Monday, May 26, 2014

 ምድራችሁን እፈውሳለሁ (ክፍል ሦስት)                                                                                                           
                                                                                              ፓስተር ሳሙኤል ሾንጋ
ምድራችሁን አፈውሳለሁ ይላል እግዚአብሔር በሚል ርዕስ ለሁለት ተከታታይ ጊዜያቶች በጣም ሰፋ ባለ መልኩ በብዙ ነጥቦች መነጋጋራችን ይታወሳል፡፡ በሁለቱም ክፍለ ውይይት በምድራችን ለሚታየው መንፈሳዊ ሕይወት ችግሮች ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ስናደርግ የቆየነው የቤተ ክርስተያናችንን ተቀዳሚ መሪዎች በተለይም በአሜሪካን አገር የሚገኙ ፓስተሮችንና ነቢያትን እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነርሱ ብቻ መወቀስ አለባቸው ወይ የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይኖርብናል፡፡ እውነት እንነጋገር ካልን መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም በአንድነት ተሳስተናል፡፡ መሪዎችን የወቀስነው መልካም ምሳሌ መሆን ስላልቻሉ ነው እንጂ ሁላችንም ጋ ችግር አለ ፡፡ ሕይወታቸው ወደ ሕብረትና ወደ ቅድስና ፣ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት ስለማያሳየን ነው እንጂ ኢትዮጵያውያን የሆንን አማኞች ሁላችን አሁን ለሚታየው ውድቀት ተጠያቂዎች ነን፡፡ እያንዳንዱ በእግዚአበሔር ፊት የሥራውን ዋጋ ይቀበላል፡፡ ወንድም እገሌ ወይም ፓስተር እገሌ አሳስቶኝ ነው ብሎ ሊያመልጥ የሚችል አንድ የለም፡፡
የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ባቆሸሽንበትና ለብዙዎች እንቅፋት በሆንንበት ሁሉ ንስሐ መግባት ይኖርብናል፡፡ ጉዳዩ ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ መንጋውን በፍቅርና በትጋት እንደ እግዚአብሔር ቃል መሠረት ያልመራን መሪዎች(ሽማግሌዎችና ፓሰስተሮች)፣ ከጌታ የተቀበልነውን ሕዝብ በእውነተኛው እግዚአብሔር ቃል ኮትኩተን ያላሳደግን መጋቢዎች፣ ወንጌል የመዳረስን ኃላፊነት ያልተወጣን ወንጌላውያን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያልሆነውን ትንቢት በመናገር ምዕመናንን ያደናገርን ነቢያት፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ያልሆን ምዕመናን፣ መዘመራን በተለይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑትን ምድራዊ ዝማሬዎችን ብቻ በመግጠም ሕዝቡን ወደ ሰማዊ እውነት ለማመልከት ያቃተን መዘምራን ሁላችንም በአንድነት ወደ እግዚአብሔር መመለስ በሚያስፈልገን ወሳኝ ወቅት ላይ መሆናችንን ልንገነዘብ ይገባናል፡፡
ይህንን ያህል ካኩ በኋላ እየተነጋርበት ወደ ነበረው አሳብ መመለስ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ምድርን ለመፈወስ ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በዝርዝር ስንመለከት ቆይተናል፡፡ እነርሱም ፡ ሰውነትን በማዋረድ በንስሐ መጸለይ፣ ከክፉ መንገድ ወይም ከኃጢአት መንገድ መመለስ ሲሆኑ እነዚህን መድረግ የሚጠበቅብን በእግዚአብሔር ስም የተጠራን የእርሱ ሕዝቦች መሆናችንን በ2ኛ ዜና 711-14 በላው ክፍለ ንባብ ተመልክተናል፡፡ በዚህኛው ክፍል ደግሞ ስለ ሦስተኛው ነጥብ እመለከታለን፡፡
3. የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ፡
የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ ለክርስና ሕይወትና ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖረን ሕብረት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው ይላል (መዝ.1054)፡ የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ ማለት ምን ማለት ነው? እግዚአብሔርን መፈለግ ማለት የእርሱን ህዉና መናፈቅ ማለት ነው፡፡ ህልውና ስንል presence የሚባለውን ነው፡፡ ይህ በብራውያን ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ ህውናውን መፈለግ ማለት በፊቱ መገኘት እንደማለት ይቆጠራል፡፡ እንግዲህ የእግዚአብርን ፊት ወዴት ብን ነው የምንፈልገው; እርሱ በሁሉ ቦታ የሚገኝ (Omnipresent) የሆነ አምላክ ነው፡፡ እርሱ መንፈስ ነው እንዴት አድርገን ነው የምንፈልገው? ተፈልጎስ የሚገኝ አምላክ ነው ወይ? እርሱ ሁሉንም ነገር በሥልጣኑ ይገዛዋል የቆጣጠረዋልም፡፡ ከዚያም አልፎ ለእኛ ለእያንዳንዳችን ቅርብ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የእርሱን ህልውና ወይም ፊቱን የምንፈልገው? እንግዲህ እርሱ በቃሉ ፈልጉኝ ያለው ይህንን ሁሉ እያወቀ ነው፡፡
የማቴዎስ ወንጌለ 2020 ስንመለከት እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሏል፡፡ ከዚህ ቃል ኪዳን የተነሳ ህልውናው ሁል ጊዜ ከልጆቹ ጋር ነው፡፡ በመከራ ጊዜ ያግዘናል፣ ስንወድቅ ያነሳናል ስንደክም ያበረታናል፣ በአጠገባችን ሆኖ በሁሉም አንጸር ልባችንን ይደግፍልናል፡፡ ይህ የቅርብ አምላክ በፊቱ እንድንሆን ዘንድ ይፈልጋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ እግዚአብሔርን እንድንፈልግ ይጠይቀናል፡፡
የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳናት እንደሚያብራልን እግዚአብሔርን መፈለግ ማለት አንድ የፋብንን ነገር ለማግኘት የሚናደርገው ዓይነት ትግል አይደለም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አልጠፋብንም፡፡ ድርምና በግ የጠፋባቸው አጥብቀው በፈለጉበት መንፈስና አእምሮ እርሱን አንፈልገውም፡፡ እግዚአብሔርን መፈለግ ስንል አንድ የጠፋብንን ነገር ለማግነት በምንበረብርበት አኳኋን እርሱን እንፈልገዋን፡ ለምሳሌ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 3-10 ባለው ቦታ የጠፋባቸውን ነገር የፈለጉ ሰዎችን እናገኛቸዋለን፡፡ አንደኛው በግ የጠፋት ሰው ሲሆን ይህ ሰው አንዱን በግ ለመፈለግ ዘጠና ዘጠኙን ሜዳ ይ ትቶ አንዱን በግ ለመፈለግ ሄደ፡፡  ሌላ ደግሞ ድሪም የጠፋባት ሴት መብራት አብርታ ቤቷንም ጠርጋ እክስታገኘው ድረስ እንደምትፈልገው ጌታ አስተማረ፡፡ የጠፋው በግ የተገኘው ወደ ዱር በመሄድ ወይም እውጭ በመውጣት አለያም በጉ ወደ ኮበለለበት አገር ሁሉ በመሄድ ነው፡፡ ድሪሙ የሚገኘው ደግሞ ሩቅ ሳይከድ እቤት ውስጥ መብራት በማብራትና ቤትን በመጥረግ ነው፡፡ አንዳንድ ነገር ሩቅ ተክዶ ይገኛል፣ አንዳንዱ ግን እዚያው እያለ የጠፋ ስለሆነ የሸፈነውን ነገር በመግለጥ ይገኛል፡፡ እንግዲህ መፈለግ ማለት ይህ ከሆነ እግዚአብሔርን ለማግኘት የምንፈልገው ሩቅ አገር በመሄድ ነው ወይስ አካባቢን በማጽዳት ነው? እግዚአብሔርስ ፈልጉኝ ሲል አንድ ቦታ ተደብቆ ከእኛ ጋር አኩኩሉ እየተጫወተ ነው ማለት ነው? እርስ አውቆ ተደብቆ እኛን ፈልጉኝ እያለ እያደከመን ነው ማለት ነው ወይስ እግዚእሔርን እንፈልግ ስንል እንዴት ነው የምንፈልገው?
እግዚአብሔርን መፈለግ ማለት ከዚህ ሁሉ የሚለይ ነው፡፡ ነገር ግን ልባችንንና አእምሮአችንን እግዚአብሔርን ለማወቅ የማዘጋጀት ሂደት እንደሆነ ያስተምሩናል፡፡ አሁንም እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ( 1 ዜና 2219)፡፡ ልብን መስጠት ማለት አውቀንና ወደን ልባችንንና አስተሳሰባችንን ለእግዚአብሔር ማስወረስና ወደ እርሱ መመለስ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በተሰሎንቄ ላሉ አማኞች ሲጽፍ ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችሁን ያቅናው(2 ተሰ 35) ይላቸዋል፡፡ እርሱን መፈለግ ማለት ከፍጹም ነፍሳችንና ልባችን ፈቃዱን፣ ፍቅሩን ፣ ሪህራኄውን፣ ምህረቱን፣ ቸርነቱንና ጸጋውን መሻትና መናፈቅ ማለታችን ነው፡፡ መፈለግ ማለት እንዲህ ከሆነ እርሱን ለማግኘት የትም ሩቅ መሄድ አያስፈልግም ምክንያቱም አምላካችን በአጠገባችን ከዚያም በቀረበ መልኩ በውስጣችን ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ፊቴን ፈልጉ ሲል ጌታ የሚፈልግብን ይህንን እንጂ ሌላ አድካሚ መንገድ እንድንሄድበት አይደለም፡፡ ስለዚህ ምድራችን እንድትፈወስ ሁላችንም የእግዚአብሀየርን ፊት ልንፈልግ ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ የሚለው ቃል ምን እደሀነ የሚገባቸው ያመኑና በስሙ የተጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሄርም ራሱ ፊቱን እንዲፈልጉ የሚጠብቅባቸው በስሙ የተጠሩትን ሰዎች ነው፡፡ ስለዚህ በሄ ክርሰቲያን የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግን ልማድዋና ባህልዋ የምታደርግ ከሆነ በእርሷ ምክንያት ምድራችን ትፈወሳለች፡፡ ስለዚህ ለሁላችንም የቀረበ አስደናቂ መልእክት ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በኢየሱ ክርስቶስ በኩል እንደ ባለጠግነቱ መጠን በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ይሙላብን ፡፡ እንደ ተስፋ ቃሉም ምድራችንን የፈውሳት ፡፡ አሜን፡፡





Sunday, May 25, 2014

ስለ ምን ትፈራላችሁ ?

                                                       ስለ ምን ትፈራላችሁ ?

