Tuesday, July 3, 2018

ሕልም የሚመስሉ እውነቶች


በዓለም ካሉ ጎጂ ፍልስፍናዎች አንዱ በእግዚአብሔር መኖር የማያምን / ኤቲይዝም/ የሚባለው ነው። የዚህ ፍልስፍና አራማጆች በእግዚአብሔር መኖር ባለማመናቸው ሳይገቱ ሌሎችም ፈለጋቸውን እንዲከተሉ ከብረት ጠንክረው መሟገታቸው የፍልስፍናውን ጎጂነት ይበልጥ ያጎላዋል። እንደ እነርሱ ትጋት ቢሆን የአዳም ዘር ሁሉ ፊቱን ከፈጣሪው መልሶ ተስፋ ቢስ ሆኖ በቀረ ነበር። ገና ጨቅላ ወጣት በነበርኩበት ወቅት የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና መዝሙር መዘመር ከልቤ ስወድ ሳለ “እግዚአብሔር የለም” የሚለውን መርዘኛ የክህደት መለከት ሲነፉ የነበሩ ወገኖች እንዴት እንዳስጨነቁን ከቶም አይረሳም። በወቅቱ የኮሚዩኒዝም ፖለቲካ ሥርዓት በየቀበሌው ያለን ለጋ ወጣቶች “ከሁሉ በላይ አብዮቱ” የሚለውን መፈክር እንዲናስተጋባ ያስገድደን ነበር። ጉዳዩ “ከሁሉ በላይ አብዮቱ” በሚለው ሳያበቃ “ከአብዮታችንና ከአንድነታችን በላይ ምንም ኃይል የለም” የሚለው ደግሞ እጅግ የከፋው ነበር። እኔና ሌሎች ጓደኞቼ በዚህኛው መፈክርና አብሮት ተያይዞ በመጡ ጣጣዎች ምክንያት መጐዳት ብቻ ሳይሆን አሳራችንን ቆጥረናል ብል እንኳ ያለፍንበትን ጨለማና አስከፊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ አይገልጸውም። ወደ ጌታ ከተሰበሰቡት ወንድም እህቶቻችን እና አባቶቻችን በቀር በጊዜው የነበራችሁ ወንድሞቼ ጋሽ ወልዴ መኩሪያ፣ ቡታቆ ቡናሮ፣ ያዕቆብ ቦጃጐ፣ በለጠ በላቸው፣ ሳሙኤል ታንጋ፣ ሚልክያስ ወኖ ፣ አቦታ አንዳቦ፣ ባልቻ ባራታ፣ እህቶቼ አዲስ ወጋሶ፣ ንግሥት ጋሞ፣ አልማዝ ዳና ፣ አባቶቼ ጋሼ ወጋሶ ሄሊሶ፣ ወጋሶ ሻማና፣ እንድሪያስ ታንቱ እና ሌሎችም ያ የጨለማ ዘመን ያልፋል ብላችሁ አስባችሁ ነበር? በፍጹም እንዳላሰባችሁና ሥርዓቱ ሲወድቅ ወንጌል በአደባባይ ሲሰበክ ሲታዩ ሕልም እንደመሰላችሁ እርግጠኛ ነኝ። እኔ በበኩሌ ከዚያው ዘመን ጋራ ሳነጻጽረው አሁን የሚታየው ሁሉ ሕልም እስክመስለኝ ድረስ እገረማለሁ። በሁላችሁም ላይ ጠባሳው አለና ይህች ጽሑፍ ለእናንተ ማስታውሻነት ትሁን። ። በተለይም በኦፋ ወረዳ በኦኮቶ ሴሬ ቀበሌ ያሳለፍንባቸውን የጭንቅ ዓመታት ከቶውንም እንደማትረሱ ዛሬ ላይ ቆማችሁ ለእግዚአብሔር የልባችሁን ምሥጋና እንደምታቀርቡ አልጠራጠርም። የዘመኑ ሁኔታ ጠባሳ ሳይጥልበት ያለፈ አማኝ ማን ነውና! በተለይም ለመስከረም 2 የአብዮት በዓል ኪነት እንዲጨፈር ጴንጤዎች ድምጻቸው ጥሩ ነው ተብሎ በኦኮቶ ሴሬ ቀበሌ ሲያከማቹን አንጨፍርም ማለታችን ምን እንዳስከተለብን ወደ ጌታ ከተሰበሰቡት ወንድማችን አማኑኤል ጐአ፣ እህታችን ኤልሳበጥ ጐአ፣ ወንደማችን መስዋዕት ማሞ በቀር ሌሎች በሕይወት ያለነው ሁላችን በደንብ እናስታውሰዋለን። እኔ በበኩሌ በአሁኑ ጊዜ መዘምራኖቻችን መድረክ ላይ የሚያደርጉት ውዝዋዜ ከደርግ ጊዜው የኪነት ጭፈራ ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ በመሆኑ አብሬአቸው ለማምለክ እስክቸገር ድረስ ጠባሳ ጥሎብኝ አልፏል። ቃላት የማይገልጹት የጨለማ ዘመን! እናንተ ያ ዘመን አለፈ ሲባል ስትሰሙና በዓይናችሁም ሲታዩ ሕልም የምታዩ አልመሰላችሁም? ያን ጊዜ የመሠረተ ትምህርት ዘማች ሆናችሁ ወደ ኦኮቶ ሴሬ ቀበሌ የተመደባችሁና እኛን ክርስቲያን ወጣቶችን በድብቅ የእግዚአብሔርን ቃል በማስጠናትና በስደቱም ምክንያት እንዳንፈራና እንዳንንሸራተት ያበረታታችሁን ታላላቆቻችን በአዲስ አባባ ኮምፓሺን ቢሮ ያለኸው ወንድም ኢሳይያስ ኦምቦሌና በወላይታ የምትገኘው ወንድም ያሲን ሾንዴ የተባረካችሁ ሁኑ።
በቀበሌአችን እሥር ቤት እያለሁ አንድ በቤተክርስቲያን ያገለግል የነበረ ግን ጌታን መከተሉን ትቶ ከካድሬዎች ጋር የተቀላቀለ መቶ አለቃ የሆነ ሰው የጠየቀኝ ጥያቄ አይረሳኝም። ያለኝ እንዲህ ነበር ፡ “እንደዚህ እየሆንክ ኖረህ በኋላ እግዚአብሔርን ባታገኘው ምን ትሆናለህ?”። ይህ ጥያቄ በጊዜው ከእኔ አቅም በላይ ሆኖ መልስ ለመስጠት ቢያስቸግረኝም ከሰነፍ ልብ የመነጨ ፣ ከሰነፍም አፍ የፈለቀ መሆኑን የተረዳሁት በአስተሳሰብም በአካልም ጎላ ካልኩ በኋላ ነው። ያነ ገና ምርቁን ከፍትፍቱ ወደምለይበት የአስተሳሰብ ደረጃ ስላልደረስኩ ነገሮቹን መገናዝብም ሆነ ጥያቄዎቹን እንደአመጣጣቸው መመለስ ሳልችል ቀረሁ። ፈተናዬ እዛጋ ሳያበቃ ሌሎች ጥያቄዎችንም ተጠይቄአለሁ። በተለይም ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ከተዘጋች በኋላ እኔና ጥቂት የአካባቢ ወጣቶች አሁንም በአቋማችን የጸናን መሆናችንን ያዩ አንዳንዶች “ አሁን ሁሉም ነገር የለም ታዲያ እምነታችሁ ምን ይጠቅማችኋል ? ብለውናል። በውስጣችን የነበረው የጌታ ፍቅር ከእርሱ ጋር አጣብቆን እንጂ የተጋፈጥናቸው ፈታኝ ጥያቄዎች ከአቅማችን በላይ በመሆናቸው ለመመለስ አቅቶን ከሕይወት መንገድ ተንሸራትተን በወደቅን ነበር። ሰውን ሁሉ የሚረዳ እግዚአብሔር እኛንም ረድቶንና ደግፎን አለፍናቸው እንጂ ጊዜያቶቹ ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። በጊዜው በወላይታ አውራጃ በኦፋ ወረዳ ያ ሁሉ እንግልት ለደረሰባቸው አሁን በህይወት ላሉም ሆነ ወደ ጌታ ለተሰበሰቡም ሁሉ ከልቤ የሆነ አድናቆት አለኝ።
