Wednesday, July 18, 2018

እኛ ስንደመር ፍትሕ ይጨምር




ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር ዶር አቢይ አህመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በአገራችን እየታየ ያለው  ፈጣን ለውጥ የሚያስገርም፣ የሚያስደምምና ለማመን ሁሉ የሚያስቸግር ሆኗል፡፡ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ዲሞክራሲን ፣ ይቅርታንና መደመርን በመስበክ ከአገር አልፎ የጎረቤት አገሮችንም ትኩረት የሳበው መሪያችን በዚህ ፕላኔት ላይ የዚህ ትውልድ የመጀመሪያው ሰው ናቸው ብል እንደሚበዛባቸው አላስብም፡፡ በአሳቤ ከዚህም ያለፈ አድናቆት  ልቸራቸው ብከጅልም አድናቆትም ከልኩ ካለፈ አምልኮት ይሆናል ብሎ ልቤ ስለነገረኝ ገታ አደረግኩት እንጂ የምለው ብዙ ነገር ነበረኝ፡፡ ሰውን ማክበር፣ የሚገባውን አድናቆት መስጠትና በጸሎትም መደገፍ  በጎ ነው፣ ያማረም የተወደደም ነው፡፡
ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን 27 ዓመት ሙሉ ሲፈርስና ሲፈራርስ የኖረውን አገር በ3 ወራት ውስጥ መልሶ ለማቆም በሄዱባቸውም መንገዶች ሁሉ ስኬትን በማግኘታቸው ከሠፈር እስከ አገር፣ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ሁሉ ከአፉ የማያወርዳቸው፣ በለበሰው ጨርቅም የሳላቸው ሰው መሆናቸውን ሳይ በአንድ በኩል በደስታ እየቧረቅኩ በሌላ በኩል ደግሞ ከሰው የተወለዱ ሥጋ ለባሽ ሰው እንጂ መልአክ አለመሆናቸውን እንዳልረሳ ልቤ ስለወተወተኝ በሁለቱ መካከል ታመምኩ እላችኋለሁ፡፡
እኛ የምናውቀው እስከአሁን ድረስ የነበሩ የቀደሞዎቹ የአገራችን መሪዎች የስላም ኃይል ፖሊስና የጠብ መንጃ አፈሙዝ  መሆኑን ያምኑ እንደነበር ነው እንጂ ፍቅር የሚለው ቃል ከመሪ አፍ ወጥቶ ሲሰበክ የሰማነው በዘመነ አቢይ ነው፡፡ እነዚያዎቹ ስለአገሩ እንኳን ሲናገሩ " ለአገሬ እሞታለሁ፣ እንሙትላት" እንጂ እንውደዳት፣ እርስ በርሳችንም እንዋደድ የሚል አሳብ እንደ ኃጢአት ወይም እንደ ሽንፈት ወስደውት ሲመሩን እዚህ ላይ ደርሰናል፡፡ እንዲያው የጠብመንጃ አፈሙዝ እንጂ ፍቅር የሚባል አያውቁም ነበር፡፡ ለአፈሙዛቸውም የሰጡት የቁልምጫ ስም " ፍቱን መድኃኒት" የሚለው ነው፡፡ መቼም ሰው እግዚአብሔር የወሰነለትን ዘመን ሲጨርስ ወደ ዘላለሙ ቤት ይሄዳል፡፡ የአንዳንዶቹ መሄድ ለአገር ጉዳት ሲሆን የአንዳንዶቹ መሄድ ደግሞ ለህዝብ እፎይታና ግልግል የመሆኑ ነገር ልባችን የሚያውቀው ሆኖ የቀድሞው የሕወሓት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሲያስፈራሩ " ፍቱን መድሓኒት ተዘጋጅቷል" ይሉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ፍቱኑ መድኃኒት ለእርሳቸውም የማይሆንበት ዘመን መጥቶ አየነው፡፡ ቅዱስ ቃሉ " ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንምና" እንዳለው ሆነ ነገሩ፡፡ እግዚአብሔር እድሜአቸውን ያርዝመውና ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶር አቢይ አህመድ ሕዝብን የሚያቃልሉበትና የሚንቁበት እንደዚያ ያለ ንግግር በአፋቸው የለም፡፡  ንግግራቸውም ሕልማቸውም  ከነዚያዎቹ ይለያል፡፡ ይቅርታና ፍቅር ነው ዜማቸው፡፡  ሰውዬ ካህን እንጂ የፖለቲካ መሪም አይመስሉም፡፡ በእውነት!

ሰላም ፣ ፍቅር ፣ ይቅርታ መደመር ፣ አንድነት የሚሉ  የዶር አቢይ መርሆዎችና ንግግሮች አንጀቴን ሲያርሱት በመሳጭና ጥዑም አንደበታቸው ብሎም በሚወስዷቸው ፈጣን እርምጃዎች ሁሉ ውስጥ  "ፍትሕ" የምትለዋን ቃል ፈልጌ ፣ ፈልጌ እንደምፈልጋት ያህል  አለማግኘቴ አየር ላይ የተንሳፈፈው ሞራሌ በመጠኑም ቢሆን ዝቅ ሊል ታገለኝ፡፡ ይህ ስሜት የሚፈጠርባቸው ሌሎችም ይኖሩ እንደሆነ ገና አላወቅሁም፡፡ ዶር አብይ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ባሰናዱት የቡፌ ግብዣ ፍቅር ፣ ሰላም፣ ይቅርታ፣ መደመር፣ወዘተ የሚሉ በየዓይነቱ በርክተው ቢቀርቡም "ፍትሕ " የምትባለዋ ቃል ከተግባር ጋር ባለመታየቷ በተሟላ ድግስ ውስጥ አንድ ወሳኝ ነገር እንደተረሳ ያህል ተሰምቶኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት እጅ ለእጅ፣ እግርም ለእግር፣ ወይም ዓይን ለዐይን፣ ጥርስም ለጥርስ እንዲከፈል፣ የእሥረኛውን ሁለት እግር የቆረጠ እንደዚያው ይደረግበት፣ ባይሆን አንደኛውም ቢሆን ብቻ ይቆረጥበት ካልሆነም ዕድሜ ልክ እሥራት ይወሰንበት፣ ብልት ያኮላሸም ብልቱ ይኮላሽ፣ የእጅና የእግር ጣቶችን ጥፍር የነቀለም ጥፍሩ ይነቀል ወዘተ የሚል ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ብቀላ Talionic Justice ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በአማሪኛ አቻ ቃሉ ምን እንደሆነ ገና አልደረስኩበትምና ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡
ይሁንና በዜጎች ላይ ያንን የመሰለ ዘግናኝ ወንጀል የፈጸሙ ወይም ያስፈጸሙ አካላት ታውቀው የኢትዮጵያን ሕዝብ ግልጽ ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ያለዚያ የተያዘው መደመር ፍትሕ የጎደለበትን በደልም የደረሰበትን  ዜጋ የሚያገልል ይሆናልና፡፡ የአገርንም ሀብት የዘረፈ፣ቢያንስ መስረቁንና አገሪቱ አጥንት እስክቀራት ድረስ  የጋጠው  የምድሩን ሕዝብ ይቅርታንና ምሕረት መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
በቅርቡ በደቡብ ክልል በወላይታ ተወላጆች ላይ የተሰነዘረ ዘርንና ብሔርን ኢላማ ያደረገውን ግዲያና ጭፍጨፋ ያየው ሰብዓዊ  ማንነትና  የሰው ሕሊና ያለው ሁሉ ተጸይፎታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ የወላይታ ብሔር ተወላጆች በሜዳ ላይ ተበትነው ይገኛሉ፡፡ ዕድሜአቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ፣የሚያጠቡ እናቶች ፣ነፍሰ ጡራን፣ አዛውንቶችና አረጋውያን ከመኖሪያ ሥፍራቸው ተፈናቅለው መግቢያ ስላጡ በሜዳ ላይ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች የመብት ጥያቄ የሚመልስ አካል እስከአሁን አለመገኘቱ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ ወደ ቀድሞው ኑሮአቸው እንደሚመለሱም የተሰጠ ምንም ተስፋ የለም፡፡
መንግሥት ፍቅርን ሲሰብክ ሳለ የወንጌል ሰባኪነት አደራ ከተሰጣቸው የአዳዲስ እምነት እንቅስቃሴ ቤተ እምነቶች አንዳንዶቹ በጭፍጨፋው ጊዜ ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ እነርሱ ለሄዱ ወገኖች በራቸው በመጠርቀም ለገዳዮች ጦርና ለአራጆች ካራ አሳልፈው የመስጠታቸውን ዜና መስማት ይበልጡኑ ልብን የጎዳ ክስተት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መመስገን የሚገባቸውን አመስግነን ብናልፍ የነገራችን ሚዛን ይጠበቃል ብዬ አምናለሁ፡፡ ጭፍጨፋው ሲበረታ ነፍስ የያዛውን ተጠቂዎች እህልና ውሃ ይዘው በማስጠጋት ነፍሳቸውን ያዳኑትን የሐዋሳ አካባቢ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር ይባርክ ካላልን በጎ ሥራን አለማሰብ ይሆናል፡፡  በአካባቢ አቸው ያሉ የሲዳማ ተወላጆችን ሰዎች እንዳያጠቁ በጥብቅ የገሰጹ የወላይታ አገር ሽማግሌዎች በእርጅናቸው ይለምልሙ፡፡ ቤታቸውንም ከፍተው በመስጠት የቻሉትን ያህል ደብቀው ያቆዩልን በሐዋሳ ከተማ ያሉ ጥቂት ሰዎች እግዚአብሔር ብድራታቸውን በመልካም ይመልስላቸው ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሐዋሳ ዙሪያ ከ80 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሜዳ ላይ ናቸው፡፡ ለዘመናት ጥረው ግረው ያገኙት ንብረትና አለን የሚሏቸው ሁሉ በብሔር ተኮር ጥቃት አራማጆች የተባበረ ክንድ  ወድሞባቸው ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል፡፡ ተጠቂዎች እምባ እየረጩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጨምሮ ሌሎች የዘር ማጥፋቱን ዘመቻ የቀሰቀሱትን የመንግሥት ባለሥልጣናትን ባለመሸማቀቅ አጋልጠዋል፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ተጠያቂነትን እንዲወስዱ በመንግሥት ተወካዮች ፊት አቤቱታ ካሰሙ በኋል ያፈሰሱት እምባ እንደ ከንቱ ተቆጥሮ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በሹመት ላይ ሹመት ማግኘታቸው የተጥቂዎችን እና የቤተስቦቻቸውን ልብ ክፉኛ ጎድቶታል፡፡  ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ሕዝብን ያሳረደ  ወንጀለኛ ና ፀረ፟ ሕዝብ አጀንዳ አቀንቃኝ ሹመትና ሽልማት ከተሰጠው የፍትሕ ጥማት የሚያቃጥለው ሕዝባችን እስከ አሁን ከተጎዳው በላይ ጉዳት በጉዳት ይጨመርበታል፡፡ ይህንን ያዩ ተጎጂዎቹና ፍትሕ ናፋቂዎች ሁሉ "መደመር" የሚለው አሳብ ቢተናነቃቸው አንፍረድባቸው፡፡ በሐዋሳና በዙሪያዋ ተበታትነው የመከራን እንጀራ እየበሉና የመከራን ውሃ እየጠጡ ያሉ ሚስኪን ኢትዮጵያውያን የዶር አቢይን የመደመር መርህ እንዴት ይቀበሉታል፣ ከማንስ ጋር ይደመራሉ የሚለው ጥያቄ ከእሳት የጋለ ነው፡፡
መንግሥት በደለኛውን ይጠይቅልን እያሉ በእምባ ለጠየቁበት ምላሹ ለገዳያቸው የላቀ ሹመት ሰጥቶ ማሳየት ቁስላቸው ላይ እንጨት መክተት ሆኖባቸዋል፡፡ ለወደፊቱም በዚያ አካባቢ የመኖር ተስፋቸውን  ጭምር አጨልሞባቸዋል፡፡ ፍቅርና መደምር የሚለው ቃል የአዋሳ ዙሪያውን ጨምሮ፣ በጌዴኦ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ ፣ በአማራና በትግራይ አካባቢ ወዘተ በሕዝብ ደም የሚረኩ ወገኖች በሚቀሰቅሱት የርስ በርስ ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ያለ ፍትሕ ሊገባቸው አይችልም፡፡ ያለ ፍትሕ የፍቅር፣የይቅርታና የመደመር ውበት ለማንም የሚታይበት አግባብ የለም፡፡
ከቡድን አሳልጣኞቹ የተማረውን ዘረኝነትና የጅምላ ጭፍጨፋ ሠርቶና ለፍቶ በሚኖረው ሕዝብ ላይ በመለማመድ ጎዳናውን በዜጎች ደም ያጨቀየ፣ የወገኖቻችንን ሬሳ በእሳት የሚያቃጥሉ አሬመኔያዊ አስተሳሰብ ያላቸውን መልምሎ ያሰማራና ከሰይፉ የተርፉትንም ንብረታቸው እንዲዘረፍና ከቄያቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጋቸው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አገርን ወክሎ አምባሳደር እንዲሆን መሾሙን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ይህ ሰው የቡድን ካቦ ለመሆን የሚያበቃ የሞራል ብቃት እንኳ  የለውም፡፡ የመንግሥትን አሰላለፍ ማበላሸቱ እየታየ በሌሎች እናካክሳለን ካልተባለ በቀር የዜጎችን መብትና ሰብአዊ ማንነታቸውን  በማርከሱ ሂስ ሊወስድ እየተገባው ለኢትዮጵያ እንደራሴ እንዲሆን መሾሙ የኢትዮጵያን ክብር ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ጎማው የሚደመረው መኪናው በወጉ እንዲሽከረከር ስለሆነ የተበላሸው ጎማ በመኪናው ከመደመሩ በፊት ተገቢው ፍተሻና ጥገና ያልተደረገ እንደሆነ በመኪናው መላ ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የመኪናውን ጤና ከሚነሳ ፣ አንዴ ተበላሽቷልና የሚመጥነው ሥራ ሊሰጠው ይገባዋል እንጂ ክብ ቅርጽ ስላለው ብቻ ጎማ ነው ተብሎ በመኪና እንደማይደመር የእኔ ምክር የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡  እውነት ለመናገር  ይህንን አስጽያፊ ድርጊት የፈጸመው የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ አምባሳደርነት ይቅርብና እርሱ በደም የተበከለው እጁን ቢታጠብ፣ በዘረኝነት ሰክሮ በሕዝብ ላይ የሚያፈጥበትን  ዓይኑን ቢሰበስብ፣ የጎረሰውን ሕወሃታዊ መርዝ ቢተፋና ቢጸዳ  ትልቅ ሥራ እንደሠራ ልንቆጥር እንችላለን፡፡ እንደ ሽፈራው ሽጉጤ ያሉት  ዶር አቢይ የሚያራምዱትን በሳል ዴሞክራሲያዊና ሕዝብን ያሳታፈ ፖለቲካ ስለማይመጥኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ራሳቸው ሰውዬን ከላይ አማስለውም ይሁን ከሥር አንድደው ወደ ብስለት ያምጡት እንጂ ሹመት አይስጧቸው፡፡ ያለዚያ እንደ አቶ ሽፈራው ያሉ ሰዎች ጠቅላይ ሚንስትራችንንም ሆነ እኛን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንገት ያስደፉናል፡፡ 
የእነሽፈራው ሽጉጤ ድርጊት የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ሕዝባዊና ኢትዮጵያ፟ መር አመራርን እንዲያጠላሸው አንሻም፡፡ ሌቦችና ዘራፊዎች ፣ ነፍሰ ገዳዮችና ጨፍጫፊዎች በሕግ የሚጠየቁበት አግባብ ችላ ከተባለ ህገ፟ወጥነትና ፍትሕ አልባነት ማንሰራራቱ አይቀርም፡፡ መደመር ፣ ፍቅር፣ ሰላም ፣አንድነትና ይቅርታ በሚለው መርህ ውስጥ " ፍትሕ በተግባር" የሚለው እንዲካተትበትና እንዲያነቡትም አቶ ሽፈራውና ግብረ አባሮቹ ተጽፎእ  ቢሰጣቸው እኛ ፍትሕ የተጠማን ሁላችንም አቢይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እየዋለ ካለው ውለታ ጋር እንደምረዋለን፡፡ እኛ ስንደመር ፍትሕ ይጨምር እንጂ አይረሳ፡፡
በመጨረሻም ፍትሕን የተጠማና ሰባዊነት ያለው ሁሉ ሰለተጎዱ ወኞቻችን ደምፁን እንዲያሰማ አቤት እንላለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሐዋሳ ከተማ ዘጠኝ እናቶች በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ልጅ ወልደው ከነሕጻናቶቻቸው ጋር እዚያው ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ከመቶ የሚበልጡ እናቶችና ሕጻናት  በአንድ ክፍል በጅምላ ታፍነው ይኖራሉ፡፡ ዘመድና ቤተሰብ የሞተባቸው ሰዎች ከወላይታ መጥተው የወገኖቻቸው ሬሳ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ በጅብ ተበልቷል የሚል ምላሽ ተሰጥቶአቸው መመለሳቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አሁን ደግሞ ተፈናቃዮቹ በአስቸኳይ አካባቢውን ለቅቀው እንዲሄዱ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑ ያንን አካባቢ የጥፋት መንደር አድርጎታል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አቢይና የእኤርትራው ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ሐዋሳን ሲጎበኙና ሕዝቡም በደስታ ሲሰክር እነዚህ ተፈናቃዮች ፍትሕ ርቆአቸው በሰቆቃ ውስጥ ነበሩ፡፡  ይህ ሁሉ ሲሆን እውነታው እንዳይታወቅ ምንም ዓይነት የመገናኛ ብዙኃን ግብቶ ሁኔታውን እንዳይዘግብ መንገዶች የተዘጉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  ጉዳዩ የብዙዎችን ልብ የሰበረና የብዙዎችን ድምፅ የሚፈልግ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለእነዚህ ድምፅ አልባ ሰዎች ድምፅ እንዲሆኑላቸው ና ከዚህ የመከራ ሕይወት የሚወጡበት መንገድ እንዲገኝ በያላችሁበት ችጩኼታችሁን እንዲታሰሙ እንማጸናለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ ጠቅላይ ሚኒስትራችንንም ከቀን ጅቦቹ ቀስት ይጠብቅልን፡፡ አሜን
ሳሙኤል ሾንጋ ነኝ
      

Tuesday, July 3, 2018

ሕልም የሚመስሉ እውነቶች


በዓለም ካሉ ጎጂ ፍልስፍናዎች አንዱ በእግዚአብሔር መኖር የማያምን / ኤቲይዝም/ የሚባለው ነው። የዚህ ፍልስፍና አራማጆች በእግዚአብሔር መኖር ባለማመናቸው ሳይገቱ ሌሎችም ፈለጋቸውን እንዲከተሉ ከብረት ጠንክረው መሟገታቸው የፍልስፍናውን ጎጂነት ይበልጥ ያጎላዋል። እንደ እነርሱ ትጋት ቢሆን የአዳም ዘር ሁሉ ፊቱን ከፈጣሪው መልሶ ተስፋ ቢስ ሆኖ በቀረ ነበር። ገና ጨቅላ ወጣት በነበርኩበት ወቅት የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና መዝሙር መዘመር ከልቤ ስወድ ሳለ “እግዚአብሔር የለም” የሚለውን መርዘኛ የክህደት መለከት ሲነፉ የነበሩ ወገኖች እንዴት እንዳስጨነቁን ከቶም አይረሳም። በወቅቱ የኮሚዩኒዝም ፖለቲካ ሥርዓት በየቀበሌው ያለን ለጋ ወጣቶች “ከሁሉ በላይ አብዮቱ” የሚለውን መፈክር እንዲናስተጋባ ያስገድደን ነበር። ጉዳዩ “ከሁሉ በላይ አብዮቱ” በሚለው ሳያበቃ “ከአብዮታችንና ከአንድነታችን በላይ ምንም ኃይል የለም” የሚለው ደግሞ እጅግ የከፋው ነበር። እኔና ሌሎች ጓደኞቼ በዚህኛው መፈክርና አብሮት ተያይዞ በመጡ ጣጣዎች ምክንያት መጐዳት ብቻ ሳይሆን አሳራችንን ቆጥረናል ብል እንኳ ያለፍንበትን ጨለማና አስከፊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ አይገልጸውም። ወደ ጌታ ከተሰበሰቡት ወንድም እህቶቻችን እና አባቶቻችን በቀር በጊዜው የነበራችሁ ወንድሞቼ ጋሽ ወልዴ መኩሪያ፣ ቡታቆ ቡናሮ፣ ያዕቆብ ቦጃጐ፣ በለጠ በላቸው፣ ሳሙኤል ታንጋ፣ ሚልክያስ ወኖ ፣ አቦታ አንዳቦ፣ ባልቻ ባራታ፣ እህቶቼ አዲስ ወጋሶ፣ ንግሥት ጋሞ፣ አልማዝ ዳና ፣ አባቶቼ ጋሼ ወጋሶ ሄሊሶ፣ ወጋሶ ሻማና፣ እንድሪያስ ታንቱ እና ሌሎችም ያ የጨለማ ዘመን ያልፋል ብላችሁ አስባችሁ ነበር? በፍጹም እንዳላሰባችሁና ሥርዓቱ ሲወድቅ ወንጌል በአደባባይ ሲሰበክ ሲታዩ ሕልም እንደመሰላችሁ እርግጠኛ ነኝ። እኔ በበኩሌ ከዚያው ዘመን ጋራ ሳነጻጽረው አሁን የሚታየው ሁሉ ሕልም እስክመስለኝ ድረስ እገረማለሁ። በሁላችሁም ላይ ጠባሳው አለና ይህች ጽሑፍ ለእናንተ ማስታውሻነት ትሁን። ። በተለይም በኦፋ ወረዳ በኦኮቶ ሴሬ ቀበሌ ያሳለፍንባቸውን የጭንቅ ዓመታት ከቶውንም እንደማትረሱ ዛሬ ላይ ቆማችሁ ለእግዚአብሔር የልባችሁን ምሥጋና እንደምታቀርቡ አልጠራጠርም። የዘመኑ ሁኔታ ጠባሳ ሳይጥልበት ያለፈ አማኝ ማን ነውና! በተለይም ለመስከረም 2 የአብዮት በዓል ኪነት እንዲጨፈር ጴንጤዎች ድምጻቸው ጥሩ ነው ተብሎ በኦኮቶ ሴሬ ቀበሌ ሲያከማቹን አንጨፍርም ማለታችን ምን እንዳስከተለብን ወደ ጌታ ከተሰበሰቡት ወንድማችን አማኑኤል ጐአ፣ እህታችን ኤልሳበጥ ጐአ፣ ወንደማችን መስዋዕት ማሞ በቀር ሌሎች በሕይወት ያለነው ሁላችን በደንብ እናስታውሰዋለን። እኔ በበኩሌ በአሁኑ ጊዜ መዘምራኖቻችን መድረክ ላይ የሚያደርጉት ውዝዋዜ ከደርግ ጊዜው የኪነት ጭፈራ ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ በመሆኑ አብሬአቸው ለማምለክ እስክቸገር ድረስ ጠባሳ ጥሎብኝ አልፏል። ቃላት የማይገልጹት የጨለማ ዘመን! እናንተ ያ ዘመን አለፈ ሲባል ስትሰሙና በዓይናችሁም ሲታዩ ሕልም የምታዩ አልመሰላችሁም? ያን ጊዜ የመሠረተ ትምህርት ዘማች ሆናችሁ ወደ ኦኮቶ ሴሬ ቀበሌ የተመደባችሁና እኛን ክርስቲያን ወጣቶችን በድብቅ የእግዚአብሔርን ቃል በማስጠናትና በስደቱም ምክንያት እንዳንፈራና እንዳንንሸራተት ያበረታታችሁን ታላላቆቻችን በአዲስ አባባ ኮምፓሺን ቢሮ ያለኸው ወንድም ኢሳይያስ ኦምቦሌና በወላይታ የምትገኘው ወንድም ያሲን ሾንዴ የተባረካችሁ ሁኑ።
በቀበሌአችን እሥር ቤት እያለሁ አንድ በቤተክርስቲያን ያገለግል የነበረ ግን ጌታን መከተሉን ትቶ ከካድሬዎች ጋር የተቀላቀለ መቶ አለቃ የሆነ ሰው የጠየቀኝ ጥያቄ አይረሳኝም። ያለኝ እንዲህ ነበር ፡ “እንደዚህ እየሆንክ ኖረህ በኋላ እግዚአብሔርን ባታገኘው ምን ትሆናለህ?”። ይህ ጥያቄ በጊዜው ከእኔ አቅም በላይ ሆኖ መልስ ለመስጠት ቢያስቸግረኝም ከሰነፍ ልብ የመነጨ ፣ ከሰነፍም አፍ የፈለቀ መሆኑን የተረዳሁት በአስተሳሰብም በአካልም ጎላ ካልኩ በኋላ ነው። ያነ ገና ምርቁን ከፍትፍቱ ወደምለይበት የአስተሳሰብ ደረጃ ስላልደረስኩ ነገሮቹን መገናዝብም ሆነ ጥያቄዎቹን እንደአመጣጣቸው መመለስ ሳልችል ቀረሁ። ፈተናዬ እዛጋ ሳያበቃ ሌሎች ጥያቄዎችንም ተጠይቄአለሁ። በተለይም ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ከተዘጋች በኋላ እኔና ጥቂት የአካባቢ ወጣቶች አሁንም በአቋማችን የጸናን መሆናችንን ያዩ አንዳንዶች “ አሁን ሁሉም ነገር የለም ታዲያ እምነታችሁ ምን ይጠቅማችኋል ? ብለውናል። በውስጣችን የነበረው የጌታ ፍቅር ከእርሱ ጋር አጣብቆን እንጂ የተጋፈጥናቸው ፈታኝ ጥያቄዎች ከአቅማችን በላይ በመሆናቸው ለመመለስ አቅቶን ከሕይወት መንገድ ተንሸራትተን በወደቅን ነበር። ሰውን ሁሉ የሚረዳ እግዚአብሔር እኛንም ረድቶንና ደግፎን አለፍናቸው እንጂ ጊዜያቶቹ ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። በጊዜው በወላይታ አውራጃ በኦፋ ወረዳ ያ ሁሉ እንግልት ለደረሰባቸው አሁን በህይወት ላሉም ሆነ ወደ ጌታ ለተሰበሰቡም ሁሉ ከልቤ የሆነ አድናቆት አለኝ።
በአሁኑ ጊዜ በአገራችን አማኞች እምነታቸውን እንዲተው የሚያነቃ ካልሆነም የፍጥኝ አስሮ የሚገርፍ ወግና ሥርዓት የለም። ፈጣሪን ክዶ በራሱ ማንነት የተጠቀጠቀ፣ ለሰሚው የማይገባ እንግዳ ቋንቋ ለዜጋው ያስተማረ፣ ሰይፍ ይዞ ቤተ እምነቶችን ያሳደደ፣ አማኒያንንም በባትሪ እየፈለገ ካሉበት ጎትቶ እያወጣ በአደባባይ ያሸማቀቀ እንደ ኮሚዩኒዝም ያለ ጉደኛ ሥርዓት አንድ ቀን መታሰቢያው ተረስቶ ፣ ድብዛውም ይጠፋል ብለን አስበን አናውቅም። በተቃራኒው ለምድሪቱ በረከት የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ መሪ መታየቱ አቤቱ እግዚአብሔር “ሆላ ላንተ” አሰኝቶናል። ጊዜያቱን ለማንጻጸር ዕድል ያገኘ፣ ዕድሜም የተቸረው ሁሉ የምለው ይገባዋል። በ1972-79 ባሉት ጊዜያቶች አንድን ክርስቲያን መንገድ ላይ አቁሞ ለማዋከብ ባለሥልጣን መሆን ሳያስፈልግ ማንም ተራ ሰው እንደፈለገው ሊስፈራራው የሚችልበት፣ ደስ ካሰኘው የሚደበድብበት ሁኔታዎች ነበሩ። ጴንጤ በሰፈራችሁ ካለ አውግዙ እያለ ጓደኛን ከጓደኛ፣ ወላጅን ከልጅ የሚያለያይ የአቴና ወጊ፣ የደብተራ፣ የጥላወጊና የአስማተኛ ቅልቅል እምነት የሚወረውርብን ቀስት አንዴም ኢላማውን ስስት አንዴም በመንገድ ላይ ሲክሽፍ ኖረን አሁን ወንጌል በአደባባይ ሲሰበክ ለማየት በቃን።
መስከረም 28 ቀን 1978 ዓ.ም በጌታ ታላቄ ከሆነው ወልዴ መኩሪያ ከተባለ ወንድሜ ጋር ተይዘን ወላይታ ሶዶ ፖሊስ ጣቢያ ታሥረን ሳለ የአሥር አለቃ አማን የተባለ የጣቢያው ፖሊስ ያደረገብኝን አስታውሳለሁ። ይህን ይህል ዘመን ቆይተን ጉዳዩን አሁንም የማስታውሰው በአሥር አለቃው ላይ ቂም ቢጤ ቋጥሬበት ሳይሆን የሁኔታዎች አስከፊነት የማይረሳ ስለነበረ፣ የጨለማው ብርታት ከአእምሮ ሊፍቁ ከሚችሉት በላይ እንዲያውም ከሁለት ቀን በፊት እንደተደረገ ያህል ስለሚሰማኝ ብቻ ነው። በትክለ ቁመናው ሞላ ያለና መካከለኛ ቁመት ያለው የአሥር አለቃ አማን በጐርናና ድምጹ ጧት ጧት በስሜ እየጠራ ወደ ውጪ ያወጣኛል፣ ሁለት እጆቼን ወደ ኋላ አድርጌ ጐንበስ ብዬ እጆቼን ከሁለት እግሮቼ መካከል ወደፊት ካሾለክኩ በኋላ ዝቅ ብዬ በሁለት እጆቼ ሁለቱን ጆሮዎቼን ይዤ በዚያው ሁኔታ ጆሮቼን ሳልለቅ የፖሊስ ጣቢያውን ግቢ እንዲዞር ያደርግኝ ነበር። ሲያሰኘው ደግሞ ያለ ምንም ምክንያት በያዘው አጭር በትር በመቀመጫዬ በኩል ያላሽቀኝ ነበር። ደስ ሲለው ደግሞ ለ3 እና ለ 4 ሰዓታት ቁጥጥ ብዬ እንዲቀመጥ ያዘኝ ነበር። ቁጥጥ ማለቱ ለመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ምንም ባይሉ ደቂቃዎች በጨመሩ ቁጥር ወገብ፣ ጉልበት ፣ የውስጥ እግር፣ ባትና ታፋ የተቆራረጠ ያህል ይታመም ይጀምራል። ቅጣቱ ሲያልቅ ቆሞ መሄድ ሌላ ፈተና ነው። ይህ ከተያዝንበት ቀን ጀምሮ በየዕለቱ ከቁርስ በፊት ለሁለት ሰዓታት ያህል ከሌሎች ስፖርት ዓይነቶች ጋር የሚሰጠኝ ቅጣት ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ጓደኛዬ ወልዴ ውስጥ ሆኖ ይቃትት ነበር። ወንጀል ሆኖ ለዚህ ሁሉ ቅጣት የዳረገን “ የመካከለኛው ዘመን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” የሚል በኤስ አይ ኤም የታተመ መጽሐፍ እኔና ወንደሜ ወልዴ በእጃችን ይዘን መገኘታችን ብቻ ነው።
ዛሬ ግን በቤተክርስቲያን ላይ እንደዚያ ዓይነት ሁሉን የሚያሸማቅቅ ስደት የለም። እምነትንም የሚቃወም የለም። ሁሉም ነገር ተቀይሮ ወንጌል በየቦታው ይሰበካል፣ መዝሙራችን በሕዝብ መመላለሻ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ሁሉ ሳይቀር እየተከፈቱ ናቸው። የሚያሳዝን ቢሆንም ጫት ቃሚዎችም ጭምር ከዘፈን ይልቅ የመዝሙር ካሴቶቻችንን እየተከፈቱ ነው። ማን ያውቃል እነርሱ ለምርቃና ብለው ቢያደርጉትም ጌታ የወንጌል ድምጹን በዚያ በኩል እያስተላለፈላቸው ይሆናል ብለን እናምናለን። እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ልንገምተው በማንችለው ፍጥነት ስለቀየረው በክርስትና ምክንያት መሸማቀቅ የለም፣ አይታሰብምም። እግዚአብሔር የት አለ? አሳየኝ እያለ የሚያፈጥ ካድሬ፣ የትምህርት ቤት መምህርም አይታይም። በመንገድ ማዕዘን ላይ ቆሞ ንብረት እየቀማና አጓጉል የአካል ክፍሎቻችንን ሲመታ ታይቶ ጴንጤዎችን አዋረደ ተብሎ የሚጨበጨብለት፣ በድርጊቱም አንጀቱ ምርስለት ያበጠ ጐረምሳም የለም። ሕልም የሚመስል ግን በዓይን የሚታይ እግዚአብሔር የሠራው ታሪክ ይሏል ይህ ነው ።
ከብዙ ዓመታት ቆይታ በኋላ ቤተሰቦቼን ለመጐብኘት ወደ ወላይታ ሄጄ ባየሁትና ለማመን በሚያስቸግር ነገር ምክንያት ወደ ማረፊያ ቦታዬ ገብቼ በሩን ከኋላዬ ዘግቼ በአምላኬ ፊት ተንበርክኬ ለእርሱ ያለኝን ምሥጋና በእምባ አቀርብኩ። ምክንያቱም ያቺ የአሥር አለቃ አማን ሲያሰቃየኝ የነበረበት ፖሊስ ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ፈርሳ በቦታዋ ትልቅ የገበያ አዳራሽ ተሠርቶ፣ በላይኛው ፎቅ ላይ ባለው የካፊቴሪያ በረንዳ ተቀምጥው ሻይ እየጠጡ ስለ መንፈሳዊ ነገር የሚመካከሩ ሰዎችን ሳይ ስሜቴን መቆጣጠር ስላቃተኝ ነው። በእውነት ሕልም የማይ መሰለኝ እንጂ እውነት አልመሰለኝም ነበር። የእናት አባቶቻችን እንባ መክኖ ሳይቀር ዘመን ቆጥሮ እግዚአብሔር በምድራችን ስለመንገሡ ያነ የነበርን ሁላችንም አሁን አውራ ምስክሮች ነን።
እግዚአብሔር ዛሬም ሕልም የሚመስሉ እውነተኛ ታሪኮችን እየሠራ በዙፋኑ ላይ ነው። በክርስትና ሕይወታችንም ሆነ በአገራችን በኢትዮጵያ የሚሆነውን ስናይ ሕልም የማየት ያህል ነው። ክቡር የሰው ልጅ ደሙ በከንቱ ሲፈስ የነበረው ታሪክ በቅጽበት ተቀይሮ የአገራችን ዜጐች የሰላም አየር መተንፈስ ፣ የሰላምን ወሬ ማውራትና መስማት መቻል፣ ያውም የአምባገነኖች አምባገነን መሪዎች ሥልጣን ተቆናጥጠው ሕዝብን እርስ በርሱ በሚያጫርሱበትና በሕዝብ ደም እንጀራቸውን በሚጋግሩበት አገር አሁን የሚታየውን የሰላምና የእኩልነት ጅማሬ ማን አስቦ ነበር? እንዲያው እውነት ነው ሕልም? ብቻውን ተአምር የሚሠራው እግዚአብሔር ብቻውን ክብር ይገባዋል።

ዲያብሎሱ ይሁዳና ሰይጣኑ ጴጥሮስ ( ሁለቱ የጌታ ደቀመዝሙሮች)


የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ መንፈሳዊ ሕይወትን ያሳድጋል፣ የሚያስገኛቸውም ቁም ነገሮች ከቁጥር ያለፉ ናቸው። የዚያኑ ያክል ደግሞ ለመተርጐም የሚያስቸግሩ የምንባብ ክፍሎችና አረፍተ ነገሮችም አሉ። አስደንጋጭና ግራ መጋባት ውስጥ የሚከቱን መኖራቸውም ግልጽ ነው። ለምሳሌ ጌታ ሲናገር፦ “ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ያለው አሳብ አስደንጋጭ ነው። ጥያቄ ከሚፈጥሩብን መካከል “አስቆሮንቱ ይሁዳ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነው እንዴት ነው?’ ኢየሱስ ደቀመዝሙሮችን ሲመርጣቸው ዲያብሎስ የሆነውን ይሁዳን ለምን አካተተው? (ዮሐ 6:70)። ለሚለው መልስ መፈለግ በራሱ ከባድ የቤት ሥራ ነው። ከደቀ መዝሙሮች መካከል “ዲያብሎስ” መሆኑ የተነገረለት ይሁዳ ነበር። አገልጋይ የሆነው በኢየሱስ ምርጫ ነው። ጌታም ማንነቱን እያወቀ መርጦታል ግን ለምን? ለመመለስ ያስቸግራል።
ይሁዳ ራሱ ወደ ኢየሱስ የቀረበ ለማስመስል ብዙ ተፍ ተፍ ይበል እንጂ የተለወጠ አገልጋይ አልነበረም። ከሌሎች ጋር ሐዋሪያ ተብሎ የወንጌል ምስክርነት ሲሰጥ ለካ እርሱ “ዲያብሎስ” ነበር። ጌታ ተአምራትን ሲያደርግ፣ በሁለት ዓሣና በአምስት እንጀራ በሺዎች የሚቆጠሩትን አጥግቦ አሥራ ሁለት መሶብ ሲስያተርፍ፣ ደቀመዛሙርትም ሰዎችን በሜዳው ላይ ባለው ሣር በሃምሳ ሃምሳ እያደረጉ አስቀምጠው ሲያገልግሉ አስቆሮቱ ይሁዳ አብሮአቸው ያገለግል ነበር። ይሁን እንጂ ሰውየው “ዲያብሎስ” ነበር። ዲያብሎስ መሆኑን ከኢየሱስና ከራሱ ከይሁዳ በቀር የሚያውቅ አልነበረም። እነዮሐንስ ያዕቆብና ጴጥሮስ ወዘተ ሌሎች ሐዋሪያት ይሁዳን በሐዋሪያነቱ እንጂ በዲያብሎስነቱ አላወቁትም። አብሮአቸው ብዙ ተጉዞአል፣ አገልግሏል፣ ምናልባትም አብሮአቸው ጸልዮም ይሆናል። እርሱ ግን ውጭው ሐዋሪያው ይሁዳ ውስጡ ግን አደገኛው ዲያብሎስ ሆኖ ኖሯል። እንደ ደቀመዛሙርት ቢያገለግልም ልቡን የገዛው ከጌታ ፍቅር ይልቅ የገንዘብ መጎምጀት ነው። ከኢየሱስ ይልቅ ገንዘብን አብልጦ በመውደዱ ለዲያብሎስ ቀኝ እጁ፣ የዓይኑም ብለን ሆኖ አገልግሏል። ኢየሱስን ለመሸጥ፣ ለጠላቶቹም አሳልፎ ለመስጠት ዋጋውን ሲተምን ሰንብቷል። ግን የሚባለው የኢየሱስ ደቀመዝሙር ነው። የተመረጠ ሐዋሪያ ነው። ፈረንጆች የመጽሐፉን ሽፋን አይተህ አትፍረድ የሚሉት ለዚህ አይደል?
ይህ አሳብ ሰው ስለ ደህንነቱ ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያደርግ ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጅምላ ከማህበረ ምዕመናን ጋር የተቀላቀሉ ያልዳኑ ሰዎች ዛሬም ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠርጠር ይኖርብናል ወይ ቢባል “በሚገባ እንጂ” የሚል ነው መልሱ። ያልዳነ ሐዋሪያ፣ ያልዳነ ወንጌላዊ፣ ያልዳነ ነቢይ ወይም መጋቢ ይኖራል ብሎ ማሰብ እንዴት ይቻላል? የሚሉ ብዙ ናቸው። ሰዎች የሚከራከሩት ስለ አገልጋይነት ጉዳይ ነው። አገልጋይ መሆን ለደህንነታችን ዋስትና አይሰጥም፣ ሊሰጥም አይችልም። አስተማሪ፣ ዘማሪ ፣ መስካሪ መሆን ዳግም መወለዳችንን አያረጋግጥም። ይህ አስደንጋጭና አስደማሚ ነው። ያለጥርጥር ለመቀበል የሚከብድ ነው። ግን ደግሞ የማይታበል ሐቅ የማይጠረጠር እውነታ ነው።
የይሁዳ ገርሞን ሳንጨርስ ኢየሱስ ጴጥሮስን “ሰይጣን” ማለቱ አያስደነግጥም? ጴጥሮስ በሐዋሪያት መካክል ዋናና አእማድ ተባለው ነበር። ሁሉን ትቶ ኢየሱስን የተከተለ ቆራጥና ተወዳጅ ሐዋሪያ! ለጌታ የሚቀናና ስለጌታ ሲል ራሱን ለሞት ለመስጠት የወሰነ ሐዋሪያ! ታዲያ አንድ ቀን ጌታ “ሰይጣን” ብሎ አረፈው። ታዲያ ማን ነው ሰው? ማነው አገልጋይ?
ይሁዳና ጴጥሮስ ሁለቱ የማይመሳሰል ማንነት አላቸው ። ይሁዳ ምኞቱና የልቡ ጩኼት ኢየሱስን ሽጦ ገንዘብ መቀበል ነበር። ጌታ እስክገልጠው ድረስ የዲያብሎስን አጀንዳ ለማስፈጸም የኖረ ነው። እንክርዳዱ ከስንዴው፣ እሾክም ከወይን ጋራ በአንድ ማሳ እንደሚኖሩ ከእውነተኞቹ ሐዋሪያት ጋር አብሮአቸው ኖሯል። ጴጥሮስ ሰይጣን የተባለበት ምክንያት ለኢየሱስ ያለውን ፍቅር በቃላት ለመግለጽ በሞከረበት ወቅት የተከሰተ ጉዳይ ነው። “ እርሱ ግን ዞር ብሎ ጴጥሮስን ፣ ወድ ኋላዬ ሂድ ፣ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና እንቅፋት ሆነህብኛል አለው(ማቴ 16:23)። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች እንዲሁም ከጸሐፍት ብዙ መከራ እንደሚደርስበት፣ እንደሚገድልና እንዲሁም በሦስተኛ ቀን እንደሚነሳ ይገልጥ ዘንድ ሲጅምር ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ አይሁንብህ ፣ ይህ አይድረስብህ ብሎ ኢየሱስን ገሰጸው። ይህንን ያለው ኢየሱስን ከማፍቀሩ የተነሳ ነበር። ቅንነቱንና ለጌታ ያለውን ፍቅር የገለጠበት መንገድ ይህ ቢሆንም አሳቡ ለካ ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ጋር ይጣረስ ኖሯል። ብዙዎቻችን እንደምናምነው ሰይጣን የጴጥሮስን ቅናአትና ለጌታም ያለው የሚቀጣጠል ፍቅር ለራሱ ዓላማ ተጠቅሞ በኢየሱስ በኩል ዓለምን ሁሉ ለማዳን የተዘረጋውን የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለማሰናከል በጴጥሮስ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ሞከረ። ጌታ የገሰጸው ያንን የሰይጣንን ዓላማ ነው። እውነተኞችም አገልጋዮች ጸጋቸውንና መንፈሳዊ ቅንአታቸውን በእውቀትና በብስለት እንዲሆም በጥበብና በማስተዋል ካላላደረጉት መንፈሳዊ በሚመስሉ ሁኔታዎች በኩል ሰይጣን ጫና ሊፈጥርባቸው እንደሚችል ከዚህ እንማራለን።
ይሁዳ ዲያብሎስ የገባበት፣ የሰለጠነበት ልቡንም ለመንግሥቱ ያስወረሰ የዲያብሎስ መኖሪያ ለመሆን ራሱን የሰጠ possessed ሲሆን (ሉቃስ 22:3፣ዮሓ 13:27) ጴጥሮስ ግን ሰይጣን ተጽዕኖ ሊያሳድር ሙከራ ደረገበት Influenced አገልጋይ ነበረ። አማኞች ከሁለቱም የሰይጣን ተንኮሎች ራሳችንን መጠብቅ ይኖርብናል። እንደ ይሁዳ በአገልጋይነት፣ በነቢይነት፣ በሐዋሪያነት፣ በመጋቢነት፣ በወንጌላዊነት ወዘተ ስም ሕዝብን እያተራመሱ የእግዚአብሄርን ክቡር ዓላማ የሚያበላሹ ራሳቸውን ስለሚያውቁ ፈጥነው መመለስ ካልቻሉ የሰበሰቡትን ሳይበሉ ገመድ ያንቃቸዋል። እንደ ጴጥሮስም በመንፈሳዊ ቋንቋ የተለወሰውን የሰይጣንን ምክር እየሰሙ ከጠራቸው ጌታ ጋር የሚጣሉ ወደ ቃሉ መመለስ ያስፈልጋቸዋል። መልካም የሚመስሉን ልምምዶችና በውስጣችን የሚሰሙን ስሜቶች ሁሉ በሕያው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ከልታሹና ካልተገሩ አደገኛነታቸው ከፍ ያለ መሆኑን ልብ ይሏል። ይሁዳ በመታነቅ ሕይወቱ ተደመደመች፣ እርሱም ወደ መረጣት የገዛ ራሱ ሥፍራ ሄደ(ሐዋ 1:25)። ጌታ ግን ጴጥሮስን በመገሰጽ ሕይወቱን አዳነው። መንፈስ ቅዱስም ሲሞላው ስለ ጌታው ትንሣኤ በድፍረት በመስበክ በሺዎች የሚቆጠሩትን ወደ እግዚአብሔር መንግስት ማረከ። ሰለ ኢየሱስ ሲል እጁን ለሰንሰለት ሰጠ። ከብዙ ተግባራትም መካከል ዘመን ተሻጋሪ ቃል ከጌታ ተቀብሎ ሁለት መጸህፍትን ጽፎ በአዲስ ኪዳን ቀኖና ውስጥ ከተተው። ባለማወቅ ያደረገው ሳይታሰብ የጌታን ማዳን ሰብኮና ጽፎ መለኮታዊ ሰነድ ትቶልን ሄደ። ፍጻሜአችን እንደ ይሁዳ ሳይሆን እንደ ጴጥሮስ በመልካም ይሁንልን። አምንእ!

Monday, March 19, 2018

ንቅስ ያለ የልብ ሰው ይሁንላችሁ፡፡

   ንቅስ ያለ የልብ ሰው ይሁንላችሁ፡፡



I. መግቢያ
ቆንጅናና ውበት በምን ይለካል? በጥቁረት ወይ በቅላት? በውፍረት ወይስ በቅጥነት? በርዝመት ወይስ በእጥረት? ውበት በእርግጥ ውበት የሚሆነው እንዴት ነው? እኔ እንደምረዳው ለቁንጅና የሚሰጠው ብያኔ እንደየሰው አተያይ ይለያያል፡፡ ለአንዱ ምድር ፊት የሆነ ፉንጋ የተባለ ለሌላው ታይቶ የማይጠገብ የዓይን ምሳ ነው፡፡ ለአንዱ እራሪ -ድንኪዬ የተባለ ለሌላው ጌጥ ፣ ለአንዱ ሸበላ ሲባል የኖረ ወደ ሌሎች ጋ ሲደርስ ፊታቸውን ሊያዙበት ሁላ ይችላሉ፡፡ ክብ ፊት የላቸውን ሰዎች የሚወድዱ እንዳሉ ሁሉ ረዘም ያለና ሾጣጣ ፊት የሚማርካቸው ብዙ ናቸው፡፡ የረዘመ አፍንጫ ያለውን ሰው ሰልካካ ብንለውም አፍንጫ ቢርዝም ማር አይቆርጥ የሚሉ ያዚያኑ ያህል ናቸው፣ እንዲያውም የተጠረበ እንጨት የሚመስላቸውም አይታጡም፡፡ ታዲያ ውበትና ቁንጂና የቱጋ ናቸው? በአገራችን አንድ ሰው ወፈር ካለና ሆዱ አካባቢ ቦርጭ ጣል ካደረገበት ተመችቶታል ከማለት አልፎ ሀብት እንዳለውም ሲታሰብ በተቃራኒው በምዕራባውያን ዘንድ ሰውን ወፍራም ነህ ማለት ሊያቀያይም ስለሚችል የማይፈለግ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ውበት አንጻራዊ ነው ብል ብዙዎቻችሁ የምትስማሙ ይመስለኛል፡፡ የውጭ ሰውነታችን የሚያምር ብቻ ሳይሆን የሚያየን ሁሉ የሚወድደው እንዲሆን እንቀባባዋለን ፣ በተቻለን መጠን እናስውበዋለን፡፡ በሰለጠነው ዘመን ብዙዎች እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ውበታቸው የቀነሰባቸው ስለሚመስላቸው የፍታቸውን መልክ በቀዶ ጥገና ዜዴ እንደ ወጣት ደምግባት ያላቸው ለመምሰል ሲሉ ከፍተኛ መጠን ያለውን ንዋይ ያፈስሱበታል፡፡ ይህን ያህል ከተለፋም በኃላ ሰው ለቁንጅና የሚሰጠው ቢያኔ ለየራስ ስለሆነ በሁሉ መደነቅና ሁሉን መማረክ አለማቻላቸው ከንቱ ኪሳራ ያስብላቸዋል፡፡ ሰው የቱንም ያህል ፊቱን ቢያሳምርና ቢቀያይር የውጭ ገጽታው እውነተኛ ማንነቱን ሊወክል አለመቻሉ በጣም አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ ለዚህ የሚደረገው ጥረት ከፈጣሪ ጋርም የሚያጣላ ሆኗል፡፡ በሰው ፊት መልካቸው የሚያምር ግን ስንት ሰም- ለበስ የሆኑ ክፉዎች እንዳሉ ቤት የቁጠረው ማለት ብቻ ይበጃል፡፡ አንነድች ውበት ማለት የውስጥ ጉዳይ ነው የሚሉት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እኔም ላሰምርበት የምፈልገው ይህንን የሚመስል ብርቱ ጉዳይ ነው፡፡እናም እንዲያው ባጭሩ ስለ የውስጥ ሰውነት ማማር ለቅምሻ ያህል የወግ ወጉን ብቻ መርጠን በእጥኑ እንመልከት፡፡
የእግዚአብሔርም ቃል ሲናገር ሰው ፊትን ያያል ይለናል፡፡ ሰው ፊትን ያያል ሲል መልክን ፣ ቁመናን፣ አለባበስን፣ አነጋገርን፣ ከሌሎች ጋር ያለ “አቀራረብ ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን እኛ እንደምናይ ፊትን አይቶ አይበይንም፡፡ እርሱ የሚያየው ልብን ነው፡፡ የሰው ልብ ከባልንጀራው የተሰወረ ነው፣ ለእግዚአብሔር ግን በግልጽ ይነበብለታል፡፡ ሰውን ሁሉ ግሩምና ድንቅ አድርጎ የሠራው እግዚአብሔር ያ ቆንጆ ነው ይህ ግን አይደለም የሚል ድራማም ከእኛ ጋር ለመጫወት ጊዜውን አይሰጥም፡፡ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነው ሐዋሪያው ጴጥሮስ ጌታ የውስጥ ሰውነታችንና ማንነታችን እንደሚያይ ብቻ ሳይሆን እንደሚያከብረውም ጭምር ሲያመለክት በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ ፣ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ ይለናል (1 ጴጥ 3፡4)፡፡ ሐዋሪያው በወንድና በሴት ማለትም በባልና በሚስት መካካል ስላለው የፍቅር ትሥሥር ሲያስተምር ነው ይህንን አሳብ ያመጣልን፡፡ ባልና ሚስት ሁለቱም በየራሳቸው ለትዳራቸው መስመር ሊጫወቱ ስለሚገባቸው ሚና በመተንተን እየተናገረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ የሚለውን ወሳኝ መልእክት ያስተላልፍልናል፡፡ እረ ለመሆኑ እንደ ፊት መልክ የልብ ሰውነትን ተመልክቶ ነጭ ወይ ጥቁር ወይም ጠይም፣ አይነ ልም ወይም መልከ መልካም ማለት ይቻል ይሆን; ካልተቻለስ ;
II. የልብ ሰው መገለጫዎች 
1. በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው የከበረ ነው፡፡
ምእራባውያን ጊዜ ወርቅ ነው ፣ ክቡር ነው ይላሉ፡፡ ቤንጃሚን ዲርሳይሊ የተባሉ ሰው ግን- "ጊዜ ወርቅ ነው እውነት ግን ከጊዜ ይልቅ ውድ ነው " ሲሉ ፣ኤልሳቤጥ ጆርጅ የተባሉ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ሴት ደግሞ "እያንዳንዱ ቀን የሚናደርገውን ሁሉ እግዚአብሔርንና መንግሥቱን ለማገልገል የሚናውለው ከሆነ የከበረ ነው " አሉ፡፡ ጆን ፓይፔር የተባሉ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰውም እንዲህ ብለው ሰበኩ- "የሚያድን እምነት ያላችሁን ሁሉ ብትሸጡና በኃጢአት የሚገኘውን የዓለም መዝገብ ሁሉ ብትተውት የሚያስተማምናችሁ ነው፡፡ የተሰወረው የቅዱስ ደስታ መዝገብ ጥልቅ ለሆነው የውስጣችሁ ጥማት ርካታን ይሰጠዋል፡፡ ከልብ የሆነው የሚያድነው እምነት ኢየሱስን በውስጣችሁ እውነት ማድረግ ብቻ ሳይሆን እርሱን ሁል ጊዜ እንድትናፍቁት ያደርጋችኋል ፣ ኢየሱስ በተስፋው በኩል ወደ እናንተ መምጣቱ በዓለም ካለው ሁሉ ይልቅ አብልጠን የምንፈልገው ትምክህታችን ነው፡፡"
ውድ ዋጋ አውጥተን ልብስና የወርቅ ጉትቻ የምንገበየው ለብሰን በሰዎች ፊት ለማማርና ለማጌጥ ነው፡፡ የሚያዩንም ደግሞ በለበስነው ልብስና የወርቃችን ጥራት መጠን ያከብሩናል፡፡ የምንሠራውን ሽሩባና የምናንጠለጥለውን ጉትቻ እኛ አናየውም የሚያዩልን ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን የሚያከብረው የልባችንን ጌጥ ነው፡፡ እርሱ ሰው ስለሚያየው የውጭ ማማር ስንጨነቅና ስንወጠር እግዚአብሔር የሚያየው የውስጥ ውበታችን አመድ እንዲለብስብን አይፈልግም፡፡ በእርሱ ፊት እጅግ የከበረ ዋጋ ያላቸው እንደነ ጋብቻ፣ የቅዱሳን አገልግሎትና ሕይወት ወዘተ፣ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱና አውራ የሆነው ሰው ለእግዚአብሔር የሚሰጠው በውስጥ የተሸለመ የልብ ሰውነት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የሚለው ቃል ክብደት ሊሰጠው እንደሚገባ ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡ 
2. የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለው ነው፡፡ 
በዚህ ሁለት ቁልፍ አሳቦች ተጠቃለው ቀርበዋል፡፡ አንደኛው የዋህነት ሲሆን ሁለተኛው ዝግተኛ መንፈስ ነው፡፡ የዋህነትና ዝግተኛ መንፈስ ማለት ምን ማለት ነው? ሁለቱም አሳቦች ትህትናን፣ ሰላማዊነትንና ጸጥታን ለማመልከት የተጠቀሱ አይደሉምን? የውጭ ሰውነታቸውን በመሸለምና በማስጌጥ ቁንጅናቸውን ለዓለም ለማሳየት የሚዳክሩ ዓለማውያን ሴቶች በበዙበት ዓለም ለእግዚአብሔር ሰዎች ደግሞ በሚያዩአቸው ሁሉና በአምላካቸው ፊት እውነተኛው ዉበታቸው የዋህና ዝግ ያለ መንፈስ ነው፡፡ በተለይም በጴጥሮስ ዘመን ያላመኑ ባሎች ያሉአቸው ክርስቲያን ሴቶች ባሎቻቸውን ለክርስቶስ ለመማረክ ውጫዊ ሰውነታቸውን ከመሸለምና በማስዋብ ይልቅ በየዋህነትና ዝግ ባለው መንፈስ በመመላለስ እንዳለባቸው ሐዋሪያዊ ትምህርት ተሰጥቶአቸዋል፡፡ የዋህነት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በብዙ መንገድ ተጠቅሷል ፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚገልጸው የዋህነት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው( ገላትያ 5፡22)፡፡ ጌታችን ኢየሱስም የዋህነትን ከእርሱ እንድንማር አሳስቦናል( ማቴ 11፡29-31)፡፡ አማኞች በየዋህነት መንፈስ በመመላለስ ክርሰቶስን መምሰል ይችላሉ፡፡ በቤትና በውጭ የክርስቶስ እውነተኛ ደቀመዝሙርነታችን ከእርሱ በምንማረው የዋህነት ልንገልጸው እንችላለን፡፡ የዋህነት በባልና በሚስት መካከል ላለው ግንኙነት እጅግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ የተለየ ግምት እንስጠው፡፡
3. የማይጠፋውን ልብስ የለበሰ ነው፡፡ 
የክርስትና ሕይወት ለማይጠፉ መንፈሳዊ ቅርሶች አድሎናል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመናችን የምናገኘቸው ሰማያዊ በረከቶቻችን የማይጠፉ በመሆናቸው ደስታችን የላቀ ነው፡፡ ለምሳሌ፡ የማይጠፋ ሕይወት(1ጴጥሮ.1፡3-4) የማይጠፋ ርስት፣ የማይጠፋ ተስፋ(1ኛ ጴጥ1፡3-4) ፣ የማይጠፋ አክሊል( 1ቆሮ.9፡) ፣ የማይጠፋ ዘር( 1ጴጥ 1፡23)፣ የማይጠፋ ቤት ወይም መኖሪያ(2 ቆሮ 5፡1-4)፣ ወዘተ በክርስቶስ በማመናችን ምክንያት ያገኘናቸው መንፈሳዊ በረከቶቻችን ሲሆኑ እነዚህ ከማናቸውም ምድራዊ እሴቶች ሁሉ ይለያሉ፣ ይበልጣሉም፣ እኛም ልንወርሳቸው ተጠርተናል፡፡ በምንም ሁኔታ ቢሆኑ ከማይጠፉ መንፈሳዊ በረከቶቻችን አንዱ የውስጥ ሰውነታችን የምንሸልመው የማይጠፋው ልብስ ነው፡፡ የልብ ሰው የሚለብሰው ልብስ የማይጠፋ በመሆኑ የተለየ ግምትና ክብር ይሰጠዋል፡፡ ይህን የውስጥ ሽልማታችንን የሚወስድብንም ሆነ የሚያስረጅብን የለም፡፡ የውስጥ ሽልማታችን በወረት ወይም በፋሽን ሽሚያ ምክንያት በሚከወን ድንገተኛ ማባከን አይጠቃም፡፡ ስለዚህ ሐዋሪያው ክርስቲያን ባለትዳር ሴቶችን ከውጭ ይልቅ ውስጣቸውን እንዲያስጌጡና እንዲሸልሙ አጠንክሮ ይመክራቸዋል፡፡ እውነተኛ ውበት የፊት ወዝ ሳይሆን በነፍስ ላይ የሚታይ ብርሃን ድምቀት ስለሆነ የዓለም ያርግልህ/ሽ ማለትስ በውስጥ ሰውነታቸው በማይጠፋ ልብስ የተሸለሙትን ነው! ውስጣችን ምንም ወዝ የጠፋበት ነጫ ጭባ ከሆነ ውጫዊ ሽልማት ብቻ ውብ አያስብለንምና፡፡
4. የተሰወረ የውስጥ ሰው ነው
የውስጥ ሰው የምንለው የማይታየው ማንነታችንን ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ነፍሳችንን፣ መንፈሳችንን፣ እና ህሊናችንን ማለታችን ሲሆን የልብ ጉዳይ ግን አውራ ነው፡፡ የሕይወት መውጫ ልብ ናት፡፡ የሰው ውድቀቱም ሆነ ጥንካሬው እንደልቡ ነው፡፡ የሕይወት አሸናፊነታችንና ጀግንነታችንም የሚገለጸው እንደ ልባችንና እንደ ሐሞታችን ነው፡፡ በእውነት እንነጋገር ካልን ብዙ የመናገራችን ብዛት የልባችንን ምስል አያሳየንም ፣እንዲያውም የጠቢብ ሰው አፍ በልቡ አይደል! ልብና ታማኝነትስ ፍጹም የማይለያዩ ሰምና ፈትል አይደሉ! ስሜታችን ግለቱ ከፍ ሲል ሰዎችን አቅፈን ልንስማቸው እንችል ይሆናል፣እውነተኛ ማፍቀር ግን ከዚያ ይለያል፡፡ አክብሮትንም ለሰዎች ልንቸራቸው እንችላለን ግን ግን ስሜትን ፣አእምሮን፣ስጋንና፣ አስተሳሰብን ሁሉ የሚማርክ ፍቅር የሚመነጨው ከውስጥ ሰውነት ከሆነው ከልብ ነው፡፡ ከልብ የሚመነጨው ፍቅር እንደገለባ እሳት በቅጽበት አይከስምም፡፡ ስለዚህ ነው ፍቅር በትዳር ውስጥ ምሶሶ ነው የምንለው፡፡ ከልብ የመነጨ ፍቅር ካለ የሕይወት ተግዳሮት በሚበዛበት ጊዜ ሁሉ እንኳን ጎጆው ሳይዘምም ይኖራል ምክንያቱም ያ ፍቅር ተሸክሞታልና፡፡ 
ስለዚህ አማኞች እህቶች ወይም ባለ ትዳሮች የውስጥ ሰውነታቸውን ማጌጥ መርሳት የለባቸውም፡፡ ከሥጋችን ይልቅ ለነፍሳችንና ለመንፈሳችን ግድ ሊለን ይገባናል፡፡ ጌታ ኢየሱስም ሲያስተምር ነፍስ ከመብል ከሰውነትም ከልብስ ይበላጣል ብሎአል(ማቴ 6፡25)፡፡ በእግዚአብሔር ጸጋና በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት እለት እለት ነፍሳችንን ልናረካት እንችላለን፡፡ ታዲያ ውስጣችን እንዴት ነው? ለሰው የተሰወረው ለእግዚአብሔር ግን የሚነበብለት ውስጣዊ ማንነታችን ሕያው ነው ወይ ሞቶብናል? ያ የተሰወረው የውስጥ ሰው! 
ለ. የልብ ሰው ባሕሪያት
ይህ ክፍል በጌታ የሆንነውን ሁላችንንም የሚመለከት ሲሆን በተለይም የማያምኑ ባሎች ያሉአቸው ክርስቲያን እህቶች እንዲያተኩሩበት ይሻል፡፡ ክርስቲያን ሴቶች ወይም ሚስቶች የተሰወረ የልብ ሰው መሆናቸውና ውስጣዊ ውበታቸው የሚታወቅባቸው መንገዶች ምን እንደሆኑ የጌታ ቃል የሚናገረንን ግልጽ አሳብ ከዚህ ቀጥሎ እንመልከት፡፡ 
1. ለባሎታቸው ይገዛሉ፡( 1ጴጥሮ 3፡1፣ ኤፌ 5፡21-22)፡፡
ሚስቶች ለባሎቸቸው እንዲገዙ የሚነግረን የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ነው፡፡ ክርሰቲያን ተጋቢዎች ወደ ክርስትና በመለወጣቸው ምክንያት በሚኖሩበት አካባቢና ዘመን ያለው የትዳር ደንብና ሥርዓት የእነርሱን የማይመለከታቸው አድርገው ለራሳቸው እንዳያስቡና ሌሎች ሰዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ራሳቸውን ለባሎቻቸው እንዲያስገዙ ይመክራቸዋል፡፡ ሐዋሪያው ጴጥሮስ በነበረበት ዘመን ሴት ልጅ ሙሉ በሙሉ በአባቷ ቁጥጥር ሥር ትሆናለች፡፡ ሴቶችን እንደ ሰው በማይቆጥረው የሮማውያን መጥፎ ልማድና ባህል መሠረት አንድ ሰው በሴት ልጁ ላይ የፈለገውን ከማድረግ አልፎ ቢፈልግ ሊገድላት ሁሉ የሚችልበት መብት ሲኖረው ይህንን የሚከለክል ሥርዓት አልነበረም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሴት ባል ስታገባም ፈቃዷ ሙሉ በሙሉ ለባሏ ይሆናል፣ እርሱም በሚስቱ ላይ የፈለገውን የማድረግ ሥልጣን ነበረው፡፡ ባል ሚስቱን ቢገድል እንኳ የሚከለከልው እስከማይኖር ድረስ ሴት ለባሏ እንደ ዕቃ ወይም እንደ ባሪያ ትገዛለት ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን የሆኑ ሚስቶች ለባሎቻቸ እንዲገዙ ጴጥሮስ የሚያሳስበው ከአሬማውያን አገዛዝና ሥርዓት በፍጹም የተለየ ነው፡፡ ክርስቲያን እህቶቻችን ለሚወዱአቸው ባሎቻቸው ሥልጣን ከልባቸው በመነጨ ፍቅር ተነስተው መገዛት እንዲኖርባቸው ጴጥሮስ ያሳስባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ፈቃድ የማይኖሩና አስቸጋሪ የሆኑ ባሎችን ለማሸነፍ የሚረዳ ዋንኛ መንገድ ነው፡፡ ፍቅር የትኛውንም ኃይል የማንበርከክ አቅም አለው፡፡ ለእግዚአብሔር ቃል የማይገዙ ለቤተሰባቸውም የማያስቡ አስቸጋሪ ባሎች በፍቅር ሊንበረከኩ ይችላሉ፡፡ ልዩነቱ አረማውያን ሴቶች ለባሎቻችው የሚገዙት እንደ ባሪያ በግድና በጉልበት ሲሆን የክርሰቲያን ሴቶች መገዛት ግን በፍቅር አስገዳጅነት በገዛ ፈቃዳቸውና በራሳቸው ተነሳሽነት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ተገዙ የሚለው ቃል ሴቶች ለወንዶች ባሪያ ሆነው እንዲረገጡላቸው የሚያዝ ሳይሆን ወድደውና ፈቅደው የሚደርጉት ልዩ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው ነው፡፡ የመገዛቱ አስገዳጅነት ለሚስቶች ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ባሎችም እኮ ለሚስቶቻቸው እንዲገዙ ቅዱስ ቃሉ ያስተምራል(ኤፌ 5፡21፣ 1ጴጥ 3፡7)፡፡ የክርስቲያናዊ ሥልጣንና መገዛት በእግዚአብሔር ፍጹም ፍርሃት በእርስ በርስ የሚደረግ እንጂ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች እግር አጣቢ የሚሆንበት አይደለም፡፡ ይልቁንስ የክርስቶስ ፍርሃትና ባልን የመውደድ ምስጢር ለገባት ሴት ሚስትነት እኮ የተከበረ ፣ ከፍ ያለና ወሳኝ ሰማያዊ ጥሪ ነው፡፡ ስለዚህ ራሷን ለበሏ ስትሰጥ የባሏ ፍቅር ደስታዋን ሙሉ ያደርግላታል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ተገዙ የሚለው አንድ መንገደኛ ለሆነ ወንድ ሳይሆን፣ ወይም የሆነ የጎረበት ሰው ሳይሆን አካሏ ለሆነው ባል ነው፡፡ ባሏ ለእርሷ አካሏ፣ ምርጫዋ ከማንኛውም ወንድ ጋር የማታወዳድረው ልዩ ጌጧ ነው፣ ከወንድሟም ይልቅ የሚቀርባትና የሚጠጋጋት ወዳጇ ነው፡፡ እናት አባትዋን ትታ የተጣበቅችበትና የተጣበቃት አጋሯ ነው ፣ እርሷም አጋሩ ናት፡፡ ታዲያ ራሷን በመስጠት ብትገዛለት ይበዛባታልን? እርሱስ ቢገዛላት ክብር አይሆንለትምን? ክርስቲያን ሚስቶች በፈቃዳቸውና በፍቅር ብቻ ሳይሆን በደስታ ሊያደርጉት ይገባቸዋል፡፡ ለትዳር ጓደኛቸው መልካምን የሚያደርጉ ሰዎች ምንም እንኳ የባሎቻቸው ወይም የሚስቶቻቸው ልብ የብረት ያህል የጠነከረ ቢመስልም በፍቅርና በደስታ በሚያደርጉት መሰጠትና መገዛት ያንን ሁሉ ሊያለሰልሱ ይችላሉ፡፡ አስቸጋሪና አመጸኛ የሆነውን ሰው ልብ ለመለወጥ በምድር ሕግ ከመግዛት ይልቅ በቤተሰብ ውስጥ የሚደረገው ፍቅርና ደግነት የተሻለ ተመራጭነት አለው፣ አላወቅንበትም እንጂ፡፡
2. ሰውነታቸውን በተገቢ ልብስ ይሸልማሉ፡፡
ሐዋሪያው ጴጥሮስም ከውጭ ማገጥ ይልቅ የተሰወረና የከበረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ ብሎ ባለትዳሮችን መከረ፡፡ የልብ ሰው መሆን ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው የሚመች እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ የውስጥ ሰውነታችንን ስለማማር ለእናንተ ጸጉርን ማሸረብ፣ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ፡ ይለናል፡ 
እግዚአብሔር ስለ አለባበሳችን ይገደዋል ወይ፣ እኛ የፈለግነውን ብንለብስ ምን ኃጢአት አለበት የሚሉ በርካታ ወገኖች እንዳሉ አልጠራጠርም፡፡ በእርግጥ ይህን አትልበስ ይህንን ደግሞ ልበስ የሚል የአዲስ ኪዳን ትምህርትም ሆነ ትዕዛዝ የለም፡፡ ሆኖም በተገቢ አለባበስ ራሳችንን እንድንሸልም ተመክረናል ፡፡ 
ሐዋሪያው ባገለገልበት ዘመን በዓለም ላይ ምግባረ ብልሹ፣ ሕይወታቸው በርኩሰትና በብልግና የተሞላ ሴሰኛ የሆኑ ሴቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሴቶች በአካላቸው ላይ የተለያዩ ምልክቶችን ከማድረጋቸውም በላይ የአለባበስ ሥርዓታቸውም ሁሉ ከክርስቲያን ሴቶች ሁኔታ በጣም የራቀና ለአእምሮ የማይመች ነበር፡፡ ከእነዚያ ሁኔታዎቻቸው አንዱ የጸጉር አሠራራቸው ነው፡፡ አሬማውያን ሴቶች ያንን ያደርጉት የነበረው በውጭ ሰውነታቸው ብቻ በማማር የውስጣቸውን ባዶነት የሚሞሉ ስለመሰላቸው ነው፡፡ አሬማውያን ሴሰኛ ሴቶች የውጭ ሰውነታቸውን ለመሸለም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያፈስሱት ለትዳር ጓደኛቸው፣ ለልጆቻቸው ወይም ለአጠቃላይ ትዳራቸው የሚሉት፣ የሚቆረቆሩለት የወይም የሚገዳቸው ነገር አልነበራቸውም፡፡ የቤተሰብ ሃላፊነት ስሜትም ስለማይሰማቸው የሚያገኙትን ገንዘብ በሽሩባና በወርቅ ያጠፉት ነበር ክርስቲያኖች ሴቶችም ከእነርሱ በመኮረጅ ልክ ዓለማያን ሴቶች እንደሚያደርጉት ዓይነት ሽሩባ መሠራትና የእነርሱን ዓይነት ልብስ መጎናጸፍ ቢሞክሩ ደግሞ በኑሮአቸው ማባከንንና በትዳራቸውም አለመስማማትን ሊፈጠር ይችላል፡፡፡፡ እነርሱ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው የቤተሰብ ኃላፊነት ስለነበራቸው ከአሬማውያን ሴቶች ይለያሉ፡፡ ከባሎቻቸው ጋር በፍቅር ገመድ የታሠሩ በመሆናቸው ውበታቸው ለባሎቻቸው ነው፡፡ ብዙን ጊዜ የትዳር ጓደኛችንን በምን እናስደስተው ወይም በምን እናስደስታት ለሚለው የብዙዎች መልስ የሚሆነው ልብስ በመግዛት ልዩ ልዩ ስጦታዎችን በማበርከት ወዘተ ነው፡፡ ይህ አባባል እውነት ነው ግን የትኛውም ስጦታና ምግብ ፍቅርን አይተካም፡፡ ሰው የሚፈልገው ምግብና ጨርቅ ሳይሆን ፍቅር ነው፡፡ ሐዋሪያው ሦስት ዓይነት የውጭ ማጋገጫ መንገዶችን ይከለክላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ጸጉርን መሸረብ ሲሆን ሁለተኛው ወርቅን ማንጠልጠል ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ልብስን መጎናጸፍ ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን ስንመለከት መልበስን፣ የወርቅ ጌጥን ፣ ጸጉርን መታጠብና ማማርን እግዚአብሔር አይቀበልም እያለ ነውን; ወይም ደግሞ ወርቅ ማድረግና በልብስ መሸለም ነውር ነው እያለ፣ ጸጉርን መሽረብን እየከለከለ፣ ኃጢአት ነውና ወርቅን አታድርጉ የወርቅንም ጉትቻ ከእናንተ አርቁ እያለ ነውን; በፍጹም አይደለም፡፡ ነገር ግን ወርቅን ማንጠጥልጠል አይሁንባችሁ የሚለው የሐዋሪያ ምክር ክርስቲያን ባለትዳሮች ውጭአቸውን ከልክ በላይ ሊያደምቅ በሚችል ልብስ ራሳቸውን ለመሸለም ሲሉ የሚያደርጉት ጥድፊያ ለመንፈሳዊ ነገር ደንታ ቢሶች እንዳያደርጋቸው የሚያሳስብ ምክር እንጂ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የነበሩ የጥንት ሰዎችን ስንመለከት እነ ርብቃና አስቴርን የመሰሉ የእምነት ሰዎች ከወርቅ በተዘጋጀው ጌጣጌጥ ተውበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ አመንዝራዎች ሴቶችና ጋለሞታዎች ውድ በሆነ ዋጋ ወርቅን በመግዛት ራሳቸውን መሸለምን ምልክታቸውና መታወቂያቸው አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ እግዚአብሔርንም እንዳያመልኩ እንቅፋት ሆኖባቸው ነበር፡፡ የምንምበላው የምንጠጣውና የምንለብሰውና እንዲሁም የምናጠለጥለው ጌጥ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም፡፡ የእምነትን ኑሮ ስንኖር ፣ ብንበላም ብንጠጣም፣ ብንብስብም ሆን ወርቅን ብናጠለጥል ለመንፈሳዊ ህይወታችን ትልቅ ትኩረትና ጥንቀቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ከጌታ ከኢየሱስ ጋር ያለንን መንፈሰዊ ትሥሥራችንን የሚያበላሽብንን ማንኛንም የውጭ ማማር ልንንቀው ያስፈልጋል፡፡ በተጨማርም የምንለብሰው ልብስ፣ የምንሠራው ሽሩባና የምናንጠለጥለው ወርቅ ለትዳር ጓደኛችንና ለልጆቻችን ወይም ለቤተሰባችን ያለንን ፍቅርና ኃላፊነት ካበላሸብን አደጋ መጣብን እንበል፡፡ ክርስቲያን እሕቶቻችን በሁሉም በኩል የቅድስና ኑሮን እንዲታይባቸው እግዚአብሔር ይፈልጋል፡፡ እንደ ክርስቲያን ሴት እኔ ምን ዓይነት ወርቅ ማድረግ ይገባኛል፣ ምን ዓይነትስ ሽሩባ ልሠራ ይገባኛል፣ ለቤተሰቤም ፣ ለእኔም ፣ እንዲሁም ለትዳር አጋሬ ደስ የሚያሰኘን ምን ዓይነት ልብስ ብለብስ ነው ማለት አስተዋይነትም ክርስቲያናዊ ጨዋነትም ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆን ልብስ እንዳለ ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር የማይሆኑ ብዙ ልብሶች እንዳሉ አይኖች ይመልከቱ፡፡ የሚያዩትን ሌሎች ሰዎችን የሚማርኩ ልብሶች እንዳሉ ሁሉ ሰዎችን ለአላስፈላጊ ፈተና የሚያጋልጡ አለባበሶች እንዳሉ ያልተገነዘበ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ደስ ያለንን ብቻ ሳይሆን ልክ የሆነውን ልንለብስና ልናደርግ እንደሚገባን ሁላችንም የምንስማማ ይመስለኛል፡፡ እንመለስበታለን !

Friday, February 23, 2018

አራቱ የኢትዮጵያ ሕመሞች


ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት አገራችን ኢትዮጵያ ፈውስ ያስፈልጋታል በሚል አንድ ጽሑፍ አዘጋጅቼ በማኅብራዊ ገጽ ላይ መለጠፌ ይታወቃል። የጽሑፌ ርዕስ “ምድራችሁን እፈውሳለሁ ይላል እግዚአብሔር” የሚል ሲሆን ብዙዎች አንብበውታል። የጽሁፉ ቁልፍ አሳብ ምድራችን/ አገራችን/ ኢትዮጵያ ያጣችሁ በረከት ሳይሆን ፈውስ ስለሆነ ለፈውሷ እንጸልይ የሚል ነበር። ምድራችን መታመሟን ሁሉም ያውቀዋል። እግዚአብሔር አምላከ “ምድራችሁን እፈውሳለሁ” ያለው ምድር በሕመም ስለምትሰቃይ ነው። የአገራችን ሕመም ቀስ በቀስ የውስጥ ሰውነትን እያዳከሙ በጊዜ ቆየታ ሕይወት እንደሚቀጥፉ ሥር የሰደዱ ሕመሞች ነው። እነዚህ chronic በመባል የሚታወቁ ሲሆን ይኸውም በሰውነት ውስጥ ሥፍራ ይዞ ቀስበቀስ አካልን የሚያደክም አደገኛ የሕመም እድገት ነው። ሰውን የሚገድሉ ሥር የሰደዱ ሕመሞች ናቸው።
እንደዚሁም ሁሉ ምድርም ለሕይወት በሚያሰጋ በከባድ በሽታ ትታመማለች። ስለዚህም ነው እግዚአብሔር ምድራችሁን እፈውሳለሁ ያለው። ሰው ሲታመም ወደ ሐኪም ቤት ይወሰዳል። ምድር ስትታመም ግን ከመለኮት ጣልቃ ገብነት በቀር ሌላ ሐኪም ቤት የለም። ምድር ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ምን ሐኪም የላትም። መድሃኒቱም ያለው በእርሱ እጅ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ መታመሟን ያወቅነውም ብዙ ቆይተን አሁን በቅርቡ ቢሆንም እኛም አብረን እየታመምን ነው። ስለዚህ ይህቺን አገር የሚወዳት ሁሉ ሊጸልይላት ይገባዋል። የአገሬ ፍቅር አለኝ የሚል ማንም ከሚዘፍንላት ይልቅ ፣ ከሚዘምርላትም ይልቅ ፣ አሁን የሌላትን መንፈሳዊ ስም ከሚስጣት ይልቅ ሊጸልይላት ይገባዋል። ስለዚህች አገር ማቅ ለብሰን ፣ አመድም ነስንሰን ፣ ከካህን እስከ ምዕመን ቢቻል በር ዘግተን ፣ ከእህል ከውሃ ተለይተን ማልቀስና መቃተት ያለብን ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። ሕመሞቿን በቀላል አማርኛ ፣ እንደሚከተለው እንድገልጽ ይፈቀድልኝ።
፩. በዘርና በጐሳ የሚከፋፍል ሕመም።
እስትሮክ አንዱን የአካል ክፍል ለይቶ የሚጐዳ የህመም ዓይነት ነው። ይህ ቀኙ እየሠራ ግራውን እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርግ ወይም ግራው ደህና ሳለ የቀኙን በኩል ከላይ እስከታች የሚያሽመደምድ በሁሉ የተረገመ በሽታ ነው። ። ይህ ዓይነቱ በሸታ ቶሎ ባይገድልም የሕመምተኛውን የመዳን ተስፋ ያጨልማል። እንደዚሁም የአገራችን ሕመም በዘር በጐሳ፣ በወገን፣ በክልል የሚከፋፈል እንደ ስትሮክ ዓይነት ነው። ሌሎች የበለጠጉና ያደጉ አገሮች የጐሳ ፖለቲካን /Ethnic politics/ በጐጂነቱ ፈርጀው ወደ እንጥሮጦስ ከጣሉና ዳግም ተንስቶ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ጥፋት እንዳያመጣ መንገዱን በጥርብ ድንጋይ ከዘጉ በኋላ ይህ አደገኛ ፖለቲካ በአገራችን የዕድገት፣ የዴሞክራሲና የልማት አምድና ምሶሶ ተደርጐ ተወስዷል። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የቋንቋዎች፣ የባህሎች ፣ የዘርፈ ብዙ ማህበራዊ እሴቶች ባለቤት መሆኗ ከፍሎ ለሚያሰቃይ በሽታ ምቹ አድርጐአታል። የአገራችን ሕዝቦች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት እንደጌጥ እየቆጠሩ እርስ በእርሳቸውም እየተቻቻሉ ፣ በአካባቢቸውም ያለውን ግብአት በጋራ እየተጠቀሙ ያለ አንዳች መገፋፋት ለዘመናት መኖራቸው፤ ሰሜኑ ከደቡቡ ሕዝብ፣ ምሥራቁ ከምዕራቡ፣ የመሀሉ ከዳሩ ሕዝብ ጋር ተረዳድተውና ተከባብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት አገር መሆኗ እውን ቢሆንም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ባመጣብን ከፋፋይ ፖለቲካ የተነሳ ሕዝቦቿ እርስ በርሳቸው ከመከፋፈልም አልፎ እስከ መገዳደል ደርሰዋል። ሥር የሰደደ በሽታ የሰውን የቀድሞ መልኩን እንደሚለውጠው ሁሉ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ድሮ የምትታወቀዋ በታሪክ ስለ እርሷ የምንሰማው፣ምሁራን ያስቀሩልንን ታሪክ የምናነበው ሳይሆን ታሪኳ ተቀይሮ፣ መልኩዋም ጠፍቶ ፣ ከቀደሞው ታሪክ ጋር የማይገጥም እንግዳ ነገር እንድናይ የሚያደርግ ሕመም ሥር እየሰደደባት ነው።
በአገሪቱ ያለው እያንዳንዱ ብሔር መነሻ ማንነት ቢኖረውም በቅድሚያ ሰው መሆኑን ያምናል፣ከዚያም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያምናል። አማራው አማራ ነኝ ቢልም ኢትዮጵያዊነቱን አይክድም ነበር። የበላይ ዘለቀ ልጅ ጐጃሜ ነኝ፣ ደግሞም ምንጃሬ፣ ሸንኮራ ነኝ ዘራፍ፣ዘራፍ ዘራፍ ቢልም ኢትዮጵያዊነቱን ሳይክድና ሳይለቅ ከሌላው ሕዝብ ጋር እርሱም አብሮ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ያምን ነበር። ሌላው ብሔር ቢሆንም እንደዚያው ነው። የአባጁራፍ ልጅ ኦሮሞ ነኝ ፣ የካዎ ጦና ልጅ ወላይታ ነኝ፣ የንጉሥ አይማሎ ልጅ ጋሞ ነኝ፣ የንግሥት ፉራ ልጅ ሲዳማ ነኝ ወዘተ ቢልም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ አገሪቱ የጋራችን ነች፣ ወንዙ ሸንተረሩ ተራራው፣ ጋራው፣ ሁሉ የጋራችን ነው፣ እያለ በልዩነቱ ውስጥ ያለውን ውበትና ጣዕም እያጣጣመና እያደነቀ፣ አንዱ የሌላውን ሕመም እየታመመ፣ በደስታውም አብሮ እየተደሰተ፣ ኢትዮጵያን በጋራ ተሸክሞ የኢህአዴግ መንግሥት አገሪቱን እስከሚቆጣጠርበት ጊዜ አደረሳት። ያውም ክብሯ ዝቅ ሳይል፣ ዳር ድንበሯ ሳይደፈር፣ አንድ ስንዝር መሬት ለጐረቤት አገር በድርድርም ሆነ ጦርን በመፍራት አሳለፎ ሳይሰጥ ነው ታዲያ! የኢህአዴግ መንግሥት ምድሩን ማስተዳደር ሲጀምር አፉን የፈታው “መገንጠል” ፣ “ክልል”፣ “የራስን መብት በራስ መወስን” በሚሉ ቃላቶች ነው። ቃላቶቹ/ አሳቦቹ ልበላቸው/ ለኢትዮጰያ ሕዝቦች አንድነትና እኩልነት ፣ ለመብታቸውም መከበር ዘብ የሚቆሙ ቢመስሉም አሁን ለሚታየው መከፋፈልና መናቆር የተጣሉ የመሠረት ድንጋዮች ናቸው። ቃላቶቹ አሳችና ግራ አጋቢዎች ናቸው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሕዝቦችን ትሥሥር ለመበጣጠስ የቻለው በእነዚህ የመሠረት ድንጋዮች ላይ ቆሞ ነው። ይህ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ አንዱን ብሔር ከሌላው፣ አንዱን ክልል ከአንዱ ጋር የሚያባላው እነዚህን በሽታ አምጪ ሕዋስ የሆኑ ቃላቶችን በምድሪቱ ላይ በመበተን ነው። ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ድረስ ተቻችለው የኖሩ፣ ተሳስበው፣ ተከባብረው፣ ተጋብተውና ተዋልደው ፣ በሁሉም ማኅበራዊ ጉዳዮች አንድ ሆነው በመልካም ትሥሥር ለዘመናት የቆዩ ሕዝቦች እርስ በርሳቸው ለመጐሻሸም፣ ለመገዳደል ፣ ለመፈነቃቀልና ለማሳደድና ለመሰደድ ከተጋለጡ ይኸው የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ እያስቆጠሩ ነው። ለዚህ ሕመሟ መድኃኒት ያልተገኘላት አገራችን ሕመሟ እየጠናባት በመሆኑ መድኃኒትና መላ ፣ መፍትሔም ያስፈልጋታል። ከመጀመሪያውም መፍትሔ ሊገኝ በማይችል ሁኔታ መርዙ ስለተቀነባበረና በየቦታውም ስለተቀበረ ሕመሟ እየባሰባት መጣ። የኢሀአዴግ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት እንዳይኖሩ በቋንቋና በብሔር እንዲከፋፈሉ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሳለው የአገሪቱ ካርታና ክልላዊ መዋቅሩ እንኳ ቢታይ ብሔርን ባህልንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወደፊት አንዱ ከሌላው ለመገንጠል እንዲያመቸው ሆን ተብሎ የተሠራ ተንኮል መሆኑ ሳይገባን ኖረናል። በአሁኑ ጊዜ መቻቻልን ትተው ወንድም ወንድሙን በጦር እያሳደደ፣ ክልሌ ስለሆነ በዚህ አካባቢ መኖር ፣ መንቀሳቀስ ፣ መሥራት ወዘተ አትችልም እያለ አብሮት የኖረውን፣ አብሮት ያደገውን ያሳድደዋል። ሁለት ሰዎች ቢጣሉና አንደኛው ቢጐዳ እነማን ናቸው የተጣሉት ተብለው በሰውነታቸውና በስማቸው መሠረት መጠየቅና ማስረዳት አግባብ ሆኖ ሳለ አሁን የሚጠይቀው ብሔር ፣ ዘር ወይም ክልል ነው። ይቀጥልና የዚህ ብሔር የዚኛውን ብሔር ደበደበ፣ ወይም የዚህ ብሔር የዚኛውን ብሔር ገደለ ይባልና ጠቡ የብሔር ይሆናል። አሁንም ይቀጥልና ይህ ብሔር ከዚኛው ብሔር ጋር ተጣላ፣ ከዚሀ ብሔር ይህን ያህል ሰው ሞተ፣ ይህን ያህል ሰው ተጐዳ የሚል ዜና ይሰራጫል። ወያኔ ሕዝባችንን እጁን ይዞ ሀ ሁ ሂ እያለ ፊደል ያስቆጠረውና ያለማመደው ይህንን ክፉ ሥራ ነው። የግለሰቦቹ ጠብ ዕለታዊ ጉዳይ የግል እንጂ የብሔር ጠብ አልነበረም ግን የተዘረጋው መዋቅር እና የተቀመመው የፖለቲካ መርዝ ይህንን መሰል በሽታ በሕዝባችን ላይ አመጣ። እውነት ለመናገር አንዱ ሕዝብ አብሮት ከኖረው፣ በባህል ፣ በሃይማኖት በጋብቻ ወዘተ ተሳስሮ፣ ተቀላቅሎ፣ አንዱ ከሌላው ጋር ተጋብቶና ተዋልዶ ለዘመናት ከኖረበት ከሌላው ህዝብ ጋር መጋጨትም ሆነ መቃቃር እንደሚገባው የሚያምን ኢትዮጵያዊ የለም። የአማራ ሕዝብ ከሮሞና ከሌላው የሲዳማ ሕዝብ ከወላይታ ህዝብ ጋር ፣ ጉጂ ከቡርጂ ጋር መተላለቅ አይገባውም ነበር። በቅርቡ እንኳ በዝዋይ ከተማ በሁለት ኢትዮጵያውያን መካከል ጠብ ቢፈጥር የኦሮሞና የወላይታ ሕዝቦች ግጭት ተደርጐ መወሰዱ ፣ አሁን ደግሞ በምሥራቁ የአገራችን ከፍል የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ቀውስ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ሕመሙ በኢትዮጵያ መላ ሰውነቷ ላይ ስለተሠራጨ ይህ አሳዛኝ ነገር ሊሆን ቻለ። የኢህአዴግ ወያኔ መንግሥት መሪዎች አሸናፊውን ለመለየት በመሀል እንዳለ ታዛቢ ነገሩን በትዝብት ያዩታል ወይም እንደ ተመልካች ይዝናኑበታል እንጂ መፍትሔ አይሰጡበትም፤ የጸጥታ ሃይሉም ሬሳ ቆጥሮ ሪፖርት ያደርጋል እንጂ በሚተላለቀው ሕዝብ መካከል ገብቶ የሕዝቡን ዋስትና አያረጋግጥም፣ ምክንያቱም ፖሊቲካው ሲጠነሰስ የተፈለገው ይኸው ነውና። ይህ በሽታ ኢትዮጵያን እንዳያጠፋት የተቻለውን መፍትሔ ሁሉ መፈለግ ያሻል። ከመፍትሔዎቹ አንዱና ቀዳሚው በእግዚአብሔር ፊት ማልቀስ ነው። ያለዚያ አሁን የተበተነው ሕመም አመንጪ የፖለቲካ ሕዋስ አካሉዋን በጣጥሶና ገነጣጥሎ ይጨርሰዋል። መንግሥት እንደሆነ የኢትዮጵያን መሬት ሲያሻው ለጐረቤት አገር እየሸጠ ፣ ሲያስፈልገው ከመሃሉ አርሶ አደሩን አፈናቅሎ መሬቱን ለባዕድ እየሸጠ ሕዝባችን ላይ ድራማ ይሠራበታል፣ ቁማርም ይጫወትበታል። በምዕራቡ በኩል አንድ የአካል ክፍል ተቆርሶ ወደ ሱዳን በኩል ወድቋል። የነገ ተረኛ ማን እንደሆነ አናውቅም።
አካልን የሚደመስሰው የፖለቲካ ሕዋስ በቤተመንግሥት ብቻ ሳይወሰን ወደ ሃይማኖቱ ውስጥም መግባቱ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ፣ በሕይወትም የመቆየቷን ጉዳይ የበለጠ አሳሳቢ አድርጐታል። ቸር ወሬ ያሰማን እንጂ ቤተክርስቲያንም በዘር ፣ በጐሳ ከተከፋፈለች ጊዜ የለውም። እንዲያውም ፈጥና ራሷን የሰባበረችው ቤተ ክርስቲያን ነች። በብሔር ወገንተኝነት ላይ የተመሠረተ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ አለ። መንግሥትም ለመከፋፈል ዓላማው እንዲያመቸው በሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የራሱ ካድሬዎች ሰግስጓል። በየእምነት ተቋማት ውስጥ የኢህአዴግ የደህንነት ካድሬዎች አሉ። የፖለቲካ መዋቅሩ ከመንግሥት ተቋማት እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ድረስ ተዘርግቷል። የወንጌል ቃል በሚገለጥበት ሥፍራ ላይ ቆመው መንግሥትን የማሞካሸት የሚቃጣቸው የቤተክርስቲያን መሪዎች ጥቂት አይደሉም።
የሕመም አምጪው ሕዋስ በአገር ቤት ብቻ ሳይወሰን ባህር ተሻግሮ በመምጣት ሕዝቦቿን እያተራመሳቸው ነው። ከቤተሰቦቻቸው ጋር በልጅነታቸው ከአገር የወጡ ልጆች የመጡበትን አገር ሲናገሩ ከምሥራቅ አፍሪካ ፣ ከኦሮሚያ ነው የመጣነው ሲሉ ከኢትዮጵያ ናችሁ ሲባሉ አይደለም ከኦሮሚያ ነው ይላሉ። እንግዲህ እነዚህ ልጆች ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳለች አያውቁም ማለት ነው። ከእነርሱ በኋላ የሚመጣው ትውልድ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንደነበረች አድርገው እንደ ታሪክ መናገራቸው አይቀርም። ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት አንዷ እንደነበረች የማያውቅ ወጣት ብዙ እንደነበረ ሁሉ ኦሮሚያ ፣ አማራ፣ ሐሬሪ፣ ቤንሻንጉል ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ ወዘተ የሚባሉት አገሮች እንደ አንድ አገር በአንድ መንግሥት አስተዳደር ሥር ነበሩ እያሉ ማውራታቸው አይቀሬ ነው። ይህ የዘመኑ መንግሥት ያመጣብን ገዳይና ኢትዮጵያን በቁሟ እያለች ሰውነቷን አፈራረሶ የሚያጠፋት በሽታ ነው።
ወያኔ ካመጣው የፖለቲካ ቀውስ የተነሳ ሰዎች በአገሪቱ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል የመዘዋወር ነጻነታቸው ጠባብና ግዱብ ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ከደቡብ ክልል ወደ አማራ ክልል ሄዶ መኖር ፣ መሥራት፣ መነገድ ይችላል? ከሰሜንም ክልል ወደ ምዕራብ ክልል ሄዶ በነጻነት መኖር የሚችልበት የዜግነት መብትም ሆነ የሕግ ዋስትና አለው? ኢትዮጵያ አለኝ የምትለው ዲሞክራሲ ይህንን ያረጋገጣል? ካልሆነ ለዚህ ሰው ኢትዮጵያ የምትባለዋ አገር የቷ ነች? የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ዴሞክራሲ የሚረጋገጠው በሕዝቦቿ አንድነት ከሆነ በተከፋፈለ ህዝብ የአገር ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ሊረጋገጥ የሚችለው እንዴት ነው? እስቲ ከአሜሪካ ፖለቲካ እንማር! አሜሪካ ከሁሉም የዓለም ዙሪያ የመጡ ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር ብትሆንም አሜሪካውያን ሌላውን ሕዝብ በእኛ ላይ መጣችሁብን በሚል አንድም ቀን ተነስተውባቸው አያውቁም። ሁሉም ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላው በመዘዋወር መሥራት፣ መማር፣ ቤት መግዛት ወዘተ የሚችሉበት መብታቸው የተጠበቀ ነው። በአገራችን ግን ዴሞክራሲ አለ ቢባልም በዴሞክራሲው ተጠቃሚዎቹ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው እንጂ ዜጋው አይደለም። የጐሳ ፖለቲካ ዜጋዎች በአገራቸው ውስጥ በየትኛውም ክልል በነፃነት የመንቀሳቀስና የመኖር ዋስትናቸውን የሚገድብ አደገኛ ሥርዓት ነው። የጐሳ ፖለቲካ ባለበት የሕዝቦች እኩልነት በሕልም ካልሆነ በውኑ አይታሰብም፣ አይሞከርምም። በአገራችን አለ የሚባለው የሕዝቦች እኩልነት በጦርነትና በጭፈራ ቀን እንጂ ሥልጣንን በመጋራት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ወዘተ በማድረግ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ለተወሰኑ ቡድኖች ጥቅም የቆመ፣ የአንዱን ወገን የበላይነትና የሌሎችን የበታችነት( Ethinic inequality)የሚያጎላ ነው። ግደይ በጠገበበት ገመዳ ጨፈረ ነው ነገሩ። የውጭ ኃይላት ወረራና ለዘመናት የነበረው ጦርነት ሊያፈርስ ያልቻለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት በጐሳ ፖለቲካ እያፈራረሰ ይገኛል።
የጐሳ ፖለቲካ የመልካም አስተዳደርም (good governance) እንቅፋት ነው። መልካም አስተዳደር ማለት የአገሪቱን ዜጐች መብትን፣ ምጣኔ ሀብትን፣ ብሔራዊ ዋስትናን፣ የአገር ሉዓላዊነትን፣ የውጭ ግንኙነትን፣ ብዝሃ ህይወት፣ ትምህርትና ጤናን የአገር መከላከያንና ዳር ድንበርን ወዘተ በሚመለከት የሚደረስ ሚዛናዊ ውሳኔ ነው። በዚህ ዓይነቱ ውሳኔ ማዕከላዊ ተዋኒያን/ central figure / መንግሥት ነው። መልካም አስተዳደር ቢያንስ ቢያንስ ስምንት ባሕሪያት አሉት። አሳታፊነት Participatory/፣የጋራ ስምምነት/Concensus/ ተጠያቂነትaccountable፣ ግልጽነት transparency ፣ ምላሽ ሰጪነት rsponsiveness፣ ውጤታማነትና ብቃት effectiveness and efficiency ፣ ሁሉን ያማከለና በእኩልነት የተከተለ equitable and inclusiveness ፣ በውሳኔ አሰጣጡ ወቅት የህግ የበላይነትን የሚከተል follows the rule law,፣የአናሳዎችን አመለካከት የሚቀበል፣ የተጠቂዎችን ድምፅ የሚሰማና የማኅበረሰቡን የአሁኑናን የመጻኢውን ጊዜ ፍላጐት አጥኖ መላሽ የሚሰጥ ነው /the views of minorities is taken into account and the present and future need of the society are heared in decision making/ ። በቃላት ደረጃ በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ና የሕግ የበላይነት እንዳለ በመንግሥት በኩል ቢወራም አመራሩ ግን የአምባገነናዊ ነው። ስለዚህ ይህች አገር መላ እሷነቷን እየፈራረሰ ካለው ከዚህ በሽታ ድና በሕይወት እንደትቀጥል፣ ከሕምሟም ነጻ እንድትሆን የመለኮት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋታል። ይህም እንዲሆን ሁሉም ወደ አምላኩ መጮኸ ያለበት ጊዜ አሁን ነው።
፪. ሥርቆት፣ ጉቦና ዝርፊያ
ሌብነትና ጉቦ የአገራችን መጣኔ ሀብት የሚጐዳ ሕመም ነው። ምድሪቱ ታማለች ስንል ኢኮኖሚው ታሟል ማለታችን ነው። ይህ ጉዳይ በአንድ ወቀት በኢትዮጵያ ፓርላማ ተነስቶ ጥልቅ ውይይት እንደተደረገበት ሁሉም ኢትዮጰያዊ ያውቀዋል። ገዥው ፓርቲ የኢትዮጰያ ኢኮኖሚ ጤናማ ነው ሲል ተቃዋሚዎች ደግሞ ኢኮኖሚው በጣም ታማሚ ነው። እንዲያውም አንድ ቀን ተዝለፍልፎ ሊወድቅ ሁሉ ይችላል ብለው ምላሽ ሰጥተዋል። ወያኔ ወደ አገራችን እንደገባ የመጀመሪያው ያደረገው ነገር ቢኖር የአገሩን አንጡራ ሀብት እየዛቀ በሰዎች ኪስ መክተት ነው። ሕዝባችንን ያማረረ ያጐሳቆለ፣ ቢያንስ የዜግነት መብቱ በአግባብ እንዳይከበር ያደረገ ፣ ምድሪቱን ከዳር እስከዳር የሸፈነ አደገኛ ሕመም ቢኖር ጉቦና ሥርቆት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ጉቦ ወይም ሌብነት አይልም። ኪራይ ሰብሳቢነት ይለዋል። ካልሆነ ስኳር መላስ ይለዋል፣ ወይም ሙስና ይላል። ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን እዋጋለሁ ይላል። ግን ሙስናውና ጉቦው መጠኑን እየጨመረ ሄደ እንጂ መፍትሔ አልተገኘለትም። በጉቦውና በሙስና የተዘፈቁት የመንግሥት አመራር አካላት፣ የፖሊቲካው ካድሬዎች፣ እና ገዥ ፓርቲ ያስቀመጣቸው የመመሪያ ኃላፊዎች በመሆናቸው ሕመሙ መድኃኒት ያልተገኘለት በዚህ ምክንያት ነው። እንዲያውም ሕመሟ ከጊዜ ወደ ጊዜም እየባሰ ሄደ። በቴሌቭዥኑና በራዲዮ ሙስናን እንዋጋ እያሉ ሕዝቡን ያጃጅላሉ። ሕዝቡ ጉቦ አይቀበል፣ መሬት የሚሸነሽነውና የሚሸጠው ተርታው ሕዝብ አይደለም፣ ወያኔና የወያኔ ካድሬዎች እንጂ! የህዝብና የመንግሥት ገንዘብ እየዘረፉ ኪሳቸው እየከተቱ በአጭር ጊዜ ሚሊየነር እየሆኑ ያሉትን ቁልፍ መሪዎችን ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡና እጃቸውን እንዲሰበስቡ መናገር ያለበት ለእነርሱ ሆኖ ሳለ በሌቦች እየተዘረፈ ያለውን ሚስኪን ሕዝብ ሙስናን ተዋጉ ይላል። ቀልድ ቢባል በሕዝብ ላይ መቀለድ አንድ ቀን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም። የኢህአዴግ መንግሥት ጠላትን አሸንፌአለሁ የሚል፣ ከራሱ አልፎ የሌላውን አገር ሰላም አስጠብቃለሁ የሚል፣ በአፍሪካ ቀንድ በጐም ይሁን አሉታዊ ተጽዕኖ የማምጣት ብቃት አለኝ የሚል መንግሥት ነው። ይህ ሁሉ ብቃት ኖሮት ሀዝቦቿን የሚቦጠቡጠውን ሙሰኛ አደብ እንዲገዛ ያላደረገው አቅም አንሶት ሳይሆን መንግሥትራሱ ሙሰኛ ስለሆነ ነው። ያለ ጉቦ የሚፈጸም ጉዳይ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እንደሌለ በአመራር መዋቅሩ ከላይ እስከታች ያሉ እያንዳንዱ ያውቃል። የትኛውም ቀላል ይሁን ከባድ ጉዳይ ያለ ጉቦ አይከናውንም። የሚከናወንላቸው ለወያኔዎችና ለፖለቲካ ድጋፊዎች ብቻ ነው። አገሪቱ የእነርሱ እንጂ የዜጋው አይደለችም። መነገድ የሚችሉት ወያኔዎችና የፖለቲካው ደጋፊዎች ብቻ ሲሆኑ ንግዳቸውን ሲነግዱም ሆነ ሲሸጡ ቀረጥ የማያስበረግጋቸው ናቸው። ዜጋው ግን የንግድ ፈቃድ ቢኖረውም ያንኑን ለማግኘት የሚከፍለው ጉቦ ሌላ ድርጅት ሊያራምድ ይችላል። በመሣሪያ አስፈራረቶም ሆነ ሰዓት እላፊ አወጆ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት ማጋዝ ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። እግዜር የለሹ የደርግ መንግሥት ወንበዴ የሚል ስም የሰጠው ለዝርፊያ ያለውን መቋመጥ ስለታዘበው ይሆናል። አሁን ምድራችን በዝርፊያ የታምሰች ናት። እናት አገራችንን ብንወዳትም፣ በሰፈነባት እንደ ባህል እየተገነባ ባለው ሌብነትና ዝርፊያ እናፍራለን። ሌባ እናት በሰረቀች ቁጥር ልጆቿ ይሸማቀቃሉ፣አንገታቸውንም ይደፋሉ።
ነቢያት ስለ ኢኮኖሚው እድገት ይናገራሉ። መጻሕፍትም እየተጻፉ ናቸው። በየመድረኩ የምንሰማው ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርካታል የሚል ነው። አንዳንዶቹ ሌሎች የሚሉትን ሰምተው እንጂ በእርግጥም እግዚአብሔር ተናግአቸው አይደለም። በአገራችን የምንሰማው ትንቢት አብዛኛው የነቢያቶቹ የግል ምኞታቸው ነው እንጂ እግዚአብሔር የሚሰጣቸው መልእክት አይደለም። ምኞትና መልእክት ይለያያል።
3ኛ. ውሸትና ማታለል፡
መንግሥታችን ልማታዊ ነኝ ይላል ግን አይደለም። ዴሞክራት ነኝ ቢልም ዴሞክራሲው የማስመሰል፣የፖለቲካ ሽፋን ለማግኘት ሲል የሚያደርገው የቃላት ቅመማ ነው። በአገራችን ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ቢኖርም ያ ሕገ መንግሥት የበላይ አይደለም። በአንድ ቀን ጉቦ ሊናድ የሚችል በአሸዋ ላይ እንደተሠራ ቤት ነው። እውነት እንነጋገር ካልን በአገራችን ላይ የመሪዎችና የካድሬዎች የበላይነት እንጂ የሕግ የበላይነት የለም። የኢሀአዴግ መንግሥት የሕገ መንግሥቱን ሥርዓት በሃይል ለመናድ የሚሹ ኃይሎች እያለ በሌሎች ላይ የሚፈረድ ቢሆንም ውሸትን እውነት አስመስሎ በመናገር የኢትዮጵያ መሪዎችን የሚያክል የለም። አንዱ ጄኔራል ሲናገሩ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የወያኔን ሠራዊት ይወደዋል ያፈቅረዋል ማለታቸው ብቻውን ለዚህ ማሳያ ነው። ክ1997 ምርጫ ጋር በተያያዘ በተነሳው ረብሻ በመንግሥት ታጣቂዎች የተገደሉ ስዎች ጉዳይ ሲነሳ የመንግሥት ባልሥልጣናት መልስ ሲሰጡ ሰዎቹ የሞቱት ባንክ ሲዘርፉ ነው ማለታቸው ሌላው ማሳያ ነው። አፈሩን ገለባ ያርግላቸውና የሞቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ደመወዛቸው ስድስት ሺህ ብር ብቻ ስለሆነ ባለቤታቸው ያንን እንደምንም አብቃቅተው እንደሚኖሩና በዓለም ላይ የመጨረሻ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሰው ማነው ቢባል እኒህ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን መስማታችን እንደ ተጨማሪ ማሳያ እንውሰድ። በምዕራቡ በኩል መሬት ለሱዳን ሊሰጥ የኢትዮጵያ መንግሥት እየተፈራረመ ያለው ለምንድነው ሲባል ለሱዳን ምንም መሬት አልተሰጠም፣ አንድም የኢትዮጵያ ገበሬ ከቦታው አልተፈናቀለም ማለቱ ሌላው ተጨማሪ ማሳያ ነው። መንግሥታችን ይህን ሁሉ እያለ መሬቱን ግን አሳልፎ እያሰጠ ነበር። ቴሌቭዝኑና ራዲዮ ቢሆን የኢህአዴግ መንግሥት ልሳን ስለሆነ እውነት ተናገረ ቢባል ሰዓት ብቻ ነው። ፖለቲካ በራሱ የቆሸሸ ጨዋታ ቢሆንም አሁን አመራር ላይ ያለውን መንግሥት ተከትሎ ወደ አገራችን የገባው የውሸት መንፈስ ግን የትም የሌለ ነው።
4ኛ. ሰብአዊ መብት ረገጣ
በዓለም አቀፍ ደረጃ የታውቁ የሰብአዊ ተሟጋቾች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን የመብት ረገጣ መስማት እጅግ የሚዘገንን ነው። በተለይም ከብሔራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት በሚወስደው ከመጠን በሚያልፍ እምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹህ ዜጎች ሕይወት ይቀጠፋል። የኢህአዴግ መንግሥት ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ ወዲህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መገመት ከሚቻለው በላይ ነው። በሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወቅት ብቻ ሕይወት የመንግሥት ታጣቂዎች በወሰዱት ተመጣጣኝ ባልሆነ የግፍ ርምጃ ክ500 በላይ ንጹሐን ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል። አምኔስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሚገልጸው ከ2015( እ ኤ አ) ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ 800 ስዎች ተገድሏል። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት አስታጥቆ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሰማራቸው ሠራዊት በንጹሐን ላይ የሚያደርሱት ከመጠን ያለፈ ጥቃት ዓለምን ሁሉ ያንገሸገሸ ነው። ምንም የፖለቲካ አቋም የሌላቸውንም ጨምሮ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ያለ ጠያቂ በእሥር ማጎር፣ ማሰቃየት፣ መገረፍ ፣ስብዕናን የሚያዋርዱ ቅጣቶችን ማድረስ ፣ ያሉበት እንዳይታወቅ ማደረግ ወዘተ ይገኙበታል። አሁን ያለ የአገራችን ስብአዊ መብት ረገጣ በየትኛውም ዘመናትና አገዛዝ ያልነበረ መሆኑ ግልጽ ነው።
ይህ በሽታ እየሰፋና መጠኑን እየጨመረ መሄዱ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ይህቺን አገር ከዚህ ችግር የሚያላቅቃት መፍትሔ ፣ የበሽታዋም መድኃኒት ከየት ይመጣ? ከተባበሩት መንግሥታት? ከልዕለ ኃያሏ አሜሪካ? ከአፍሪካ ሕብረት? ወይስ ከአውሮፓ ህብረት? ኢትዮጵያን ለመፍትሔ ፍለጋ በአሜሪካን አገር ከጮኹ፣ መንገድ አጣብበው ኡኡታና እሪታ ካበዙ ዘመን የለውም። አሁን አሁን እሱም ተከልክሏል ወይ እነርሱ ስልችቶአቸው ተውት መሰለኝ ጋብ ብሏል። በሰማይ ንጉሥ በእግዚአብሔር እጅ ግን መፍትሔ አለ። እርሱ በሰዎች ልጆች መንግሥት የሚሰለጥን ነው። ምድራችሁን እፈውሳለሁ ያለው እርሱ ስለሆነ መፍትሔና መላ ፍለጋ በእርሱ ደጅ እሪ እንበል፣ ኡኡታም እናሰማ። እርሱ ምድራችንን የፈውሳታል ፣ ለገዥዎቻችንም ልቦና ይሰጣቸዋል፣ የሕዝባችን እምባና የግፍ የሚፈሰው ደም ያበቃል። የአገራችን ጉዳይ ፈውስ የሚያስፈልገው ሕመም በመሆኑ ለመድኃኒትጥ ፍለጋ መሮጥ አለብን። መድኃኒቱ በጦርነት አይገኝም፣የሃያላን አገሮች ቢሮ በር ላይ ተሰባስበው እሪታ በማሰማትም አይገኝም። መድሓኒቱ እንዲገኝ በፍጹም ልብ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ፊቱን ስንፈልግ ብቻ ነው። የአገራችን ፈውስ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ ከሌላ ቦታ ከየትም አይመጣምና። እግዚአብሔር አገራችንን የጐሳ ፖለቲካ፣ ሥርቆትና ዝርፊያ፣ውሸትና ማታለል እና ሰብአዊ መብት ረገጣ ከተባሉት ሥር የሰደዱ በሽታዎች አገራችንን ይፈውሳት! አሜን እንበል።

LikeShow more reactions
Comment
Comments
Workneh Koyra Pastor, it is so powerful and absolutely right. May the Lord heal our land and bless our country.
Manage


LikeShow more reactions
Reply8w
Silas Amenta Belete እውነትን በመግለጥ ላይ የተመሰረተውን መጣጥፍህን በጣም እወደዋለሁ ሸክምህን እጋራዋለሁ ሁሉን ለሚችል ጌታ እንደ ግለሰብና እንደ ቤተክርስቲያን በፀሎት ማስታወቅ ይጠበቅብናል ጌታ ይባርክህ መጋቢ ሳሚ
Manage


LikeShow more reactions
Reply8w
Jara Tekleab Pastor, you are right to the point and well explained. I hope our country will heal from these 5 Chronic deceases. May God give all Ethiopians his blessing to love one another and unite.
Manage


LikeShow more reactions
Reply8wEdited

Thursday, May 11, 2017

የተዋረድን ቢመስለንም የክብር ቀን ይመጣል፡፡

                                                            ከመጋቢ ሳሙኤል ሾንጋ

ይህንን ጽኹፍ ለማዘጋጀት ከመጀመሪያው ዕቅድ አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን በየ15 ቀኑ እየጓዝኩ በሚሰብክባት የሰውዝፍልድ ሚቺጋን ኢትዮጵያ ወንጌጌላዊት ቤክ አባልና አገልጋይ የሆነች እህት በራዕይ መጽሐፍ 11 ፡ 4 ላይ ስለሚገኙ ስለ ሁለት ወይራዎች ምስጥራት እንድነግራት ስለጠየቀችኝ ለእርሷ ምላሽ እንዲሆን ብዬ ያዘጋጀሁትን ምላሽ ነው አሁን የማቀርብላችሁ፡፡ መቼም በመድረክ ማገልገል በተለይም ቃሉን እየተረጎምን የምናስተምር ከሆነ ከአገልግሎት በመልስ ሌሎች ክፍሎችንም እንድናብራራላቸው የሚጠይቁ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፡፡ ይህንን ክፍል እንዳብራራላት የጠየቀቺኝን እህት እያሰገንኩ እኔም አሳቡን ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ጭንቀቴ እንደ ፓስተሯ ለምታየኝ ቅንና የቃሉ ወዳድ ለሆነቺው እህቴ የተሳሳተ ነገር እንዳልናገር ነበር፡፡ እንግዲህ አሳቡን፡ካየሁና ለእርሷም ምላሽ ከሰጠሁ በኋላ ለራሴም ትልቅ መልእክት ስለሆነኝ  ጓደኞቼም እንዲያነቡት ባደርግስ ብዬ ስላሰብኩ ይኸውና ከነማብራሪያ ከዚህ እንደሚከተለው ስላስቀመጥኩ ተቋደሱት፡፡
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ለመተርጎም ከባድ ከምንላቸው መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መጽሐፉ አቡቀለም ሲስ ተብሎ ከሚጠሩት መጽሓፍት ጋር የሚመደብ ስለሆነ ነው፡፡ እንደዚህ ባሉት መጽሓፍት አንዳንድ አሳቦች ከተለመደው ውጭ በሆኑ ቋንቋዎች ወይም የአገላለጽ ዘይቤዎች ስለተነገሩ ትርጉሙን በቀላሉ ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡ አቡቀለም ሲስ ማለት መገለጥ ወይም ራዕይ እንደማለት ነው፡፡
በምዕራፍ 11 ቁጥር 4 ላይ የተጠቀሱ ሁለቱ ወይራዎች እነማን ናቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ወደ ምንባብ ክፍል መሄድ ያስፈልጋል፡፡ በታላቁ መከራ ጊዜ በምድር ላይ ሊነሱ ስላሉት ሁለት ምስክሮች ፣ ሁለቱ ወይራዎች ወይም ሁለቱ መቅረዞች የሚናገር ሲሆን የክፍሉን ሙሉ አሳብ ለማግኘት ከቁጥር 1-13 ሙሉን ማበብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የንባብ ክፍል በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙ ሰባት ወዮዎች በሁለተኛው ውስጥ ያለ ነው፡፡ በተለይም ስለ ሁለቱ ምስክሮች ሦስት መሠረታዊ አሳቦችን እናገኛለን፡፡ 1. ስለ ሁለቱ ምስሮች አገልግሎት (3-6)፣ 2. ስለ ሁለቱ ምስክሮች አሟሟት( 7-10) እና 3. ስለ ሁለቱም ምስክሮች ትንሳኤ ( 11-13) እናያለን፡፡ 
ታዲያ እነዚህ ማናቸው የሚለውን ለመመለስ የሞከሩ ብዙ የስነ መለኮት አስተማሪዎችና ተማሪዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእግዚአብሔር ሰዎች በመከራው ጊዜ ስለ እምነታቸው ቢሰደዱም እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ የሚሆን መልእክት መስጠትን አልተወም፡፡ እነዚህ ሁለቱ ምስክሮች በታላቁ መከራ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሕዝብ እጅግ በጣም አስፈላጊዎች ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ክፍል ውስጥ እነዚህ ሁለቱ ምስክሮች እነማን እንደሆኑ አልገለጻም፡፡ ስለዚህ ነው የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተለያዩ ትርጉሞችን መስጠት የቻሉት፡፡ እነዚህን የተለያዩ ትርጎሞቹን እንደሚከተለው አስቀምጬዋለሁ፡፡
1. ሙሴና ኤልያስ ናቸው፡፡ ይህንን ትርጉም የሚከተሉ ሰዎች በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 11 ላይ ያሉ ምስክሮች ሙሴና ኤልያስ በብሉይ ኪዳን ጊዜ ያደርጉ የነበሩትን አይነት ተአምራት ማድረጋቸው ስለተጠቀሰ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የሆኑት ሙሴና ኤልያስ እንደገና ወደ ሕይወት ተመልሰው ይመጡ ይሆናል ብለው ነው የሚተረጉት፡፡
2. ሄኖክና ኤልያስ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ትርጉም መሰረት እግዚአብሔር ሄኖክንና ሙሴን ሳይሞቱ ወደ ሰማይ እንደወሰዳቸው በብሉይ ኪዳን ስለተጸፋና አሁንም እነዚህ ሁለቱ ምስክሮች ከሞት ከተነሡ በኋላ ሳይሞቱ መወሰዳቸው በምንባብ ክፍል ስለተጠቀሰ እነርሱ ይሆናሉ፡፡
3. ኤልያስና ሚልክያስ ይሆናሉ፡፡ መሲሁ ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ኤልያስ ይመጣል ብሎ ሚልክያስ ስለተነበየ ኤልያስና ትንቢቱን የተናገረው ሚልክያስ ራሱ ይሆናል ብለው ያስተምራሉ፡፡
4. ያዕቆብና ጴጥሮስ ናቸው፡፡ እዚህ ሁለቱ ሮማውያን የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያንን ባሳደዱበት ጊዜ የተገደሉና ለከፍተኛ እሥራትና ግርፋት ከዚያም ለሞት የተሰጡ በመሆናቸው በዚህ መከራ ጊዜ ከሙታን ተነስተው የሚያገለግሉ እነርሱ ይሆናሉ በሚል ነው፡፡
5. ቅዱሳን በሙሉ ናቸው፡፡ ይህንን አሳብ የሚሰጡ ሰዎች እንደሚናገሩት ሁለቱ ምስክሮች የተባሉት ሁለት ግለሰቦች ሳይሆኑ ሁለቱን የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ይዘው በመከራ ውስጥ ላሉት ሁሉ የሚመሰክሩ ቅዱሳን ወገኖች ናቸው፡፡
እንግዲህ የምንባብ ክፍሉ ስለ ሰዎቹ ማንነት በግልጽ ባይነግረንም እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን መልእክት በጊዜው ላሉ አማኞች የሚተነብዩ ወንጌሉን የምስራች የሚሰብኩ መሆናቸው ግን እሙን ነው፡፡ አገልግሎታቸውም በትንቢተ ዳንኤል 12፡11 ላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት ለ 1260 ቀናት ወይም 42 ወራት ነው፡፡ ያ ማለት ለሶስት ዓመት ተኩል ያገለግላሉ ማለት ነው፡፡ የዮሐንስን ራእይ በምናጠናበት ወቅት የትንቢተ ዳንኤልንም መጽሐፍን አንድ ላይ ማጥናት ያለብን ለዚህም ጭምር ነው፡፡ የትንቢተ ዳንኤልም መጽሐፍ እንደ ዮሐንስ ራዕይ ዓይነት የአቡቀለም ሲስ የሆኑ መልእክቶች አሉበት ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ክፍል ያሉትን አሳቦች በሦስት ከፍለን እንይ፡፡
1. የሁለቱ ምስክሮች አገልግሎት
ሁለቱ ምስክሮች በሚገለግሉበት ወቅት ማቅ ለብሰው እንደሚሆን ዮሐንስ ይነግረናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ በሙላት በሚሰበክበትና የእግዚአብሔር ክብር በምንቀሳቀስበት ወቅት በአንጻሩ ደግሞ ሰዎች ኃጢአትን ሲለማመዱ ሲያዩ ነቢያትና ነገሥታት ካህናትም ማቅን መልበሳቸው የእግዚአብሔር ፍርድ ስላለ ንስሐ መግባት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ለዚህም ኢሳ 12፡22፣ ኤር.4፡8፣ኤር 6፡26፣ ዮናስ3፡5፣6፣8፣ ማቴ 11፡21ን መመልከት ይቻላል፡፡
የሁለቱ ምስክሮች አገልግሎት ከምርኮው ወደ እሥራኤል አገር ከተመለሱ በኃላ ወደ ተሐዲሶ ለማምጣት ያገለገሉ የዜሩባበልና የካህኑ የኢያሱን አገልግሎት ይመስላል( ዘካርያስ 4፡2-3፣11-14)፡፡ ምክንያቱም እነዚህ መቅረዞች ተብለዋል፡፡ በዘካርያስ መጽሐፍ አንድ
መቅረዝ ያለ ሲሆን በዮሐንስ ራዕይ ግን ሁለት መቅረዞች ተጠቅሰዋል፡፡ በዮሐንስ ራዕይ በራሱ ደግሞ መቅረዝ የክርስቶስን ቤተ ክርሰቲያን የሚወክል መሆኑን ደግሞ በመዕራፍ አንድ ላይ መመልከት ይቻላል( 1፡12-13)፡፡ በዘካሪስ ላይ ያለው መቅረዝ መንፈስ ቅዱስን የሚያመለክት ሲሆን በታላቁ መከራ ጊዜ የሚነሡ ሁለቱ ምስክሮች ( ሁለቱ መቅረዞች) የአገልግሎታቸውን ኃይል የሚቀበሉት ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህን ኃይል ከመንፈስ ቅዱስ ከተቀበሉ በኋላ በመቅደሱ ሆነው ልክ እንደ መቅረዝ የጌታን ብርሃን የሚሳዩ የእግዚአብሔር እውነተኛ ምስክሮች ይሆናሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተደግፈው ዓለምን ሁሉ ለሚቆጣጠረው እግዚአብሔር ምስክሮች ይሆናሉ፡፡
ሁለቱ ምስክሮች ነቢዩ ኤልያስ በ2ኛ ነገስት 1፡10-14 እንዳደረገው ሊጎዱአቸው በሚመጡ ጠላቶቻቸው ላይ እሳትን ከሰማይ በመጥራት ራሳቸውን ለመከላከል የሚችሉበት እግዚአብሔር ኃይል እንደሚሰጣቸው እንመለከታለን፡፡ ከእነዚህ ምስከሮች አፍ እሳት እንደሚወጣ መናገሩ ቀጥተኛ ትርጉም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ተአምራትን እንዲያደርጉ በኃይል እንደሚሞላቸው ከክፍሉ እናገኛለን፡፡ ልክ ሙሴና ኤልያስ ሲያደርጉ እንደነበረው ሁሉ ውሃን የመለወጥና መቅሰፍትን በምድር ላይ የማምጣትና ዝናብ እንዳይወርድ የመከልከል ሥልጣን እንደሚሰጣቸው እንመለከታለን( ዘጸአት 7፡17-21፣ 9፡14፣ 11፡10፣ 1ሳሙ.4፡8፣ ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሚዎች ሁለቱ ምስክሮች ( ሁለቱ ወይራዎች) ኤልያስና ሙሴ ናቸው ያሉበት ምክንያትም ይህ ነው፡፡
2. የሁለቱ ምስክሮች ሞት
አገልጋዮች በታላቅ ኃይልና ጸጋ ሲያገለግሉ ሁል ጊዜ አድፍጦ የሚጠብቃቸው ጠላት እንዳለ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ አውሬው እነዚህን ሰዎች ሊገድላቸው የሚችለው ግን እነርሱ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን አገልግሎት ከጨረሱና እግዚአብሔርም የፈቀደለት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ምስክሮቹ ከትክክለኛ ጊዜአቸው በፊት ሊሞቱ አይችሉም፡፡ የእግዚአብሔር ጊዜ ሲደርስና እነርሱም አገልግሎታቸውን ሲያጠናቅቁ እንዲገድላቸው ተፈቀደለት፡፡ ይህ አውሬ ሐሰተኛው ክርስቶስ ነው፡፡ አውሬው የሁለቱ ምስክሮች ሬሳ በመንገድ ላይ ተኝቶ ሁሉም እንዲያያቸው ማድረጉ እነርሱን ማዋረዱ ሲሆን ይህም በቀድሞ የእግዚአብሔር ቃል በተነገረባቸው ዘመናት ተከናውኗል( መዝ 79፡2,3)፡፡ ጠላት አጋጣሚውን ካገኘ በሙሉ ኃይሉ በመጠቀም የእግዚአብሔር የሆኑትን አገልጋዮች ያዋርዳል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ምስክሮች የሞቱባትና የተዋረዱባት ከተማ ከሰዶምና ከገሞራ ጋር ተመሳሳይነት ያላት፣ በከፍተኛ ሁኔታ በደል፣ የምግባር ውድቀት፣ እግዚአብሔርን አለመውደድና ሕዝብን የመጭቆን ሁኔታ የሚታይባት ናት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ የተሰቀለባት ከተማም ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያላት ናት፡፡ ምክንያቱም ሐሰተኛው ክርስቶስ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ስለሆነ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው አገልግሎታቸው በታላቅ ተአምራት ሲታጀብ የነበረ ሁለቱ ወይራዎች አሁን ተገድለው ሬሣቸው በመንገድ ላይ ተጥሎ ሁሉም እየመጣ ያየው ጀመር፡፡ ጠላት የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ሲያዋርድ እንደዚህ ነው፡፡
የእነዚህ ሰዎች ሬሳ የወደቀው በአንድ ከተማ ሲሆን ቃሉ ግን ከነገድ ከቋንቋ አህዛብ የሆኑ ሁሉ በመንገድ ላይ የወደቀውን የሁለቱ ምስክሮችን ሬሣ ለሶስት ቀን ያዩታል፡፡ እንዴት አድርገው በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች ይህንን ሊያዩ ይችላሉ፡ እንግዲህ በጊዜ ከፍተኛ ስልጣኔ ስለሚሆን ምናልባት ሁሉም በያለበት ሆነው በቴሌቭዥን ወይም በሌላ የመገናኛ መንገድ ሊመለከቱት ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ሕዝቦች ከተለያዩ ወገኖች ተውጣጥተው በወቅቱ እነዚህን ሰዎች ለማየት ሲሉ በኢየሩሳሌም የሚገኙበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በታላቁ መከራ ጊዜ ሰው ሁሉ የተደሰተበትን ሁኔታ የሚያሳይ ብቸኛው ታሪክ ይህ ነው፡፡ የምድር ወገኖች በእነዚህ ምስክሮች ሞት ምክንያት በጣም ይደሰታሉ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔርን የማዳን ወንጌል ስለማይሰሙ ነው፡፡ ልብ እንበል የወንጌል ሰባኪዎች፣ አስተማሪዎች ቅዱሳም ምስክሮች ሲወድቁና ሲዋረዱ ወንጌልን የመስበኩ ሥራ የሚቋረጥ ስለመሰለው አውሬውና ተከታዮቹ አጅግ አድርገው ይደሰታሉ፡፡ ይህኛው በምድር ላይ የመጨረሻው የሰው ልጆች ፈንጠዚያ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላ ደስታ የሚባል በምድር ላይ አይሆንም ወይም ያበቃል ማለት ነው፡፡ ይህ የሚገርም ነው፡፡
3. የሁለቱ ምስክሮች ትንሳኤ
በዚህ ክፍል የሚያስደንቀው ነገር ሁለቱ ምስክሮች ሞተዋል ተብለው ከነገድ ከቋንቋ እና ከየአገሩ ሰዎች ሁሉ ተሰብስበው ደስታቸውን ከገለጹ በኋላ እንደገና ተነስተው፣ ወደ ሕይወት ተመልሰው መታየታቸው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የወጣው ሕይወት መንፈስ ለሞተው ሰውነታቸው ሕይወትን እንደሰጠ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሞተው ሕይወትን በመስጠት የሚታወቅ አምላክ ነው( ሕዝ 37፡5፣10፣ሮሜ 4፡17)፡፡ የሞቱ ምስክሮች በድን ሰውነታቸው በሰዎች ፊት በእግር መቆሙ በሞታቸው ለተደሰቱት ጠላቶቻቸው ሁሉ ድንጋጤ ሊፈጥር የሚችል ነው፡፡ የእግዚአብሔርንም ሆነ የሰውን የሆኑ ጠላቶችን እግዚአብሔር የሚያዋርደውና የሚስደነግጠው እንደዚህ ዓይነት ተአምራቶችን በማሳየት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በዓይናቸው ከሚያዩት ድንቅ በተጨማሪ ከሰማይ የመጣው ድምጽ የበለጠ አስደንጋጭ የሚሆን ነበር፡፡ እንዲህ ነው የሚለው “ወዲዚህ ውጡ”፡፡ ከዚያም እነርሱም ለጣላቶቻቸው እየተመለከቱአቸው በደመና ወጡ፡፡ አውሬ ሐሰተኛው ወይም ሰይጣን መግደል ይችላል፣ ሬሳንም ማዋረድ ይችላል፣ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣውን ትንሳኤና በክብር መውጣትን ሊከለክል አይችልም፡፡ ተገድለው ሬሳቸው እንኳ እንዳይቀበር ተደርገው የተዋረዱና በውርደታቸው ጠላቶቻቸው የተደሰቱበት እነዚህ ሁለቱ ምስክሮች ወደ ሰማይ የወጡት በእግዚአብሔር ድምጽ ነው፡፡ ይህ ድምጽ የጌታቸው የኢየሱስ ድምጽ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ለባሪያዎቹ ይገለጥና ይናገራቸው የነበረው የሞትንና የስዖልን መክፈቻ ቁልፍ የያዘውና በሰባቱ ወርቅ መቅሮች መካከል ይመላለስ የነበረው ኢየሱስ ነውና፡፡ ዛሬ በተለያዩ ሁኔታዎችና ምክንያ የተዋረዳችሁ ካላችሁ፣ የተሰበራችሁና የወደቃችሁ ካላችሁ፣ ከጠላቶቻችሁም ሲፈነጥዙባችሁ እያያችሁ ቅስማችሁ የተሰበረ ልባችሁ የወረደባችሁ ወገኖቼ ዛሬ ለእናንተ የምሥረች አለኝ፡፡ የሞትና የሲዖል መክፈቻ ቁልፍ ያለው ጌታ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል ፣ ውርደታችሁንም በክብር ይለውጥ ዘንድ አለ፡፡
እነዚህ ሁለቱ ምስክሮች ወደ ሰማይ የወጡት በደመና ሲሆን ይህም “ሸክና ግሎሪ” ተብሎ የሚጠራውን የእግዚአብሔርን ክብር የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ደመና የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ ነው፡፡ እነርሱ ወደ ሰማይ የወጡበት ሁኔታ ከጌታ ከኢየሱስ አወጣጥ ጋር ይመሳሰላል፡፡ አንደኛ ሰዎች እያዩ፣ ሁለተኛ በደመና ነው የተወሰዱት( ሐዋ 1፡9)፡፡ ይህ የክብር መነጠቅ በብሉይ ኪዳን ከኤልያስ
መነጠቅ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው(2ኛ ነገሥት 2፡11)፡፡ እንደዚሁም ደግሞ አማኞች በደመና እንደምንነጠቅ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል( 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡17)፡፡ በሞታቸው የተደሰቱ ፣ በውርደታቸውም የፈነጠዙና የቧረቁ ጠላቶቻቸው ዓይናቸው እያየ ፣ ጆሮአቸውም እየሰማ ሲነጠቁ ደግሞ ምንም ማለት አልተቻላቸውም፡፡ ቁጥር 13ን በምንመለከትበት ጊዜ የምድር መናወጥ 7000 ሰዎችን ሲገድል ሐሰተኛው ክርስቶስ ሊያድናቸው እንዳልቻለና በዚህ ያሉት ደግሞ ለእግዚአብሔር ክብር እንደሰጡ እንመለከታለን፡፡ ሰይጣን ለጊዜው ኃይል ያገኘ እና ያሸነፈ ይምሰል እንጂ እግዚአብሔር ግን ክብሩን ሳይወስድና ባሪዎቹንም ሳያከብር በፍጹም አይተውም፡፡ እንግዲህ ከሰባቱ ወዮዎች የሁለተኝ ወዮ የተጠናቀቀው አገልጋዮች ሞት በሕይወት፣ ውርደታቸውንም በክብር ለውጦ ራሱም ከጠላቶቹ ሁሉ ክብርን በወሰደበት አስደናቂ ክንውን ነው፡፡ ሃሌሉያ

Thursday, April 6, 2017

እንጀራው


በዚህ ሳምንት እኔና ውድ ባለቤቴ የወር አስቤዛችንን ( ቀለባችንን ማለቴ ነው) ለመሸማመት ከመኖሪያ ቦታችን ትንሽ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ገበያ አዳራሽ ሄድን፡፡ የገበያ ቦታው ሜድቴራኒያን ፉድ ማርኬት Mediterranean food market ተብሎ የሚጠራ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከሌሎች ገበያ አዳራሾች ሁሉ ይልቅ ይኸኛውን አዘውትረው የሚጎብኙበት ትልቁ ምክንያት የአበሻ ምግብ ለመሥራት የሚያስችሉ ቅመማቅመሞች በየዓይነቱ ስለሚገኙበት ነው፡፡ ለምሳሌ ፡ በርበሬ፣ ኮረርማ፣ እርድ፣ ቀረፋ ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ምጥምጣ፣ ቡና፣ ወዘተ ሁሉም በየዓይነቱ ይሸጥበታል፡፡ ቅመሞቹ በትናንሽ ብልቃጦች እየታሸጉ በላያቸው ላይ ምንነታቸውን የሚያሳይ ጽሑፍና መለያ ቁጥር ከታተመባቸው በኋላ በተመደበላቸው መደርደሪያ ላይ በተርታ ተደርድረው ይገኛሉ፡፡ እንዲያው ባንገዛቸውም እንኳን እነዚያን ማየት ለዓይን ምግብ ነው፡፡ ታዲያ በአገር ቤት ሳለን እንደነበረው በትንሽ ብር ፌስታል ሞልቶ መመለስ ያለ እንዳይመስለን አደራ፡፡ በአንዲት ትንሽ ብልቃጥ የታሸገችው በርበሬ ዋጋ አይቶ በአገራችን ገንዘብ ካሰሉት ዋጋው ያስደነግጣል፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር ለመግዛት ሲታሰብ በአገር ቤቱ ገንዘብ ማስላት አይታሰብም፣ ማስላቱም ተገቢ አይደለም፡፡ 
የአሜሪካኖች ምግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልታሰበ ቦርጭ እያሸከመ ስለሚያስቸግር ከዚህ ሁሉ እዳ ውድም ቢሆን የአገራችንን ምግብ ለምን አልበላውም በሚል እዚህ አገር ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ሽሮና እንጀራ ተለይቶን አያውቅም፡፡ ለታናሽ ልጃችን ፌቬን ደግሞ የአሜሪካኖች ምግብ ተመራጭ ብቻ ሳይሆን ከተመራጭ በላይ ነው፡፡ አልፈ አልፎ እንገዛላታለን እኛም የምንቀማምሰው በእርሷ ምክንያት ነው፡፡ ከፈቀድንላትማ ያለ እርሱ ባትበላ ደስታውን አትችለውም፡፡ እውነት መናገር ይሻላል የአሜሪካኖች ምግብ ሲጣፍጥ አይጣል ነው፡፡ ቢሆንም የሽሮን ውለታ መርሳት ጥሩ አይደለም ብለን ስለመከርናት እግዘር ይስጣትና እሺ ብላ ከእኛ ጋር የአበሻውን ምግብ በሥነሥርዓት እየበላችው ነው፡፡ ከምግብ ሁሉ ታማኝና ባለውለታችን ሽሮ ነው፡፡ መሸለም ቢያስፈልግ በመጀመሪያው የክብር መዳሊያ መጥለቅ ያለበት በሽሮ አንገት ነው፡፡ አንድም ቀን ሰልችቶን አያውቅን ፣ እኛም አንሰለቸውም፡፡ ይኸውና ሽሮአችን ባሕር ተሸግሮ በመምጣት የተለመደ አገልግሎቱን እየሰጠን ነው፡፡ ባለቤቴ ተዋበች ሌላ ማንኛውንም ምግብ ብትበላ እንጀራ ካልቀመሰች የሆነ ነገር የሚጎድልባት ይመስላታል፡፡ በፌቬንና በእርሷ መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ እኔ ባለቤቴን አልፌ አልፎ እመክራታለሁ፡፡ ታበዥዋለሽ እላታለሁ፡፡ እምቢ ስትለኝ “ቃሉ ሁሉንም በልክ አድርጉ ይላል” ብዬ ልሰብካት ብሞክር የቱጋ ነው የጻፈው ትለኛለች፡፡ የተጻፈ ነገር ካለ ንገረኝ እንጂ ያልተጻፈውን አታንብብ ትለኛለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ ውስጥ “አውድ” የሚባል ነገር መኖሩን በሰበብ በአስባቡ የነገርኩአትን ይዛ “አውድ ጠብቅ” እያለች ወደ እኔ ታነጣጥርብኛለች፡፡ በገዛ እጄ ስለ አውድ ነግሬአት ራሴው አፍ አጣሁ፡፡ እንዲያውም የእንጀራና የቡና ፍቅር እየባሰባት መሄዱን ሳይ “ይህ የእንጀራ ፍቅር በዝቷል፣ ወደ ሰማይም ሄደሽ እንጀራ እበላለሁ እንዳትይ እዚያ እንጀራ የሚባል ምግብ አይኖርም ይልቁንስ የተሻለና ከሁሉም የላቀ ሕይወት ነው የሚጠብቀን እንጂ” እያልኩ ሊሰብካት ቢሞክር አሁንም “ይህ ትምህርት ከእውነተኛው አስተምህሮ ጋር ስለጣጣሙ እርግጠኛ ሁን እንጂ እኔ መንግሥተ ሰማይ ሄጄ እንጀራ አልጋግርም የሚጋግርልኝም ይኖራል ብዬ አላስብም” ትለኛለች፡፡፡ ባለቤቴንና ልጀቼን ይህንን አታድርጉ ብዬ በቃል ጥቅስ ከመገሰጼ በፊት አውዱን በጥንቃቄ የመመልከት ግዴታ ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ ያውም እኔው ራሴ አውድ context ስለሚባል ነገር ነግሬአቸው ያመጣሁት መዘዝ ነው፡፡ እኔ የሚቀለኝና ነጻነት የሚሰማኝ በመነቃቂያ ኮንፍራንስ ስሰብክ ነው፡፡ እዚያ ከየት አመጣኸው የሚል የለም፡፡ የተሳሳተም ቢሆን ተናግረው አሜን በሉ ሲባል አሜን የሚባልበት ቦታ ነው፡፡ እኔ እዚያም ቢሆን አውድ እጠብቃለሁ እንጂ ምክንያቱም ወደ ቤት ስመለስ ባለቤቴ “እሺ የዛሬው አገልግሎት እንዴት ነበር ታዲያ?" ብላ ሳትጠይቀኝ አልፋ አታውቅም፡፡ እኔም ‘ጌታ ይመስገን በጣም ጥሩ ነበር” እላታለሁ፡፡ እዚያጋ ቢያበቃ መልካም ነበር ግን አያበቃም፡፡ “ስለ ምን ሰበክ?” የሚለው ጥያቄ ይከተለኛል፡፡ ይህን ጊዜ ከስብከቴ መካከል ደግ ደጉን መርጬ በጥንቃቄ እነግራታለሁ፡፡ ባለቤቴ አገልግዬ ስመለስ በጥያቄ ማጣደፍ ብቻ ሳይሆን በጌታ የተሳካ የስብከት አገልግሎት እንዳቀርብ አጥብቃ ትጸልይልኛለችና ስለ እርሷ ጌታን አመሰግናለሁ፡፡ ታዲያ በእኔ ቤት መንፈሳዊ ነጻነት ፣ በነጻነት መስበክ፣ ጥቅስ እየጠቀስኩ አንዱን ከአንዱ ጋር አገናኝቼ ማሳመን በቀላሉ እልሆን እያለ መጥቷል፡፡ በመሆኑም ደስተኛ ነኝ፡፡ ባለቤቴንና ልጆቼን እግዚአብሔር ስለሰጠኝ ምስጋናዬም የላቀ ነው፡፡
ባለቤቴ ቡናንም ስትወድ አይጣል ነው፡፡ እኔ ደግሞ ቡና አልጠጣም፡፡ ጧትና ማታ ቡና ካላፈላሽ እያልኩ የማስቸግር ባል ባለመሆኔ ራሱ ልታመሰግነኝ ሲገባት “ባትጠጣ ሙሉ መብት አለህ፣ ማንም በግድ ጠጣ አይልህም፣ ደግሞ ብትጠጣም ችግር የለውም ለራሴ ሳፈላ እግሬ መንገዱን ትጠጣለህ” ትለናለች፡፡ይህ እኮ በእኛ ቤት የሴቶች እኩልነት ብቻ ሳይሆን የሴቶች የበላይነትም መኖሩንም ያሳያል፡፡ አሁን አሁን በተለይም ወተት በቡና የሚባለውን በትንሽ በትንሹ ስትሰጠኝ ቀየችና ለእኔ በማይገባኝ ሁኔታ የቡናውን መጠኝ ከቀን ወደ ቀን በዛ እያደረገች ምን አለፋችው በቡና ሱስ አስያዘቺኝ፡፡ አሁን በቁጥጥሯ ሥር ገብቻለሁ፡፡ በአገሬ ሳለሁ ለቡና ሱስ ያልተንበረኩ ሰው አሁን ከምሳ በኋላ ያቺን ወተት በቡና የምትለዋን ካልጠጣሁ ይደክመኝ ጀመረ፡፡ 
ለማንኛም እኔና ባለቤቴ ወደ ሜዲትራኒያን ገበያ አዳራሽ የሄድነው ጤፍ፣ ገብስና ቡና ለመግዛት ነው፡፡ እዚያ የኢትዮጵያ ቡናም አለ፡፡ባለቤቴ የምትፈልገውን ዕቃ እየመረጠች በጋሪው ላይ ስታስቀምጥ የእኔ ሥራ ጋሪውን እየገፋሁ ከኋላዋ መከተል ነው፡፡ እርሷ የመረጠችውን ብቻ ነው እንጂ የእኔ ምርጫ ውሃ አያነሳም፡፡ ከኋላዋ ሆኜ ያንን ጋሪ እየገፋው እያለ ዓይኔ በአንድ ነገር ላይ አረፈ፡፡ ከፊት ለፊታችን ባለው ጠሬጴዛ ላይ በሚያምር ንጹሕ ላስትክ ታሽጎ የተደረደረ ደስ የሚል ነገር፡፡ ምግብ ነው ታዲያ! ገበያተኞች አንዱ ከሌላው እየተከተሉ የሚያነሱት፡፡ ገበያ አዳራሹ የዐረቦች በመሆኑ ምክንያት ብዙ ዐረቦች ይገበዩበታልና እነርሱም ያንን ሲያነሱ አየሁ፣ ሶማሊያውያንም ፣ ሱዳናውያንም በየተራ እየመጡ ሲወስዱ አየሁ፡፡ እኔም ተጠጋሁና አይቼ ልቤን ደስ አለው፡፡ ለባለቤቴ አሳየሁአት፣ አየሽው ይህንን ነገር አልኩአት፡፡ ለካ እርሷ ከእኔ በፊት አይታዋለች ግን እንደ እኔው አልገረማትም፡፡ ነገሩ እንጀራ ነው፡፡ እንጀራ በዚህ ገበያ ሲሸጥ ከዚያም አልፎ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑትም ጭምር ተሻምተው ሲወስዱ አታይም እንዴዬ አልኳት፡፡ ያውም እኮ ነጭ ወረቀት የመሰለ እንጀራ እኮ ነው፡፡ የእንጀራ ፍቅር የባለቤቴን ያህል ባይሆንም እንጀራን እወደዋለሁ ፡፡ የአገሬ ምግብ እንደዚያ ሲሸጥ በማየቴ ኩራት ኩራት አለኝ፡፡ በአገራችን የነጭ ጤፍ እንጀራ የሚበላው ሀብታም ሰው ቤት ነው ፡፡ ይህ ደግሞ ከንጣቱ ጋር ልስላሴው ራሱ ብላው ብላው የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን እንጀራ ወዳድ ባለቤቴ ያሳየችው ቸልተኝነት አንድ ጥየቄ እንድጠይቃት አደረገኝ፡፡ ይህንን እንጀራ አልወደድሺውም አልኳት፡፡ እርሷም መልሳ እንዲህ አለችኝ “እንጀራ ይመስልሃል? ይህ እኮ እውነተኛ እጀራ ሳይሆን ዱቄቱን ሳልፍራይዜር ከሚባል ኬምካል ካር ቀላለቅለው ስለሚጋግሩ የነጣው በዚያ ምክንያት ነው የለሰለሰውም ለዚያ ነው፡፡ እውነተኛ እንጀራ ግን እንደዚህ አይለሰልስም አይነጣምም፡፡ ይህኛው ሁለትና ሦስት ቀን እዚህ ቢውል አይደርቅም አይሰባበርም፡፡ እውነተኛው እንጀራ ግን ጠሬጴዛ ላይ እንደዚህ አይቀመጥም ፣ በልዩ ጥንቃቄ በኮባና በሌሎች ቅጠሎች ተሸፋፍኖ በእቃ ውስጥ ነፋስ በማይነካው መልኩ ይቀመጣል፣ ይህኛው እንጀራ ከኬሚካሉ የተነሳ ለጤና ጎጂ ሲሆን እውነተኛው ግን በጣም ጤናማ ነው፣ ጤፋችን ብረት በተባለ ንጥረ ነገር የበለጸገ ስለሆነ ለጤና ጠቃሚ ነው፣ አሁን እኔ የጤፉን ዱቀት ወስጄ ስጋግረው የሚወጣው እንጀራና ይህኛው እንጀራ በምንም ሊገናኙ አይችሉም” አለችና አስዳችኝ፡፡ 
ከዛ በኋላ ራሴን ጠየቅኩኝ እነዚያ ሰዎች ታዲያ እንጀራ እንጀራ እያሉ የሚሻሙት ለምንድነው አልኩ፡፡ መልሱ እውነተኛውን እንጀራ ስለማያውቁ ነው፡፡መለስለሱንና መንጣቱን እንጂ በማስመሰል የተሠራ የሀሰት እንጀራ መሆኑን አላውቁትም ማለት ነው፡፡ ሐሰት መሆኑን የምታውቀው ኢትዮጵያዊቷ ባለቤቴ የእውነተኛው እንጀራ ጋጋሪ ኢትዮጵያዊት ስለሆነች ነው፡፡ በመሠረቱ እንጀራ ከመነሻው የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግብ እንጂ የዓረቦችም የሶማሊያውያንም አይደለም፡፡ የሱዳኖችም ምግብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያውያን ምግብ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትየጵያውያን ሐሰተኛውን እንጀራ ከእውነተኛው የመለየት ብቃት አላቸው፡፡ ሌሎች ግን ይህ ብቃት ስሌለላቸው በብረት የበለጸገውን የጤፍ እንጀራ ሳይሆን ኬምካል የተሞጀረበትን ነጭ እንጀራ ይበሉታል፡፡ 
ከዚህ የተማርኩት አንድ መንፈሳዊ ቁም ነገር አለ፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሐሰት አስተማሪዎችንና የሐሰት ትንቢቶችን፣ ተአምራቶችን እንዲሁ በቀላሉ ልንለያቸው አንችልም፡፡ እውነተኛውን ትምህርት ካላወቅን በቀላሉ እንወሰድባቸዋለን፡፡ የሐሰት ትምህርቶች ይመርካሉ፣ ብዙዎች ይከተሉአቸዋል፣ ያደንቁአቸዋልም፡፡ ነገር ግን ከእውነተኛው ትምህርት ጋር ሲያስተያዩት ውስጣቸው በገዳይ መርዝ የተመላ ነው፡፡ እውነተኛው እንጀራ ዋጋው ውድ ሲሆን ሐሰተኛው ደግሞ ቀለል ባለ ዋጋ እንደሚገኝ ሁሉ የስህተት ትምህርትቶችና ትንቢቶች እንደ ልብ ይገኛሉ፡፡ ሐሰተኛውን ከእውነተኛው ለመለየት ቀላሉ መንገድ እውነተኛውን ትምህርት በሚገባ ማወቅ ነው፡፡ባለቤቴ ኢትዮጵያዊ በመሆኗ እውነተኛውን እንጀራ ስለምትጋግር ሱዳናውያንና ሶማሊውያን የሚገዙት ሳልፍራይዜር ያለበት እንጀራ እንደምግብም አልታይ አላት፡፡ እኔም ምስጥሩም ስለማላውቅ ልቤ በዚያ እንጀራ ተማርኮ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ቤተ ክርስቲያን በሐሰት ትምህርትና በጤናማ ትምህርት፣ በሐሰት ትንቢትና በእውነተኛ ትንቢት ፣በሀሰት ተአምራትና በእውነተኛው ተአምራት መካከል ያለውን ልዩነት ምዕመናን ተረድተው በሐሰተኛው መርዝ እንዳይጠቁ እውነተኛውን ትምህርት በማስጨበጥ ልትተጋ ይገባታል፡፡ ፈጣሪ በቸርነቱ ይጠብቀን ይርዳንም ፡፡ አሜን