Thursday, February 23, 2017

     በአገልግሎታችን ቅዱሳንን እንዴት መጥቀም እንደሚገባን ( 2017-35)
                                                                                                   

                                                                                           ከመጋቢ ሳሙኤል ሾንጋ

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 1993 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት የበርካታ እንስሳትና የሰው ሕይወት ጠፍቶ ነበር፡፡ በጊዜው የተከሰተው ተፈጥሮአዊ አደጋ በጣም አስከፊ በመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት/United Nations  በጉዳት ላይ ለነበረው ሕዝብ ሰብአዊ ርዳታ እንዲሰጡ የተለያዩ ዘርፍ ባለሙያ ሰዎችን ወደ ደቡብ ሱዳን መላኩ ይታወሳል፡፡ በጊዜው የህክምና ባለሙያዎች፣ የሰብአዊ ርዳታ ሰጪ አካላት ወዘተ  መድኃኒት፣ ምግብና ሌሎች አሰፈላጊ  ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ቦታው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በወቅቱ ከተንቀሳቀሱት ውስጥ ዓለም አቀፍ ጋዘጤኞችም የነበሩበት ሲሆን ታዋቂ ፎቶጆርናሊስት ደቡብ አፍሪካዊው ኬቪን ካርቴር ይገኝበታል፡፡ ኬቪን ከልዑካን ቡድኑ ጋር ወደ ደቡብ ሱዳን ከደረሰ በኋላ በካሜራው ያነሳቸው ፎቶግራፎች በጣም ተደናቂነትን ያኙና በሥፍራው ስለነበረው የድርቅ ሁኔታ በጣም በኃይለኛው ሁኔታ የሚገልጹ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ልጆች ውሃ ከማጣታቸው የተነሳ ላሞች ሽንት ሲሸኑ ከስር ቀርበው ሲጠጡ፣ ወይም ጭንቅላታቸውን አስጠግተው ሲታጠቡ ኬቪን በካሜራው አንስቷል፡፡ ከሁሉም ፎቶዎቹ ይልቅ ግን በወቅቱ ሁሉንም ያስደነቀችና የኬቪንንም ዝና እጅግ ያወጣችው ፎቶ ሌላ ነበረች፡፡ አንዲት በረሀብ በጣም ከመጎዳቷ የተነሳ ሰውነቷን መሸከም ያቃታት፣ በአካላቷ  ላይ ምንም ሥጋ የሌላት ፣ ቆዳዋና አጥንቷ የተጣበቀ የሚመስል ሕጻን ልጅ በአንድ በረሀማ በሚመስል ቦታ  ፣ በሰውነቷ ላይ ምንም ልብስ ሳይኖር ራቁቷን ሆና ጭንቅላቷን በሁለት እግሮቿ መካከል አድርጋ በግምባሯ ተደፍታ ፣  በአጠገቧ ምንም ሰው ሳይኖር ነገር ግን ከኋላ አንድ የፈረጠመ ጆፌ አሞራ ተንሰፍስፎ ሲጠብቃት ሳለ ኬቪን በካሜራው አነሳና ለዓለም ሕዝብ አሳየ፡፡ ያ ፎቶግራፍ በደቡብ ሱዳን የነበረው ድርቅ አስከፍነቱ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያስረዳ በመሆኑ በጊዜው የዓመቱ ምርጥ ፎቶ ተብሎ ተመረጠ፡፡ በዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ ያለው በሥነ ጽሑፍ፣ በጋዜጠኝነት፣ በሙዚቃ ድርሰት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረቱት ሽልማት የሚሰጠው Pultizer price የተሰኘው ድርጅት የሚሰጠውን ሽልማት ያሸነፈ አስደናቂ ፎቶ ሆኖ ተመረጠ፡፡ ከዚያ በኋላ የኬቪን ዝና እጅግ ወጣ፣ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ገናናና እና ታዋቂ ሆነ፡፡ የኬቪን ፎቶ የፓልትዘርን ሽልማት ስላሸነፈ የሽልማት ስነሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሕፈት ቤት ተዘጋጀለት፡፡ ከተለያዩ የሙያ ባለሙያዎች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ከጋዘጠኞችና የፊልም ባለሙያዎች የእንኳን ደስ ያለህ መልእክት ከየአቅጣጫው ጎረፈለት፡፡ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት በታዳሚዎች ፊት  በሙያውም ስኬታማ ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ ከጋዘጠኞች ለሚቀርብለት ጥያቄ መልስ እየሰጠና በደቡብ ሱዳን በረሀ ላይ ያቺን ሕጻን እንዴት በካሜራው እንዳገኛት ስለብልሃቱና ስለጥበቡ  እያብራራ ከሁሉም ሰው አድናቆትን  እያኘ ሳለ ከጉባኤ በስተ መጨረሻ በኩል አንድ ሰው አንድ ወሳኝ ጥያቄ አቀረበለት፡፡ ጥያቄውም እንዲህ የሚል ነበረ፡፡ “የልጅቷ መጨረሻ ምን ሆነ?”  