ምድራችሁን
እፈውሳለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር
Pastor Samuel Shonga
በአገራችን
ሰው ሁሉ የሚሻውና ለወገኑም የሚመኝለት ሙሉ
ጤናን ነው። ለወዳጃችን መልካሙን ስንመኝለት
አምላክ ጤናን ይስጥህ እንጂ ሁሉም ይደረስበታል
እንላለን። “ዋናው ጤና ነው” ማለት አንዳንዴ
እንደ ልማድ የሚዘወተር ንግግር ቢመስልም
ቂሉ የጤናን አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ
ጉልበታም አባባል መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
የጤንነት ጉዳይ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሻና
ከብልጥግናም የሚበልጥ ዋጋው የማይታወቅ
ሀብት ስለሆነ ብዙዎች ስለ ጤናቸው ስሉ ብዙ
ሀብታቸውን ለሕክምና ሲያፈሱት ከሚጠብቁት
ጤና ጋር ሲወዳደር ስለ መዋዕለ ንዋያቸው ምንም
አይጨነቁበትም። ጤና ቢጎደል የሀብት ክምችት
ብቻውን ባለቤቱን የሚያስደስትበት አቅም
ሊኖረው አይችልም።
የጤና
ችግር ያለበት ሰው ከምንም በላይ ፈውስ ይናፍቃል።
ዛሬ በዓለም ላይ በብዙ ሀብትና ባለጠግነት
የተጎበኙ፣ የተከማቸ ብርና ወርቅ ያላቸው፣
ዳሩ ግን ከዚያ ገንዘብ እንደ ልባቸው መመገብና
መደሰት እንዳይችሉ የጤናቸው ሁኔታ እንቅፋት
ስለሆነባቸው አምላክ ሀብት ከሚሰጠኝ ጤናን
ቢሰጠኝ ይሻለኝ ነበር የሚሉ ጥቂት አይደሉም።
የጤና ማጣት ብዙ ነገርን ሊያቃውስ የሚችል
ታላቅ የሕይወት ተግዳሮት ነው። ስለዚህ የታመመ
ሁሉ ፈውስ ያስፈልገዋል። የሚያስፈልገን ግን
መለኮታዊ ፈውስ ነው። የሥጋ ፈውስ ብቻ ሳይሆን
የምድር ፈውስም በሚያስፈልገን ወሳኝ ወቅት
ላይ እንገኛለን።
ይህንን
መልዕክት የምታነቡ ወገኖቼ ሁሉ መልዕክቱን
በልባችሁ አኑራችሁ በሕያው እግዚአብሔር ፊት
እንድትፀልዩ አደራ ለመስጠት እፈልጋለሁ።
ማንበብና መፀለይ ብቻ ሳይሆን ለምታዉቁትና
የጌታ ነገር ግድ ይለዋል ብላችሁ ለምትታመኑበት
ሰው አስተላልፋችሁ አደራ በአምላክህ ፊት
ስለ ኢትዮጵያ ፀልይ እንድትሉ በጌታ ፍቅር
እማፀናችኃለሁ። መልእክቱን ሳስተላልፍ
ማራኪና ደማቅ የአገላለጽ ዘይቤ ለመጠቀም
ያልቻልኩት የሥነ ጽሑፍ ሰው ባለመሆኔ ነው።
ስለዚሀ አንባቢያኖቼ ደካማ በሆነው አማሪኛዬ
ምክንያት የሚተላለፈውን የጌታን ድምፅ ሳታገኙት
እንዳትቀሩ አደራ።
ስለ
ራሴ ብዙ መናገር የጽሑፍ መልዕክቴ ዋና ዓላማ
ባይሆንም መቼም ትውውቅ ሳይደረግ ወደ ንግግር
ስለማይገባ ጥቂት ልበላችሁ። ተወልጄ ያደግኩት
በክርስቲያን ቤተሰብ ሲሆን የጌታን አገልግሎት
የጀመርኩት በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ
ሳለሁ የቅዱሳንን እግር በማጠብ ነበር። ቀጥሎም
በቤተ ክርስቲያን የወጣቶች አገልግሎት ፣
በወንጌላዊነትና በጌጃ ቃለ ሕይወት ቤተ
ክርስቲያን ዋና መጋቢነት ለ7 ሙሉ
ዓመታት በማገልገል የጌታን ታላቅ እጅ ለማየት
ዕድሉን አግኝቻለሁ።
ከወላይታ
ጀምሮ በናዝሬትና በአዲስ አባባ በነበረኝ
የአገልግሎት ዘመኔ ስለ አገራችን ስለ ኢትዮጵያ
ብዙ ከሚያነቡላት ጋር የማንባት ከሚቆረቆሩላትም
ጋር የመቆርቆር ዕድል ጌታ ስለ ሰጠኝ በጣም
ደስተኛ ነኝ። ስለ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ስለሚነገረው
ትንቢትና ስለምድሪቱ ይማለድ ዘንድ ስለተዋቀረው
የፀሎት ኔትወርክ ክብሩን ጌታ ሊወስድ ይገባዋል።
ከቅዱሳን ወገኖቼ ጋር ባሳለፍኩባቸው ጊዜያት
ስለ አገራችን ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ሁኔታዎች
እንድማልድ በልቤ ውስጥ ትልቅ ሸክም አደረብኝ።
ከአገሬ
ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣሁት ሐምሌ 26
ቀን 2003 ዓ.ም.
