Wednesday, July 18, 2018

እኛ ስንደመር ፍትሕ ይጨምር




ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር ዶር አቢይ አህመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በአገራችን እየታየ ያለው  ፈጣን ለውጥ የሚያስገርም፣ የሚያስደምምና ለማመን ሁሉ የሚያስቸግር ሆኗል፡፡ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ዲሞክራሲን ፣ ይቅርታንና መደመርን በመስበክ ከአገር አልፎ የጎረቤት አገሮችንም ትኩረት የሳበው መሪያችን በዚህ ፕላኔት ላይ የዚህ ትውልድ የመጀመሪያው ሰው ናቸው ብል እንደሚበዛባቸው አላስብም፡፡ በአሳቤ ከዚህም ያለፈ አድናቆት  ልቸራቸው ብከጅልም አድናቆትም ከልኩ ካለፈ አምልኮት ይሆናል ብሎ ልቤ ስለነገረኝ ገታ አደረግኩት እንጂ የምለው ብዙ ነገር ነበረኝ፡፡ ሰውን ማክበር፣ የሚገባውን አድናቆት መስጠትና በጸሎትም መደገፍ  በጎ ነው፣ ያማረም የተወደደም ነው፡፡
ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን 27 ዓመት ሙሉ ሲፈርስና ሲፈራርስ የኖረውን አገር በ3 ወራት ውስጥ መልሶ ለማቆም በሄዱባቸውም መንገዶች ሁሉ ስኬትን በማግኘታቸው ከሠፈር እስከ አገር፣ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ሁሉ ከአፉ የማያወርዳቸው፣ በለበሰው ጨርቅም የሳላቸው ሰው መሆናቸውን ሳይ በአንድ በኩል በደስታ እየቧረቅኩ በሌላ በኩል ደግሞ ከሰው የተወለዱ ሥጋ ለባሽ ሰው እንጂ መልአክ አለመሆናቸውን እንዳልረሳ ልቤ ስለወተወተኝ በሁለቱ መካከል ታመምኩ እላችኋለሁ፡፡
እኛ የምናውቀው እስከአሁን ድረስ የነበሩ የቀደሞዎቹ የአገራችን መሪዎች የስላም ኃይል ፖሊስና የጠብ መንጃ አፈሙዝ  መሆኑን ያምኑ እንደነበር ነው እንጂ ፍቅር የሚለው ቃል ከመሪ አፍ ወጥቶ ሲሰበክ የሰማነው በዘመነ አቢይ ነው፡፡ እነዚያዎቹ ስለአገሩ እንኳን ሲናገሩ " ለአገሬ እሞታለሁ፣ እንሙትላት" እንጂ እንውደዳት፣ እርስ በርሳችንም እንዋደድ የሚል አሳብ እንደ ኃጢአት ወይም እንደ ሽንፈት ወስደውት ሲመሩን እዚህ ላይ ደርሰናል፡፡ እንዲያው የጠብመንጃ አፈሙዝ እንጂ ፍቅር የሚባል አያውቁም ነበር፡፡ ለአፈሙዛቸውም የሰጡት የቁልምጫ ስም " ፍቱን መድኃኒት" የሚለው ነው፡፡ መቼም ሰው እግዚአብሔር የወሰነለትን ዘመን ሲጨርስ ወደ ዘላለሙ ቤት ይሄዳል፡፡ የአንዳንዶቹ መሄድ ለአገር ጉዳት ሲሆን የአንዳንዶቹ መሄድ ደግሞ ለህዝብ እፎይታና ግልግል የመሆኑ ነገር ልባችን የሚያውቀው ሆኖ የቀድሞው የሕወሓት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሲያስፈራሩ " ፍቱን መድሓኒት ተዘጋጅቷል" ይሉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ፍቱኑ መድኃኒት ለእርሳቸውም የማይሆንበት ዘመን መጥቶ አየነው፡፡ ቅዱስ ቃሉ " ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንምና" እንዳለው ሆነ ነገሩ፡፡ እግዚአብሔር እድሜአቸውን ያርዝመውና ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶር አቢይ አህመድ ሕዝብን የሚያቃልሉበትና የሚንቁበት እንደዚያ ያለ ንግግር በአፋቸው የለም፡፡  ንግግራቸውም ሕልማቸውም  ከነዚያዎቹ ይለያል፡፡ ይቅርታና ፍቅር ነው ዜማቸው፡፡  ሰውዬ ካህን እንጂ የፖለቲካ መሪም አይመስሉም፡፡ በእውነት!

ሰላም ፣ ፍቅር ፣ ይቅርታ መደመር ፣ አንድነት የሚሉ  የዶር አቢይ መርሆዎችና ንግግሮች አንጀቴን ሲያርሱት በመሳጭና ጥዑም አንደበታቸው ብሎም በሚወስዷቸው ፈጣን እርምጃዎች ሁሉ ውስጥ  "ፍትሕ" የምትለዋን ቃል ፈልጌ ፣ ፈልጌ እንደምፈልጋት ያህል  አለማግኘቴ አየር ላይ የተንሳፈፈው ሞራሌ በመጠኑም ቢሆን ዝቅ ሊል ታገለኝ፡፡ ይህ ስሜት የሚፈጠርባቸው ሌሎችም ይኖሩ እንደሆነ ገና አላወቅሁም፡፡ ዶር አብይ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ባሰናዱት የቡፌ ግብዣ ፍቅር ፣ ሰላም፣ ይቅርታ፣ መደመር፣ወዘተ የሚሉ በየዓይነቱ በርክተው ቢቀርቡም "ፍትሕ " የምትባለዋ ቃል ከተግባር ጋር ባለመታየቷ በተሟላ ድግስ ውስጥ አንድ ወሳኝ ነገር እንደተረሳ ያህል ተሰምቶኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት እጅ ለእጅ፣ እግርም ለእግር፣ ወይም ዓይን ለዐይን፣ ጥርስም ለጥርስ እንዲከፈል፣ የእሥረኛውን ሁለት እግር የቆረጠ እንደዚያው ይደረግበት፣ ባይሆን አንደኛውም ቢሆን ብቻ ይቆረጥበት ካልሆነም ዕድሜ ልክ እሥራት ይወሰንበት፣ ብልት ያኮላሸም ብልቱ ይኮላሽ፣ የእጅና የእግር ጣቶችን ጥፍር የነቀለም ጥፍሩ ይነቀል ወዘተ የሚል ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ብቀላ Talionic Justice ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በአማሪኛ አቻ ቃሉ ምን እንደሆነ ገና አልደረስኩበትምና ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡
ይሁንና በዜጎች ላይ ያንን የመሰለ ዘግናኝ ወንጀል የፈጸሙ ወይም ያስፈጸሙ አካላት ታውቀው የኢትዮጵያን ሕዝብ ግልጽ ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ያለዚያ የተያዘው መደመር ፍትሕ የጎደለበትን በደልም የደረሰበትን  ዜጋ የሚያገልል ይሆናልና፡፡ የአገርንም ሀብት የዘረፈ፣ቢያንስ መስረቁንና አገሪቱ አጥንት እስክቀራት ድረስ  የጋጠው  የምድሩን ሕዝብ ይቅርታንና ምሕረት መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
በቅርቡ በደቡብ ክልል በወላይታ ተወላጆች ላይ የተሰነዘረ ዘርንና ብሔርን ኢላማ ያደረገውን ግዲያና ጭፍጨፋ ያየው ሰብዓዊ  ማንነትና  የሰው ሕሊና ያለው ሁሉ ተጸይፎታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ የወላይታ ብሔር ተወላጆች በሜዳ ላይ ተበትነው ይገኛሉ፡፡ ዕድሜአቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ፣የሚያጠቡ እናቶች ፣ነፍሰ ጡራን፣ አዛውንቶችና አረጋውያን ከመኖሪያ ሥፍራቸው ተፈናቅለው መግቢያ ስላጡ በሜዳ ላይ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች የመብት ጥያቄ የሚመልስ አካል እስከአሁን አለመገኘቱ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ ወደ ቀድሞው ኑሮአቸው እንደሚመለሱም የተሰጠ ምንም ተስፋ የለም፡፡
መንግሥት ፍቅርን ሲሰብክ ሳለ የወንጌል ሰባኪነት አደራ ከተሰጣቸው የአዳዲስ እምነት እንቅስቃሴ ቤተ እምነቶች አንዳንዶቹ በጭፍጨፋው ጊዜ ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ እነርሱ ለሄዱ ወገኖች በራቸው በመጠርቀም ለገዳዮች ጦርና ለአራጆች ካራ አሳልፈው የመስጠታቸውን ዜና መስማት ይበልጡኑ ልብን የጎዳ ክስተት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መመስገን የሚገባቸውን አመስግነን ብናልፍ የነገራችን ሚዛን ይጠበቃል ብዬ አምናለሁ፡፡ ጭፍጨፋው ሲበረታ ነፍስ የያዛውን ተጠቂዎች እህልና ውሃ ይዘው በማስጠጋት ነፍሳቸውን ያዳኑትን የሐዋሳ አካባቢ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር ይባርክ ካላልን በጎ ሥራን አለማሰብ ይሆናል፡፡  በአካባቢ አቸው ያሉ የሲዳማ ተወላጆችን ሰዎች እንዳያጠቁ በጥብቅ የገሰጹ የወላይታ አገር ሽማግሌዎች በእርጅናቸው