የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ አገልግሎት
ከፓስተር ሳሙኤል ሾንጋ
በአንድ ወቅት በአሜሪካን አገር ግራንድ ራፒዲስ በሚባለው ከተማ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የእግዚአብሔርን ፊት በጾምና በጸሎት እየፈለግን ባለበት ሰዓት የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያካፍል የተመረጠው ሰው ለመልእክቱ መግቢያ ያደረገውን የማይረሳ ምሳሌ ሁል ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡ እንዲሀ ነው ነገሩ! እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2009 የተባበሩት መንግታት የኢኮኖሚ ፎረም ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ የተለያዩ የመንግሥታቱ አባል አገሮች ተወካዮች የየአገራቸውን የሥራ ሪፖርት ይዘው ቀርበው ነበር፡፡ ከአገሮች የመጡ ተወካዮች ምን ለመሥራት ታሰቦ ምን አንደተከናወነና እንዴት ያለ ለውጥ እየታየበት እንደሆነ እያካፈሉ አንዳቸው ከሌላው ልምድም እየቀሰሙ ባለበት ወቀት የአንድ አገር ሪፖርት ግን የብዙዎችን ልብ የነካና የተደነቀ ነበረ፡፡ ያቺ አገር በሩቅ ምሥራቅ የምትገኝ ባርማ በመባል የምትታወቅ አገር ነች፡፡ ባርማ በ2009 ዓ.ም ልትሠራ ያቀደችውና ያከናወነችው ሌሎች አገሮች ካቀረቡት ጋር በፍፁም የማይገናኝ ነገር ግን ሁሉንም ያስደነቀ አቀራረብ ነበር፡፡ ሌሎች ያቀረቡት ስለ ልማት፣ ስለ አኮኖሚያዊ እድገት፣ ስለ ውጭ ግንኙነትና ስለ ወታደራዊ ዝግጅቶቻቸው ሆኖ ካቀዱት ምን ያህል እንደተሳካላቸው ነበር ያቀረቡት፡፡ ነገር ግን ባርማ በ2009 መግቢያ ላይ የያዘቺው እቅድ በአገሪቱ ውስጥ ያለ እያንዳንዱን ዜጋ በነፍሰ ወከፍ ደስተኛ እንዲሆን ስለማድረግ ነበር፡፡ ከልማት ሥራዎች ሁሉ የሚቀድመው ዜጋው ረክቶና ተደስቶ የመኖር ጉዳይ ስለሆነ ከዚህ አንፃር አቅዳ 90 በመቶ እንደተሳካላት ያቀረበቺው ሪፖርት ሁሉንም የጉባኤ ተሳታፊዎችን ሊያስደንቅ ችሏል፡፡
ይህ ለእኛ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለምናገለግል
ሰዎች እጅግ በጣም አስገራሚ ትምህርት ያለበት
ምሳሌያዊ መልእክት ነው፡፡ እኛ ከባርማ
መንግሥት ይልቅ የምናገለግላቸውን ቅዱሳን
ልባቸው እንዲያርፍ ማድረግ ይኖርብናል፡፡
እግዚአብሔርም እኛን በዚህ ምድር ላይ
ያስቀመጠን የእርሱን አሳብ እያለገልን በስሙ
የተጠሩትን ሁሉ እንድናንፃቸው ነው፡፡
የአገልጋዮች አገልግሎት
የምዕመናንን ልብ ያሳፈርፍ
ዘንድ ይገባል፡፡ ይህ እንዲሆን
ደግሞ የእግዚአብሐሔር ቃል ይመክረናል፡፡
አገልግሎታችን የቅዱሳንን ልብ ማሳረፍ እንዳለበት
የሚያስተምረውን ትምህርት ለማግኘት ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ
ለፊልሞና የጻፈውን መልእክት ከቁጥር 1-7
መመልከት
ይኖርብናል፡፡ ወደ ዋናው አሳባችን ከመግባታችን
በፊት ስለ ፊልሞና መጽሐፍ ሁለት ወይም ሦስት
መሰረታዊ በሕሪያቶችን እንመለከታለን፡፡
·
የፊልሞና
መጽሐፍ ሐዋሪያው
ጳውሎስ በእሥር
ቤት ሆኖ ከጸፋቸው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት
አንዱ ነው፡፡ ጳውሎስ
ይህንን መፅሐፍ በሚጽፍበት ወቅት በሮም እሥር
ቤት ሊሆን ይችላል፣ ወይም በሌላ ቦታ ሊሆን
ይችላል ብቻ መልእክቱን
ያስተላፈው ከእሥር ቤት ነው፡፡ የፊልሞናን
መጽሐፍ በጣም ተናፋቂ ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይህ ነው፡፡ ከየትና እንዴት በማንስ ተጻፈ የሚለው አሳብ የሚተላለፈው
መልእክት ተሰሚነት እንዲኖረውና አቅም እንዲያገኝ ያደርገዋል(
ቁ.9)፡፡
·
የፊልሞና
መፅሐፍ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካሉና በጣም አጠር
ካሉ ወይም ምዕራፍ ከሌላቸው መጻሕፍት አንዱ
ነው፡፡
በጠቅላላው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ አራት
ያህል መጻሕፍት በምዕራፍ ያልተከፈሉ ሲሆን
እነርሱም አብዲዩ፣2ኛ
ዮሐንስ፣
3ኛ
ዮሐንስ ና ፊልሞና ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት
በምዕራፍ አይከፋፈሉ እንጂ ትልቅ ቁም ነገር
ያዘሉ ናቸው፡፡ በምዕራፍ
ያልተከፈሉበት ምክንያት አጠር ባለ መልክ
ስለቀረቡ ብቻ እንጂ መልእክቱ ከእግዚአብሔር
ስላልሆነ አይደለም፡፡
·
የፊልሞናን
መጽሐፍ ልዩ የሚያደርገው የመልእክታቴ ምጋቤ
አካል ከሆኑት መጸሕፍት የሚመደብ መሆኑ ነው፡፡
ይህ
መጽሐፍ ለቡድን ወይም ከቤተ ክርስቲያን ወይም
ለአንድ አገልግሎት ክፍል የተላከ ሳይሆን
የሕዝብ እረኛና አገልጋይ ለሆነ
ሰው በግሉ የተላከ የመጋቢያዊ መልእክት ያዘለ
ነው፡፡ ለአንድ ግለሰብ የተላኩ ሌሎችም
መጻሕፍት በአዲስ ኪዳን ውስጥ
ያሉ ሲሆን ሁላቸውም የየራሳቸው ባሕሪያት
ያሉአቸው ናቸው፡፡
በዚህ
አጭር ትምህርት ውስጥ ሐዋሪያው ጳውሎስ
ለፊልሞና
የሚያቀርበውን መልእክት ሁሉንም ማየት እችልም
፣ ነገር ግን ከቁ 1-7
ያለውን
ብቻ እንመለከታለን፡፡ ይህንን
መልእክት የሚያስተላልፈው የእግዚአብሔር
ሰው ጳውሎስ የጌታ አገልጋይ ከሆነው ከፊልሞና
ጋር ትልቅ የአገልግሎት
መተሣሠር ነበረው፡፡ ጳውሎስ በእሥር ቤት
ሆኖ ስለ ፊልሞና አገልግሎት የሰማው ነገር
በእርሱ ላይ የፈጠረው አዎንታዊ ተጽእኖ በዚህ
የንባብ ክፍል ውሰጥ ይገኛል፣ ምክንያቱም
ጳውሎስ በፊልሞና አገልግሎት ምክንያት
መጽናናቱንና መደሰቱን ይናገራል(
ቁ.
7)፡፡
ጳውሎስ የተደሰተበትና በብዙ መጽናናት
የተጽናናበት ምክንያት አለ፣ ያውም በፊልሞና
አገልግሎት በቤተ ክርሰቲያን
ያሉ ቅዱሳንን
ልብ አርፏል፡፡ የምዕመናንና
የአገልገሎት አጋሮችን ልብ የሚያሳርፍ
አገልግሎት ማገልገል እንዴት ያለ ትልቅ መታደል
ነው!
ፊልሞና
የሚያገለግለው አገልግሎትና በቤተ ክርስቲያን
ውስጥ የሚያደርገው ሥራና ተግባር ሁሉ የሕዝቡን
ልብ ከመረበሽና መንፈሳቸውን ከማናወጥ ይልቅ
ልባቸውን የሚያሳርፍ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛ
ዛሬ በዚህ ዘመን የምንገኝ አማኞች የቅዱሳንን
ልብ ከማሳረፈ አንፃር እንዴት አይነት አገልግሎት
እየሰጠን እንደሆነ ራሳችንን መመልከት
ይኖርብናል፡፡ እስቲ የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ
ሕይወትና አገልግሎት ምን እንደሚመስል ሐዋሪያው
ጳውሎስ ለፊልሞና ከጻፈው መልእክት እንመልከት፡፡
1.
