ወንጌላውያን ሆናችሁ እንዴት ኬክ ትበላላችሁ በሚል፡፡ እውነት ለመናገር እኛ በጊዜው ኬክ ምንበላው በሁለት ወር አንዴ ያውም አንዱን ኬክ ለሁለት ነበር( አጋጭተን ማለት ነው)፡፡ ያንኑንም ባንበላ ኬክ ቀርቶብን እንደምንጎዳ አንቆጥርም ነበር፡፡  ጊዜያትን ቆጥረን ለሁለት አጋጭተን በበላንባት ቀንም ቢሆን እኒያ አባታችን ወደዚያ ካፍተሪያ ገቡና አዩብን፡፡ ሲቆጡ እውነት አድርገን አልወሰድንም፣ የሚቀልዱ መስሎን እኛም ሳቅ ሳቅ ማለታችን በበለጠ አስቆጣቸው፡፡ የምራቸው መሆኑ ሲገባን ስሜታችን ልውጥውጥ ስልብን ጊዜ ክርስትናችን እንዳይከዳን ብለን እንደምንም ያቺን ደቂቃ ችልን ማለፋችንን አስታውሳለሁ፡፡ ወንጌላዊ ኬክ መብላት መሪውን እስክያስቆጣ ድረስ ወንጀል የሆነበት ምክንያት እስከ አሁንም አልገባኝም፣ ሊገባኝም አይችልም፡፡ በእሳቸውና በብጤዎቻቸው አስተያየት ኬክ መብላት ለወንጌላዊ የተከለከለ፣ የበላ እንደሆነ  በኃጢአት እንደሚወድቅ ፣ እሳቸው ልጆቻቸውና ሌሎች አይደለም ኬክ ሌላም አልፈው ቢበሉ ግን የፈቀደ ነው፡፡ ለማንኛውም ቤተ ክርስቲያን ስለ ባሕታዊነትም ሆነ ስለ ብልጽግና ብትሰብክ ስለ ገንዘብ ያላት አቋሟ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስለ ገንዘብ የምትሰብከው ምዕመናን አሥራታቸውን በጊዜ እንዲሰጡ፣ ለሕንጻ ግንባታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ጊዜ ዳጎስ ያለ ገንዘብ፣ ወርቅና  ሌላም ንብረት በመስጠት ውድድር እንዲሽቀዳደሙ ነው፡፡ የስብከቱም ርዕስ ስጡ ይሰጣችኃል፣ ስጡ ትባረካላችሁ ወዘተ ነው፡፡ በገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ሊሰብኩ መጥተው የእኔ ሥራ በየሄድኩበት ኪስ ማስወለቅ ነው ብለው ያለምንም እፍረት የሚናሩ ሰባኪዎች አሉ፡፡ አሁን የምስተዋለው የቤተ ክርስያናት የገንዘብ አመለካከትና ገንዘብን የማግኛ ዓላማና መንገድ ከላይ ካየናቸው እውነታ ብዙም የዘለሉ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ገንዘብ የሚለው ተዝቆ የማያልቅ ትምህርት አለ፡፡ ገንዘብን በጽድቅ ስለ ማግኘትና በጽድቅ ስለ ማውጣት፣ በገንዘብ ቤተ ክርስቲያንን ስለማገልገልና ስለ መስጠት ቃሉ በጥልቀት ያስተምራል፡፡ ገንዘብና አማኞች ሊኖራቸው ስለሚገባቸው መሠረታዊ እውነት ትልቅ ነገረ መለኮት ሊበጅለት ይችላል፡፡ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አባሎቻችን ንግዳቸው በትምህርትና በእውቀት የተደገፈ እንዲሆን በማሰልጠን በተሰማሩበት ሙያ እድገት እያሳዩ ለራሳቸውም ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለምድሩ በረከት እንዲሆኑ የማዘጋጀት ሥራ መሥራት የቤተ ክርስያን ኃላፊነት ነው፡፡ አማኞች የገንዘቡን ቁልፍ ቦታ እንዲይዙ፣ እንዲያድጉ፣ ከማጭበርበር ነጻ በሆነ መንገድ እየነገዱ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ተወዳዳሪነታቸውን ማሳየት እንዲችሉ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያን በእጇ ያሉትን ሰዎች በትጋት ማሰልጠን፣ ማስታጠቅ፣ በሀብታቸው እንዲያድጉ ማበረታታት ይኖርባታል፡፡ ስጡ ይሰጣችኋል፣ ትባረካላችሁ የሚለው ትምህርት ኪስ ለማውለቅ ብቻ የሚደረግ የመድረክ መታለያ ከመመስል ማለፍ ይኖርበታል፡፡ ፖለቲከኞች ገንዘብ ላላቸው እንደ ቅቤ ይቀልጣሉ አሊያም በሰበብ በአስባቡ ይጠፉአቸዋል፡፡ ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሀ አገር የፖለቲካው ጨዋታም ቢሆን የሚሰምረው ከገንዘብ ጋር ነው፡፡ ገንዘብ ከእውቀት በላይ ይጮሃል፣ ይሰማልም፡፡ ከመሸታ ቤት ወጥቶ ወደ ቤተ መንግሥት ሲገባ ፈቃድ አይጠይቅም ሰተት ብሎ በፓርላማ ይቀመጣል፡፡ ድምጹም ያስጋባል፡፡ ከዚያ ሲወጣ በሴትኛ አዳሪ ቤት አልፎ ወደ ቤተ መቅደስ ሲመጣ በእለቱ መርሀ ግብር ሴሌዳ ውስጥ ለብቻው ጊዜ ይመደብለታል፡፡ በሰማይ መንገድ እንዳለው ንጣፍ ዓለትን ያለ መሰርሰሪያ በስቶ የመግባት ችሎታ ባለቤት እንደሆነ የሚያምኑ ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከልጅ እስከ አዋቂ ፣ ከምሁር እስከ አላዋቂ፣ ከመምህር እስከ ተማሪ፣ ከካህን እስከ ምዕመን ፣ ከአገር መሪ እስከ ቤተሰብ አስተዳዳሪ ድረስ ለገንዘብ ያልተንበረከከ፣ በገንዘብም ያልተፈተነና ያልተሸነፈ አለ ማለት ያስታዝባል፣ ዋሾም ያደርጋል፡፡  ለገንዘብ ሲል ሲሉ ባልገባቸው ፖለቲካ ውስጥ የሚንደፋደፉ፣ አገር ለቀው የኮበለሉ፣ እምነታቸውን የለወጡ ፣ ነቢያት ሳይሆኑ ነቢያት ነን ያሉ፣ ሐዋሪት ሳይሆኑ ሐዋሪያት ነን ያሉ ከቁጥር በላይ ናቸው፡፡ ከፈለገ እንደ አምላክ ሰውን ይገዛል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ አለባት ካልን በአገሪቱ መዋዕለ ንዋይ ወይ ምጣኔ ሀብቱ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ አባላትን የሚታዘጋጅበት ስልት መቀየስ ይኖርባታል፡፡ ስጡ ትባረካላችሁ፣ ከምትለው ትምህርቷ ባለፈ ገንዘብን የማግኘት መንገዱ ይህ ነው፣ በዚህ መንገድ ሂዱና በልጽጉ፣እደጉ፣ ከዚያ ቤተሰባችሁን ፣ ቤተ ክርስያናችሁንና አገራችሁን አገልግሉ የሚለውን ትምህርት አጥብቃ ማስተማር ይኖርባታል፡፡ የነጋዴዎችና የባለሙያዎች አገልግሎት መደራጀት አለበት፡፡ አገልገሎቱም እንዲያድግ በባለሙያዎች አማካይነት ተከታታይ ትምህርትና ሥልጠና እየተሰጠ ነጋዴዎች በንግዳቸው ክህሎትም ተግባራዊነትም እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል፡፡ እግዚአብሔርም እንዲባርካቸው መጸለይ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው ዓለም ተጽእኖ ሊታመጣ አትችልም፡፡ መንግሥት ሙስናን እዋጋለሁ ሲል ቤተ ክርስቲያን  የጽድቅን አሠራር ይዛ ሥርቆት ኃጢአት ነው፣ ጉቦ ኃጢአት ነው፣ ማጭበርበር ኃጢአት ነው የምትልና ልሳኗ የሚሆኑ ንጹሐን ነጋዴችን ማሰማራት ከቻለች በፓርላማ ወንበር ባይኖራት እንኳ በፖለቲካው ለውጥ የሚያመጣ አንድ ርምጃ ፈቀቅ ብላለች ማለት ይቻላል፡፡ በገንዘብ ላይ ግልጽነትን ልማዷ መሆን አለበት፡፡ በየእሁዱ ሳምታዊ የገቢና የወጪ ሪፐርት በአጭሩ ለምዕመናን የሚያቀርቡ ቤተ ክርሰቲያናት ያሉ አይመስለኝም፡፡ ግን መለመድ ያበት ነው፡፡ በጥቅሉ ቤተ ክርሰቲያን በአገሪቱ ኢኮኖሚ ግንባታ ቀደም የሚሆኑ ሊኖሩ ይገባቸዋል፣ እርሷም በዘርፉ መሰለፍ ይኖርባታል፡፡ ይህ ከሆነ በፖለቲካው ላይ ለውጥ ማምጣት ትችላለች ባይ ነኝ፡፡ 
                
3.     የትምህርት አቅጣጫዎች Educational Aspect

ቤተ ክርቲያን በፖለቲካ ትሳተፍ የሚሉ ወገኖችን አልቃወማቸውም ግን መቼም ቢሆን ወደ ሥራ ሲገባ መሣሪያ ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ወደ ፖለቲካው ስትገባ ውጤታማ እንድትሆን የሚያደርጉ  መሣሪያዎች ( tools)ያስፈልጉአታል፡፡ ከመሣሪዎች አንዱ የትምህርት  ብቃት ነው፡፡ ፖለቲካ ራሱ እውቀትን የሚጠይቅ መሆኑ በማንም ሊካድ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ወንጌላውያ አብያተ ክርሰቲያናትን በተማሩ ሰዎች ባርኮአታል፡፡ ብዙ የህክምና ባለሙያዎችና የመረጃ ተክኖሎጂ አባላት አሉአት፡፡ ባለሙያዎቻችን አብዛኛዎቹ ሐኪሞች ወይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሮፌሴሮች ናቸው፡፡ ሚሲዮናውያን ከዋሉልን ዉለታዎች አንዱ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች የሕክምና ሙያ እንዲሰለጥኑ በማድረጋቸው ወላጆች ልጆቻቸውን የሕክምና ዶክተሮች  እንዲሆኑ ማበረታታት የባህል ያህል ቦታ ያለው ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ከሌላው ሙያ ጋር ሲነጻጸር ዶክተሮች ብዙ ናቸው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ፖለቲካ እንደ ኃጢአት ስለተወደሰ በፖለቲካ ትምህርት የተካኑ አባላት አሉ ማለት ያስቸግራል፡፡ ፖለቲካዊ ሳይንስ(political science ) የሚማሩ ክርስቲያን ተማሪዎች ምን ያህል ናቸው፡፡ የአመራር ትምህርት ( leadership)በከፍተኛ ዲግሪ የሚማሩ ለዚህም ዝንባሌ ያላቸው አባላት እና የአባላት ልጆች አሉን ወይ;፣አገራዊ( national)፣አህጉራዊና (continental) ዓለም አቀፋዊ( global) ሕግ ጠበብት አሉን ወይ; ካሉን ደግሞ  ቤተ ክርስቲያን በገንዘብም ቢሆን ደግፋ ከፍተኛ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የተንቀሳቀሰችበት አጋጣሚ አለ ወይ? የሚሉ መሰል ጥያቄች መልስ ማግኘት ያበት ይመስለኛል፡፡ የሥነ መለኮትን ትምህርት ( Theology) የሚማሩ አገልጋዮቿን ገንዘብ ከፍላ እንደምታስምር ሁሉ በፖለቲካና በሕግ እንዲሁም  አመራር አስተማማኝ አቅም ለመገንባት ገንዘቤተ ክርስቲያን  አውጥታ በመስኩ የሚማሩትን ሰዎች ማፍራት አለባት ባይ ነኝ ፡፡ ተሳሳትክ ትሉኝ ይሆን? የህክምና ባለሙያዎች በረከት ሆነውልናል፣ የሥነ መለኮት ተማሪዎችም የእግዚአብሔርን ቃል አስታጠቀውናል፡፡  ፖለቲካ ግን ሙያቸው ስላይደለ እነርሱን ከዚህ አንጻር  መጠበቅ የለብንም፡፡ ፖለቲከኛ መሆን ግን ሌላ ብቃትና ክህሎትን እውቀትንም የሚጠይቅ ስለሆነ በጉዳዩ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ሥነ መለኮት ተቋማት በእነዚህ ዘርፎች ሰዎችን ማሰልጠን ቢችሉስ ኃጢአቱ  እምኑ ላይ ነው? በአመራር በኩል የተጀመረ አስደሳች ነገር አለ፡፡ ወንጌላውያን አብያ ክርስቲያናት ተባብረው የፖለቲካ ትምህርት ከፍተው አባሎቻቸውን በከፍተኛ ዲግሪ ቢያሰለጥኑና የአገሪቱን ፖለቲካ እንዲመሩ የሚያስችል ክህሎት ቢያስታጥቁአቸው ራዕይ የጣሉ ያስመስልባቸው ይሆን? እኔ ግን ይህ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡  ክርስቲያን በፖለተካዊ ሳይንስ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የትምህርት ዘርፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ  አባላት እንዲኖሩአት መጸለይና መሥራት  ይኖርባታል፡፡ ያለዚያ ግን ወደ ፖሊቲካው ሜዳ ወጥታ ያለ በቂ መሣሪያ ወደ ጦር ሜዳ እንደሄደ ተዋጊ ሠራዊት ትሆናለች፡፡ 
ቤተክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ የሕበረተሰቡ አካል እንደመሆኑዋ መጠን ሕብረተሰቡን የሚለከት ነገር ሁሉ እርሷን ወደ ጎን ስለማይተዋት በህብረተሰቡ እልተእለት ጉዳዮች ላይ መግባት አለባት የሚል ሙግት በብዙ ይደመጣል፡፡ ሕብረተሰቡ ከሚጋፈጣቸው እለትተእለት ጉዳዮች አንዱ ፖለቲካና ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው፡፡  እኔ በበኩሌ ቤተ ክርስቲያን ሠርታ ልትጨርሰው የማትችለው በጣም ብዙ ሥራ ስላላት ያንኑን ትወጣው ፣ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተውላቸው እያልኩ ግን እንዲያው የግድ በፖለቲካ መሳተፍ አለባት ካልን መወሰድ ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጫለሁ፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው ውጤታማ እንዲትሆን ከፈለግን ተወዳዳሪነቷ ሊታሳይባቸው ከሚገባ ጠርዞች ሦስቱን ማለትም በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባት ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ትንታኔዬን ካቆምኩበት ልቀጥል፡፡ 
4
5.      የፖለቲካው አቅጣጫዎች Political Aspect

 ቤተክርስቲያን  የሕብረተሰቡ አካል እንደመሆኑዋ መጠን በህብረተሰቡ እለት ተእለት ጉዳዮች ላይ መግባት አለባት የሚል ሙግት በብዙ ይደመጣል፡፡ ሕብረተሰቡ ከሚጋፈጣቸው እለት ተእለት ጉዳዮች አንዱ ፖለቲካና ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው፡፡  እኔ በበኩሌ ቤተ ክርስቲያን ሠርታ ያልጨረሰቺው በጣም ብዙ ሥራ ስላላት ያንኑን ትወጣው ፣ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተውላቸው እያልኩ ግን እንዲያው የግድ በፖለቲካ መሳተፍ አለባት ካልን መወሰድ ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሳቤን አስቀምጫለሁ፡፡ እንደ እኔ  ቤተክርስቲያናችን መንግሥት ለምክርና ለጸሎት እስክፈልጋት ድረስ የከበደችና የተሞገሰች እንድትሆን እንናፍቃለን፡፡ መንግሥት  በከባባድ ጉዳዮቹ ላይ የቤተ ክርስቲያንን የጸሎት ርዳታ የሚሻበት እና በአገራዊ ጉዳይ መፍትሔ አመንጪና የችግሮችም ፈቺ እንደሆነች ተቀብሎ ራሱ ነይ ታስፈልጊናለሽ እያለ የሚያማክራት ቢሆን እንዴት በተደሰትን! ታላላቅ የአሜሪካን መሪዎች የተወደዱ አገልጋይ የሆኑ ዶር ቢሊ ግርሃምን እየጠሩ እንዲጸልዩላቸው ያደረጉበት ጊዜያቶች ብዙ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በጆርጅ ዴቭልዩ ቡሽ  ፕሬዝዳንታዊ በዓለ ስመቱን በጸሎት የመሩት ዶር ቢሊ ነበሩ፡፡ ቢሊ በአጭሩ እንደሚከተለው ጸልየው ፕሬዝዳንቱን ለሥራ አሠማሩ፡
 And now we come to a new era in our history. In Thy sovereignty Thou hast permitted George Bush to lead us at this momentous hour of our history for the next four years. As he today places his hand upon the Bible and solemnly swears before Thee to preserve, protect and defend the Constitution, give him the wisdom, integrity and courage to help this become a nation that is gentle and kind. Protect him from physical danger, and in the lonely moments of decision grant him Thy wisdom to know what is morally right and an uncompromising courage to do it. Give him a cool head and a warm heart. Give him a compassion for those in physical, moral and spiritual need. O God, we consecrate today George Herbert Walker Bush to the presidency of these United States with the assurance that from this hour on, as he and his family move into the White House, they will have the presence and power of the One who said, “I will never leave thee or forsake thee. [Hebrews 13:5(  የቢሊ ግርሃም ልጅ ፍራንክሊን ግርሃም ከጻፈው የኢሜይል መልእክት የተወሰደ)፡፡

 የኢትዮጵያ መንግሥትም ፕሬዝዳንቱንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲሰይም እጃቸውን ጭነው ተሽዋሚውንና አገሩን በጸሎት ለእግዚአብሔር አሳልፈው የሚሰጡ መሪዎች እንዲኖሩን ብንጸልይና ብንሠራበትስ! በአገራችን ላይ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ አመራር እንዲሰፍን  ብንቃትትስ? ፓርላማው ስብሰባውን ከመጀመሩ በፊት የቤተ ክርስቲያን ቡራኬና ጸሎት የሚያስቀድምበት ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ መንፈሳዊ ጦርነት ብንዋጋስ? ሌላውን ሁሉ ትተን በዚህ በኩል ብንተጋ የበለጠ መልካም ይመስለኛል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው መሳተፍ ግድ ነው ካልንና በመስኩ  ውጤታማ እንዲትሆን ከፈለግን ተወዳዳሪነቷን ሊታሳይባቸው ከሚገባ ጠርዞች ሦስቱን ማለትም በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባት ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ትንታኔዬን ካቆምኩበት ልቀጥል፡፡ 
በፖለቲካ ውጤታማ መሆን እንዴት እንደሚቻል ከእኔ ይልቅ የዚያ ዘርፍ ባለሙያዎች ቢናገሩ የበለጠ ክብደት ይኖረዋል፣ ሰሚውም ጆሮውን የሚሰጠው ያኔ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአጠቃላይ ምልኬታዬ ተነስቼ የሚከተሉት ነጥቦች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡   የፖለቲካውን ሳይንስ መማር አስፈላጊ ቢሆንም ከዚያ ጋር አብረው የሚሄዱ ተጓዳኝ ነገሮች የመኖራቸው ሐቅ ሊሸሸግ አይችልም፡፡ ፖለቲከኛ መሆን ብዙ ረግዳሮት የሚበዛበት፣ ብዙ ተቃዋሚም ጠላትምንም የሚያፈሩበት ፣ ከተሳካም ደግሞ ለብዙ ሽልማትና ክብር የሚያበቃ ከፍ ያለ ሙያ ነው፡፡ ይህ ሙያ በህብረተሰቡ ውስጥ ልዩነትን የሚያመጣ በመሆኑ የዚያኑ ያህል አቅም የሚጠይቅ ነው፡፡ በሙያው ውጤታማ ለመሆን ጥንክሮ ከመሥራት ጋር ጠቢብ መሆንም ያስፈልጋል፡፡ ግን ውጤታማ ፖለቲከኛ ምን ዓይነት ነው፡፡
·         ተናጋሪነት( Eloquency)፡
የንግግር ችሎታ በፖለቲካው ዓለም ቀዳሚና ተወዳጅ ጉዳይ ነው፡፡ እውቀትን በንግግር መግለጽ የማይችሉ ሰዎች የፖለቲካው መሪ መሆን  ያስቸግራቸዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ትኩረት ከሳቡና አድማጫቸውን ማስከተል ከቻሉ የዓለም የፖለቲካ መሪዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው በአንድ ርዕሰ -አሳብ ተናግረው የማሳመን ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ነው በፖለቲካው ትምህርት ቤት በሕዝብ ፊት የመናገር Public speaking እና ግንኙነት communication የመሳሰሉት እንደ ዋና ኮርስ ተደርገው የሚሰጡት፡፡ ውስጣቸው በእውቀት የታመቀ ብዙ ምሁራን ቢኖሩንም ፊት ለፊት የሚታዩት ግን ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ የሚናገሩ ሰዎች ይደመጣሉ፡፡
በዓለማችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚታይ ለውጥ ያመጡ  የቤተ ክርስያቲን መሪዎች እንዳሉ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የደቡብ አፍሪካው ዴድሞንድ ቱቱ የደቡብ አፍሪካ አንግሊካን ቤተ ክርሰቲያን ካህን ነበር፡፡ ቱቱ በጆሐንስቤርግ  በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ስነ መለኮት ኮሌጅ St Peter Theological College ገብቶ ከተማረ በኋላ ከኪነግስ ኮሌጅ/ King”s College/ በሥነ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪ አገኘ፡፡ ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ጋር ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ሥፍራ ያለው ነው፡፡ በተለይም ከቅዱስ ጴጥሮስ ኮሌጅ ከተመረቀ በኋላ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ካህን ሆኖ ተሾመ፡፡  ወደ እንግሊዝ አገር በማቅናት  የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የሚያስተዳድረው የሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶች ፌንድ (Theoogical Education fund of the World councel of Churches) በተባለው ድርጅት ውስጥ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖው አገልግሏል፡፡ ከእንግልዝ የ3 ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲመለስ ደግሞ  የቅድስት ማሪያም ካቴድራል( Dean of St Mary’s Catedral) ዲን ሆነው ተሸመዋል፡፡ ታዲያ ቱቱ ኤች ኤ ቪ ኤዲስን፣ የዘር መድሎን፣ ድህነት፣ ወሲባዊ ትንኮሳን፣እና መሳሰሉትን በጥብቅ በመዋጋቱና በዚህ ረገድ ባስመዘገበው አመርቂ ውጤት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ለመቀበል ችሏል፡፡ ዴስሞንድ ቱቱ በትምህርት ብቃቱ እርሱን በብዙ የሚበልጡ ሰዎች ቢኖሩም ግን የንግግር ችሎታው በበለጠ አጉልቶታል፡፡ እንደ ሶቅራጥስ ፣ ሸክስፔር፣ አሌክሳንደር ፖፔ እና የከሳሰሉት የዓለማችን እውቅ  ፈላስፋዎችና መሪዎች የተናገሩት አሳብ እንደ እንደሚጠቀስ ሁሉ የዴስሞንድ ቱቱም ጥቅሶች በርካታዎች ናቸው፡፡ ሌላው አስገራሚ ተናጋሪ ሰው የአሜሪካው የጥቁሮች መብት ተሟጋች የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው፡፡ ሉተር ስለ ሰብዓዊ መብት የሚከራከር ቢሆንም የመጥመቃውያን ቤተ ክርሰቲያን መጋቢ ነበር፡፡ አባቱም ሆኑ አያቱ በአትላንታ ጆርጂያ ባለው የአቤንኤዜር መጥመቂያውያን ቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች በመሆናቸው ሉተር ከልጅነቱ ጀምሮ ከቤተሰቡ መንፈሳዊ ነገር እየተመገበ አድጎ እንደወላጆቹ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ራሱን የሰጠ ሰው ነበር፡፡ በአልባማ ሜንቶጎሞሪ የሚገኘው የዳክስተር መጥመቃውያን ቤተ ክርሰቲያን ዋና መጋቢ ሆኖ እስከሞት እለቱ ድረስ አገልገሏል፡፡ ከቤተክርስቲያን አገልግሎቱ ጎን ፍትህ በተጓደሉባቸው ቦታዎች ሁሉ በመገኘት ስለ ሰዎች ልጆች መብት ለመከራከር 6 ሚሊዮን ማይልስ በመጓዝ 25 ሺህ ጊዜ ንግግር አድርጓል፡፡ በተለይም 250000 ሕዝብ በተሰበሰበበት በዋሽንግተን ባደረገው “እኔ ሕልም አለኝ / I have a dream /” በተሰኘው ንግግሩ ታይም መጋዝይን  የተሰኘው መጽሔት  “ man of the year (የዘመኑ ሰው )” የሚል ስም ሰጥተውታል፡፡ ከሰብኣዊ መብት ጋር በተያያዘ 25 መጻሕፍትን ጽፎ ከሕዝብ አስነብቧል፡፡  ለሰብአዊ መብት ባደረገው ተጋድሎ ጥቁሮች ከነጮች ጋር እኩል በሕዝብ አውቶቡስ እንድሳፈሩ እስከማድረግ ከመድረሱም በላይ ባደረገው መስዋዕትነት በተሞላው እንቅስቃሴው ምክንያት ከኖቬል በሽልማት የተገኘውን 54 123 የአሜሪካን ዶላር ከሰብአዊ መብት እንቅስቃሴ እንዲውል አበርክቷል፡፡ በእነዚያ ጊዜያቶች ሁሉ ኪንግ በነጮች ፖሊስ እየተያዘ ወደ እሥር ቤት ወርዷል፣ ቤቱም በቦምብ ጋይቷል፡፡ በመጨረሻም በዚህ እንቅቃሴው ምክንያት በባላንጣዎቹ ደረሰበት ጥቃት ሕይወቱን ሊያጣ ችሏል፡፡ በእነዚያ ሁሉ ጊዜያቶች የሚያሰማቸው ንግግሮች የአድማጩን ትኩረት በመሳብ ልዩነቶች ማምጣት ችለዋል፡፡
ሌላው ሰው ፈራክሊን ግርሃም ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወንጌላዊው ፍራንክሊን በፖለቲካ መሪዎች ዘንድ ትልቅ ግምት ያገኘው ስለ ፖለቲካ ተናግሮ ሳይሆን ለውጥ የሚያመጣ እንቅስቃሴ አድርጎ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ካደረጋቸው አውራ ተግባራት የተወሰኑትን ብንጠቅስ  ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የግብረ ሰዶማዊን ጋብቻ በጠቅላይ ፍርድ ቤት አስወስነው አንጀታችንን ባሳረሩበት ወቅት ጋብቻን የሚደነግግ እግዚአብሔር እንጂ መንግሥት ወይም ጠቅላይ ፍርድ ቤት አይደለም በማለት ቀጥተኛ ተቃውሞ በማሰማት ግንባር ቀደም ሰው ሊሆን ቻለ፡፡ የአሜሪካው ሕዝብ ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ በሚዘጋጁት ወቅት በ50ዎቹ ግዛቶች በመዘዋወር የአደባባይ ጸሎት እንዲደረግ ሕዝበ ክርስቲያኑንን አንቀሳቅሷል፡፡  እኔ በምኖርበት የሚቺጋን ግዛት ጸሎቱ የተካሄደው በግዛቱ ገዥ ቢሮ ግቢ ውስጥ ሜዳ ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጡ ወንጌላውያ አማኞች በተሰበሰቡበት ሲሆን አሜሪካውያን በጸሎት ሰዓት ተንሰቅስቀው ሲያለቅሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በዚህ የጸሎት ፕሮግራም ነው፡፡ ፍራንክሊንም በንግግር ችሎታው የተመሰገነ በመሆኑ የታላላቅ መሪዎችን ጆሮና ልብ እየማረከ ያለ የዘመናችን እውቅ አገልጋይ ነው፡፡    
ለመጥቀስ ያህል ብቻ እንጂ እነዚህን የሚመስሉ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎችና  ታሪኮቻቸው አሉ፡፡ ስለዚህ እኛ ከእነርሱ ብዙ መማር እንችላል፡፡ አማኞችና አገልጋዮች በፖለቲካው ተሳትፈው ለውጥ እንዲያመጡ እንጂ በፖለቲካው መሳተፋቸው ቁጥር ለመሙላት ብቻ እንዲሆን ይገባል ብዬ የማምንበት አቅም እስከአሁን አላገኘሁም፡፡ ተናጋሪዎች የሆኑ ፣ ፖለቲካን በየአንጓው እየሰበሩ ማስቀመጥና ለሚፈልገውም መስጠት የሚችሉ አባሎቻችን ካሉ እናበረታታቸውና ይሳተፉበት፡፡ መንግሥትንም በእኩይ ተግባሩ ይቃወሙት፣ በመልካም ሥራውም ያወዲሱት እላለሁ፡፡
ባለፈው በአገራችን በሕዝብና በመንግሥት መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት መንግሥት የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎችንና ሌሎችን ለውይይት ጋብዞ ነበር፡፡ በዚያ ውስጥ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችም ነበሩ( የሃይማኖት መሪዎች ስለሆኑ ነው የተጠሩት ማለት ነው)፡፡ እነዚህ ወገኖች በዚያ ሥፍራ ተገኝተው የሚባለውን ሰሙ፣ ከገዥ ፓርቲም ሆነ ከተቃዋሚ የፖለቲካ አባላት የሚወረወረውን ክርክር አደመጡ፣ ከዚያም ወደ ቤታቸው መጡ፡፡ በዚያ ፎረም መሳተፋቸውንም ያወቅነው ምስላቸውን ቴሌቭዥን ስናይ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በጣም ደስ ይለናል፡፡ መሪዎቻችን በስብሰባው በተገኙበት አጋጣሚ ከገዥው ፓሪቲም ሆነ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ተቋማት፣ ለመንግሥትና ለሕብረተሰብ የሚሆን ነገር ሲናገሩ ግን አልሰማናቸውም፡፡ በቤተ ክርስቲያናቸው ጣሪያ ሲያርገበግቡ ፣ መድረኩንም ሲያናውጡ የምናያቸው ሰባኪዎች በቤተ መንግስት አካባቢ ጸጥ ረጭ ያሉት ምን ነክቶአቸው ነው ባንል ይሻላል፡፡  እነዚህ ሰዎች የጸሎት ሰዎች ናቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ናቸው እንጂ ፖለቲካን የሚያውቁ አይደሉም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቋንቋ እንጂ የፖለቲካ ነገር ውስጣቸው የለም፡፡ ስለዚህ ምን እንዲሉ ይጠበቃል?  መሄድ ሄደዋል፣ መሳተፍንም ተሳትፈዋል፣ የተጠሩበት ቦታ ሁሉ  ዋናውን  መሪ መላክ የቤተ ክርሰቲያን የቆየ ባህል ስለሆነ ያንን ልማድ ይዘው እዚያ ቦታ ሄዱ እንጂ ምን እንደሚያደርጉ ገብቶአቸው  አልነበረም፡፡ እንዳይናገሩ የአገሪቱን የፖቲካ አካሄድ አያውቁትም፣ የፖለቲካው ቃላትም/ terminology/ የላቸውም ፡፡ እነርሱ ያላቸው የሥነ መለኮታዊ ቃል  theological terms ነው፡፡ ያንን እዚያ ቢናገሩ የሚያደምጣቸውም የሚረዳቸውም የለም፡፡  በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ያለን አገልጋዮች በሕዝብ ፊት ቆመን የመናገር እድላችን ከፖለቲካኞች ይልቅ የሰፋ ነው፡፡ የምንናገረው ግን የአንድ አቅጣጫ ንግግር/ Monologue/ የሚባል ዓይነት ነው ፡፡ ያውም አንደዳንዴ ተፋልሶ የበዛበት ቢሆንም ማንም አያርመውም፡፡ አንዳንዴ ሰፊ ሰዓት ተጠቅመን በተናርነው ነገር ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ቁም ነገር ሳንሰጥ ከመድረክ ስንወርድ አድማጩ እግዚአብሔር ይባርክህ ብሎ ይመርቀናል፡፡ ሰባኪዎች ሁሉ እንደዚያ ናቸው እያልኩ አይደለም፡፡ ይህ አሳብ በጣም በሚገርም ሁኔታ አስተምረውን  የቤተ ክርስቲያንን ያሳደጉ የተባረኩ አስተማሪዎቻችንን አይመለከትም፡፡ አንዳንድ ትርጉም የሌለው እንጨት እንጨት የሚል ነገር  እየተናገሩ ሕዝቡን የግድ አሜን እንድል ወይም እንዲያጨበጭብ የሚያድርጉ ፣ ቤተ መቅደሱንም በሁኬትና በጩኸት ሞልተው የሚወርዱ የዘመናችን ሰባኪዎችን ነው እንጂ፡፡ እንዲያም ሆኖ ጉባኤያችን ይባርካቸዋል፣ ይመርቃቸዋልም፡፡ በዚህ ልማድ የኖረ ሰው ወደ ሌላው አደባባይ ቢሄድና እናገራለሁ ቢል አሜን የሚለው የለም፣ ተከራካሪ ነው ያለው፡፡ ፖለቲካ በመንፈስ ሳይሆን በአእምሮ የሚሠራ ሰለሆነ አንድ ዓረፍተ ነገር ጣል ባደረግን ቁጥር ሁሉ አሜን በሉ የምንበልበት ቦታ አይደለም፡፡ እስቲ መድረኮቻችንን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚተላለፉ መልእክቶችን ፣ የመልእከቶችንም ይዘት ፣ ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃልም ጋር  ስላላቸው መስማማት ተመልከቱ፡፡ በሰማናቸው ቁጥር ምነው መካሪ በተገኘ የሚያሰኙ ናቸው፡፡ ምነው እነዚህን ሰባኪዎች እጃቸውን ይዞ የሚመራ የታጣው ያስብላል፡፡ ይህንን ስናይ ቤተ ክርሰቲያ በፖለቲካው ትሳተፍ ለማለት አቅም ያንሰናል፡፡ ምን ይዛ ፣ ማንን ይዛ የሚለው መሰመር ይኖርበታል፡፡  ስለዚህ ቤተክርስቲያን  በንግግር ችሎታቸው ላቅ ያሉና  ተከራክረው ሌላውን መቋቋም የሚችል  ፣ የሚናገሩትንም ነገር የሚያውዉና ፣ የራሳቸውንም አሳብ ከጥቃት የመመከት ብቃት ያላቸውን  ሰዎችን በፖለቲካው ማሰለፍ ከቻለች ውጤታ ትሆናለች እላለሁ፡፡ ያለዚያ ግን በፖለቲካው እንድትሳተፍ ባንመክራት ይሻላል፡፡  
