Thursday, February 9, 2017


እግዚአብሔር ሲገለጥ

                                                                                                     ከመጋቢ ሳሙኤል ሾንጋ 

መገለጥ የሚለውን አሳብ የምንረዳበትና ለቃሉ የምንሰጠው ፊቺ እንደየሰው ሲለያይ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ መገለጥ ማለት አንድ ተደብቆና ተሸፍኖ የቆየ ነገር በግልጽ የሚታይበት ሂደት ነው፡፡ ለምሳሌ በመጋረጃ የተሸፈነ አንድ ነገር ለሰው ሁሉ ሊታይ በሚችልበት ሁኔታ የመጋረጃው ሽፋን ተነስቶ ግልጥ ሲል ነገሩ ተገለጠ እንለዋለን፡፡  ወይም መኖሩ በማይታወቅና በማይታይበት ቦታና ሁኔታ የነበረ ወይም የኖረ አንድ ነገር በድንገት ወደ እይታ ሲመጣ መገለጥ ሆነ ማለት ነው፡፡ በክረምት ጥቁር ደመና የተሸፈነችውና ከሰው ሁሉ እይታ የተሰውረችው ፀሐይ ባልተጠበቀ ሰዓት ደማናው ሲገፈፍ ሙሉ በሙሉ ግልጥ ብላ ለሁሉ ትታያለች፡፡ ያነ ፀሐይ ተገለጠች እንላለን፡፡ ይህ በመጠኑም ቢሆን የመገለጥን  ሂደት ሊያስረዳን የሚችል ነው፡፡
የእግዚአብሔርን ቃል በምንመለከትበት ወቅት ትልቁ መገለጥ እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠበት መንገድ ነው፡፡ ይህ መገለጥ ሪቨሌሺን ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሪቬላቲዮ ከተባለው የላቲን ቃል ጋር ተዛማጅነት እንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት አስተማሪዎች እግዚአብሔር ራሱን ለሰው የገለጠበትን መንገድ አስመልክተው አራት  የመገለጥ ዓይነቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ አንደኛው አጠቃላይ መገለጥ( General Revelation) ሲሆን ይህ እግዚአብሔር ራሱን በፍጥረተ- ዓለምና በታሪክ የገለጠበት መንገድ ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩ መገለጥ(Special Revelation) የተባለው ሲሆን እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍትና በልጁ በኢየሱስ በኩል ራሱን የገለጠበት ሆኖ የሰውን ልጆች ወደ ደህንነት የሚያመራ ነው፡፡ ሦስተኛው ሂደታዊ  መገለጥ ( Progressive Revelation) ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መገለጥ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የገባው ተስፋ ወይም ሊያደርገው የጀመረው ነገር ደረጃ በደረጃና በሂደት እየተከናወነና ይበልጡንም ግልጽ እየሆነ እስከ አዲስ ኪዳን የዘለቀበት ሂደት ነው፡፡ አራተኛው እግዚአብሔር በአንድ ሰው ሕይወት በግሉ የሚገለጥበት ፣ያንን ሰው በተለየ መልኩ ለዓላማው የሚጠራበት፣  በሁኔታው ላይ ጣልቃ የሚገባበትና፣ ያንን ግለሰብ በገጠመው የህይወት ተሞክሮ ውስጥ ተገኝቶ የሚናገርበት ፣ የሚያጽናናበት ወይም የሚመራበትና የሚረዳበት የመገለጥ ዓይነት ሲሆን ይህኛው  ግላዊ መገለጥ ( Personal Revelation) በመባል የሚታወቅ ነው፡፡