ነበር። በዕለቱ
ከባለቤቴና ከሁለት ልጆቻችን ጋር በኢትዮጵያ
አቆጣጠር ከምሽቱ 5 ሰዓት
ተኩል ከአዲስ አባባ ተነስተን ሊነጋጋ ሲል
በፍራንክፈርት ካረፍን በኃላ በማግሥቱ በአሜሪካ
ውስጥ በትልቅነትዋ ወደ ምትታወቅዋ ኒው ዮርክ
ከተማ ስንደርስ ወደ ግራንድ ራፒዲስ የሚወስደን
አውሮፕላን ስላመለጠን እዚያው ኒው ዮርክ
ማደር ግዴታችን ሆነ። የአውሮፕላኑ ሁኔታ
ቢያሳዝነንም ባለበቴና ልጆቻችን ከመንገዱ
ድካም የተነሳ በኒው ዮርክ በማደራችንና እረፍት
ማድረግ በመቻላችን ደስ ብሎአቸው ነበር።
ለእኔ ግን ያቺ ምሽት ለብቻዬ ከጌታ ጋር ስለ
አገሬ በልዩ ሁኔታ ስነጋገር ያሳለፍኩባት
የተለየች ምሽት ነበረች። ያረፍነው ራማዳ
ፒላዛ ሆቴል በተሰኘው ሥፍራ ሲሆን ወደ ሆቴሉ
ዘግይተን ስለ ደረስን ከታች ባሉ ፎቆች ክፍል
ስላልነበር ወደ 11ኛ
ፎቅ ላይ ለመዉጣት ብንገደድም ሆቴሉ ኤልቬተር
የተሰኘ መሣሪያ የተገጠመለት ስለሆነ ወደምንፈለገው
ፎቅ ለመድረስ ልፋት አልጠየቀንም። ሁላችንም
ወደ ክፍላችን ከግባን በኃላ ሥጋችንን ለመደገፍ
ጥቂት የሚበላና የሚጠጣ ነገር ሸምቼ ባመጣም
ቤተሰቦቼ ከበድ ያለ ድካም ስለ ጫጫናችውና
እንቀልፍ በኃይል ስላሸለባቸው አልተሳካልኝም።
ዳሩ ግን እኔ ጥቂት ቀማመስኩና በመስኮት በኩል
የኒው ዮርክ ከተማ በከፍል ስለምትታይ ወንበር
ሳብ አደረግኩና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው
ጥበብ ምንኛ ታላቅ ነው የሚያስኘውን የከተማዋን
ውበት ማድነቅ ጀመርኩ፡፡ ከተማው በምሽት
ለሚያይ እንግዳ ሰው በእጅ የተሠራ ብሎ ለማመን
የሚያደናግር ውበትና ለዓይንም የሚታክት
ስፋት ያለው ነው።
በዚህ
ወቅት ነው እንግዲህ እግዚአብሔርን አንድ
ጥያቄ የጠየቅሁት። ለመሆኑ ኢትዮጵያም በዚህ
ምድር ላይ ትኖራለች ፣ኒው ዮርክም ከእኛ ጋር
በዚህ ፕላኔት ላይ እኩል ኑሮ ትጋራለች ማለት
ነው? አልኩኝ።
በአገሬ ሳለሁ ስለ ኢትዮጵያ ከሚፀልየው ይልቅ
በተለየ መልክ መፀለይ የጀመርኩት ከዚያች
ሌሊት ጀምሮ ነው።
በጌታ
ፊት ከልብ በሆነ መቃተትና ምልጃ እንድቆይ
የእግዚአብሔር መንፈስ ይምራኝ ነበር። አዳሩን
በዚያ ሁኔታ ምንም እንቀልፍ የሚባል ሳያሸልበኝ
አድሬ ወደ ግራንድ ራፒዲስ ከድረስንም በኃላ
በምድሪቱ ላይ የሚታየው የልምላሜ ሁኔታ
በአገራችን በየትኛውም ክልል፣በደቡብና
በምዕራብ ካየሁት በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነው
ብል ቅንጣት ያህል ተጋኖ አይኖርበትም። ይህንን
የምነግራችሁ ሌላውን ፈርጀ ብዙ የሕዝቡን
ዕድገት ሳልጨምር የከተሞችን ድምቀትና የምድሩን
ልምላሜ ብቻ በመጥቀስ ነው። በእነዚህ የፀሎት
ጊዜያቶች እግዚአብሔር ግልጽ መልዕክት ሰጠኝ።
እግዚአብሔር
አምላክ በፀሎቴ ወቅት የተናገርኝን መልዕክት
በጣም ታዋቂ ለሚባሉ ፓስተሮች ሳካፍላቸው
ምንም ግምት አለመስጠት ብቻ ሳይሆን እንደቀልድም
ጭምር ማየታቸው ከምንም በላይ አስገርሞኛል።
ቢሆንም ለአፍሪካ ቀንድ ሸክም ተሰምቶአቸው
በጾምና በፀሎት የሚጋደሉ ወገኖችን ጌታ
አዘጋጅቶልኝ የውስጤን መልዕክት ለእነርሱ
በማካፈሌ ደስታዬ አጥፍ ድርብ ሆነ። የቱንም
ያህል ቢዘከዘክ የማያልቅ ቁጥር ሥፍር የሌለው
ጉዳይ ስላለ በጣም ሩቅ ሳልሄድ በቀጥታ ወደ
መልዕክቴ መግባት ይሻለኛል።
በፀሎቴ
“ጌታ ሆይ ኢትዮጵያን ለምን አትጎብኝም?”
እያልኩ ሳነባ ከበፊቱ
ይልቅ የተለየ መረዳት በአእምሮዬ እንዲፈስ
ያደረገው የጌታ መንፈስ ነው ብዬ አመንኩ።
ምክንያቱም እንደዚያ ዓይነት መረዳት ከዚያች
ጊዜ በፊት በአገሬ በነበርኩበት ጊዜ አልነበረኝም።
በአሜሪካ ውስጥና በካናዳ ያሉ የተወሰኑ
አካባቢዎችን ባየሁ ቁጥር የፀሎቴ ጥያቄ “
ጌታ ሆይ ኢትዮጵያ መቼ ነው የምትባርከው?”
የሚል ነበር። ይህንን
የሚለው በረከት ማለት በዓይን የሚታይ በቁሳዊና
በምድራዊ ንዋይ መንበሽበሽ እንደሆነ ከነበረንም
ልማድና ከልማዳዊ ስብከት ተጽእኖ ሥር ስለወደቅኩ
እንደነበር ብዙም አልገባኝም ነበር። የጌታ
መንፈስ ፣ መንፈስ ቅዱስ ግን “ምድሪቱ
በረከት አላነሳትም ይልቁንም ያጣችው
ፈውስ ነው”አለኝ። ይህ ድምፅ በጣም
ግራ አጋባኝ። ምን ማለት ነው በረከት አላነሳትም
ፈውስ ነው ያጣችው ማለት? ከዚህ
አሳብ በኃላ አስተሳሰቤ ተቀየረ።
በእርግጥም
አገራችን የተባረከች ናት። እግዚአብሔር
ኢትዮጵያን በብዙ አንጻር ባርኳታል። ``ምድራችን
ፍሬውን ከመስጠት አቋርጦ አያውቅም። ወንዞቻችን
መፍሰሳቸውን ቀጥለዋል። በምድሪቱ ዉስጥ
ስላለው የማዕድን ክምችት ባለሙያዎች የሚነግሩን
ዘገባ ለማመን የሚያስቸግር ነው። ይህ አሁን
የመጣ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው።
ወርቅና የድንጋይ ከሰል በቅርብ ጊዜ ትግላችን
የመጣ ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክ ከዘመናት
በፊት በምድራችን ውስጥ ያስቀመጠልን ነው።
ልዩነቱ ይህ ሁሉ መኖሩ የታወቀው ጊዜው ስለደረሰ
አሁን በመሆኑ ነው እንጂ። በፊት ያልነበሩና
አሁን የተከሰቱ ደግሞ አሉ። ለምሳሌ የሂዳሴው
ግድብ የአገራችንን የቀድሞውን መጥፎ ሥዕል
የቀየረ የዘመኑ አስደናቂ የሰው ልጅ ሥራ ነው።
ታዲያ አገራችን አልተባረከችም ሳይሆን
እግዚአብሔር የሰጣትን በረከት አልተጠቀመችበትም
ነው ማለት ያለብን። የጌታ መንፈስ በግልጽ
የነገረኝ ይህንን ነው። “እግዚአብሔር
ኢትዮጵያን በሁሉም አንጻር ባርኮአታል ነገር
ግን አገሪቱ መባረክዋን ገና አልተረዳችምና
ባረከኝ ትላለች። የምድሪቱን ፍሬ ሕዝቦችዋ
መብላት አልቻሉም። ፍሬዎች ስል የሰብል ፍሬ
ማለቴ ሳይሆን ለማንኛውም ዕድገት ምክንያት
የሚሆኑ የአገሪቱ ብርቅ ልጆች፤ ምሁራን፣ህስቶሪያንስ፣
የህክምና ዶክተሮች፣ መሀንዲሶች፣ፕሮፌሰሮች፣የሂሳብ
ባለሙያዎች በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣
በካናዳ እና በስካንዲኒቪያ አገሮች ተበታትነው
የሚገኙትን ማለቴ እንደሆነ ልብ ያለው ሁሉ
ልብ ይበል። እነዚህ በረከቶቻችን አይደሉም
ወይ? በእርግጥ
ከእግዚአብሔር የተሰጡን በረከቶቻችን ቢሆኑም
አልተጠቀምንባቸውም። እግዚአብሔር ባርኮናል
እኮ። በውጭ ዓለም ያሉ ሰዎች ስለ እኛ የነበራቸው
ግምት ረሀብተኞች፣ ለማኞች፣ጨካኞችና ጦረኞች
እንደሆንን ነው። አንዳንዶቹ እንዲያውም
የምናድርበት ቤት፣የምንለብሰው ጨርቅ እንኳን
የሌለን ይመስላቸዋአል። ለዚህ ነው ስንተዋወቃቸውና
ከኢትዮጵያ ነን ስንላቸው አንዳንዶቹ በአእምሮአቸው
ካለው ሥዕል የተነሳ እዝን ትክዝ ብለው ያዩንና
እንኳን ደህና መጣህ! እዚህ
አገር ስለ መጣህ በጣም ደስ ብሎሃል አይደል?
