Wednesday, May 7, 2014

እግዚአብሔር ታማኝ ነው፡፡


                                 ከፓስተር ሳሙኤል ሾንጋ 

ሮጄር ስሚስ ግንቦት 7 ቀን ጧት ወደ ሥራ ቦታው ለመድረስ መኪና እንዲተባበሩት( ራይድ እንዲሰጡት ማለት ነው) ሹፌሮችን እየለማመነ በመንገድ ዳር ይጓዛል፡፡ ያንን ዕለት በፍፁም ሊረሳው አይችልም፡፡ በዕለቱ የተሸከመው ሻንጣ አቅሙን ከመፈታተኑም በላይ በእጅጉ አድክሞታል፡፡ የሚለብሳትን የሠራዊት ደንብ ልብስ ለአንዴና ለሁሌ አውልቆ ለመጣል ጓጉቷል፡፡ በመንገድ ዳርም ሆኖ በጎዳናው ላይ ለሚነጉዱ መኪናዎች ሁሉ የተባበሩኝ ምልክት እያሳየ እያለ አንዲት ጥቁር ዘመናዊ ካዲላክ ስትመጣ በርቀት አይቶ መኪና የማግኘቱን ተስፋ ቢቆርጥም ዘመናዊዋ ካዲላክ መኪና አጠገቡ ስትርስ ቆመች፡፡ ሮጄር ስሚስም ወደ ካዲላክ መኪናዋ ሮጠና ቦርሳውንም ከኃላዋ በኩል ወርውሮ ወደ ውስጥ ሲገባ ወንበር ጎተት አድርጎለት እንዲቀመጥ ያጋበዘውን፣ ማለፊያ ልብስ ያደረገውን መልከ መልካም ሰው አመስገኖ በፊት ለፊት ወንበር ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ፡፡ የመኪናው ነጂ ሚስተር ሃኖቬር ይባላል፡፡ ሚሰተር ሃኖቬርና ሚሰተር ሮጄር ስሚዝ ለመግባባት የሚያስችላቸውን ንግግር ጀመሩ፡፡
ሃኖቤር ፡ ወደ ሥራ ነው የምትሄደው?
ሮጄር ስሚስ፡ አዎን
ሃኖቤር፡ ወደ ችካጎ የምትሄድ ከሆነ ዕድለኛ ነህ፡፡
ሮጄር ስሚስ፡ ያንን ያህል አልሄድም፣ አንተስ ወደ ቺካጎ ነህ?
ሃኖቤር፡ እዚያ የንግድ ሥራ አለኝ ፣ ስሜ ሃኖቤር ይባላል፡፡
ደዚህ እያሉ ብዙ ካወጉ በኋላ አማኙ ሮጄር ስሚስ ለዚህ በንግድ ሥራው ውጤታማ ለሆነና ዕድሜውም ወደ 50 ለተጠጋው ሰው ለሃኖቬር ስለ ክርስቶስ መመስከር ታላቅ ፍላጎት ተሰማው፡፡ ከቤቱም ወጥቶ እስከዚያ ቦታ ድረስ ለ30 ደቂቃ ያህል በካዲላክ መኪና ቢጓዙም ምንም አልመሰከረለትም ነበር፡፡ የምስክርነት ተግባሩን ለመከወን ወይንም ለመተው ጊዜው አሁን መሆኑን ተረዳና ጎሮሮውንም ለንግግር አጽድቶ ፣ሚስተር ሃኖቤር! እኔ ዛሬ ስለ አንድ አንገብጋቢ ጉዳይ ልነግርህ እወዳለሁ አለው፡፡ ከዚያም አስከተለና ስለ ደህንነት መንገድ በሰፊው ከገለጸለት በኋላ ክርስቶስን የግል አዳኙ አድርጎ እንዲቀበል ጠየቀው፡፡
ያንን ምስክርነት የሰማው ሃኖቬር መኪናዋን ከመንገድ ዳር አንሸራትቶ ለአፍታ ሲያቆማት ሮጄር በአግራሞት ቢመለከተውም የተባለውን ሰምቶ ሃኖቤር  ከመኪናው  የሚያስወርድ መሰለው፡፡ ነገር ግን ሀብታሙ ነጋዴ አጎንብሶ ጌታን ከተቀበለ በኋላ ሮጄርን ማመስገን ጀመረ፡፡ “ይህ በሕይወቴ ከተከሰቱ ታላላቅ ቁም ነገሮች አንዱ ነው” ይላል ሮጄር፡፡ ከዚያም ሁኔታ በኋላ ሮጄር ከሃኖቤር ተለይቶ ወደ አቅጣጫው አመራ፡፡ ሃኖቬርም ወደ ቺካጎ ሄደ፣ ሁለቱ በዚያው ተለያዩ፡፡
ከአምስት ዓመት በኋላ ሮጄር ትዳር መሥርቶ ፣ የራሱንም ንግድ አቋቁሞ ፣ ከሁለት ዓመት ልጁ ጋር ወደ ቺካጎ ለመሄድ ሻንጣውን እየቀረቀበ እያለ አንዲት ነጣ ያለች የንግድ ካርድ አገኘ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ከሃኖቤር የተበረከተች ነች፡፡ ሮጄር ወደ ቺካጎ ከደረሰ በኋላ የሃኖቬር የንግድ ማዕከል የሚገኝበት ቦታ በካርዷ ላይ በተገለጠው አድራሻ መሠረት ፈልጎ አገኘና ወደዚያው አመራ፡፡ ወደ ቦታው ሲደርስ የእንግዳ ተቀባዩዋ የሃኖቬርን ባለቤት የሆኑትን ሚስስ ሃኖቬርን እንጂ ሚስተር ሃኖቬርን ማግኘት የማይቻል መሆኑን ስታረጋግጥለት ሮጄር ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ስለተቸገረ ግር አለበት፡፡ የእንግዳ ተቀባዩዋ በጥሩ ሁኔታና በመልካም አቀባበል ብታስተናግደም ግራ መጋባቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሆኖም አንዲት አምሳ ዓመት የሚሆናትን ንቁ ሴት እንዲያነጋግራት አድራጋዋለች፡፡
ሴትዮዋ (ሚስስ ሃኖቬር) "ባለቤቴን ተውቀዋለህን?አለችው፣  እጇን እየዘረጋች፡፡ ሮጄርም በማስከተል፣ አንድ ቀን ጧት የመኪና ርዳታ እንዲያደርጉለት በመንገድ ላይ ሆኖ ሲለማምን ሃኖቬር እንዴት ያለ እገዛ እንዳደረገለት በዝርዝር ሁሉንም ተረከላት፡፡ ሚስስ ሃኖቬር መለስ አደረገችና ያ ሆነው መቼ እንደሆነ ቀኑን ለማወቅ ፍላጎት አድሮባት ጠየቀች፡፡ ሮጄርም የዛሬ አምስት ዓመት ግንቦት 7 ቀን ሲሆን ያ ቀን ከሠራዊት የተባረረበት ቀን መሆኑንም በማስታወስ አረጋገጠላት፡፡ ያን ቀን የሆነ ልዩ ነገር ምን እንደሆነ ስትጠይቀው ለመናገር ቢያቅማማም የሆነውን ሁሉ መመስከር አስፈላጊ ንደሆነ ተሰማው፡፡  ስለ ወንጌል እንደገለጸለትና ሃኖቬርም መኪናውን ከመንገድ ዳር አስጠግቶ አቆመና አጎንበሶ በማልቀስ በዚያን ቀን ሕይወቱን ለክርስቶስ መስጠቱን ነገራት፡፡  ይህንን ምስክርነት የሰማችው ሚስስ ሃኖቬርም ሰውነቷ እየተንቀጠቀጠ ስትነፋረቅ ሮጄር ስሚስም "አሁን ባለቤትሽ ወዴት አለ?" ብሎ ጠየቃት፡፡ እስዋም ስቃ እየተናነቃት በደከመ ቃል ባለቤቷ ፣ ከእርሱ (ከሮጄር) ከተለየ በኋላ ያኔ ግንቦት 7 ቀን የመኪና ግጭት ስለገጠመው ወደ ቤትም ሳይገባ  በዚያው እንደቀረና እንደሞተ ነገረቺው፡፡ ስለ ባለቤቷ መዳን  ለረጅም ዓመታት በእግዚአብሔር ፊት ስትጸልይ ጌታ የተስፋ ቃል ቢሰጣትም ባለቤቷ መዳኑን ሳታይ በመቅረቷ ሕይወቷን ለጌታ መስጠት ካቆመች አምስት ዓመት እንደሆናት ገለጸችለት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የተናገረውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም አምላክ ስላልመሰላት ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት ባለቤቷ ደህንነት እንዲያገኝ አጥብቃ ፀልያለች፣ ጌታም ወደ ደህንነት እንደሚመራው የተስፋ ቃል ሰጥቶአታል፡፡ ይሁን እንጂ ያ ተስፋ ተፈጽሞ ለዓመታት የጸለየቺው ጸሎትም ተመልሶ በዓይንዋ ሳታየው የምትወደው ባሏ ሃኖቬር እስከ ወዲያኛው ተለያት፡፡ እርሷም ለአላኳ ያላትን መታመን አበላሸች፡፡
እንግዲህ ይህቺ ሴት እንደዚህ የወሰነቺው እግዚአብሔር ለባልዋ መዳን የጸለየቺውን ጸሎት ሰምቶ የመለሰላት ስላልመሰላት ነው፡፡ አንዳድ ጊዜ በክርስቲያኖች ሁሉ ሕይወት ይህንን የሚመስል ነገር ይከሰታል፡፡ የጸሎታችን መልስ ከመዘግየቱ የተነሳ ጌታ ጸሎታችንን እየሰማው ስለመሆኑ እንጠራጠራለን፡፡ ይህ በክርስትና ሕይወታችን የሚገጥመን ትልቁ የአጭር ጊዜ መልስ የማይገኝለት ፈተና ነው፡፡ እግዚአብሔር ነቢይ ልኮ ወይም በአንድ ሌላ ሰው አማካይነት የጸለይከውን/ሺውን ጸሎት ሰምቻለሁ ካላለ ወይም ደግሞ የለመንነውን ነገር በእጃችን አስቀምጦልን ካላየነው ለጸሎታችንም ሆነ ለገባልን የተስፋ ቃል ታማኝ የሆነ አይመስለንም፡፡ እግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ሚስስ ሃኖቤር ለባሏ መዳን የጸለየቺውን ፀሎት ሰምቶ ባሏንም ወደ ደህንነት አምጥቶ ሳለ እርስዋ ግን እግዚአብር ታማኝ አልሆነልኝም ብላ ለአምስት ዓመት ለእሱ ያላትን መሰጠት አቀዘቀዘችበት፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሁሉ ማለትም ለወንዶች፣ ለሴቶች፣ ለወጣቶች፣ ለአዋቂዎች፣ ለጎልማሶችና ለአዛውንት የታመነ አምላክ ነው፡፡ ለአገልጋዮች ፣ ለመሪዎችና ለቤተ ክርስቲያን ሁሉ እርሱ የታመነ እውነተኛ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም ቃል የሚነግረን ይህንን ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያረጋግጡልናል፡፡በብሉይም ሆ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የእርሱ ታማኝነት ተወስቷል፡፡ ቀናት ይለዋወጣሉ ፣ ይቀያየራሉም፡፡ ሰዎችም የጊዜውን ተጨባጭ ሁታዎችን እያዩ ይቀያየራሉ፣ ይለዋወጣሉም፡፡ መንግተትም ሥፍቸውን ይለቃሉ፣ሕጋቸውም ከእርሱ ጋር ያልፋ ይህ ሲሆን የሰዎችም አኗኗር እንደነበረ መቀጠል አይችልም፡፡ እኛም ለጌታ ያለን ታማኝነት ይቀየራል ይፋልም፡፡ ጌታ ግን ለእኛ ሁል ጊዜ ታማኝ ነው፡፡ የጸሎታችን መልስ ሲዘገይብን እኛም ከዚህ የተነሳ ሥፍራችንን ብንለቅም የዘላለም አምላክ ግን ሁል ጊዜ የታመነ ነው፡፡ የጸሎታችን መዘግየት የእርሱን ታማኝነት አያጎድለውም ይልቁንስ እርሱን በእምነት ባለመጠበቃችን የእኛን ታማኝነት ያጎድልብናል እንጂ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እርሱ ታማኝነት እንደሚከተለው ይነግረናል፡፡
እርሱ አምላክ ነው ሥራውም ፍጹም ነው፣ በመንገዱም ሁሉ የቀና ነው፣የታመነ አምላክ ክፋት የሌለበት እውነተኛና ቅን ነው(ዘዳግም 32 4 )
 ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሳ ነው፡፡ ርኅራኄው አያልቅምና፡፡ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፡፡ታማኝነትህም ብዙ ነው፡፡ ሰቆ. ኤር.322)
 አንተም አምላህ እግዚአብሔር እርሱ አምለክ እደሆነ ፣ለምወድዱትም ትዕዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ ደሆነ እወቅ( ዘደግም 79)