አገልገሎቱ
የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፈው
አገልጋይ
የይቅርታ ልብ ያለው ነው፡፡
ጳውሎስ
ይህንን መልእክት ለፊልሞና የሚልክበት ተቀዳሚ
ምክንያት በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል
ክርስትያናዊ ይቅርታን ለማስፈን ነው፡፡ ይህ የፊልሞና መጽሐፍ ሙሉውን የሚናገረው ስለ
ይቅርታ ነው፡፡ ፊልሞና በፍቅርና ሌሎች መልካም
ሥራዎች የቅዱሳንን ልብ ያሳረፈ ምርጥ አገልጋይ
ቢሆንም ጳውሎስ በድጋሚ ስለ አናሲሞስ
ይጠይቀዋል፡፡ አናሲሞስ የፈልሞና አገልጋይ
(በጥንት
አባባል ባሪያው)
የነበረ
ሰው ነበረ፡፡ ከፊልሞናም ጋር አብሮ ይኖር
ነበር፡፡ ነገር ግን ፊልሞናን ዘርፎ የኮበለለ
ሰው ነው፡፡ ይህ በመሆኑ የፊልሞና ልብ በአናሲሞስ
ማዘኑ የማይቀር ነገር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ
አናሲሞስ ኮብልሎ በሄደበት ጳውሎስ አገኘውና
ወንጌል ሰበከለት፣ አናሲሞስም በጌታ
በኢየሱስ አመነ፡፡ ጳውሎስ በሮም እሥር ቤት
በነበረበት ወቅት በወንጌል እንዲያምን ምክንያት
ስለሆነው አናሲሞስ ይረዳውና ያግዘዘው ነበር፡፡
በዚህን ጊዜ የአናሲሞስ ለጳውሎስ አስፈላጊ
ሰው ቢሆንም ያለ ፊልሞና ፈቃድ ለራሱ ሊያስቀረው
ስላልፈለገና በሁለቱ መካከል የይቅርታ መንፈስ
እንዲሰፍን ስለፈለገ ወደ ፊልሞና ይልከዋል፡፡
እንዲያውም ፊልሞና አናሲሞስን እንደ ወንድሙ
እንዲቀበለው ይማጸነዋል፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን
የተደበለውንም ሁሉ በእርሱ ላይ እንዲቆጥርበት
ይጠይቀዋል፡፡ እንግዲህ ከዚህ የምናየው
እርቅና ሰላም በሌለበት ሥፍራ ሁሉ ጭንቀትና
መረበሽ እንዲሁም አለመረጋጋት መኖሩን ነው፡፡
ስለዚህ ነው ሐዋሪያው እባክህ ልቤን አሳርፍልኝ
የሚለው! ይህ
የጌታ አገልጋይ ባደረጋቸው ሥራዎች ሁሉ
የቅዱሳንን ልብ በማሳረፍ የሚታወቅ ቢሆንም
አሁን ደግሞ ለአናሲሞስ ይቅርታ በማድረግ
የበለጠ የጳውሎስን ልብና የሌሎችን ልብ
እንዲያሳርፍ ይጠይቀዋል፡፡ ይቅርታ ሲደረግ
የቅዱሳን ልብ ያርፋል ማለት ነው፡፡ ሁለት
የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሲጨቃጨቁና ሲቃረኑ
እንቅልፉን የሚያጣው ምዕመኑ ነው፡፡ ሁለት
መጋቢዎች ባለመግባባት እርስ በእርሳቸው
ሲገፋፉ የሚያዝነውና የሚረበሸው ጉባኤው
ነው፡፡ መሪዎች እርስ በእርሳቸው የሰላምና
የፍቅርን አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት
በምዕመናን መካከል ያለው ደስታና ፍንደቃ
ትልቅ ይሆናል፡፡
የብሉይ
ኪዳን መጸሕፍትን በምንመለከትበት ወቅት
የእሥራኤል ሕዝብ ለጦርነት ከተጋለጠባቸው
ምክንያች አንዱ የመሪዎች ሁኔታ ነው፡፡
በአንጸሩ ደግሞ አገርን ከሚመሩ ነገሥታት
የተነሳ ምድርት አርፋ እንደምትቀመጥ የእግዚአብሔር
ቃል ይናገራል፡፡ በእርሱ ጊዜ ምድሪቱ በሰላም
አርፋ ተቀመጠች ይላል(2ኛ ዜና 15 11-15፣19፣20፡30)፡፡ እንደዚሁም ሁሉ
በቤተ ክርስቲያንም የሚያገልግሉ መሪዎች
እርስ በርሳቸው በፍቅር ሲቀባበሉና ሲዋደዱ
በመላ ቤተ ክርስቲያን የሚታየው ደስታ
እጅግ የላቀ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ
ፊልሞናን ልቤን አሳርፍልኝ ማለትም
ይቅርታ በማድረግ ልብ የሚሳርፍ ሥራህን ቀጥል
ማለቱ ነው፡፡
ዛሬም
በእኛ ዘመን የሚያስፈልገን የአገልግሎት ብዛት
አይደለም፡፡ ብዙ መስበክም አይደለም፡፡ ነገር
ግን የቅዱሳንን ሁሉ ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ
ሆነን መገኘት ነው፡፡ እኛ ይቅርታን የማይቀበል
በቀለኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ያደግን ሰዎች
ነን፡፡ አብዛኛው ባህላችን ቁጣና በቀል የተሞላ
ነው፡፡ ብድር በምድር የሚለው አስተሳሰብ
አብሮት ከማደጉ የተነሳ ትውልዳችን ይቅርታን
መጠየቅን እንደ ሽንፈት፣ ይቅርታን ማድረግን
እንደ ሞኝነት የሚቆጥር ትውልድ ነው፡፡ ይህ
አስተሳሰብ አብሮን ሳላደገ ጌታን ተቀብለን
አገልጋዮችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሆንንም
በኃላ እንኳ ያ አብሮን ያደገው ልማዳችን
ከውስጣችን አልወጣ ብሎ ጊዜ ይወስድብናል፡፡