 በአራቱም የመገለጥ ዓይነቶች ዙሪያ አንድ ሁለት እያልን ብናወጋ ማለፊያ በሆነ ነበር ግን የዚህ ገጽ ውስንነት ስለማያላውሰን በአራተኛው የመገለጥ ዓይነት ብቻ እናተኩር፡፡ በሕይወታችን እግዚአብሔር መገለጡ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እርሱ ሲገለጥ ሕይወታቸንን ይቀይረዋል፡፡ እኛም እርሱ የተገለጠልንን ቀን ልንረሳው አንችልም፣ ሁኔታውም በፍጹም ከአእምሮአችን አይጠፋም፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈልገው በግሉ ይገለጥለታል፣ ዓላማውንም ያሳውቀዋል፡፡ ክርስትናንም ልዩ የሚያደርገው በእግዚአብሔር መገለጥና በእርሱ መታየት ላይ የሚያተኩር መሆኑ ነው፡፡  እግዚአብሔርን በግላቸው የተረዱት ሰዎች በመንፈሳዊ አኗኗራቸው ከሌሎች ይለያሉ፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ጌታ በግሉ ተገልጦለት ስላየመከራን እንኳ ቢቀበልም ከክርስቶስ መለየትና ከሰማይም ለተገለጠለት ራዕይ እምቢ ማለት አልቻለም( ሐዋ 9፣ ገላትያ፣2ኛ ቆሮ 12) ፡፡ በእርሱ ዘመን ክርስቶስን ለመከተል የወሰኑ ግን በትንሽ መከራ ወይም በመጠነኛ ድሎት ምክንያት ከመንገዳቸው የተመለሱ ብዙዎች ነበሩ፡፡  ለዚህም የገላትያ መጽሐፍ ምዕራፍ 3  እንደሚነግረን የዴማስ ሕይወት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ጳውሎስን ግን ኢየሱስን የሙጥኝ ያለው፣ ሰይፍም ቢሆን ሞት፣ ስደት ቢሆን ረሀብ፣ ከፍታ ቢሆን ዝቅታ፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን ያለውና የሚመጣ ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ካለኝ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየኝ እንዳይችል ተረድቻለሁ(ሮሜ 8፡39) እንዲል ያደረገው በሕይወቱ የታየው የእግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያንና በቤተሰብ ውስጥ አብረውን ያሉ ልጆቻችን ወይም የትዳር ጓደኞቻችን ወይም የቤተ ክርስቲያን አባላት ለጌታ የተሰጡ እንዲሆኑ እንጎተጉታቸዋለን፡፡  በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲቀጣጠሉ ጌታንም የሙጥኝ እንዲሉት እንጨቀጭቃቸዋለን፡፡ አንዳንዶቹ ወዲያውኑ የሚገርም ለውጥ ሲያመጡ አንዳንዶቹ ደግሞ ስለ መንፈሳዊ ነገር ግድ የሌላቸው ይሆናሉ፡፡ የአገልጋዮች ግፍት ወይም የቤተሰብ ጉትጎታ ሰዎችን ይሉኝታ ያስይዛቸው ወይም ደንደሳም ሃይማኖተኛ ያደርጋቸው እንደሆነ ነው እንጂ ከጌታ ጋር አያጣብቃቸውም፡፡ እግዚአብሔር በሕይወታቸው የተገለጠላቸው ሰዎች ግን የማንንም ግፍት አይፈልጉም፡፡ ሲነገራቸው እንኳ የሰማሪያ ሰዎች “የምናምነው ስለ ቃላችሁ ሳይሆን እኛ ራሳችን ሰምተነዋል እርሱ መድኃኒት እንደሆነ አውቀናል” ማለት ይጀምራሉ( ዮሐ 4፡42)፡፡ ሰዎች ጌታን እንዲወዱትና እንዲያመልኩት ከማበረታታት ጎን እግዚአብሔር እንዲገለጥላቸው መጸለይ የበለጠ ነገር ነው፡፡ 
 በእግዚአብሔርን ቃል በሁለቱም ኪዳናት ስንመለከት ጌታ በግላቸው ተገልጦላቸው ሕይወታቸውን ከለወጠላቸው  ሰዎች  የምማረው ብዙ ነገር አለ፡፡ በእነርሱ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችንም ጌታ ሲገለጥ የሚያመጣው ለውጥና ልዩነት እንዳለ በእርግጥ የታመነ ነው፡፡
·      እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ተገልጦ ምድረ በዳን ቤተ መቅደስ አድርጓል( ዘፍጥረት 21፡10-21፣ 28፡ 10-19)
የምድረ በዳ ሕይወት እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚናገር ምድረ በዳ ሰው የሌለበት ፣ እንጨት ወይም ጥላ የማታይበት፣ ውሃ የሚባል ነገርማ በፍጹም የማይገኝበት ነገር ግን ከድንጋይና ከአሸዋ ሌላ፣ እባብና ግንጥ የሚተራመስበት ደረቅና የተቃጠለ የምድር ክፍል ነው (መዝ 63፡1)  ያዕቆብ ያንን የምድረ በዳ ሕይወት ተለማምዶታል፡፡ እግዚአብሔርም በምድረ በዳ ሕይወቱ ሲገለጥ አይቶታል፡፡  በእንዲህ ዓይነቱ ሕይወት እግዚአብሔር ሲገለጥ፣ ወይም ሲታይ ፣ ወይም ድምጹን ሲያሰማ እንዴት ያማረ ነው! እንዴትስ ያለ እረፍት የሚሰጥ ነው! በምድረ በዳው ሕይወት እግዚአብሔር ሲገለጥ!
ያዕቆብ ከወንድሙ ጦር ሸሽቶ  ላባና ባቱኤል የተባሉ አጎቶቹ ወዳሉበት አገር ሲሄድ ከቤርሳቤህ ምድረበዳ  ተነስቶ ወደ አንድ ሥፍራ ሲደርስ ፀሐይ ጠለቀችበት ማለትም ቀኑ መሸበትና ሌሊቱ ገባ፡፡ አይቶት የማያውቀው አደገኛ ምድር፣  ያውም ምድረ በዳ ሆኖ ጊዜው ሌሊት አስፈሪም ጨለማ የጋረደበት ጊዜ፡፡ ይህ አስጨናቂ  የሕይወት ተሞክሮ ነው፡፡ የሚያስደስተው ግን እግዚአብሔር በዚህ ሁኔታ ለያዕቆብ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገለጠለት፡፡ እናቱና አባቱ ሲመሰክሩ በጆሮው ብቻ ሲሰማ የነበረው ያዕቆብ የአባቱንና የአያቱን የቃል ኪዳን አምላክ በአይኑ ያየው ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ምድረ በዳ ነው፡፡ በዚያ በሌሊት የድንጋይን ቋጥኝ ተንተርሶ በተኛበት አስፈሪ ስፍራ አምላኩ ተገለጠለት፡፡
መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተዘርገቶ ቅዱሳት መላእክት ሲወጡበትና ሲወርዱበት  ሲያይ ቦታው ምድረ በዳ መሆኑን ሳይረሳው እንደማይቀር  ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ መሰላል በእግዚአብሔርና በባሪያው መካከል ሲላለው እውነተኛና የማይበላሸ ው ሕብረት ምሳሌ ነው፡፡ መላእክቱ ደግሞ በምድረ በዳ ያለቺው ነፍስ የእግዚአብሔርን ርዳታ እንዲታገኝ የሚያግዙ የእግዚአብሔር አገልጋዮች አብረው መኖራቸውን የሚመለክት ነው፡፡ ምስኪኑና  ረዳት የሌለው ያዕቆብ በተኛበት ሥፍራ ከተተከለው መሰላል በላይ የተገለጠው ያህዌ የተባለው የአባቶቹ አምላክ እግዚአብሔር ማንነቱንና ለእርሱ ያለው ዓላማ በቃላት አስረዳው፡፡ በዚያ ምልክት እንኳ ማሳየት በማይቻልበት ፣አቅጣጫውን መለየት በማይታሰብበት ጭው ባለው ምድረ በዳ አምላክ ተገለጠለት ማለት ነው፡፡  ያዕቆብም እግዚአብሔር የተናገረውን የተስፋ ቃል ሁሉ ከሰማ በኋላ “ይህ ሥፍራ እንዴት ያስፈራል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም ፣ ይህም የሰማይ ደጅ ነው” አለ፡፡ ለዚህ ነው እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ሲገለጥ ምድረ በዳውን ቤተ መቅደስ ያደርጋል ያልኩት፡፡ ያውም መላእክት አምልኮን ሲያጅቡ በግልጥ የሚታይበት ድንቅ ቤተ መቅደስ!
·         እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ተገልጦ በምድረ በዳ ምንጭን አዘጋጅቷል (ዘፍ 21፡8-21)፡፡
እግዚአብሔር በምድረ በዳ ከተገለጠላቸው ሰዎች ታሪከ የአጋር ሕይወት አንዱ ነው፡፡  አጋር ለአብራሃም የወለደቺው ልጅ ሲሰቅ ያየች ሣራ የባሪያይቱ ልጅ ከይስሐቅ ጋር አይውርስምና ከልጇ ጋር እንዲያባርራት በፈቀደች ጊዜ አብርሃም አቁማዳ ሙሉ ውሃ አሸክሞአት ከነልጀዋ ከቤት አስወጣት ፡፡ እነርሱ በነበሩበት የጥንት ባህል የቁባት ልጅ እናቱን እንጂ አባቱን ስለማይወርስ ( መሳፍንት 9፡1-3) አብርሃም ከነልጇ ከቤቱ አስወጣት፡፡ አጋርም የመከራከር መብት ስላልነበራትና ዳኛም ስለማታገኝ  እርሱ ያሸከማትን እንጀራ ( ዳቦ ማለት ነው፣) የውሃ አቁማዳና ልጇን ተሸክማ ወጣች፡፡ አቁማዳ ማለት ከከብት ቆዳ የሚሠራ እንደ ከረጢት ያለ ነገር ሆኖ እንደነ ውሃ ፣ ዘይትና የወይንን ጠጅ የመሳሰሉት ፈሳሽ ነገሮችን የሚይዙበት ስልቻ ሲሆን በአብዛኛው በሰው ትከሻ ሳይሆን በአህያ ወይም በሌላ ከብት የሚጫን ከበድ ያለ ነገር ነው፡፡  አብርሃም ለመንገዷ እንዲሆንላት ካሸከማት ጓዝ ውስጥ ይህ አቁማዳ የተባለ ንቅንቅ የማይል ነገር አለበት፡፡ እርሷም ይህን ሁሉ ተሸክማ  የት እንደምትሄድ ሳታውቅ  እየተቅበዘበዘች ቤርሳቤህ ወደሚባል ምድረ በዳ ስትደርስ አብርሃም የሰጣት ውሃ ከአቁማዳዋ  አለቀባት፡፡ የሰው ውሃ ያልቃልና፣ ሲያልቅም በምድረበዳ ነውና የአጋርና የልጇ  ሕይወት አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ በተለይም ልጇ በሞትና በሕይወት መካከል ሲሆን ሞቱን በዓይኗ  ላለማየት ስትል ጥላው መሄድ ነበረባትና ርቃ ሄደች፡፡ የጭንቅ ጊዜ፣ የምድረበዳ ሕይወት ማለት እንግዲህ ይህን የሚመስል ነው፡፡ ልጇ ቢጮኽም ጩኸቱ በውስጡ እንጂ ቃሉን ለማሰማት አቅም አንሶታል፡፡ ከምድረ በዳ ቃጠሎ የተነሳ ደክሞት ተዝለፍልፎ ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን በዚህ ሁኔታ የልጁን ጩኸት ሰማ ፣ የእናቲቱንም ጭንቅ ተመለከተ፡፡ በምድረ በዳው ተገልጦላቸው አጋር የውሃ ምንጭ እንዲታይ አይኗን ከፈተላት፡፡ እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ሲገለጥ በምድረ በዳ ምንጭን ይሰጣል ይሏል ይህ ነው፡፡ ይህ መገለጥ እንግዲህ ለአጋር ለብቻዋ የታየ፣ በእርሷና በአምላኳ መካከል የተከናወነ የሕይወቷ ተሞክሮ ነው፡፡ ይህንን አብርሃም አያውቀውም፣ ለሣራም አልታያትም፡፡ ለአጋር ብቻ የሆነላት መገለጥ ነው ምክንያቱም ያለችበትን የምድረበዳ አስከፊ ሕይወት የምታውቀው እርሷና እርሷ ብቻ ናትና፡፡ ይህ ዛሬ የምድረ በዳ ሕይወታቸውን ብቻቸው እየተጋፈጡ ላሉት ወገኖች ትልቅ መልእክት ነው፡፡ አብርሃም ለአጋር እንደባሏ ፣ ለልጁ እንደ አባቱ ያደረገላቸው  ርዳታ ቢኖር ከቤት ሲወጡ ውሃና እንጀራ መስጠት ነው፡፡ ያ ግን ጊዜያዊና በምድረ በዳ የሚያልቅ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መገለጥ ያመጣላት መፍትሔ ግን ከአብርሃም አቁማዳ በላይ ሆነውን  ነው፡፡ ሰው የሚሰጠው ውሃ በምድረበዳ ቢያልቅ በእግዚአብሔር እንታመን ምክንያቱም እርሱ ውሃው ያለቀበትን አቁማዳ ሳይሆን የማያልቀውን ምንጭ የምናይበትን ዓይን ይከፍቶ ይሰጠናልና፡፡ 
ጌታ ኢየሱስ በምድረ በዳ ተፈትኗል፡፡ በምድረ በዳው ሳይረታ ሰይጣንን በሥልጣናዊ ቃሉ አሸንፏል፡፡ ዛሬም የሞተላቸው ውድ ባሪዎቹ ነፍስ በምድረ በዳ ስትቅበዘበዝና ስትጮኽ ተገልጦ ሕይወታቸውን በመለወጥ በተስፋ ቃሉ መጽናናትን ይሰጣቸዋል፡፡  ሕይወቴ ምድረ በዳ ሆነብኝ ለምትል ነፍስ  መኖሩን ያሳያታል፡፡ ያኔ ተንከራታቹ እረፍት፣ ተቅበዝባዡ እፎይታን ያገኛል፣ ሚስክኑም በክንዱ ተደግፎ ከምድረ በዳው ይወጣል፡፡ ኑሮዬ፣ ትዳሬ፣ አገልግሎቴ ምድረ በዳ ሆነብኝ ለምትል ነፍስ ሁሉ እርሱ ፈጥኖ ይደርስላታል፡፡
·         እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ተገልጦ በእሥር ቤት መውጪያን አዘጋጅቷል(ሐዋ 12 ፡-12)
እግዚአብሔር በአስር ቤት ተገልጦ እስረኛውን ከእሥር አስመልጧል፡፡ ንጉሥ ሄሮዲስ የጌታን ሐዋሪያ ያዕቆብን በሰይፍ ከገደለው በኋላ ድርጊቱ የአይሁድን ሕዝብ ደስ ስላሰኛቸው ጴጥሮስን ጨምሮ ያዘው፡፡ ጴጥሮስም እንደ ያዕቆብ ከደቀመዛሙርት መካከል  እንደ አእማድ የሚታይ ስለሆነ በአይሁዶች ዘንድ የእርሱ መታሠር ብቻ ሰይሆን መገደል ራሱ ለንጉሡ ትልቅ አክብሮትን ሊያሰገኝለት የሚችል ነው፡፡  ይህ ጊዜ በኢሩሳሌም ውስጥ ያሉ አማኞች ከአይሁዶች ብቻ ሳይሆን ከንጉሥ ሔሮድስ ጭምር ከፍተኛ መከራና  ስደት የሚቀበሉበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ጴጥሮስ በጥብቅ እስራት ተደርጎበት እያዳንዳቸው አራት ጭፍራ ባለበት በአራት ግሩፕ ወታደሮች ይጠበቅ ነበር፡፡ በሰንሰለት ታሰሯል፣ያውም በሁለት ሰንሰለት፡፡ የእሥር ቤቱም ደጆች በሙሉ በጥንቃቄ ተዘግተዋል፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን መለኮታዊ የሆነ የጦር መሣሪያ ስነበራት ያንን ትጠቀምበት ጀመረች፡፡ እርሱ “ጥብቅ ጸሎት” ይባላል፡፡ ያን መሣሪያ ተጠቅማ በእግዚአብሔር ፊት ጥብቅ  የሆነ ጸሎት ስታደርግ እግዚብሔር የወህኒ ቤቱን አልፎ ተገለጠ፡፡
ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር።እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና። ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ።ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም።የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ( ሐዋ 12፡1-11)።
 በጊዜው በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ስደት ከሃይማኖታዊ ወደ ፖለቲካዊ እንድምታ መሸጋገር የጀመረበት ሁኔታ ነበር፡፡በሐዋሪያት ሥራ 12 ላይ የምናነበው ስደት ከምንም ሁኔታ ወይም ከማንም ተነስቶ ሳይሆን ንጉሡ ሄሮዲስ በአይሁዶች ፊት ሙገሳንና ዝናን ለማግኘት ሲል ብቻ ያስነሳው ስደት ነበር፡፡ የያዕቆብ አንገት በሰይፍ ስለት መቀላቱ አይሁዶችን ሲያስፈነጥዛቸው ማየት ለሄሮዲስ ሌሎችንም ጨምሮ እንዲቀላ ወኔውን ቀሰቀሰለት፡፡ ስለዚህ ቀንደኛ የሆነውን ሐዋሪያ መግደል የተለየ ስሜት የሚፈጥር እንደሆነ ስለገመተ ጴጥሮስን ወደ ወህኒ አስገባው፡፡ ሔሮዲስ ጴጥሮስን ቢይዘውም ግን ፍርሃት እንዳለበት የሚያሳየው ለጥበቃ የተመደበው የወታደሩ ብዛት፣ የሰንሰለቱ ብርታት( አንድ ሊበቃው ሲችል በሁለት ሰንሰለት መታሠሩ)፣የብረት መዝግያውን ጨምሮ በአራት በሮች የሚዘጋ ወህኒ ቤት መሆኑ ራሱ የንጉሠ ነገሥቱን በራስ አለመተማመንና ክርስቲያኖች ተጽዕኖ አሳዳሪዎች መሆናቸው የሚያስረዳ ነው፡፡ ንጉሡ መፍራቱና እሥራቱን ማጥበቁ በሱ ቤት ተገቢ ነው ምክንያቱም በተለያዩ ጊዜያቶች ተይዞ ወደ ወሂኒ ቤት ሲጣል የወህኒው ደጆች እየተከፈቱ ከወጡት እሥረኞች አንዱ ይኸው ጴጥሮስ ነው፡፡  ስለዚህ እንዳያመልጥ በሚል 16 ወታደሮች በ4 ጭፍራ ሆን እዲጠብቁና ፣ እያንዳንዱ በር ጠንካራ መዝግያ የተጠመለት እንዲሆን አደረገ፡፡ ከውህኒ የማምለጡ ሂደት በሰው ኃይል የሚሆን ስለመሰለው ነው፡፡ ጴጥሮስ ግን በሁለት ሰንሰለት ታሥሮ በሁለት ወታደሮች መካል መካከል ተኝቶ ነበር፡፡ ትናንትና የያዕቆብ አንገት መቀላቱን ካየ በኋላ አሁን እንቅልፉን የሚለጥጠው እርሱ የማይቀላበት ምን ምክንያት ይኖራል ብሎ ነው ያስብላል፡፡ አገልግሎቴን ጭርሻለሁ ብሎ ነው? ልጅ እንዳለው ባናውቅም ቢያንስ ሚስት እንዳው በቃሉ ተነግሯልና ስለ ትዳር ጓደኛው እንኳ አያሳስበውም የሚያስብል ነው፡፡  ከእግዚአብሔር ቃል እንደምንረዳው ጴጥሮስ በእንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ገብቶም ቢሆን እንቅልፉን የተኛት ምክንያት አለው፡፡ አንደኛው ገና ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት በዕድሜው እስከ እርጅና እንደሚኖር ነግሮታል( ዮሐ 21፡18)፡፡ ስለዚህ የሚመጣበትን መከራ ሳያስብ አስጨናቂ በሚመስሉ ሁኔታው ውስጥ ያለፍርሃት የተኛ ነበር፡፡ እርሱ ቢተኛም የሄሮዲስ እቅድ በያዕቆብ እንዳደረገው የእርሱንም አንገት መቅላት ወይም በአይሁዶች ፊት በእንጨት መንጠልጠል፡፡ ነገሩ አልታወቀም ግን ይፋ የሚሆነው ሌሊቱ ሲነጋ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለ ነው እንግዲህ ከላይ እንዳነበብነው የእግዚአብሔር መልአክ በወህኒ ቤት ውስጥ የተገለጠው፡፡ ሰንሰለቱም ከጴጥሮስ እጅ የወደቀው፣ የነሐሱ ደጅ ያለ ቁልፍ ተከፈተው፡፡ በቤተ ክርስያን የሚደረገውን ጥብቅ ጸሎት የሰማው እግዚአብሔር በአደገኛ ሁኔታ ታስሮ ተስፋ ላጣው ሰው እሥራቱን ሲበጥስለት ጠላቱንም መና ሲስቀረው እናያለን፡፡ ይህ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ ጣልቃ ገብነትን የሚያሳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር በአስቸጋሪ ነገሮቻችን ጣልቃ ሲገባ  እንዴት ያለ መልስ እንደሚሰጥ ከዚህ ክፍል መረዳት ይቸላል፡፡

እግዚአብሔር በእኛ ሕይወት የሚገለጠው አንድ ጊዜ ብቻ ሰሳይ በተደጋጋሚ ፣ ሁል ጊዜም ነው፡፡ እኛ የእርሱን ርዳታ በምንፈለግበት ወቅት ወይም እርሱ ራሱ ለዓማው እኛን በሚፈልገን ጊዜ ሁሉ በሕይወታችን ይገለጣል፡፡ ትላንት ተገለጥኩላችሁ አይበቃችሁምን ያዕቆብ በረከትን ለማግኘት ሲል  ወንድሙን አታሏል የፈለገውንም በረከት አግኝቷል ግን ያ በማጭበርበር ያገኘው በረከት ሙሉና  የሚያሳርፈው  አልነበረም፡፡ በማጭበርበር የሚመጣ በረከት ለመንከራተት ይዳርጋል፡፡ እግዚአብሔር ተገልጦ የሚሰጠው የሚሰጠው በረከት ግን ያሳርፋል፣ባለጠጋም ያደርጋል፡፡ የእርስ በረከት እውነተኛ በረከት ነው፡፡
የሰው ሕይወት ደግሞ በየዕለቱ ለውጥና ተሃዲሶን የሚፈልግ ነው፡፡ የእኛ ሕይወት ትርጉም ያለው የሚሆነው የተለወጠ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔርም በተለወጠ ማንነት መሥራት ደስ ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም ሲቀረው እንመለከታለን፡፡ ይህ ማለት የያዕቆብ የሁለንተናው መቀየርን የሚያመለክት ነው፡፡ ስሙን ቀየረ ማለት ሁለመናውን ቀየረ ማለት ነው፡፡ ዛሬ እኛ የእግዚአብሔርን መገለጥ የምንፈልገው ለምን እንደሆነ ራሳችንን መመልከት ይኖርብናል፡፡ ሕይወታችን እንዲለውጥ ብለን የእርሱን መገለጥ ልንጠባበቅ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ሲገለጥ ከጓዳ እስከ የአደባባይ ሕይወታችን ድረስ ይቀየራል፡፡ የአምልኮ ሕይወታችን ይቀየራል፣ ዝማሬው ሁሉ ይቀየራል ፣ አኗኗራችንና አካሄዳችን ሁሉ ይቀይራል፡፡ እነሲሳያስ፣ እነቂስ ልጅ ሳዖል፣ የመሳሰሉት የተቀየሩት እግዚአብሔርን ስላዩ ነው፡፡ ስለዚህ በግል፣ በቤተሰብና በቤተክርስቲያን  ሕይወታችን የሚያስፈልገን የእግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡ በምድራችን መለኮታዊ መገለጥ ሲሆን እገዚአብሔርን ያየ ሁሉ ይከተለዋል ይሰግድለታልም፡፡ እግዚብሔርም ፊት ለፊት አየሁት ሰውነቴም ድና ቀረች ማለት ይጀምራል፡፡ እግዚብሔር ተገልጦ ሲነካ የሚሰብረው የአካል ክፍል እያለም የሚሰማን ግን ፈውስና ደህንነት ስሆነ ሰውነቴ ድናለች ማለት እንጀምራለን፡፡ ሁለንተናዊ ፈውስ የሚሆነው እግዚአብሔር ሲገለጥ ነው፡፡ የኢየሩሳሌም አማኞች አጥብቀው በመጸለያቸው የእግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት እነዳዩት ሁሉ እኛ ዛሬ ከምንመ በላይ ስለ እግዚአብሔር መገለጥ አጥብቀን መጮኽ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ሲገለጥ!




No comments:

Post a Comment