ይላሉ። ሌላ ጊዜ
ስንገናኝ ደግሞ ጨዋታውን ከበፊቱ ጨመር
ያደርጉና ስለ አኗኗራችን እንድናውራላቸው
ይፈልጋሉ። ቤት አላችሁ? ምግብ
አብስላችሁ ነው የምትበሉት ? ልብስ
መልበስ የጀመርከው መቼ ነው? ይሉናል።
ስንነግራቸው እውነት አልመስል ይላቸዋል።
ይህንን ሳይ ልቤ ከመጠን በላይ ያዝናል።
ለምነድነው ብዬ ሳስብ ለካ አንዳንድ አገር
ጎቢኚዎች ወደ እኛ ሲመጡ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ
ሕዝቦች፣ቋንቋና ባህል ባለቤት እንደመሆንዋ
መጠን በአንዳንድ አካባቢዎች ራቁታቸውን
የሚሄዱ ወገኖቻችንን ፎቶ አንስተው ቪዲዮም
ቀርጾአችው ይመጡና ሌላውን አካባቢ ሳያሳዩ
ኢትዮጵያ ይህን ትመስላለች ብሎአቸው ኖሮአል።
አንዳንድ ተንኮለኛ አገር ጎብኚ አይጥፋምና።
ስለዚህ ነው ምንኖረው እቤት ውስጥ ሳይሆን
እውጭ፣ ሁላችንም ልብስ ሳንልብስ ራቁታችንን
የምንሄድ የመሰላቸው እንጂ በርግጥ የተባለውንም
ያህል ረሀብተኞች ሆነን አልነበረም። የውጭ
አገር ጎብኚዎች ብቻ ሳይሆኑ የአገራችንም
ሰዎች ከሆኑት አንዳንዶች ከፈረንጆች የገንዘብ
ድጋፍ ሊያገኙ ሲሉ የሚጠቀሙባቸው ቪዲዮችና
ፎቶግራፎች ገጽታችንንና ምሥላችንን ሊያበላሹ
እንደቻሉ ምንም አልጠርጥርም። ይህንን
ለማረጋገጥ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጀቶች
የሚሠሩ ሰዎች ካሜራ ይዘው ወደ አንድ መንደር
ሲገቡ ማየት ብቻ በቂ ነው። የእነሱ ካሜራ
የሚያውቀው ደሳሳ ቤት፣ ጫማው የተቀዳደደ
ሚስኪን ለማኝ፣ጭራሮ የጫነ አህያ የሚነዳ
ሽማግሌ ፣ ቁምጣ ሳይኖረው በባዶ እግሩ እየሄደ
በጭቃ የመንከባለል ሕፃን ፣በሆነ ህመም
ምክንያት ሰውነቱ የገረጣ ሰው ወዘተ እንጂ
እንዲያው ሌላ የተሻለ ነገር ካሜራቸው ያየዋል
ወይ? ፎቶስ
ያነሱታልን? ካልሆነ
ደግሞ ፈንዱን ማግኘት ቀላል ላይሆን ይችላልና
መፍረድ ቢያስቸግርም አሳዝኙ ነገር ፎቶ
የሚያነሷቸውና በቪዲዮ የሚቀርጿቸው ሰዎች
ከሚመጣው ገንዘብ ጋር ሳይተያዩ ከቀሩ ነው።
እንግዲህ ይህን የሚምስሉ አጥር የጣሱ ነገሮች
ገጽታችንን አበላሹት እንጂ አገራችንማ ሀብታም
ነች።
የሰው
ኃይል የአገሪቱ በረከት ነው። ሰዎችና ሙያቸው
ለአገሪቱ ዕድገት ወሳኝ ነበር። ዳሩ ግን
የተማሩ ወንድሞቻችን እህቶቻችን በሙያቸ
ሌሎች አገራትን እያሳደጉ ናቸው። ታዲያ ለምን
አልተጠቀምንባቸውም? መልሱ
ግልጽ ነው፣ ምድሪቱ ፈውስ ያስፈልጋታል።
አገራቸውን ስላልፈለጉት ነው? በጭራሽ!
እነዚሀስ በረከቶቻችን
አይደሉምን? ያለ
ምንም ጥርጥር በረከቶቻችን ናቸው። በአሜሪካን
አገር ታላላቅ ሥራዎችን የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን
ሳይንትስቶች ለምን በአገራቸው አልሠሩም?
ምድሪቱ ገና ስላልተፈወሰች
ብቻ ነው። ሁሉም ነገር መልካም ነው ብንልም
ልንክድ በማንችልበት ሁኔታ ጭንገፋው በዝቶአል።
ጭንገፋና ሞት አለ፣በሽታ አለ፣ ያልተነቀለ
ርግማን አለ፣ያልደረቀ ቁስል አለ፣ያልታበሰ
እምባ፣ያልተከፈለ የደም ዕዳ በምድሪቱ ላይ
አለ። የምድሪቱ ፍሬዎች ጨንግፈዋል። ፍሬው
ጨነገፈ ስል ለጊዜው የእርሻ ቡቃያ ማለቴ
ሳይሆን ብርቅና ውድ ልጆችዋን ማለቴን ከፍ
ብሎ ጠቅሼአለሁ። ኢትዮጵያ ፍሬዎችዋ ለምን
ጨነገፉ? መልሱ
ግልጽ ነው። ምድሪቱ የተባረከች ሆና ሳለ ፈውስ
ስላልፈጠነ ነው። እንጀራቸውን በግፍ ተቀምተው
ያለቀሱ፣በዓይናቸው ፊት ልጆቻቸው የተገደለባቸው
ወላጆች፣ወላጆቻቸው የተገደለባቸው ልጆች
ያለቀሱበት እምባ ገና አልታበሰም ይለኛል
የእግዚአብሔር መንፈስ። እግዚአብሔር የነገረኝ
ሌላ አስገራሚ ነገር አለ። በምድሪቱ ደም
የፈሰሰው ከውጭ በመጣ ወራሪ ጠላት ሳይሆን
በወገናቸው ላይ በሚጨክኑ በምድሪቱ ሰዎች
ነው። ይህ የበቀለኝነት መንፈስ አሁን በስውር
እየሠራ ያለበት ጊዜ ነው። አንድ አስቂኝ የሆነ
መፈክር በጣም ትዝ ይለኛል። “ይውደም” የሚል።
በወቅቱ አድኃሪ ይውደም፣አቆርቋዥ ይውደም
እገለ ይውደም ፤ ጴንጤ ይውደም ሲባል እንደ
ነበር በደንብ አስታውሳለሁ። ይውደም የሚለው
ማንን ነው? ያው
ወገኑን ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላውን ጠላት
አልነበረም። ያ ሥርዓት እንዳለውም ብዙ ነገር
አውድሞ በመጨረሻም ራሱ ወደመ። ያኔ አሁን
የሚታየው ማዕድን አልነበረምን?
አባይስ ደርቆ ነበር
እንዴ? ምን
ነበር ቸግሩ? በማውደም
የሚያምን እግዚሔር የለሹ ሥርዓት እግዚአብሔርንም
የለም አለ፣እግዚአብሔር የፈጠረውንም ይውደም
አለ፣ አስባለ፣በምድሪቱም የእርስ በርስ
መራገም አስለመደ ። ያ ውድቀት ተንሰራፍቶ
ስለ ቆየ ህዝባችን ከደቀበት ለመነሳት ረዥም
ጊዜ ፈጅቶበታል። አሁን በእግዚአብሔር ርዳታ
የትንሣኤ ተስፋ ቢታያትም ምድሪቱ ፈውስ
ያስፈልጋታል።
አገራችን
የምግብ ዋስትና ለማረጋግጥ ከሚሠሩ አገሮች
ተርታ ተሰልፋ በዓለም በምሳሌነት መጠቀሷ
የሁሉንም ትኩረት ከመሳቡም በላይ ኢትዮጵያውያንና
ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ያኮራ የተወደደም
ንግርት ነው። አርሶ አደሩ ከምን ጊዜም በላይ
በእርሻ ከፍተኛ ምርት በማግኘቱ ኑሮው ተሻሽሎለታል
የሚለውን ዜና መስማት ኢትዮጵያ በበረከት
ጎዳና ላይ መገኘቷን የሚያመላክት በመሆኑ
እጅግ ደስ ይለናል። የሌላውን አላውቅም በውጭ
አገር እንደ መኖሬ መጠን ይህን የመሰለ ዜና
ስሰማ የአገሬ ናፍቆት በምን መጠን እንደሚጨምር
ማስረዳት ለእኔ በእውነት የከባድ ከባድ ነው።
የማቃቸው ትናንሽ የገጠር ወንዞች ሁላ የስፉና
የጎለበቱ የሚመስለኝ ጊዜ አለ። ሰው ሁሉ
ችግርን ወግድ ያለ፤ የምግብ እጦት ከምድሪቱ
ጥርግርግ ብሎ የወጣ የሚመለኝም ጊዜ ጥቂት
አይደለም። ዳሩ ግን ይህ ሁሉ እየተነገረ ጉርሻ
በገንዘብ እየተሸጠ መሆኑን ማየት ደግሞ በጣም
ያሳዝናል። የሚያሳዝነው ጉርሻው መሸጡ ብቻ
ሳይሆን ቡፌ እንደሚጠብቅ የሠርግ ቤት እድምተኛ
ነፍሱን በጉርሻ ለመታደግ ተራውን በሰልፍ
የሚጠብቀው ሰው ብዛት ነው። የብዙዎች ልብ
ይህንን ሲያይ እንደሚሰበር አያጠራጥርም።
ይህ የሆነው ለምንድነው? በምድሪቱ
ፍሬ ለሕዝቦችዋ አንሶ ሳይሆን የበረከት ሁሉ
በረከት የሆነው መለኮታዊ ፈውስ ገና ስላልተገለጠ
ነው። ኦ! ፈውስ
ያስፈልገናልና እግዚአብሔር አምላክ በእውነት
ምድራችንን ይፈውሳል!!
እግዚአብሔር
የሰጠን በረከቶቻችን የምንላቸው ልጆቻችን
ሲሆኑ ለምድራችችን ጌታ የሰጠን ትልቁ በረከት
የሰው ኃይል ነው። የአንዲት አገር ልማትም
የሚፋጠነው ባለው በሰው ኃይል መሆኑን ማንም
ሊክደው አይችልም። የአገራችን የሰው ኃይል
ግን በየትኛውም ቀዳዳ ቢሆን ከአገሪቱ መውጣትን
ይፈልጋል። እውነት እንነጋገር ካልን ከቄስ
እስከ መጋቢ ከኢትዮጵያ ይልቅ በውጭ መኖርን
ይፈልጋል ። አንድ ሰው በሆነ አጋጣሚ አንዴ
ወደ ውጭ ከወጣ እግዚአብሔር ስለተናገረኝ
እዚህ አገር አገለግላለሁ ይልና ይቀራል።
ይህንን ልምምድ ያመጡት ታላላቅ መሪዎቻችን
ናቸው። በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን
ዘንድ ቀዳሚ መሪዎች ያልናቸው በምክንያት
የአሜሪካን ምድር ይርግጧትና ጌታ ተናገረኝ
በሚል መንፈሳዊነት ሰምጠው ይቀራሉ። በእርግጥ
ጌታ የሚናገራቸው ቢኖሩም ለአብዛኛዎቹ
የሚነግራቸው ልባቸው እንጂ ጌታ አይደለም።
ይህ ለምንድነው የሚሆነው የሚል ካለ ቤተ
ክርስቲያንም ራሷ ካልተፈወሰች ፈውስ ልታመጣ
ስለማትችል ነው። ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከአገልጋይ
እስከ ምዕመን ደስ የሚለው ከኢትዮጵያ ይልቅ
በአሜሪካ ቢኖር ነው። ይህንን አንድ በሚገርም
ገጠመኝ ባስቀምጥ ደስ ይለኛል። የማስተር
ዲግሪዬን ለመሥራት ወደ አሜሪካ ስገባ ሌላ
ሰው የአፍሪካ አገር ከሆነችው ከማላዊ ከነቤተሰቡ
ለተመሳሳይ ፕሮግራም መጥቶ በአንድ ሰሚናሪ
ውስጥ መማር ጀመርን። ሁለታችንም የምንሠራው
ማስተር በሁለት ዓመት የሚጠናቀቅ ፕሮግራም
ቢሆንም እርሱ አስቀድሞ በርቀት ትምህርት
ፕሮግራም በርከት ያሉ ኮርሶችን ወስዶ ስለ
ነበር ከእኔ ቀድሞ አጠናቀቀና ቶሎ ብዬ ወደ
አገሬ ልሂድ ዲግሪውንም ቢሆን በፖስታ ላኩልኝ
ብሎ ሄደ። የምረቃው ጊዜ ደረሶ ውጤቱን እስክቀበል
ድረስ እንኳ ሊቆይ አልፈለገም። የእሱ ሲገርመኝ
ባለቤቱና ልጆቹ ወደ ማላዊ ተመልሰው እንደሚሄዱ
ካወቁበት ጊዜ አንስቶ በፊታቸው ይታይ የነበረው
ደስታ በቃላት የሚገለጽ አልነበረም። በተቃሪኒው
ደግሞ ትምህርቴን ስጨርስ ወደ ኢትዮጵያ
እንሄዳለን ስላቸው የእኔ ልጆች ምንም መልስ
ሳይሰጡ ቃልም ሳይተነፍሱ ወዲያው ፊታቸው
ሲለዋወጥና ዓይናቸው እንባ ሊያፈስ ሲከብድ
ሳይ ግራ መጋባት ውስጥ መውደቄን አስታውሳለሁ።
በእውነት አሁን ማላዊ ከኢትዮጵያ የተሻለች
አገር ሆና ነው? ብዬ
አልኩ፣ ሰውንም ለመጠየቅ ሞከርኩ። በእውነት
እላችኃለሁ የሰማሁት ነገር አገራችን በብዙ
እንደምትበልጥ ነው። ታዲያ ለምንድነው ታላላቅ
ኢትዮጵያውያንም ጭምር ከአገር መውጣትን
እንደ ስኬት የሚቆጥሩት ወይም ከአገር የወጡ
ዕለት የግልግል ስሜት የሚሰማቸው?