ስለዚህ ብዙዎቻችን በእግዚአብሔር ቤት
እንበቃቀላለን፣ አንዳችን ሌሎችን
እናሳድዳለን፡፡በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች
እናገለግላለን፣ ግን በእግዚአብሔር መድረክ
ላይ እያለንም በቀለኝነት ያጠቃናል፡፡ ይህ
ከመሆኑ የተነሳ የእግዚአብሄርም ልብ አልተደሰተም
የቅዱሳንም ልብ አላረፈም፡፡ ዛሬም ቢሆን
እያንዳንዳችን ቆም ብለን እኛ የእግዚአብሔርን
ሕዝብ እያሳረፍን ነው ወይስ እያሳዘንን;
እያራወጥነው
ወይስ እያረጋጋነው፣ እያጽናናነው ወይስ
እያስጨነቅነው ነው የሚለውን ጠይቀን መልስ
ማግኘት ይኖርብናል፡፡ የእግዚብሄርን ቃል
በማስተማርና የተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጻፍ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ዘንድ
ትልቅ አክብሮት ያላቸው ዶር ጆን ማካርተር
ይቅርታ አለማድረግ እንዴት ያለ ክፉ ነገር
እንደሆነ እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡
·
ይቅርታን
አለማድረግ ባለፈው የመራርነት ሕይወት እሥረኞች እንድንሆን የሚያደርገን ነው፡፡
·
ይቅርታን
አለማድረግ ለሰይጣን አሠራር የተከፈተ በር
የሚሰጥ ሲሆን እኛም አጋንንትን በዚያው እንኳን
ደህና መጣህ እያልነው ነው፡፡
·
ይቅርታ
አለማድረግ በእኛና በእግዚአብሔር መካካልላለን
ሕብረት እንቅፋት ነው፡፡ ምከንያቱም ጌታ
ኢየሱስ ሲያስተምር ለሰዎች ኃጢአታቸውን
ይቅር ባትሉ የሰማዩ አባታችሁ ኃጢአታችሁን
ይቅር አይላችሁም፡፡
ለሰዎች
ኃጢአታቸውን ይቅር ካላልን ደስታችንና ሰላማችን
ይወሰድብናል፡፡ ጳውሎስ በፊልሞናና በአናሲሞስ
መካከል ሆኖ ሁለቱን የሚሸመግላቸው ይመስላል፡፡
አናሲሞስ ፊልሞናን በጣም አድርጎ በድሎታል፡፡
ጳውሎስና ፊልሞና በነበሩበት ዘመን አናሲሞስ
ያደረገውን ዓይነት በደል የፈጸመ በባህላቸው
መሠረት ይወገዛል ፣ ይሰደዳል
እንዲያውም ይገደላልም፡፡ አናሲሞስ የፈጸመው
ወንጀል በማንኛውም ማኅበራዊ ና ሕዝባዊ ጉዳዮች
ሥፍራ እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው፡፡ምክንያቱም
አናሲሞስ ለፊልሞና ባሪያው ሆኖ እያለ ያንን
በአሠሪዎች ዘንድ ከባድ ወንጀል ሆኖ የሚታወቀውን ጥፋት ሠራ፡፡ ምናልባት አናሲሞስ ከአካባቢው
የሸሸው የሚደርስበትን መከራ ፈርቶም ሊሆን
ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ ግን ይህንን
በደለኛውን ሰው እንደወንድምህ ቁጠረው ይላል፡፡
ይህ ቀላል ሊሆን የማይችበት ምክንየት አለ፡፡
አንደኛ ባሪያና ጌታ ሁለቱ እኩል በማዕድ
መቀመጥ የሚችሉበት ባህላዊ አግባብ በጊዜው
አልነበረም፡፡ ዘራፊና ቀመኛ ምንም ቢሆን
ከተቀማው ሰው ጋር ሕብረት እንዲያደርግና
ከዚያም አልፎ እንደ ወንድም ሊቀበል የሚችል
ሥርዓትም ሆነ ልማድ አልነበረም፡፡ የእግዚአብሔር
ህግ ግን ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ እንደ ወንድምህ
ቁጠረው ፣ ባሪያ ከነበረበት እንደ ወንድምህ
አድርገው የሚል ነው፡፡ ጥፋት አድርሶ የኮበለለውን
የጠገበ ሠራተኛ ወደ ሥራው እንዲመለስ
አሠሪውን እንማፀነው ይሆናል ፣ ወንድም
አድርገው ማለት ግን ምንም የማይታሰብ
ነው፣ ማለት የሚፈልግም ካለ ደግሞ ሆን ብሎ
ሽምግልናውን ለማደፍረስ እንዳሰበ ሰው ሊፈረጅበት ሁላ ይችላል፡፡ ጳውሎስ ለፍልሞና
የሚናገረው መልእክት ግን ወደ ሥራው እንዲመላስ
ከሚለው የዘለለና እንደ ወንድም ቁጠረው የሚለው
ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ክርስትና ሲገባን
ብቻ ነው፡፡ ስለ ይቅርታ ሰብከው ሲመለሱ
ወንድማቸውን ይቅር አልልም ብለው ሳምንት
ሙሉ ሽማግሌ የሚያመላልሱ አገልጋዮች ብዙ
ናቸው፡፡ እነዚህ ስብከት ችለዋል እንጂ
ክርሰትናው ገና አልገባቸውም
አሊያም
ክርስትና የሚያሰከፍለውን ዋጋ ገና አላወቁትም፡፡
ምክንያቱም ክርስትና የዘረፈህን
ጥጋበኛና ጎረምሳ አገልጋይን ወደ አንተ
ሲመጣ እንደ ወንድምህ አድርገው እንጂ እንደ
ሠራተኛህ አትየው የሚል ነው፡፡
ጳውሎስ
ስለ ፊልሞና የተረዳው ሁሉ አዎንታዊ ነው፡፡
የሚያርምበት አንድም ነገር እስከማይኖርበት
ድረስ ሕይወቱ የተመሰከረለት ሰው ነው፡፡ ምን
አይነት ማራኪ ሕይወትና የተመረቀ ባሕሪይ ነው!
አሁን
ግን ለአናሲሞስ ይቅርታ በማድረግ የበለጠ
ይመሰገናል፣ ክርሰቲያናዊ ጀግና ይባላል ወይም
ብዙ የሆነው መልካም ነገሩ በአንድ ነገር
ምክንያት
ብቻ ዋጋው ሊረክስበት ይችላል፣ ያውም ይቅርታ
በማድረግ ወይም ባለማድረግ፡፡ ብዙ የመድረክ
ጀግኖች ተፈትነው ጊዜ ሳይወስድባቸው ክብደታቸው ሲቀልል ታይተዋል፡፡
እኔ እኮ ጌታን ካገኘውና በመንፈስ ቅዱስ
ከተሞላው ይህን ያህል ዓመት ሆኖኛል፣ እነ
እገሌም በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉት እኔ እጅ
ጭኜ ስጸልይ ነው ብለው የሰውን ሁሉ እትኩሮት
ሲሲቡ የኖሩ ቱባዎቻችን ክርስትናቸው ከወጣበት
በአንዴ ሲወርድ ያየነው ለባልንጀራቸው ይቅርታ
እንዲያደርጉ ሲጠየቁ ያዙኝ ለቀቁኝ ሲሉ
ያየን ቀን ነው፡፡ ስለዚህ የዛሬ አገልጋዮችና ምዕመናንም ብንሆን ጳውሎስ እኛንም ጭምር ነው እየተናገረን ያለው፡፡ ምን ያህል ወንድሜን ይቅር ብየዋለሁ? ምን ያህልስ በይቅርታ ልብ እመላለሳለሁ ወይስ በቀለኛ ነኝ? ከዚህ የተነሳ ጌታ በዙሪያዬ ያስቀመጣቸው ቅዱሳን ልባቸው በእኔ ሥራና አገልግሎት አርፏል ወይስ እኔ እንዴት ነኝ? ብለን ለራሳችንም መልስ መስጠት ይኖርብናል፡፡ሰውን ከልቡ ይቅር የሚልና በደልን የማይቆጥር የክርስትና ሕይወት የገባውና በእርግጥ የተለወጠ አማኝ ነው፡፡ ይህ ማንነት እንዲኖረን ያስፈልገናል፡፡
2.
የቅዱሳንን
ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ስለ ሰዎች
ሕይወት የሚጨነቅ ነው(
ቁ.4)፡፡
ከፊልሞና
ሕይወት የምንማረው እርሱ ለሰዎች ግድ የሚለውና
ለእነርሱ የሚጨነቅ ማንነት ያለው መሆኑ ነው፡፡
በቅዱሳን ሁሉ ዘንድ ፍቅር ያለው ሰው ነበር፡፡
እርሱ ከተወሰኑ
ሰዎች ጋር በፍቅር የተሳሰረ ፣ ከተቀሩት ጋር
ደግሞ አኩራፊ ዓይነት ሰው አልነበረም፣
ይልቁንስ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር በፍቅር የሚኖር
ሰው ነው፡፡ ይህ ፍቅር ደግሞ ለሰዎች ሁሉ
ሸክም እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ ጳውሎስ
ያደረገውን ደግሞ ሲናይ ለፍልሞና ፍቅር
እንዳለው ያሳየናል(
ከቁ.11-14)፡፡
አናሲሞስ ከፊልሞና ይልቅ የሚያስፈልገው
በእሥር ቤት ላለው ለጳውሎስ
ነው፡፡ ጳውሎስም አናሲሞስን ከእራሱ ጋር
ቢያቆየው የማይወቀስበት ብዙ ምክንያቶች
አሉ፡፡ አንደኛው፣ አናሲሞስ ገና ጌታን ሳያገኝ
ከፊልሞና ኮብልሎ ሄዷል፡፡ ሁለተኛ ወንጌል
መስክሮ እንዲለወጥ ምክንያት ስለሆነው
አሁን የወንጌል ልጁ ሆኖታል፡፡ ስለዚህ
ቢያስቀረው
ፊልሞናም ቢሆን ቅር ሊሰኝበት አይችልም፡፡
ይሁን እንጂ
ጳውሎስ ከራሱ ጥቅም ይልቅ የፍልሞናን
በመስቀደም አናሲሞስን ወደ ፊልሞና ሲልከው
እንመለከታለን፡፡ ከእኔ ይልቅ የአንተ ይሻላል
የሚል አቅም ያለው ክርስትና ያለው ሰው ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት የቅዱሳንን ልብ
የሚሳርፍ ነው፡፡ እግዚአብሔርም
ደስ የሚሰኝበት በእንዲህ
ዓይነቱ ሕይወት
ነው፡፡
3. የቅዱሳንን
ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ስለ እግዚአብሔር
የሚያስብ ነው(ቁ
4-5)፡፡
የእግዚአብሔር
ክብርና ከእርሱ ጋር ያለን ሕብረት ግድ የሚለን
ስንሆን የቅዱሳን ልብ ያርፋል፡፡ ጳውሎስ
በዚህ ክፍል ስለ ፍልሞና እምነት ሰምቶ
እግዚእብሔርን ያመሰግናል፡፡ እምነት እኛን
ከእግዚአብሔር ጋር ያገናኘናል፡፡ ፍቅር
ደግሞ ከሰዎች ጋር ያገናኘናል፡፡ እምነት
ግን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ያንን መሰጠት፣
በርሱ ያለንን መተማመን እንዲሁም በጌታችን
በፍጹም ማረፋችንን የሚያመለክት ነው፡፡
ፈልምና እውነተኛ የሆነ እምነት የነበርው
ሰው ነው፡፡ በእውነትም የተመሰከረለት አማኝ ነው፡፡ ስለዚህ ይቅርታ ማድረግ
አይከብደውም፡፡ ሰዎች ከወንድሞቻቸው ጋር
ያላቸውን ነገር የሚያበላሹት ከእግዚአብሔር
ጋራ ያላቸው ነገር መበላሸት ሲጀምር ነው፡፡
ብዙዎች ከእግዚአብሔርና ከወንድሞቻቸው ጋር
ካላቸው ህብረት ይልቅ ለመድረካቸውና ለአገልጋይነት
ስማቸው ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ በአንድ
ወቅት የንስሐና የእርቅ ጥሪ እየተደረገ
ሰዎች በመካከላቸው ያለውን ቁርሾ
እንዲስያወግዱ ይጋበዙ እንደነበር የሚታወስ
ነው፡፡ ይህ በአዲስ አባባ ከተማ በሁሉም ዞኖች
እየተደረገ ባለበት ወቅት እኔም በአንድ ቤ/ክ
መልእክት እንዳቀርብ ስለተመደብኩ ጌታ የሰጠኝን
ቃል ሳካፍል መንፈስ ቅዱስ በጉባኤው መካከል
የሚያስገርም መነቀቃት ሲያደርግ ስላየሁ
ከሁለት ቀን በኋላ ይህንን መልእክት በሌላ
ቦታ ለመስበክ ሄድኩ፡፡ ቦታው ከአዲስ አባባ
400 ኪሎ
ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ጉባኤው በጣም
ትልቅ በመሆኑ ጸሎት ቤቱ ስላልቻለ ፕሮግርሙ
የተካሄደው በሜዳ ላይ ነበር፡፡ በዚያ ኮንፍራንስ
መልእክት ካቀረብኩ በኋላ የንሰሐ ጥሪ ሳቀርብ
አንድ ወጣት ሚስቱን እንደበደላትና ይቅርታ
ሊጠይቃት እንደሚፈልግ ተናገረ፡፡ ስለዚህ
ከፕሮግራሙ መልስ ከቤተ ክርስቲያን መጋቢ
ጋር በመሆን ሚስቱን አስጠራናትና ይቅርታ
እንድታደርግለት ስንጠይቃት አባቴ ይህንን ጉዳይ መስማት አለበት አለች፡፡ አባቷ የቤተ ክርስቲያን
ሽማግሌ ስለሆነ ከሰዎች ጋር የነገውን ፕሮግራም
በሚመለከት አንዳንድ ሥራዎችን እየሠራ ካለበት
አስጠራነውና ጉዳዩን ሁሉ አጫወትነው፡፡
ልጅቷ ይቅርታ አድርጋ ወደ ትዳሯ የመመለስ
ልብ ቢኖረትም የአባቷ አቋም ግን ከጠበቅነው
በላይ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ ልጅቱ ከባሏ
ጋር በተፈጠረው ጊዜያዊ አለመግባባት ምክንያት ካለችበት ትዳር ወጥታ ወደ አባቷ ቤት መጥታ
እዛው ናት፡፡ ጉዳዩን ለማስተካካል በጣም
ሰፊ ጊዜ ወሰደብን፡፡ ልጁን የበደለውን ሰው
ይቅር እንዲል ደጋግመን ብንለምነውና ብማጸነው
አባትዬው በጭራሽ እምቢ አለ፡፡ በመጨረሻም
ላይ እንዲህ ዓይነት ክርስቲና ይዘህ የቤተ
ክርስቲያን ሽማግሌ ልትሆን
ስለማትችል አግደንሃል ሲሉት እንደዚህ ከሆነ
እሺ እንዳላችሁት ይሁን አለ፡፡ ወጣቱ ባለትዳር
ሚስቱን ይዞ ቤቱ ቢገባም ይህ ሽማግሌ ስለ
ክርስቲናውና እግዚአብሔር ስለሚጠብቅበት
ኑሮ ሳይሆን የተጨነቀው ስለ ሽምግልናው መሆኑ
የሁላቸንንም ልብ እንዳሳዘነ አስታውሳሁ፡፡
ዛሬም
በእኛ ዘመን ስለ ስማቸውና ስለ መድረካቸው
እንዲሁም በሰው ፊት ስለሚታየው አገልግሎታቸው
እንጂ ስለማይታየው መንፈሳዊ ሕይወታቸውና
የጌታ መንፈስ ከእነርሱ ስለሚፈልግባቸው ነገር ግድ የማይላቸው ብዙ አገልጋዮችና
መሪዎች ይኖራሉ፡፡ ፊልሞና ግን እንዲህ
ዓይነት ሰው አይደለም፡፡ የሰሙትን ሁሉ
የሚያስመሰግን እምነት ያለው ሰው ነው፡፡
ስለ እምነቱና ከእግዚአብሔር ጋር ስላው ሕብረት
ግድ የሚለው ሰው ካሉት መለያዎች አንዱ
ወንድሙን የሰዎችን ልብ ማሳረፉ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት እግዚአብሔርን
ያስደስዋል ፣ የቅዱሳንንም ልብ ያሳርፋል፡፡
4. የቅዱሳንን
ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ስለ እውነተኛ ሕብረት
የሚያሳስበው ነው፡(
6)፡፡
በጌታ
ያለን አማኞች ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር
እውነተኛ እምነትን የቅዱሳን ሕብረት እንደሚከተለው
ነው፡፡ አንድነት፣የወንድማዊ ፍቅርና ሰላም
የክርስትያንነታችን ምልክትና የሕይወታችን
ክፍል ነው፡፡ ከሌሎች ጋር በምናሳልፍበት
ወቅት ከሌሎች እንማራለን፣ እንታነጽባቸዋለንም፡፡
ወደ ቤተ ክርስቲያን የምንሄደው ስብከት
ሰምተንና ተነቃቅትን ለመመለስ ብቻ ከሆነ ያ
ሁኔታ እኛን ራስ ወዳዶች ያደርገናል፡፡
ይልቁንም ወደ ቅዱሳን ሕብረት የምንሄደው ለሌሎች በረከት ለመሆን፣ ከእነርሱም
ጋር ለመተያየትና እርስ በእርሳችንም ለመልካም
ሥራ እንድንነቃቃመም ጭምር ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር
ቤት የምንሄደው ለጋራ በረከት ነው፡፡
የወንድማችንን ሐዘን ሀዘናችን ደስታውንም
ደስታችን ልናደርግ ነው ፡፡ የእኛንም ሸክም
እነርሱ እንዲጋሩ ለማድረግ ጭምር እንጂ
ተሰብከን፣ ወይም ሰብከን ወይም ዘምረን ወይም
ለራሳችን በረከቱን አፍሰን ልንመጣ ብቻ
አይደለም፡፡ ቅዱሳንም ልብ
የሚያርፈው ይህ ሲሆን ነው፡፡
5. የቅዱሳን
ልብ የሚያርፍበት አገልጋይ ስለ መንፈሳዊ
እውቀት የሚያሳስበው ነው(
ቁ6)፡፡
እውቀት ስንል ተራ መረጃ ሳይሆን ስለ እግዚአብሔር
ያለን ጥልቅ መረዳት ማለታችን ነው፡፡ የእግዚአብሔርን
ነገር በጽንሰ አሳብ ደረጃ ማወቅናTheoritical
kbowledge በሕይወት
ልምምድ ውስጥ ገብተን ማወቅ /exprencial
knowledge/ ሁለት
የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ፅንሰ አሳብ በሆነው
እውቀት ወደ ንስሐ አምልኮ፣ እንዲሁም ወደ
ይቅርታ ሕይወት መድረስ አይቻልም፡፡ በአገራችን
ሳለሁ በአውሮጳና በአሜሪካ እንዲሁም በሌሎች
የምዕራብ አገሮች በየክረምቱ ስለሚወርደው
በረዶ ከሚሰማው ነገር ተነስቼ ለሌሎችም ሰዎች
አስረዳቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የተቆረቆሩ
የፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ ክርስቲያን ሕንጸዎች
ጣሪያቸው ከመሀል ከፍ ያለና ዳርና ዳሩ ዝቅ
ያለ ሲሆን ይህ አሠራር ምዕራባውያን በረዶው
ሲወርድ ጣሪያው ላይ ሆኖ እንዳይጎዳው
እየተንሸራተተ እንዲወርድ አድርገወው
ስለሚሠሩት ሚሲዮናውያኑ ወደ አገራችን ሲመጡ
ያንን የለመዱትን ዓይነት ቤት ስለሚሠሩ ነው
የጸሎት ቤቶቸችን ሕንጻዎች ከሌላው የተለዩ
የሚሆኑት ሲባል ስለ ሰማሁ እኔም ለብዙዎች
የሰማሁትን ያንኑን አስረዳ ነበር፡፡ ነገር
ግን ያንን ሁሉ የማስረዳው በረዶውን በዓይኔ
እንኳን ሳላየው ነበር፡፡ ከብዙ ጊዜያት በኋላ
ወደ ሚቺጋን መጥቼ በረዶ ሲወርድ፣ ከተማውን
ሁሉ ሲሸፍን፣ መንገዱን ሁሉ ሲዘጋ በቤቶች
ሁሉ ጣሪያ ላይ ተከምሮ ከዚያ እየተንሸራተተ
ሲወድቅ፣ በጎዳናዎች ሁሉ ተከምሮ ለመንዳት
ሲያስቸግርና እያንዳንዱ የሚቺጋን ነዋሪ
በወፋፈፍራም
ልብሶች ተጀቡኖ ሲሄድ ሳይ ለበረዶ ያለኝ
እውቀት የተለየ ሆነ፡፡ እንዲያውም እኔ በበረዶ
ላይ ሲነዳና መኪናዬ መንገድ ስታ የወጣችበትን
አጋጣሚ ሁሉ ሳስበው ሰው በመረጃ ብቻ የሚያውቀው
እውቀት በሕይወት ልምድ ከሚያውቀው ምን ያህል
የተለየ እንደሆነ በበለጠ
ተገነዘብኩ፡፡ ጳውሎስም ይህ የሕይወት ልምድ
እውቀት እንዲበዛለት ለፍልሞና
እንደሚጸልይለት ቃል ይገባለታል፡፡ ይህ
ጥልቅ እውቀትና መረዳት አፓጎኒሲስ ተብሎ
የሚጠራ ሲሆን ስለ እግዚአብሔርና
በእኛ ውስጥ ስላለው መንፈሳዊ ነገር ጥልቅ
የሆነ መረዳት a deep
understanding about God and about what in us/ ማለታችን
ነው፡፡ በእኛ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀመጠው
በጣም ብዙ የሆነ መልካም
ነገር አለ፡፡ ጌታ ኢየሱስን ካመንንበት ጊዜ
ጀምሮ ከእርሱ በጣም ብዙ መንፈሳዊ ስጦታዎችን
ተቀብለናል፡፡ ይህንን እግዚአብሔርን አውቆ
መከተልና አውቆም ማገልገል ሕይወታችንን
ያሳድገዋል፤ በእግዚአብሔርም ላይ ያለን
መተማመን ይጨምራል፡፡ በእኛ ዘንድ ያለውን ሁሉ
በማወቅ የሚለው አሳብ ልዩ
ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ እግዚአብሔር በእኛ
ብዙ መልካም ነገሮችን አስቀምጧል፡፡ ከጌታ
ያገናቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች
ክርስቶስን ወደ ማወቅ
እንድንደርስ የሚያደርጉን ናቸው፡፡ ስለዚህ
የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ በክርስቶስ
ስላው እውቀት ግድ የሚለው ነው፡፡
6.
የቅዱሳንን
ልብ የሚያሳርፍ አገልጋይ ለክርስቶስ ክብር
ግድ የሚለው ነው(ቁ.6)፡፡
ፍልሞና
ሁሉንም ነገር ያደረገው ለክርስቶስ ነው፡፡
መንፈሳዊ ፍሬንም የሚያፈራው ለክርስቶስ
ነው፡፡ ጳውሎስ በአንተ ያለው ነገር ለክርስቶስ
ፍሬን እንዲያፈራ እለምናለሁ በማለት ለፍልሞና
የሚጸልየውን የጸሎት ይዘት ይገጻል፡፡
በአገልግሎታችን ፍሬን ብናፈራ ያ ፍሬ ክርስቶስን
ለማክበር መሆን አለበት፡፡ ሰዎችንም
በአገልግሎታችን የምናዘጋጀው ለክርስቶስ
ነው፡፡ ክርስቶስ በእኛ ሕይወትና ኑሮ በሚከብርብት
ወቅት የምናገልግላቸውና አብረውን ጌታን
የሚያመልኩ ሰዎች ልባቸው ያረፈ ይሆናሉ፡፡
ስለዚህ
ጳውሎስ ይህንን
አንቀጽ ሲደመድም ልቤን አሳርፍልኝ ይላል፡፡
ዛሬም ሰዎች ተጨንቀዋል፣
ፈርተዋል፣ተረብሸዋል፣ ግራም ተጋብቷል፣ምእናንም
በአገልጋችና በመሪዎች መካከል ካለው አላስፈላጊ
ሽኩቻ የተነሳ ተንገላትተዋል፣ከቦታ ወደ ቦታ
ተንከራተዋል፣ ከአንዱ አበባ ተነስታ በሌላው
ላይ እንደምትቀመጥ ከዚያም ተነስታ ወደሌላው
አበባ እንደምትበር ንብ ተጉላልተዋል ፡፡
በመንፈሳዊ
ሕይወታቸው መጠንከር አልቻሉም፡፡ አማኞች
ሥር መስደድ ሲጀምሩ መሪዎችና መድረክ ናፋቂ
ሰባኪዎች ካሉበት ሥፍራ ያፈናቅሉአቸዋል፡፡
ከዚህም የተነሳ በመንፈሳዊ ሕይወት መጭብርብር
ውስጥ ገብተዋል ፣አያሌዎችም ለአውሬ ተጋልጠዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ አገልጋዮች
ስለ እነርሱ ግድ አላለንም፡፡ ስለዚህ
ቆም ብለን በማሰብ
የምዕመናኖቻችን ልብ ልናሳርፍ ይገባናል፡፡
ጳውሎስ ለፍልሞና የሚልከው ይህ መልእክት
ለአገልጋዮች ሁሉል ማነንቂያ ደወል ነው ብዬ
አምናለሁ፡፡ የቅዱሳንን ልብ የሚያሳርፈውን
ማንነት እግዚአብሔር ይስጠን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment