Thursday, April 6, 2017

ረጅም ነኝ ግን ሰሞኑን ቁመቴ የማጠሩ ነገር ኣሳሰበኝ፡፡




ረጅም ነኝ ግን ሰሞኑን ቁመቴ የማጠሩ ነገር ኣሳሰበኝ፡፡
እኔ ስለራሴ የተረዳሁትና ሰዎችም የሚመሰክሩልኝ በጣም ረጅም እንደሆንኩ ነው፡፡ እንዲያውም በቤተሰባችን ብቻ ሳይሆን በተወለድኩበት አካባቢ እንደ እኔ ያለ ረጅም ሰው የለም ማለት እችላለሁ፡፡ ለቀበሌያችንና ለወረዳችን የመረብ ኳስ ስጫወት በጣም ነበር የማስደስተው፡፡ በቤተክርስቲያን ስናገለግልም መዘምራን በደረጃ ላይ ሲቆሙ እኔ ከፊት ባለው ደረጃ ላይ ከቆምኩኝ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ከቆሙት ጋር እኩል እሆናለሁ፡፡ በኳየር አገልግሎት ጊዜ ከኋላ መቆም የማልፈልገው ጭንቅላቴ ኮርኒሱን ስለሚነካብኝ ነው፡፡ ስለዚህ ፊቴን ወደ ሌሎች መዘምራን አዙሬ ጎኔን ለጉባኤው ሰጥቼ ከዳር በኩል እቆማለሁ፣ ከዚያ መዘምራኑ ከያዙት ከየትኛውም ደብተር ላይ እያየው መዘመር እችላለሁ፡፡
ወደ ስብከት አገልግሎት ስገባ ከመዘምራን ተለየሁ እንጂ መዘምራን ሲያገለግሉ ደስ ይለኛል፡፡ የዛሬውን አያርገውና ኳየሮች የሚዘምሩት መዝሙር ለረጅም ጊዜ ከልብ አይጠፋም ነበር፡፡ በመከራም ቀን እንደ ትንቢት ቃል የቅዱሳንን ልብ ደግፏል፡፡ ለምሳሌ “ድሉ የጌታችን ነው ፣ድሉ የአምላካችን ነው ድሉ” የሚለውን መዝሙር የሰማሁት በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1973ዓ.ም ማለትም ከ36 ዓመት በፊት ነው፡፡ ሌሎችም በጊዜው የተዘመሩ መዝሙሮች አይረሱኝም፡፡ በጊዜው የወላይታ ቤተ ክርስቲያን በመራራ ስደት ውስጥ ሳለች የመሠረተ ክርስቶስ ቤክ መዘምራን ወደ ቦታው ተንቀሳቅሰው በ”ኦቶና” ዓመታዊ ኮንፍራንስ ላይ ሲዘምሩና ሕዝቡ አብሮአቸው በእምባ ሲራጭ እኔና እኩያዎቼ ከመድረኩ ፊት ለፊት በመሬት በተጎዘጎዘው ሣር ላይ እንድንቀመጥ አስተናጋጀች ስላስገደዱን እዚያው ሆኜ ነው የሰማሁት፡፡ ይህ መዝሙር ዛሬም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ትኩስ መልእክት ያለው ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በመዝሙር የማገልገል ጥማት ውስጤ ገብቶ ስለነበር እስከአሁን አራት በሚያህሉ ኳየሮች አገልግያለሁ፡፡ ታዲያ መዘምራኖቹ በቁመቴ ብቻ ሳይሆን ድምጼም ዝማሬውን ስለሚያተራምስባቸው ይቸገሩብኝ ነበር፡፡ እኔም ከመዘምራን ጋር ባገለገልኩባቸው ጊዜያቶች ቅር ያለኝ ነገር ቢኖር አብሬአቸው ፎቶ መነሳቴ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር የተነሳሁአቸው ፎቶዎቼ አብዛኛዎቹ ወይ ከአንጌቴ፣ ወይ ከፍንጫዬ በላይ የላቸውም፡፡ ጌታ ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር እንዳለኝ መጽኸፉ ስለነገረኝ እኔም ይቅር ብዬአቸው ነው እንጂ ያኔ ፎቶ ባነሱን ሰዎች ላይ ቂም ቢጤ ሁሉ ቋጥሬባቸው ነበር ፡፡አጫጭሮቹ ከእግራቸውም ከጭንቅላቸውም በሌንሳቸው እንዲገቡ ብለው እኔን ከአጭሮቹ ትክክል ቆርጠውኛልና፡፡