ፓስተር ሳሙኤል ሾንጋ
       ሕያው ፍጡር በሆነ በተለይም በሰዎችና በእንስሳት ሁሉ ከሚታይ ስሜት አንዱ ፍርሃት ነው፡፡ የዓለም ጠበብት የፍርሃት ዓይነቶችን በተለየ መልክ ያስቀምጡታል፣ ይገልጹታልም፡፡ ፍራስቴር ኬንት የተባሉ እውቅ ፀሐፊ “nothing to fear” 1977 Doubleday and Company በተሰኘው ጽሑፋቸው ካሰፈሩት ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያህል ፔላዶፊያ የሚባለው የፍርት አይነት አለ፡፡ ይህ ዓይነቱ ፍርሃት የጸጉር መመለጥና ጸጉራቸው የተመለጠ ሰዎችን መፍራት ነው፡፡ ኤሮፎቢያ የሚባለው ደግሞ ሊመጣ ያለውን ረሀብ ወይም ድርቅ እያሰቡ መጨነቅን የሚያመለክት ሲሆን ቻዬቶፎቢያ በመባል የሚታወቀው ፍርሃት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ጸጉራም ሰዎችን መፍራት ሲሆን ፔላዶፊያ የተሰኘው ተቃራኒ ነው፡፡ በስተግራ በኩል ስላሉ የአካል ብልቶቻችን እያሰቡ መጨነቅና መፍራት ሌቮፎቢያ የሚባለው ሲሆን በተቃራኒው ስለ ቀኝ የአካል ብልቶች እያሰቡ መጨነቅና መፍራት ዴክስትሮፎቢያ ይባላል፡፡ ይህ ማለት ጉበቴ ታሞ ይሆን ፣ ሳምባዬ ቆስሎ ይሁን ፣ ኩላቴን ካንሰር ይዞ ይሆን በማለት አሳብን በማውጣትና በማውረድ አእምሮን በፍርሃት መሙላት ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወደ ሐኪም ቤት ሄዶ ለመመርምር ሰፊ ዕድል እኳን እያለ ያንን ወደ ጎን ትተው ስለ ሕመም የሚፈሩ ሰዎች ሌቮፎቢያና ዴክትሮፎቢያ ያጠቸው ናቸው፡፡ ምንም ሳያማቸው እንዲያው ከመሬት ተነስተው ሊያመኝ ነው መሰለኝ ብለው ቤተሰብና ጎረቤትን የሚያሸብሩ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ሌላ ደግሞ ካሊፕሮፎቢያ የሚባል የፍርሃት ዓይነትም አለ፡፡ ይህኛው ደግሞ ስለ ሥውር ወይም ድብቅ ስለሆኑ ነገሮችና ስለ ትርጉማቸው እያሰቡ መፍራት ነው፡፡ አውሮራፎሪያ የሚባለው የሚገርም የፍርሃት ዓይነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ስለ ሰሜናዊ ብርሃናት እያሰቡ መፍራት ነው፡፡ ለእንዲህ ዓይነት የተጋለጡ ሰዎች ሌሊት ሲሆን በሰሜን ዋልታ አካባቢ ከርቀት የሚታዩትን ብርሃናትን ይፈራሉ፡፡ እነዚህ ብርሃናት ምንም የሚያደርጉ ባይሆኑም የሚያዩ ሰዎች ግን ዝም ብለው ይፈሩአቸዋል፡፡ የሚገርመው ፍርሃት ደግሞ ስታብስባስፎቢያ የሚባው ስለ መቆምና ስለ መሄድ መፍራት ነው፡፡ ሰዎች በአንድ ሥፍራ ለቆም ይፈራሉ ከዚያ ቦታ ስለመንቀሳቀስም ይፈራሉ፡፡ እዚያ ጋ ቁም ሲባሉ እፈራለሁ፣ ተንሳቀስ ሲባሉም እፈራለሁ የሚሉ ሰዎች ያለባቸው ችግር ሲሆን ይህ ዓይነቱ ግራ የሆነው የሆስታብስባስፎቢያ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በሕዝብ ፊት አንድን ነገር ለመጻፍ እፈራሁ የሚሉ ሰዎች ያሉ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ያላቸው ፍርሃት ጋራፎፎቢያ የሚባለው ነው፡፡ ፍርትን ራሱን መፍራት ደግሞ ያለ ሲሆን እሱኛው ፎቦፎቢያ ተብሎ ያጠራል፡፡ እነዚህና የሚመስሉ ሌሎችም የፍርሃት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን እነዚህ ሁሉም ምንም የተጋባቸው ፍርሃቶች ሳይሆኑ አላስፈላጊ ፍርሃቶች ናቸው፡፡
        ፍርሃት በሰው ሕይወት ለምን ይፈጠራል ማለት አንችልም፡፡ በእርግጥ የሚያስፈሩ ነገሮች ስላሉ ለመፍራ እንገደዳለን፡፡ የሚነድ እሳት ስናይ፣የከባድ መሣሪያ ፍንዳታ ስንሰማ በውስጣችን የሚፈጠረው ፍርሃት ተገቢና ኃጢአት የሌለበት ነው፡፡ የመኪና መንገድ የሚያቋርጥ አንድ ሰው ከላይና ከታች የሚተምሙትን  አዎቶሞቢሎችና ካሚዮኖችን ሲያይ ልቡ በጣም ይፈራል፡፡ ያየው ነገርና ያለበት ቦታ እንዲፈራ ያስገድደዋል፡፡ ነገር ግን ነገ ምድር ብትናወወጥ ምን እሆናለሁ ፣ ልጆቼንስ በምን ውስጥ እሰውራለሁ? ወይም ከአዳም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሞቱና በመቃብር ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢነሱ ምድር እንዴት ትበቃለች በሚል እያሰበ እንቅልፉን እንዳጣ ሰውዬ ዓይነቱ ፍርሃት ምን ይባላል?
          የእግዚአብሔር ቃል እንዳንፈራ በተደጋጋሚ ይናራል፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን አትፍሩ የሚል የማጽናኛ ቃል በብዙ ቦታ እናገኛለን፡፡ እግዚአብሔር አትፈሩ የሚለን እንደምንፈራ ስላወቀ ነው፡፡ ስለፈራችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ምንም እድል ፋንታ የላችሁም አልተባልንም፡፡ ታላላቅ ተአምራን ያደረጉ የብሉይ ኪዳን ታላላቅ ሰዎች መፍራት በማይገባቸው ሁኔታ ፈርተዋል፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ኤልያስ ኤልዛቤልን ፈርቶ አንድ ቀን ሙሉ መንገድ እንደሮጠ በቃሉ እናነባለን፡፡ የሲዶናውያን ንግሥት ኤልዛቤል በኤልያስ አገልግሎት ስምንት መቶ አምሳ ነቢያቶችን በማጣቷ ስለተቆች ነገ በዚህን ሰዓት ከእነዚህ ነቢያት እንደ አንዱ ነፍስ ባላድርግብህ አማልክት ይህንን ይጨምሩብኝ ስትለው ነፍሱን ለማዳን ሮጠ፡፡ ከአንድ ቀን በፊት ግን ከበዓል ነቢያት ጋር በአምላኩ ስም ተወራርዶ ከሰማይ እሳት ካዘነበ በኃላ 450 የበዓል ነቢያትን አሳርዶ ነበር፡፡ ነገር ግን ኤልዛቤልን ዛቻ ሲሰማ ነፍሱን ለማዳን ሮጦ ሲደክመው ከክትክታ ዛፍ ሥር ሆኖ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴ ውሰድ ብሎ የጸለየው ከፍርሃት የተነሳ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጸሎት ትክክለኛ ጸሎት ሳይሆን ፍርሃት የወለደው ነው፡፡ ኤልዛቤል ስትዝትበት ትናንት በእርሱ ጸሎት እሳት ያወረደውን ጌታ እዛው ባለበት ቦታ ሆኖ መጠየቅ እንዴት እንደጠፋበት ያስገርማል፡፡ እግዚአብሔርን ከመጠየቅ መሮጥ የሚያዋጣው መስሎት ይሆን? አናውቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የምንጸልያቸው ትክክለኛ ያልሆኑና በውስጣችን ያለው ፍርሃት የሚያመነጫቸው ጸሎቶች አሉ፡፡ ኤልያስ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔርን ግደለኝ የሚለው ከልቡ ሞት ፈልጎ ነው ማለት ያስቸግራል ምክንያቱም የአንድ ቀን መንገድ ሮጦ የመጣው ከሞት ለማምለጥ ነውና፡፡ የሚጠይቀው በእርግጥ ለመሞት ከሆነም እግዚአብሔርን ግደለኝ ከሚል ይልቅ ኤልዛቤል ጋ መሄድ ነበረበት፡፡ እገድላለሁ ያለቺው ሴት እዛው እያለች እርሷን ሸሽቶ መጥቶ በሕይወቱ ትልቅ ሥራ ለመሥራት የመረጠውን እግዚአብሔርን ግደለኝ ማለቱ ከመፍራቱና ከመጨነቁ የተነሳ የተናገራቸው አሳቦች ናቸው፡፡ እንግዲህ ስው ሁሉ ፍርሃት አለበት፡፡ ዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በሕይወቱ ስለ ገጠሙት ፍርሃቶችና የፍርሃት ምክንቶች ሲገል በወንዝ ፍርሃት፣ በመንገድ ፍርሃት፣ በወገኔ በኩል ፍርሀት ፣ በአህዛብ በኩል ፍርሃት፣ በከተማ ፍርሃት ፣ በምድረ በ ፍርሃት፣ በባሕር ፍርሃት ፣ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ (2 ቆሮ. 1126) ብሏል፡፡
          ሐዋሪያው ጴጥሮስም የማዕበሉ ጌታ የሆነ ኢየሱስ በአጠገቡ እያለ እንኳን ፈራ፡፡ የማይፈራ ሰው አንድም የለም፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር ቃል በተደጋጋሚ አትፍሩ የሚለን ስለምንፈራ ነው፡፡ የማይፈራውን ሰው አትፍራ የሚለው የለውም፡፡ ልጆቻችንን አትፍሩ የምንላቸው መፍራታቸውን ስናይ እንጂ እንዲሁ ከመሬት ተነስተን አትፍሩ አንላቸውም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትንቢት በተናገሩ ነቢያቶችም ሆኑ መልእክት በጻፉልን ሐዋሪያት በኩል በተደጋጋሚ አትፍሩ የሚል መልእክት የተሰጠን እግዘአብሔር መንቦቅቦቃችንን ስላወቀልንና ስለተረዳልን መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የእርሱ የሆኑትን አትፍሩ እያለ የሚያጽናናበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሁሉ በአንድ ጊዜ ማየት አንችልም፡፡ ለአሁኑ ግን ለምን መፍራት እንደለለብን በትንቢተ ኢሳያስ 431-7 ያለውን ፍል እመለከታለን፡፡ ዚህ ክፍል የጌታ ቃል አትፍሩ እያለ ሁለት ጊዜ ይናገራል(.1 እና ቁ 5)፡፡ እጅግ በጣም አስፈሪ በሆኑ በሁኔታዎች ውስ ብናልፍም እኳ ጌታ አትፍሩ ይለናል፡፡ በዚህ የንባ ክፍል በሰዎች ልጆች ሕይወት በአስፈሪነታቸው አቻ የማይገኝላቸው ሁለት ነገሮች እንደ ምሳሌ ቀርበዋል፡፡ አንዳኛው ውሃ ሲሆን ሁለተኛው እሳት ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱም ለሰው ልጆች ጥቅም የሚሰጡ ቢሆኑም ከልኩ ካለፉ ግን አስፈሪዎች ናቸው፡፡ ውሃ በምንጠጣው፣ በምንታጠበው፣ ምግባችንን በምናበስለውና እርሻችንን በምለማው ወዘተ ልክ ሲሰጠን እንጂ ከዚያ ካለፈ ግን ደገኛ ነው፡፡ ከልኩ ያለፈ ውሃ ለመቆጣጠር የይቻውን ጥፋት ያስከትላል፡፡ በጃፓን አገር የነበረው የሱናሚ አደጋ ስናስብ ውሃ ያንን የሚመስለውን አገር ለማውደም ምም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 2011 ላይ በተከሰተወ ረእደ- መሬትና የውሃ መጥለቅለቅ 125 ሺህ ቤቶች ተጠራርገው ተወስደዋል፡፡ በጊዜው የወደመው ንብረት በ310 የቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት ነው፡፡ ይህ የውሃ ጥፋት ከንብረት በላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል፡፡ በጃፓን ምሥራቅ ጫፍ ላይ የተነሳው የጎርፍ አደጋ መኪናዎችን፣ ጀልባዎችን ካሚዮኖችን፣ እንዲሁም ደግሞ መኖሪያ ቤቶችን ሲያገኛቸው ሁሉም እንደ ቅጠል እየተንሳፈፉለት ተጠራርገው መድረሻቸው ወዳልታወቀ ሥፍራ ተወስደዋል፡፡ ውሃ በእጥፊነቱ የሚታወቅ እደሆነ የእግዚአብሔርም ቃል ይነግረናል፡፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ የወጣውን የሰውን ጥፋት ሲያይ ምድርን የቀጣው በጥፋት ውሃ ነበር(ዘፍ.7)፡፡ ያ የጥፋት ውሃ ወደ መርከብ ውስጥ የገቡት ብቻ ሲቀሩ በምድር ላይ ያሉትን ተንቀሳቃሾች ሁሉ አጠፋ፡፡ እግዚአብሔር የእሥራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ባሪነት ነፃ ያወጣበት ጊዜ በግብጻውያን ይ ያደረገው የመጨረሻው ቅጣት በውሃ እንዲወሰዱ ማድረግ ነበር፡፡ ውሃ ሚያስከትለው ጥፋ ከፍተኛ ነው፡፡ ዳዊት እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ቶቹን እንዳፈረሰለት ሲመሰክር ውሃ እንዲያፈርስ እግዚአብር ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው ሲል ያንን ሥፍራ ኤልፐራሲም አለ( 2 ሳሙ.520).፡፡ ይህ ማለት ውሃ ትላልቅ ግንቦችን ለማፍረስ የሚችልበት ኃይል ያለው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ነቢዩ ናሆምም እግዚአብሔር በጠላቶቹ ላይ መዓቱን ሲልክ በሚያጥለቀልቅ ጎርፍ እንደሚያስወስዳቸው ተናገረ( ናሆም 15-9)፡፡
         እሳትም በምንሞቀው ልክ፣ እህላችንን በምናበስልበት ልክ፣ እንዲሁም የአካባቢያችንን ቆሻሻ በማቃጠል በማስወገድ በምንችልበት ልክ ብቻ ሲሰጠን በጣም ይመቸናል፡፡ ከዚያ በዘለለ መልኩ ከከልሉ የወጣ እሳት እጅግ በጣም የሚያፈራና በቃል ሊገለጥ የማይቻል ጥፋትና ውድመት ሊያደስ የሚችል ነገር ነው፡፡ የእግዚአብርን የፍርድ ጥልቀት ለማሳየት መጽሐፍ ቅዱስ ከእሳት ጋር ያመሳስለዋል፡፡ እግዚአብሔን ራሱን የሚባላ እሳት ነው ይለዋል( )፡፡ የመጨረሻውና ከባዱ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚከናውንበትን ሁኔታ ከእሳት ጋር ያያይዘዋል( ገሀነመ እሳት ወይም የእሳት ባህር በማለት)፡፡ እሳት የበላውን ነገር መልሶ ለምንም ገር ማዋል በጣም አስቸጋሪ ይሆናል አይቻልምም፡፡ እሳት አንድን ነገር ከነበረበት ሁኔታ በአጭር ደቂዎች ውስጥ ወደ አመድ ሊለውጥ ይችላል፡፡ ቤቶችን ንዳልነበሩ ለማድረግ ምንም ጊዜ አይወስድበትም፡፡ በአለም ሥልጣኔ ትልቁን ሥፍራ የምትይዘውን አሜሪካንን በየዓመቱ የሚፈታተን ነገር ቢኖር የዱር እሳት /wild fire/ የሚባል ነው፡፡ ይህ ሳት ሲነሳ በተለይም በበስተ ደቡብ ምዕራብ አካባቢ ያ ደኖችን እንዳነበረ ያጋቸዋል፡፡ የግዙፍ ሥልጣኔ ባለበት የሆነቺው አሪካ ይህንን ለመከላከል ምንም ግኝት የላትም ፡፡ሳያስቡት ቀርተው ሳይሆን ያንን ማግኘት አሰልቺም አድካሚም ስለሚሆንባቸው ሊሆን ይላል፡፡ ከሥልጣኔ ጋር በተያያዘ በምጣኔ ሀብት የበለጸጉ አገሮች የመብረቅ መከላከያ የመሳሰሉ ነገሮች አሉአቸው ፣ አዳጊ አገሮችም ይህን እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ግን እሳትና ውሃን ንዲሁም የሚያስትሉአቸውንም ጥፋት ለመመከት ምንም መከላከያ የላቸውም፡፡ የእሳት አደጋ ቢርጌድ የሚባል ቢኖርም የተወሰኑ ትናንሽ ቃጠሎዎችን ከማጥፋት በቀር ሌላ ከዚያ ያለፈ ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ የሚገርመው ነገር እሳት ዓለት ማቅለጥ ሁሉ ይችላል፡፡ የእሳተ ገሞራ ፍሳሽ እኮ የአለት ቅላጭ ነው፡፡ ታዲያ እሳት ይህን ያህል አቅም ያለው ከሆነ አደገኛነቱና አጥፊነቱም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡
        እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ለሕዝቡ ያስተላፈላቸው መልእክት በእሳት ውስጥ እያለፉ እንደማይቃጠሉ፣ በውሃም ውስጥ ሲሄዱ እንደማይሰምጡ የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ በውሃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፣በወንዞች ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፣ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አያቃጥልህም ፣ ነበልባሉም አይፈጅህም( ኢሳ 432) ይላል፡፡ ይህ አባባል ምን ያህል አስገራሚ ቃል እንደሆነ እናስብ፡፡ ሰው እንዴት ነው እሳት ውስጥ ገብቶ የማይቃጠለው? በውሃ መካከልስ እየሄደ እንዴት አይሰጥም? በእሳት ውስጥ ያለ ሰው እንዴት ሆኖ ነው ነበልባሉ የማይፈጀው? በእውነት ይህ አስገራሚ የሆነ የእግዚአብሔርን ጥበቃና እርሱ ለእኛ የሚሰጠውን ዋስትና ያረጋግጥልናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕይወታችን በእሳት ውስጥ እንደማለፍና በወንዞች መካከልም እንደመራመድ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በርካታ አስደናቂ እውነቶችን እንማራለን፡፡
        1.      እሳትና ውሃ ማለፊያችን እንጂ መኖሪያችን አይደለም፡፡ አዎን በሕይወታችን እንደ እሳት የሚነድዱና እንደ ውሃ የሚመነቃቅሩ ፈታኝ ሁኔታዎች ሊፈጠሩብ ይችላሉ፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ እናልፍበታለን እንጂ ዕጣ ፋንታችን አይሆንም፡፡ ቃሉ በእሳት ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ፣ በሄድህ ጊዜ ይላል እንጂ እሳቱና ውሃው መኖሪያህ በሆነ ጊዜ አይልም፡፡ ስለዚህ እሳቱ ውስጥ መግባታችንን ብቻ አንመልከት በውስጡ አልፈን ወደ ጫፉ ወይም ወደ ዳር እንደምንወጣም ደግሞ እናስብ፡፡ የማዕበሉና ኃይል ስናይና የእሳቱን ትኩሳት ስንሰማ እንጨነቃለን፡፡ በዚያ ውስጥ የምናልፍበት ጊዜው አጥሮልን ለማየትና ቶሎ ለመገላገል እንቸኩላለን፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ጊዜ ሳይሆን በእኛ ጊዜ እንዲሆንልን ስለምፈልግ ነው፡፡ እግዚአብሔርም በሥጋ ዓይናችን ስለማይታየን ከውሃው ሙላት፣ ከማዕበሉ ጉልበትና ከእሳቱ ትኩ ጋር የምንታገለው እኛው ብቻ ይመስለናል፡፡ ትላንት እግዚአብሔር እንዴት እንደረዳንና እንዳሻገረን ሳይሆን ዓይናችን የሚያርፈው ከፊታችን ሆኖ የሚንቀለቀለው እሳትና በሚገለባበጠው ወጀብ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ መንገዱ የረዘመብን ስለመሰለን እንጨነቃለን፣ እግዚአብሔርም የተወን ይመስለናል፡፡ በቀን 24 ሰዓታት ብቻ መኖራቸው ለማንም ግልጽ ቢሆንም መከራን የምንቀበልባት ሌሊት ሰዓቱ የተጨመረ ይመስልብናል፡፡ አንዳንዴ 2 ሰዓት ያህል ጊዜ የሁለት ወር ያህል ይረዝምብናል፡፡ ይህ የሚሆነው ቶሎ ነግቶልን ብርሃን ለማየት ስለምንጣደፍ ነው፡፡ ሌሊቷ ግን በተወሰነላት መሠረት እንጂ እኛ ስለ ቸኮልን ብላ ከእኛ ጋር አትጣደፍም፡፡ የሆነ ሆኖ ሌሊቱ ምንም መራራ ብትሆንም ስለ እኛ ብላ ሳይሆን እንዲትነጋ በተወሰነላት መሠረት መንጋቷ አይቀርም፡፡ የሚገርመው ግን ያቺ ሌሊት ሰትነጋ ምንም ሳንሆን ማደራችንን እንገነዘባለን፡፡ በሰላም ያሳደረን የተጨነቅንበት ጭንቀት ሳይሆን ማዕበሉን የሚቆጣጠር፣ የእሳቱን ኃይል የሚያደርገውና ጨለማውን የሚያበራው ጌታ ከልሎን ስለሚያሻግረን ነው፡፡ እርሱ አሁንም በምንሄድበት መንገድ ሁሉ ከእኛ ጋር ሆኖ ያሻግረናል፡፡
          2.     እሳቱ መጥሪያችን እንጂ መጥፊያችን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ወደ እሳት ውስጥ ሲያስገባን ሊያጠፋን ወዶና አቅ አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚያ ሁኔታ ውስጥ በማሳለፍ የጠራንና ወደ ከበረው የሕይወት ደረጃ የደረስን እንድንሆን ወዶ ነው፡፡ በአንገታችንና በእጃችን የምደርገው ወርቅ እንደዚያ ያማረውና ለሰው ሁሉ እይታ የሚስብ የሆነው እንዲሁ በቀላሉ ሳይሆን በእሳት ተፈትኖ ካለፈ በኃላ ነው፡፡ የክርስትና ሕይወትም እንደ እሳት ተፈትን የምናልፍበት መንገድ ነው( 1 ጴጥ.411)፡፡ ወደ እሳት ውስጥ ሳያልፍና ሳይቀልጥ የሚያምር መልክ ያለው ወርቅ እንደሌለ ሁሉ እግዚአብሔር ባዘጋጀለት የፈተና መንገድ ሳያልፍ ወደ ክብርና መንፈሳዊ በረከት ሊደርስ የሚችል ርስትናና የክርስትና ሕይወት ሊኖር አይችልም፡፡ ልብስ ስንለብስ መልበስ የሚያምረው በውሃ ከታጠበ በኃላ በካውያ በደንብ ሲተኮስ ነው፡፡ የምንበላው ምግብም የሚያረካ ጣዕምና የሚስብ ቃና ወይም ሽታ የሚኖረው በእሳት የተቀቀለ፣የተጠበሰ ወይም የተቆላ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በእሳት ውስጥ ማለፍ ወደተሻለና ወደሚፈለግ ማንነት ያሸጋግረናል፡፡
        3.    እግዚአብሔር እሳቱን አጠፋለሁ ወንዙንም አደርቃለሁ የሚል ተስፋ አልገባልንም፡፡ እሳቱ እየነደደ ሳትቃጠሉ፣ ወንዙም ሞልቶ እየፈሰሰ እናንተ ግን ሳትሰጥሙ እንዲታልፉ አድርጋችኋለሁ ነው ያለን እንጂ፡፡ በዚህ ሁኔታ ስንሆን አምላካችን ከሚነደው የእቶን የበላይ ፣ የወንዙም ሙላት በእርሱ ፊት ኃይል የሌለው መሆኑን እንማርበታለን፡፡ እሳቱ ቢጠፋና ውሃውም ቢደርቅ የእግዚአብሔርን ታላቅነት የምናይበት መንገድ ብዙም አይሆንም፡፡ ያስፈራንም የእሳቱ መንደድና የወንዙ ሙላት ነው፡፡ ያ ባይሆንማ ምኑን አይተን ነው የምንፈራው፡፡ የሕይወት ጉዞ ያለ ምንም መውጣትና መውረድ የምንጓዝበት ቢሆንማ አትፍሩ ባልተባልን ነበር፡፡ የእግዚአብሐየርን ሥራ በሰዎችም ሕይወት ያደረገውን ሁሉ በምናይበት ጊዜ የሚያሰፈራውን ነገር አጥፍቶና ግድሎ ሳይሆን ያ አስፈሪ እንዳለ ሕዝቡን ግን ያስመለጠበትን ታሪክ እንመለከታለን፡፡ የእሥራኤል ሕዝብ ከግብዕ ባሪበት ወጥና አምልጦ ወደ ተስፋው ምድር በሚጓዝበት ወቅት በፊታቸው የነበረውን የኤሪትራን ባሕር አላደረቀላቸውም ይልቁን ከፈለላቸውም እንጂ፡፡ ሲድራቅ ፣ ምሳቅ አብዲናጎ ወደ ሚነደው እቶን እሳት ውስጥ በተጣሉ ጊዜ እሳቱን አላጠፋላቸውም ፣ ነገር ግን ሰውነታቸውን የእሳቱ ሽታ እንኳ እንዳይነካቸው ከሥስቱ ጋር አራተኛ ሆኖ ወደ እሳቱ ገባ እንጂ፡፡ ዳንኤል ወደ አንዳሳዎች ጉድ ጓድ የተጣለትን አስደናቂ ታሪክ ስናይ ጌታ እነዚያን ጨካኝ አናብስትን አልገደላቸውም፡፣ መላእክቱን ልኮ አፋቸውን ዘግቶ ባሪያውን ግን በጭናቸው እንተራሶ አሳደረው እንጂ፡፡ እነዚህን ታሪኮች ያየ ሁሉ የሚደደነው ለዚህ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር እሳት ሲነድ ፣ ማዕበል ሲያናውጠን ፣ እዲሁም ደግሞ በመንገዳችን ወንዙ ሲሞላ ሁሉ በዚያ ውስጥ ሰላም ያሳፈናል፡፡ ስለዚህ እሳቱ እየነደደ፣ ሰይጣንም እንደተራበ አንበሳ እያገሳ እኛ ግን በድል እንጓዛለን፡፡ እግዚእሔርም ለእኛ ወዳዘጋጀልን የክብር ሥፍራም እንደርሳለን እንጂ በመንገድ አንቀርም፡፡ ስለዚህ ጌታ አትፍሩ ይለናል፡፡
         4.     በውሃ ውስጥ የምናልፍበት ምክንያት እግዚአብሔር በዚያ ውስጥ መንገድ ስላለው ነው( ኢሳ. 4315)፡፡ እግዚአብሔር በዚያ መንገድ ባይኖረው ኖሮ እኛም ባላለፍንና በዚያው ሰምጠን በቀረን ነበር፡፡ ብዙ የምናውቃቸው ነገሮች ቢኖሩንም የእግዚአብሔርን መንገድ ማወቅ ግን እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ንገድ እኛ ከለመድነው ውጭ ነው፡፡ እንደነ ሙሴ የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች የእዚአብሐሔርን መንገድ መወቅ እንዲችሉ አማላቸውን አብቀው ለምነዋል፡፡ እርሱም ሲናገር መንገዱ ከእኛ መንገድ በፍጹም የሚለይ መሆኑን ተናግሮናል፡፡ አሳችሁ እንደአሳቤ መንገዴም እንደ መንገዳችሁ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር፣ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው( ኢሳ 557)፡፡ እግዚአብሔር በወጀባና በአውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው(ናሆም 17)፡፡ ስዚህም ይህ እግዚአብር ሕዝቡን ራሱ መንገድ እየመራ ምድረ በዳው ሳያቃጥለው፣ ውሃውም ሳያሰጥው ያሻግረዋል፡፡ ጎርፉ እንዳይስደውም ጥንቃቄ ያደርግለታ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የምንጓዝበት መንገድ እግዚአብሔር ያዘጋጀልን ስለመሆኑ እርግጠኛ እንሁን እንጂ አውሎ ነፋስና ወጀብ ስለ መኖሩ አንጨነቅ፡፡ በምናነበው ክፍል በቁ 16ላይ የእግዚአብሔር መንገድ እንዴት እንደሆነ ሲናገር እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውሃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል ይላል፡፡
          5. በእሳት ውስጥ ስናልና በውሃ ውስጥ ስንሄድ ጌታ ከእኛ ጋር ይሆናል(.25)፡፡ በውሃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፡፡ የእግዚአብሔር ነገር ፍፁም ለማመን የሚያስቸግር አንዳንዴም ምኝነት ይመስላል፡፡ ይሁን አንጂ ለሚታመኑበት ደግሞ እውነት ነው፡፡ ከፍ ብሎ እንደተገለጸው እሳት አያቃጥለንም ውሃም ሊያሰጥምን አይችልም ስንል አንድ ፍጥረታዊ ሰው ቢሰማን ስለ ሞኝነታችን ከልቡ ሊስቅ ይችላል፡፡ ምስጥሩ ግን ውሃው የማስጠም ባሕሪዩን ስለተው ወይም እሳቱም ከማቃጠል በርዶ ሳይሆን ጌታ አብሮን መኖሩ ልዩነቱን ማምጣቱ ነው፡፡ በሕይወታችን እንደ እሳት የሚፈትን ነገር ቢገጥመንና እንደ ማዕበልም ያለ ሁኔታ ተነስቶ ቢያናውጠን ከሚናየው ነገር ይልቅ ከእኛ ጋር ያለውን የጌታን ህልውና እንመልከት፡፡
         6. በእግዚአብሔር ዓይን ታይተናል፣ በውድ ዋጋም ተገዝተናል(.1)፡ እግዚአብሔር አምላካችን በእኛና የእኛ በሆነው ሁሉ ላይ ባለቤት ነው፡፡እርሱ በእኛና ጉዳዮቻችን ላይ ያገባዋል ፡፡ እሥራኤል እግዚአብሔርን ባለመታዘዛቸውና በመንገዱ ባለመሄዳቸው ምክንያት ጥቂት ጊዜ ቀጥቶአቸዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ምናልባት እግዚአብሔር ከምድር ላይ የሚያጠፋቸው መስሎአቸው አስበውም ይሆናል፡፡ ከዚህ የተነሳ በሕይወታቸው ፈርተውና ሰግተው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እነርሱ እንደሚያስቡት ሳይሆን እግዚአብሔር ለእነርሱ የተለየ ልብ ነበረው፡፡ ምንም እንኳን የማይታዘዙ ቢሆኑም እግዚአብሔር አሁንም ሕዝቡን ይፈልገዋል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በመሆናቸው ከእርሱም ጋር አብረው ስለኖሩ እርሱ ዓመጽን እንደማይወድና በዚያም ምክንያት እንደሚቀጣ ያውቃሉ፡፡ ለምርኮ የተጋለጡትም ካለመታዘዛቸው የነተነሳ መሆኑን በደንብ ተረድተዋል፡፡ ያ የእግዚአብሔር ቅጣት ያላላቀና እነርሱም የሚጠፉ መስሎአቸው ፈርተዋል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ነቢዩን ልኮ ሲያጽናናቸው “አሁንም እሥራኤል ሆይ የፈጠረህም እሥራኤል ሆይ፣የ ሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡ ተበዥቼሃለሁና አትፍራ ፣ በስምህ ጠርቼሃለሁና አንተ የእኔ ነህ” በማለት ለሕዝቡ ያለው አቋም ያስረዳል፡፡ ስለ ማነቱም ሲናገር እኔ አምላክህ ነኝ የሠራሁህም እኔ ነኝ፣ ደግሞም በዋጋ ገዝቼህ ወደ እኔ መልሼሃለሁ፡፡ ስለዚህ አንተ የእኔ ስለሆንክ አትፍራ በማለት ያጽናናቸዋል፡፡ የአምልኩን ምሕረትና ቸርነት ለሚናፍቀው የእሥራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ያለው ጥንቃቄና ረህራሄ እጅግ በጣም ከፍ ያለ መሆኑን ከዚህ አገላለጹ መረዳት እንችላለን፡፡ ምንም እንኳን እግዚአብሔርን ማስደሰት የምንችልበት ማንነት ባይኖረንና እርሱን የሚያሳዝን ነገሮችን ለማድረግ በጣም የተጋለጥን ብንሆንም አሁንም ስለ እኛ ግድ ይለዋል፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ነን፣ የእርሱ የእጅ ሥራዎች ነን ምክንያቱም እርሱ ሠርቶናልና፡፡ እርሱ በዋጋ ገዝቶን የቃል ኪዳኑ ሕዝብ አድርጎናል፡፡ ስለዚህ አትፍሩ ይለናል፡፡
