·         ቆራጥነት፡
ለሰዎች ልጆች መብት ተከራክረው ውጤት ያሰመዘገቡ ቆራጥ አቋም ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የሚኖሩት ከራሳቸው ሳይሆን ለሰው ስለሆነ ሞታቸውንም ስለ ሰው ነጻነት ሲሉ ሞተዋል፣፣ በየአሥር ቤቶቹ ተንገላተዋል፡፡ በፖለቲካ መሳተፍ የሚፈልግ ሰው ሁሉ ቆራጥ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የሚያስከፍለው ዋጋ መኖሩን ማወቅና ዋጋውንም ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርበታል ፡፡ እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ ያደረጉት ይህንን ነው፡፡  ለወንጌላዊ ያሬድ ጣላሁን ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጥታ ደብዳቤ ጽፎ በማህበራዊ መገናኛ ለጥፏልና፣ ወንጌላዊ ያሬድ በጽሑፍ ካስተላለፈው መልእክት በተጨማሪ በሕዝብ ፊት ቀርበው ንግግር አድርጓል፡፡ በጣም ጠንካራ አሳቦችን ተናገሯል፡፡ በሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን ጥላቻ  በማውገዝ በመናገሩ አደንቀዋለሁ፡፡ ጨለማ ጨለማን ስለሚወልድ  መንግሥት በሕዝብ ገንዘብ በተገዛው መሣሪያ ሕዝብን መልሶ መግደልን እንዲተው፣ ጦር ሠራዊቱ የጠመንጃ አፈሙዙን እንዲያዘቀዝቅ  መንግሥት መማጸኑ በጀ የሚያስብለው ነው፡፡ ድፍረትና የአገር ፍቅር የተሞላበት ንግግር ነው፡፡ “ይህንን ተማጽኖ በኢትዮጵያ ላይ ሰላም ሰፍኖ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ገንቢ የሆነ ድርድር ተደርጎ የሁሉም ሕዝብ ድምጽ ተሰምቶ በሰዎች መካከል እኩልነት ተከብሮ እስከማይ ድረስ ይህንን ጩኼቴን አላቆምም፡፡” በማለት ቃል ገባ፣ ጉባኤተኛውም አጨበጨበለት፡፡ እኔም ስሰማው እንደ አገራችን አባባል በልቤ “ አንበሳ” አልኩት፣ አሁን ቆራጥ የቤተ ክርስቲያናችን ልጅ ተገኘ አልኩ፡፡ በተለይም የአገራችን ሕዝቦች መታሰር፣ መገረፍ፣ አገር ጥሎ መሰደደድ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ያለው ወጣት እየደረሰበት ያለው የህልና ስብራት ከፍተኛ መሆኑን መናገሩ ያስመሰግነዋል፣ የአገርና የሕዝብ ተቆርቋርነቱን ያሳያል፡፡በዚሁ ቢቀጥልበት መልካም ነው ብዬ ተመኘሁለት፡፡  ይህንን ስል ከልቤ ነው፡፡ ወንጌላዊ ያሬድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ምክንያት ሰው ሁሉ ሰግቶ የት እንዳለ ስልክ እየደወሉ እንደጠየቁት ይናገር ነበር፡፡ ግን እኮ ከወንጌላዊ ያሬድ በፊት ወንጌላዊ ጸጋአብ በቀለ ብስለት የተሞላውን ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ታዲያ  እነ ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን ምን ዋጣቸው? እንደዚያ ግዳይ እንደጣለ ሰው በጣም ሲንጎማለሉ የነበሩ ምንነው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኃዋላ የውሃ ሽታ ሆኑ? የሆነ ሕዝባዊ ሰልፍ እየተጠበቁ ነው ማለት ነው? ትግሌን እቀጥላሁ አልተውም ሲሉ የነበሩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ ሕዝቡ ወደ ቤቱ ሲገባ እነርሱም አብረው ቤታቸው ገቡ፡፡ ከመጀመሪያውም ቢሆን የሕዝብ እንቅስቃሴ አይተው አለሁ ለማለት ያደረጉት እንጂ እውነተኛ አቋም ኖሮአቸው ፣ በራሳቸውም ተነሳስተው የሕዝብ ጉዳት ከንክኖአቸው አይደለም እንዳያስብላቸው ፈራሁላቸው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላስ ቢሆን ሰዎች አላታሠሩም? የመንግሥት ተቃዋሚዎች እስከዛሬ ዝም አላሉም፡፡ የወንጌል ሰባኪዎች ነን ያሉ ግን ለሕዝብ እታገላለሁ፣ ትግሌንና ተቃውሞዬን አልተውም ብለው በዓለም መድረክ ተናግረው ከዚያ ወዳጅ ያፈሩ ወንጌላውያኖቻችን አፋቸውን ዘጉ፡፡ ለነገሩ ወንጌላው ያሬድ መልእክቱን ከመጻፉ ቀደም ብሎ ወንጌላዊ ጸጋአብ በቀለ ጠንካራ መልእክት ጽፏል የሚራግብለትን አላገኘም አንዲ፡፡ ታዲያ ጸጋአብ እስከ አሁን ማን ነካው? ነገሮችን