በቤተ ክርስያቲናችን የበረውን ትልቁን ፑልፒት አጫጭሮቹ ሰባኪዎች አይወዱትም ነበር፡፡ ያንን ፑልፒት ያስቀየረን አንዱ የእነርሱ ብሶት ነው፡፡ ፑልፒቱ ስለሚከልላቸው ከሥሩ ለእነርሱ ተብሎ የተዘጋጀ ኩርሲ አይነት ነገር ስላለ ሲሰብኩ እዚያ ላይ ይወጣሉ፡፡ ከዚያ እንደምንም ብለው ከደረታቸው በላይ ይታያሉ፡፡ ሊሰብኩ እዚያ ላይ ወጥተው "እታያለሁ?"ብለው ጉባኤውን የጠየቁ ሁሉ ነበሩ ብል ታምኑኛላችሁ? አሁን ብዙ ሲዘመር አልሰማውም እንጂ አንድ "መሸሸጊያ ዋሻ 2x መከታ ጋሻችን" የሚል ተወዳጅ መዝሙር ነበርና ከምንወዳቸው ሽማግሌዎቻችን አንዱ ይህን ምዝሙር እያዘመረ ጉባኤውን ሲመራ በተለይ መሸሸጊያ ዋሻ የሚለው ቃልጋ ሲደርሱ በዚያ ፑልፒት ሥር እየተደበቀና ከዚያም ብቅ እያለ ሲመራ ጥሩ ምሳሌ ይሆንለት ነበር:: ታዲያ ከመድረኩ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ የሚሯሯጥ ሰባኪ ያ ፑልፒት አይመቸውም፡፡ እኔ ስሰብክ ግን ያንን ኩርሲ ስለማልፈልግ ወደ ጎን አሽቀነጥረውና መሬቱ ላይ ቆሜ እንኳ ጉባኤው ከደረቴ ሳይሆን ከወገቤ በላይ ያየኝ ነበር፡፡ አስቡ እንግዲህ! የቤተክርሰትያናችን አባቶች ቅጽል ስም ሁላ አውጥተውልኛል፡፡ በጣም የምናከብራቸው የነበረ ጋሼ ጥላሁን “ሰማይ ዛፉ” ፣ “ብቅል አውራጅ”፣ ይሉኝ ነበር፡፡ ጋሼ ወልደአምላክማ በስሜ ከሚጠሩኝ “ቀውሌ” ሲሉኝ ይቀላቸዋል፡፡ ጋሼ ማሞ ደግም ልክ እንደ ጋሽ ጥላሁን “ሰማይ ዛፉ” እንደሚሉኝ ልንገራችሁ፡፡ የማታውቁኝ ወገኖቼ ምን ያህል ረጅም እንደሆንኩ በዚህ ይግባችሁ ብዬ ነው፡፡
በረዶ ካልዘነበ በቀር አንዳድ ጊዜ ከባለቤቴ ጋር በእግር እንጓዛለን( ባለንበት አገር ዎክ ይባላል)፡፡ ታዲያ የምንጓዘው እያወራን ነው፡፡ ምን አለፋችሁ ባለቤቴ ቀስ ብላ የመናገር ባሕሪይ ስላላት እሷ የምትለው እኔጋ አይደርስም፡፡ እኔ ከላይ ሆኜ ስለምናገር እያንዳንዱን ነገር ትሰማለች፡፡ ስንቸገር ለምን እኔና አንቺ በስልክ አናወራም እላታለሁ፡፡ አብረን እየተጓዝን ወደ አንድ የገበያ አዳራሽ ስንደርስ እርሷ የሆነ ዕቃ እንግዛ ብላኝ ወደ ውስጥ ስንገባ ህንዳዊው የሱቁ ባለቤት አላየንም ነበር ግን ኮሜዲኖው አጠገብ ቆመን ስናናግረው በሆነ ወንበር ላይ የቆምኩ መስሎት አንገቱን አሰግጎ ወደ ጫማዬ አየኝና "በምን ላይ ቆመህ ነው ?" ያለኝ ቀን እንዴት እንደሳቅኩ ልነግራችሁ አልችልም፡፡ የሰውዬው አባባል በአዲስ አበባ ቦሌ ቃለ ሕይወት ቤክ አገልግዬ ስመለስ አንዲት የሀብታም ልጅ የምትመስል ከእናቷ ጋር ስትሄድ ነበርና በአጠገባቸው ሳልፍ አይታኝ እንደመሞላቀቅ አድርጎአት "ወይኔ ጂሴስዬ....