Tuesday, May 20, 2014


የቅዱሳንን  ልብ የሚያሳርፍ አገልግሎት
                                                                       

                                                   ከፓስተር ሳሙኤል ሾንጋ 

በአንድ ወቅት በአሜሪካን አገር ግራንድ ራፒዲስ በሚባለው ከተማ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የእግዚአብሔርን ፊት በጾምና በጸሎት እየፈለግን ባለበት ሰዓት የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያካፍል የተመረጠው ሰው ለመልእክቱ መግቢያ ያደረገውን የማይረሳ ምሳሌ ሁል ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡ እንዲሀ ነው ነገሩ!  እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2009 የተባበሩት መንግታት የኢኮኖሚ ፎረም ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ የተለያዩ የመንግሥታቱ አባል አገሮች ተወካዮች የየአገራቸውን የሥራ ሪፖርት ይዘው ቀርበው ነበር፡፡ ከአገሮች የመጡ ወካዮች ምን ለሥራት ታሰቦ ምን አንደተከናወነና እንዴት ያለ ለውጥ እየታየበት እንደሆነ እያካፈሉ አንዳቸው ከሌላው ልምድም እየቀሰሙ ባለበት ወቀት የአንድ አገር ሪፖርት ግን የብዙዎችን ልብ የነካና የተደነቀ ነበረ፡፡ ያቺ አገር በሩቅ ምሥራቅ የምትገኝ ባርማ በመባል የምትታወቅ አገር ነች፡፡ ባርማ በ2009 .ም ልትሠራ ያቀደችውና ያከናወነችው ሌሎች አገሮች ካቀረቡት ጋር በፍፁም የይገናኝ ነገር ግን ሁሉንም ያስደነቀ አቀራረብ ነበር፡፡ ሌሎች ያቀረቡት ስለ ልማት፣ ስለ አኮኖሚያዊ እድገት፣ ስለ ውጭ ግንኙነትና ስለ ወታደራዊ ዝግጅቶቻቸው ሆኖ ካቀዱት ምን ያህል እንደተሳካላቸው ነበር ያቀረቡት፡፡ ነገር ግን ባርማ በ2009 መግቢያ ላይ የያዘቺው እቅድ በአገሪቱ ውስጥ ያለ እያንዳንዱን ዜጋ በነፍሰ ወከፍ ደስተኛ እንዲሆን ስለማድረግ ነበር፡፡ ከልማት ሥራዎች ሁሉ የሚቀድመው ዜጋው ረክቶና ተደስቶ የመኖር ጉዳይ ስለሆነ ከዚህ አንፃር አቅዳ 90 በመቶ እደተሳካላት ያቀረበቺው ሪፖርት ሁሉንም የጉባኤ ተሳታፊዎችን ሊያስደንቅ ችሏል፡፡
ይህ ለእኛ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለምናገለግል ሰዎች እጅግ በጣም አስገራሚ ትምህርት ያለበት ምሳሌያዊ መልእክት ነው፡፡ እኛ ከባርማ መንግሥት ይልቅ የምናገለግላቸውን ቅዱሳን ልባቸው እንዲያርፍ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔርም እኛን በዚህ ምድር ላይ ያስቀመጠን የእርሱን አሳብ እያለገልን በስሙ የተጠሩትን ሁሉ እንድናንፃቸው ነው፡፡ የአገልጋዮች አገልግሎት የምዕመናንን ልብ ያሳፈርፍ ዘንድ ይገባል፡፡ ይህ እዲሆን ደግሞ የእግዚአብሐሔር ቃል ይመክረናል፡፡ አገልግሎታችን የቅዱሳንን ልብ ማሳረፍ እንዳለበት የሚስተምረውን ትምህርት ለማግኘት ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን መልእክት ከቁጥር 1-7 መመልከት ይኖርብናል፡፡ ወደ ዋናው አሳባችን ከመግባታችን በፊት ስለ ፊልሞና መጽሐፍ ሁለት ወይም ሦስት መሰረታዊ በሕሪያቶችን እንመለከታለን፡፡
·         የፊልሞና መጽሐፍ ዋሪያው ጳውሎስ እሥር ቤት ሆኖ ከጸፋቸው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ ጳውሎስ ይህንን መፅሐፍ በሚጽፍበት ወቅት በሮም እሥር ቤት ሊሆን ይችላል፣ ወይም በሌላ ቦታ ሊሆን ይችላል ብቻ መልእክቱን ያስተላፈው ከእሥር ቤት ነው፡፡ የፊልሞናን መጽሐፍ በጣም ተናፋቂ ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይህ ነው፡፡ ከየትና እንዴት በማንስ ተጻፈ የሚለው አሳብ የሚተላለፈው መልእክት ተሰሚነት እንዲኖረውና አቅም እንዲያገኝ ያደርገዋል( .9)፡፡
·         የፊልሞና መፅሐፍ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካሉና በጣም አጠር ካሉ ወይም ምዕራፍ ከሌላቸው መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ በጠቅላላው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ አራት ያህል መጻሕፍት በምዕራፍ ያልተከፈሉ ሲሆን እነርሱም አብዲዩ፣2 ዮሐንስ፣ 3ኛ ዮሐንስ ና ፊልሞና ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በምዕራፍ አይከፋፈሉ እንጂ ትልቅ ቁም ነገር ያዘሉ ናቸው፡፡  በምዕራፍ ያልተከፈሉበት ምክንያት አጠር ባለ መልክ ስለቀረቡ ብቻ እንጂ መልእክቱ ከእግዚአብሔር ስላልሆነ አይደለም፡፡
·         የፊልሞናን መጽሐፍ ልዩ የሚያደርገው የመልእክታቴ ምጋቤ አካል ከሆኑት መጸሕፍት የሚመደብ መሆኑ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ለቡድን ወይም ከቤተ ክርስቲያን ወይም ለአንድ አገልግሎት ክፍል የተላከ ሳይሆን የሕዝብ እረኛና አገልጋይ ለሆነ ሰው በግሉ የተላከ የመጋቢያዊ መልእክት ያዘለ ነው፡፡ ለአንድ ግለሰብ የተላኩ ሌሎችም መጻሕፍት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉ ሲሆን ሁላቸውም የየራሳቸው ባሕሪያት ያሉአቸው ናቸው፡፡
በዚህ አጭር ትምህርት ውስጥ ሐዋሪያው ጳውሎስ ለፊልሞ የሚያቀርበውን መልእክት ሁሉንም ማየት እችልም ፣ ነገር ግን ከቁ 1-7 ያለውን ብቻ እንመለከታለን፡፡ ይንን መልእክት የሚያስተላልፈው የእግዚአብሔር ሰው ጳውሎስ የጌታ አገልጋይ ከሆነው ከፊልሞና ጋር ትልቅ የአልግሎት መተሣሠር ነበረው፡፡ ጳውሎስ በእሥር ቤት ሆኖ ስለ ፊልሞና አገልግሎት የሰማው ነገር በእርሱ ላይ የፈጠረው አዎንታዊ ተጽእኖ በዚህ የንባብ ክፍል ውሰጥ ይገኛል፣ ምክንያቱም ጳውሎስ በፊልሞና አገልግሎት ምክንያት መጽናናቱንና መደሰቱን ይናገራል( . 7)፡፡ ጳውሎስ የተደሰተበትና በብዙ መጽናናት የተጽናናበት ምክንያት አለ፣ ያውም በፊልሞና አገልግሎት በቤተ ክርሰቲን ያሉ ቅዱሳን ልብ አርፏል፡፡ የምዕናንና የአገልገሎት አጋሮችን ልብ የሚያሳርፍ አገልግሎት ማገልገል እንዴት ያለ ትልቅ መታደል ነው!
ፊልሞና የሚያገለግለው አገልግሎትና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያደርገው ሥራና ተግባር ሁሉ የሕዝቡን ልብ ከመረበሽና መንፈሳቸውን ከማናወጥ ይልቅ ልባቸውን የሚያሳርፍ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛ ዛሬ በዚህ ዘመን የምንገኝ አማኞች የቅዱሳንን ልብ ከማሳረፈ አንፃር እንዴት አይነት አገልግሎት እየሰጠን እንደሆነ ራሳችንን መመልከት ይኖርብናል፡፡ እስቲ የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ ሕይወትና አገልግሎት ምን እንደሚመስል ሐዋሪያው ጳውሎስ ለፊልሞና ከጻፈው መልእክት እንመልከት፡፡
1. አገልገሎቱ የቅዱሳንን ልብ ሚያሳርፈው አገልይ የይቅርታ ልብ ያለው ነው፡፡
ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለፊልሞና የሚልክበት ተቀዳሚ ምክንያት በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል ክርስትያናዊ ይቅርታን ለማስፈን ነው፡፡ ይህ የፊልሞና መጽሐፍ ሙሉውን የሚናገረው ስለ ይቅርታ ነው፡፡ ፊልሞና በፍቅርና ሌሎች መልካም ሥራዎች የቅዱሳንን ልብ ያሳረፈ ምርጥ አገልጋይ ቢሆንም ጳውሎስ በድጋሚ ስለ አናሲሞስ ይጠይቀዋል፡፡ አናሲሞስ የፈልሞና አገልጋይ (በጥንት አባባል ባሪያው) የነበረ ሰው ነበረ፡፡ ከፊልሞናም ጋር አብሮ ይኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ፊልሞናን ዘርፎ የኮበለለ ሰው ነው፡፡ ይህ በመሆኑ የፊልሞና ልብ በአናሲሞስ ማዘኑ የማይቀር ነገር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አናሲሞስ ኮብልሎ በሄደበት ጳውሎስ አገኘውና ወንጌል ሰበከለት፣ አናሲሞስም በጌታ  በኢየሱስ አመነ፡፡ ጳውሎስ በሮም እሥር ቤት በነበረበት ወቅት በወንጌል እንዲያምን ምክንያት ስለሆነው አናሲሞስ ይረዳውና ያግዘዘው ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ የአናሲሞስ ለጳውሎስ አስፈላጊ ሰው ቢሆንም ያለ ፊልሞና ፈቃድ ለራሱ ሊያስቀረው ስላልፈለገና በሁለቱ መካከል የይቅርታ መንፈስ እንዲሰፍን ስለፈለገ ወደ ፊልሞና ይልከዋል፡፡ እንዲያውም ፊልሞና አናሲሞስን እንደ ወንድሙ እንዲቀበለው ይማጸነዋል፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን የተደበለውንም ሁሉ በእርሱ ላይ እንዲቆጥርበት ይጠይቀዋል፡፡ እንግዲህ ከዚህ የምናየው እርቅና ሰላም በሌለበት ሥፍራ ሁሉ ጭንቀትና መረበሽ እንዲሁም አለመረጋጋት መኖሩን ነው፡፡ ስለዚህ ነው ሐዋሪያው እባክህ ልቤን አሳርፍልኝ የሚለው! ይህ የጌታ አገልጋይ ባደረጋቸው ሥራዎች ሁሉ የቅዱሳንን ልብ በማሳረፍ የሚታወቅ ቢሆንም አሁን ደግሞ ለአናሲሞስ ይቅርታ በማድረግ የበለጠ የጳውሎስን ልብና የሌሎችን ልብ እንዲያሳርፍ ይጠይቀዋል፡፡ ይቅርታ ሲደረግ የቅዱሳን ልብ ያርፋል ማለት ነው፡፡ ሁለት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሲጨቃጨቁና ሲቃረኑ እንቅልፉን የሚያጣው ምዕመኑ ነው፡፡ ሁለት መጋቢዎች ባለመግባባት እርስ በእርሳቸው ሲገፋፉ የሚያዝነውና የሚረበሸው ጉባኤው ነው፡፡ መሪዎች እርስ በእርሳቸው የሰላምና የፍቅርን አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በምዕመናን መካከል ያለው ደስታና ፍንደቃ ትልቅ ይሆናል፡፡
የብሉይ ኪዳን መጸሕፍትን በምንመለከትበት ወቅት የእሥራኤል ሕዝብ  ለጦርነት ከተጋለጠባቸው ምክንያች አንዱ የመሪዎች ሁኔታ ነው፡፡ በአንጸሩ ደግሞ አገርን ከሚመሩ ነገሥታት የተነሳ ምድርት አርፋ እንደምትቀመጥ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ በእርሱ ጊዜ ምድሪቱ በሰላም አርፋ ተቀመጠች ይላል(2ኛ ዜና 15 11-15፣19፣20፡30)፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በቤተ ክርስቲያንም የሚያገልግሉ መሪዎች እርስ በርሳቸው በፍቅር ሲቀባበሉና ሲዋደዱ በመላ ቤተ  ክርስቲያን የሚታየው ደስታ እጅግ የላቀ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ ፊልሞናን  ልቤን አሳርፍልኝ  ማለትም ይቅርታ በማድረግ ልብ የሚሳርፍ ሥራህን ቀጥል ማለቱ ነው፡፡
ዛሬም በእኛ ዘመን የሚያስፈልገን የአገልግሎት ብዛት አይደለም፡፡ ብዙ መስበክም አይደለም፡፡ ነገር ግን የቅዱሳንን ሁሉ ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ሆነን መገኘት ነው፡፡ እኛ ይቅርታን የማይቀበል በቀለኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ያደግን ሰዎች ነን፡፡ አብዛኛው ባህላችን ቁጣና በቀል የተሞላ ነው፡፡ ብድር በምድር የሚለው አስተሳሰብ አብሮት ከማደጉ የተነሳ  ትውልዳችን ይቅርታን መጠየቅን እንደ ሽንፈት፣ ይቅርታን ማድረግን እንደ ሞኝነት የሚቆጥር ትውልድ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ አብሮን ሳላደገ  ጌታን ተቀብለን አገልጋዮችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሆንንም በኃላ  እንኳ ያ አብሮን ያደገው  ልማዳችን ከውስጣችን አልወጣ ብሎ ጊዜ ይወስድብናል፡፡ ስለዚህ ብዙዎቻችን በእግዚአብሔር ቤት እንበቃቀላለን፣ አንዳችን ሌሎችን እናሳድዳለን፡፡በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እናገለግላለን፣ ግን በእግዚአብሔር መድረክ ላይ እያለንም በቀለኝነት ያጠቃናል፡፡ ይህ ከመሆኑ የተነሳ የእግዚአብሄርም ልብ አልተደሰተም የቅዱሳንም ልብ አላረፈም፡፡  ዛሬም ቢሆን እያንዳንዳችን ቆም ብለን እኛ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እያሳረፍን ነው ወይስ እያሳዘንን; እያራወጥነው ወይስ እያረጋጋነው፣ እያጽናናነው ወይስ እያስጨነቅነው ነው የሚለውን ጠይቀን መልስ ማግኘት ይኖርብናል፡፡ የእግዚብሄርን ቃል በማስተማርና የተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጻፍ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ትልቅ አክብሮት ያላቸው ዶር ጆን ማካርተር  ይቅርታ አለማድረግ እንዴት ያለ ክፉ ነገር እንደሆነ እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡
·         ይቅርታን አለማድረግ ባለፈው የመራርነት ሕይወት እሥረኞች እንድንሆን የሚያደርገን ነው፡፡
·         ይቅርታን አለማድረግ ለሰይጣን አሠራር የተከፈተ በር የሚሰጥ ሲሆን እኛም አጋንንትን በዚያው እንኳን ደህና መጣህ እያልነው ነው፡፡
·         ይቅርታ አለማድረግ በእኛና በእግዚአብሔር መካካልላለን ሕብረት እንቅፋት ነው፡፡ ምከንያቱም ጌታ ኢየሱስ  ሲያስተምር ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ የሰማዩ አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም፡፡ 
ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ካላልን ደስታችንና ሰላማችን ይወሰድብናል፡፡ ጳውሎስ በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል ሆኖ ሁለቱን የሚሸመግላቸው ይመስላል፡፡ አናሲሞስ ፊልሞናን በጣም አድርጎ በድሎታል፡፡ ጳውሎስና ፊልሞና በነበሩበት ዘመን አናሲሞስ ያደረገውን ዓይነት በደል የፈጸመ በባህላቸው መሠረት ይወገዛል ፣  ይሰደዳል እንዲያውም ይገደላልም፡፡  አናሲሞስ የፈጸመው ወንጀል በማንኛውም ማኅበራዊ ና ሕዝባዊ ጉዳዮች ሥፍራ እንዳይኖረው  የሚያደርግ ነው፡፡ምክንያቱም አናሲሞስ ለፊልሞና ባሪያው ሆኖ እያለ ያንን በአሠሪዎች ዘንድ ከባድ ወንጀል ሆኖ የሚታወቀውን ጥፋት ሠራ፡፡  ምናልባት አናሲሞስ ከአካባቢው የሸሸው የሚደርስበትን መከራ ፈርቶም ሊሆን ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ ግን ይህንን በደለኛውን ሰው እንደወንድምህ ቁጠረው ይላል፡፡ ይህ ቀላል ሊሆን የማይችበት ምክንየት አለ፡፡ አንደኛ ባሪያና ጌታ ሁለቱ እኩል በማዕድ መቀመጥ የሚችሉበት ባህላዊ አግባብ በጊዜው አልነበረም፡፡ ዘራፊና ቀመኛ ምንም ቢሆን ከተቀማው ሰው ጋር ሕብረት እንዲያደርግና ከዚያም አልፎ እንደ ወንድም ሊቀበል የሚችል ሥርዓትም ሆነ ልማድ አልነበረም፡፡ የእግዚአብሔር ህግ ግን ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ እንደ ወንድምህ ቁጠረው ፣ ባሪያ ከነበረበት እንደ ወንድምህ አድርገው የሚል ነው፡፡ ጥፋት አድርሶ የኮበለለውን የጠገበ ሠራተኛ ወደ ሥራው እንዲመለስ አሠሪውን እንማፀነው ይሆናል ፣ ወንድም  አድርገው  ማለት ግን ምንም  የማይታሰብ ነው፣ ማለት የሚፈልግም ካለ ደግሞ ሆን ብሎ ሽምግልናውን ለማደፍረስ እንዳሰበ ሰው ሊፈረጅበት ሁላ ይችላል፡፡ ጳውሎስ ለፍልሞና የሚናገረው መልእክት ግን ወደ ሥራው እንዲመላስ ከሚለው የዘለለና እንደ ወንድም ቁጠረው የሚለው ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ክርስትና ሲገባን ብቻ ነው፡፡ ስለ ይቅርታ ሰብከው ሲመለሱ ወንድማቸውን ይቅር አልልም ብለው ሳምንት ሙሉ ሽማግሌ የሚያመላልሱ አገልጋዮች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ስብከት ችለዋል እንጂ ክርሰትናው ገና አልገባቸውም አሊያም ክርስትና የሚያሰከፍለውን ዋጋ ገና አላወቁትም፡፡ ምክንያቱም ክርስትና የዘረፈህን ጥጋበኛና  ጎረምሳ አገልጋይን ወደ አንተ ሲመጣ እንደ ወንድምህ አድርገው እንጂ እንደ ሠራተኛህ አትየው የሚል ነው፡፡
ጳውሎስ ስለ ፊልሞና የተረዳው ሁሉ አዎንታዊ ነው፡፡ የሚያርምበት አንድም ነገር እስከማይኖርበት ድረስ ሕይወቱ የተመሰከረለት ሰው ነው፡፡ ምን አይነት ማራኪ ሕይወትና የተመረቀ ባሕሪይ ነው! አሁን ግን ለአናሲሞስ ይቅርታ በማድረግ የበለጠ ይመሰገናል፣ ክርሰቲያናዊ ጀግና ይባላል ወይም ብዙ የሆነው መልካም ነገሩ በአንድ ነገር ምክንያ ብቻ ዋጋው ሊረክስበት ይችላል፣ ያውም ይቅርታ በማድረግ ወይም ባለማድረግ፡፡ ብዙ የመድረክ ጀግኖች ተፈትነው  ጊዜ ሳይወስድባቸው ክብደታቸው ሲቀልል ታይተዋል፡፡ እኔ እኮ ጌታን ካገኘውና በመንፈስ ቅዱስ ከተሞላው ይህን ያህል ዓመት ሆኖኛል፣ እነ እገሌም በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉት እኔ እጅ ጭኜ ስጸልይ ነው ብለው የሰውን ሁሉ እትኩሮት ሲሲቡ የኖሩ ቱባዎቻችን ክርስትናቸው ከወጣበት በአንዴ ሲወርድ ያየነው ለባልንጀራቸው ይቅርታ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ ያዙኝ ለቀቁኝ  ሲሉ  ያየን ቀን ነው፡፡ ስለዚህ የዛሬ አገልጋዮችና ምዕመናንም ብንሆን ጳውሎስ እኛንም ጭምር ነው እየተናገረን ያለው፡፡ ምን ያህል ወንድሜን ይቅር ብየዋለሁ? ምን ያህልስ በይቅርታ ልብ  እመላለሳለሁ ወይስ በቀለኛ ነኝ? ከዚህ የተነሳ ጌታ በዙሪያዬ ያስቀመጣቸው ቅዱሳን ልባቸው  በእኔ ሥራና አገልግሎት አርፏል ወይስ እኔ እንዴት ነኝ? ብለን ለራሳችንም መልስ መስጠት ይኖርብናል፡፡ሰውን ከልቡ ይቅር የሚልና በደልን የማይቆጥር የክርስትና ሕይወት የገባውና በእርግጥ የተለወጠ አማኝ ነው፡፡ ይህ ማንነት እንዲኖረን ያስፈልገናል፡፡
2. የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ስለ ሰዎች ሕይወት የሚጨነቅ ነው( .4)፡፡
ፊልሞና ሕይወት የምንማረው እርሱ ለሰዎች ግድ የሚለውና ለእነርሱ የሚጨነቅ ማንነት ያለው መሆኑ ነው፡፡ በቅዱሳን ሁሉ ዘንድ ፍቅር ያለው ሰው ነበር፡፡ እር ከተወሰኑ ሰዎች ጋር በፍቅር የተሳሰረ ፣ ከተቀሩት ጋር ደግሞ አኩራፊ ዓይነት ሰው አልነበረም፣ ይልቁንስ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር በፍቅር የሚኖር ሰው ነው፡፡ ይህ ፍቅር ደግሞ ለሰዎች ሁሉ ሸክም እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ ጳውሎስ ያደረገውን ደግሞ ሲናይ ለፍልሞና ፍቅር እንዳለው ያሳየናል( ከቁ.11-14)፡፡ አናሲሞስ ከፊልሞና ይልቅ የሚያስፈልገው በእሥር ቤት ላለው ለጳውስ ነው፡፡ ጳውሎስም አናሲሞስን ከእራሱ ጋር ቢያቆየው የማይወቀስበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው፣ አናሲሞስ ገና ጌታን ሳያገኝ ከፊልሞና ኮብልሎ ሄዷል፡፡ ሁለተኛ ወንጌል መስክሮ  እንዲለወጥ ምክንያት ስለሆነው አሁን የወንጌል ልጁ ሆኖታል፡፡ ስለዚህ ቢያስቀረው ፊልሞናም ቢሆን ቅር ሊሰኝበት አይችልም፡፡ ይንጂ ጳውሎስ ከራሱ ጥቅም ይልቅ የፍሞናን በመስቀደም አናሲሞስን ወደ ፊልሞና ሲልከው እንመለከታለን፡፡ ከእኔ ይልቅ የአንተ ይሻላል የሚል አቅም ያለው ክርስትና ያለው ሰው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት የቅዱሳንን ልብ የሚሳርፍ ነው፡፡ እግዚአብሔም ደስ የሚሰኝበት ዲህ ዓይነቱ ሕይወት ነው፡፡
3. የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ስለ እግዚአብሔር የሚያስብ ነው(4-5)፡፡
የእግዚአብሔር ክብርና ከእርሱ ጋር ያለን ሕብረት ግድ የሚለን ስንሆን የቅዱሳን ልብ ያርፋል፡፡ ጳውሎስ በዚህ ክፍል ስለ ፍልሞና እምነት ሰምቶ እግዚእብሔርን ያመሰግናል፡፡ እምነት እኛን ከእግዚአብሔር ጋር ያገናኘናል፡፡ ፍቅር ደግሞ ከሰዎች ጋር ያገናኘናል፡፡ እምነት ግን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ያንን መሰጠት፣ በርሱ ያለንን መተማመን እንዲሁም በጌታችን በፍጹም ማረፋችንን የሚያመለክት ነው፡፡ ፈልምና እውነተኛ የሆነ እምነት የነበርው ሰው ነው፡፡ በእውነትም የተመሰከረለት አማኝ ነው፡፡ ስለዚህ ይቅርታ ማድረግ አይከብደውም፡፡ ሰዎች ከወንድሞቻቸው ጋር ያላቸውን ነገር የሚያበላሹት ከእግዚአብሔር ጋራ ያላቸው ነገር መበላሸት ሲጀምር ነው፡፡ ብዙዎች ከእግዚአብሔርና ከወንድሞቻቸው ጋር ካላቸው ህብረት ይልቅ ለመድረካቸውና ለአገልጋይነት ስማቸው ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የንስሐና የእርቅ ጥሪ እተደረገ ሰዎች በመካከላቸው ያለውን ርሾ እንዲስያወግዱ ይጋበዙ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ይህ በአዲስ አባባ ከተማ በሁሉም ዞኖች እየተደረገ ባለበት ወቅት እኔም በአንድ ቤ/ክ መልእክት እንዳቀርብ ስለተመደብኩ ጌታ የሰጠኝን ቃል ሳካፍል መንፈስ ቅዱስ በጉባኤው መካከል የሚያስገርም መነቀቃት ሲያደርግ ስላየሁ ከሁለት ቀን በኋላ ይህንን መልእክት በሌላ ቦታ ለመስበክ ሄድኩ፡፡ ቦታው ከአዲስ አባባ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ጉባኤው በጣም ትልቅ በመሆኑ ጸሎት ቤቱ ስላልቻለ ፕሮግርሙ የተካሄደው በሜዳ ላይ ነበር፡፡ በዚያ ኮንፍራንስ መልእክት ካቀረብኩ በኋላ የንሰሐ ጥሪ ሳቀርብ አንድ ወጣት ሚስቱን እንደበደላትና ይቅርታ ሊጠይቃት እንደሚፈልግ ተናገረ፡፡ ስለዚህ ከፕሮግራሙ መልስ ከቤተ ክርስቲያን መጋቢ ጋር በመሆን ሚስቱን አስጠራናትና ይቅርታ እንድታደርግለት ስንጠይቃት አባቴ ይህንን ጉዳይ መስማት አለበት አለች፡፡ አባቷ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ስለሆነ ከሰዎች ጋር የነገውን ፕሮግራም በሚመለከት አንዳንድ ሥራዎችን እየሠራ ካለበት አስጠራነውና ጉዳዩን ሁሉ አጫወትነው፡፡ ልጅቷ ይቅርታ አድርጋ ወደ ትዳሯ የመመለስ ልብ ቢኖረትም የአባቷ አቋም ግን ከጠበቅነው በላይ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ ልጅቱ ከባሏ ጋር በተፈጠረው ጊዜያዊ አለመግባባት ምክንያት ካለችበት ትዳር ወጥታ ወደ አባቷ ቤት መታ እዛው ናት፡፡ ጉዳዩን ለማስተካካል በጣም ሰፊ ጊዜ ወሰደብን፡፡ ልጁን የበደለውን ሰው ይቅር እንዲል ደጋግመን ብንለምነውና ብማጸነው አባትዬው በጭራሽ እምቢ አለ፡፡ በመጨረሻም ላይ እንዲህ ዓይነት ክርስቲና ይዘህ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ትሆን ስለማትችል አግደንሃል ሲሉት እንደዚህ ከሆነ እሺ እንዳላችሁት ይሁን አለ፡፡ ወጣቱ ባለትዳር ሚስቱን ይዞ ቤቱ ቢገባም ይህ ሽማግሌ ስለ ክርስቲናውና እግዚአብሔር ስለሚጠብቅበት ኑሮ ሳይሆን የተጨነቀው ስለ ሽምግልናው መሆኑ የሁላቸንንም ልብ እንዳሳዘነ አስታውሳሁ፡፡
ዛሬም በእኛ ዘመን ስለ ስማቸውና ስለ መድረካቸው እንዲሁም በሰው ፊት ስለሚታየው አገልግሎታቸው እንጂ   ስለማይታየው መንፈሳዊ ሕይወታቸውና የጌታ መንፈስ ከእነርሱ ስለሚፈልግባቸው  ነገር ግድ የማይላቸው ብዙ አገልጋዮችና መሪዎች ይኖራሉ፡፡ ፊልሞና ግን እንዲህ ዓይነት ሰው አይደለም፡፡ የሰሙትን ሁሉ የሚያስመሰግን እምነት ያለው ሰው ነው፡፡ ስለ እምነቱና ከእግዚአብሔር ጋር ስላው ሕብረት ግድ የሚለው ሰው ካሉት መለያዎች አንዱ ወንድሙን የሰዎችን ልብ ማሳረፉ ነው፡፡  እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት እግዚአብሔርን ያስደስዋል ፣ የቅዱሳንንም ልብ ያሳርፋል፡፡
4. የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ስለ እውነተኛ ሕብረት የሚያሳስበው ነው፡( 6)፡፡ 
በጌታ ያለን አማኞች ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር እውነተኛ እምነትን የቅዱሳን ሕብረት እንደሚከተለው ነው፡፡ አንድነት፣የወንድማዊ ፍቅርና ሰላም የክርስትያንነታችን ምልክትና የሕይወታችን ክፍል ነው፡፡ ከሌሎች ጋር በምናሳልፍበት ወቅት ከሌሎች እንማራለን፣ እንታነጽባቸዋለንም፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምንሄደው ስብከት ሰምተንና ተነቃቅትን ለመመለስ ብቻ ከሆነ ያ ሁኔታ እኛን ራስ ወዳዶች ያደርገናል፡፡ ይልቁንም ወደ ቅዱሳን ሕብረት የምንሄደው ለሌሎች በረከት ለመሆን፣ ከእርሱም ጋር ለመተያየትና እርስ በእርሳችንም ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃመም ጭምር ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት የምንሄደው ለጋራ በረከት ነው፡፡ የወንድማችንን ሐዘን ሀዘናችን ደስታውንም ደስታችን ልናደርግ ነው ፡፡ የእኛንም ሸክም እነርሱ እንዲጋሩ ለማድረግ ጭምር እንጂ ተሰብከን፣ ወይም ሰብከን ወይም ዘምረን ወይም ለራሳችን  በረከቱን አፍሰን ልንመጣ ብቻ አይደለም፡፡ ቅዱሳንም ልብ የሚያርፈው ይህ ሲሆን ነው፡፡
5. የቅዱሳን ልብ የሚያርፍበት አገልጋይ ስለ መንፈሳዊ እውቀት የሚያሳስበው ነው( 6)፡ እውቀት ስንል ተራ መረጃ ሳይሆን ስለ እግዚአብሔር ያለን ጥልቅ መረዳት ማለታችን ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ነገር በጽንሰ አሳብ ደረጃ ማወቅናTheoritical kbowledge በሕይወት ልምምድ ውስጥ ገብተን ማወቅ /exprencial knowledge/  ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ፅንሰ አሳብ በሆነው እውቀት ወደ ንስሐ አምልኮ፣ እንዲሁም ወደ ይቅርታ ሕይወት መድረስ አይቻልም፡፡ በአገራችን ሳለሁ በአውሮጳና በአሜሪካ እንዲሁም በሌሎች የምዕራብ አገሮች በየክረምቱ ስለሚወርደው በረዶ ከሚሰማው ነገር ተነስቼ ለሌሎችም ሰዎች አስረዳቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የተቆረቆሩ  የፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ ክርስቲያን ሕንጸዎች ጣሪያቸው ከመሀል ከፍ ያለና ዳርና ዳሩ ዝቅ ያለ ሲሆን ይህ አሠራር ምዕራባውያን በረዶው ሲወርድ ጣሪያው ላይ ሆኖ  እንዳይጎዳው እየተንሸራተተ እንዲወርድ  አድርገወው ስለሚሠሩት ሚሲዮናውያኑ ወደ አገራችን ሲመጡ ያንን የለመዱትን ዓይነት ቤት ስለሚሠሩ ነው የጸሎት ቤቶቸችን ሕንጻዎች ከሌላው የተለዩ የሚሆኑት ሲባል ስለ ሰማሁ እኔም ለብዙዎች የሰማሁትን ያንኑን አስረዳ ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ሁሉ የማስረዳው በረዶውን በዓይኔ እንኳን ሳላየው ነበር፡፡ ከብዙ ጊዜያት በኋላ ወደ ሚቺጋን መጥቼ በረዶ ሲወርድ፣ ከተማውን ሁሉ ሲሸፍን፣ መንገዱን ሁሉ ሲዘጋ በቤቶች ሁሉ ጣሪያ ላይ ተከምሮ ከዚያ እየተንሸራተተ ሲወድቅ፣ በጎዳናዎች  ሁሉ ተከምሮ ለመንዳት ሲያስቸግርና እያንዳንዱ የሚቺጋን ነዋሪ በወፋፈፍራም ልብሶች ተጀቡኖ ሲሄድ ሳይ ለበረዶ ያለኝ እውቀት የተለየ ሆነ፡፡ እንዲያውም እኔ በበረዶ ላይ ሲነዳና መኪናዬ መንገድ ስታ የወጣችበትን አጋጣሚ ሁሉ ሳስበው ሰው በመረጃ ብቻ የሚያውቀው እውቀት በሕይወት ልምድ ከሚያውቀው ምን ያህ የተለየ  እንደሆነ በለጠ ተገነዘብኩ፡፡ ጳውሎስም ይህ የሕይወት ልምድ እውቀት እንዲበዛለት ለልሞና እንደሚጸልይለት ቃል ይገባለታል፡፡ ይህ ጥልቅ እውቀትና መረዳት አፓጎኒሲስ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ስለ እግዚአብሔርና በእኛ ውስጥ ስላለው መንፈሳዊ ነገር ጥልቅ የሆነ መረዳት a deep understanding about God and about what in us/ ማለታችን ነው፡፡ በእኛ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀመጠው በጣም ብዙ የሆነ መልካ ነገር አለ፡፡ ጌታ ኢየሱስን ካመንንበት ጊዜ ጀምሮ ከእርሱ በጣም ብዙ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ተቀብለናል፡፡ ይህንን እግዚአብሔርን አውቆ መከተልና አውቆም ማገልገል ሕይወታችንን ያሳድገዋል፤ በእግዚአብሔርም ላይ ያለን መተማመን ይጨምራል፡፡ በእኛ ዘንድ ያለውን ሁሉ በማወቅ የሚለው አሳብ ል ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ብዙ መልካም ነገሮችን አስቀምጧል፡፡ ከጌታ ያገናቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች ክርስቶስን ወደ ወቅ እንድንደርስ የሚያደርጉን ናቸው፡፡ ስለዚህ የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ በክርስቶስ ስላው እውቀት ግድ የሚለው ነው፡፡
6. የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ለክርስቶስ ክብር ግድ የሚለው ነው(ቁ.6)፡፡
ፍልሞና ሁሉንም ነገር ያደረገው ለክርስቶስ ነው፡፡ መንፈሳዊ ፍሬንም የሚያፈራው ለክርስቶስ ነው፡፡ ጳውሎስ በአንተ ያለው ነገር ለክርስቶስ ፍሬን እንዲያፈራ እለምናለሁ በማለት ለፍልሞና የሚጸልየውን የጸሎት ይዘት ይገጻል፡፡ በአገልግሎታችን ፍሬን ብናፈራ ያ ፍሬ ክርስቶስን ለማክበር መሆን አለበት፡፡ ሰዎችንም በአገልግሎታችን የምናዘጋጀው ለክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ በእኛ ሕይወትና ኑሮ በሚከብርብት ወቅት የምናገልግላቸውና አብረውን ጌታን የሚያመልኩ ሰዎች ልባቸው ያረፈ ይሆናሉ፡፡
  ስለዚህ ጳውሎስ ይንን አንቀጽ ሲደመድም ልቤን አሳርፍልኝ ይላል፡፡ ዛሬም ሰዎች ተንቀዋል፣ ፈርተዋል፣ተረብሸዋል፣ ግራም  ተጋብቷል፣ምእናንም በአገልጋችና በመሪዎች መካከል ካለው አላስፈላጊ ሽኩቻ የተነሳ ተንገላትተዋል፣ከቦታ ወደ ቦታ ተንከራተዋል፣ ከአንዱ አበባ ተነስታ በሌላው ላይ እንደምትቀመጥ ከዚያም ተነስታ ወደሌላው አበባ እንደምትበር ንብ ተጉላልተዋል ፡፡  በንፈሳዊ ሕይወታቸው መጠንከር አልቻሉም፡፡ አማኞች ሥር መስደድ ሲጀምሩ መሪዎችና መድረክ ናፋቂ ሰባኪዎች ካሉበት ሥፍራ ያፈናቅሉአቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ በመንፈሳዊ ሕይወት መጭብርብር ውስጥ ገብተዋል ፣አያሌዎችም ለአውሬ ተጋልጠዋል፡፡  ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ አገልጋዮች ስለ እነርሱ ግድ አላለንም፡፡ ስለዚህ  ቆም ብለን በማሰብ የምዕመናኖቻችን ልብ ልናሳርፍ ይገባናል፡፡ ጳውሎስ ለፍልሞና የሚልከው ይህ መልእክት ለአገልጋዮች ሁሉል ማነንቂያ ደወል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የቅዱሳንን ልብ ሚያሳርፈውን ማንነት እግዚአብሔር ይስጠን፡፡ አሜን፡፡





  

Wednesday, May 7, 2014

እግዚአብሔር ታማኝ ነው፡፡


                                 ከፓስተር ሳሙኤል ሾንጋ 

ሮጄር ስሚስ ግንቦት 7 ቀን ጧት ወደ ሥራ ቦታው ለመድረስ መኪና እንዲተባበሩት( ራይድ እንዲሰጡት ማለት ነው) ሹፌሮችን እየለማመነ በመንገድ ዳር ይጓዛል፡፡ ያንን ዕለት በፍፁም ሊረሳው አይችልም፡፡ በዕለቱ የተሸከመው ሻንጣ አቅሙን ከመፈታተኑም በላይ በእጅጉ አድክሞታል፡፡ የሚለብሳትን የሠራዊት ደንብ ልብስ ለአንዴና ለሁሌ አውልቆ ለመጣል ጓጉቷል፡፡ በመንገድ ዳርም ሆኖ በጎዳናው ላይ ለሚነጉዱ መኪናዎች ሁሉ የተባበሩኝ ምልክት እያሳየ እያለ አንዲት ጥቁር ዘመናዊ ካዲላክ ስትመጣ በርቀት አይቶ መኪና የማግኘቱን ተስፋ ቢቆርጥም ዘመናዊዋ ካዲላክ መኪና አጠገቡ ስትርስ ቆመች፡፡ ሮጄር ስሚስም ወደ ካዲላክ መኪናዋ ሮጠና ቦርሳውንም ከኃላዋ በኩል ወርውሮ ወደ ውስጥ ሲገባ ወንበር ጎተት አድርጎለት እንዲቀመጥ ያጋበዘውን፣ ማለፊያ ልብስ ያደረገውን መልከ መልካም ሰው አመስገኖ በፊት ለፊት ወንበር ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ፡፡ የመኪናው ነጂ ሚስተር ሃኖቬር ይባላል፡፡ ሚሰተር ሃኖቬርና ሚሰተር ሮጄር ስሚዝ ለመግባባት የሚያስችላቸውን ንግግር ጀመሩ፡፡
ሃኖቤር ፡ ወደ ሥራ ነው የምትሄደው?
ሮጄር ስሚስ፡ አዎን
ሃኖቤር፡ ወደ ችካጎ የምትሄድ ከሆነ ዕድለኛ ነህ፡፡
ሮጄር ስሚስ፡ ያንን ያህል አልሄድም፣ አንተስ ወደ ቺካጎ ነህ?
ሃኖቤር፡ እዚያ የንግድ ሥራ አለኝ ፣ ስሜ ሃኖቤር ይባላል፡፡
ደዚህ እያሉ ብዙ ካወጉ በኋላ አማኙ ሮጄር ስሚስ ለዚህ በንግድ ሥራው ውጤታማ ለሆነና ዕድሜውም ወደ 50 ለተጠጋው ሰው ለሃኖቬር ስለ ክርስቶስ መመስከር ታላቅ ፍላጎት ተሰማው፡፡ ከቤቱም ወጥቶ እስከዚያ ቦታ ድረስ ለ30 ደቂቃ ያህል በካዲላክ መኪና ቢጓዙም ምንም አልመሰከረለትም ነበር፡፡ የምስክርነት ተግባሩን ለመከወን ወይንም ለመተው ጊዜው አሁን መሆኑን ተረዳና ጎሮሮውንም ለንግግር አጽድቶ ፣ሚስተር ሃኖቤር! እኔ ዛሬ ስለ አንድ አንገብጋቢ ጉዳይ ልነግርህ እወዳለሁ አለው፡፡ ከዚያም አስከተለና ስለ ደህንነት መንገድ በሰፊው ከገለጸለት በኋላ ክርስቶስን የግል አዳኙ አድርጎ እንዲቀበል ጠየቀው፡፡
ያንን ምስክርነት የሰማው ሃኖቬር መኪናዋን ከመንገድ ዳር አንሸራትቶ ለአፍታ ሲያቆማት ሮጄር በአግራሞት ቢመለከተውም የተባለውን ሰምቶ ሃኖቤር  ከመኪናው  የሚያስወርድ መሰለው፡፡ ነገር ግን ሀብታሙ ነጋዴ አጎንብሶ ጌታን ከተቀበለ በኋላ ሮጄርን ማመስገን ጀመረ፡፡ “ይህ በሕይወቴ ከተከሰቱ ታላላቅ ቁም ነገሮች አንዱ ነው” ይላል ሮጄር፡፡ ከዚያም ሁኔታ በኋላ ሮጄር ከሃኖቤር ተለይቶ ወደ አቅጣጫው አመራ፡፡ ሃኖቬርም ወደ ቺካጎ ሄደ፣ ሁለቱ በዚያው ተለያዩ፡፡
ከአምስት ዓመት በኋላ ሮጄር ትዳር መሥርቶ ፣ የራሱንም ንግድ አቋቁሞ ፣ ከሁለት ዓመት ልጁ ጋር ወደ ቺካጎ ለመሄድ ሻንጣውን እየቀረቀበ እያለ አንዲት ነጣ ያለች የንግድ ካርድ አገኘ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ከሃኖቤር የተበረከተች ነች፡፡ ሮጄር ወደ ቺካጎ ከደረሰ በኋላ የሃኖቬር የንግድ ማዕከል የሚገኝበት ቦታ በካርዷ ላይ በተገለጠው አድራሻ መሠረት ፈልጎ አገኘና ወደዚያው አመራ፡፡ ወደ ቦታው ሲደርስ የእንግዳ ተቀባዩዋ የሃኖቬርን ባለቤት የሆኑትን ሚስስ ሃኖቬርን እንጂ ሚስተር ሃኖቬርን ማግኘት የማይቻል መሆኑን ስታረጋግጥለት ሮጄር ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ስለተቸገረ ግር አለበት፡፡ የእንግዳ ተቀባዩዋ በጥሩ ሁኔታና በመልካም አቀባበል ብታስተናግደም ግራ መጋባቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሆኖም አንዲት አምሳ ዓመት የሚሆናትን ንቁ ሴት እንዲያነጋግራት አድራጋዋለች፡፡
ሴትዮዋ (ሚስስ ሃኖቬር) "ባለቤቴን ተውቀዋለህን?አለችው፣  እጇን እየዘረጋች፡፡ ሮጄርም በማስከተል፣ አንድ ቀን ጧት የመኪና ርዳታ እንዲያደርጉለት በመንገድ ላይ ሆኖ ሲለማምን ሃኖቬር እንዴት ያለ እገዛ እንዳደረገለት በዝርዝር ሁሉንም ተረከላት፡፡ ሚስስ ሃኖቬር መለስ አደረገችና ያ ሆነው መቼ እንደሆነ ቀኑን ለማወቅ ፍላጎት አድሮባት ጠየቀች፡፡ ሮጄርም የዛሬ አምስት ዓመት ግንቦት 7 ቀን ሲሆን ያ ቀን ከሠራዊት የተባረረበት ቀን መሆኑንም በማስታወስ አረጋገጠላት፡፡ ያን ቀን የሆነ ልዩ ነገር ምን እንደሆነ ስትጠይቀው ለመናገር ቢያቅማማም የሆነውን ሁሉ መመስከር አስፈላጊ ንደሆነ ተሰማው፡፡  ስለ ወንጌል እንደገለጸለትና ሃኖቬርም መኪናውን ከመንገድ ዳር አስጠግቶ አቆመና አጎንበሶ በማልቀስ በዚያን ቀን ሕይወቱን ለክርስቶስ መስጠቱን ነገራት፡፡  ይህንን ምስክርነት የሰማችው ሚስስ ሃኖቬርም ሰውነቷ እየተንቀጠቀጠ ስትነፋረቅ ሮጄር ስሚስም "አሁን ባለቤትሽ ወዴት አለ?" ብሎ ጠየቃት፡፡ እስዋም ስቃ እየተናነቃት በደከመ ቃል ባለቤቷ ፣ ከእርሱ (ከሮጄር) ከተለየ በኋላ ያኔ ግንቦት 7 ቀን የመኪና ግጭት ስለገጠመው ወደ ቤትም ሳይገባ  በዚያው እንደቀረና እንደሞተ ነገረቺው፡፡ ስለ ባለቤቷ መዳን  ለረጅም ዓመታት በእግዚአብሔር ፊት ስትጸልይ ጌታ የተስፋ ቃል ቢሰጣትም ባለቤቷ መዳኑን ሳታይ በመቅረቷ ሕይወቷን ለጌታ መስጠት ካቆመች አምስት ዓመት እንደሆናት ገለጸችለት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የተናገረውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም አምላክ ስላልመሰላት ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት ባለቤቷ ደህንነት እንዲያገኝ አጥብቃ ፀልያለች፣ ጌታም ወደ ደህንነት እንደሚመራው የተስፋ ቃል ሰጥቶአታል፡፡ ይሁን እንጂ ያ ተስፋ ተፈጽሞ ለዓመታት የጸለየቺው ጸሎትም ተመልሶ በዓይንዋ ሳታየው የምትወደው ባሏ ሃኖቬር እስከ ወዲያኛው ተለያት፡፡ እርሷም ለአላኳ ያላትን መታመን አበላሸች፡፡
እንግዲህ ይህቺ ሴት እንደዚህ የወሰነቺው እግዚአብሔር ለባልዋ መዳን የጸለየቺውን ጸሎት ሰምቶ የመለሰላት ስላልመሰላት ነው፡፡ አንዳድ ጊዜ በክርስቲያኖች ሁሉ ሕይወት ይህንን የሚመስል ነገር ይከሰታል፡፡ የጸሎታችን መልስ ከመዘግየቱ የተነሳ ጌታ ጸሎታችንን እየሰማው ስለመሆኑ እንጠራጠራለን፡፡ ይህ በክርስትና ሕይወታችን የሚገጥመን ትልቁ የአጭር ጊዜ መልስ የማይገኝለት ፈተና ነው፡፡ እግዚአብሔር ነቢይ ልኮ ወይም በአንድ ሌላ ሰው አማካይነት የጸለይከውን/ሺውን ጸሎት ሰምቻለሁ ካላለ ወይም ደግሞ የለመንነውን ነገር በእጃችን አስቀምጦልን ካላየነው ለጸሎታችንም ሆነ ለገባልን የተስፋ ቃል ታማኝ የሆነ አይመስለንም፡፡ እግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ሚስስ ሃኖቤር ለባሏ መዳን የጸለየቺውን ፀሎት ሰምቶ ባሏንም ወደ ደህንነት አምጥቶ ሳለ እርስዋ ግን እግዚአብር ታማኝ አልሆነልኝም ብላ ለአምስት ዓመት ለእሱ ያላትን መሰጠት አቀዘቀዘችበት፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሁሉ ማለትም ለወንዶች፣ ለሴቶች፣ ለወጣቶች፣ ለአዋቂዎች፣ ለጎልማሶችና ለአዛውንት የታመነ አምላክ ነው፡፡ ለአገልጋዮች ፣ ለመሪዎችና ለቤተ ክርስቲያን ሁሉ እርሱ የታመነ እውነተኛ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም ቃል የሚነግረን ይህንን ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያረጋግጡልናል፡፡በብሉይም ሆ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የእርሱ ታማኝነት ተወስቷል፡፡ ቀናት ይለዋወጣሉ ፣ ይቀያየራሉም፡፡ ሰዎችም የጊዜውን ተጨባጭ ሁታዎችን እያዩ ይቀያየራሉ፣ ይለዋወጣሉም፡፡ መንግተትም ሥፍቸውን ይለቃሉ፣ሕጋቸውም ከእርሱ ጋር ያልፋ ይህ ሲሆን የሰዎችም አኗኗር እንደነበረ መቀጠል አይችልም፡፡ እኛም ለጌታ ያለን ታማኝነት ይቀየራል ይፋልም፡፡ ጌታ ግን ለእኛ ሁል ጊዜ ታማኝ ነው፡፡ የጸሎታችን መልስ ሲዘገይብን እኛም ከዚህ የተነሳ ሥፍራችንን ብንለቅም የዘላለም አምላክ ግን ሁል ጊዜ የታመነ ነው፡፡ የጸሎታችን መዘግየት የእርሱን ታማኝነት አያጎድለውም ይልቁንስ እርሱን በእምነት ባለመጠበቃችን የእኛን ታማኝነት ያጎድልብናል እንጂ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እርሱ ታማኝነት እንደሚከተለው ይነግረናል፡፡
እርሱ አምላክ ነው ሥራውም ፍጹም ነው፣ በመንገዱም ሁሉ የቀና ነው፣የታመነ አምላክ ክፋት የሌለበት እውነተኛና ቅን ነው(ዘዳግም 32 4 )
 ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሳ ነው፡፡ ርኅራኄው አያልቅምና፡፡ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፡፡ታማኝነትህም ብዙ ነው፡፡ ሰቆ. ኤር.322)
 አንተም አምላህ እግዚአብሔር እርሱ አምለክ እደሆነ ፣ለምወድዱትም ትዕዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ ደሆነ እወቅ( ዘደግም 79)
የእስራኤል ታዳጊ ቅዱሱም፥ እግዚአብሔር፥ ሰዎች ለሚንቁት ሕዝብም ለሚጠላው ለገዥዎች ባሪያ እንዲህ ይላል። ስለ ታማኙ ስለ እግዚአብሔር ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፥ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳ(ኢሳያስ 497)
በሕይወት ዘመናችንም ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ስራመድ ያየናቸውና የሳለፍናቸው መንገዶችም እግዚአብሔር አምላካችን ታማኝ መሆኑን ይነግሩናል፡፡ እግዚአብሔር እኛ ታማኝ ከሆነባቸው ከብዙ መንገዶች የሚከተሉትን ንመልት፡፡
1. እግዚአብሔር በቃሉ የታመነ ነው( ዕብ፡ 1023)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስብራውያን መልእክት ምዕራፍ 1023 ላይ ቃሉን የሰጠ የታመነ ነው ብሎ ይነግረናል፡፡ እግዚብሔር ለሕዝቡ የተስፋ ቃል ይሰጣል የሰጠውንም የተስፋ ቃል ይፈጽመዋል ፣ምክንያቱም እርሱ የተናገርን የተስፋ ቃል ለመፈም የሚተጋ አምላክ ነው፡፡፡፡ እርሱ የሰጠው የተስፋ ቃል አይወድቅም፣ አይሻርም ፣ ሳይፈጸምም አይቀርም ምክንያቱም ግዚአብሔር በቃሉና በሰጠው የተስፋ የታመነ አምላክ ነውና(ዘኁልቁ 2319)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰው ስላይለ አይዋሽም ፣ ሐሰትን አይናገርም፡፡ እርሱን ከሌሎች የአህዛብ አማልክት ልዩ የሚያደርገው የተናረውን ቃል በወሳኝ ሰዓትና ሁኔታ መፈጸሙ ነው፡፡ ብዙ ተስፋ የሚገቡ ግን አንዱንም መፈጸም የማይችሉ አያሌ ሰዎች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን በቃሉ የታመነ አምላክ ነው፡፡ እርሱ የማይዋሽና ሐሰትን የማይናር መሆኑን ጣዖት አምላኪዎች ራሳቸው እንኳን ያውቃሉ፡፡ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም ይዋሽም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም ያለው እኮ እግዚአብሔርን የማያመልክ የሞአብ ጠንቋይ ሆነ በለዓም ነው፡፡ ቃልቻዎች የእግዚአብሔርን ታማኝነት የሚመሰክሩ ከሆነ እኛ በየቀኑ እጁን እየተለማመድን የምንኖር አማኞች ደግሞ እንዴት ስለ እርሱ ታማኝነት አብልጠን አንመሰክርም? እነርሱ እግዚአብሔርን በሩቅ ያውቁታል፣ እኛ ግን በቅርባችን ሆኖ ፣ ከዚያም አልፎ በአጠገባችን ብቻ አይደለም በውስጣችን አድሮ ነው የምናውቀው፡፡ የጣዖት አምላኪዎች አምላካችንን የሚያውቁት ድንገተኛ በሆነ ጉዳይ ሲገለጥ፣ እነርሱን ሲቀጣቸውና የሕዝቡን ጩኼት ሰምቶ ሲመልስ፣ ተአምራትንም ሲያደርግ አይተው በፍርሃት ተውጠው ነው የሚያውቁት ፡፡ እኛ ግን በመከራችንም ሆነ በደስታችን ፣ በውድቀታችንም ሆነ በትንሳኤያችን ሁሉ ጌታችን ከእኛ ጋር ሆኖ አብሮ ሁሉን ሲጋፈጥ ስላየነውና ስለተለማመድነው በዚህ እናውቀዋን፡፡ አምላካችን እውነተኛ መሆኑን ጣዖትን የሚያመልኩም ሁሉ ያወቁት የእነርሱ አምላክ እንደ እኛው እግዚአብሔር አለመሆኑን እያዩና እያነጸጻሩ ስለሆነ በዚህ ያውቃሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ለእኛ ለአማኞቹ ዋሽቶብ አያውቅም፡፡ ሐሰት ለመናገር የሚችልበት ባሕሪይ የለውም፡፡ እርሱ በቃሉ የታመነ ነው፡፡
2. እግዚአብር በጥሪው የታመነ ነው ( 1 ቆሮ. 18-91 ተሰሎንቄ 524)፡፡
እግዚአብሔር ሲጠራን ካለንበት ሁኔታ ወደ ራሱ አሳብና ወደ መንግሥቱ ሊያሸጋግረን ነው፡፡ በፊት ከነበርንት ሁኔታ ይልቅ የተለ እንደሆነ ወደሚያውቅበት መልካም ሁኔታ አሸጋገረን ማለት ነው፡እንደዚም ደግሞ እኛን ከጠረን በኋላ ከሚያስፈልግን ነር አንድ አላጎደለብንም፡፡ ስለዚህ በእግዚአብር በአምላካችን እንደላደላለን ምክንያቱም ሱ በሁሉም መንገድና ኔታ ታማኝ አባታችንና አምላችን ነውና፡፡
እግዚአብሔር ለእኛ የሚያደርገው ግብዣ አንድ ትልቅ ንጉሥ ለልጁ ሠርግ ያዘጋጀው ግብዣ ዓይነት ነው፡፡ ንጉሡ ለልጁ ሠርግ ባዘጋጀው ግብዣ እንዲገኙ የተጠሩት ሰዎች እጅግ በጣም እድለኞች ናቸው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 22 የምናየው ይህንን ነው፡፡ ሁሉ ተዘጋጅቶአልና ወደ ድግሴ ኑ ብሎ ነው የጠራው፡፡ በጥንት ዘመን አንድ ግብዣ በሚደረግበት ወቅት የተቀጠረው ቀንና ሰዓት ለሰው ሁሉ ክፍት ሆኖ ይጠብቃል፡፡ በዚያን ወቅት ግብዣ ሁለት ደረጃ ያለው ሲሆን የመጀመሪያው  የሠርግ ዜ የተቀጠረ መሆኑንና ተጋባዞችም የክብር እንግዳ ሆነው የተመረጡ መሆናቸውን አውቀው በእለቱ ለመምጣት ራሳቸውን እንዲዘጋጁ የሚነገር ነው( ማቴ.222) ፡፡ የሚጋበዘውም ሰው የክብር እንግዳ ሆኖ ነው የሚጋበዘው፡፡  ሁለተኛው በግዣው ዕለት የግብዣው ደጋሽ የድግሡ ዝግጅት ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ የተመረጡት ወደ ግብዣው አዳራሽ እንዲመጡ የሚያደርገው ጥሪ ነው፡፡ በሁለተኛው ግብዣ የሚደረገው ጥሪ ከመጀመሪያው ይለያል፡፡ በመጀመሪያው የታደሙ መሆናቸውን የማሳወቅ ጥሪ ሰሆን ሁለተኛው ግን ዝግጅቱ ሁሉ ተጠናቋልና ገብታችሁ መጋበዝ፣ መብላትና  መጠጣት  ትችላላችሁ የሚል ጥሪ ነው፡፡ ድግሴን አዘጋጀሁ፣ኮረማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፣ ሉም ተዘጋጅቷል፣ ወደ ሠርጌ ኑ(.4 ላይ እንደዚህ እናባለን)፡፡ እንደዚህ ዓነቱ ግብዣ በሁሉም ዘንድ የሚፈለግና ሁሉም የሚቀበለው ነው፡፡ እዲሁም በክርስቶስ ዘመን የነበሩ ፈሪሳውያን ደዚያ ያለውን ግብዣ በጣም ይወዱታል፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ በግብዣ ሥፍራ የክብርን ወንበር ይፈልጋሉ ያው ለዚህ ነው( ማቴ.236)፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ግብዣ ሁሉም ሰው የሚፈልገው ቢሆንም ወደ ግብዣው አዳራሽ መግባት የሚችሉት ጥሪውን ሰምተው ምላሽ በመስጠት ወደ ሥፍራው የሚመጡ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልን ግብዣ የከበረና እኛ በእግዚአብር ፊት የታየንና የተከበርን መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
እግዚብሔር በብሉይ ኪዳን ነበሩ የእሥል ሕዝብ ሆነ በአዲስ ኪዳን ለነው አማኞች ሁሉ እንደየሁኔታችን የሚያቀርብልን ጥሪ አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል በትንቢተ ኢሳያስ  551-3 ባለው ክፍል ያቀረበው ጥሪ ለእሥራኤል ሕዝብ እጅግ ወሳኝ ጥሪ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡ እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ፡ ገንዘብም የሌለችሁ ኑና ግዙ ብሉም ያለ ገንዘም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ፡፡ ገንዘብ እንጀራ ላይደለ የድካማችሁን ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላች; አድምጡኝ ፤በረከትን ብሉ ፣ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው ፡፡ ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች የታመነቺይቱን የዳዊትን ምሕረት ፣ የዘላላምንም ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ፡፡
ይህ  ዋጋ ከፍለው እጀራና ውሃ ወተትም መግዛት ለማይችሉ ደካች የቀረበ ጥሪ ነው፡፡ እንጀራና ውሃ እንዲሁም ወተት የሚያስፈልጋቸው  መግዛት ንዳይችሉ ገንዘብ የሌላቸው፣ የተጠሙና የተራቡ  ብዙ አሉ፡፡ ምድራዊ ሀብትና ባለጠግነት ቢኖራቸውም በነፍሳቸው የጽድቅ ረሀብና ጥማት ያለባቸው ነገር ን በገዛ ሥራዎቻቸው ርካታንና ጥጋብን ማግኘት ያቃቸው አያሌዎች ናቸው፡፡ ጌታ እንደነዚህ ያሉትን  ኑና ያለ ገንዘብ ግዙ ይላቸዋል፡፡ እንዴት  ነው ያለ ገንዘብስ የሚገዛው? ዋጋው ስለተከፈለ ምን እከፍላለው ብለው ሳይጨነቁ ወስደው እዲበሉና እንዲጠጡ የተሰጠ ጥሪ ነው፡፡
የውሃ ጉዳይ ለእግዚአብሔር ሕዝብ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያተቱም ያ ውሃ ለመኖር አይችሉም ነበርና፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ሥራና የእርሱ መለኮታዊ አሠራር በተገለጡባቸው በብዙ ሥፍራዎች የውሃ አስፈላጊነት ተገልጧል፡፡ የእሥራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ትተው ሌሎች አማልክትን ባመለኩበት ወቅት ጌታ ሲናገራቸው "እኔን የሕይወት ዉሃ ምንጭ ትታችሁ ለእናንተ ውሃ ሊይዙ የማይችሉ የተቀደዱ ጉድጓዶችን ቆፈራችሁ" ይላቸው ነበር( ኤር.213)፡፡ ለተጠማ ሁሉ የሚሰጥ ውሃ ነው፡፡ ውሃ ለጥም ካታ ከመዋሉም ባለፈ በሰው ልጆች ሕይወት ሁሉ የማያስፈልግበት ጊዜና ሁኔታ የለም፡፡ ውሀ ለምግብ አገልግሎት፣ በቤት ግንባታ፣ ለሰውነትና ለዕቃዎች ንጽሕና፣ ለእርሻ አገልግሎት፣ እንዲሁም ደግሞ ለፋብሪካዎችና ለእንዱሰተሪዎች ምርታማነት ሁሉ ውሀ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ምድራዊና ቀሪ ሲሆኑ እግዚአብሔር ለሚያምኑት ሁሉ የሚሰጠው ውሀ ሰዎች ጠጥተው ዳግም እንዳይጠሙ የሚያደርግ የሕይወት ውሀ ነው፡፡ ይህን ውሀ የሕይወት ጥማት ያለበት ሁሉ እንዲወስድና እንዲጠጣ ጌታ ይጠራል፣ ጥሪውንም ተቀብለን ለመጣነው ሁሉ የማያጠራጥር ርካታ ይሰጠናል፡፡ ጌታ የሌለው ሰው በምድረ በዳ እንዳለ የሚጠጣውንም ውሀ እንዳጣ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውሃ ኑ ያለ ዋጋም ግዙ በማለት በቃሉ ይጋብዛል፡፡
የሰው ልጅ ለራሱ የሚያደርገው ጥረት ሁሉ የሚያጠግበው ስላይደለ እግዚአብሔር የገዛለትን እንጀራና ውሃ በነፃ ወስዶ እንዲበላና እንዲጠጣ ተጋብዟል፡፡ እግዚአብር የሚሰጠው የሕይወት እንጀራና የሕይወት ውሃ ለዘላለም የሚያጠግብና የሚያረካ ነው፡፡ ይህን ጥሪ ይፈጽምልን ዘንድ እርሱ የታመነ አምላክ ነው፡፡
በአዲስ ኪዳንም የተደረገ ሌላ አንድ ትልቅ ጥሪ አለ ያውም እረፍት እድናገኝ የተደረገልን ጥሪ ነው፡፡ እናንተ ደካች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳፋችኋለሁ(ቴዎስ 1128)፡፡ ጌታ የሚጠራቸው የዓለምና የጢአት ንደሁም የሥጋ ሽክም በቶባቸው መሸከም ያቃታቸውን በራሱ ዘንድ ሊያሳርፋቸው ወዶ ያቀረበው ጥያቄ ነው፡፡ ታዲያ እግዚአብንደዚህ ያሉትን ከሸክማቸው ጋር የሚንገላቱትንና ድም ያለባቸውን በእርግጥ ያሳርፋቸዋልን? መልሱ አዎን እርሱ በጠራን ጥሪ የታመነ አምላለሆነ ያሳርፈናል፡፡ ስለዚህ ይህንን የሕይወት ግብዣ ሰምተው ፈጥነው ያልመጡ ሁሉ የንጉሡን ሠርግ ችል ብላው ወደየገዛ መንገዳቸው እንደሄዱ ተጋባዦች ናቸው፡፡ የማይገኝ በረከት አምልጦአቸዋል፡፡ በሌላ ሥፍራ ከሚደረገው ድግስ ሁሉ የተለየና የላቀ ድግስ ስለሆነ ይህንን ድግስ ቸል ብሉ ሌሎች ያልታደሙ ያተጠበቁም መጥተው የድግሱን አዳራሽ ይሞሉታል፣ዝግጅቱ ሁሉ ለእርሱ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው ጌታ የሚያደርግለትን ጥሪ ሰምቶ ወደ እርሱና እርሱ ወደሚሰጠው እረፍት መምጣት አለበት፡፡ ጌታም ሊረዳንና ከሸክማችንም ሁሉ ያሳርፈን ዘንድ የታመነ አምላክ ነውና፡፡
3.      እግዚአብር በጥበቃው የታመነ ነው(2 ተሰ.33)፡፡
21ኛው ክፍለ ዘመን የምኖር አማኞች የክርስትና ምልክት አድርገን የምንጠቀመው መስቀል እንደሆነ ሁሉ በጥንት ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የእምነታቸው ምልክት አድርገው ከተጠቀሙባቸው ምልክቶች የበግ ጠቦት በብብቱ አቅፎ የያዘ አንድ ሰው ምስል እንደነበር ያታወቃል፡፡ በእርግጥ እነዚያ ወገኖች የክርስትናቸው ምልክት ይህ ብቻ ሳይሆን የዓሣ ምሥል ፣ በእሳት ውስጥ የሚገኙ የሦስት ሰዎች ምስል፣ የዘንባባ ዝንጣፊና ሌሎችም ያሉ ሲሆን የበጉን ጠቦት የተሸከመ ሰው ምሥል ግን በስዴትና በመከራ ውስጥ ሲያልፉ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ማጽናናትና እንዴትስ ያ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የሚያሳይ ትርጉም ያለው ምልክት ነበር፡፡ በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ካለን ግንኙነት አንዱና ትልቁ የእረኛና የበግ ግንኙነት ነው፡፡ እግዚአብሔር እረኛችን ሲሆን እኛ ደግሞ በጎቹ ነን፡፡ እግዚአብሔር የሕዝቡ እረኛ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ መዝ 231-6 ያለው ክፍል ዳዊት እግዚአብሔርን እረኛዬ ነው ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር ራሱ ለሕዝቡ እንዴት ዓይነት እረኛ እንደሆነ በትንቢተ ኢሳያስ 40 11 ላይ አረጋግጧል፡፡ መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል ይላል ፡፡ ንጉሡ ዳዊትም በዝማሬው ላይ የእግዚአብሔርን እረኝነትና ጥበቃ ግልጽ አድርጎ ያስተምረናል፡፡ የክርስትና ሕይወት በተራራና በሸለቆ ንዲሁም በሽንተረር እንደጓዝ ነው፡፡ በጎች በገደላገደልና በቋጥኝ ድንጋዮች መካከል በሚያልፉበት ወቅትም እረኛቸው ወደ ገቡበት ሥፍራ ገብቶ እንደሚፈልጋቸው ሁሉ የእግዚአብሔርም ጥበቃ እንደዚያው ነው፡፡ ዳዊት ሲዘርም በሞት ጥላ መካካል እንኳን ቢሄድ ክፉን እንደማይፈራ ይናገራል፡፡ ለእግዚአብሔር ሰዎች የሞት ጥላ ማለፊያቸው እንጂ መኖሪያቸው አይደለም፡፡ አቋርጠው የሚያልፉበት መንገድ እንጂ መሞቻቸው አይደለም፡፡ የአማኞች ሕይወት ፍጻሜው እግዚአብሔር ያየላቸው የበረከት ሥፍራ እንጂ የሞት ጥላ አይደለም፡፡ ይህንን የሞት ጥላ መንገድ ሳናልፍበት ወደ ጸዮን የምንሄድበት አቋራጭ መንገድ ግን የለንም፡፡ ቢሆንም ጌታ ከእኛ ጋር ስለሚሆን ክፉ አያስፈራንም፡፡
ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቶቹ ውስጥ የእግዚአብሔርን ጥበቃ አውስቷል፡፡ ለተሰሎንቄ አማኞች በጻፈው መልእክት የሚጠብቃችሁ የታመነ ነው( 2 ተሰ. 33) ይላል፡፡ እግዚአብሔር በታማኝት ይጠብቀናል ስንል ምን ማለታችን ነው፡ እርሱ እንደምንደ ሳይሆን የገዛ በጎቹን የሚጠብቅ የበጎች ባለቤት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ስለ ማኝ እረኝነቱ ሲናገር ፡
መልካም እረኛ እኔ ነኝ፡፡ መልካም እረኛ ነፍሱን ለጎቹ ያኖራል እረኛ ያልሆነው በጎቹም እርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ተኩላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል፡፡ ሞያተኛ ስለሆነ ለጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል፡፡ መልካም እረኛ እኔ ነኝ፡፡ አ ንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ(ዮሐ.1011-15)፡፡

በዚህ ክፍል ጌታ የሱስ የራሱን እረኝነት ከሞያተኞች ሥራ ጋር በማነጸጸር ያስተምረናል፡፡ ሞያተኞች ለበጎች ባለቤትት ስለማይሰማቸው ነጣቂ አውሬ በሚመጣበት ጊዜ በጎችን ለአውሬዎች ሰጥተው ይሸሻሉ፡፡ የበጎች ባለቤት የሆነው መልካም እረኛ ግን ነፍሱን ለበጎቹ የሰጣል ንጂ ትቶ አይሸሽም፡፡ ጌታ ኢየሱስም መልካም እረኛችን ሆኖ ሰይጣን ሌባው ሊሰርቀን፣ ሊርደንና ሊያጠፋን በሚመጣበት ወቅት ስለ እኛ ነፍሱን አሳል ሰጠ፡፡ እግዚአብር ለእኛ ያለውን በቃ ስንመለከት የራሱ ምክንያቶች አሉት፡፡ ለምን እግዚአብር ይጠብቀናል?
· እኛ እንዳንጠፋ፡ ሌባው እንዳይሰርቀን፡፡ እንዳያርደን ነው፡፡
· እንዳንሰናከል ነው፡፡ ይሁዳ 24
· በክብሩ ፊት ያለነቀፋ ለመቆም እንድንችል ነው፡፡
ጆን ፓንቶን የተባለ ሚሺነሪ ከሚስቱ ጋር የሚስዮናዊነት አገልግሎቱን ለመስጠት ወደ ኒዩ ሄብሪድስ አይስላንድ ሄዶ ለረጅም ጊዜያት ጌታን አገልግሏል፡፡ በዚያ አገር በሚሲዮን ጣቢያ እያለ ከአገሩ ሰዎች አንዳንድ ክፉዎች በጆን ፓንቶንና በባለቤቱ ድንገተኛ አደጋ ለማድረስ ወደ ሚስዮን ጣቢያው ቀረቡ፡፡ ሚሲዮናውያኑ ባልና ሚስትም አደጋ እንዳጠላባቸው ቢያውቁም ጊዜው ከእኩለ ሌሊት ያለፈ በመሆኑ ምንም ይሁን ምን የሚመጣውን መከራ ከመቀበል ሌላ ማድረግ አልቻሉም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም የበለጠ መፍትሔ ተንበርክኮ መጸለይ እንደሆነ ስለሚያምኑ በአምላካቸው ፊት ጥብቅ ፀሎት አደረጉ፡፡ የሚስዮን ጣቢያ በአደጋ ጣዮች ምክንያት በከፍል በእሳት የተቃጠለ ቢሆንም ሌሊቱ ሲነጋ እነዚያ ሊገድሉአቸው የመጡ ሰዎች በግቢው ውስጥ አንዳቸውም አለመኖራቸውን ስለተረዱ ሚሲዮናውያኑ ባልና ሚስት በጣም ተደነቁ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን ስለ ሰማ አመስግነው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፡፡ ከዓመት በኋላ ሚስዮናውያኑን ለመግደል ከመጡ ሰዎች አንዱ የሆነው የጎሳ መሪ ጌታ ኢየሱስን የግል አዳኙ አድርጎ ተቀበለ፡፡ ስለ ሕይወታቸውና ስላለፉባቸው አንዳንድ አጋሚዎች ሲመሰክሩ ሳለ ጆን ፓንቶን ያን ጊዜ ቤታቸውን እያቃጠሉ እያለ ለምን ሳይገድሉአቸው ትተው እንደሄዱ ሲጠይቀው የጎሳ መሪ የሆነው አዲሱ ሰው ሲመልስ በጥየቄ መልክ "ያን ቀን ከእናንተ ጋር የነበሩ ግን እነዚያ ሰዎች እነማን ናቸው "? አለው፡፡ ከሚሲዮናዊያን ጋር ማንም እዳልነበረ ሲነግሩት በመገረም እኛ ያንን ግቢ ትተን የሄድነው ቤቱን እያቃጠልን ወደ እናንም እየቀረብን ሳለ ሚያብረቀርቅ መጎናጸፊያ የለበሱ፣ የተመዘዘ ሰይፍ የያዙና የሚያስፈሩ በመቶ የሚቆጠሩ በትክለ ቁመናቸው ግዙፍ የሆኑ ሰዎች የሚሲዮናውያኑን ቤት ከብብው ስላየን ከእነርሱ የሚሰነዘርብንን ጥቃት ፈርተን ሸሸንና ሄድን ብሎ መሰከረ፡፡ ጆን ፓንቶንና ባለቤቱ ጥቃት በተቃጣባቸው ቀን ይታያቸው የነበረው የአደጋ ጣዮች ሁኔታ እንጂ በዙሪያቸው ያለ የእግዚአብሔር ጥበቃ አልነበረም፡፡ ነገር ግን እነርሱ ባያዩትም እግዚአብሔር ልዩ የሆነ ጥበቃ በዙሪያቸው አድርጎላቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ነው የጌታ ቃል ጌታ ሳንሰናከል የሚጠብቀን እንደሆነ የሚነግረን( ይሁዳ 24)፡፡ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር አምላካችን ከክፉዎች ሁሉ ይታደገናል፡፡ እግዚአብሔር የሚጠብቀንም ያማቋረጥ ነው፡፡ እሥራኤል የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋም( መዝ 1263)፡፡ ስለዚህ ይህ የሚጠብቀን አምላክ እግዚአብንደማነንም ሳይሆን የታመነ መሆኑን አውቀን በእርሱ ሙሉ በሙሉ ልንታመንና ልንደገፍበት ይገባናል፡፡
4. በመከራ ሊደግፈን በፈተናም ጊዜ ሊያበረታን የታመነ ነው(1ቆሮ. 10 13 ፡፡ )
የሰው ልጆች ሕይወት በመከራና በፈተና የተከበበ ነው፡፡ እያንዳንዳችን የምናልፍበት የመከራና የፈተና መንገድ አለ፡፡  ክርስትናም መከራ እንዳበት የታመነ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ይህንን አረጋገግጦልናል፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስም በስሙ መከራ እንቀበል ዘንድም ጭምር እንደተጠራን ስተምረናል( ፊልጵ 121)፡፡ የሆነ ሆኖ መከራ ለማም የሚመች አይደለም፡፡ የመከራ ብዛት ብዙዎችን ሥፍራቸውን ሊያስለቅቅ የሚችል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልዩ ፀጋ ካልተገለጠ ተሰናክንበት ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሐሔር በዚያ ፈተና ውስጥ ብቻችን አይተወንም፡፡ ስለ ክርስቶስ ስንሰደድ ስንነቀፍና በሕይወታችን መከራና መነቀፍ ሲበዛ ጌታን ማመስገን እንዳለብን ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ያስተምረናል( 1ጴጥ. 411-14)፡፡ ምክንያም በክርስቶስ ስም በምንነቀፍበት ወቅት የክብር መንፈስ የእግዚአብር መንፈስ በእኛ ላይ ስለሚያርፍ ነው፡፡ በ 1ቆሮ. 10 13 ላይም እንደምመለከተው እግዚአብሔር አምላክ ማናችንንም ከምንችለው በላይ እንደማይፈትነን ቃል ገብቶልናል፡፡ መጠኑን ያለፈ በሌሎች ላይ ያልሆነ ፈተናና መከራ እዲደርስብን ጌታ አይፈቅድም፡፡ በእኛ ላይ ጌታ የማይፈቅዳቸው ነገሮች አሉ፣ አንደኛው ከምንችለው መጠን አብልጠን እንድንፈተን የማይፈቅድ ሲሆን ሌላው ደግሞ ፍርዳችን በድር ላይ እንዲጣመም አይፈቅድም፤በምድር ላይ የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በች ይረግቸው ዘንድ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ የሰውንም ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም(ሰቆ.334-36)፡፡  እግዚአብሔር እንድንፈተን ቢፈቅድም የምንችለውም ያህል ብንፈተንም እርሱ ከፈተና ጋር መውቻውንም ደግሞ ያዘጋጅልናል፡፡ ስለዚህ ፈተናና መከራ፣ ችግርና ጭንቀት በሚገጥመን ጊዜ ሁሉ መፈተናችንን ሳይሆን በእኛ ፈተና ጊዜ ጎልቶ የሚታየውን የእግዚአብርን ታማኝነት እንድንመለከት ይገባናል፡፡
5. ኃጢአታችንን ይቅር ሊለንና ሊያነጸን የታመነ ነው(1ዮሐ 1-7-9)፡፡
ኃጢአት በነፍሳችን ላይ ያለ ዕዳ፣ በእእምሮአችንም ያለ ማቋረጥ የሚከሰን ባላንጣችን ነው፡፡ ሕይወታችንንም የሚያዳክምና የሚያቆሽሽ መጥፎ እድፍ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት የሚያበላሸው ኃጢአት ነው፡፡ የእግዚአብሔርም የማዳን ክንድ በሕይወታችን እንዳይገለጥ የሚያደርግ ነው፡፡  የዚህ ዓለም ትልቁ ችግር የምጣኔ ሀብትና የሌላ እጥረት ሳይሆን ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግኑኝነት ከማበላሸቱ የተነሳ በምድር ላይ ያመጣው መርገም ነው ፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ከአምላኩ ጋር ያለውን ሕብረት ለማደስ የሚችለው ከኃጢአቱ የታጠበና የነጻ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በጣም የሚያስገርመው ነገር ኃጢአት የሚያስከፍው ዋጋ ውድ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ለኃጢአቱ የሚገባውን ዋጋ ለመክፈል የሚችል ብቃት ያለው ማንም አልተገኘም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያደረገልን ይቅርታና የበደል ሥርየት በፊቱ ብቁ እንድንሆን አድርጎናል፡፡
እግዚአብሔር የሰውን ኃጢአት ይቅር ካላለ ሰው የእግዚአብሔርን ፊት ማየት የሚችልበት መንገድ የለውም፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሁላችንንም ኃጢአት በጌታ በኢየሱስ በኩል ይቅር አለ፡፡ ኃጢአታችን ይቅር መባሉ  ከእግዚአብር የተሰጠን ትልቁ እድል ነው፡፡ እርሱም ደግሞ ኃጢአታችንን ቅር ል ከዓመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነ ነው፡፡
6.      ጸሎታችንን በመስማት የታመነ ነው( 1 ዮሐ 513)፡፡
እግዚአብሔር ጸሎቴን ይሰማል ወይስ አይሰማም የሚለው የብዙዎች ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ የጸሎታችን መልስ ሲዘገይ እግዚአብሔርን የረሳው ይመስለናል፡፡ አምላካችን ለእኛ ያለው ዓላማም ግልጽ አልሆን ይለናል፡፡ ይህም ደግሞ በምድር ላይ የሚገጥመን ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ይህ የሚሆነው እኛ እግዚአብሔር በራሱ መንገድና ጊዜ ሳይሆን እኛ በመረጥነው መንገድና በቀጠርነው ቀን እንዲሠራ ስለምንፈልግ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የምንጠብቀው እኛ በምናውቃት በዚያች በለመድናት አንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ እንሳሳታለን፣ በጌታችንም ላይ ያለን እምነት ይሸረሸርብናል፡፡ እርሱ እንደሆነ ከተለመደው ውጭ መሥራት ልማዱ ነው፡፡ ከሰማይ የሚወርደውን ዝናብና ደመና ስንጠባበቅ ከምድረ በዳ ጎርፍ አምጥቶ ምድሪቱን ሊያረሰርስ የሚችል ነው፡፡ ከንጉሥ ጎተራ እህል ለሚጠብቀው ረሀብተኛ ሕዝብ ስንዴና ዱቄት ለመስጠት ለምጻሞችን በማንቀሳቀስ ለወራሪ ኃይልም የነጎድጓድና የፈረስ ድምፅ አሰምቶ ብዝበዛ እንዲበዛ የሚያደርግ አስገራሚ አምላክ ነው፡፡ እርሱ በራሱ መንገድ እንዲሠራና በራሱም ቀን እንዲመጣ እንጂ እኛ በለመድናት በዚያች አንዲት መንገድ ብቻ እንዲሠራ አንጠብቅ፡፡ በአንድ መንገድ ብቻ የተሰጠን ደህንነታችን ብቻ ነው፡፡ ለደህንነት የተሰጠን መንገድ አንድ ብቻ ሲሆን ያውም ጌታችንና ኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እግዚአብሔር የሰውን ጸሎት ሰምቶ የሚመስቸው መንገዶች በጣም ዙ ናቸው፡፡ ሚስስ ሃኖቬር ስለ ባሏ መዳን ለዓመታት ስትጸልይ ቆይታ ባሏ ከመሞቱ በፊት ስለመዳኑ እርግጠኛ ስላልነበረች እግዚአብሔር የገባውን  የተስፋ ቃል አይፈጽምም ብላ ለእርሱ ያላትን ፍቅር ለአምስት ዓመት አቀዘቀዘችበት፡፡  እግዚአብሔር ግን መንዱም ቀኑም ከእኛው የተለየ ነው፡፡ ፀሎታችን የዘገየ፣ ተስፋ ቃሉም ፈጽሞ የተረሳ ቢመስለን እግዚአብሔር ግን የለመንነውንና የጠየቅነውን ሁሉ ሊሰጠን የታመነ አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋሪያው ዮሐንስ  በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንምን ይሰማናል (1ዮሐ 513) ብሎ ይነግረናል፡፡  ለምንድነው የምንደፍረው? እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደሚሰማ ምንም ጥርጥር ሳይኖርብን በጌታ እንታመናለን ማለቱ ነው፡፡  አምላካችን ጸሎታችንን ሰምቶ መልስ ሊሰጥ የታመነ አምላ ነው፡፡ ክብር ለስሙ ይሁን፡፡ አሜን፡፡
በመጨረሻም ከሰው ይልቅ እግዘአብሔር ብቻ የታመነ አምላ በመሆኑ እምነታችንንና ተስፋችን በእርሱላይ ብቻ ልንጥል ይገባናል፡፡  የእግዚአብሔር ተስፋ ሩቅ የሆነባችሁ ፣ የገባላችውም ቃል የተረሳ የመሳለችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ዛሬም አልረሳችሁምና በፊቱ በእምነት ቁሙ፡፡  በመከራና በችግር ውስጥ ሆናችሁ እርሱን ለምትጠብቁ፣ የተነሳው ወጀብና አውሎ ነፋስ ታንኳችውን የሚያንገላታባችው  ሁሉ ጌታ እግዚአብሔር በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ የታመነ አምላክ መሆኑን አውቃችሁ  በእርሱ ልትደገፉ  ይገባቸዋል፡፡እግዚአብሔር የታመነና እውነተና አምላክ በመሆኑ በእርሱ ታመኑ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕይወት ሰልፍና ጦርነት የሚበዛባት ከመሆኗ የተነሳ በእናንተና በሞት መካከል አንድ ርምጃ ብቻ  የቀረ  እስክመስላችሁ ድረስ በሥጋት ውስጣ ያላችሁ ውድ የጌታ ባሪያዎች አምላካችሁ የሆነው እግዚአብሔር ዛሬም በጥበቃው ላይ ስለሆነና ለአውሬው አሳፎ ስለማይሰጣችሁ ከዳዊት ጋር እግዚአብሔር እረኛዬ ነው ፣ምንም አላጣም፣አርፋለሁ፣መስክ አለኝ ፣አልፈራም እከብራለሁ፣ በጠላቴም ፊት በዘይት እቀባለሁ እያላችሁ ዘምሩ፡፡ ጠላታችሁ በማግሳቱ ና አብዝቶ በመጨኹ በከንቱ የሚደክመው እርሰ ነው እናንተስ በዓለቱ ውስጥ ተሸሽጋችኋልና አትፍሩ፡፡ የለመናችሁትና የጸለያችሁትን ከገመታችሁትና ካሰባችሁት በላይ አድርጎ ሊሰጣችሁ የእኛ አምላክ የታመነ በመሆኑ በፊቱ በርቱ፡፡ ፀጋውም ይብዛላችሁ፡፡ ኢየሱስ ጌታ፣ኢያሱስ ንጉሥ ፣ ኢየሱስ ሁል ጊዜ! አሜን፡፡