ካካበድናቸው ሳናውቅ የራሳችን አድናቂዎች እንሆናለን፡፡   እኔ እንዲያው ሳየው  ወንጌላዊ ያሬድ ሁለት ችግሮች ተስተውሎበታል፡፡ አንደኛ ምንም የመንግሥት አካል በሌለበት ተቃዋሚዎች ብቻ በተሰበሰቡበት፣ ለንግግሩ ምላሽ የሚሰጠውና ሰምተውም የለውጥ ርምጃ የሚወስድ በሌለበት ፣ በእያንዳንዱ ዐረፍተ ነገር መካካል የሚያጨበጭብ ጉባኤ ፊት ብቻ ነው የተናገረው፡፡ ይህ ብቻ ቆራጥነትን አያሳይም፡፡ በእርግጥ ንግግሩ ጭብጨባ ያንሰዋል የሚያስብል ነው፡፡ በቤተ ክርሰቲያን ያለው ሕዝብ በገባውም ባልገባውም እንዲያጨበጭብ አጨብጭቡ እንጂ አያልን ሕዝባችንን እንዲያው አጭብጫቢ አድርገነዋል፣ ያንን ይዘን ደግሞ ወደ ሌሎች አደባባይ እየሄድን ነው፡፡ አጨብጫቢዎች ሲከተሉአቸው ደስ የሚላቸው መሪዎች ለስህተት የተጋለጡ ናቸው፡፡ ወንጌላዊ ያሬድም ለሚያጨበጭቡ ብቻ ከመናገር እልፍ እንዲል ይጠበቅበታል፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ  ለውጥ ያመጡት ፍትህ ተጓደለ ወደተባለው ሥፍራ ሁሉ በመንቀሳቀስ በአደባባይ  የመንግሥት አመራር አካላትን ወታደሮቻቸውን ጭምሮ ከ25000 በላይ ሕዝብ በአንድ መቀመጥ የሚያደምጡትን  ንግግር በማድረግ ነው፡፡  በአጭብጫቢው ፊት በተዘጋ ቤት ውስጥ ብቻ ተናግሮ ቢሆን ኖሮ ተደብቆ ድንጋይ የመወርወር፣ በጨለማም የማፍጠጥ ያህል ብቻ ሆኖ በቀረበት ነበር፡፡ ወንጌላዊ ያሬድም  እልፍ ማለት ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ ሁሉም እኮ በየቦታው እንደዚያ ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰውም እኮ በአንድ ቦታ ንግግር አድርጓል፣ እርሱም ያራገበለት የለም እንጂ፡፡ እርሱ እንዲያውም ሕዝብ ለሰላማዊ ሰልፍ ከመውጣቱ በፊት ነው ይናገር የነበረው፡፡   ወንጌላዊ ያሬድ  እንደ መካለለኛ nutral ሰው ሳይሆን እንደ ፓለቲካኛና እንደ መንግሥት ተቃዋሚ ሰው ነው የተናገረው፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ ወገን ብቻ እንዲደመጥ ያደርገዋል፡፡ ያንን ንግግር ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አንድ ጥግ ለያዙ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለመንግስትም መናገር ነበረበት፡፡ መንግሥት ይህን ሰምቶ የለውጥ ርምጃ ወሰደ አልወሰደ መንግሥትን ማሰማት ይገባል፡፡ ሁለተኛ የእግዚአብሔርን ቃል ያለቦታው መጥቀሱ አግባብ አይደለም፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን ሰባኪዎቿ  አጥብቃ የሚታሳስበውና የምትወተውተው ግን ሊታረም ያልቻለ ድክመታችን ነው፡፡ ቃሉን ከሚገጥመው አሳብ ጋር ካላዘመድነው አድማጩን እናሳስተዋለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል  አማኞች የአንድ አካል ብልቶች፣ ቤተ ክርሰቲያንም የክርሰቶስ የአካል ብልት እንደሆነች ይናገራል፡፡ ይህን ትምህርት ግን አገርና የአገር ሕዝቦች የአንድ አካል እንደሆኑ ለማስተማር መጠቀም ቃሉን እየቦጨቁ ያለቦታው መደረት ይሆናል፡፡ የሕዝቦች አንድነት ለማሳየትና ለመስበክ ከተፈለገ ሌላ ክፍል መምረጥ ይቻል የለምን? “ባሪያ በነገሠ ጊዜ ሰነፍም እንጀራን በጠገበ ጊዜ የተጠላች ገጊዜ ምድር ትናወጣለች” /መጽሐፈ ምሳ 30፡21-22/ የሚለውን የጠቢቡ ሰለሞንን ምሳሌ የጠቀሙ ራሱ በጣም ወጣ ያለ ነው፡፡ እነዚህን መጠቀማቸውን ስናይ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያለ ቦታቸው የተለጠፉ ናቸውና ይታሰብበት ለማለት ነው፡፡
ለወደፊትም ቢሆን ለብዙ ዘመናት በአገልጋይነት ቆይቻለሁ፣ ሰባኪ፣ ወንጌላዊ ቄስ ወዘተ ነኝ እያልን ፖለቲካውን ደግሞ መነካካት ስንጀምር ቀጣዩንም ውስብስብ መንገድ ለመጓዝ ቆራጥነትን እንደሚስፈልግ ስለማሰቡ የእኔ ምክር ከሚያስፈልጋቸው ልክ በላይ የላቁ አገልጋዮች ስላሉን በዚሁ ላቁምና አሳቤን ልቋጭ፡፡ የገብሷን እሸት ከመብላት በፊት በደንብ ማሸት፣ ያለዚያ ሳሉ አያስተኛምና እንዲሉ በአንድ ነገር ውስጥ ከመግባት በፊት ማሰብ ፣ የሚያስከፍለውንም ዋጋ መተመን የሚያሻ ይመስለኛል፡፡  ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ ትሳተፍ ስንል ብቅ ብለው ጥፍት የሚሉ ፣ ነገር ሲሞቅ የሚግሉ፣ ገና ሊበርድ ሲል ደግሞ ቀድመው ወደበረዶነት የሚቀየሩ ሳይሆን በእርግጥ ዋጋ ከፍዬ ለሕዝቤና ለምድሬ ለውጥ አመጣለሁ የሚሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ሊኖሩአት እንደሚያስፈልግ እናስምርበት፡፡
       

      


1 comment:

  1. ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡

    ReplyDelete