ሰውዬው ምን ያክላ.....ል" ማለቷን አስታወሰኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተቃራኒውም ይገጥመኝና አቤት የጌታ ሥራ እንዴት ግሩም ነው እላላሁ፡፡ ለአገልግሎት ሌላ ቦታ ካልሄድኩ በግራድ ራፒዲስ ከተማ ወደሚገኘው ካልቬሪ ቤተክርስቲያን ሄደን የጌታን ቃል እንሰማለን፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ስድስት የሙጪያና የመግቢያ በሮች አሉት፡፡ አንድ ቀን ግን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ስንገባ የመጀመሪያውን ፈረቃ ተካፍለው የሚወጣውና ሁለተኛውን ለመካፈል የምንገባው ሰዎች ዌስት ጌት (የምዕራቡ መግቢያ በር) በኩል ባለው በተላለፊያ ላይ ተገናኘን፡፡ ታዲያ በፈረንጆች አካባቢ ረጅም ሰውና ሽማግሌዎችን ማየት እንደ ልብ ስለሆነ እንደ እኛ አይገርማቸውም፡፡ ግን ያን ቀን የሚወጣው ሕዝብ ሲወጣ እኛ ደግሞ ስንገባ ከፊት ለፊቴ አንዲት ዕድሜዋ በግምት ከ25-30 ውስጥ የሚሆናት ወጣት ሴት በሕዝቡ መካከል ወደ እኛ አቅጣጫ ትመጣ ነበር፡፡ ከሰው ሁሉ ከፍ ብለን የምንታየው እኔና እርሷ ብቻ ነበርን፡፡ ግን ሆን ብላ ወደ እኔ መጣችና በአጠገበ አለፈች፡፡ ታዲያ ምን አለፋችሁ ወደ አናቴ ቁልቁል እያየችኝ ስታልፍ አንዱ ሽማግሌ ፈረንጅ ተክ ብሎ ሳቀ፡፡ አንተንም የሚበልጥ መኖሩን እወቅ የሚል ይመስላል፡፡
እኔም ይህንን ሁሉ የዘከዘኩት በቁመቴ ላዝናናችሁ ወይም ላስቀናችሁ አይደለም፡፡ ቁመቴ 6.5 ሃይት መሆኑ በህግ ተረጋግጦ በመንጃ ፈቃዴና በሌሎች ሕጋዊ ሰነዶች ላይ ሰፍሮ እያለ ሰሞኑን አጭር መሆኔ ሲነገረኝ ክው ብዬ ስለ ደነገጥኩኝ የሚያጽናና መልእክት ወይም ምክር ካላችሁ እንድትለግሱልኝ በማለት ነው እንጂ፡፡ አጭር መሆኔ የተነገረኝ ከሀኪም ወይም ከሌላ ባለሙያ አይደለም፡፡ ካለሁበት አገርም አይደለም፡፡ ከነቢያት አገር ከኢትዮጵያ ነው፡፡ አንድ ሰው በቫይበር ግሩፕ ፈጠረና እኔንም እዚያው ውስጥ አካቶኝ መልእክት ስለላከብኝ ማን አንደሆነና የእኔንም ስልክ ከየት እንዳገኘ እንዲነግረኝ መልእክት ላኩበት፡፡ ከዚያ በዚያው በቫይበር ደውሎልኝ ማእረጉን በማስቀደም ስሙን ነገረኝ፡፡ ስሙን ለጊዜው ላቆይና ወንድማችን በማዕረጉ ነቢይ ነው፡፡ ፕሮፌት …….. እባላለሁ ከኢትዮጵያ አለኝ፡፡ ማዕረግ ያልኩበት ምክንያት አሁን አሁን ወንጌላዊነት ፣ መጋቢነት ፣ ወይም ሓዋሪያነትና ነቢይነት ለአገልግሎት እንደተሰጠን የጸጋ ስጦታ ሳይሆን እንደ ማዕረግ ስለሚታይና ሰዎችም በዚያ ማዕረግ ካልተጠሩ ስለሚከፋቸው ነው፡፡ እንግዲህ አሳብ እየተለዋወጥን እያለ ጌታ ስላገናኘን አመሰገነና በሰዓቱ እግዚአብሔር ስለ እኔ የሚያሳየውን ነገር ስላለው ልነግረኝ ፈቃደናነቴን ጠየቀኝ፡፡ ፕሮፌት ነኝ ስላለ እና እኔም የነቢያትን አገልግሎት ስለማከብር ንገረኝ አልኩት፡፡ ብዙ ነገር ነገሮኝ ያንን ሁሉ በምልክት ሊያጸናልኝ ፈልጎ ማረጋገጫ በምልከት ይደረድርልኝ ጀመር፡፡ “አንደኛ፣ በ1996 ዓ. መጨረሻና በ1997 መግቢያ ላይ በሕይወትህ አንድ ነገር ሆኗል፡፡ ሁለተኛ፣ አንተ ጥቁር ሰማያዊ መኪና አለችህ፡፡ ሦስተኛ፣ በግራ እግርህ ከጉልበትህ በታኝ ቆስሎ የዳነ ምልክት አለብህ፡፡ አራተኛ አንተ ረጅም ሰው አይደለህም በቁመትህ ከአጭር ሰው ትንሽ ከፍ ትላለህ፡፡ ይህንን የምነግርህ እምነት እንዲሆንህ ነው አሜን በል፣ ” አለኝ፡፡ እኔም አሜን አልኩ፡፡ ለምን አሜን አልክ አትበሉኝ
ስለ ቁመቴ ማጠር ስሰማ በጣም ደነገጥኩ፡፡ መልሼ “እኔ እኮ በጣም ረጅም ሰው ነኝ፡፡ እንዲያውም ድሮ ከጋምቤላ አካባቢ መጥተው ለአየር ኃይል መረብና ቅርጫት ኳስ የሚጫወቱ ረጃጅም ሰዎች ነበሩ:፡ ወይም ከቦረና ነገሌ መጥተው በመረብ ኳስ ሜዳ ያገኘናቸው ሰዎች ካልሆኑ እሰከአሁን በቁመት የሚያክለኝ ሰው አልገጠመኝም፣ አንተ ደግሞ ከአጭር ሰው ትንሽ ከፍ እንደምል ትነግረኛለህ፡፡ ነገሩ እንዴት ነው?” ስለው፣ “እንግዲህ እኔ የማውቀው ነገር የለም ጌታ ያሳየኝ ይህ ነው” አለኘኝ፡፡ የቁጣ መልስ ስለመሰለኝ ጨዋታችንን እዚውጋ አበቃን፡፡ ደግሜም ያንን ሰው አላገኘሁትም፡፡
ታዲያ ምን አሳሰበህ የሚል ቢኖር ከላይ በተጠቀሱት ዓመታት በሕይወቴ የሆኑ ብዙ ነገሮች ነበሩና ትክክል ነው ብዬ ተቀበልኩ፡፡ በእግሬም ላይ ገጣባ መኖሩ እውነት ነው፡፡ በልጅነቴ የአጋም ፍሬ ለመብላት ብዬ ዛፍ ላይ ወጥቼ ከአንዱ ዛፍ ወደ ሌላ እየተሸገጋርኩ እያለ የቆምኩበት እንጨት በመሰበሩ ከከፍታ ላይ ተወርውሬ ስወድቅ ከታች የቆመው ሹልና ደረቅ እንጨት ተቀብሎኝ እግሬ ውስጥ በመሸንቀሩ ምክንያት በጣም ቆስዬ ነበርና ያ ስድን ገጣባው እዚያ አለ፡፡ መኪናዬም ጥቁር ሰማያዊ ነች፡፡ እነዚህ ምልክቶች ልክ መሆናቸውን ሳይ ነው የደነገጥኩት፡፡ ይህን ሰው ከማግኜቴ ከሁለት ሳምንታት በፊት ወደ መታጠቢያ ቤት ስገባ የበሩ የላይኘው ጉበን አናቴን ደርግሞት ስለነበር ያ አሳጥሮኝ ይሆን እንዴ ብዬም አሰብኩ፡፡ ደግሞ የተናገረው ጌታ ነው ሲለኝ እንዴት አልጨነቅም? ቁመቴን የሰጠኝ ጌታ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አምናለሁ፡፡ በቤተ ክርስቲያኔ ከእኔ ጋር አብሮ እንዲሠራ የተመደበ መጋቢ ነበርና ሰዎችን ለመገብኘት አብረን ስንሄድ እርሱ አጭር ብቻ ሳይሆን ሆዱም ላይ ቦርጭ ነገር ጣል ስላደረገችበት እንዲያው ድቡልቡል ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አብረን ስንሄድ የእርሱ አባት በርቀት ሆነው አይተውን ኖሯልና ለምን ከዚያ ከረጅሙ ጓደኛው ጋር ይሄዳል ቢቀርበትስ ምን አለበት ብለው እቤታቸው ያወሩትን ወንድሙ ሲነግረን አይዞህ ብዬ አጽናንቼዋለሁ፡፡ አንተንም እኔንም እግዚአብሔር ግሩምና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮናለልና ከእኔ ጋር ለመሄድ አትፍራ እለው ነበር፡፡ እጥረቱን ባደንቅለትም በሆድ ላይ ስለሚከመረው ቦርጭ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሁሉ እነግረዋለሁ፡፡ አጭር ሰው ቦርጭ ከበዛበት ደረቱ ላይ ይወጣበትና ወደኋላ ይለጥጠዋል፡፡እንዲያውም በእርሱ ቁመት ልክ ሆነው በጣም ቦርጫም የነበሩ አቢዬ ደመቀ የሚባሉ የእኛ አካባቢ ሰው ከቦርጫቸው መብዛት የተነሳ ሆዳቸውን ወደላይ የሚያዩ ይመስላሉ፡፡ ታዲያ አብዬ ደመቀ ጫማቸውን ማየት ስለማይችሉ ጫማቸውን ሲያስጠርጉ ሊስትሮዎቹን በጣም ሲያስጠነቅቁአቸው "ጫማዬን በደንብ ጥረጉልኝ ፣ እኔ ባላይ እግዜር ያያችኋል" ይሉ እንደነበር ሁሉ ነግሬው እንደ እርሳቸው እንዳይሆን አስጠነቅቀዋለሁ-- ከዚያ ውጭ አጫጭሮች በጣም ያስፈልጉናል እነርሱ ባይኖሩ ማን ረጅም ይለናል? እኛስ ባንኖር እነርሱንስ አጭር ማለት እንዴት ይቻላል? አንዳችን ለሌላችን እናስፈልጋለን ማለት ነው፡፡ እኔን እግዚአብሔር ግሩምና ድንቅ አድርጎ በመፍጠሩ እያመሰገንኩ ስኖር ሳለ ቁመቴ ማጠሩን ከነቢይ መስማቴ እንዴት አያስደንግጠኝ? ደግሞ ረጅም መሆኔን ነግሬው ማብራሪያ ሲጠይቀው “እኔ የማውቀው ነገር የለም እግዚአብሔር ያሳየኝን ነገርኩህ” ማለቱ በበለጠ እንዳስብ አደረገኝ፡፡ ከጌታ የተቀበልኩትን ቁመት ምንም ሳልጠቀምበት ስለቀረሁ ተወሰደብኝ ማለት ነው ብዬም አሰብኩ፡፡ ያንን ጋሽ ጥላሁንና ጋሼ ማሞ ያሉኝን ብቅል እንኳ ሳላወርድ ቀርቼ ይሆናል እያልኩ ሌሊቱን ሙሉ አሰብኩ፡፡ በአንድ በኩል ከብቅል ጋር ምንም ጉዳይ እንዳይይኖረኝ ዳግም ተወልጃለሁና ብቅል ባይወርድም ተጠያቂ አልሆንም ብዬ ልጽናና ሞከርኩ፡፡ነቢይ ኢዩ ጩፋ ቁመታቸው ያጠረ ሰዎችን አስረዝማለሁ በማለት ሲዳክር ያየሁት ስለነበረ እግዚአብሔር አጫጭሮችን እያስረዘመ እኔን ረጅሙን የሚያሳጥረኝ ምን አግኝተብኝ ይሁን ብዬ አሰብኩ፡፡ ቃሉ "ለሰው ሁሉ ከሚሆን በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም"( 1 ቆሮ 10፡13) ይለናል፡፡ ግን እኔ እኮ ለሰው ሁሉ ከሚሆን በቀር የተለየ ፈተና ገጥሞኛል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አስከ አሁን ድረስ ከእኔ በቀር ቁመቱን ያሳጠረለት ሰው አልሰማሁም አላየሁም በማለት ከጌታ ጋር በቃሉ ተሟገትኩ፡፡
ጠዋት እንደምንም ነጋልኝና ቁመቴን ለማየት ወደ ማስታወትጋ ሄድኩ፡፡ እቤታችን ያለው ማስታወት ከደረት በላይ እንጂ ሙሉ ቁመት ስለማያሳይ አልተሳካልኝም፡፡ ነገር ግን ባለቤቴ ሶፋችን ላይ ቁጭ ብላ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበች ሳለ ጠጋ ብዬ በስሟ ጠራሁአትና “ቁመቴ ማጠሩ አያሳዝንሽም?” አልኳት፡፡ ያንን ቃል ስደግምላት አይኗን ከመጽሐፉ ነቀለችና ወደ እኔ አየት ካደረገች በኋላ ወደ ንባቧ ተመለሰች፡፡ አሁንም እንደገና ጠየቅኳት ፡፡ ከዚያ እንዲህ አለቺኝ፡፡ “ምን ሆነህ ነው ደግሞ ዛሬ? ብላ ወደ ንበቧ መለስ አለች ወዲያው ደግሞ ወደ እኔ አየት አደረገቺኝና “ትላንት የት ሄደህ ነበር? ሰሞኑን የሆነ ቦታ ሄደሃል ማለት ነው? አለችኝ፡፡ እግዚአብሔር ቁመቴ ማጠሩን በነቢይ በኩል ተናረኝ ስላት የሳቀቺው ሳቅ ራሱ አስደነገጠኝ፡፡ እኔ የቃሉ አስተማሪ ሆኜ በዚህ መታሌለን እንደ መንፈሳዊ ጅልነት አድርጋ ወሰደቺውና “እግዚአብሔር ሥራ ጨረሰና የአንተን ቁመት እየለካ መዝናናት ጀመረ ማለት ነው?” አለች፡፡ እንግዲህ ነቢያት እውነተኞች ናቸው.፣ ከእግዚአብሔር ናቸው የሚባለው በምልክት የሚነገረው ነገር ካለንበት አካላዊና ማህበራዊ ነገሮቻችን ጋር መግጠሙን ስናይ አይደል? ያ ነቢይ የነገረኝ ምልክት አብዛኛው ትክክል ነው፡፡ ግን ግልጥ የሆነውን ከኢትዮጵያ እስከ አሜሪካ ድረስ ያለው ሕዝብ በአደባባይ የሚያየውን ረጅሙን ቁመቴን አጭር ያለው እግዚአብሔር ነው ሲባል ማመኔ ባለቤቴን ምን ነካህ ቢያስብላት ምን ጥፋት አለባት?እኔም ሳስበው እግዚአብሔር ስለ እኔ የመኪና ቀለምና የቁመቴ ጉዳይ ዋና አጀንዳው አለመሆኑን የነቃሁት ብዙ ከለፋሁ በኋላ ነው፡፡ ባለቤቴ ያንን ጥያቄ ባትጠቀኝና ከእኔ ጋር ብትደነግጥ ምን ልንሆን እንደምንችል ገምቱ፡፡
ከዚህ የምንረዳው ሐሰተኞች ነቢያቶች የሚባሉት ውሸት ብቻ የሚናገሩ እንዳይደሉ ነው፡፡ ሐሰተኞች እውነት በሚመስሉ በርካታ ነገሮች ውስጥ ሐሰተኛ መርዛቸውን ሸፍነው ስለሚያቀርቡ ሐሰትነታቸውን መለየት ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ በሰሙት ነገር ወዲያው የሚወሰዱ የእኔ ቢጤዎቹ በቀላሉ ይመረዛሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ያ ነቢይ በቫይበር ግሩፕ ካካተታቸው ሰዎች ውስጥ የማውቀው አንድ ወዳጄ ስለነበረ መደወል አስፈከገኝ፡፡ ስለ ሁኔታው ሳጫውተውና ነቢይ ነኝ ስለተባለውም ሰው ያውቅ እንደሆነ ብዬ ስጠይቀው የነገረኝ ነገር በበለጠ አስደመመኝ፡፡ በአገር ቤት እያለ እንደሚያውቀውና ጥሩ የሆነ የአገልግሎት ሕይወት እንደነበረውም አጫወተኝ፡፡ ነገር ግን አሁን የሰዎችን ፌስ ቡክ እየወሰደ ከዚያ መረጃዎችን ከሰበሰበ በኋላ ጌታ ተናገረኝ እያለ ወደ ሰዎች እንደሚደውል አስረዳኝ፡፡ ይህ ማለት የእኔ መኪና ቀለም ጥቁር ሰማያዊ መሆኑ የተነገረው ከጌታ ሳይሆን ከፌስ ቡክ ነው ማለት ነው፡፡የቁመቴም ጉዳይ ቢሆን ከውድ ባለቤቴ ጋር ሆኜ የተነሳሁትና ለቫይበር ፕሮፋይል ያደረግኩት ፎቶ በእርግጥም የአጭር ሰው ይመስላል ፡፡ ከእርሷ ጋር እኩል ለመሆን በደረጃ ላይ ሰበር ብዬ የተነሳሁት ስለሆነ ነቢዩ ከዚያ ሊያይ እንደሚችል ገባኝ፡፡ አንዳንዶች መዘምራን ቅኔና ወይም ዜማ ከዓለማዊ ዘፈን በመቅዳታቸው እነርሱም በዘመሩበት አማኞች በየሰፈሩ በመሰደባቸው የመጣብን ቁስል እያመረቀዘና እየጠዘጠዘን ባለበት ጊዜ የትንቢትን መልእክት ከፌስ ቡክ የሚቀዱ ደፋር ነቢያት የሚያታልሉን አጋጣሚ መፈጠሩ አስተክዞኛል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተታለሉ ስንቶች ይሆኑ? ምን ይበጃል ትላላችሁ?
LikeShow more reactions
Comment

2 comments:

  1. ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡

    ReplyDelete
  2. ሰላም ፣ ስሜ ፒተር ከካናዳ ነው። ከታላቋ ፊደል አታሚ ዶ / ር ሳንጎ ጋር አንድ አስደናቂ ተሞክሮ ማካፈል እፈልጋለሁ ፣ ባለቤቴ አጭበረበረችኝ ፣ እና እሷ ለመፋታት ምክንያት የሆነ ጠብ እንዳደረግን ሳውቅ ግን ባለቤቴን በጣም እወዳታለሁ ፣ እሷ በጣም ጥሩ እና ከባለ ገጸ -ባህሪዎች ጋር ጥሩ ቢመስልም እኔ ግን ባለቤቴ ለፍቺ ምክንያት በሆነው በእኔ ላይ እንዲያጭበረብር አልፈልግም ነገር ግን ይህ ቢሆንም እሷን በጣም ስለምወዳት አሁንም መል back እፈልጋለሁ። በመስመር ላይ የፍቅር ጥቅሶችን ስፈልግ አለቀስኩ እና ታመምኩ ፣ ሰዎች ስለ ዶ / ር ሳንጎ እና ስለ ታላቁ ሥራው ሲያወሩ አየሁ ፣ ጉዳዩ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ነበር ፣ የእውቂያ መረጃውን ትተው ሄደዋል ፣ ዶ / ር ሳንጎ አገኘሁ እና ነገረኝ ከ 24 ሰዓታት በኋላ ፍቺውን ይሰርዛል ብለው አይጨነቁ እና በሚቀጥለው ምሽት በጣም የሚገርመኝን ለማድረግ የጠየቀኝን ሁሉ ካደረግሁ በኋላ ባለቤቴ ከእኔ ጋር ትመለሳለች ፣ መልሷን እንድወስድላት እየለመነችኝ ባለቤቴ ተንበርክኮ ነበር። እና እሷ እንኳን ከወላ parent ጋር መጣች ፣ እንደገና አመሰግናለሁ ፣ ዶ / ር ሳንጎ ፣ በእውነት ለእኔ ለእኔ በረከት ነዎት ፣ እሱ ሊረዳዎ ይችላል! በኢሜልዎ ላይ Dr.Sango ን ያነጋግሩ ፤ spellspecialistcaster937@gmail.com

    ReplyDelete