በአሁኑ ጊዜ በአገራችን አማኞች እምነታቸውን እንዲተው የሚያነቃ ካልሆነም የፍጥኝ አስሮ የሚገርፍ ወግና ሥርዓት የለም። ፈጣሪን ክዶ በራሱ ማንነት የተጠቀጠቀ፣ ለሰሚው የማይገባ እንግዳ ቋንቋ ለዜጋው ያስተማረ፣ ሰይፍ ይዞ ቤተ እምነቶችን ያሳደደ፣ አማኒያንንም በባትሪ እየፈለገ ካሉበት ጎትቶ እያወጣ በአደባባይ ያሸማቀቀ እንደ ኮሚዩኒዝም ያለ ጉደኛ ሥርዓት አንድ ቀን መታሰቢያው ተረስቶ ፣ ድብዛውም ይጠፋል ብለን አስበን አናውቅም። በተቃራኒው ለምድሪቱ በረከት የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ መሪ መታየቱ አቤቱ እግዚአብሔር “ሆላ ላንተ” አሰኝቶናል። ጊዜያቱን ለማንጻጸር ዕድል ያገኘ፣ ዕድሜም የተቸረው ሁሉ የምለው ይገባዋል። በ1972-79 ባሉት ጊዜያቶች አንድን ክርስቲያን መንገድ ላይ አቁሞ ለማዋከብ ባለሥልጣን መሆን ሳያስፈልግ ማንም ተራ ሰው እንደፈለገው ሊስፈራራው የሚችልበት፣ ደስ ካሰኘው የሚደበድብበት ሁኔታዎች ነበሩ። ጴንጤ በሰፈራችሁ ካለ አውግዙ እያለ ጓደኛን ከጓደኛ፣ ወላጅን ከልጅ የሚያለያይ የአቴና ወጊ፣ የደብተራ፣ የጥላወጊና የአስማተኛ ቅልቅል እምነት የሚወረውርብን ቀስት አንዴም ኢላማውን ስስት አንዴም በመንገድ ላይ ሲክሽፍ ኖረን አሁን ወንጌል በአደባባይ ሲሰበክ ለማየት በቃን።
መስከረም 28 ቀን 1978 ዓ.ም በጌታ ታላቄ ከሆነው ወልዴ መኩሪያ ከተባለ ወንድሜ ጋር ተይዘን ወላይታ ሶዶ ፖሊስ ጣቢያ ታሥረን ሳለ የአሥር አለቃ አማን የተባለ የጣቢያው ፖሊስ ያደረገብኝን አስታውሳለሁ። ይህን ይህል ዘመን ቆይተን ጉዳዩን አሁንም የማስታውሰው በአሥር አለቃው ላይ ቂም ቢጤ ቋጥሬበት ሳይሆን የሁኔታዎች አስከፊነት የማይረሳ ስለነበረ፣ የጨለማው ብርታት ከአእምሮ ሊፍቁ ከሚችሉት በላይ እንዲያውም ከሁለት ቀን በፊት እንደተደረገ ያህል ስለሚሰማኝ ብቻ ነው። በትክለ ቁመናው ሞላ ያለና መካከለኛ ቁመት ያለው የአሥር አለቃ አማን በጐርናና ድምጹ ጧት ጧት በስሜ እየጠራ ወደ ውጪ ያወጣኛል፣ ሁለት እጆቼን ወደ ኋላ አድርጌ ጐንበስ ብዬ እጆቼን ከሁለት እግሮቼ መካከል ወደፊት ካሾለክኩ በኋላ ዝቅ ብዬ በሁለት እጆቼ ሁለቱን ጆሮዎቼን ይዤ በዚያው ሁኔታ ጆሮቼን ሳልለቅ የፖሊስ ጣቢያውን ግቢ እንዲዞር ያደርግኝ ነበር። ሲያሰኘው ደግሞ ያለ ምንም ምክንያት በያዘው አጭር በትር በመቀመጫዬ በኩል ያላሽቀኝ ነበር። ደስ ሲለው ደግሞ ለ3 እና ለ 4 ሰዓታት ቁጥጥ ብዬ እንዲቀመጥ ያዘኝ ነበር። ቁጥጥ ማለቱ ለመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ምንም ባይሉ ደቂቃዎች በጨመሩ ቁጥር ወገብ፣ ጉልበት ፣ የውስጥ እግር፣ ባትና ታፋ የተቆራረጠ ያህል ይታመም ይጀምራል። ቅጣቱ ሲያልቅ ቆሞ መሄድ ሌላ ፈተና ነው። ይህ ከተያዝንበት ቀን ጀምሮ በየዕለቱ ከቁርስ በፊት ለሁለት ሰዓታት ያህል ከሌሎች ስፖርት ዓይነቶች ጋር የሚሰጠኝ ቅጣት ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ጓደኛዬ ወልዴ ውስጥ ሆኖ ይቃትት ነበር። ወንጀል ሆኖ ለዚህ ሁሉ ቅጣት የዳረገን “ የመካከለኛው ዘመን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” የሚል በኤስ አይ ኤም የታተመ መጽሐፍ እኔና ወንደሜ ወልዴ በእጃችን ይዘን መገኘታችን ብቻ ነው።