በዚህን ጊዜ ኬቪን ደነገጠ፡፡ አንደበቱ ተሳሰረ፡፡ በዓይነ  ሂሊናው ወደ ደቡብ ሱዳን በረሀ ጭልጥ ብሎ ሄደ፡፡ ሰውነቱ ይንቀጠቀጥ ጀመር፡፡ ልጅቷ ምን ሆነች ለሚለው ጥያቄ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘውን ሕዝብ አስተሳሰብ በአንዴ ቀየረው፡፡ ጉባኤተኛው ሕዝብ ኬቪን ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ይሰጥ ይሆን ብሎ በጉጉት እየጠበቁ ሳለ  እርሱ ምንም ሳይመለስ ያን ጥያቄ ያቀረበው ሰው ሌላ ጥያቄ በከፍተኛ  ጩኼት “ ልጅቷን አዳንካት ወይ “ በሚል አስከተለበት፡፡ ኬቪን ልቡ ይመታ ጀመር፡፡ ራሱን በዚያ ሥፍራ ማቆየት ስላልቻለ ከወንበሩ ተነስቶ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ በዚያው ወደ አዳራሹ ሳይመለስ ወደ ትውልድ አገሩ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀና፡፡ ቢሆንም ከህልናው ክስ መሸሽ ስላልቻለና ስለተሰቃየ በተወለደ በ33 ዓመቱ አንድ ወረቀት ጽፎ አጠገቡ አስቀመጠና ራሱን ሰቅሎ ሞተ፡፡
ኬቪን ወደ ደቡብ ሱዳን የተላከበት ዋንኛ ምክንያት ለራሱ ዝና እንዲሠራ አልነበረም፣ የሌሎችን ሕይወት ለማዳን እንጂ፡፡ እንደዚያች ላሉ ሕጻናትና ለሌሎች በድርቁ ለተጎዱት ሰዎች የነፍስ አድን ርዳታ እንዲያደርስላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የዚያች ልጅ ሕይወት እየመጣባት ካለው አሞራ ማዳን ሲችል ተልዕኮውን ወደ ጎን በመተው የራሱን ዝና ለማውጣት የሚችለውን ሥራ ብቻ ሥርቶ ልጅቷን በዚያ በረሀ ለአሞራ ተዋት፡፡ ሌሎችን ለመጥቀም የተሰጠውን ተልዕኮ ዘንግቶ ራሱን መጥቀም ፣ በሰዎች ጉዳት እርሱ የመክበርን መንገድ ተከተለ፡፡ በመጨረሻም በጣም ወሳኝ ወቅት ላይ ልጅቷን አዳንካት ወይ የሚል የቀረበለት ጥያቄ ያንን ክብርና ዝናውን ሁሉ አበላሸበት፡፡
ይህ በእግዚአብሔር ቤት ቅዱሳንን ለመጥቀም ከጌታ የአገልግሎትን አደራ ለተቀበልን ሁሉ ማንቂያ ደወል ሊሆን የሚችል ምሳሌያዊ አሳብ ነው፡፡ እኛ የተጠራነውና አገልግሎትን የተቀበልነው ሌሎችን ለመጥቀም ነው፡፡ አገልግሎት የሚለው አሳብ ራሱ ሌላውን ማገዝ፣ መጥቀም፣ መርዳት ወይም ለሌሎች ጥቅም መኖር ማለት ነው፡፡ ይሁን አንጂ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎትና አገልጋይ ማለት የተሳሳተ ሥፍራ ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ ከቅርበ ጊዜ ወዲህ በቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መሆን ሌሎችን የመጥቀም ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ  በሰዎች መጠቀም፣ የተገኘውን ዕድል ሁሉ ለራስ መውሰድ( taking an Advantage to own self ) መሆን እየመሰለ መጣ፡፡ ሰዎችን አዋርደን እኛ ክብር ማግኘት፣ ሰዎችን ዝቅ አድርገናቸው ወይም ጎድተናቸው እኛ ዝናን ማግኘት፣ ድፍረት በባይሆነኝም የሰዎችን ኪስ አራቁተን እኛ ማለትም አገልጋዮች የሆንንው እኛ ብቻ  መበልጸግን ልማድ እያደረግን እንገኛለን፡፡ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያንና ለአገልጋዮች የሰጠን ተልእኮ ወደ ጎን የተተወ ይመስለኛል፡፡ ልክ የፎቶግራፍ ጋዜጠኛው ኬቪን የተባበሩት መንግሥታት የሰጡት ተልእኮ የተጎዳውን ሕዝብ እንዲያድን ሆኖ ሳለ እርሱ ግን ያንን ሰውን የማዳን ሥራ ወደ ጎን ትቶ የተራቡ ሕጻናትን ለአሞራ ሰጥቶ ለራሱ ክብር ዝና፣ ገንዘብ ሽልማት፣ ታዋቂነትን የሚያተርፍበትን መንገድ እንደተከተለ ሁሉ ዛሬ እኛም አገልግሎታችንን ለሌሎች ጥቅም መስጠት ትተን ለራሳችን ክብርና ዝና የምንኖር እንዳይሆን መጠንቀቅ እንዳለብን የሚያሳስበንን መልእክት ሐዋሪያው ጳውሎስ ከኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከተናገረው አሳብ እንመለከታለን፡፡
ሐዋሪያው ጳውሎስ በመልእክቱ መግቢያ ላይ እንዲህ ይላል፡፡
ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።
ጳውሎስ ሌሎችን የመጥቀሙን አገልግሎት በኤፌሶን ላሉት አማኞች በትክክል አስመስከሯል፡፡ እንዲያውም እርሱ በዚያ ሲያገለግል ሁለት ዓይነት ሰዎች እንደነበሩ ከክፍሉ አጠቃላይ አሳብ እንረዳለን፡፡ አንደኛዎቹ የሐሰት ትምህርት አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ጳውሎስ ስለ እነርሱ ሲገልጽ ከተኩላ ጋር ይመስላቸዋል፡፡ ከአውሬዎች ጋር ይመስላቸዋል፡፡ ነጣቂዎች ናቸው ይላቸዋል፡፡ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ይላቸዋል፡፡ ደቀመዛሙርትን ወደ ኋላ  የሚስቡ፣ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ እንደሆኑ ያሳስባል( ቁ 29-30)፡፡ አገልጋዮች ናቸው፣ የወንጌል አገልጋዮች፣ ሰባኪዎች ናቸው ግን በመንጋው ላይ የሚጨክኑ ፣ የአውሬነትና የተኩላነት ልብ ያላቸው፣ የሚነጥቁና የሚያጣምሙ መሆናቸው በጣም የሚያስገርም ነው፡፡ አንድ ሰው ወደ አገልግሎት ሲገባ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ልጥቀም ብሎ ካልሆነ የራሱን የሚመግብ ጨካኝና ነጣቂ ነው የሚሆነው፡፡ ያ ደግሞ መጥፎ መርገም ነው፡፡ ልክ ኬቪን ልጅቷ አዳንካት ወይ የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት ግራ እንደተጋባና ራሱን ከሥፍራው እንዳገለለ ሁሉ አገልጋዮች አንድ ቀን መጠየቃችን አይቀርም፡፡
ሁለተኛው ጳውሎስ ራሱ ሲሆን የኖረው ለአማኞች ጥቅም ሲል እንደሆነ ይናገራል፡፡ በእስያ  ለሦስት ዓመታት ኖሯል፡፡ በዚያን ጊዜ ጢራኖስ በሚባል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እያስተማረ ለሁለት ዓመታት መኖሩን በሐዋሪያት ሥራ ምዕራፍ 20 ላይ እናገኛለን፡፡ ከዚያም በላይ ዘመናትን ኖሮ ሊሆን ይችላል ግን በኖረባቸው ጊዜያቶች ሁሉ ለቅዱሳን የሚጠቅመውን አድርጓል፡፡ ከሽማግሌዎች ጋር ሆኖ የሦስት ዓመት አገልግሎቱን ሲገግምና ሲከልስ የእግዚአብሔርን ሰዎች ከሚጠቅማቸው ነገር አንዱንም እንዳላስቀረ በልበ ሙሉነት ይናገራል፡፡
በዚህ ክፍል ሐዋሪያው ርግጠኛ ሆኖ የሚናገረው ከቤተ ክርሰቲያን ሕዝብ ከሚጠቅማቸው ነገር አንድ እንኳ እንዳላስቀረባቸው ነው፡፡ የሚያደርጋቸውን ሁሉ ነገሮች ያደረገው ለአማኖቹ እንድጠቅማቸው ብሎ ነው፡፡ የእውነተኛ አገልጋይነት ሕይወትም እኮ እ ሌላውን በመጥቀም ነው፡፡ ወንጌላችን ራሱ ሌሎችን መጥቀም ነው፡፡ ጳውሎስ በሌላም ሥፍራ ሰዎችን ለመጥቀም ራሱን እንደሰጠ ሲናር እንዲህ አለ፡፡
ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። አይሁድንእጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ(1 ቆሮ 9፡19-22)።
ጳውሎስ ለተለያዩ ሰዎች ወንጌልን ሰብኮ እነርሱ ደህነነትን የሚያገኙበት መንገድ ሲናገር እነርሱን መጥቀም ይለዋል፡፡ በሌላም ሥፍራ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ስናገር በምድር መኖሩ ራሱ ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ለአማኞች ጥቅም እንደሆነ ይናገራል፡፡ ለእርሱ ወደ ክርስቶስ መሄድ እጅግ የተሻለና የበለጠ ነገር እንደሆነ ቢያምንም በሥጋ ከእነርሱ ጋር መኖር ግን ከእርሱ ይልቅ ለእነርሱ/ ለአማኞቹ/ ጥቅም እንደሆነ ያስረዳል፡፡ እንዲህም ሲል፡
ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው( ፊልጵስዩስ 1፡19-23)።
እኛስ ዛሬ ራሳችንን ስንፈትሽ  እግዚአብሔር በሰጠን ዘመን ባገለገልንባቸው ሥፍራዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚጠቅም አገልግሎት እንደሰጠን እርግጠኞች ነንን? ለእግዚአብሔር ሕዝብ የምንጠቅም አገልጋዮች እንድንሆን እግዚአብሔር ይፈልጋል፡፡ በእውነት በዚህ ዘመን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ካስተማረው ትምህርት በአገልገሎታችን እንዴት ቅዱሳንን መጥቀም እንደምንችል አራት መሠረታዊ ነጥቦችን እንመለከታለን፡፡ በአገልግሎታችን ሌሎችን መጥቀም የምንችለው እንዴት ነው?