የእስራኤል ታዳጊ ቅዱሱም፥ እግዚአብሔር፥ ሰዎች ለሚንቁት ሕዝብም ለሚጠላው ለገዥዎች ባሪያ እንዲህ ይላል። ስለ ታማኙ ስለ እግዚአብሔር ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፥ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳ(ኢሳያስ 497)
በሕይወት ዘመናችንም ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ስራመድ ያየናቸውና የሳለፍናቸው መንገዶችም እግዚአብሔር አምላካችን ታማኝ መሆኑን ይነግሩናል፡፡ እግዚአብሔር እኛ ታማኝ ከሆነባቸው ከብዙ መንገዶች የሚከተሉትን ንመልት፡፡
1. እግዚአብሔር በቃሉ የታመነ ነው( ዕብ፡ 1023)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስብራውያን መልእክት ምዕራፍ 1023 ላይ ቃሉን የሰጠ የታመነ ነው ብሎ ይነግረናል፡፡ እግዚብሔር ለሕዝቡ የተስፋ ቃል ይሰጣል የሰጠውንም የተስፋ ቃል ይፈጽመዋል ፣ምክንያቱም እርሱ የተናገርን የተስፋ ቃል ለመፈም የሚተጋ አምላክ ነው፡፡፡፡ እርሱ የሰጠው የተስፋ ቃል አይወድቅም፣ አይሻርም ፣ ሳይፈጸምም አይቀርም ምክንያቱም ግዚአብሔር በቃሉና በሰጠው የተስፋ የታመነ አምላክ ነውና(ዘኁልቁ 2319)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰው ስላይለ አይዋሽም ፣ ሐሰትን አይናገርም፡፡ እርሱን ከሌሎች የአህዛብ አማልክት ልዩ የሚያደርገው የተናረውን ቃል በወሳኝ ሰዓትና ሁኔታ መፈጸሙ ነው፡፡ ብዙ ተስፋ የሚገቡ ግን አንዱንም መፈጸም የማይችሉ አያሌ ሰዎች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን በቃሉ የታመነ አምላክ ነው፡፡ እርሱ የማይዋሽና ሐሰትን የማይናር መሆኑን ጣዖት አምላኪዎች ራሳቸው እንኳን ያውቃሉ፡፡ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም ይዋሽም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም ያለው እኮ እግዚአብሔርን የማያመልክ የሞአብ ጠንቋይ ሆነ በለዓም ነው፡፡ ቃልቻዎች የእግዚአብሔርን ታማኝነት የሚመሰክሩ ከሆነ እኛ በየቀኑ እጁን እየተለማመድን የምንኖር አማኞች ደግሞ እንዴት ስለ እርሱ ታማኝነት አብልጠን አንመሰክርም? እነርሱ እግዚአብሔርን በሩቅ ያውቁታል፣ እኛ ግን በቅርባችን ሆኖ ፣ ከዚያም አልፎ በአጠገባችን ብቻ አይደለም በውስጣችን አድሮ ነው የምናውቀው፡፡ የጣዖት አምላኪዎች አምላካችንን የሚያውቁት ድንገተኛ በሆነ ጉዳይ ሲገለጥ፣ እነርሱን ሲቀጣቸውና የሕዝቡን ጩኼት ሰምቶ ሲመልስ፣ ተአምራትንም ሲያደርግ አይተው በፍርሃት ተውጠው ነው የሚያውቁት ፡፡ እኛ ግን በመከራችንም ሆነ በደስታችን ፣ በውድቀታችንም ሆነ በትንሳኤያችን ሁሉ ጌታችን ከእኛ ጋር ሆኖ አብሮ ሁሉን ሲጋፈጥ ስላየነውና ስለተለማመድነው በዚህ እናውቀዋን፡፡ አምላካችን እውነተኛ መሆኑን ጣዖትን የሚያመልኩም ሁሉ ያወቁት የእነርሱ አምላክ እንደ እኛው እግዚአብሔር አለመሆኑን እያዩና እያነጸጻሩ ስለሆነ በዚህ ያውቃሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ለእኛ ለአማኞቹ ዋሽቶብ አያውቅም፡፡ ሐሰት ለመናገር የሚችልበት ባሕሪይ የለውም፡፡ እርሱ በቃሉ የታመነ ነው፡፡
2. እግዚአብር በጥሪው የታመነ ነው ( 1 ቆሮ. 18-91 ተሰሎንቄ 524)፡፡
እግዚአብሔር ሲጠራን ካለንበት ሁኔታ ወደ ራሱ አሳብና ወደ መንግሥቱ ሊያሸጋግረን ነው፡፡ በፊት ከነበርንት ሁኔታ ይልቅ የተለ እንደሆነ ወደሚያውቅበት መልካም ሁኔታ አሸጋገረን ማለት ነው፡እንደዚም ደግሞ እኛን ከጠረን በኋላ ከሚያስፈልግን ነር አንድ አላጎደለብንም፡፡ ስለዚህ በእግዚአብር በአምላካችን እንደላደላለን ምክንያቱም ሱ በሁሉም መንገድና ኔታ ታማኝ አባታችንና አምላችን ነውና፡፡
እግዚአብሔር ለእኛ የሚያደርገው ግብዣ አንድ ትልቅ ንጉሥ ለልጁ ሠርግ ያዘጋጀው ግብዣ ዓይነት ነው፡፡ ንጉሡ ለልጁ ሠርግ ባዘጋጀው ግብዣ እንዲገኙ የተጠሩት ሰዎች እጅግ በጣም እድለኞች ናቸው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 22 የምናየው ይህንን ነው፡፡ ሁሉ ተዘጋጅቶአልና ወደ ድግሴ ኑ ብሎ ነው የጠራው፡፡ በጥንት ዘመን አንድ ግብዣ በሚደረግበት ወቅት የተቀጠረው ቀንና ሰዓት ለሰው ሁሉ ክፍት ሆኖ ይጠብቃል፡፡ በዚያን ወቅት ግብዣ ሁለት ደረጃ ያለው ሲሆን የመጀመሪያው  የሠርግ ዜ የተቀጠረ መሆኑንና ተጋባዞችም የክብር እንግዳ ሆነው የተመረጡ መሆናቸውን አውቀው በእለቱ ለመምጣት ራሳቸውን እንዲዘጋጁ የሚነገር ነው( ማቴ.222) ፡፡ የሚጋበዘውም ሰው የክብር እንግዳ ሆኖ ነው የሚጋበዘው፡፡  ሁለተኛው በግዣው ዕለት የግብዣው ደጋሽ የድግሡ ዝግጅት ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ የተመረጡት ወደ ግብዣው አዳራሽ እንዲመጡ የሚያደርገው ጥሪ ነው፡፡ በሁለተኛው ግብዣ የሚደረገው ጥሪ ከመጀመሪያው ይለያል፡፡ በመጀመሪያው የታደሙ መሆናቸውን የማሳወቅ ጥሪ ሰሆን ሁለተኛው ግን ዝግጅቱ ሁሉ ተጠናቋልና ገብታችሁ መጋበዝ፣ መብላትና  መጠጣት  ትችላላችሁ የሚል ጥሪ ነው፡፡ ድግሴን አዘጋጀሁ፣ኮረማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፣ ሉም ተዘጋጅቷል፣ ወደ ሠርጌ ኑ(.4 ላይ እንደዚህ እናባለን)፡፡ እንደዚህ ዓነቱ ግብዣ በሁሉም ዘንድ የሚፈለግና ሁሉም የሚቀበለው ነው፡፡ እዲሁም በክርስቶስ ዘመን የነበሩ ፈሪሳውያን ደዚያ ያለውን ግብዣ በጣም ይወዱታል፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ በግብዣ ሥፍራ የክብርን ወንበር ይፈልጋሉ ያው ለዚህ ነው( ማቴ.236)፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ግብዣ ሁሉም ሰው የሚፈልገው ቢሆንም ወደ ግብዣው አዳራሽ መግባት የሚችሉት ጥሪውን ሰምተው ምላሽ በመስጠት ወደ ሥፍራው የሚመጡ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልን ግብዣ የከበረና እኛ በእግዚአብር ፊት የታየንና የተከበርን መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
እግዚብሔር በብሉይ ኪዳን ነበሩ የእሥል ሕዝብ ሆነ በአዲስ ኪዳን ለነው አማኞች ሁሉ እንደየሁኔታችን የሚያቀርብልን ጥሪ አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል በትንቢተ ኢሳያስ  551-3 ባለው ክፍል ያቀረበው ጥሪ ለእሥራኤል ሕዝብ እጅግ ወሳኝ ጥሪ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡ እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ፡ ገንዘብም የሌለችሁ ኑና ግዙ ብሉም ያለ ገንዘም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ፡፡ ገንዘብ እንጀራ ላይደለ የድካማችሁን ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላች; አድምጡኝ ፤በረከትን ብሉ ፣ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው ፡፡ ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች የታመነቺይቱን የዳዊትን ምሕረት ፣ የዘላላምንም ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ፡፡
ይህ  ዋጋ ከፍለው እጀራና ውሃ ወተትም መግዛት ለማይችሉ ደካች የቀረበ ጥሪ ነው፡፡ እንጀራና ውሃ እንዲሁም ወተት የሚያስፈልጋቸው  መግዛት ንዳይችሉ ገንዘብ የሌላቸው፣ የተጠሙና የተራቡ  ብዙ አሉ፡፡ ምድራዊ ሀብትና ባለጠግነት ቢኖራቸውም በነፍሳቸው የጽድቅ ረሀብና ጥማት ያለባቸው ነገር ን በገዛ ሥራዎቻቸው ርካታንና ጥጋብን ማግኘት ያቃቸው አያሌዎች ናቸው፡፡ ጌታ እንደነዚህ ያሉትን  ኑና ያለ ገንዘብ ግዙ ይላቸዋል፡፡ እንዴት  ነው ያለ ገንዘብስ የሚገዛው? ዋጋው ስለተከፈለ ምን እከፍላለው ብለው ሳይጨነቁ ወስደው እዲበሉና እንዲጠጡ የተሰጠ ጥሪ ነው፡፡
የውሃ ጉዳይ ለእግዚአብሔር ሕዝብ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያተቱም ያ ውሃ ለመኖር አይችሉም ነበርና፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ሥራና የእርሱ መለኮታዊ አሠራር በተገለጡባቸው በብዙ ሥፍራዎች የውሃ አስፈላጊነት ተገልጧል፡፡ የእሥራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ትተው ሌሎች አማልክትን ባመለኩበት ወቅት ጌታ ሲናገራቸው "እኔን የሕይወት ዉሃ ምንጭ ትታችሁ ለእናንተ ውሃ ሊይዙ የማይችሉ የተቀደዱ ጉድጓዶችን ቆፈራችሁ" ይላቸው ነበር( ኤር.213)፡፡ ለተጠማ ሁሉ የሚሰጥ ውሃ ነው፡፡ ውሃ ለጥም ካታ ከመዋሉም ባለፈ በሰው ልጆች ሕይወት ሁሉ የማያስፈልግበት ጊዜና ሁኔታ የለም፡፡ ውሀ ለምግብ አገልግሎት፣ በቤት ግንባታ፣ ለሰውነትና ለዕቃዎች ንጽሕና፣ ለእርሻ አገልግሎት፣ እንዲሁም ደግሞ ለፋብሪካዎችና ለእንዱሰተሪዎች ምርታማነት ሁሉ ውሀ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ምድራዊና ቀሪ ሲሆኑ እግዚአብሔር ለሚያምኑት ሁሉ የሚሰጠው ውሀ ሰዎች ጠጥተው ዳግም እንዳይጠሙ የሚያደርግ የሕይወት ውሀ ነው፡፡ ይህን ውሀ የሕይወት ጥማት ያለበት ሁሉ እንዲወስድና እንዲጠጣ ጌታ ይጠራል፣ ጥሪውንም ተቀብለን ለመጣነው ሁሉ የማያጠራጥር ርካታ ይሰጠናል፡፡ ጌታ የሌለው ሰው በምድረ በዳ እንዳለ የሚጠጣውንም ውሀ እንዳጣ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውሃ ኑ ያለ ዋጋም ግዙ በማለት በቃሉ ይጋብዛል፡፡
የሰው ልጅ ለራሱ የሚያደርገው ጥረት ሁሉ የሚያጠግበው ስላይደለ እግዚአብሔር የገዛለትን እንጀራና ውሃ በነፃ ወስዶ እንዲበላና እንዲጠጣ ተጋብዟል፡፡ እግዚአብር የሚሰጠው የሕይወት እንጀራና የሕይወት ውሃ ለዘላለም የሚያጠግብና የሚያረካ ነው፡፡ ይህን ጥሪ ይፈጽምልን ዘንድ እርሱ የታመነ አምላክ ነው፡፡
በአዲስ ኪዳንም የተደረገ ሌላ አንድ ትልቅ ጥሪ አለ ያውም እረፍት እድናገኝ የተደረገልን ጥሪ ነው፡፡ እናንተ ደካች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳፋችኋለሁ(ቴዎስ 1128)፡፡ ጌታ የሚጠራቸው የዓለምና የጢአት ንደሁም የሥጋ ሽክም በቶባቸው መሸከም ያቃታቸውን በራሱ ዘንድ ሊያሳርፋቸው ወዶ ያቀረበው ጥያቄ ነው፡፡ ታዲያ እግዚአብንደዚህ ያሉትን ከሸክማቸው ጋር የሚንገላቱትንና ድም ያለባቸውን በእርግጥ ያሳርፋቸዋልን? መልሱ አዎን እርሱ በጠራን ጥሪ የታመነ አምላለሆነ ያሳርፈናል፡፡ ስለዚህ ይህንን የሕይወት ግብዣ ሰምተው ፈጥነው ያልመጡ ሁሉ የንጉሡን ሠርግ ችል ብላው ወደየገዛ መንገዳቸው እንደሄዱ ተጋባዦች ናቸው፡፡ የማይገኝ በረከት አምልጦአቸዋል፡፡ በሌላ ሥፍራ ከሚደረገው ድግስ ሁሉ የተለየና የላቀ ድግስ ስለሆነ ይህንን ድግስ ቸል ብሉ ሌሎች ያልታደሙ ያተጠበቁም መጥተው የድግሱን አዳራሽ ይሞሉታል፣ዝግጅቱ ሁሉ ለእርሱ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው ጌታ የሚያደርግለትን ጥሪ ሰምቶ ወደ እርሱና እርሱ ወደሚሰጠው እረፍት መምጣት አለበት፡፡ ጌታም ሊረዳንና ከሸክማችንም ሁሉ ያሳርፈን ዘንድ የታመነ አምላክ ነውና፡፡
3.      እግዚአብር በጥበቃው የታመነ ነው(2 ተሰ.33)፡፡
21ኛው ክፍለ ዘመን የምኖር አማኞች የክርስትና ምልክት አድርገን የምንጠቀመው መስቀል እንደሆነ ሁሉ በጥንት ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የእምነታቸው ምልክት አድርገው ከተጠቀሙባቸው ምልክቶች የበግ ጠቦት በብብቱ አቅፎ የያዘ አንድ ሰው ምስል እንደነበር ያታወቃል፡፡ በእርግጥ እነዚያ ወገኖች የክርስትናቸው ምልክት ይህ ብቻ ሳይሆን የዓሣ ምሥል ፣ በእሳት ውስጥ የሚገኙ የሦስት ሰዎች ምስል፣ የዘንባባ ዝንጣፊና ሌሎችም ያሉ ሲሆን የበጉን ጠቦት የተሸከመ ሰው ምሥል ግን በስዴትና በመከራ ውስጥ ሲያልፉ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ማጽናናትና እንዴትስ ያ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የሚያሳይ ትርጉም ያለው ምልክት ነበር፡፡ በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ካለን ግንኙነት አንዱና ትልቁ የእረኛና የበግ ግንኙነት ነው፡፡ እግዚአብሔር እረኛችን ሲሆን እኛ ደግሞ በጎቹ ነን፡፡ እግዚአብሔር የሕዝቡ እረኛ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ መዝ 231-6 ያለው ክፍል ዳዊት እግዚአብሔርን እረኛዬ ነው ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር ራሱ ለሕዝቡ እንዴት ዓይነት እረኛ እንደሆነ በትንቢተ ኢሳያስ 40 11 ላይ አረጋግጧል፡፡ መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል ይላል ፡፡ ንጉሡ ዳዊትም በዝማሬው ላይ የእግዚአብሔርን እረኝነትና ጥበቃ ግልጽ አድርጎ ያስተምረናል፡፡ የክርስትና ሕይወት በተራራና በሸለቆ ንዲሁም በሽንተረር እንደጓዝ ነው፡፡ በጎች በገደላገደልና በቋጥኝ ድንጋዮች መካከል በሚያልፉበት ወቅትም እረኛቸው ወደ ገቡበት ሥፍራ ገብቶ እንደሚፈልጋቸው ሁሉ የእግዚአብሔርም ጥበቃ እንደዚያው ነው፡፡ ዳዊት ሲዘርም በሞት ጥላ መካካል እንኳን ቢሄድ ክፉን እንደማይፈራ ይናገራል፡፡ ለእግዚአብሔር ሰዎች የሞት ጥላ ማለፊያቸው እንጂ መኖሪያቸው አይደለም፡፡ አቋርጠው የሚያልፉበት መንገድ እንጂ መሞቻቸው አይደለም፡፡ የአማኞች ሕይወት ፍጻሜው እግዚአብሔር ያየላቸው የበረከት ሥፍራ እንጂ የሞት ጥላ አይደለም፡፡ ይህንን የሞት ጥላ መንገድ ሳናልፍበት ወደ ጸዮን የምንሄድበት አቋራጭ መንገድ ግን የለንም፡፡ ቢሆንም ጌታ ከእኛ ጋር ስለሚሆን ክፉ አያስፈራንም፡፡
ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቶቹ ውስጥ የእግዚአብሔርን ጥበቃ አውስቷል፡፡ ለተሰሎንቄ አማኞች በጻፈው መልእክት የሚጠብቃችሁ የታመነ ነው( 2 ተሰ. 33) ይላል፡፡ እግዚአብሔር በታማኝት ይጠብቀናል ስንል ምን ማለታችን ነው፡ እርሱ እንደምንደ ሳይሆን የገዛ በጎቹን የሚጠብቅ የበጎች ባለቤት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ስለ ማኝ እረኝነቱ ሲናገር ፡
መልካም እረኛ እኔ ነኝ፡፡ መልካም እረኛ ነፍሱን ለጎቹ ያኖራል እረኛ ያልሆነው በጎቹም እርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ተኩላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል፡፡ ሞያተኛ ስለሆነ ለጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል፡፡ መልካም እረኛ እኔ ነኝ፡፡ አ ንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ(ዮሐ.1011-15)፡፡

በዚህ ክፍል ጌታ የሱስ የራሱን እረኝነት ከሞያተኞች ሥራ ጋር በማነጸጸር ያስተምረናል፡፡ ሞያተኞች ለበጎች ባለቤትት ስለማይሰማቸው ነጣቂ አውሬ በሚመጣበት ጊዜ በጎችን ለአውሬዎች ሰጥተው ይሸሻሉ፡፡ የበጎች ባለቤት የሆነው መልካም እረኛ ግን ነፍሱን ለበጎቹ የሰጣል ንጂ ትቶ አይሸሽም፡፡ ጌታ ኢየሱስም መልካም እረኛችን ሆኖ ሰይጣን ሌባው ሊሰርቀን፣ ሊርደንና ሊያጠፋን በሚመጣበት ወቅት ስለ እኛ ነፍሱን አሳል ሰጠ፡፡ እግዚአብር ለእኛ ያለውን በቃ ስንመለከት የራሱ ምክንያቶች አሉት፡፡ ለምን እግዚአብር ይጠብቀናል?
· እኛ እንዳንጠፋ፡ ሌባው እንዳይሰርቀን፡፡ እንዳያርደን ነው፡፡
· እንዳንሰናከል ነው፡፡ ይሁዳ 24
· በክብሩ ፊት ያለነቀፋ ለመቆም እንድንችል ነው፡፡
ጆን ፓንቶን የተባለ ሚሺነሪ ከሚስቱ ጋር የሚስዮናዊነት አገልግሎቱን ለመስጠት ወደ ኒዩ ሄብሪድስ አይስላንድ ሄዶ ለረጅም ጊዜያት ጌታን አገልግሏል፡፡ በዚያ አገር በሚሲዮን ጣቢያ እያለ ከአገሩ ሰዎች አንዳንድ ክፉዎች በጆን ፓንቶንና በባለቤቱ ድንገተኛ አደጋ ለማድረስ ወደ ሚስዮን ጣቢያው ቀረቡ፡፡ ሚሲዮናውያኑ ባልና ሚስትም አደጋ እንዳጠላባቸው ቢያውቁም ጊዜው ከእኩለ ሌሊት ያለፈ በመሆኑ ምንም ይሁን ምን የሚመጣውን መከራ ከመቀበል ሌላ ማድረግ አልቻሉም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም የበለጠ መፍትሔ ተንበርክኮ መጸለይ እንደሆነ ስለሚያምኑ በአምላካቸው ፊት ጥብቅ ፀሎት አደረጉ፡፡ የሚስዮን ጣቢያ በአደጋ ጣዮች ምክንያት በከፍል በእሳት የተቃጠለ ቢሆንም ሌሊቱ ሲነጋ እነዚያ ሊገድሉአቸው የመጡ ሰዎች በግቢው ውስጥ አንዳቸውም አለመኖራቸውን ስለተረዱ ሚሲዮናውያኑ ባልና ሚስት በጣም ተደነቁ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን ስለ ሰማ አመስግነው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፡፡ ከዓመት በኋላ ሚስዮናውያኑን ለመግደል ከመጡ ሰዎች አንዱ የሆነው የጎሳ መሪ ጌታ ኢየሱስን የግል አዳኙ አድርጎ ተቀበለ፡፡ ስለ ሕይወታቸውና ስላለፉባቸው አንዳንድ አጋሚዎች ሲመሰክሩ ሳለ ጆን ፓንቶን ያን ጊዜ ቤታቸውን እያቃጠሉ እያለ ለምን ሳይገድሉአቸው ትተው እንደሄዱ ሲጠይቀው የጎሳ መሪ የሆነው አዲሱ ሰው ሲመልስ በጥየቄ መልክ "ያን ቀን ከእናንተ ጋር የነበሩ ግን እነዚያ ሰዎች እነማን ናቸው "? አለው፡፡ ከሚሲዮናዊያን ጋር ማንም እዳልነበረ ሲነግሩት በመገረም እኛ ያንን ግቢ ትተን የሄድነው ቤቱን እያቃጠልን ወደ እናንም እየቀረብን ሳለ ሚያብረቀርቅ መጎናጸፊያ የለበሱ፣ የተመዘዘ ሰይፍ የያዙና የሚያስፈሩ በመቶ የሚቆጠሩ በትክለ ቁመናቸው ግዙፍ የሆኑ ሰዎች የሚሲዮናውያኑን ቤት ከብብው ስላየን ከእነርሱ የሚሰነዘርብንን ጥቃት ፈርተን ሸሸንና ሄድን ብሎ መሰከረ፡፡ ጆን ፓንቶንና ባለቤቱ ጥቃት በተቃጣባቸው ቀን ይታያቸው የነበረው የአደጋ ጣዮች ሁኔታ እንጂ በዙሪያቸው ያለ የእግዚአብሔር ጥበቃ አልነበረም፡፡ ነገር ግን እነርሱ ባያዩትም እግዚአብሔር ልዩ የሆነ ጥበቃ በዙሪያቸው አድርጎላቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ነው የጌታ ቃል ጌታ ሳንሰናከል የሚጠብቀን እንደሆነ የሚነግረን( ይሁዳ 24)፡፡ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር አምላካችን ከክፉዎች ሁሉ ይታደገናል፡፡ እግዚአብሔር የሚጠብቀንም ያማቋረጥ ነው፡፡ እሥራኤል የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋም( መዝ 1263)፡፡ ስለዚህ ይህ የሚጠብቀን አምላክ እግዚአብንደማነንም ሳይሆን የታመነ መሆኑን አውቀን በእርሱ ሙሉ በሙሉ ልንታመንና ልንደገፍበት ይገባናል፡፡