ዛሬ ግን በቤተክርስቲያን ላይ እንደዚያ ዓይነት ሁሉን የሚያሸማቅቅ ስደት የለም። እምነትንም የሚቃወም የለም። ሁሉም ነገር ተቀይሮ ወንጌል በየቦታው ይሰበካል፣ መዝሙራችን በሕዝብ መመላለሻ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ሁሉ ሳይቀር እየተከፈቱ ናቸው። የሚያሳዝን ቢሆንም ጫት ቃሚዎችም ጭምር ከዘፈን ይልቅ የመዝሙር ካሴቶቻችንን እየተከፈቱ ነው። ማን ያውቃል እነርሱ ለምርቃና ብለው ቢያደርጉትም ጌታ የወንጌል ድምጹን በዚያ በኩል እያስተላለፈላቸው ይሆናል ብለን እናምናለን። እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ልንገምተው በማንችለው ፍጥነት ስለቀየረው በክርስትና ምክንያት መሸማቀቅ የለም፣ አይታሰብምም። እግዚአብሔር የት አለ? አሳየኝ እያለ የሚያፈጥ ካድሬ፣ የትምህርት ቤት መምህርም አይታይም። በመንገድ ማዕዘን ላይ ቆሞ ንብረት እየቀማና አጓጉል የአካል ክፍሎቻችንን ሲመታ ታይቶ ጴንጤዎችን አዋረደ ተብሎ የሚጨበጨብለት፣ በድርጊቱም አንጀቱ ምርስለት ያበጠ ጐረምሳም የለም። ሕልም የሚመስል ግን በዓይን የሚታይ እግዚአብሔር የሠራው ታሪክ ይሏል ይህ ነው ።
ከብዙ ዓመታት ቆይታ በኋላ ቤተሰቦቼን ለመጐብኘት ወደ ወላይታ ሄጄ ባየሁትና ለማመን በሚያስቸግር ነገር ምክንያት ወደ ማረፊያ ቦታዬ ገብቼ በሩን ከኋላዬ ዘግቼ በአምላኬ ፊት ተንበርክኬ ለእርሱ ያለኝን ምሥጋና በእምባ አቀርብኩ። ምክንያቱም ያቺ የአሥር አለቃ አማን ሲያሰቃየኝ የነበረበት ፖሊስ ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ፈርሳ በቦታዋ ትልቅ የገበያ አዳራሽ ተሠርቶ፣ በላይኛው ፎቅ ላይ ባለው የካፊቴሪያ በረንዳ ተቀምጥው ሻይ እየጠጡ ስለ መንፈሳዊ ነገር የሚመካከሩ ሰዎችን ሳይ ስሜቴን መቆጣጠር ስላቃተኝ ነው። በእውነት ሕልም የማይ መሰለኝ እንጂ እውነት አልመሰለኝም ነበር። የእናት አባቶቻችን እንባ መክኖ ሳይቀር ዘመን ቆጥሮ እግዚአብሔር በምድራችን ስለመንገሡ ያነ የነበርን ሁላችንም አሁን አውራ ምስክሮች ነን።
እግዚአብሔር ዛሬም ሕልም የሚመስሉ እውነተኛ ታሪኮችን እየሠራ በዙፋኑ ላይ ነው። በክርስትና ሕይወታችንም ሆነ በአገራችን በኢትዮጵያ የሚሆነውን ስናይ ሕልም የማየት ያህል ነው። ክቡር የሰው ልጅ ደሙ በከንቱ ሲፈስ የነበረው ታሪክ በቅጽበት ተቀይሮ የአገራችን ዜጐች የሰላም አየር መተንፈስ ፣ የሰላምን ወሬ ማውራትና መስማት መቻል፣ ያውም የአምባገነኖች አምባገነን መሪዎች ሥልጣን ተቆናጥጠው ሕዝብን እርስ በርሱ በሚያጫርሱበትና በሕዝብ ደም እንጀራቸውን በሚጋግሩበት አገር አሁን የሚታየውን የሰላምና የእኩልነት ጅማሬ ማን አስቦ ነበር? እንዲያው እውነት ነው ሕልም? ብቻውን ተአምር የሚሠራው እግዚአብሔር ብቻውን ክብር ይገባዋል።

No comments:

Post a Comment