ይለምልሙ፡፡ ቤታቸውንም ከፍተው በመስጠት የቻሉትን ያህል ደብቀው ያቆዩልን በሐዋሳ ከተማ ያሉ ጥቂት ሰዎች እግዚአብሔር ብድራታቸውን በመልካም ይመልስላቸው ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሐዋሳ ዙሪያ ከ80 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሜዳ ላይ ናቸው፡፡ ለዘመናት ጥረው ግረው ያገኙት ንብረትና አለን የሚሏቸው ሁሉ በብሔር ተኮር ጥቃት አራማጆች የተባበረ ክንድ  ወድሞባቸው ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል፡፡ ተጠቂዎች እምባ እየረጩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጨምሮ ሌሎች የዘር ማጥፋቱን ዘመቻ የቀሰቀሱትን የመንግሥት ባለሥልጣናትን ባለመሸማቀቅ አጋልጠዋል፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ተጠያቂነትን እንዲወስዱ በመንግሥት ተወካዮች ፊት አቤቱታ ካሰሙ በኋል ያፈሰሱት እምባ እንደ ከንቱ ተቆጥሮ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በሹመት ላይ ሹመት ማግኘታቸው የተጥቂዎችን እና የቤተስቦቻቸውን ልብ ክፉኛ ጎድቶታል፡፡  ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ሕዝብን ያሳረደ  ወንጀለኛ ና ፀረ፟ ሕዝብ አጀንዳ አቀንቃኝ ሹመትና ሽልማት ከተሰጠው የፍትሕ ጥማት የሚያቃጥለው ሕዝባችን እስከ አሁን ከተጎዳው በላይ ጉዳት በጉዳት ይጨመርበታል፡፡ ይህንን ያዩ ተጎጂዎቹና ፍትሕ ናፋቂዎች ሁሉ "መደመር" የሚለው አሳብ ቢተናነቃቸው አንፍረድባቸው፡፡ በሐዋሳና በዙሪያዋ ተበታትነው የመከራን እንጀራ እየበሉና የመከራን ውሃ እየጠጡ ያሉ ሚስኪን ኢትዮጵያውያን የዶር አቢይን የመደመር መርህ እንዴት ይቀበሉታል፣ ከማንስ ጋር ይደመራሉ የሚለው ጥያቄ ከእሳት የጋለ ነው፡፡
መንግሥት በደለኛውን ይጠይቅልን እያሉ በእምባ ለጠየቁበት ምላሹ ለገዳያቸው የላቀ ሹመት ሰጥቶ ማሳየት ቁስላቸው ላይ እንጨት መክተት ሆኖባቸዋል፡፡ ለወደፊቱም በዚያ አካባቢ የመኖር ተስፋቸውን  ጭምር አጨልሞባቸዋል፡፡ ፍቅርና መደምር የሚለው ቃል የአዋሳ ዙሪያውን ጨምሮ፣ በጌዴኦ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ ፣ በአማራና በትግራይ አካባቢ ወዘተ በሕዝብ ደም የሚረኩ ወገኖች በሚቀሰቅሱት የርስ በርስ ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ያለ ፍትሕ ሊገባቸው አይችልም፡፡ ያለ ፍትሕ የፍቅር፣የይቅርታና የመደመር ውበት ለማንም የሚታይበት አግባብ የለም፡፡
ከቡድን አሳልጣኞቹ የተማረውን ዘረኝነትና የጅምላ ጭፍጨፋ ሠርቶና ለፍቶ በሚኖረው ሕዝብ ላይ በመለማመድ ጎዳናውን በዜጎች ደም ያጨቀየ፣ የወገኖቻችንን ሬሳ በእሳት የሚያቃጥሉ አሬመኔያዊ አስተሳሰብ ያላቸውን መልምሎ ያሰማራና ከሰይፉ የተርፉትንም ንብረታቸው እንዲዘረፍና ከቄያቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጋቸው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አገርን ወክሎ አምባሳደር እንዲሆን መሾሙን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ይህ ሰው የቡድን ካቦ ለመሆን የሚያበቃ የሞራል ብቃት እንኳ  የለውም፡፡ የመንግሥትን አሰላለፍ ማበላሸቱ እየታየ በሌሎች እናካክሳለን ካልተባለ በቀር የዜጎችን መብትና ሰብአዊ ማንነታቸውን  በማርከሱ ሂስ ሊወስድ እየተገባው ለኢትዮጵያ እንደራሴ እንዲሆን መሾሙ የኢትዮጵያን ክብር ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ጎማው የሚደመረው መኪናው በወጉ እንዲሽከረከር ስለሆነ የተበላሸው ጎማ በመኪናው ከመደመሩ በፊት ተገቢው ፍተሻና ጥገና ያልተደረገ እንደሆነ በመኪናው መላ ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የመኪናውን ጤና ከሚነሳ ፣ አንዴ ተበላሽቷልና የሚመጥነው ሥራ ሊሰጠው ይገባዋል እንጂ ክብ ቅርጽ ስላለው ብቻ ጎማ ነው ተብሎ በመኪና እንደማይደመር የእኔ ምክር የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡  እውነት ለመናገር  ይህንን አስጽያፊ ድርጊት የፈጸመው የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ አምባሳደርነት ይቅርብና እርሱ በደም የተበከለው እጁን ቢታጠብ፣ በዘረኝነት ሰክሮ በሕዝብ ላይ የሚያፈጥበትን  ዓይኑን ቢሰበስብ፣ የጎረሰውን ሕወሃታዊ መርዝ ቢተፋና ቢጸዳ  ትልቅ ሥራ እንደሠራ ልንቆጥር እንችላለን፡፡ እንደ ሽፈራው ሽጉጤ ያሉት  ዶር አቢይ የሚያራምዱትን በሳል ዴሞክራሲያዊና ሕዝብን ያሳታፈ ፖለቲካ ስለማይመጥኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ራሳቸው ሰውዬን ከላይ አማስለውም ይሁን ከሥር አንድደው ወደ ብስለት ያምጡት እንጂ ሹመት አይስጧቸው፡፡ ያለዚያ እንደ አቶ ሽፈራው ያሉ ሰዎች ጠቅላይ ሚንስትራችንንም ሆነ እኛን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንገት ያስደፉናል፡፡ 
የእነሽፈራው ሽጉጤ ድርጊት የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ሕዝባዊና ኢትዮጵያ፟ መር አመራርን እንዲያጠላሸው አንሻም፡፡ ሌቦችና ዘራፊዎች ፣ ነፍሰ ገዳዮችና ጨፍጫፊዎች በሕግ የሚጠየቁበት አግባብ ችላ ከተባለ ህገ፟ወጥነትና ፍትሕ አልባነት ማንሰራራቱ አይቀርም፡፡ መደመር ፣ ፍቅር፣ ሰላም ፣አንድነትና ይቅርታ በሚለው መርህ ውስጥ " ፍትሕ በተግባር" የሚለው እንዲካተትበትና እንዲያነቡትም አቶ ሽፈራውና ግብረ አባሮቹ ተጽፎእ  ቢሰጣቸው እኛ ፍትሕ የተጠማን ሁላችንም አቢይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እየዋለ ካለው ውለታ ጋር እንደምረዋለን፡፡ እኛ ስንደመር ፍትሕ ይጨምር እንጂ አይረሳ፡፡
በመጨረሻም ፍትሕን የተጠማና ሰባዊነት ያለው ሁሉ ሰለተጎዱ ወኞቻችን ደምፁን እንዲያሰማ አቤት እንላለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሐዋሳ ከተማ ዘጠኝ እናቶች በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ልጅ ወልደው ከነሕጻናቶቻቸው ጋር እዚያው ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ከመቶ የሚበልጡ እናቶችና ሕጻናት  በአንድ ክፍል በጅምላ ታፍነው ይኖራሉ፡፡ ዘመድና ቤተሰብ የሞተባቸው ሰዎች ከወላይታ መጥተው የወገኖቻቸው ሬሳ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ በጅብ ተበልቷል የሚል ምላሽ ተሰጥቶአቸው መመለሳቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አሁን ደግሞ ተፈናቃዮቹ በአስቸኳይ አካባቢውን ለቅቀው እንዲሄዱ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑ ያንን አካባቢ የጥፋት መንደር አድርጎታል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አቢይና የእኤርትራው ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ሐዋሳን ሲጎበኙና ሕዝቡም በደስታ ሲሰክር እነዚህ ተፈናቃዮች ፍትሕ ርቆአቸው በሰቆቃ ውስጥ ነበሩ፡፡  ይህ ሁሉ ሲሆን እውነታው እንዳይታወቅ ምንም ዓይነት የመገናኛ ብዙኃን ግብቶ ሁኔታውን እንዳይዘግብ መንገዶች የተዘጉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  ጉዳዩ የብዙዎችን ልብ የሰበረና የብዙዎችን ድምፅ የሚፈልግ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለእነዚህ ድምፅ አልባ ሰዎች ድምፅ እንዲሆኑላቸው ና ከዚህ የመከራ ሕይወት የሚወጡበት መንገድ እንዲገኝ በያላችሁበት ችጩኼታችሁን እንዲታሰሙ እንማጸናለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ ጠቅላይ ሚኒስትራችንንም ከቀን ጅቦቹ ቀስት ይጠብቅልን፡፡ አሜን
ሳሙኤል ሾንጋ ነኝ
      

No comments:

Post a Comment