ብዬ ራሴን ጠየቅኩ።
በረከት አንሶ ሳይሆን ፈውስ ስላልተገኘ ነው
መልሴ። አሜሪካንና እንግሊዝ ፈረንሳይና
የዓረቡ ዓለም ተፈውሰዋልና ነው ሕዝባችን
ወደ እነዚያ የሚኮብልለውና የሚጎርፈው?
የሚል ጥያቄ ቢኖር
ግን ለዚህ የሚሆን መልስ የለኝም። ምን ይሁን
ምን እግዚአብሔር ምድሪቱን እፈውሳለሁ ብሎኛል።
በለጽገዋል
ወደ ተባሉት የምዕራቡ አገሮች ሄዶ መኖር ሌላ
ነገር ነው። ወደ አሜሪካና ወደ ካናዳ የሚከደው
የበልፀጉና ያደጉ ስለሆኑ በትምህርትም ሆነ
በሌላ እንጠቀምበታለን፤ ኑሮአችንም ይሻሻልልናል
በሚል ነው እንበል። ዳሩ ግን በአፍሪካ አገሮች
ስለ ተበታተኑት ኢትዮጵያውያን ምን እንላለን?
ሌላው ቢቀር በኢትዮጵያ
ከመኖር ይልቅ በጅቡቲ መኖር የተሻለ እንደሆነ
ተቆጥረው ወደዚያ የሚኮበልሉ ወገኖቻችን
ጉዳይስ ምን ሊባል ነው? አሁን
አሁን እንዴት እንደሆነ አላውቅም ግን ከሁለት
ዓመት በፊት ወደ ሱዳን ለመሄድ ቪዛ ለመጠየቅ
ከሜክሲኮ አደባባይ በታች የሚገኘውን የሱዳን
ኤምባሲ ሲያጨናንቅ የነበረው የወጣቱ ቁጥር
አስደንጋጭ ነበር። ግን እኮ ሱዳንና ግብጽ
ዕጣ ፈንታቸው የሚወሰነው በአባይ ወንዝ ነው።
የግብጽ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ
በምትገነባው የሂዳሴ ግድብ ምክንያት ለካቢኔው
ንግግር ሲያድርግ “ ግብጽ ማለት አባይ ማለት
ነው አባይ ከሌለ ግብጽ የለችም፤አባይ ደማችን
ነው” ማለታቸው ይታወቃል። አባይ ግን መነሻው
ከኢትዮጵያ ምድር ነው ። አሁን አሁን የሂዳሴ
ግድብ መገንባቱ የተስፋ ፍንጣቂ ቦግ ብሎ
እንዲታይ አደርጓል። ወደ ሱዳን መግቢያ ቪዛ
በሕጋዊ መንገድ ማግኘት ባይችሉ በሕገ ወጥ
ደላሎች አማካይነት ድንበር አልፈው ሲሄዱ
ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ ወንድሞቻችንና
እህቶቻችን ከቁጥር በላይ ናቸው ብል እንደማጋነን
ሊቆጠርብኝ ስለሚችል ይቅርብኝ። ምን ይሁን
ምስጢሩ? እኛ
በእጃችን ያለውን በረከት
ማየት ያልቻልነው ለምንደነው?
መልሱ
በጣም ቀላል ነው። እንደ ፖለቲከኛ ለሚያስብ
ሰው ብዙ መልስ ይኖረው ይሆናል። እንዲያውም
የሕዝቡ ፍላጎትና አቅርቦት ስላልተመጣጠነ
ነው ሊባልም ይችል ይሆናል፣ ወይም ዜጋው
የአገሩን ሥራ ንቆ ነው የሚል መልስ ይሰጥበት
ይሆናል። ይኸው ለዜውጋው የኮብል ስቶን ሥራ
ዕድል ተመቻችቶለታል ቢባል ውሸት አይሆንም።
እንዲያውም ከዚያ አልፎ ዜጎች በተለይም ወጣቶች
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪና በሌሎች
ማህበራት እየተደራጁ ሥራ እንዲፈጥሩና
ራሳቸውንም አገራቸውንም እንዲያሳድጉ ሁኔታዎች
መመቻቸታቸው ሊካድ የሚችል አይደለም፣ የከፍተኛ
ትምህርት ተቋማት ምሩቃንም ጭምር በኮብል
ስቶን ሥራ ተሰማርተው ራሳቸውንና ሕዝባቸውን
ብሎም ቤተሰባቸውን እያጠቀሙ ነው የሚለውን
ዘገባ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሲተላለፍ ሳይ
ዓይኔን ማመን አቅቶኝ በአጠገቤ የነበረውን
ሰው ( ኢትዮጵያዊ
ነውና)ይህ
ነገር አልገባኝም አንተስ ገብቶሃል?
ስለው ፈገግ ብቻ አለ
እንጂ ምንም መልስ ሊሰጠኝ አልፈለገም። እኔም
ደግሜ አልጠየቅኩትም። የሆነ ሆኖ ሊባል
የሚችለው ይህና መሰል ነገር ነው። ከዚህ ውጭ
ሊሆንም አይችልም፣ እንዲሆንም መጠበቅ
የለብንም። ይህ ሁሉ ቢሆንም የሕዝባችን
መሰደድ አላበቃም። ለምን ለሚለው ምላሽ መገኝት
ይኖርበታል። በሰው ዘንድ ካለው መልስ ይልቅ
የእግዚአብሔር ይለያል። እንደ መንፈሳዊ ሰው
ሆነን መንፈስ ቅዱስ የሚለንን ከሰማን ግን
ይህ ሁሉ ጭንገፋና ተርምስ እልባት የሚያገኘው
ምድራችንና የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፈውስ
ሲገናኙ ብቻ ነው። ፈውስ ያስፈልገናል። ኦ!!
ለኢትዮጵያ ምድር
ፈውስ ያስፈልገዋል። ፈውስ! ፈውስ!
ፈውስ!