4. በመከራ ሊደግፈን በፈተናም ጊዜ ሊያበረታን የታመነ ነው(1ቆሮ. 10 13 ፡፡ )
የሰው ልጆች ሕይወት በመከራና በፈተና የተከበበ ነው፡፡ እያንዳንዳችን የምናልፍበት የመከራና የፈተና መንገድ አለ፡፡  ክርስትናም መከራ እንዳበት የታመነ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ይህንን አረጋገግጦልናል፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስም በስሙ መከራ እንቀበል ዘንድም ጭምር እንደተጠራን ስተምረናል( ፊልጵ 121)፡፡ የሆነ ሆኖ መከራ ለማም የሚመች አይደለም፡፡ የመከራ ብዛት ብዙዎችን ሥፍራቸውን ሊያስለቅቅ የሚችል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልዩ ፀጋ ካልተገለጠ ተሰናክንበት ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሐሔር በዚያ ፈተና ውስጥ ብቻችን አይተወንም፡፡ ስለ ክርስቶስ ስንሰደድ ስንነቀፍና በሕይወታችን መከራና መነቀፍ ሲበዛ ጌታን ማመስገን እንዳለብን ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ያስተምረናል( 1ጴጥ. 411-14)፡፡ ምክንያም በክርስቶስ ስም በምንነቀፍበት ወቅት የክብር መንፈስ የእግዚአብር መንፈስ በእኛ ላይ ስለሚያርፍ ነው፡፡ በ 1ቆሮ. 10 13 ላይም እንደምመለከተው እግዚአብሔር አምላክ ማናችንንም ከምንችለው በላይ እንደማይፈትነን ቃል ገብቶልናል፡፡ መጠኑን ያለፈ በሌሎች ላይ ያልሆነ ፈተናና መከራ እዲደርስብን ጌታ አይፈቅድም፡፡ በእኛ ላይ ጌታ የማይፈቅዳቸው ነገሮች አሉ፣ አንደኛው ከምንችለው መጠን አብልጠን እንድንፈተን የማይፈቅድ ሲሆን ሌላው ደግሞ ፍርዳችን በድር ላይ እንዲጣመም አይፈቅድም፤በምድር ላይ የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በች ይረግቸው ዘንድ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ የሰውንም ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም(ሰቆ.334-36)፡፡  እግዚአብሔር እንድንፈተን ቢፈቅድም የምንችለውም ያህል ብንፈተንም እርሱ ከፈተና ጋር መውቻውንም ደግሞ ያዘጋጅልናል፡፡ ስለዚህ ፈተናና መከራ፣ ችግርና ጭንቀት በሚገጥመን ጊዜ ሁሉ መፈተናችንን ሳይሆን በእኛ ፈተና ጊዜ ጎልቶ የሚታየውን የእግዚአብርን ታማኝነት እንድንመለከት ይገባናል፡፡
5. ኃጢአታችንን ይቅር ሊለንና ሊያነጸን የታመነ ነው(1ዮሐ 1-7-9)፡፡
ኃጢአት በነፍሳችን ላይ ያለ ዕዳ፣ በእእምሮአችንም ያለ ማቋረጥ የሚከሰን ባላንጣችን ነው፡፡ ሕይወታችንንም የሚያዳክምና የሚያቆሽሽ መጥፎ እድፍ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት የሚያበላሸው ኃጢአት ነው፡፡ የእግዚአብሔርም የማዳን ክንድ በሕይወታችን እንዳይገለጥ የሚያደርግ ነው፡፡  የዚህ ዓለም ትልቁ ችግር የምጣኔ ሀብትና የሌላ እጥረት ሳይሆን ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግኑኝነት ከማበላሸቱ የተነሳ በምድር ላይ ያመጣው መርገም ነው ፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ከአምላኩ ጋር ያለውን ሕብረት ለማደስ የሚችለው ከኃጢአቱ የታጠበና የነጻ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በጣም የሚያስገርመው ነገር ኃጢአት የሚያስከፍው ዋጋ ውድ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ለኃጢአቱ የሚገባውን ዋጋ ለመክፈል የሚችል ብቃት ያለው ማንም አልተገኘም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያደረገልን ይቅርታና የበደል ሥርየት በፊቱ ብቁ እንድንሆን አድርጎናል፡፡
እግዚአብሔር የሰውን ኃጢአት ይቅር ካላለ ሰው የእግዚአብሔርን ፊት ማየት የሚችልበት መንገድ የለውም፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሁላችንንም ኃጢአት በጌታ በኢየሱስ በኩል ይቅር አለ፡፡ ኃጢአታችን ይቅር መባሉ  ከእግዚአብር የተሰጠን ትልቁ እድል ነው፡፡ እርሱም ደግሞ ኃጢአታችንን ቅር ል ከዓመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነ ነው፡፡