1.    ለአገልጋይነት የሚገባ ባሕሪይ /An aproprate character/ ሲኖረን ነው፡፡

ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤ ጳውሎስ በዚህ ሥፍራ ወደ ሌሎች አሳቦች ሁሉ ከመግባቱ በፊት ስለ ራሱ የአገልጋይነት ባሕሪይ አጠንክሮ ይናገራል፡፡ በአማኞች መካከል በተመላለሰባቸው ጊዜያቶች ሁሉ 3 ዋና ዋና የአገልጋይ ባሕሪያትን ማሳየቱን በልበ ሙሉነት ይገልጻል፡፡ 1. ትሁት ነው፡፡ 2. የእምባ ሰው ነው፡፡ 3. ለጌታ የተገዛ ሰው ነው፡፡ ትህትና የሌለው ሰው በእግዚአብሔር አገልግሎት ቢሰማራም ቅዱሳንን ሊጠቅም አይችልም፡፡ እንዲያውም የእርሱ አገልጋይነት ለቤተ ክርስቲያን ሸክምና ፈተና ነው፡፡ ትህትና የትዕቢት ተቃራኒ ሲሆን በምድር ላይ እጅግ አስቸጋሪ ኃጢአት ቢኖር ትዕቢት ነው፡፡ ትዕቢተኛ ሰው መንፈሳዊ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ቅዱሳንን ይጎዳል፣ አገልግሎትንም ያበላሻል፡፡  ትሁታን ባሉበት ግን ፍሬ አለ፣ ነጻነት አለ፣ ሰላምም አለ፣ ሁም በደስታ ጌታን ያልካል ያገለግላልም፡፡ ጳውሎስ በዚህ ሕይወቱ የተመላለሰ አገልጋይ ነበር፡፡ እርሱ ትሁት ብቻ ሳይሆን የእምባ ሰው ነው፡፡ ስለ አማኞች በእግዚአብሕር ፊት የሚያነባ ሰው ነው፡፡ አማኞችን ሲያስተምራቸውና ሲገስጻቸውም ሁሉ በእምባ ነበር (ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ ቁ 31)፡፡ የምናገለግለው አገልግሎት ከእውቀት ፣ ከትምህርት፣ ከልምድ ሁሉ በላይ እምባን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ጨምሮ በዘመኑ ሁሉ ለጌታ የተገዛ ሰው መሆን ይገባል፡፡ ጳውሎስ ከአይሁዶች ሴራና ዛቻ ቢደርስበትም እንኳ በሕይወቱ አንድም ቀን የትዕቢት ነገር አልታየበትም፡፡ይልቁንም ከእምባ ጋር ለጌታ እየተገዛ ዘመመኑን ሊኖር የቻለ ሰው ነው፡፡ የጌታ ባሪያ ጳውሎስ እነዚህ ሦስት ዋና ዋና መልካም ባሕሪያት የታየበት ድንቅ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፡፡
በዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው አንድ ሰው የአገልግሎት ስጦታ መኖሩን ብቻ ነው፡፡ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ የፈውስ አገልጋይ፣ ተአምራት የሚያደርግ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ እኛም አገልጋዮች የሆንነው የምናተኩረው በዚያ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚባርከን በእኛ አገልግሎትም ሌሎችን የሚባርካቸው ባለን መንፈሳዊ ሕይወት ለውጥና ባሕሪይ(Charactor) መሰረት ነው፡፡ ይህ በጣም መሠረታዊ ነገር ነው፡፡  ጳውሎስ በምዕመናን መካካል ሲመላለስ እነዚህን ቁልፍ ባሕሪያትና ያሳየው ለአንድ ጊዜ ቆይታ ብቻ ወይም የሆነ ነገር ሲፈልግ ፣ ወይም አንድ ነገር እንዲሆንለት ሰዎችን ሊያማልል ያደረገው የግብዝነት ነገር አልነበረም፡፡ ነገር ግን የሁል ጊዜ የሕይወቱ ተሞክሮ እንደሆነ ሲገልጽ ወደ እስያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ባሕሪያት የታዩበት እንደነበረ ይናገራል፡፡ ስለዚህ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሌሎች የአገልግሎት  ክፍሎች ተሰማርተን ስናገለገል በእውነት ሌሎችን እንጥቀማቸው ካልን ወደ መሠረቱ መመለስ ይኖርባናል፡፡ ያውም ከተሰጡን የጸጋ ሥጦታዎች በላይ በእግዚአብሔርና በሕዝቡፊት ያለን የሕይወት ለውጥ ምን እንደምመስል መገምገምና መረዳት ያስፈልገናል፡፡

2.   አገልግሎታችን ሥልታዊነት Strategy ያለው ሲሆን ነው፡፡

 የምንሰጠውን አገልግሎት የትና እንዴት እንደምንሰጥ በትክክል ማወቅ ቅዱሳንን ለመርዳት የሚያግዘን አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሐዋሪያው የአገልግሎቱ ሽፋን( a ministerial scope) ለማን፣ ለምንና   እንደሆና ከየት እስከ የትም መሆን እንዳለበት የተረዳ ሰው መሆኑን በዚህ ክፍል ያሳየናል፡፡ (ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ፣ቁ.20-21)፡፡ ጳውሎስ በዚህ አሳቡ ማንን እንደሚጠቅም ያውቅ ነበር፣ የት እንደሚጠቅማቸውም ያውቅ ነበር፡፡ በእርሱ አገልግሎት የሚጠቀሙት ሰዎች ሁሉ ማለትም አይሁድም አሕዛብም ናቸው፡፡ በዚያ ጊዜ የዓለም ሕዝብ አይሁድና አሕዛብ ተብሎ በሁለት ጎራዎች የተከፈሉ ቢሆንም የጳውሎስ አገልግሎት ግን  ለሁሉም ነበረ፡፡  እርሱ ራሱ ሁሉንም የሚጠቅም አገልጋይ ነበረ፡፡ ሁሉንም ማገልገሉና መጥቀሙ የሕይወቱ መመሪያ ስለነበረ ለፊልጵስዪስ ሰዎች ሲጽፍ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ(ፊልጵ 2፡4) በማለት ጠንካራ መመሪያ ሰጥቶ አለፈ፡፡  የጳውሎስ ሥረ- መሠረቱ አይሁዳዊ ቢሆንም እርሱ ግን አህዛብ የሆኑ ግሪኮችንም ይጠቅማቸው ነበር፡፡ ደካሞችን ይጠቅማቸው ነበር፡፡ የተጠቁትን፣ የተጣሉትን፣ የተገለሉትን፣ አምላክ የላቸውም የተባሉትን፣ አገርም የሌላቸው የተባሉትን፣ ያልተገረዙ የተባሉትን ሁሉ ለመጥቀም ያገለግል ነበረ፡፡ በጳውሎስ አገልግሎት ውስጥ ልዩነት የሚባል ነገር ስላልነበረ እርሱ ለሁሉም የሚጠቅም አገልጋይ ሆነ፡፡
ጳውሎስ  የአገልግሎቱን ተደራሲያን ብቻ ሳይሆን የት ማገልገል እንዳለበትም የተረዳ ሰው ነበረ፡፡  አገልግሎቱ ጉባኤም በየቤታቸውም  ሁሉ ነበር፡፡ የሐሰት አስተማሪዎች ትልቁ ትኩረታቸው ቤት ለቤት እየዞሩ የቅዱሳንን ቤት መብላት፣ በእምነታቸው ያልበረቱትና አንዳንድ ቅምጥል ሰዎችን ማሳት ነው፡፡ በኢየሱስም ጊዜ የፈሪሳውያን ትልቅ ስህተት ከነበረው አንዱ ቤት ለቤት እየዞሩ የመበለቶችን ቤት መብላት ነው፡፡ በአንጻሩም ደግሞ እውነተኞች አገልጋዮች እውነተኛና ጤናማ የሆነ አገልግሎት ይዘው ወደ የቤቱ ሄደዋል፡፡ ኢየሱስም ወደ የቤቱ ሁሉ ሂዱ ስትሄዱም ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ፣ ያቀረቡላችሁንም ብሉ ያለው አገልጋዮች ወንጌልን ለመስበክም ሆነ አማኞችን በእምነታቸው ለማጽናት የቤት ቤት አገልግሎት በጣም ተፈላጊ ስለነበረ ነው፡፡ አሁንም ይህ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ በአገልጋይነት ስም  ብዙ ሰዎች ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የቅዱሳንን እምነት እየሸረሸሩ እንደሆነ በግልጽ የሚታይነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ቤት ለቤት አገልግሎትን እያስቀሩ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በቤተ ክርስቲያን የሚደረገው የፈውስ አገልሎት መልካም ቢሆንም አስተምሮአዊ መርሆ ግን ሙሉ በሙሉ እየተረሳ ነው፡፡ በያዕብ 1፡16 ላይ ማንም የታመመ ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ ራሱ ይጥራ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩ ይላል፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን ለመጣሷ ይህ ምሳሌ ነው፡፡ ሰዎች በአደባባይ ግሩም ክርስቲያኖች ቢመስሉም እቤታቸው የሚኖሩበት ሕይወት መታየት ይኖርበታል፡፡ በቤታቸው መከራን የሚቀበሉ፣ ሕይወት የተበላሸባቸው፣ የቅዱሳንን ድጋፍና ምክር የሚፈልጉ ሲኖሩ በጉባኤ አገልግሎት ብቻ መፍትሔ ልናስገኝላቸውና ልንጠቅማቸው አንችልም፡፡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ወደ እነዚያ ሰዎች በማቅናት ባሉበት ሁኔታ ሲገለግሉአቸው ይገባል፡፡ በተለይም የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከጌታ የተሰጣቸውን መንፈሳዊ ሥልጣን ከሚገልጹባቸው መንገዶች አንዱ ወደታመሙ ሰዎች ቤት በመሄድ ቃሉን ማስተማር ፣ አስፈላጊውን ምክር በመስጠት ፣በጌታ ስም ዘይት ቀብተው በመፀለይ ድዊውን የመፈወስአገልግሎት ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ጉባኤ ላይ የሚደረገው የፈውስ አገልግሎት ለወንጌል ሥርጭት ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ የሚያስተምረን ግን ማንም የታመመ ቢኖር የቤተ ክርስያንን ሽማግሌዎች ወደ ቤቱ እንዲጠራና አገልግሎቱን እንዲካፈል ነው፡፡ የቤት ለቤት አገልግሎት ቃሉን ለማስተማር፣ መንፈሳዊ ምክርንም ለመስጠት ፣ የቅዱሳንን የእርስ በርስ ህብረት ለማጠናከርና የስተት ትምህርቶች ለመከላከል የሚረዳበመሆኑ በአደባባይ ያለውን አገልግሎት ከማካሄድ ጎን ይህኛውንም ማጠናከር ተገቢ ነው፡፡ ከመድረክ አገልግሎት ይልቅ ቤት ለቤት ተዘዋውሮ ማገልገል በጣም አድካሚ ነው፣ታዋቂም አያስብልም፡፡ ስለዚህ ብዙዎች አይሞክሩትም፣ አይፈልጉትምም፡፡ በተለይም መድረክ ተኮር መጋቢዎች መዕመናን ወደ እነርሱ እንዲመጡ እንጂ ወደ መዕመናን ወርደው በቤታቸው ማገልገል አያስቡትም፡፡ ቅዱሳንን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚጠቅም የእረኝነት  ልብ ያላቸው መጋቢያን ግን የኢየሱስንና የጳውሎስን ፈለግ ተከትለው የሚያለግሉአቸውን ምዕመናን በቤትም በጉባኤም ያለግሉአቸዋል፡፡
ከጳውሎስ አገልግሎትየምንማረውሌላው ቁም ነገር የሚያገለግላቸውን ሰዎችና ቦታን ለይቶ ማወቅ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚያገለግልም ያውቅ ነበር፡፡ እርሱ በበጉባኤም ሆነ  በቤትም ያደረገው ምንድነው; ሦስቱ የአገልግሎቱ ስልቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነርሱም ማስተማር፣ በስበክ( እየመሰከርኩ አወራሁላችሁላችሁ ይላል እርሱ)ቁ 20፣ መገሰጽ( ቁ.31) ናቸው፡፡ ሐዋሪያት ፣ ነቢያት፣ አስተማሪዎች፣ የወንጌል ሰባኪዎችና እረኞች ሽማግሌዎች አሁን በእጃቸው የለውን ሕዝብ ቤቤቱ እየገቡ ቢያስተምሩ፣ ቢሰብኩ፣ በድካማሙም አባታዊና መጋቢያዊ ግሳጼ እየሰጡ ማገልገል ከቻሉ በእውነት ጠቅመዋል ማለት ነው፡፡ በዛሬው ጊዜ ወደ ሰዎች ቤት የሚሄዱ አገልጋዮች አሉ፡፡ መነሳት ያለበት ጥያቄ ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው፣ ማንስ ጋ ይሄዳሉ፣ ሄደውስ ምን ያድርጋሉ የሚለው ነው፡፡ ይህ በትክክል መለስ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ወደ ሰዎች ቤት መሄድ ያለባት ቤተክርስቲያን ናት፣ ወይም ደግሞ ቤተክርስቲያን የወከለቻቸው አገልጋዮች በዓላማና በመርሀ ግብር ፣ ያለምንም ልዩነት ወደ እያንዳዱ ምዕመን በመግባት ሕይወታቸውን ማደስ ማስተማር፣ መምከር፣መገሰጽ ይኖርቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን ሀሰተኞች ተኩላዎች መንጋውን ይበሉባቸዋል፡፡    
         

3.   አገልግሎታችን ቁም ነገርና ይዘት /substance and content/ ያለው ሲሆን ነው፡፡

ሰዎችን በአገልግሎታችን የምንጠቅመው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጠናከሩ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ በመስጠት ነው ፡፡  ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም(20-21)። አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳትዩ አውቃለሁ( ቁ.25)። የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም(ቁ 27)። ጳውሎስ እንደሚነግረን እርሱ ወደየቤቱም በየጉባኤ ምን ያደርግ ነበር  የሚለው ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ሰዎች ቤት መሄድ ወይም በጉባኤ ፊት መቆም ብቻ ሳይሆን ምን አደረጉ የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ ጳውሎስ አስተማረ፣አወራላቸው( ሰበከላቸው) ፣ በቁጥር 31 ላይ እንደምንመለከተው ያለማቋረጥ ሌሊትና ቀን ያውም በእምባ ሆኖ ይገስጻቸው ነበር፡፡ ሲሰብክና ሲያስተምርም መንፈሳዊ ቁም ነገር ያለበትን ስብከትና ትምህርት ያስተላልፍ እንደ ነበርከፍ ብሎ አይተናል፡፡ የመልእክቱ ይዘትስ ምን እንደነበር መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሰዎች ወደ ሰዎች ቤት መሄዳቸው ወይም ለአገልግሎትመድረክ ላይ መውጣታችን ብቻ ሳይሆን የምንለው ምንድነው የሚለው ደግሞ ሌላው ወሳኝ አሳብ ነው፡፡ ባለፈው ሁለት ዓመት አካባቢ ወደ ጌታ የሰበበሱቡት  ተወዳጁ የቅዱሳት መጻሕፍት አቀንቃኝ፣ አስተማሪና ሰባኪ የነበሩ ዶር ጆን ስቶት በአንድ ስብከታቸው ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “ኢየሱስ ካልተዘመረ ዘማሪው መዝሙሩን አልዘመረውም፣ ኢየሱስ ካልተሰበከ ሰባኪው ስብከቱን አልሰባከውም፣የኢየሱስ ሥልጣን ካልታከለበት ጸሎቱም አልተጸለየም”፡፡ ይህ የቀድሞ ሐዋሪያት ያደረጉት  አባቶቻችንም የተከተሉት ሲሆን እኛም ጠንክረን ሊናደርገው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ሓዋሪያው ጳውሎስ መልእክቱም ለሰዎች ያስተላፈው ስለ ንስሐና በኢየሱስ ክርስቶስ ስለማመን(ቁ 20-21)፣ እና  ስለ እግዚአብሔር መንግሥት(ቁ.25) ይስብክና ያስተምር ነበር፡፡ እንደዚህ ዓነቱን አገልግሎት ስንሰጥ ሰዎች ይጠቀማሉ፣ይጠነክራሉ፡፡ ጳውሎስ ለራሱ ጥቅምና ዝና የሆነውን ስብከት አይሰብከም፣ እንደዚያ ያለውንም ትምህርት አያስተምርም፡፡ ራሱን አያወድስም ይልቁንስ ኢየሱስን ነው ያሳየው፡፡ ያ አገልግሎቱ እስከ ዛሬ ድረስ ወደ እኛ ዘለቀ፡፡ ዛሬ በየመድረኩ የሚሰበኩትና የሚተላለፉት ስብከቶችና ትምህርቶች ምን ይዘት አላቸው የሚለው አሳሳቢ እየሆነ በመጣበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ሰውን ለማስደሰት ተብሎ በሚደረጉ ውድድሮች ከቁም ነገሩ ይልቅ ገለባው እየበዛ ነው፡፡ ከሰማያዊው ትምህርት ይልቅ ምድራዊ ብልጽግና ፣ ስኬት፣ የመሳሰሉት ይተኮርበታል፡፡ ካልሆነም ደግሞ የግለሰቦች ማንነት የኢየሱስን አዳኝነትና ክብር እስክሸፍን ድረስ አየተወራና እየተነገረ ነው፡፡ ይህንን ትምህርት እያዘጋጀሁ ሳለ ወደ አገር ቤት ሲደውልና ስለ አንዳንድ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሲጠይቅ የአንድ ዕድሜ ጠገብ  ስለሆኑ አባት ይነግሩኝ ነበር፡፡ እኒህ ሰው አቶ ባንጫ በመባል የሚታወቁ ሲሆን ዶር ላምቤ ወደ ወላይታ ገብተው ወንጌል ሲሰብኩ የዶክተሩን በቅሎ በመጎተት ከረዱአቸው ወጣቶች አንዱ ሲሆኑ በወላይታ ውስጥ ወንጌልን በማሰራጭትና ቤተ ክርስቲያንንም በመምራት ትልቅ ዋጋ የከፈሉ ሰው ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ጓደኞቻቸው ሁሉ ወደ ጌታ ተሰብስበው እርሳቸው ብቻ በሕይወት ያሉ ናቸው፡፡ ሰዎች ስለእሳቸው አገልግሎትና ታሪክ ለመጻፍ ፈልገው ሲጠይቋቸው የመለሱላቸው መልስ የሚገርም ነው፡፡ እኔ በሕይወት እያሁ የእኔን ታሪክ አትጻፉ፣ መጻፍ ከፈለጋችሁም የኢየሱስን ሥራና ታሪክ ጻፉ እንጂ የእኔን እንድትጽፉ አልፈልግም በማለት ነው፡፡ ይህ አስገርሞኛል፡፡ ሰው ራሱን ለማሳየት፣ ዝናውን ለማግኘት፣ ክብርንም ለማግኘት ብዙ ነገሮችን በሚያደርግበት ወቅት የእኔ ታሪክ አይጻፍም ማለት፣ ያውም የተሠራ የሚታይ ታሪክ እያለ አለመፍቀድ እንዴት ያለ አስደናቂ ጉዳይ ነው፡፡  በአገልግሎታችን ሰዎችን መጥቀም  የምንችለው መንፈሳዊ ቁም ነገርና ይዘት ያለበትን መልእክት ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን እውነት፣ ሥነ-መለኮታዊና አስተምህሮአዊ የሆነውን በታማኝነት ያቀረብንላቸው እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ያስተማርናቸው፣ የሰበክናቸው፣ እና በትጋት የገሠጽናቸው እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ያለዚያ እያሳሳትናቸውና እየበደልናቸው መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ እግዚአብሔር ግን ቅዱሳንን እንድንጠቅም ስለሚፈልግ ከሰጠን መንገድ አንዱ ቁም ነገርን መናር፣ ቁም ነገርን ማስተማር፣ ቁምነገርን ማድረግም ነው፡፡   

4.   በአገልግሎታችን የቁርጠኝነት ሕይወት/ Determination/  ሲኖረን ነው፡፡

አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ (ቁ.22-24) ።


አሁን ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ ነው፡፡ በዚያ ምን እንደሚገጥመው አያውቅም ግን መከራ እንደሚደርስበት ከመንፈስ ቅዱስ ተረድቷል፡፡ ቢሆንም ግን መከራ ተቀብሎም ቢሆን በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳንን በወንጌል ለመጥቀም ቆረጠ፡፡ እንዲሁም ሰዎች መከራ መኖሩን ተረድተው ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ አጥብቀው ቢለምኑትም በኢየሩሳሌም ለመሞትም እንኳ ዝግጁ መሆኑን በቁርጠኝነት ተናገረ፡፡  ሰዎች ከሚናገሩት ይልቅ ጳውሎስን ይገዛው የነበረው እርሱ የተቀበለው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ ወደ ወንጌል አገልግሎት የሚሄደው በእግዚአብሔር መንፈስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ነው፡፡ እርሱን የሚመራው የእግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ምንም እንኳ  ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የሚጠብቀው መከራና ስደት ቢሆንም በእግዚአብሔር መንፈስ ተሥሮ ወደዚያ ሥፍራ እንደሚጓዝ በግልጽ ተናራቸው፡፡  ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የሚጠብቀው መከራ ወንጌልን በመስበኩ ምክንያት ከአይሁዶች የሚደርስት ስደት ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን እርሱ ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄደው በመንፈስ ታሥሮ መሆኑን ግልጽ አደረገላቸው፡፡ በወንጌል አገልገሎት ውስጥ  ይህን የሚመስል ዋጋ መክፈል የሚስፈልገው ለምንድነው? መስዋዕትነት  ከፍሎ ማገለገል የሚያስፈልግበት ምክንያትማ የተሰጠው አገልግሎት  ስለነበረው ነው፡፡ እንዲሮጥ የተሰጠው ሩጫ ስላለ ነው፡፡ከኢየሱስ የተቀበለው አገልግሎት መፈጸም ስላለበት ነው፡፡ ይህን ሩጫ ማጠናቀቅና አገልግሎትን መፈጸም ሲባል መከራና ስደት መኖሩ በግልጽ እየተነገረም ቢሆን ወደ አገልሎቱ እንዲንገሰግሥ ያስገድደናል፡፡ ነፍሴ በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጣራታለሁ ያለው ለዚህ ነው፡፡ ይህ ሐዋሪያው ጳውሎስ ለወንጌል አገልግሎትና በወንጌል ሌሎችን ለመጥቀም ምን ያልህ እንደተሰጠ የሚመለክት ነው፡፡ እርሱ ገና በኤፌሶን ከተማ ወንጌልን መስበክ በጀመረበት ወቅት መከራና ስዴት አንዲሁም በሚሰብከው ወንጌል እውነት ምክንያት በከተማው ውስጥ ሁከት ከተነሳት ጊዜ ጀምሮ ወንጌልን በመከራ መስበክን ተለማምዷል፡፡በገና በደማስቆመንገድ ሲጠራ በጌታ ስም መከራን የሚቀበል አገልጋይ እን ደሚሆን በጌታ የተነገረለት ሰው ስለነበርና ያንን ሁሉ አልፌ እዚያጋ ስለደረሰ በኢየሩሳሌም ሰለሚጠብቀው  መከራ የሚፈራበት ምክንያት አልነበረውም፡፡   ለእግዚአብሔር አገልሎት ታማኝ የሆኑ አገልጋዮች በመከራም ውስጥ ሆነው ጌታን ያገለግሉታል፡፡ እኛ ሁላችንም እኮ ከእኛ በፊት የሄዱ ሰዎች የከፈሉበት ዋጋ ውጤቶች ነን፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን እኛ ከዳንን ይበቃናል ብለው አልተቀመጡም፡፡ ወንጌልን በብዙ መስዋዕትነት ለእኛ ሰበኩልን፡፡ እግዚአብሔር በመስዋዕትነት የምናለግለውን አገልግሎት እጅግ በጣም አድርጎ ያከብረዋል፡፡ ቁርጠኝነት ካላቸው አገልጋዮች ጋር እግዚአብሔር ይቆማል፡፡ ስለዚህ  ከጌታየተቀበልነውን አገልግሎትና ሩጫ በመፈጸም የእግዚአብሔርን መንጋ ለመጥቀም እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡  

No comments:

Post a Comment