የእግዚአብሔር መሊኮታዊ
ፈውስ!!!! እግዚአብሔር
ምድሪቱን እፈውሳለሁ ይላል።
እግዚአብሔር
ይህንን መልዕክት ወደ ልቤ ሲያመጣ የዛሬ አራት
ዓመት አካባቢ በማገለግላት ቤተ ክርስቲያን
የወንጌል ሥርጭት ኮንፍረንስ ሲካሄድ የፕሮግራሙ
አስተባባሪዎች ወደ ነበርኩበት ቢሮ ያመጡት
ወጣት ያጫወተኝና በሕይወቱ የገጠመው አሰቃቂ
ምስክርነት ትዝ ብሎኝ ማልቀሰን የሚነግራችሁ
ቅንጣት ያህል ይቅር የቅንጣት ሲባሪ ያህል
ውሸት ሳልጭምርበት ነው። ወጣቱ ከአገልጋዮቹ
ጋር የተገናኘው ከኮንፈራንሱ ስብከት በኃላ
ጌታን ለመከተል ለሚሹ ወገኖች ጥሪ ሲደረግላቸው
አብሮአቸው ተነስቶ ምክር ወደ ሚሰጥበት ክፍል
በመሄዱ ሲያማክሩት ነው። በውስጡ ጌታን
የመቀበል ፍላጎት ጨርሶ አልነበረም። ሥራ
ፍለጋ ወደ ሱዳን ከተሻገረ በኃላ የገጠመው
ሥራ ሳይሆን ከሞት ያልተናነሰ ስቃይ ነበር።
ሄዶ የገባበት የመከራ ማጥ የሰው ልጅ እንዴት
ቻይ ነው? የሚያሰኝ
ነው። ወደ ሱዳን እንደተሻገረ ሕገ ወጥ ደላሎች
ተለዩትና የወደቀው በድንበሩ አካባቢ ባሉ
ለሰብዓዊነት ምንም ደንታ በሌላቸው በሱዳን
ወታደሮች እጅ ነበር። ከአፉ አውጥቶ እንደተናገረኝ
ወታደሮቹ ልብሱን ካስወለቁት በኃላ አንድ
እግሩን በገመድ ወደ አንድ አቅጣጫ ሌላው
እግሩን ደግሞ ወደ ተቃራኒው በኩል ወጥረው
ተራ በተራ ሲገናኙት ሲቃዩን መቋቋም አቅቶት
ራሱን በሳተበት እግሮቹን ፈትተው በዚያ በረሃ
ላይ ጥለውት እንደሄዱና ራሱን ሲያወቅ ግን
አንድም ሰው በአጠገቡ እንዳልነበረ ያስረዳኝ
ነበር። ይህ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ከእርሱ
በፊት የነበሩ ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ
ስለነበሩና ስላየው እርሱም ቢሆን ከዚህ
ሊያመልጥ የሚችልበት ምንም ቀዳዳ ስላልነበረው
ሳይወድ የግዱን ራሱን ለአውሬዎቹ አሳልፎ
ሰጠ። ነፍሱን ለማዳን ጫካ ለጫካ እየተንፏቀቀ
ወደ አንድ ጎዳና ላይ ሲወጣ እግዚአብሔር
ያዘጋጀለት አንድ ሩህሩህ ሰው በመኪናው ወደ
ኢትዮጵያ ድንበር አሻግሮት ተመለሰ። ከዚያ
ወዲያ ገንዘብ ለምኖ ምግቡን እየበላ ፣ ባለ
መኪኖችንም እገዛ እየጠየቀ ወደ አንድ የኢትዮጵያ
ከተማ ደረሰና በእጁ ባለችው ትንሽ ገንዘብ
የማደሪያ ክፍል ተከራይቶ በተኛበት ያኔ የሱዳን
ወታደሮች ሲግናኙት የቆሰለው ሰውነቱ ከመጠን
በላይ ደምቶ ነበረና የማደሪያ ቤቱ አንሦላ
በደም ስለ ተበከለ ማጠብ ነበረበት። ችግሩ
ግን ሳሙና መግዣ የሚሆን ገንዘብ አልተረፈውም
ነበር። ዳሩ ግን የሆቴሉ አልጋ ቤት ሠራተኞች
ችግሩን ሊረዱለት ስላልቻሉ እንዴት እንዳዋከቡትና
እንዳመነጫጨቁት ሲያብራራ የሚሰማውን ሰው
ከልብ ያስለቅሳል። የሚያሳዝነው ይህ ሰው
ሹፌሮችን ለምኖም ቢሆን ወደ መሀል አካባቢ
እንዳይመጣ ደም ይፈሰዋል። እንዲህ ዓነቱን
ችግር ይዞ በሰው መኪና መሳፈር ከጭንቅም በላይ
ጭንቅ ነው። ገና የሕክምና ርዳታ ሊያገኝ ወደ
ሚችልበት ሥፍራ ስላልደረሰ የሚያደርገው ሁሉ
ጠፍቶት ነበር። ይሁንና እግዚአብሔር ረድቶት
ወደ አዲስ አባባ ሲደርስ ወላጅ አባቱ ሲያየው
ትምህርቱን አቋርጦ በመሄዱ ምክንያት ተቆጥቶ
ስለ ነበር ወደ ቤት እንዳይገባ ከለከለው።
ከዚያ በኃላ ዘመዱ ወደ ሚሆን ሰው ሄዶ የደረሰበትን
ሁሉ ሲያጫውተው በጣም አዘነና ወደ ሆስፒታል
ወስዶት የሕክምና ርዳታ ከተደረገለት በኃላ
የጤናው ሁኔታ መሻሻል ቢያሳይም ፊስቱላ ለሚባል
ችግር መጋለጡን አጫወተኝ።
ይህ
ወጣት ወደ እኔ የመጣበትን ምክንያት ግልጽ
ሲያደርግልኝ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ
የመሆን ፍላጎት ኖሮት ሳይሆን ላለበት ችግር
እገዛ እንድናደርገለት ብቻ ነው። እርሱ አንድ
ሆኖ አየነው እንጂ በሱዳን በኩል ከአገር ሲወጡ
ለከፈተኛ ችግር የተጋለጡ፣የአካል ጉዳት
የሚደርስባቸው፣ህይወታቸውንም የሚያጡ
ቁጥራቸው ሊገመት ከሚችለው በላይ መሆኑን
ሲያጫውተኝ ቆይቶ ከቢሮዬ ከሄደ በኃላ ብቻዬን
እንዴት እንዳለቀስኩ ትዝ አለኝ። ልብ እንበል!
አንድ ተማሪ ወደ
ዪኒቨርሲቲ ሲገባ ራሱንም፣ ወገኑንም፣
አገሩንም የመጥቀም ተስፋ ሰንቆ እንደሆነ
ለሁሉም ግልጽ ነው። ተምሮ የመሻሻል እድል
ያላቸውም ጭምር እንደ ምንም ብለው ከዚህች
አገር የሚወጡበትን ቀዳዳ መፈለጋቸው እጅጉን
የሚያሳሰብም የሚያሳዝንም ጉዳይ ነው።ይህ
በሰው ዘንድ መፍትሔ የሌለው ጉዳይ ነው።
ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣው ፈውስ ግን
መፍትሔ ይሆናል።
ይህ ብቻ አይደለም። በኮንቴይነር ተጭነው ሲውሰዱ በሙቀት ታፍነው ያለቁ 48 ኢትዮጵያውያን እኮ ወደ አሜሪካን ወይንም ወደ ካናዳ ሲሄዱ ነበር ብሎ ሊያሳምነን የሚችል አይኖርም። ወደ አፍሪካ አገር ሲሄዱ እንጂ። ሌሎች ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ዓረብ አገር ሲወሰዱ ተመሳሳይ ዕጣ ገጠሞአቸዋል። ይህንንስ እግዚአብሔር አምላክ ምን ይላል? በየዕለቱ የሚፈሰውን ደም፣በግፍ የሚያልቀውንስ የወንድሞቻችን ሕይወት ተመልክቶ የሚፋረድስ አካል ይገኝ ይሆን? ነገሩስ ራሱ እንዲህ የሆነው ለምንድነው? ሕዝቡስ ለእንደዚህ ዓይነት ሕይወት አልፎ የተሰጠበት ሌላ አገር በምድር ላይ ይኖር ይሁን? በእውነት ጌታ ምድራችንን ሲፈውሰው ይህ ሁሉ ታሪክ ይሆናል።
ይህ ብቻ አይደለም። በኮንቴይነር ተጭነው ሲውሰዱ በሙቀት ታፍነው ያለቁ 48 ኢትዮጵያውያን እኮ ወደ አሜሪካን ወይንም ወደ ካናዳ ሲሄዱ ነበር ብሎ ሊያሳምነን የሚችል አይኖርም። ወደ አፍሪካ አገር ሲሄዱ እንጂ። ሌሎች ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ዓረብ አገር ሲወሰዱ ተመሳሳይ ዕጣ ገጠሞአቸዋል። ይህንንስ እግዚአብሔር አምላክ ምን ይላል? በየዕለቱ የሚፈሰውን ደም፣በግፍ የሚያልቀውንስ የወንድሞቻችን ሕይወት ተመልክቶ የሚፋረድስ አካል ይገኝ ይሆን? ነገሩስ ራሱ እንዲህ የሆነው ለምንድነው? ሕዝቡስ ለእንደዚህ ዓይነት ሕይወት አልፎ የተሰጠበት ሌላ አገር በምድር ላይ ይኖር ይሁን? በእውነት ጌታ ምድራችንን ሲፈውሰው ይህ ሁሉ ታሪክ ይሆናል።
አንዲት
ኢትዮጵያዊት በሊባኖስ አገር በሚገኘው
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት በሊባኖሳውያን
ስትደበደብ ኤምባሲያችን ሊከላከላት አለመቻሉ
ብዙዎቻችንን አስገርሞናል። ልጂቱ
“ወይኔ....ወይኔ...አልገባም”
እያለች ወደ መኪና ውስጥ ሊከቷት ከሚታገሉ
የዓረብ ጎርምሶች ጋር ብቻዋን ስትጋፈጥ ቤቴ
ነው ነፍሴን ያድንልኛል ብላ የመጣችበት
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምንም ሳይመስለው መቅረቱ
ከሁኔታው በላይ ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን
ማለት ነው አሰኘቶናል። በመጨረሻም የልጅቷ
ሞት ሲነገረን ምርር ያለ ልቅሶ አልቅሰናል።
የልጅቷን ማንነት በፍጹም ባላውቅም ሁኔታው
ከልቤ አልወጣ ብሎ ለወራት አሰቃየኝ።
መንግሥታችን ለዚህ ጉዳይ የሰጠው ተገቢ ምላሽ
ይኖራል ብዬ አምናለሁ። ያቺ ልጅ እንደ ምሳሌ
እንጠቀምባት እንጂ በዓረቡ አገራት ሕይወታቸው
ተቀጭቶ በከንቱ የቀሩ እጅግ ብዙ ናቸው። ይህ
እስከመቼ? ኢትዮጵያ
እስክትባረክ? አዎን
ነው መልሱ ግን በርከት ብቻውን አይለውጠንም፣
መለኮታው ፈውስ ግን ያስፈልገናል፣እግዚአብሔር
አምላክም ይፈውሰናል። ካልተፈወስንማ ሀብቱን
በአፉ ብቻ እንደሚቆጥር በሽተኛ ባለጠጋ
እንሆናለን። የምሥራቹ ግን እግዚአብሔር
አምላክ እፈውሳችኃለሁ ይለኛል።
እግዚአብሔር
ምድራችንን ይፈወሳል ስንል ምን ማለታችን
ነው? ይህንን
በብዙ አንጻር መመልከት እንችላለን። ከፍ
ብሎ እንደጠቀስኩት በፊታችን ስናያቸው የነበረ
ታላላቅ መሪዎቻችን ሮል ሞዴሎቻችን ሳይሆኑ
ቀሩ። በአራትና አምስት ሺህ የሚቆጠር ጉባኤያቸውን
ጥለው ይመጡና አንዱ ያገለግልበት ሥፍራ ይሄዱና
በምዕመናን ሲሻሙ ማየት እንዴት እንደሚያሳፍር።
በዚያም ላይ ጌታ የአገልግሎት በር ከፍቶልኛል
ሲሉ መስማት ተራ ተረት ሆኖአል። ይህ ሲገርም
እንደምንም ብለው ወደ ኢትዮጵያ ይሄዱና ሥልጠና
ልስጣችሁ፣ስብከት ልስበካችሁ፣ኑ ተስብሰቡ፣
ገንዘብንም አምጡ ሲሉ የዋህ የአገራችን ሕዝብ
ይንገላቱታል። ከሚሰጡስ ሥልጠና ምን ታምር
ይፈጠር ይሁን ብሎ ቢጠበቅ እውነት እላችሓለሁ
በኢትዮጵያ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን
በመሪዎች ክፍል የሚሰጠው ሥልጠና ትልቅ ቁም
ነገር ይገኝበታል። ቄስ እንትና፣ዶር እንትና፣
ፓስተር እንትና ወዘተ መጥተው ሥልጠና ስለሚሰጡ
ተጋብዛችኃል እንዳትቀሩ፣ ቦታው ኢምፔርያል
ሆቴል፣ሼበሌ ሆቴል፣ገነት ሆቴል ፣ወዘተ
ሆቴል ይባልና ሲከድ እነዶክተር እንትና ያምጡት
ነገር እዚህ ግባ የማይባል፤ወደ መጣንበት
ሥፍራ ተመለሰን ሥራ ላይ ማዋል ይቅርና ውድ
የአገልግሎት ጊዜአችንን በከንቱ ያባከንንበት
የኪሣራ ጊዜያቶች በርካታ ናቸው። ከመጀመሪያውም
ቢሆን እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ ሥልጠና ለመስጠት
ጸሎት ቤቶችን ሸሽተው በየሆቴሉ መመሸጋቸውና
ሕዝቡንም ማንገላታታቸው ጥያቄ ይፈጥርብን
ነበር። እንዲያው ወጣ ማለት ጥሩነው ብለን
ነው እያተባለ ተጀመረና አሁን አሁን ያለ ሆቴል
መንፈሳዊ ስብሰባ አይካሄድም ወደ ሚባልበት
ጀረጃ የደረስን ይመስላል። ይህቺ ናት መነቃቃት!
በአገር ቤት እያለሁ
ዛሬ ዶር እንትና ምን ነካቸው ትምህርታቸው
የተበታተነ፣ጭራው ከጭንቀላቱ የማይለይ፣ውሉ
የጠፋበት በዚያ ላይ እንጨት እንጨት የሚል
ሆነሳ? ኧረ
የእኛ ችግር ይሆናል እየተባባልን የነበረው
ለካ ስላልገባን ነው። እኔም እግር ጥሎኝ ወደ
አሜሪካ መጣሁና ወደ ኢትዮያ ሲሄዱ በዚያ
ምስኪን ሕዝብ ላይ በቃ ከመላእክት መንደር
የወረዱ ዓይነት መስለው መንፈሳዊ ነኝ ለማለት
ያህል ግዳይ እንደጣል ሰው ወዲያና ወዲህ
ሲንጎራደዱ ያየናቸው እነ ጋሽ እንትና ለካ
እዚህ አገር ያሰለቹ በጥባጭ ኖረዋል። ይህን
በመሰለ ሥጋዊ ጦርነት ውስጥ ኖረው ታዲያ ምን
ጠብ የሚል ነገር ሊሰጡን ይችላሉ?
በጌታ ፊት በትጋትና
በቅንነት በጸሎትና በእምባ ከአምላኩ ጋር
ተጣብቆ በኖረው ሕዝብ ላይ ይመጡና ዝም ብለው
ያቅራሩበታል እንጂ በጭራሽ ሕዝቡንስ መጥነውት
አይደለም። ያም ሳያንስ ጌታ ሊሠራ ተነስቶአልና
ያላችሁን ስጡ ሲሉ መቼም ሕዝባችን የእግዚአብሔር
ስም ሲጠራና በስሙ አንድ ነገር ሲጠየቅ መግፋት
አይሆንለትምና እያመጣ ይሰጣል። ጌታ ለመሥራት
ከተነሳ ገንዘቡ ምንድነው? እጅ
መንሻ ወይስ ትራንስፖርት? በእውነት
እላችኃለሁ እግዚአብሔር ያለ እኛ መሥራት
ይችላል። እንዲያውም የሰውን ገንዘብ ተስፋ
አድርጎና በሥጋ ለባሹ ተደግፎ የሚሠራ አምላክ
አይደለም። ይህንን የሚጠይቅም ስሌለለ
በመንፈሳዊነት ስም ምንነቱ የማይታወቅ
የገንዘብ አሰባሰብ ያደርጉታል። ከዚያ ጌታ
ይባርካችኃል ይሉና እነሱ ይባረኩበታል።
ይህንን ያዩ ማንነታቸው የማይታወቅ አንዳንዶች
እየተነሱ ጌታ ተናግሮኛልና ኮንፍራንስ
አዘጋጅቻለሁና ወደ ስታዲየም ውጡ የሚል ፖስተር
በየቦታው ይለጥፍና ይህንን ምስኪን ሕዝብ
ይጠራል። ዓላማው ጌታ የተናገረውን መልእክት
ማስተላለፍ ሳይሆን ባለፈው እነ ዶ/ር፣ፓስተር፣ቄስ
ወዘተ እንዲህ አድርገው ገንዘብ ዝቀው ሄደዋልና
እኔም ይህቺ የሃይማኖት ነጻነት የተባለች
ነገር እያለች ልዛቅ በሚል ነው። ምክንያቱም
ቀዳሚ የቤተ ክርስቲያን መሪ ተብዬዎቹ ያመጡብንና
እያስለመዱን ያለው ይኸው ነዋ። ሕዝባችንስ
ቢሆን ለስንቱ ይስጥ? ግብሩን
ይክፈል የሂዳሴ ግድቡን? ቫቱን
ይክፈል ዳቦውን ይግዛ? አሥራትና
መባውን ለሚገለገልበት ቤተ ክርስቲያን ይስጥ
የተቸገረውን ይርዳ ወይስ በመንፈሳዊነት ስም
በሚመጣው ሌባ ይዘረፍ? ይኼ
እንግዲህ ፈውስ የሚያስፈልገው ጎናችን ነው።
አደባባይ
የወጣው ሕዝብ ምን አተረፈ ቢባል ያው ትባረካላችሁ
ይባልላቸዋል ካልሆነም እፍ እያሉበት ሲገፈትሩት
ሲገነደስ ውሎ /ለዚያውም
ተራ ከደረሰው ነው/ ወደ
ቤቱ ይመለሳል። ተሰበከ ቢባል የደረቁ አጥንቶች፣
አልአዛር፣ደም የፈሰሳት ሴት፣ የኢያሪኮ
ግንብ መውደቅ፣ ናቸው። በአንድ ሰሞን ልብህን
በአህያ ላይ አትጣል የሚለው ስብከት ከገጠር
እስከ ከተማ ብቻውን በየቦታው ይስበከብበት
እንደነበር አስታውሳለሁ። አሁን አሁን ደግሞ
ኢትዮጵያ አገራችን የተስፋ ቃል ያላት ነች
የሚለው ነው ስብከቱ። እንዲህ ዓይነቱ የተስፋ
ቃል ምን ላይ ነው የተጻፈው ተብለው አንዳንዶቹ
ሲመልሱ “እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች
ተብሎ ተጽፎአል ይላሉ። ይህ ነው ተስፋ ቃሉ?
ኢትዮጵያ ኮ በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ 40 ጊዜ
የተጠቀሰች አገር ነችና ቃል ኪዳን አላት
ብለውም እርፍ። እንዲህ ዓይነቱ ስብከት የእነ
ዶር እንትና ስብከት ነው፡፡ ያሁኖቹም የቀዱት
ከዚያ ነው። እነጋሽ ፤ ዶር ፣ቄስ ፣ፓስተር
እንትናማ ለኢየሱስ ብቻ የሚሰጠውን ስም (
ሜልከፀዴቅ የተባለውን)
ጓደኛቸው ሲያከናንቡት
ትንሽም ያላፈሩ፣ተወቅሰውም ተሳስተናል
ለማለት ልብ የሌላቸው መሆናቸውን ሥራቸው
ሲገልጣቸው ኖረዋል። የአሁኖቹም መንጋ አልባ
መጋቢዎችም ከቀደሙት የሰሙትን ደገሙት እንጂ
ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 40
ጊዜ ስለ መጠቀስዋ
እርግጠኛ ለመሆን አንድ ሁለት ብለው ቆጥረው
አይምስለኝም። ዎይ አርባ ጊዜ-----!
40 ጊዜ ይቅርና 40000
ጊዜ ብንጠቀስስ ያ
ለመንፈሳዊነታችን ወይም የቃል ኪዳን ሕዝብ
ለመሆናችን ማረጋገጫ ሊሆን የቻልበት ምክንያት
ምን ይሆን? ኢትዮጵያ
በ66ቱ መጻሕፍት
ውስጥ 40 ተጠቅሳለች
እያሉ ነው። መለኪያው ይህ ከሆነ ግብፅ በመጽሐፍ
ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ በሆነው በኦሪት
ዘፍጥረት ብቻ ከ154 ጊዜ
በላይ ተጠቅሳለች። በተቀሩት 65ቱ
ውስጥ ያለውን ብንደምርበት ስንት ሊሆን
እንደሚችል እንገምት። ታዲያ መንፈሳዊው ማን
ነው? ግብጽ
ወይስ ኢትዮጵያ? እግዚአብሔር
ካደለን መልሱን ከእነ ዶር፣ቄስ ፣ፓስተር፣
ሰባኪ ወዘተ እንትና እንሰማለን። ሕዝባችን
ግን ያሳዝነናል። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር
ይህንንም ይፈውሰዋል። እርሱ ምድራችሁን
እፈውሳለሁ ብሎአልና። ለዛሬ እዚህ ላይ ጌታ
እናድርግና ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን። እስከ
አሁን አንድ ጥቅስ እንኳን አላነበብክልንም
እግዚአብሔር በምንድነው የተናገረህ?
የምትሉኝ ውዳጆቼ
እኔም በምትሉት ሁሉ እስማማለሁ። ሁሉንም
እንደርስበታለን። እስከዚያው በቸር ሰንብቱ፣
ጌታም በሰላም ያገናኝን።
No comments:
Post a Comment