6.      ጸሎታችንን በመስማት የታመነ ነው( 1 ዮሐ 513)፡፡
እግዚአብሔር ጸሎቴን ይሰማል ወይስ አይሰማም የሚለው የብዙዎች ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ የጸሎታችን መልስ ሲዘገይ እግዚአብሔርን የረሳው ይመስለናል፡፡ አምላካችን ለእኛ ያለው ዓላማም ግልጽ አልሆን ይለናል፡፡ ይህም ደግሞ በምድር ላይ የሚገጥመን ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ይህ የሚሆነው እኛ እግዚአብሔር በራሱ መንገድና ጊዜ ሳይሆን እኛ በመረጥነው መንገድና በቀጠርነው ቀን እንዲሠራ ስለምንፈልግ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የምንጠብቀው እኛ በምናውቃት በዚያች በለመድናት አንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ እንሳሳታለን፣ በጌታችንም ላይ ያለን እምነት ይሸረሸርብናል፡፡ እርሱ እንደሆነ ከተለመደው ውጭ መሥራት ልማዱ ነው፡፡ ከሰማይ የሚወርደውን ዝናብና ደመና ስንጠባበቅ ከምድረ በዳ ጎርፍ አምጥቶ ምድሪቱን ሊያረሰርስ የሚችል ነው፡፡ ከንጉሥ ጎተራ እህል ለሚጠብቀው ረሀብተኛ ሕዝብ ስንዴና ዱቄት ለመስጠት ለምጻሞችን በማንቀሳቀስ ለወራሪ ኃይልም የነጎድጓድና የፈረስ ድምፅ አሰምቶ ብዝበዛ እንዲበዛ የሚያደርግ አስገራሚ አምላክ ነው፡፡ እርሱ በራሱ መንገድ እንዲሠራና በራሱም ቀን እንዲመጣ እንጂ እኛ በለመድናት በዚያች አንዲት መንገድ ብቻ እንዲሠራ አንጠብቅ፡፡ በአንድ መንገድ ብቻ የተሰጠን ደህንነታችን ብቻ ነው፡፡ ለደህንነት የተሰጠን መንገድ አንድ ብቻ ሲሆን ያውም ጌታችንና ኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እግዚአብሔር የሰውን ጸሎት ሰምቶ የሚመስቸው መንገዶች በጣም ዙ ናቸው፡፡ ሚስስ ሃኖቬር ስለ ባሏ መዳን ለዓመታት ስትጸልይ ቆይታ ባሏ ከመሞቱ በፊት ስለመዳኑ እርግጠኛ ስላልነበረች እግዚአብሔር የገባውን  የተስፋ ቃል አይፈጽምም ብላ ለእርሱ ያላትን ፍቅር ለአምስት ዓመት አቀዘቀዘችበት፡፡  እግዚአብሔር ግን መንዱም ቀኑም ከእኛው የተለየ ነው፡፡ ፀሎታችን የዘገየ፣ ተስፋ ቃሉም ፈጽሞ የተረሳ ቢመስለን እግዚአብሔር ግን የለመንነውንና የጠየቅነውን ሁሉ ሊሰጠን የታመነ አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋሪያው ዮሐንስ  በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንምን ይሰማናል (1ዮሐ 513) ብሎ ይነግረናል፡፡  ለምንድነው የምንደፍረው? እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደሚሰማ ምንም ጥርጥር ሳይኖርብን በጌታ እንታመናለን ማለቱ ነው፡፡  አምላካችን ጸሎታችንን ሰምቶ መልስ ሊሰጥ የታመነ አምላ ነው፡፡ ክብር ለስሙ ይሁን፡፡ አሜን፡፡
በመጨረሻም ከሰው ይልቅ እግዘአብሔር ብቻ የታመነ አምላ በመሆኑ እምነታችንንና ተስፋችን በእርሱላይ ብቻ ልንጥል ይገባናል፡፡  የእግዚአብሔር ተስፋ ሩቅ የሆነባችሁ ፣ የገባላችውም ቃል የተረሳ የመሳለችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ዛሬም አልረሳችሁምና በፊቱ በእምነት ቁሙ፡፡  በመከራና በችግር ውስጥ ሆናችሁ እርሱን ለምትጠብቁ፣ የተነሳው ወጀብና አውሎ ነፋስ ታንኳችውን የሚያንገላታባችው  ሁሉ ጌታ እግዚአብሔር በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ የታመነ አምላክ መሆኑን አውቃችሁ  በእርሱ ልትደገፉ  ይገባቸዋል፡፡እግዚአብሔር የታመነና እውነተና አምላክ በመሆኑ በእርሱ ታመኑ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕይወት ሰልፍና ጦርነት የሚበዛባት ከመሆኗ የተነሳ በእናንተና በሞት መካከል አንድ ርምጃ ብቻ  የቀረ  እስክመስላችሁ ድረስ በሥጋት ውስጣ ያላችሁ ውድ የጌታ ባሪያዎች አምላካችሁ የሆነው እግዚአብሔር ዛሬም በጥበቃው ላይ ስለሆነና ለአውሬው አሳፎ ስለማይሰጣችሁ ከዳዊት ጋር እግዚአብሔር እረኛዬ ነው ፣ምንም አላጣም፣አርፋለሁ፣መስክ አለኝ ፣አልፈራም እከብራለሁ፣ በጠላቴም ፊት በዘይት እቀባለሁ እያላችሁ ዘምሩ፡፡ ጠላታችሁ በማግሳቱ ና አብዝቶ በመጨኹ በከንቱ የሚደክመው እርሰ ነው እናንተስ በዓለቱ ውስጥ ተሸሽጋችኋልና አትፍሩ፡፡ የለመናችሁትና የጸለያችሁትን ከገመታችሁትና ካሰባችሁት በላይ አድርጎ ሊሰጣችሁ የእኛ አምላክ የታመነ በመሆኑ በፊቱ በርቱ፡፡ ፀጋውም ይብዛላችሁ፡፡ ኢየሱስ ጌታ፣ኢያሱስ ንጉሥ ፣ ኢየሱስ ሁል ጊዜ! አሜን፡፡





  

1 comment: